ድብደባ ከተፈጸመባቸው ሁለት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የአንደኛው ሕይወቱ አለፈ
ታምሩ ጽጌ
–ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ ናቸው
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አካባቢ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ፣ ሁለት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የጥበቃ ሠራተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው አንደኛው ሕይወቱ ማለፉ ተረጋገጠ፡፡
ጥር 23 ቀን 2007 ዓ.ም. የግማሽ ዓመት ፈተናቸውን ካጠናቀቁት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል፣ ሙሉቀን ከበደና ታምራት አባተ የተባሉ ተማሪዎች በዕለቱ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ታውቋል፡፡ ተማሪዎቹ ፈተናቸውን እንዳጠናቀቁ ከግቢ ወጥተው ሲዝናኑ ካመሹ በኋላ ወደ ማደሪያ ክፍላቸው ሲመለሱ፣ ፀደቀ አድማሱ ከሚባለው ተጠርጣሪ የጥበቃ ሠራተኛ ጋር መጋጨታቸውን ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ሊገቡ ሲሉ ተጠርጣሪው እንዲቆሙ ሲያደርጋቸው ተማሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጡበትን መታወቂያ ቢያሳዩም፣ ከተጠርጣሪው ጋር ሊግባቡ ባለመቻላቸው ድብድቡ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ተጠርጣሪው በወቅቱ ይዞት በነበረው የእንጨት ዱላ ደጋግሞ ሲደበድባቸው የተመለከተ ሾፌር፣ ሌሎች የተኙ ጥበቃዎችን በማስነሳቱ የተፈጠረው ድብድብ የቆመ ቢሆንም፣ ተማሪዎቹ በደረሰባቸው ድብደባ ተጎድተው ስለነበር በአቅራቢያቸው በሚገኘው ጥሩነሽ ቤጂንግ ጠቅላላ ሆስፒታል መወሰዳቸውም ተጠቁሟል፡፡
ታምራት አባተ የተባለው ተማሪ በጥሩነሽ ቤጂንግ ጠቅላላ ሆስፒታል በተደረገለት ሕክምና የተረፈ ቢሆንም፣ የደረሰበት ድብደባ ከባድ በመሆኑ ለተጨማሪ ሕክምና ሪፈር የተደረገው ተማሪ ሙሉቀን፣ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሕክምና ላይ እያለ ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል፡፡ ፖሊስ በድብደባው ተሳትፈዋል በማለት በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ተጠርጣሪ የዩኒቨርሲቲውን የጥበቃ ሠራተኞችን ፍርድ ቤት አቅርቦ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመጠየቅ በምርምራ ላይ መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
አያት የመኖሪያ ቤቶች ስራ ድርጅት በሊዝ ወስዶ መሠረቱ ወጥቶ ያለቀ ቦታ ለኢሊሌ ሆቴል ተወሰነ
ታምሩ ጽጌ
–መሠረቱን ለማውጣት ከ3.7 ሚሊዮን ብር በላይ እንደወጣበት ተገልጿል
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ካዛንቺስ ከኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ወረድ ብሎ የሚገኘውን፣ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አያት አክሲዮን ማኅበር በሊዝ የወሰደውና መሠረቱ ወጥቶ ያለቀ ቦታ፣ ፊት ለፊቱ ለሚገኘው ኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በፍርድ ቤት ውሳኔ ተሰጠ፡፡
ከ20 በላይ ክሶች ተመሥርቶባቸውና ጥፋተኛ ተብለው 11 ዓመታት የእስርና የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አያሌው ተሰማ ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑበት አያት አክሲዮን ማኅበር፣ ቦታውን በሊዝ የወሰደው ከአራት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ስፋቱም 1,696 ካሬ ሜትር ነው፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ቦታውን በሊዝ የወሰደው ባለ16 ፎቅ ለመኖሪያና ለቅይጥ የንግድ ሥራ ሕንፃ ለመገንባት ነበር፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቦታውን በሊዝ ያስተላለፈው ለልማት መሆኑን በመግለጽ፣ አያት አክሲዮን ማኅበር ምንም ዓይነት ግንባታ አላካሄደም በማለት በሊዝ አዋጁ የተፈቀደው የመጠበቂያ ጊዜ እንዳለፈ አስታውቆ ካርታውን ማምከኑም ተጠቁሟል፡፡
የኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት አቶ ገምሹ በየነ ቦታው ከሆቴላቸው ፊት ለፊት በቅርበት ላይ መሆኑን በመግለጽ፣ መሰጠት ያለበት ለመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ለእሳቸው መሆኑን ለክፍለ ከተማው በማመልከታቸው ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱም ተገልጿል፡፡ የሆቴሉን ባለቤት አቶ ገምሹንና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደርን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት የከሰሰው አያት አክሲዮን ማኅበር፣ ለመሠረት ማውጫ ከ3.7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዳወጣበትና ካርታው ከመምከኑ በፊት ሊነገረው ሲገባ፣ በድብቅ ማምከኑ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ሲከራከር ከርሟል፡፡
ጉዳዩን ሲመረምር የከረመው ፍርድ ቤቱ ማኅበሩ ቦታውን በተነጠቀ ወይም ካርታው በመከነ በ15 ቀናት ውስጥ ለአስተዳደሩ የቦታ አመላለስ ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ማቅረብ እንደነበረበት አስታውቋል፡፡ ያንን ሳያደርግ ወደ ፍርድ ቤት መምጣቱ (ክስ መመሥረቱ) ሕጉን ያከበረ አካሄድ አለመሆኑን በመጠቆም፣ 1,696 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ለኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል መሰጠቱ ተገቢ መሆኑን በውሳኔው አስታውቋል፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ
የኦሕዴህ አባላት በሰማያዊ ምልክት ሊወዳደሩ ነው
- “ለአንድ አላማ እንታገላለን” አቶ ግርማ በቀለ
- “መሰባሰባችን ትግሉን ያጠናክረዋል” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
የኦሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት (ኦሕዲኅ) አባላት በሰማያዊ ፓርቲ ምልክት ለመወዳደር መወሰናቸውን የኦሕዲኅ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጹ፡፡ ‹‹ጥቅምት 26/2006 ዓ.ም ፓርቲው ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ አባላቱና አመራሩ ከአገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር በውህደት መስራት እንዳለባቸውና በኦሕዲኅ ስም የሚደረገው የመጨረሻ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲሆን ወስነው ነበር›› ያሉት ሊቀመንበሩ የፓርቲው እጩዎች በሰማያዊ ፓርቲ ስምና ምልክት መመዝገባቸው አባላቱና አመራሩ ‹‹አገራዊ ፓርቲ ጋር በውህደት አሊያም በሌላ መንገድ አብረን መስራት አለብን፡፡›› በሚል በጠቅላላ ጉባኤው ያስተላለፉት ውሳኔ አካል ነው ብለዋል፡፡
አቶ ግርማ ፓርቲያቸው ከሰማያዊ ጋር ሆኖ ለመታገል የተነሳበትን ምክንያትም ‹‹አሉ ከሚባሉት 70 ያህል ፓርቲዎች አብዛኛዎቹ የክልል ፓርቲዎች ናቸው፡፡ የክልል ፓርቲዎች በአገራችን ፖለቲካ ፋይዳ ያለው ለውጥ እያመጡ አይደለም፡፡ የክልል ፓርቲዎች ሲጠናከሩም ቢሆን ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እንደሚያመዝን ተረድተናል፡፡ በተቃራኒው አገር አቀፍ ፓርቲዎች ሲጠናከሩ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አቶ ግርማ አክለውም ‹‹እስካሁን የክልልና አገራዊ ፓርቲ ተባብለን ተበታትነን ቆይተናል፡፡ አሁን ግን የተሻለ ለውጥ ለማምጣት አንድ አይነት ጥያቄ አንስተን፣ በአንድ አላማ ለመታገል ወስነናል፡፡ አንድነት ኃይል በመሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተሻለ ለውጥ እንደምናመጣ የሚል ትልቅ ተስፋ አለን›› ብለዋል፡፡
ፓርቲው ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ስምምነት በመፈረሙ አባላቱ በሰማያዊ ፓርቲ ስር ሆነው እንዲወዳደሩ ለምርጫ ቦርድ ባስገባው ደብዳቤም ‹‹የዚህ ስምምነት አላማ ፈራሚዎች ለ2007 ዓ.ም አጠቀላይ አገራዊ ምርጫ አባላትን በጋራ በአንድ የመወዳደሪያ ምልክት ማቅረብ፣ ማለትም የአንዱ ፓርቲ አባልና አመራር በሌላው ፓርቲ ሥምና ምልክት የሚወዳደሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ስምምነት ሲደረስም ተግባራዊ ማድረግ ነው›› ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የቀድሞ የአንድነት አባላት ወደ ሰማያዊ ፓርቲ መምጣታቸውን አስታውሰው አሁንም የኦሕዲኅ አባላት በሰማያዊ ፓርቲ ስር ለመወዳደር በፓርቲው ጥላ ስር መሰባሰባቸው ሰላማዊ ትግሉን እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአንድነት መቆማችንና መሰባሰባችን ትግሉን ያጠናክረዋል፡፡ ኢህአዴግ የአንድነት አመራሮችና አባላት ወደ ሰማያዊ በመምጣታቸው፣ ሰማያዊም እጁን ዘርግቶ በመቀበሉ ከፍተኛ ፍርሃት ተፈጥሮበታል፡፡›› ብለዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል አክለውም ‹‹አሁንም ሌሎች ፓርቲዎች መቀላቀላቸው ለኢህአዴግ ትልቅ ስጋት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በቴሎቪዥንና በራዲዮ እጩ ያቀረቡ ፓርቲዎችን ሲያስተዋውቅ የሰማያዊን ስም ሳይጠቅስ ቀርቷል፡፡ በተቃራኒው በሬዲዮና በቴሊቪዥን ሰማያዊ ተቋማትን አይቀበልም እያለ በሀሰት እየወነጀለ ያለው የተቃውሞ ጎራው በአንድነት በመቆም እየተጠናከረ በመምጣቱ ነው፡፡›› ሲሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በሰማያዊ ስር መሰባሰባቸው ያለውን ፋይዳ መግለፃቸውን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
የመሐል ዳኛው ሸለመ በቀለ ራሳቸውን ከተሰየሙበት ችሎት አገለሉ፤ ፤የጋዜጠኞቹ እና ብሎገሮቹ ጉዳይ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቀርቧል
በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ፍርድ ቤት ሲመላለሱ የነበሩት 9 ተጠርጣሪዎች ዛሬ ለ19ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ እንደትላንትናው ሁሉ ዘግይቶ ተጀመረው ቸሎት የመሃል ዳኛው አንዲነሱ የቀረበውን አቤቱታ ምርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር ፡፡ በዚህም መሰረት ያለመሃል ዳኛ የመጡት ሁለት የግራ እና የቀኝ ዳኞች ተሰይመው አቤቱታውን ካነበቡ በኋላ ማለትም
1.ዳኛው ለአቃቤ ህግ ተደጋጋሚ የማሻሻል እድል በመስጠት አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብታችንን ነፍገውናል
2. ፍርድ ቤቱ ራሱ የሰጠውን ትእዛዝ ራሱ ሽሮ ያለምንም የፍሬ ሃሳብ ለውጥ ያለተሻሻለ ክስ ተቀብሏል
3. ሃሳባችንን ስንገልጽ ክልከላዎች ይደረጉብናል በመሆኑም ለዚህ የፍትህ መጓደል መሃል ዳኛው ሚና ዋሳኝ ነው ብለን ስለምናምን አንዲቀየሩልን እንጠይቃለን የሚል ሲሆን ዳኞቹ አቤቱታው አግባብነት የሌለው ነው ውሳኜው በመሃል ዳኞች ብቻ ሳይሆነ በጋራ የሚወሰን ስለሆነም ጭምር አቤቱታውን ውድቅ አድርገነዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም እንዲህ አይነት አቤቱታ ውድቅ ሲሆን ለእያንዳንዳቸው ተከሳሾች 500 ብር የሚያስቀጣ ቢሆንም በስሜታውነት ነው ያቀረቡት በማለት ፍርድ ቤቱ አልፎታል ብለዋል ፡፡
በመቀጠል መሃል ዳኛውን ይዘው በመምጣት ችሎቱን አሟልተው አንደሚመለሱ ገልጸው መሃል ዳኛውን ይዘው መጥተው ደግመው ተሰይመዋል፡፡ መሃል ዳኛ አቶ ሸለመ በቀለ እነደተሰየሙ የምናገረው ነገር አለኝ በማለት ” ምንም አንኳን ሌሎቹ ዳኞች በዳኝነት አንድቀጥል ቢፈቅዱልኝም እኔ ግን በዚህ ክስ መቀጠል አልፈልግም ከዚህ በኋላ የምሰጠውም ዳኝነትም ቢሆን አመኔታ ስለማያገኝ አንድቀየር ማመልከቻ አስገብቻለሁ በማለት ራሳቸውን ከችሎቱ እንዲያገሉ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ አዲስ ዳኛ ተተክቶ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል አንደሚቀበል እና ሌላ ቀጠሮ እነደሚሰጥ ተገልጿል፡፡ የተከሳሾች ጠበቆች በበኩላቸው ይህ ጉዳይ ተጠናቆ መቅረብ ሲገባው እነደገና ሌላ ቀጠሮ መሰጠቱ አግባብ ስላልሆነ አጭር ቀጠሮ ይሰጥልን በማለታቸው የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ለየካቲት 11 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ጦማሪ አቤል ዋበላ ላይ እየደረሰ ያለ ማሰቃየት
ጦማሪ አቤክ ዋበላ በበኩሉ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ለማቅረብ አንደሚፈልግ ተናግሮ ሲፈቀድለት ትላንትና ከፍርድ ቤት መልስ ጀምሮ በውሻ ሰንሰለት ታስሮ እንዳደረና ሲሰደብና ሲያዋርዱት አንደነበር ተናግሯል፡፡ ትላንትና ከፍርድ ቤት ወደ ማረሚያ ቤት በሚመለሱበት ወቅት ጠባቂዎቹ በካቴና ሳያስሩት አንደረሱት እና በራሳቸው ጥፋት የተነሳ ለምን አልታሰርክም ሲሉኝ ራሳችሁ ስላላሰራችሁኝ ብዬ በመመለሴ እናሳይሃለን በሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ወደ ቅሊንጦ መመለሱን አና እዚያ ከደረሰ ጀምሮ በውሻ ሰንሰለት ታስሮ ማደሩን ማእከላዊ በደረሰበት ድብደባ የተነሳ የጆሮ ማዳመጫ መሳሪያ ለማድረግ ተገዶ የነበረ በመሆኑ የጆሮ ማዳመጫ መሳሪያውንም አንደተቀማ ገልጾ ከዚህ ስወጣ ምን አንደሚጠብቀኝም አላውቅም ህይወቴ አደጋ ላይ ነው ሲል በከፍተኛ ምሬት እንባ እየተናነቀው ተናግሯል ፡፡ አቤት የደረሰበትን ሰቆቃ ሲናገር ችሎቱን ሲታደሙ የነበሩት ወላጅ አባቱ እህቱና ሌሎች ጓደኞች ሲያለቅሱ ታይተዋል፡፡
በቦታው የነበሩት የማረሚያ ቤቱ ተጠሪ ምክትል ሳጅን ዘውዱ በፍርድ ቤቱ ተጠርተው የተጠየቁ ሲሆን የማውቀው ነገር የለኝም በማለት መልሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የአቤልን አቤቱታ በጽሁፍ አንዲያስገባ የተናገረ ሲሆነ ማረሚያ ቤቱ በሚቀጥለው ቀጠሮ ምላሹን ይዞ እነዲመጣ በማዘዝ ችሎቱ ተጠናቋል፡፡
በተያያ ዜና በእስር ላይ በሚገኙት የዞን 9 ብሎገሮችና ጋዜጠኞች የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ጉዳይ ለተባበሩት መንግሰታት ድርጅት አለአግባብ እስር የተፈጸመባቸው ዜጎችን ጉዳይ lሚያይ ቡደን ቀርቧል ፡፡ በቡድኑ አሰራር መሰረት የኢትዬጲያ መንግሰት የቀረበበትን አቤቱታ አስመልክቶ መልስ ለመስጠት ጊዜ ይሰጠዋል፡፡ አቤቱታው
የታሰሩትን ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ያጋጠማቸውን የመብት ጥሰት ዝርዝር
2. የመታሰራቸው ምክንያት አግባብ አለመሆን የክሱን አለም አቀፍ መብቶችንም ሆነ የወንጀል ህግ መሰረቶች የጣሰ እና ሃሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ መሆኑን የሚያስረዳ ሲሆን መንግሰት ላይ የቀረበውን ክስ ያዘጋጁት Ethiopian Human Rights Project እና Freedom Now በተባሉ ድርጅቶች ናቸው፡፡
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ደብዳቤ
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ደብዳቤ
ቀን 02/06/2007 ዓ.ም
ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- የልጄ ተመስገን ደሳለኝን ጉብኝት ይመለከታል
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከአብራኬ የወጣ ሁለተኛ ልጄ ነው፡፡ ገና ከህፃንነቱ ጀምሮ ለሰው አሣቢ፣ ሀገር ወዳድና ታታሪ ስለመሆኑ ከእኔ በላይ የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡ ልጄ ተመስገን ለወገኔ አሰብኩ ባለ በእስር ቤት ያለጎብኚ እየተሰቃየብኝ ይገኛል፡፡ መቼም፣ የእናት ሆድ አያስችልምና እባካችሁ ልጄን ታደጉት፡፡ እባካችሁ ቢያንስ ካለበት እየሄድኩ የልጄን አይን እንዳይ እንዲፈቀድልኝ ተባበሩኝ፡፡ የልጄን ድምጽ ከሠማሁ ይኸዉ አንድ ወር ሞላኝ፡፡ ታናሽ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለወንድሙ ብሎ የቋጠረዉን ምሣ ይዞ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ቢሄድም በማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች ተደብድቦ የያዘውን ምግብ እንኳ ሣያደርስ ሜዳ ላይ ተደፍቶ ተመልሷል፡፡ መቼም እናንተም ልጆች ይኖራችኋል፤ ደግሞም የልጅን ነገር ታውቁታላችሁ፡፡ እኔ አሁን በእርጅና ዕድሜዬ ላይ እገኛለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ብቆይም ለትንሽ ጊዜያት ነው፡፡ በዚህች ጊዜ ውስጥ ልጄን እየተመላለስኩ እየጠየኩ፣ ድምፁን እያሰማሁ፣ አይዞህ እያልኩ ብኖር ለእኔ መታደል ነበር፡፡ እባካችሁ እርዱኝ የልጄ ድምጽ ናፈቀኝ፡፡ እሱን መጎብኘት የተከለከለበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንኳን እስካሁን አላወቅሁም፡፡ ከወንድሙ ድብደባ በኋላም ጥር 10 ወደ ጠዋት አካባቢ የሄዱት ጓደኞቹ እና ወንድሞቹ ሳያዩት ተመልሰዋል፡፡
ተምዬ ስታመም የሚያስታምመኝ፣ “አይዞሽ እማዬ” የሚለኝ ረዳቴ ነው፡፡ ሌላ ዘመድ የለኝም፡፡ የምተዳደረውም ልጆቼ ለፍተውና ደክመው በሚያመጧት ትንሽ ብር ነው፡፡ ዛሬ ግን ይኸዉ ልጆቼም ወንድማቸውን ለማየት እየተንከራተቱ ነው፡፡
በእናታችሁ ይዣችኋለሁ፤ ከቻላችሁ ልጄ እንዲፈታልኝ እና እኔም ያለችኝን ቀሪ የእድሜ ዘመን አይን አይኑን እያየሁ እንድኖር እንድታደርጉልኝ፤ ይህን ማድረግ ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ካለበት ድረስ እየተመላለስኩ እኔና ሌሎች ልጆቼ እንዲሁም ወገኖቹ እንዲጠይቁት ቢደረግልኝ ስል በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡ ልጄን አውቀዋለሁ፡፡ አንድ ነገር ሲገጥመዉ ሆድ ይብሰዋል፡፡ ቢያንስ እንኳን ቤተሰቦቹን ሲያይ ስለሚፅናና ይኸዉ እንዲፈቀድልኝ እማፀናለሁ፡፡ እኔ ምንም አቅም የሌለኝ አሮጊት ነኝ፡፡ ሁሉንም ለናንተ ሠጥቻችኋለሁ፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር እንደምታስተካክሉልኝ እና እንደገና የልጄን ፊት እንዳይ እንደምታደርጉኝ ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡
እንግዲህ የየካዉ ቅዱስ ሚካኤል ይከተላችሁ፡፡ መቼም የእናትን ሆድ ታውቁታላችሁ፤ የልጅ ነገር አያስችልም፡፡ ሆድም ቶሎ ይሸበራል፡፡ ስለዚህ እባካችሁ እኔንም ልጆቼንም እርዱን እንላለን፡፡
ግልባጭ
_ ለጠ/ሚኒስተር ፅ/ቤት
_ የህግና፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
_ ለአፈ-ጉባኤ ፅ/ቤት
_ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ)
_ ለእምባ ጠባቂ
_ ለአሜሪካ ኢምባሲ
_ ለእንግሊዝ ኢምባሲ
ከሰላምታ ጋር
ወ/ሮ ፋናዬ እርዳቸው