Daily Archives: January 18th, 2015

የእንግሊዝ የፓርላማ ልዑክ አባላት በአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ ለመደራደር ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ ነው

አቶ አንዳርጋቸው ባለፈው ወር ከባለቤታቸው ጋር በስልክ ተነጋግረዋል

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ

የእንግሊዝ የፓርላማ አባላትን የያዘ የልኡካን ቡድን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ከእስር ማስፈታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመደራደር በቀጣዩ ወር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ የዘ ኢንዲፔንደንት ዘገባ አመልክቷል፡፡

ሁሉንም የእንግሊዝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባልነት የያዘው የፓርላማ አባላት የሰብዓዊ መብቶች ቡድን ምክትል ሊቀመንበር ጀርሚ ኮርባይን የሚመሩት የልኡካን ቡድኑ፣ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በመምከር የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ እንዳይሆንና ግለሰቡ ከእስር እንዲፈቱ ለማስቻል እንደሚሰሩ ዘገባው አመልክቷል፡፡አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንግሊዛዊ ዜግነት ያላቸው እንደመሆኑ የእንግሊዝ መንግስት ጉዳዩን አጽንዖት ሰጥቶ መከታተልና ግለሰቡን ከሞት ማዳን ይጠበቅበታል ያሉት ኮርባይን፤ ቡድኑ አቶ አንዳርጋቸው ግልጽ ባልሆነና ተቀባይነት በሌለው የህግ አካሄድ ለእስር ተዳርገዋል ብሎ እንደሚያምን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ አቶ እንዳርጋቸው የአሸባሪ ቡድን አባል ቢሆኑም በእስር ላይ ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ሲል በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወሳል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ነሐሴና ታህሳስ ወር ላይ ከተደረጉት ሁለት የመንግስት ተወካዮች ጉብኝቶች ውጭ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለመጎብኘት እንዳንችል አግዶናል ብለዋል፡፡

የእንግሊዝ መንግስት የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ገልጸው፣ በግለሰቡ ላይ የተጣለው የሞት ፍርድ ተፈጻሚ እንዳይሆን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ማድረጉን እንደቀጠለበትም አስረድተዋል፡፡በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የኢትዮጵያን መንግስት ለማፍረስ የሚሰራ አሸባሪ ቡድን አባል ናቸው፣ በእስር ላይ ሆነውም ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው፤ እስረኞችን ማሰቃየት ኢሰብአዊ ድርጊት እንደመሆኑ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ  አይደለም ሲሉ መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ግን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ከቅርብ አመታት ወዲህ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚፈጸምባቸው ስቃይ እያየለ መምጣቱን የሚያመላክት መሆኑን አክሎ ገልጿል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ ባለፈው ወር እንግሊዝ አገር ወደምትገኘው ባለቤታቸው ስልክ ደውለው መገናኘታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በአብዛኛው ስለልጆቻቸው ጉዳይ እንዳወሩ፣ ደህንነታቸውን እንደገለጹላቸው፣ እንዲሁም ለልጆቼ የማይሆን ተስፋ መስጠት አልፈልግም ማለታቸውን ባለቤታቸው እንደተናገሩ አመልክቷል ሲል አዲስ አድማስ ዘግቧል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ “ግንቦት 7” የተባለ የተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅት ዋና ፀሐፊ መሆናቸውና በኢትዮጵያና በየመን የደህንነት ኃይሎች ከየመን ታግተው መታሰራቸው ይታወቃል፡፡

%d bloggers like this: