Daily Archives: February 18th, 2015

የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያን ሴቶች የወሊድ መከላከያ እንዲወስዱ ተገደዋል መባሉን እስራኤል አመነች

ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ቤተ እስራኤላውያን ሴቶች ለረዥም ጊዜ የሚያገለግለውን ዴፖ ፕሮቬራ የተባለ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት ለመወጋት ካልተስማሙ ወደ እስራኤል ሊገቡ እንደማይችሉ ይነገራቸው እንደነበር ይታወቃል።

ክሊኒኩን ያስተድድር የነበረው “Joint Distribution Committee” እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውንጀላውን ማስተባበላቸው የሚታወስ ቢሆንም ዛሬ በወጣው ሪፓርት የእስራኤል መንግስት ውንጀላውን አምኗል።

ethio-jewish

በርካታ ሴቶች፣ በኢትዮጵያ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ሳሉ በክትባት መልክ የሚሰጠውን የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒት እንዲወስዱ እንዴት ያግባቧቸውና ያስፈራሯቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ቤተ-እስራኤላውያኑ ሲገልፁ “የማትወስዱ ከሆነ ወደ እስራኤል አትሄዱም፤ እርዳታና ህክምናም አታገኙ ተባልን፡፡ ይሄኔ ፈራን፤ ምንም ምርጫ አልነበረንም፡፡ ያለ እነሱ እርዳታ መውጣት አንችልም ነበር፡፡ ስለዚህ ክትባቱን ለመወጋት ተስማማን፡፡” ሲሉ ቤተ-እስራኤላውያን መናገራቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በመጥቀስ ዎርልድ ቡሌቲን ዘግቧል፡፡ ቤተ-እስራኤላውያኑ ከዚህ ቀደም በእስራኤል መንግሥትና ቀድመው እስራኤል በገቡ ዜጎች ከተለያዩ ማኀበራዊ የመንግሥት አገልግሎቶች ጭምር ይገለሉ እንደነበር መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር በ15 ከተሞች የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ

“ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” በሚልመርህ የሚካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ የካቲት 22 ቀን 2007 ዓም በ15 ከተሞች እንደሚካሄድ ትብብሩ አስታውቋል።

ከግራ ወደ ቀኝ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከ(ሰማያዊ) እና አቶ ግርማ በቀለ ከ(ኦህዴህ)

ከግራ ወደ ቀኝ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከ(ሰማያዊ) እና አቶ ግርማ በቀለ ከ(ኦህዴህ)

“የሙስሊም ማህበረሰቡ ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓም በኑር መስጂድ ፣ የካቲት 6 ቀን 2007 ዓም ደግሞ በአንዋር መስኪድ ያደረገው ተቃውሞ እንዲሁም የባህርዳር ከተማ ህዝብ ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓም ያሳየው ህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል በሃይል ሊዳፈን ቢችልም እንደማይጠፋ ትምህርት ሰጥቷል” ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ትብብሩ፣ ገዢው ፓርቲ እያደረሰ ያለው የመብት ረገጣ፣ የሙስና መስፋፋትና የመልካም አስተዳደር እጦት የህዝቡን የለውጥ ፍላጎትና የትግል ተነሳሽነት እንዳሳደገው ገልጿል።

ትብብሩ ገዢው ፓርቲ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ከቃላት ያለፈ እምነትም ሆነ ቁርጠኝነት እንደሌለው በመግለጽ፣ ምርጫ ቦርድን በቁጥጥር ስር በማዋል ጠንካራ ፓርቲዎችን ከመጪው ምርጫ ለማግለል እየሰራ መሆኑን የአንድነትና መኢአድን ጉዳይ በመግለፅ አብራርተዋል።

ከሰሞኑ ኢቢሲ ያቀረበው የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የመኖር ትርጉም ዋጋ የሚያሳጣው ‹‹መንግስትንና የመንግስት አስፈጻሚዎችን ከተቻችሁ፣ ካላከበራችሁ ወይም ጸጥ ለጥ ብላችሁ የምርጫ አጃቢ ካልሆናችሁ እስከ 15 ዓመት ትታሰራላችሁ›› የሚል አንድምታ ያለው በ ‹‹ባለሙያዎች ትንታኔ ›› ሥም የተላከው የማስፈራሪያ መልዕክትና የሌሉ የፈጠራ ክሶችን ለመፈብረክ በአባል ፓርቲዎቻችን ላይ ‹‹የሞተ ጉዳይን ከመቃብር በመቀስቀስ›› እና በአዲስ መልክ የተጀመረው የሚዲያ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በግልጽ ያስተላለፈው ገዢው ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ስርአት እንዳይኖር መፈለጉን ነው ሲል አክሏል።

የእኛ፣ የአገራችንና ዜጓቿ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በሁለት አማራጮች ላይ የተንጠለጠለ ነው የሚለው ትብብሩ አንድም ያለውን አምባገነናዊ ሥርዓት ተቀብለን፣የአገራችን ሉዓላዊነት በጥያቄ ውስጥ ባለበት፣ የጭቆና ቀንበር ተሸክመን በከፋ ውርደት ሥር ሰጥ ለጥ ብሎ መገዛት፤ አሊያም አምባገነንነትና ጭቆናን “በቃ” በማለት በሕዝባዊ የተቀናጀ ሰላማዊ ትግል ለአገራችን ሉዓላዊነትና የዜግነት ክብራችንን ለማስመለስ በህገ መንግስታዊ መብታችን ተጠቅመን ትግላችንን እስከማይቀረው ለውጥ/ ድል ደጃፍ ድረስ በቆራጥነት መቀጠል፣ ናቸው ብሏል፡፡

ሁሉን አቀፍ የነፃነትና ክብርን የማስመለስ ሰላማዊ ትግል ለ9ኙ ፓርቲዎች ብቸኛ አማራጭ መሆኑም ትብብሩ አስምሮበታል፡፡

ፓርቲዎቹ በመጨረሻም በሚደረገው አገራዊ፣ ሰላማዊና ሕዝባዊ ትግል በማይቀረው የሥርዓት ለውጥ ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በአንድነትና በቆራጥነት ህዝቡ እንዲነሳና በየካቲት 22 የተቃውሞ ሰልፍ ላይ እንዲገኝ በመግለጫቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የዞን 9 ብሎገሮችና 3ቱ ጋዜጠኞች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

∙ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል

z9

በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው 6ቱ የዞን 9 ብሎገሮችና 3ቱ ጋዜጠኞች ዛሬ የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ለ20ኛ ጊዜ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ሲሆን፣ በዚህ መሰረትም ተከሳሾች ከችሎት እንዲነሱ አቤቱታ ያቀረቡባቸው ሰብሳቢ ዳኛ ሳይቀየሩ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡ በመሆኑም ከሁለተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ ጀምሮ እያንዳንዳቸው ‹‹በክሱ ላይ የተጠቀሰውን ወንጀል ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም?›› የሚል ጥያቄ እየቀረበላቸው ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

በዚህ መሰረት ሁሉም ተከሳሾች የቀረበባቸውን የሽብር ክስ እንዳልፈጸሙ ለችሎቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉን ጨምሮ ተከሳሾቹ ክሱን በተደጋጋሚ ቢያነቡትም ግልጽ ሊሆንላቸው እንዳልቻለ ቢገልጹም የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠት እንዳለባቸው ተገልጾ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ የተጠቀሰውን ክስ እንዳልፈጸመ በመግለጽ “ህግ የተከበረበት ሀገር ቢሆን ኖሮ በእኔ ቦታ ከሳሾቼ ነበሩ መቆም ያለባቸው” ብሏል፡፡ ሌሎችም እንዲሁ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡ 10ኛ ተከሳሽ ተስፋለም ወልደየስ በበኩሉ፣ “እኔ ጋዜጠኛ ነኝ፤ ጋዜጠኝነት ወንጀልም ሽብርም አይደለም፡፡ ጥፋተኛ አይደለሁም” ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ አቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያሰማ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ከመጋቢት 21-23  ቀን 2007 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት ቀጠሮ መስጠቱን የነገረ-ኢትዮጵ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አቤቱታ ላይ ቀጠሮ ሰጠ

prisoners

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በዘላለም ወርቃገኘው ክስ መዝገብ የተከሰሱት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በማረሚያ ቤት አስተዳደር ላይ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጠ፡፡ በዛሬው ችሎት የተከሳሾቹ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ‹‹ህዳር 12 ለ 13 ቀን 2007 ዓ.ም አጥቢያ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ የተጠርጣሪዎቹ ንብረት ተወስዶባቸዋል፣ የሰብአዊ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል፣ ድንገተኛ ፍተሻው ህገ ወጥ ነው›› በሚል በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ላይ ላቀረቡት አቤቱታዎች ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን መልስ ሰምቷል፡፡

የማረሚያ ቤቱ መልስ በጽሁፍ ከቀረበ በኋላ በቃልም እንዲቀርብ በታዘዘው መሰረት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የቀጠሮ ማረፊያ አስተዳደር አስተዳዳሪ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አምባዬ ክቡር ፍተሻው መካሄዱን አምነው ነገር ግን፤ ‹‹ፍተሻው የተከናወነው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከጠዋቱ 12 ሰዓት በኋላ ነው፡፡ ፍተሸውም በአቤቱታው ላይ እንደቀረበው ባልታወቁ ሰዎች ሳይሆን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጥበቃዎች ነው የተከናወነው›› ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ የፍተሻውን አላማም ‹‹የታራሚዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የተከለከሉ ነገሮችን ፈትሾ ለማስወገድ ነው፡፡ በፍተሸውም ሚስማር፣ ስለት ነገሮች፣ እንዲሁም ብጥብጥ የሚቀሰቅሱ ጽሁፎች ተገኝተዋል፡፡›› ብለዋል፡፡

ባለፈው የአብዛኛዎቹ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ሲደረግ የ7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን፣ እንዲሁም 8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ የተወሰኑ የክስ ማሻሻያዎች እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረት በዛሬው ዕለት በሁለቱ ተከሳሾች ላይ አሻሽየዋለሁ ያለውን ክስ አቃቤ ህግ ይዞ ቀርቦ በንባብ አሰምቷል፡፡

በመጨረሻም በፍተሻው ወቅት ተፈጽሟል በሚል በተከሳሾቹ ጠበቃ የቀረበውን አቤቱታና ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን መልስ አገናዝቦ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም፤ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ የቀረበው ማሻሻያ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ‹‹ተሸሽለዋል ወይንም አልተሸሻሉም›› የሚለውን ለመወሰን ለየካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ቀጠሮ መሰጠቱን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ትናንት ምሽት በቡራዩ ከተማ በደረሰ ከባድ የመኪና አደጋ የ12 ሰዎች ሕይወት አለፈ

በቡራዩ ከተማ ልዩ ስሙ ቀርሳ በተባለው አካባቢ ትላንት የካቲት 9 ቀን 2007 ኣ.ም. ምሽት በደረሰ አሰቃቂ የመኪና አደጋ የ12 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ሁለት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡

አደጋው የደረሰው ትላንት ምሽት 1 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ላይ ሲሆን፥ ወደ አዲስ አበባ ይመጣ የነበረ ሲኖ ትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ከሚኒባስ ጋር በመጋጨቱ ነው።

በግጭቱ ሳቢያ የተነሳው ከባድ የእሳት አደጋም በመኪናው ውስጥ ለነበሩት ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት እንደሆነ ቢነገርም፤ የአደጋውን ምክንያት በተመለከተ ይህ እስከ ተዘገበበት ድረስ  ከገለልተኛ አካልም ሆነ ከፖሊስ ምርመራ የተገኘ ማረጋገጫ የለም፡፡

በአደጋው ወቅት በመኪናዎቹ ላይ የደረሰ ቃጠሎ

በአደጋው ወቅት በመኪናዎቹ ላይ የደረሰ ቃጠሎ

%d bloggers like this: