የመድረክ እጩ ተወዳዳሪ በትግራይ ተምቤን በፖሊስ ተደበደበ
የወርቃ ኣምባ ምርጫ ክልል መድረክን ወክሎ ለክልል ምክርቤት በእጩነት የቀረበው ወጣት ዜናዊ ኣስመላሽ በፖሊስ ተደብድቦ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶታል።
ወጣት ዜናዊ ኣስመላሽ ትናንት ቅዳሜ የካቲት 7 ቀን 2007ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት የወርቃ ኣምባ ከተማ ኣስተዳዳሪ ተስፋይ ሃይሉ “..ይዛቹ ኣምጡት ብሎናል..” በማለት ሃፍተ ኪሮስ የተባለ ፖሊስና ገብረተኽለ ወለቸኣልና ገብረጀወርግስ ሙሉ የተባሉ ሚሊሻዎች ወደ ፖሊስ ኮሚኒቲ እየደበደቡ ወስደውታል። በወቅቱ በርካታ ህዝብ እየተመለከተ የነበረ ሲሆን ድብደባው በህዝቡ እርዳታ እንዲቆምና ወደ ዋና ፖሊስ ጣብያ ወስደው እንዲያስሩትና ድብደባው እንዲያቋርጡት ተቃውሞው በማሰማቱ ድብደባው ተቋርጧል።
ተደባዳቢው ፖሊስና ሚልሻዎቹ ለምን እንደደበደቡት ሲጠየቁ “..ወደ ፖሊስ ጣብያ ስንወስደው ቀስ እያለ ሲሄድ ፈጠን በል ስንለው ቀስ እያለ በመሄዱ ነው..” ሲሉ መልሰዋል።
ፖሊስ ኣዛዡ ያለ ምንም ምክንያት እንደተደበደበ ካረጋገጠ በሗላ “..ፖሊሱ ሰካራም መሆኑና ቅር ሊለው እንደማይገባው..” ነግሮ ማታ ሰዎስት ሰዓት ከእስር ቤቱ ኣስፈትቶታል።
ወጣት ዜናዊ ኣስመላሽ ከእስር ከተለቀቀ በሗላ በጤና ኬላ የህግምና እርዳታ ተደርጎለታል።
ማታ 5 ሰዓት ኣከባቢ ፖሊስ ሃፍተ ኪሮስ ከ3 ሚልሻዎች በመሆን ወዳረፈበት ቤት በመሄድ ለባለ ቤቱ ማስፈራራት ኣድርሰዋል።
የህወሓት መንግስት በሑመራና ሽረ የሚገኙ ኣባሎቻችንም ተመሳሳይ ድብደባ ኣድርሰዋል ሲል በመቀሌ የመድረክ አመራር አባል ገልፀዋል፡፡
በከተማ ባቡር መስመር ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ተዘጋጀ
ታምሩ ጽጌ
– ሰሞኑን ሁለት ተሽከርካሪዎች በመስመሩ ላይ ጉዳት አድርሰዋል
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ በሚገኘው የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱ ተጠቆመ፡፡
የቀላል የባቡር ፕሮጀክቱ የመጨረሻ ምዕራፍ የሙከራ አገልግሎት የተጀመረ ቢሆንም፣ ሰሞኑን በመስመሩ ላይ የተከሰቱ ሁለት አደጋዎች ፕሮጀክቱን በማከናወን ላይ ያሉትን ቻይናውያን ሳይቀር ሥጋት ላይ ጥለዋል፡፡
በመሆኑም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተሽከርካሪዎችና እግረኞች በምን ሁኔታ እንደሚስተናገዱ፣ በተለይ ተሽከርካሪዎች ለሚያደርሱት ጉዳት ተጠያቂ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ መረቀቁንና ለውይይት ለሕዝብ ሊቀርብ መሆኑን፣ የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ አስረድተዋል፡፡
የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ሌሊቱን አንድ የግል ንብረት የሆነ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ከነጭነቱ ሳሪስ ኦይል ሊቢያ ዲፖ ፊት ለፊት ያለውን የባቡር ሐዲድ አጥር ጥሶ ገብቷል፡፡ ተሽከርካሪው ምንም እንኳን በሰው ሕይወት ላይ አደጋ ባያስከትልም፣ እስካሁን በውል ያልታወቀ ኪሳራ ማድረሱ ታውቋል፡፡ አደጋ የደረሰበት የመስመሩ አጥር መልሶ ከተገጣጠመ በኋላ፣ ባቡር እንዲያልፍበት ተደርጎ ጥንካሬው ሲፈተሽ ችግር እንደሌለው መረጋገጡን አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡ ወጪውን በሚመለከት የኢንሹራንስ ግምት እየተጠበቀ መሆኑንም አክለዋል፡፡
በተለይ ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ተናግረው፣ ወደፊት ባቡሩ ሙሉ በሙሉ ሥራ በሚጀምርበት ወቅት ምን ያህል የከፋ ነገር ሊገጥም እንደሚችል ጠቋሚ በመሆኑ ሕግ መውጣቱ ተገቢ መሆኑን፣ በፍጥነት ፀድቆ ወደ ተግባር መሄድ እንደሚገባ መናገራቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡