Daily Archives: January 3rd, 2015

“ህልም አንደሆነ አይታሰርም”

 አቤል ዋበላ

(ከአቃቂ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት)

Abel

‹‹ ስሜ አቤል ዋበላ ነው፡፡ አዲሱ አመት ሲጠባ በአዲስ መንፈስአዲስ ህልም ለአገሬ ማለም የነበረኝንም ማጠናከር እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያችን የብሄር፣ የሃይማኖት፣ የሀብት፣ የትምህርት፣ የፖለቲካአመለካከት እና ሌሎችም ልዩነቶች አብሮነታችንን የማያደናቅፉባት ከነልዩነታችን በጋራ ለታላቅነት የምንጠቀምባት ለሁላችንም ዕኩልዕድል እና ተጠቃሚነት የሚቀርብባት ሁላችንም እንደየ ችሎታችን ለጋራ ደህንነታችን ነፃነታችን እና ብልፅግናችን የምንሰራባት ብቻሳይሆን በጋራ ስኬታማ የምንሆንባት እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዕኩል የሚያፈቅራት ኢትዮጵያ እንድትሆን እመኛለው፡፡ ይህ የእኔ ኢትዮጵያዊ ሕልም ነው፡፡››

ከላይ የሰፈረው ጽሁፍ ዞን ዘጠኝ ባዘጋጀው አራተኛው የበይነ መረብ ዘመቻ(Online Campaign) ላይ የተጠቀምንበት ነበር፡፡ የዘመቻው ርዕስ  አብረን ኢትዮጲያዊ ህልም እናልም ሲሆን የተካሄደውም በ2005ዓ.ም መገባደጃ ወርሃ ጰግሜ ላይ ነው፡፡ በአጋጣሚ ዘመቻው መንግስት የማናውቀውን ወንጀል እየፈለገብን እንደሆነ ከሁነኛ ምንጮች ከተረዳንበት ወቅት ጋር ገጥሟል፡፡ ለነገሩ ጠቅላይ ሚንስትሩበቀደም ፓርላማ ቀርበው ‹‹ኢህአዴግ ሀሳብ የሚፈራ ድርጅት አይደለም››ሊሉ እንደፎከሩት ሳይሆን የሃሳብ ልዩነት እንደሚያስበረግገው ስለምናውቅ መስጋታችን አልቀረም፡፡ ከሌሎች ምንጮችም እርግጠኛ ያልሆኑመረጃዎች ደርሰውን ነበር፡፡ ይሄኛው ግን እርግጥ የሆነ ጅቡ ከበራፍ ላይ እንደቆመ የሚያበስር ነው፡፡

እንደ ሌሎች ዘመቻዎች ሕገ መንግስታዊነት፣ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ….. የመሳሰሉ ለሃገራችን “ቅንጦት” የሚመስሉ ርዕሶችን ማንሳት አልፈለግንም፡፡ አሁን የድራማውዘመን ተቀይሮ እውናዊ ሆኗል፡፡ ይህም የኔ የምንለው ትውልድ ምን አይነት ውስብስብ ችግር ውስጥ እንደተዘፈቀ በብርቱ እንድናስብአደረገን፡፡ ለዚህም ነበር ሁሉን የሚያሳትፍ የትውልድ አቻዎቻችንን የሚጠራ ሰፊ ርዕስ የመረጥነው፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰውውጤቱ አርኪ ነበር፡፡

ስርዓቱ ግን ስለሃገራችን ያገባናልማለታችንን የትውልድ አቻዎቻችንን መፈለጋችንን አልወደደውም፡፡ የዘውጉን እውናዊነት ለማጠናከር ትምህርት ሊሰጠን ወደደ፡፡ መምህራን፣የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ቤተ ሙከራ ተዘጋጀ፡፡ አንደ አጋጣሚ ብቻ ሆኖ ከዞን ዘጠኝ ኢ-መደበኛ የጦማሪያን ቡድን ስድስታችንእና ሌሎች ሶስት ጋዜጠኞች (ኤዶም ካሳዬ፣ ተስፋለም ወልደየስ እና አስማማው ኃ/ጊዎርጊስ) ለተማሪነት ተመረጥን፡፡ ትምህርቱም ሚያዚያ17/2006 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ ውንጀል ምርመራ ዘርፍ (በተለምዶ ማዕከላዊ) ተጀመረ፡፡

ትምህርት አንድ

የመጀመሪያው ትምህርት የሀገራችንኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ መረዳት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ትንታኔ የሚሰጥ ወዳጃችን በዞን ዘጠኝየሚደረጉ ሙከራዎችን አድንቆ ተጨማሪ መስራት ያለብንን ስራዎች ሊጠቁመን ‹‹ እናንተ ብዙ ጊዜ የምታተኩሩት የከተማ ፖለቲካ ላይ ነው፡፡ እስኪ ወደገጠር ጫንጮ እንኳን ሂዱ ከገበሬው ጋር ጠጅእየጠጣችሁ ብሶቱን አድምጡና ጻፉ፡፡›› እንዳለን አስታውሳለሁ፡፡

እኛም ይህን ትችት ሙሉ ለሙሉ ተቀብለንበተግባር ባናደርገውም ከከተማ ወጣ ብሎ ለመመለስ ዕቅድ ይዘን ነበር፡፡ ማእከላዊ ግን ይህን ድካማችንን አቅልልሎ ሁሉንም አይነትኢትዮጵያዊ መልኮችን ከየአቅጣጫው አመጣልን፡፡ እነ ኡባንግን ከጋምቤላ፣ እነዚያድን ከደጋሃቡር፣ እነ አብድልከሪምን አቤኒሻንጉል፣እነ አያያዎን ከጎንደር፣እነ ቄስ ብርሃኔ ከአክሱም፣ እነ ሼህ መሀመድን ከጅማ አሰባሰበልን፡፡ የእስር ቤቱን ጨለማ ቀን እና ጨለማሌሊቶች ከልብ በሆኑ ወሬዎች አደመቅናቸው፡፡ ፖለቲካዊ ብልጣብልጥነት ያልነካካው ከጭቆናው የመጀመሪያ ረድፍ ገፈት ቀማሾች የሚቀዳእውነትን አደመጥን፡፡በሰውነት ከመከበር አንስቶ እስከ የምድሪቱን ፍሬ በዕኩልነት መጠቀም ጥሮ ግሮ ኑሮን ለማሸነፍ የሚያስችሉ ዕድሎችፍትሕአዊነት፣ ሳይፈሩና ሳያፍሩ ሀሳብን መግለጽ በወረዳና ቀበሌ ደረጃ የሚያስከፍለው ዋጋ፣ ከስር ባሉ የቢሮክራሲው አካላት የሚፈፀምተቋማዊ ግፍ በአጠቃላይ አድርባይነትና አስመሳይነት በመላው ሀገሪቱ እንዴት እንደሰፈነና ብዙሃኑም ኑሮውን በቀቢጸ ተስፋ እንደሚገፋተረዳን፡፡ ሁሉም የጎላው ምስል ግን ዛሬም ፌደራሊዝሙ መሰረታዊ የሆኑትን የስልጣንና የሀብት (Power and Resource)ጥያቄዎችእናዳልመለሰ በጉልህ ይናገራል፡፡

ከመታሰሬ በፊት በነበረኝ ግምትበርካታ የኦሮሞዎ ተወላጆችን በማረሚያ ቤት እንደማገኝ ጠብቄ ነበር የመጀመሪያው ሰሞን  ከዚህ የተለየ ነበር፡፡ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ከታሰሩ አንዳንድ ሙስሊም ኦሮሞዎችበስተቀር ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች አልነበሩም፡፡ ይሄ ግን ብዙ አልቆየም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ የኦሮሚያ ልዩ ዞንን በሚነካውአዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን የተነሳ በተፈጠረው ግርግር በርካታ ኦሮሞ ተማሪዎች ከየዩንቨርስቲው ተለቅመው መጡ፡፡ ያንየስቃይ ቤት በሳቅ ጨዋታቸው አደመቁት፡፡ ውይይታችንም ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን ዳሰስን፡፡ እኛም ብዙ ተማርን፡፡ በእነርሱ መሪነት በህብረትየምናዜማቸው የኦሮሚኛ ዘፈኖች የነበርንበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አስረሱን፡፡

ከሁሉም ከሁሉም biyya Toodhuufen silaala yaa Biyaa Dubro maagala (የጠይም ቆንጆዎች መፍለቂያ ሀገሬ መጥቼ አይሻለሁ) የሚለውን እንጃየኔን ቀልብ የሳበ ዜማው አንጀቴን ሰርስሮ የገባ ነበር፡፡ አገሬ ጠያይም ቆንጆ ልጆችሽ በነፃነትና በእኩልነት እንዲኖሩብሽ አልማለሁ፡፡ይህ የኔ ኢትዮጵያዊ ሕልም ነው፡፡

ትምህርት ሁለት

ሁለተኛው ትምህርት በተግባር የተደገፈነው፡፡ በተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት የተሰሩ የሰብዐዊ መብት አያያዝ ሪፖርቶችን ማንበብ ከጀመርኩኝ ጥቂት አመታት አልፈዋል፡፡ሁሌም እንደተለመደው ኢትዮጵያ የዜጎቻቸውን ሰብዐዊ መብት ከሚጥሱ እና የማሰቃየት ተግባር የሚፈፅሙ በተለይም በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ የሚጠራው የመንግስት ተቋም በዋነኝነትእንደሚጠቀስ ብዙዎቹ ሪፖርቶች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት እስካሁን ድረስ የማሰቃየት ተግባርን (Torture) እኔም ሆነ ጓደኞቼየምንረዳው እንደማንኛውም የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲሁ ነበር፡፡በተለይ እኔ በበኩሌ የተለየ ትኩረት እንደማልሰጠው አልሸሽግም፡፡

አሁን እነዚያ የአለማወቅ ወራት አልፈዋል፡፡ በታሪክ መጽሃፍት ላይበዘመነ ደርግ እንደሚፈጸሙ ያነበብናቸው አስከፊ ተግባራት አሁንም በሃገራችን እንደሚፈፀሙ ህያው ምስክሮች ሆነናል፡፡ ከስነ ልቦናዊየማሰቃየት ተግባር አንስቶ የተለያዩ የማሰቃያ ቁሳቁስ በመጠቀም እስከሚፈፀሙ ዘግናኝ ተግባሮች በእኛና በሌሎች ላይ ሲፈፀም ተመልክተናል፡፡በከፍተኛ ድብደባ እግሮቹ የሚወላከፉ፣ መራመድ አቅቶት በሸክም ወደ ማረፊያ ቤት የሚመለስ፣ በግርፋት ብዛት ጀርባው ብዙ ሰንበርየተጋደመበት፣ ብልቱ ላይ ሁለት ሌትር ውሃ በመንጠልጠሉ ምክንያት ሽንቱን መሽናት የተቸገረ፣ ጆሮው በጥፊ ደንቁሮና አፍንጫው የሚደማሰው መመልከት የየዕለት ተግባራችን ሆነ፡፡ በኤሌክትሪክ ሾክ የተደረጉና ‹ወፌ ላላ› ተገልብጠው እንደተገረፉ የሚናገሩ ተጠርጣሪዎችምአጋጥመውኛል፡፡ ስድብ፣ ዛቻውና የማዋረዱ ተግባር አእምሮ ሊቆጣጠረው የሚችል አይደለም፡፡ የቀረውን የማሰቃየት ተግባር ሲፈፀም ያዩናበራሳቸው ላይ የተፈፃመባቸው ይናገሩት፡፡

ይህ ተቋም ባለበት ከተማ ምንም ነገር እንዳልተፈጠሩ ቆጥሬ ስራዬንእየሰራሁ እየበላሁ እና እየጠጣሁ በቆየሁባቸው ዓመታት አፈርኩኝ፡፡ በአገሬ ኢ-ዲሞክራሲያዊነት እንዲታለፍ ዲሞክራሲያዊነት እንዲጀመርከዜሮ ትንሽ ከፍ የሚል መፍጨርጨር በማድረጌ ግን ተፅናናሁኝ፡፡ የማሰቃየት ተግባርን በንድፈ ሀሳብ ደረጃ መረዳትና  መረጃዎችን በልብ ማኖር አንድ ነገር ነው፡፡ ዘግናኝ የማሰቃየት ተግባር የተፈፀመበትተጠቂ ማግኘትና ማናገር ሌላ አንድ ነገር ነው፡፡ የማሰቃየት ተግባርን በራስ ሰውነት ማስተናገድ ግን ከሁሉም ይለያል፡፡ ባለቅኔውመማር አንድም ብሎ ባሳር እንዳለ ከዚህ በላይ ትምህርት ከወዴት ይገኛል!?

የፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ ምርመራ ደግሞሳይንስ፡፡ ሀገራችን የምር በሽብርና የሌሎች ወንጀሎች ስጋት ቢኖርባት ተጠርጣሪዎችን መርምሮ ለፍርድ የማቅረብ ዋና ሀላፊነት ያለበትይህ የፍትህ አካል ነው፡፡ በአግባቡ ከተከናወነ ሕጋዊነትን ባህል የሚያደርግ ነገር ግን ተጠርጣሪዎች ላይ የማሰቃየት ተግባር የሚፈፀምበትከሆነ ደግሞ ሙሉ የፍትህ ስርዓቱን አቀጭጮ የሚያስቀር ነው፡፡ ይህንን የሰው ልጅ ማሰቃያ ስፍራ ለቀን ወደ ማረሚያ ቤት ስንወሰድአበራ ጀምበሬ Agony in the grand palace ላይ ያሰፈረውን Commit to paper the suffering inthe dark chamber Anomee to the world all the unbeatble torture የሚለውን ግጥም እያሰብኩኝአንድ ተጨማሪ ህልም አለምኩኝ፡፡ ይህን ፖለቲካዊ የሀሳብ ልዩነትን መዳመጫና የህሊና እስረኞችን ደምማፍሰሻ የሆነ ተቋም ሙዚየምተቀይሮ ማየት ነው፡፡ ይህ የኔ ኢትየጵያዊ ህልም ነው፡፡

ትምህርት ሶሰትየትውልድ እዳ

ሶስተኛው ትምህርት የሚገኘው መንግስት ወደ ጦማርያን እጁን እንዲሰድያደረገውን ተግባርና እስሩን ተከትሎ የታየውን ምላሽ በመገምገም ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን ቮልቴር  If you wish to converse with me define yourterms እንዳለው ከዚህ በኋላ ‹‹ትውልድ›› ወይም ‹‹የትውልድ ልሂቃን›› ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ ብያኔ ሰጥቼእቀጥለላሁ፡፡ የነገሩን ውል ለመጨበጥ ትንሽ ወደኋላ መንደርደር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ትውልድ ስንል ተቀራራቢ የእድሜ ክልል ውስጥየሚገኝ መሰረታዊ ለውጥ በሌለውና አንድ ሊባል በሚችል ስርዓተ ትምህርት ያለፈ የአንድ ስርዓት(Regime) ውጤት የሆነ እና የዘመኑንመንፈስ የተሸከመ ማለታችን ነው፡፡ የትውልድ ልሂቃን ስንል ደግሞ ሰፊውን የልህቅነት ትርጓሜ ሊገኝ ከሚችለው ነገር አብላጫውን ያገኙ(those who get the most of what there is to get)የሚለውን እንወስዳለን፡፡ ይህንን ብይን መሰረት በማድረግአንድ ሰው ያገኘውን የትምህርትና የስራ እድል የገቢ መጠንና በማህበረሰቡ ያለውን ቦታ ከጠቅላላው የሀገሪቱ ዜጋ ጋር በማወዳደርየእርሱ ስፍራ የቱጋ እንደሆነ ይረዳል፡፡

አንድ ትውልድ ዘመኑ የሚጠይቀውን ኃላፊነት በአግባቡ ካልተወጣ በዚያችሀገር ያሉ ችግሮችን ለማስተካከል ያለው እድል እየጠበበ ይመጣል፡፡ ሳንካ መፍትሄ ሳያገኝ በዘገየ መጠን የበለጠ እየከበደ እና እየተወሳሰበስለሚሄድ መፍትሔ ለመስጠት አዳጋችና ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናል፡፡

የሀገራችንን የቅርብ ጊዜ ታሪክ በዚህ አውድ ስናጤን ከጣሊያን ወረራበኋላ ሀገሪቱን የተረከበው ልሂቅ የፊውዳል ስርዓቱ ዘመኑን እንደማይመጥን እና የሕዝቡን ችግር የመፍታት አላማ እንደሌለው ተገንዝቦለመሰረታዊ ለውጥና ማሻሻል ከመስራት ይልቅ ስርዓቱ የፈጠረለትንና የፈቀደለትን የትምህርትና የስራ እድል በመጠቀም ስርዓቱን ማገልገልምርጫው አድርጓል፡፡ የነዚህ አዳዲስ ምሁራን ዘመኑን ያልዋጀ ጥረት የተመለከተው ማኅበረሰብም ‹‹ከእጅ አይሻል ዶማ›› ብሎ ይጠራቸው ነበር፡፡ በዘመኑ ከነበሩት ስመጥር ቴክኖክራቶች አንዱ የሆኑት የቀድሞውብሔራዊ ባንክ ገዢ  ተፈራ ደግፌ “minutes of an Ethiopian century “ በተሰኘው መጽሐፋቸው ይህንን እውነታ በሀዘኔታ ያስታውሱታል፡፡

‹‹The tragedy of our Post-war generationof Ethiopian elite was that we adapted an attitude of public silence andprivate passivity on this professional level walking away from society insteadof confronting its problems››

ልሂቁ ከ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት በቀር ምንም ሊጠቀስ የሚችል እንቅስቃሴሳያደርግ ዝምታን መምረጡ ለሚቀጥለው ትውልድ ግዙፍ ያልተሰሩ የቤት ሥራዎችን እንዳስረከበው መረዳት አያዳግትም፡፡ በክፍሉ ታደሰስሌት መሰረት 1930ዎቹ፣ በ1940ዎቹ እና በ1950ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ የተወለዱና በ1960ዎቹ እና በ1970ዎቹ ንቁ የፖለቲካተሳትፎ የነበረውን ልሂቅ ያቀፈው ‹‹ያ ትውልድ›› ከወታደራዊው መንግሥትና እርስ በእርሱ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ትግል አድርጓል፡፡እንደመሬት ላራሹ ያሉ ውጤቶች ቢገኙበትም ሕጋዊነትን ዲሞክራሲያዊነት እንዲጀመር መሰረት ባለመጣሉ በኋላ ለመጡት ሁለት አምባ ገነንሥርዓቶች መነሳት መንስዔ ሆኗል፡፡

ወታደራዊ መንግሥት ወድቆ የሽግግር መንግስት የተቋቋመ ሰሞን ስመ ጥሩኢኮኖሚስት እሸቱ ጮሌ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ ማኅበረሰብ እንዲመሰረት የ1966ቱን አብዮት ለመራው ትውልድ የሰጠውእድል በወታደራዊው ኃይል መጨናገፉን በመጥቀስ ‹‹ታሪክ ሀገራችንንየምንታደግበት እና ከገባችበት አዘቅት ውስጥ ጎትተን የምናወጣበት ተጨማሪ እድል ሰጥቶናል፡፡ ለአንድ ትውልድ የሚሰጥ ሁለት እድልእንዲሁ በዋዛ የሚገኝ አይደለም፡፡ ሁለቱንም በግዴለሽነትና በሞኝነት ማባከን በቀጣዩ ትውልድ ይቅር የማይባል ወንጀል ነው፡፡››ብለው ቢመክሩም ያ ትውልድ ከራሱ ታሪክ ሳይማር ቀርቶ ዳግም አገሪቱን ወደኋላ የሚጎትት ስህተት ሰርቷል፡፡

በስርዓቱ አምባገነንነት የተነሳ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በንቃትመሳተፍ የነበረበት አዲስ ትውልድ (በ1980ዎቹ እና በ1990ዎቹ) ምንም ሊጠቀስ የሚችል ነገር ሳይሰራ አልፏል፡፡ ስደተኛው ጋዜጠኛመስፍን ነጋሽ ከምርጫ 97 ጋር ከተያያዙ እንቅስቃሴዎች በስተቀር ጉልህ ድርሻ ያልነበረውን ይህንን ትውልድ ‹‹የጠፋ ወይም የባከነ›› ብሎ ጠርቶታል፡፡ ምርጫ 97ትም በቅንጅትምሆነ በሕወሀት ኢኅአዴግ በኩል የመሪነት ሚና የተጫወቱት የያ ትውልድ አባላት በመሆናቸው ለትውልዱ ሙሉ እውቅና ለመስጠት ይከብዳል፡፡

ከዚህ ተስፋ ሰጭ ሙከራ በኋላ ስርዓቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የግል ሚዲያውንናሲቪል ማኅበረሰቡን አዳዲስ አፋኝ አዋጆች በማውጣት ፣ በማሰር እና በሌሎች እኩይ ተግባራት ማዳከሙ ሁላችንም የምናስታውሰው የቅርብጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ነው ዞን ዘጠኝ ኢ-መደበኛ የጦማርያን ቡድን  መንቀሳቀስ የጀመረው፡፡ የመጀመሪያዋ ጦማር ‹‹የሚያገባው ትውልድ ፍለጋ››በሚል ርዕስ የወጣች ሲሆን ይህምዞኑ ከዚያ በኋላ ያደረጋቸውን እንቅስቃሴዎች በሙሉ የቃኘ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ከየትኛውም ብሔር ፣ ሃይማኖትና ፖለቲካዊ አስተሳሰብያልወጣና አማራጭ ትርክት በማቅረብ ትውልዱ በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ማነቃቃትን አላማው ያደረገ ነበር፡፡ አቅማችንበፈቀደ መጠን ከአለፉት ትውልዶች በተለይም ከያ ትውልድ ለመማር ሞክረናል፡፡ የሀገሪቱ ችግሮች ውስብስብ መሆናቸውን በመረዳት የትውልድአቻዎቻችንን እኛም የምንማርበት መድረክ እንዲሆን ምኞታችን ነበር፡፡ ዝምታው ተሰብሮ በኃላፊነት ውይይት እንዲጀመር ተነሳሽነቱንወሰድን፡፡

የውይይቱ መንፈስም ከጽንፈኝነት የፀዳ የሀሳብ ልዩነትን የሚያከብርእና ለአካዳሚያዊ ሀሳቦች ልዕልና የሚሰጥ ለማድረግም ሞክረናል፡፡( ህገ መንግስቱ ይከበር ሰልን የወያኔን ህገ መንግስት እውቅናሰጡ ብለው ያጣጣሉን ድምጾች ቀላል አልነበሩም) ሀገራችን ያላት ደካማ የውይይት ባህልና ሥርዓቱ በየጊዜው የሚፈጥሯቸው ወደርየለሽብሶቶች ዋነኛ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ እኛም የዚህ ማኅበረሰብ ባህልና ታሪክ ውጤቶች በመሆናችን መፈተናችን አልቀረም ፡፡ ነገር ግንለጫና አልባው ውይይት (endless conversation) በተለይ እርስ በርሳችን በነበረን መስተጋብር ታማኞች ነበርን፡፡

ብዙዎች እንደቂልነት ሊወስዱት ቢችሉም የውይይቱ መድረክ አፍቃሪ ኢኅአዴግየሆኑ ሰዎችና ራሱን ስርዓቱን የሚጨምርና የማያበሳጭ እንዲሆን በተቻለን መጠን ጥንቃቄ እናደርግ ነበር፡፡ ይህንን ጥረታችንን ብዙሰዎች  ትንሽ ሙከራችንን በለጋስነት እንዲወስዱት አደረጋቸው፡፡ ይህለጋስነት በሀገር ውስጥ እና በባህር ማዶ የሚገኙ የምናከብራቸው ሰዎችንና ተቋማትን ይጨምራል፡፡ እንደጠበቅነውም ብዙ ያልሆኑ ነገርግን በቂ ሊባሉ የሚችሉ የትውልድ አቻ ወዳጆችን አፈራልን፡፡ ዞኑም የዘጠኝ ሰዎች ብቻ መሆኑ አከተመ፡፡ ‹‹ይህንን ብታስተካክሉት›› ‹‹ይህቺን ደግሞ እንዲህ ብታደርጓት›› እያሉ ድካማችንን እና ስንፍናችንን ማየት የማይፈልጉ ብዙ ሆኑ፡፡

በዚህ ሂደት እኛም ብዙ ተማርን፡፡ የተወሰኑ ኢ-መደበኛ የቡድኑ አባላትምየሕይወት ውሳኔዎችን በመወሰን ስራዎችን በመተው አራማጅነትን እና ጦማሪነት ጋር የተያያዙ ሙያዎች ውስጥ ገቡ፡፡ በፊት የምናከናውናቸውንትንንሸ ስራዎች መስራት ለእኛ የማያረካ አክባሪዎቻችንንም መናቅ ሆኖ ተሰማን፡፡ ለበለጠ ስራ እራስን ወደ ማዘጋጀት ያሉብንን የአቅምናየቁርጠኝነት ችግሮች ለመፍታት ረዘም ያሉ እቅዶችን ያዝን፡፡

እኛ እንዲህ እና እንዲያ እያልን እናስባለን፡፡ መንግስት ደግሞ ስልካችንንጠልፎ ከዋልንበት እየዋለ በብዙ ጆሮዎችና አይኖች እየሰለለን ወንጀል ሳይሆን ሰበብ ፈልጎ ሊያስረን አድፍጧል፡፡ በመጀመሪያ ‹‹ለራሳችን ትክክል ያልሆነ ትልቅ ግምት ስለሰጠን ነው እንጂ መንግሥትእኛን ምንሰራችሁ? ምንአጠፋችሁ ብሎ ያስረናል?›› ብለን አጣጣልነው፡፡ የመታሰራችን ምልክቶች ሲገዝፉ ደግሞ ከብዙ ማሰላሰሎችእና ክርክሮች በኋላ እስከአሁን ያደረግነው ‹‹ወንጀል››  ከሆነ ካቴናው በእጃችን እንዲገባ ፈቅደን ጡመራውን እንደምንቀጥል በይፋ አውጀንተመለስን፡፡

ጤናማ ሕዝባዊ ተዋስኦ (public Discourse) እንዲዳብርና ኃላፊነትየሚሰማው ትውልድ እንዲፈጠር መድከም በእኛ የተጀመረ አይደለም፡፡ ብዙዎች በእስር፣ በግዞት (በስደት) እና በሞት ዋጋ የከፈሉበትነው፡፡ የኛን ትውልድ መንፈስ ለማረቅ ያደረጉት እያንዳንዱ ነገር በህሊናችን የገነነና በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ ነው፡፡ ማንምሊቀይረው በማይችለው የተፈጥሮ ኡደት እኛም ባለተራ ሆነናል፡፡ አገር አገር የምንለው በግልብ ብሔረተኝነትና በአጉል አርበኝነት መንፈስበመነሳት አይደለም፡፡ የሀገር አመሰራረት ንድፈ ሀሳብና የአለማችን ጂኦ-ፖለቲካዊ እውነታ በመገንዘብ ነው እንጂ፡፡ ሀገራችን ከታሪኳ፣ከራሷና ከአሁኗ ጋር እንድንታረቅ ዋና ፍላጎታችን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው የመናገር ነፃነት ሳይገደብ ሁሉም የሀገሪቱ ጉዳዮችየሰለጠነ ጫና አልባ ውይይት ሲደረግባቸው እንደሆነ እናምናለን፡፡

ከትውልድ ጥቂቶችን በማሰር፣ ከሀገር እንዲወጡ በማስገድዶ በማሰደድእና በመግደል የትውልድ ጥያቄን መቀልበስ ይቻላል ብሎ የሚያስብ ቢኖር እንዳይስት ይጠንቀቅ፡፡ የ1953ቱን መፈንቅለ መንግሥት  መክሸፍን ተመልክቶ ንጉሱ የመፈንቅለ መንግሥቱን ጠንሳሾች በማሰርና በአደባባይበመስቀል የትውልዱን የለውጥ ጥያቄ ያዳፈኑ መስሏቸው መሰረታዊ ማሻሻል ማድረጉን እንዳይዘነጉ ከመከሩ ሰዎች ውስጥ አንዱ ደራሲ ዶክተርሀዲስ አለማየሁ ናቸው፡፡ በዚህ ታሪካዊ ምክራቸውን ንጉሱ ከቁብ ባይቆጥሩትም‹‹ለማናቸውም ነገር መነሻ የሆነው ሥሩ እንደተደበቀ ተቀምጦ ከላይ እንደሚታየው ቅርንጫፉን ብቻ ቢጨፈጭፉትና ለጊዜውእንኳ የጠፋ ቢመስል የተመቸ ጊዜ ሲያገኝ የተደበቀው ስር ዳብሮ ተስፋፍቶ ለመጥፋትም እንደሚያስቸግር ሆኖ ይነሳል›› ብለውተንብየው ነበር፡፡ የዚህ ዘመንም ነገር ጥቂት እድሜ የሰጠው ሰው ሲፈፀም የሚያየው ነው፡፡

እስር ሲታሰብ ብዙ ስጋቶች ወደአዕምሮ ይመጣሉ፡፡ ከሁሉም የሚከብደውግን ቤተሰብን ማንገላታትና በማረሚያ ቤት ተረስቶ መቅረት ነው፡፡ ቀበቶዬን አስረክቤ ወደማረሚያ ቤት ስወሰድ ይህንን እያወጣሁኝእያወረድኩኝ ነበር፡፡ ያለፉት ሰባት ወራት የእስር ቆይታዬን ግን በመጠኑም ቢሆን መሳሳቴን ነግሮኛል፡፡ ማዕከላዊ ጨለማ ቤት በነበርኩኝጊዜ ጠያቂ ሰው ማግኘት የሚፈቀደው በሳምንት አንድ ቀን ለቤተሰብ አባላት ብቻ ነበር፡፡( እሱም ከሁለት ሳምንት “ምርመራ” በኋላከቤተሰብ ውጭ ጠያቂ ሲመጣ እኛን ማግኘት ስለማይፈቀድ የጠያቂው ስም በቁራጭ ወረቀት ላይ ተፅፎ ይመጣ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ለእኔብዙ ትርጉም ነበራቸው፡፡ በእስር ቤት አለመረሳቴን እና ስለእኔ እስር የሚጨነቁ ወዳጆች እንዳሉኝ እዚያ ጨለማ ቤት ያለሁት ለግልጉዳዬ ሳይሆን ማኅበረሰባዊ ጉዳይ(public cause) ይዤ መሆኑ እያስታወሰ መንፈሴ ሳይሰበር ያኖረኝ ነበር፡፡ ፍርድ ቤት ስንቀርብከሩቅ የማያቸው ብዙ ፊቶች መንፈስን የሚያረጋጉና የሚያጽናኑ ናቸው፡፡ በሀገር ውስጥ እና በባህር ማዶ ያሉ የቅርብ ጓደኞቻችን በአካልነው እንጂ በመንፈስ ከእኛ ጋር አልታሰሩም ማለት ይከብዳል፡፡ ከከንፈር መጠጣ በዘለለ  እስሩ እንዳይከብደን እና በሕግ ፊት (ይፈተን ዘንድ ነው እንጂ የፍትሕ ስርዓቱብቻውን ተነጥሎ ጤናማ እንደማይሆን ለቀባሪው ማርዳት ነው) ንጽህናችንን ለማረጋገጥ የሚያስፈልገውን ከማድረግ አልቦዘኑም፡፡

ማንዴላ አንድ ሰው ወህኒ እስኪወርድ ድረስ በእውነት ሀገሩን አያውቃትም(It is said that no one truly knows a nation until one has been inside itsjails) ያለው ምንኛ ልክ ነው! እኛም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እንደገባ ተማሪ በግርምት እየተማርን ነው፡፡ ከመማር የሚገኝደስታ ደግሞ እጅግ ጣፋጭ ነው፡፡

አሁን……..

አሁን በምናብ ወደ አዲስ አበባ የቀጠሮ እስረኛ ማረፊያ ቤት (ቂሊንጦ)እንሂድ፡፡ የእኛው ቀለብ (Ration) በጎላና በሰፌድ ተደርጎ እየገባ ነው፡፡ ድምጽ ማጉያው ‹‹ሰዓቱ የቆጠራ ስለሆነ ማንኛው ታራሚ በየቤቱ በር ላይ እንዲሰለፍ ›› እያለ ይለፍፋል፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎችበኋላ የቤቱ በር ከውጭ ይቆለፋል፡፡ የቤቱ ካቦ የቤቱን በር እየደበደበ ‹ቆጠራ! ቆጠራ!ቆጠራ!….. እያለ ይጮሀል፡፡ በፊትበቀላሉ የማደርጋቸው ማኪያቶ እንደመጠጣትና በአውራ መንገድ ነፋሻ አየር እየተቀበሉ በዝግታ መራመድ የማልችል እስረኛ ሆኛለሁ፡፡ነገር ግን ሰማዩን እያየሁ ስለነገ፣ ስለአገሬ አልማለሁ፡፡ ህልም እንደሆነ አይታሰር!

ልዩ ማስታወሻ፡- አቤል ዋበላ ባለፈው ሚያዝያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. በግፍ ታስሮ የሚገኘው የዞን 9 ድረ-ገፅ አባል ብሎገርና የኢትዮጵ አየር መንገድ ቴክኒሻን ነው፡፡ ይህም ፅሑፍ ከዞን 9 ማኀበራዊ ሚዲያ ገፅ የተወሰደ ነው፡፡

%d bloggers like this: