Daily Archives: January 17th, 2015

አንድነት ፓርቲ የምርጫ ቦርድ ውሳኔን እንደማይቀበለውና በሁለት ሳምንት ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንደማያደርግ አስታወቀ

ከግራ ወደቀኝ የአንድነት ፓርቲ የወቅቱ አመራሮች አቶ በላይ ፈቃዱ፣ አቶ ግርማ ሰይፉ እና አቶ ዘካርያስ የማነብርሃን

ከግራ ወደቀኝ የአንድነት ፓርቲ የወቅቱ አመራሮች አቶ በላይ ፈቃዱ፣ አቶ ግርማ ሰይፉ እና አቶ ዘካርያስ የማነብርሃን

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራና ሪፖርቱን እንዲያቀርብ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ባለፈው እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤ አድርጎ አቶ በላይ ፈቃዱን በድጋሚ የፓርቲው ፕሬዘዳንት አድርጎ መርጧል፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው በድጋሚ ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ የሁለት ሳምንት ጊዜ መስጠቱን ተከትሎ አንድነት በድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ እንደማያደርግ ፓርቲው ጥር 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በተያያዘ ዜና የመላው ኢትዮጵ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)ም እንዲሁ እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ ምርቻ ቦርድ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. አድርጎ አቶ ማሙሸት አማረን ፕሬዘዳንት አድርጎ መምረጡ ቢታወቅም፤ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ድርጅቱ ድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ የሉለት ሳምንት ጊዜ መስጠቱን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ መኢአድ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ የሰጠውን ትዕዛዝና ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበለውና በድጋሚም ጠቅላላ ጉባኤ እንደማያደርግ አስታውቋል፡፡

aeup

መኢአድና አንድነት ለሁለተኛ ጊዜ ጥር 3 ቀን 2007 ኣ.ም. ያደረጉትን ጠቅላላ ጉባኤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲታዘብ ህጉ በመደንገጉና ፓርቲዎቹ በደብዳቤ ጥሪ ቢያደርጉለትም ምርጫ ቦርድ በሁለቱም ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተወካዩን አለመላኩ ታውቋል፡፡

በተለይ አንድነት ፓርቲ ድጋሚ ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንደማይጠራ ይፋ ከማድረጉ በተጨማሪ “ይህ በማን አለብኝ ሰሜት የተሰጠ ውሳኔ ሳይታረም ቢቀርና ገዢው ፓርቲ ያለምንም ጠንካራ ተቀናቃኝ ብቻውን ሮጦ ብቻውን እንዲያሻንፍ የሚያደረግ ተቋማዊ ሴራ ቦርዱን በታሪክ ተጠያቂ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በዚህች ሀገር ዘላቂ ሰላም ላይ ለሚፈጠረው አደጋ ቦርዱ ከተጠያቂነት እንደማይድን ለማስታወስ እንወዳለን፡፡” ብሏል፡፡

የፓርቲውን ሙሉ መግለጫ ከታች ይመልከቱ፡-

udj

የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዳይፈጠር የምርጫ ቦርድ ታሪካዊ ወንጀል እየፈፀመ ነው፡፡
———-
ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
የተሰጠ መግለጫ
————————-
የአንድነት ፓርቲ በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲፈጠር በምንም መለኪያ በገለልተኝነት የማንጠብቃቸውን የዲሞክራሲ ተቋማት በተግባር ለመፈተን እንዲቻል የሁለት ሺ ሰባት ምርጫን በሁሉም ሂደቶች ህዝቡን በማሳተፍ እንደሚወዳደር እና ህዝብን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ እና የኢህአዴግ አገዛዝ የመጨረሻ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ይህን ስንወስን እነዚህ ተቋማት ገለልተኝነታቸውን አረጋግጠው ታሪክ የሚሰሩበት እድልም ያገኛሉ የሚል ተሰፋ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ይህን እድል ከመጠቀም እና በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ከመወጣት ይልቅ ለገዢው ፓርቲ ያለውን ወገንተኝነት በምርጫው ሂደት ዋዜማ በይፋ እያረጋገጠ ይገኛል፡፡ አሁንም ቦርዱ ወሰነ ተብሎ በሚዲያ የተገለፀው እንዲሁም ለፓርቲያችን በፅሁፍ የተሰጠው “በአስራ አምስት ቀን ውስጥ በጋራ ጉባዔ አድርጉ” የሚል ትዕዛዝ፤ ቦርዱ በተደጋጋሚ ፓርቲያችንን ደንብ እንዲያከብር እየጠየኩ ነው በማለት ከደንብ ውጭ እንድንሰራ የአዛኝ ቂብ አንጓች ሆኖዋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ የመጥራት ኃላፊትን ያለበት የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ወይም ደግሞ በአባላት ጥያቄ የጠቀላላ ጉባዔ አባላትን አንድ ሶስተኛ ፊርማ አስባስበው በኦዲትና ኢንስፔክሽን ትዕዛዝ መሆኑ በግልፅ እየታወቀ ከፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ ውጭ በ15 ቀን ውስጥ ጉባዔ ጥሩ የሚል ትዕዛዝ፤ ቦርዱ ከገዢው ፓርቲ ጎን ተሰልፉ እየተጫወተ አንድነትን ከጫወታ ለማስወጣት ካለሆነ ሌላ ምንም ትርጉም ልንሰጠው አንችልም፡፡ ይህ ደግሞ ቦርዱ እየሰራ ያለውን ታሪካዊ ወንጀል ይፋ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ በማን አለብኝ ሰሜት የተሰጠ ውሳኔ ሳይታረም ቢቀርና ገዢው ፓርቲ ያለምንም ጠንካራ ተቀናቃኝ ብቻውን ሮጦ ብቻውን እንዲያሻንፍ የሚያደረግ ተቋማዊ ሴራ ቦርዱን በታሪክ ተጠያቂ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በዚህች ሀገር ዘላቂ ሰላም ላይ ለሚፈጠረው አደጋ ቦርዱ ከተጠያቂነት እንደማይድን ለማስታወስ እንወዳለን፡፡

በዚህ አጋጣሚ አንድነት ፓርቲ የሰላማዊ ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እና ህዝቡን የስልጣን ባለቤት የማድረግ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በቀጣይ ሳምንታትም በመንግሰትና በቦርዱ ላይ ጫና ማሳደሩን እንደሚቀጥልበት እያረጋገጥን አንድነት ፓርቲ ወደ ህገወጥነት የሚወሰደውን “የጋራ ጉባዔ” አካሂዱ የሚለው የምርጫ ቦርድ ውሳኔ የማንቀበለው መሆኑን ለመላው አባላትና ደጋፊዎች ማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

ጥር 8 ቀን 2007

ድል የህዝብ ነው!!!

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)

አቶ ብርሃኑ አዴሎ በቀረበባቸው ቅሬታ በድጋሚ ተነሱ

ዮሐንስ አንበርብር

 አቶ ብርሃኑ አዴሎ ከአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተርነት ኃላፊነታቸው በሕዝብ ቅሬታ ምክንያት እንዲነሱ ተደረገ፡፡ አቶ ብርሃኑ በሕዝብ ቅሬታ ምክንያት ከኃላፊነታቸው ሲነሱ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡

 

አቶ ብርሃኑ አዲሎ

አቶ ብርሃኑ አዲሎ

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ብርሃኑ፣ ታኅሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጻፈ ደብዳቤ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈው ደብዳቤ አቶ ብርሃኑ ከኃላፊነታቸው የሚነሱበትን ምክንያት ባያብራራም፣ ከታኅሳስ 24 ቀን ጀምሮ መነሳታቸውን ይገልጻል፡፡ ተቋሙን በተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩም የተቋሙ የፓተንት ክፍል ዳይሬክተር አቶ ግርማ በጅጋ ተሹመዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ በአሠራር ችግሮች ከሠራተኞች ቅሬታዎች ይነሱባቸው እንደነበር፣ ከተቋሙ ደንበኞች ማለትም የንግድ ምልክት የሚያወጡ ወይም ምልክቶቻቸው እንዲከበሩ የሚፈልጉ የንግድ ተቋማትና ግለሰቦች ቅሬታ ይቀርብባቸው እንደነበር ምንጮች አስረድተዋል፡፡

እነዚህ ቅሬታዎች በቀጥታ ለተወካዮች ምክር ቤት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት እንደቀረቡ ምንጮች አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ችግሮቹን የሚያጣራ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ተዋቅሮ የማጣራት ተግባራት ሲከናወኑ እንደነበሩ የሚያስታውሱት ምንጮች፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ደሚቱ አንቢሳና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድር ከአጣሪ ኮሚቴ አባላቱ መካከል እንደነበሩም ገልጸው፣ ከኃላፊነት የተነሱትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ እስከ 1998 ዓ.ም. ድረስ የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ፡፡ በወቅቱ ከተወለዱበት የደቡብ ክልል ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት በአቶ ብርሃኑ ላይ የተፈራረሙትን የቅሬታ አቤቱታ (ፔቲሽን) ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ማስገባታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የተቋቋመ አጣሪ ኮሚቴ ባቀረበባቸው ሪፖርት ከካቢኔ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸውና ከኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲነሱ መደረጉም አይዘነጋም፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ አቶ ብርሃኑ አዴሎን ለማነጋገር በተደጋጋሚ የግል ስልካቸው ላይ በመደወል ለማግኘት የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን በመጥቀስ ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

መኢዴፓና ኢብአፓ በፓርቲዎች ላይ የሚፈፀመው ደባና ዛቻ እንዲቆም ጠየቁ

 • “ምርጫ ቦርድ የኢህአዴግ አምስተኛ አባል ፓርቲ ሆኗል”-ፓርቲዎቹ

  የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ) እና
  የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) በምርጫ ዋዜማ
  ገዥው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም
  በሰማያዊ፣ አንድነትና መኢአድ ላይ የሚፈፅሙትን ደባና ዛቻ
  እንዲያቆሙ ጠየቁ፡፡ ፓርቲዎቹ ህዳር 7/2007 ዓ.ም ‹‹በምርጫ
  ዋዜማ በፓርቲዎች ላይ የሚደርሰው ደባና ዛቻ በአስቸኳይ
  ይቁም›› በሚል በጋራ ባወጡት መግለጫ ኢህአዴግ ምርጫ
  ቦርድን በመሳሪያነት በመጠቀም ሰማያዊ፣ አንድነትና መኢአድ
  ላይ ወከባና ዛቻ እየፈፀመ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ መግለጫው
  ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጉ እያለ ለማዋከብ ቢጥርም
  መኢአድና አንድነት የተዋጣለት ጠቅላላ ጉባኤ አድርገዋል
  ብሏል፡፡

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ሰማያዊ ፓርቲ አገራዊ ግዴታውን
እየተወጣ በመሆኑ፣ እንዲሁም መኢአድና አንድነት ብቃት ያላቸው
ልሂቃንን ማፍራት ስለቻሉ በተፈጠረበት ስጋት ፓርቲዎቹን
ለማጥፋት እየጣረ መሆኑንና ምርጫ ቦርድም የኢህአዴግ
አምስተኛ አባል ፓርቲ እስኪመስል ድርስ የገዥው ፓርቲ
መጠቀሚያ ሆኗል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከገዥው ፓርቲ መሳሪያነት
ወጥቶ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣም ፓርቲዎቹ
በመግለጫቸው ማሳሰባቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

አርበኞች- ግንቦት 7 ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ለህዝቡ ጥሪ አቀረበ

bbbbbb

ንቅናቄው በግንቦት 7 እና በ አርበኞች ግንባር መካከል የተደረገውን ውህደት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ” እኛ መዋሃድ መወሰናችንን ስንገልጽ፤ በተናጠል ከሚደረጉት – በጋራ የሚደረጉ የትግል ጥረቶች ውጤታማ ይሆናሉ በሚል ብቻ ሳይሆን፣፡”የተቃዋሚ ድርጅቶች፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ በሀገርና በሕዝብ ደረጃ ትርጉም ያለው ሥራ በጋራ መስራት አይቻሉም’ የሚለውን፣ አስከፊ ተመክሮና አመለካካት ለመስበርም ጭምር ነው። ” ብሏል።

” ከትናናሽ ድርጅቶች ዙሪያ ከሚሽከረከሩ ሀሳቦችና ስሜቶች ለመውጣትና ሀገራዊና ሕዝባዊ የሆነውን ጉዳይ ለማስቀደም የወሰነ ማንኛውም ድርጅት፣ አርበኞችና ግንቦት7፣ እንደደረሱበት የውህደት ውሳኔ ፤ወይም በሌሎች በጋራ ሊያሰሩ በሚችሉ ስምምነቶች አብሮ ለመስራት መወሰን የማይችልበት ምንም ምክንያት አይታየንም። ” ብሏል ንቅናቄው።

” በወያኔ አድሎ ስርዓት የተንገፈገፈና ትግሉን ለመቀላቀል የቆረጠ ማንኛውም ዜጋ፣ የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም ትግሉን መቀላቀል ይችላል ” ያለው አርበኞች-ግንቦት 7፤ ” የኢትዮያ ሕዝብ በአንድነት የተነሳ ቀን ደግሞ፣ የወያኔ ግብዓተ መሬት ይፈጸማል ብለን ከልብ እናምናለን። ” ሲል የመተባበርን አንድነት በ አጽንኦት ገልጿል።

ንቅናቄው ለተቃዋሚ ድርጅቶች ባስተላለፈው መልእክት ” ዛሬ በአርበኞችና በግንቦት 7፣ የተጀመረው ጉዞ ውጤታማ በመሆን ሀገራዊና ታሪካዊ ትርጉም እንዲኖረው፣ ሌሎችም በተግባር የምትንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ወያኔን የማስወገድንና ብሎም ሀገር የማረጋጋቱን ሀላፊነት በጋራ እንድንወጣ የሚያስችል መቀራረብ እንድናደርግ ፣ በውህደት በመሰረትነው- በአርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ፣ ሥም፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ” ብሏል።

ንቅናቄው ለወታደራዊና የፖሊስ ሠራዊት አባላት ባስተላለፈው መልእክት ደግሞ፤ ” የወያኔን ዘረኛና አባገነን ቡድንን ዕድሜ ለማሳጠርና ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ሀገር እንድትኖር፣ የሰሞኑን ቆራጥ የዓየር ሃይል መኮንንኖች ያሳዩትን ዓርያነት በመከተልና በተገኘው አጋጣሚና ሁኔታ በመጠቀም በየቦታው የሚደረገውን ትግል እንድትቀላቀሉ በውህዱ ድርጅታችን ሥም፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ” ብሏል።

ንቅናቄው በመጨረሻም ” የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፣በረጅም ታሪክህ አይተሄው ለማታውቀው ውርደት፣ ክፋት፣ የመከፋፈልና የመጋጨት አደጋ የዳረገህን እና ሀገርና ሕዝብን የማራከስና የመሸጥ ዕኩይ ተግባር የተጠናወተውን አገዛዝ ከነግብር አበሮቹ ጠራርጎ ለማስወገድ በተጀመረው የጋራ ትግል ውስጥ በቀጥታ እንድትሳተፍ አለያም በምትችለው ቀዳዳ ሁሉ ድጋፍ እንድታደርግ፣ በአርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሥም፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ” ሲል መግለጫ ማውጣቱን የኢሳት ዘገባ አመልክቷል፡፡

%d bloggers like this: