Daily Archives: January 11th, 2015

ሰማያዊ ፓርቲ ይቅርታ እንደማይጠይቅ አስታወቀ

የሰማያዊ ፓርቲ ዓርማ

የሰማያዊ ፓርቲ ዓርማ

ሰማያዊ ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤትን እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በጽሑፍ ይቅርታ ይጠይቅ በማለት የተላለፈው ውሳኔ ከሕግ አግባብ ውጪ ስለሆነ ተቃውሞውን በመግለጽ ይቅርታ እንደማይጠይቅ አስታወቀ፡፡

የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ባለፈው ሐሙስ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቦርድን ስም አጥፍቷል ብለዋል፡፡ ‹‹በተሻሻለው የምርጫ ሕግ አንቀጽ 102 (4)ሀ፣ ለ እና ሠ እንዲሁም 102 (6) ሐ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቦርዱን ሥልጣን መቀበል፣ ሕጋዊ ትዕዛዙንና መመርያውን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ቦርዱ በሚያዘጋጃቸው የጋራ የምክክር መድረኮች ወይም ሌሎች መድረኮች ላይ ወኪል የመላክ ኃላፊነት እንዳለባቸውና በሐሰት ስም ከማጥፋት መቆጠብ እንዳለባቸው ያመለክታሉ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ግን ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት ያዘጋጃቸውን የጋራ ምክክሮች እንዲበተኑ ሙከራ አድርጓል፣ እየረገጠ ወጥቷል፣ በሐሰት ቦርዱን ወንጅሏል፡፡ እንዲሁም የስም ማጥፋት ዘመቻ አድርጓል፤›› በማለት ፓርቲው በጽሑፍ ይቅርታ እንዲጠይቅ ቦርዱ ወስኗል በማለት አስታውቀዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ውሳኔውን አስመልክቶ፣ ‹‹እኛ ይህን የምንረዳው የምርጫ ቦርድ የራሱ አቋም ሳይሆን ኢሕአዴግ በቦርዱ ውስጥ ምን ያህል ሚና እንዳለው ያጋለጠ ውሳኔ መሆኑን ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

‹‹ቀደም ባሉት ጊዜያት የሰጠነው አስተያየትና ስብሰባ ረግጠን መውጣታችን ዘለፋ መስሎ ከተሰማቸው አትዝለፉን እንነጋገር ማለት መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ይቅርታ ጠይቁኝ ብሎ ማስፈራራት አገራችንን አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ይቅርታ መቀለጃ አይደለም፡፡ እኛም በዚህ ምክንያት አናስተናግደውም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በተጨማሪም በመሠረቱ እኛ አንድ ድርጅት ነን፡፡ ምርጫ ቦርድም እንዲሁ አንድ ድርጅት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ሊግባቡ የሚችሉት ደግሞ በሕግና በደንብ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ካጠፋ ወይ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳል፣ ወይም ቦርዱ ባለው ሥልጣን ችግሩ ይፈታል፡፡ ቦርዱም ካጠፋ እንዲሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ይቅርታ ጠይቀኝ ብሎ መጠየቅ ፍፁም ተቋማዊ አሠራር አይደለም፤›› በማለት ውሳኔውን ፓርቲያቸው እንደሚቃወም አስታውቀዋል፡፡

አንድነት ፓርቲ በድጋሚ በጠራው አስቸኳይ ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዘዳንቱን በመምረጥ ተጠናቀቀ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ዓርማ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ዓርማ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በመጪው ምርጫ ግንቦት 2007 ዓ.ም. ለመሳተፍ መወሰኑን እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ 450 ዕጩዎቹን በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ ማቅረቡን ይፋ ካደረገ በኋላ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ አድርጎ የፓርቲውን ፕሬዘዳንቱን ካለተመረጠ ምርጫው ላይ እንዳይሳተፍ አደርጋለሁ ባለው መሰረት ዛሬ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ቀበና በሚገኘው የፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት አዳራሽ ጠቅላላ ጉባዔው መካሄዱ ታውቋል፡፡ ፓርቲውን ለመምራት በዕጩነት ቀርበው የተወዳደሩት አቶ በላይ ፈቃዱ፣ አቶ አለነ ማህፀንቱ እና አቶ ዳግማዊ ተሰማ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተደረገው የአንድነት ጠቅላላ ጉባዔ በከፊል

ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተደረገው የአንድነት ጠቅላላ ጉባዔ በከፊል

ለፕሬዘዳንትነት የተወዳደሩት ሶስቱም ዕጩዎች በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በትምህርታቸው የማስተርስ ድግሪ፣ በፖለቲካ ተሳትፎ ሶስቱም በአንድነት ፓርቲ በተለያየ ከፍተኛ አመራርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በሙያቸውም የተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ማገልገላቸው ተጠቁሟል፡፡ በመጨረሻም በነበረው ውድድር አቶ አለነ ማህፀንቱ ራሳቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ከውድድሩ ውጭ በማድረግ በአቶ በላይ ፈቃዱና በአቶ ዳግማዊ ተሰማ መካከል በተደረገ የምረጡኝ ቅስቀሳና ውድድር የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ባደረጉት የምስጢር ድምፅ አሰጣጥ መሰረት አቶ በላይ 183 ድምፅ በማግኘት የአንድነት ፕሬዘዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ አንድነት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የጠቅላላ ጉባዔው አባላት 320 ሲሆን፤አቶ በላይም የአባላቱን 57.2 በመቶ ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል፡፡

ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተደረገው የአንድነት ጠቅላላ ጉባዔ በከፊል

ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተደረገው የአንድነት ጠቅላላ ጉባዔ በከፊል

ውጤቱን ተከትሎም ተፎካካሪያቸው የነበሩት አቶ ዳግማዊ ተሰማ ለአቶ በላይ ፈቃዱ የእንኳን ደስ ያሎት መልዕክት በማስተላለፍ መጪውን ምርጫ አንድነት ፓርቲ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በጋራ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸውና ለዚህም በፓርቲው የሚሰጣቸውን የስራ ድርሸና ተልዕኮ ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ መግለፃቸውን ከስፍራው የአዲስሚዲያ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ በመጨረሻም አቶ በላይ ፈቃዱ ፓርቲውን በፕሬዘዳንትነት ለመምራት ቃለ መሐላ መፈፃማቸው ታውቋል፡፡

አዲሱ የአንድነት ፓርቲ ተመራጭ ፕሬዘዳንት አቶ በላይ ፈቃዱ ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ

አዲሱ የአንድነት ፓርቲ ተመራጭ ፕሬዘዳንት አቶ በላይ ፈቃዱ ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ

በጉባዔው ላይ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዦች የተገኙ ሲሆን፤ በሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ ህግ መሰረት ሂደቱን መታዘብ የነበረበት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሂደቱን ለመታዘብ እንደማይገኝና ወኪልም እንደማይልክ ቀደም ሲል ከፓርቲው ለተደረገለት ጥሪ በደብዳቤ ማሳወቁ ተጠቁሟል፡፡ ቀደም ሲል ታህሳስ 2006 ዓ.ም. የፓርቲው ፕሬዘዳንት የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው በመልቀቅ ለፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ካስረከቡ በኋላ አቶ በላይ ፈቃዱ ያለፉት 3 ወራት የፓርቲው ፕሬዘዳንት ሆነው ማገልገላቸው አይዘነጋም፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ታሪካዊ የሆነው ጣይቱ ሆቴል የእሳት አደጋ ደረሰበት

አዲስ አበባ ፒያሳ የሚገኘው ጣይቱ ሆቴል በእሳት ሲቃጠል

አዲስ አበባ ፒያሳ የሚገኘው ጣይቱ ሆቴል በእሳት ሲቃጠል

ዛሬ እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከረፋዱ 5 ሰዓት አካባቢ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ዘመናዊ ሆቴል የሆነው ጣይቱ ሆቴል የእሳት አደጋ ቃጠሎ ደርሶበታል፡፡ ሆቴሉ ነሐሴ1898 ዓ.ም. በንጉሱ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ባለቤት እቴጌ ጣይቱ ብጡል አማካኝነት ጣይቱ ሆቴል በሚል በአዲስ አበባ መሐል ፒያሳ ተመስርቶ ኢህአዴግ ስልጣን እስኪይዝ ድረስ በመንግስት ስር የሚተዳደር ሆቴል የነበረ ሲሆን ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ግን ወደ ግል በማዞር አቶ ፍፁምዘዓብ አስገዶም ለተባሉ ግለሰብ መሸጡ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ በርካታ የታሪክ ባለሙያዎችና የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅት አባላትና አመራሮች የሀገሪቱ ታሪክ ቅርስ አካል ተደርጎ የተመዘገበን ሆቴል በርካሽም ሆነ በውድ መሸጥ ተገቢ እንዳልሆነ አጥብቀው ቢከራከሩም በኢህአዴግ ተቀባይነት ሳያገኝ ቢቀርም ዛሬ ከባድ የሚባል የእሳት አደጋ ቃጠሎ ደርሶበታል፡፡ የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ከሆቴሉ ያለው ርቀት ከ1 ኪሎ ሜትር የማይበልጥ ቢሆንም በፍጥነት መጥቶ መከላከል ባለመቻሉ ሆቴሉን ጨምሮ ከአደጋው መትረፍ የሚችሉ በርካታ ንብረቶች መውደማቸውን ከስፍራው የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡

በአሁን ወቅት የጣይቱ ሆቴል ባለቤት የሆኑት አቶ ፍፁምዘዓብ አስገዶም የቀድሞ የህወሃት ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ስየ አብርሃ ታናሽ ወንድም የአቶ አሰፋ አብርሃ ባለቤት ወንድም ሲሆኑ፤ ከአቶ አሰፋ አብርሃ ጋር በተያያዘ ሆቴሉን ሲገዙ ሙስና ፈፅመዋል በሚል ለ6 ዓመታት ታስረው መለቀቃቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ በሆቴሉ ላይ ከባድ የሚባል የእሳት አደጋ መድረሱ የታወቀ ቢሆንም፤የአደጋው መንስኤ፣በአደጋው የወደመው ንብረት በአሀዝም ሆነ በዓይነት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም፡፡

%d bloggers like this: