በአዋሳ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ የሟቾች ቁጥር ከ20 በላይ ነው ሲሉ የቃጠለው ሰለባ የሆኑ ሰዎች ገለፁ
በደቡብ ክልል ዋና ከተማ በአዋሳ የካቲት 14 ቀን 2007 ዓም በደረሰው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ የሟቾች ቁጥር በመንግስት እንደተገለጸው አንድ ሳይሆን ከ20 በላይ መሆኑን ተገጂዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ከፍተኛ ንብረት ከወደመባቸውና እሳቱ ሲነሳ በስፍራው ከነበሩት መካከል አንዱ ለኢሳት ሲናገር፣ እርሱ የ6 ሰዎችን የተቃጠለ አስከሬን ማየቱን፣ በስፍራው የሚገኙ ጓደኞቹ ደግሞ በአጠቃላይ እስካሁን 27 አስከሬን ተፈልጎ መቀበሩን ተናገሩዋል።
አንድ ህጻነት እና አንዲት እናት ከ3 ልጆቿ ጋር ሞታ መመልከቱን፣ በማግስቱ ደግሞ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች ሞተው ማየቱን የሚናገረው ግለሰቡ፣ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች አካባቢውን ከነዋሪው በመከለል ማታ ማታ የተቃጠለ አስከሬን እየፈለጉ በመቅበር ላይ ናቸው ብሎአል። እናቶች አሁንም ድረስ ልጆቻቸውን እየጠየቁ ቢሆንም፣ በከንቲባው በኩል የሚሰጠው ምላሽ አሳዛኝ መሆኑን ግለሰቡ ገልጿል። ነዋሪዎቹ በመንግስት በኩል በቂ እርዳታ እንዳልተደረገላቸው በምሬት ተናግረዋል።
መንግስት የእሳቱን መነሻ እስካሁን ይፋ አላደረገም። ነዋሪዎች እንደሚሉት ግን መስተዳድሩ ቦታውን ለመሸጥ እሳቱን ሆን ብሎ አስነስቶታል። በጉዳዩ ዙሪያ የአዋሳን ከንቲባ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራም እንዳልተሳካ በመግለፅ ኢሳት ዘግቧል፡፡
በአዲስ አበባና በክልሎች በርካታ ኢትዮጵውያን ሙስሊሞች በመንግሥት እየታሰሩ መሆኑ ተሰማ
ከጥር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ የኃይማኖት ነፃነት መብትና ህገ-መንግሥቱ እንዲከበር፤ በሰላማዊ መንገድ እየጠየቁ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሙስሊሙ ማኀበረሰብ የመንግሥትን ህገወጥ እርምጃ ተቃውሞ መቀጠሉን ተከትሎ፤አሁንም በያዝነው የካቲት 2007 ዓ.ም. ከየቤቱና ከስራ ቦታ ጭምር የጅምላ እስሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የክልል ከተሞች የሚመጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የመንግሥትን ያይል እርምጃ እና የኃይማኖት ነፃነት መብታቸው እንዲከበርና መንግሥትም ከኃይማኖት ጣልቃ ገብነት እንዲወጣ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ተከትሎ ሰሞኑን የጅምላ እስር እየተካሄደ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የጅምላ እስሩ እየተከናወነ የሚገኘው መንግሥት በመጪው ምርጫ 2007 ዓ.ም. ከሙስሊሙ ማኀበረሰብ ድጋፍ እንደሌለው በመረዳቱና በርካቶችም የድምፅ መስጫ በረቀት መውሰዳቸው የደረሰው መረጃ አስደንግጦት እንደሆነ ቢጠቆምም፤ ከመንግሥት በኩል ግን እየተወሰደ ስላለው የጅምላ እስር የተሰጠ ምንም ዓይነት ማብራሪያም ሆነ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በተለይ ሰሞኑን በተወሰደውና እየተወሰደ ባለው የጅምላ እስር ተጠናክሮ መቀጠሉን ከመጠቆም ባለፈ፤እስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደታሰሩ ግን ለማወቅ አልተቻለም፡፡
ከዚህ ቀደም መንግሥት የኢትዮጵያ ሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ጋር ሲደራደር ቆይቶ፤ በመጨረሻም በጅምላ በማሰር የሽብር ክስ መስርቶባቸው የኮሚቴው አባላት ያለምንም ፍትህ እስካሁን በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
ከምርጫው ውጭ እንዲሆን የተደረገው አንድነት ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ላይ ያቀረበው ክስ ለየካቲት 27 ተቀጠረ!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በብሔራዊ ምርቻ ቦርድ አማካንነት ከግንቦቱ 2007 ዓ.ም. ሀገር አቀፍ ምርጫ ውጭ እንዲሆን መደረጉን በመቃወም በፌደራሉ ከፍኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ በፍትሐ ብሔር 11ኛ ችሎት የመሰረተው ክስ ለየካቲት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠዋት ተቀጠረ፡፡
ይህንንም በተመለከተ ፓርቲው በማኀበራዊ ሚዲያ ገፁ ላይ “ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በምርጫ ቦርድ እና በኢህአዴግ ሴራ ለእነ አቶ ትዕግስቱ አወሉ በኃይል ተላልፎ መሰጠቱ የሚታወቅ ነው። በዚህም ምክንያት ህጋዊው የአንድነት አመራር በምርጫ ቦርድ ላይ ክስ መስርተዋል፤ ፍርድ ቤቱ ልደታ በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት 11ኛ ፍትሀ ብሔር ችሎት ለየካቲት 27 ከጠዋቱ 3:30 ጉዳዩን ለማየት ቀጠሮ ሰጥተዋል፤ በመሆኑም በቅርብ የምንገኝ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች በችሎቱ ላይ በአካል በመገኘት ለህጋዊው አንድነት ያለንን አጋርነት እንድናሳይ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።” ብሏል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦር ከተመሰረተ ጀምሮ ከገዠው ህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ጠንካራ ተፎካካሪ ናቸው ተብለው የሚገመቱትንና በከደፍተኛ ደረጃ የህዝብ ተቀባይነት ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም ከዚህ በፊት የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረንስ(ኦብኮ)ን ያፈረሰ ሲሆን፤ በቅርቡ ደግሞ የግንቦቱ ምርጫ 2007 ዓ.ም. ዋዜማ ላይ አንድነት ፓርቲን እና መኢአድን በማፍረስ ምርጫ ቦርድ ያፈረሳቸውን ፓርቲዎች ስም ለፈለጋቸው ሰዎች መስጠቱን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ለግንቦቱ ምርጫ 2007ዓ.ም. በዕጩነት እንዳይቀርቡ ተደረገ
- “ምርጫ በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በሎተሪ ሆኗል” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
አዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 5 ለመጭው ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ሊቀርቡ የነበሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት “ከቀረቡት 17 ዕጩዎች መካከል በተጣለ ዕጣ ወድቀዋል” በመባላቸው ለመጭው ምርጫ በዕጩነት እንዳይቀርቡ መደረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል በዕጩነት በቀረቡበት ወረዳ 5 የምርጫ ጣቢያ ኢህአዴግ፣ የትግስቱ አንድነት፣ ቅንጅትን ጨምሮ ሌሎች ስድስት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ያለ ምንም ዕጣ አልፈዋል የተባለ ሲሆን “የሚያልፉት በዕጣ ነው” የተባሉት ሰማያዊን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መካከል ሰማያዊና ሌሎች አራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች “ዕጣ አልወጣላቸውም፡፡” ተብሏል፡፡
ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት “ሰማያዊ ህዝብ ውስጥ በሰፊው እየገባና እያንቀሳቀሰ ያለ ግንባር ቀደም ፓርቲ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ ያሉን ጨምሮ ዕጣ ውስጥ አይገቡም፡፡ ሰማያዊ ደግሞ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ከማያደርጉት ፓርቲዎች ጋር ዕጣ ውስጥ ገብቶ ወደቀ መባሉ ዴሞክራሲ ከጅምሩ ጀምሮ የህዝብ ድምጽ ሆኖ እያለ በእኛ አገር ሎተሪ ሆኗል ማለት ነው፡፡” ብለዋል
ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ሂደቱ ምንም ይሁን ምን አንድን ፓርቲ ወይንም ተወካይን ህዝብ ነው መምረጥ ያለበት፡፡ ህዝብ የሚፈልገውና የሚመረጥ ፓርቲ ነው ለምርጫ መቅረብ ያለበት፡፡ አሁን ግን እየተባለ ያለው በአንድ በኩል ህዝብ የማይፈልገው ያለ ዕጣ ሲገባ፣ በሌላ በኩል ህዝብ የሚፈልገው ሰማያዊን የመሰለ ፓርቲ ዕጣ ውስጥ ገብቶ አላለፈም እየተባለ ነው፡፡ በአንድ በኩል ህዝብ የተማረረባቸው ያለ ቅድመ ሁኔታ ህዝብን እንደሚያንቀሳቅስ የሚታወቀው ሰማያዊ ደግሞ ህዝብ ስፈለገው አሊያም በጥንካሬው ሳይሆን በሎተሪ ወድቀሃል ተብሏል›› ሂደቱ የተሳሳተ ነው ማለታቸውን ጨምሮ ነገረ-ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡
በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ ዜጎች ወደ ሀገር መግባት የምትፈልጉ ተመዝገቡ ሲል ጥሪ አስተላለፈ
ግሩም ተ/ኃይማኖት
(ከየመን)
በየመን ሰነዓ ያለ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ “..አሁን በየመን ውስጥ ያለው ሁኔታ አስጊ ነው፡፡ ማኛውችሁም ወደ ሀገር መግባት የምትፈልጉ ዜጎች ሁሉ ተመዝገቡ እና ተዘጋጅታችሁ ተቀመጡ፡፡ ችግር በሚነሳ ሰዓት ወደ ሀገር እንድትገቡ ኤምባሲው አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ዜጎቹን በትኖ ኤምባሲው ስለማይዘጋ አለን…ተመዝገቡ፤ እስከ መጨረሻው ዜጋዎቻችንን ሳናወጣ ኤምባሲውን አንዘጋም…” ማለታቸው በየመን በስደት ለሚኖሩ ኢትዮጵውን ደስታ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የመን ያለችበት የከፋ የፖለቲካ ውጥረት አስፈሪ እና በከፍተኛ ሁኔታ የእርስ በእርስ ጦርነት ያስከትላ ተብሎ ተፈርቷል፡፡ አንዳንዶች ከሶማሊያ በከፋ ሁኔታ በዘር፣ በጎሳ የመከፋፈል ግጭት ይካሄዳል ብለው ይገምታሉ፡፡ በእርግጥም አይቀሬ አይነት እየሆነ ነው ያለው፡፡ ከ16 በላይ ኤምባሲዎች ዘግተው ወጥተዋል፡፡ UNHCR ስደተኛውን በትኖ ሰራተኞቹን አውጥቷል፡፡ ጥቂት የመናዊያን ሰራተኞች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ ማንኛውም መንግስታዊ ተቋማት ወለም ዘለም፣ አገም ጠቀም አይነት ነው አስራራቸው፡፡ ፈራ ተባ እያሉ…ነው ሂደታቸው፡፡
ተቃውሞውና ድጋፉ በማይለይበት ሁኔታ ሰላማዋ ሰልፈኞች በከተማዋ በተለያየ አቅጣጫ ብቅ ጥልቅ ይላሉ፡፡ መሳሪያ በታጠቁ ወታደሮች እና የሁቲ አማጺሚሊሻዎች ከተማዋ ተወጥራ የሞት አረማሞዋን የምታዜም…የማትወልደው ምጥ የምታምጥ መስላለች፡፡ ይህ ሁኔታ ፍርሃት ያልፈጠረበት ሀገር ዜጋ የለም፡፡ አሜሪካን የመን ሰነዓ ከተማ ውስጥ የነበረውን ሼራተን ሆቴል ተከራይተው ወታደራዊ ቤዝ አድርገው የነበሩ ወታደሮቻቸውን አንስተው ኤምባሲውን ዘግተው ያላቸውን መረጃ ሁሉ አጥፍተው ወጥተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ በሰው አልባ የጦር ጀት ታጅበው ነው የሄዱት፡፡ በሰላም ከየመን ምድር ወጥተዋል፡፡ ሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ ዜጎቻቸውን የማውጣት ስራ ሰርተዋል እየሰሩም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኤምባሲም ዜጎቼ ሆይ ሲል መልዕክት አስተላልፏል፡፡ በየመን በርካታ ኢትዮጵያውያን በስደት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
በየመን ሰነዓ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲን ጥሪ አስመልክቶ ጋዜጠኛ ግሩም ከየመን “በእውነቱ ይህ እሳቤ ራሱ የሚያስመሰግን መሆኑ አይካድም፡፡ ሁሉ ዜጎቹን የበተነ ላለመሆን ይህ በጎ ጅምር ነው፡፡ ‘..ኑ!! ተመዝገቡ፡፡..’ የሚለው ጥሪ ለቦንድ ወይም ለእከሌ ልማት ማህበር ክፈሉ ለማለት ሳይሆን ህይወታችሁን አድኑ በመሆኑ ከልብ ያስመሰግናል፡፡” ሲል በፌስ ቡክ ገፁ አስፍሯል፡፡