Daily Archives: January 24th, 2015

የመኢአድ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ዘመነ ምህረት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ፓርቲው ገለፀ

AEUO

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የፓርቲያቸው ምክትል ፕሬዝደንት እና የሰሜን ቀጠና ኃላፊ የሆኑት አቶ ዘመነ ምህረት እጅግ ዘግናኝ ድብደባ ደርሶባቸው ሲል ፓርቲው ጥር 15 ቀን 2007 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡ አቶ ዘመነ የመኢአድን ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ወደ መኖሪያቸው ጎንደር ከተማ ከተመለሱ በኋላ ከፍተኛ የደህንነት ክትትልና ጫና ይደረግባቸው እንደነበር ለፓርቲያቸው አሳውቀው ነበር ያለው ፓርቲው ጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም ጎንደር ከሚገኘው መኖሪያው ቤታቸው ከባቤታቸውና ከህፃን ልጃቸው ፊት የፖሊስ ልብስ በለበሱ አካላት ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን ግልጾአል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፓርቲው አባላት ባደረጉት ክትትል አቶ ዘመነ አዘዞ የሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ውስጥ እንደሚኙ አረጋግጠናል ያለው መግለጫው የሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይገመት ከፍተኛ ስቃይና ሰቆቃ ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡

ከአቶ ዘመነ በተጨማሪ ጠቅላላ ጉባኤውን ተሳትፈው የተመለሱት የፓርቲው የማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ አቶ እያሱ ሁሴን 3 አመት ተፈርዶባቸው እስር ቤት እንደሚገኙ፣ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ፣ መ/አ ጌታቸው መኮንን፣ አቶ ጥላሁን አድማሴ የተባሉትን ጨምሮ ሌሎችም የፓርቲው አመራሮች ለእስር መዳረጋቸውን ያወሳው መግለጫው በአመራርና አባላቶቻቸው ላይ የሚደረገው እስር መኢአድ ምርጫውን ተጠቅሞ በገዥው ፓርቲ ላይ ጫና ማሳደር ስለሚችል እንደሆነ ተገልጾአል፡፡

በሌላ በኩል በአባላቶቻቸው ላይ በሚደርሰው በደልና ጫና ባሻገር ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ከምርጫ 2007 እንዳይሳተፍ የኢህአዴግ ቀኝ እጅ ሆኖ በመስራት ላይ እንዳለ ያወሳው መግለጫው ፓርቲው በምርጫው እንዳይሳተፍ ከተደረገ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል፡፡ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ በፓርቲው ላይ የሚፈጽመውን በደል ተከትሎ ፓርቲው በሚደርገው ትግልም ህዝቡ ከጎኑ እንዲቆም ጥሪ ማቅረቡን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በኤርትራ የታሰሩ 6 ጋዜጠኞች ተፈቱ

Eritrean_J

የኤርትራ  መንግስት ባለፈው የካቲት 2001 ዓ.ም. በርካታ ጋዜጠኞች በጅምላ ካሰረቻቸው መካከል በረከት ምስግና፣ ይርጋዓለም ፍስሃ፣ ባሲሎስ ዘሞ፣ ንጉሴ ክፍሉ፣ግርማይ አብርሃም እና ጴጥሮስ ተፈሪ ከ6 ዓመታት እስር በኋላ መፈታታቸውን ድንበርየለሹ የጋዜጠኞች ቡድን (Reporters without Border)  ይፋ አድርጓል፡፡

ጋዜጠኞች በሬዲዮ ባና፣ በሬዲዮ ዛራ እና በሬዲዮ ድምጺ ሃፋሽ ይሰሩ የነበረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ወቅት ከታሰሩት ጋዜጠኞች መካከል ባለፈው መጋቤት 2005 ዓ.ም. 7 ጋዜጠኞችን እንዲሁ የኤርትራ መንግስት በዋስ መፍታቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ እና ስዩም ፀሐዬን ጨምሮ 16 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን አስታውሷል፡፡

ሰሞኑን ከእስር ስለተፈቱት ጋዜጠኞች ያሉበት ሁኔታና የቴንነት ጉዳይን በተመለከተ እስካሁን ለማወቅ እንዳልተቻለና ይህንንም ለማወቅ ክትትል እንደሚያደርጉ የተቋሙ የአፍሪካ ጉዳይ ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡

በተለይ በአፍሪካ ጋዜጠኞችን በማሰር ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር ኤርትራ ቀዳሚ ሀገር እንደሆነች እና ለጋዜተኞች ከማይመቹ የዓለማችን ሀገራት እጅግ አደገኛ በሚል ዝርዝር ውስጥ መግባቷ ይታወሳል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ባህሪ ያላት ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ መንግስት ስልጣን ላይ ያሉት አካላት በትጥቅ ትግል ወደ ስልጣን እንደመጡ አይዘነጋም፡፡

አንድነት ፓርቲ እሁድ “የነፃነት ቀን ቀርባለችና ወደ አደባባይ ውጡ” በሚል ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቷል

-የሰልፉን ቅስቀሳ ተከትሎ የፓርቲው ወጣት አመራሮች ታስረዋል

.አንድነት ፓርቲ የጠራው የነገው ሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ተጠናክሮ ቀጥሏል

udj

አንድነት ፓርቲ ለነገ እሁድ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢህአዴግና በምርጫ ቦርድ በኩል ፓርቲው ወደ ምርጫ ውድድር እንዳይገባ የሚደረገውን እንቅስቃሴና ድርጊት በመቃወም የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉን ተከትሎ ዛሬ ጥር 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃም፣ ምክትል ኃላፊው አቶ ንዋይ ገበየሁ፣ የኤዲቶሪያል ቦርድ ኃላፊው አቶ ሰለሞን ስዩም እና የፓርቲው የአዲስ አበባ ወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል እና ሌሎች አመራሮች አቶ ያሬድ አለማየሁ፣ አቶ ሲሳይ ጌትነት፣ አቶ ማቲያስ ሐረጉ በፀጥታ ይሎች መታሰራቸውና ወዳልታወቀ ስፍራ የተወሰዱ ሲሆን፤ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አቶ አስራት አብርሃም፣ አቶ ንዋይ ገበየሁ፣ አቶ ሰለሞን ስዩም  እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል መፈታታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ፓርቲው ሰልፉን እንዲጠራ ያስገደደው ምርጫ ቦርድ ከሀገሪቱ የምርጫ አዋጅ ህግ አግባብ ውጭ በአንድ ወር ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ በመወሰኑ ሲሆን፤ ቅሬታ ነበረን በሚል ጥያቄ ካቀረቡት ዋነኞቹ አቶ አየለ ስሜነህ እና አቶ ኢሳይያስ ቱሉ ምርጫ ቦርድ እና ባልፈለግነው መንገድ ፓርቲውን ለሁለት ለመክፈል በመሞከሩ፣እኛ ደግሞ አንድነት አንድ ነው እንዲከፈልም ስለማንፈልግ ተመልሰን ወደ ዋናው ፓርቲያችን ቢሮ ተመልሰናል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም አንድነት ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲታዘብ ጥሪ ሲደረግለት እነ አቶ አየለ ስሜነህ ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ደብዳቤ ስላስገቡ ቦርዱ ሁለት ቦታ ለመታዘብ ወኪል መላክ እንደማይችል በጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፓርቲው ደብዳቤ መፃፉ ታውቋል፡፡

ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ምርጫ ቦርድ ለአንድነት ፓርቲ የፃፈው ደብዳቤ

ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ምርጫ ቦርድ ለአንድነት ፓርቲ የፃፈው ደብዳቤ

አቶ አየለ ስሜነህ በበኩላቸው እኛ ጠቅላላ ጉባኤ አልጠራንም፣ የነበርነው የአንድነት ፓርቲ አባላት ከ15 አንበልጥም፤ ነገር ግን የፓርቲው አባላት ያልሆኑ ከ60 በላይ ሰዎች በስብሰባችን ላይ ተገኝተዋል፣የሆቴል አዳራሽ ኪራይ ማን እንደከፈለ አናውቅም፣ ተከፍሎላችኋል እዛ ሆቴል ሂዱ እንባላለን፣ይሄ ሁሉ ስላላማረን እና ፓርቲያችን አንድነት አንድ ስለሆነ ወደ ፓርቲያችን ተመልሰናል ሲሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ከግራ ወደ ቀኝ አቶ አየለ ስሜነህ እና አቶ ኢሳይያስ ቱሉ አንድነት ፓርቲ ዋናው ጽህፈት ቤት ውስጥ  ከተመለሱ በኋላ

ከግራ ወደ ቀኝ አቶ አየለ ስሜነህ እና አቶ ኢሳይያስ ቱሉ አንድነት ፓርቲ ዋናው ጽህፈት ቤት ውስጥ ከተመለሱ በኋላ

ምርጫ ቦርድ ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲታዘብ ለቀረበለት ጥሪ እነ አቶ አየለ ስሜነህም ጠርተውናል ሲል በፃፈው ደብዳቤ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ አቶ አየለ ስሜነህ በበኩላቸው እኛ ምንም ዓይነት ጠቅላላ ጉባኤ አልጠራንም፣በመካከላችን የነበረው ጥቂት አለመግባባት እንዲፈታ ስንል እንጂ ከፓርቲው ህልውናም ሆነ አሰራር ጋር ቅሬታም ሆነ ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራ የሚል ጥያቄ አላቀረብንም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

nebe

በአሁን ወቅት ጥያቄ ነበረን ያሉት አቶ አየለ፣ ያለንን ጥያቄ በፓርቲያችን ውስጥ ሆነን እንፈተዋለን፣ ወደ ውጪ ይዘን መውጣታችን ትክክል እንዳልነበረና እኛ ባላሰብናውና ባልፈለግነው መንገድ ፓርቲው ላይ በእኛ ስም አደጋ ለመፍጠር እየተሰራ እንዳለ ስንገዘነብ ተመልሰናል፣ መጀመሪያም ቢሆን ፓርቲው አልተከፈለም፣ እኛም ጥያቄ አቀረብን እንጂ ከፓርቲው አልወጣንም ሲሉ አክለዋል፡፡ አቶ አየለ ስሜነህ  ለጋዜጠኞች የሰጡትን መግለጫ ለራሱ ለምርጫ ቦርድ ግልባጭ ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርበው የነበሩት አቶ አየለ ስሜነህ ወደ ፓርቲው መመለሳቸውን ቢያሳውቁም፤ ምርጫ ቦርድ ግን በነ አቶ አየለ ስሜነህ ስም ሌላ አካል እያደራጀ መሆኑን በመጥቀስ ፓርቲው ድርጊቱን ለማውገዝ የሰልፍ መጥራቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ፓርቲው ድርጊቱን የኢትዮጵያ ህዝብም እንዲረዳውና እንዲያወግዘው ለነገ እሁድ ጥር 17 ቀን 2007 ኣ.ም. የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉን መጥራቱን ፓርቲው አስታውቋል፡፡ ከዚህ በኋላ ፓርቲው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በመላ ሀገሪቱ ማካሄድና ነውጥ አልባ የነፃነት ትግሉን አጠናክሮ ከመቀጠል ውጭ ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንደማይጠራ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ ወደ ፓርቲያቸው ስለተመለሱት አቶ አየለ ስሜነህ እስካሁን ባይዘግብም ፓርቲው እንደተከፈለ አድርገው ከሬዲዮ ፋና እና ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን  በተደጋጋሚ ከሚያቀርቡት በስተቀር ምርጫ ቦርድ እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም፡፡

udj3

የነገው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ መነሻ አዲስ አበባ ቀበና መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ፊትለፊት ከሚገኘው የፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት ሲሆን፤ የሰላማዊ ሰልፉ መነሻ ሰዓት ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት መሆኑንም ታውቋል፡፡

የሰልፉ መዳረሻ ቦታ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጀርባ እና ዋናው ፖስታ ቤት ፊትለፊት በሚገኘው ኢትዮ-ኩባ አደባባይ መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት (እሁድ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም.) የተቃውሞ ሰልፉ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በደብረ ማርቆስ፣ በአርባምንጭ አካባቢ ከምባ ወረዳ፣በጂንካ እና በሸዋ ሮቢት እንደሚደረግ በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት በመወሰኑ በክልሎችም የሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ቀጥሏል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ቀኑ እንዲራዘም የመንግስት አካላትና ዲፕሎማቶች ጥረት ቢያደርጉም፤የአንድነት ፓርቲ ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ መብታችንን ከእንግዲህ ለምነን አናገኝም፣ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉም በታቀደለት መሰረት ይቀጥል ሲል መወሰኑን ፓርቲው አስታውቋል፡፡

ፓርቲው ከላይ ከተጠቀሱት 5 ከተሞች በተጨማሪ በተከታታይ በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞችም የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ እንደሚቀጥል ይፋ አድርጓል፡፡

%d bloggers like this: