Daily Archives: February 13th, 2016

እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ተከላከሉ ተባሉ

*ተከሳሾች 200 የሰው መከላከያ ምስክሮች አሉን ብለዋል

የኢትዮ-ኤርትራ ድንበርን አቋርጠው ኤርትራ የሚገኘውን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ወታደራዊ ክንፍ ሊቀላቀሉ ከአዲስ አበባ ተነስተው ሲጓዙ ማይካድራ የሚባል የድንበር ከተማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሶ የፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የመሰረተባቸው እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡

ዛሬ የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾቹ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ወ/ሪት እየሩሳሌም ተስፋው፣ አቶ ፍቅረማርያም አስማማው እና አቶ ደሴ ካህሳይ አቃቤ ህግ ያቀረበባቸውን ክስ በሰነድና በአንድ የሰው ምስክር ማስረጃዎች አስረድቷል በሚል ተከሳሾች መከላከል ይገባቸዋል ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

Birhanu Tekleyared, et.al

ተከሳሾች 14ኛ ወንጀል ችሎት እንዲቀየርላቸው አቤቱታ አቅርበው እንደነበር በማስታወስ ይህ ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ችሎቱ ብይኑን እንዳያሰማ ቢጠይቁም፣ ችሎቱ ‹‹አቤቱታው ቶሎ ብይን እንዲሰጣችሁ የሚጠይቅ ነው፣ በመሆኑም ብይኑ ተሰርቷል›› ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡ በዚህም ተከሳሾች ብይኑ አይሰማብን የሚለውን ጥያቄ ባለመቀበል ችሎቱ ብይኑን በንባብ አሰምቷል፡፡

እነ ብርሃኑ ተከላከሉ መባላቸውን ተከትሎ መከላከያ ማስረጃዎች ያቀርቡ ከሆነ በሚል ፍርድ ቤቱ ጠይቆ፣ ተከሳሾች 200 የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች በጋራ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም መከላከያ ማስረጃዎችን ለማድመጥ ለመጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች እያዘጋጁት የነበሩት የተከሳሽነት ቃል ጽሁፍ በማረሚያ ቤት ፖሊሶች እንደተወሰደባቸው ለፍርድ ቤቱ በመግለጽ ከዚህም በኋላ ተመሳሳይ ለችሎት የሚቀርቡ ማስረጃዎችን ማዘጋጀት እንዲችሉ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ችሎት የቀረቡት እነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን እና እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጠኝ 14ኛ ወንጀል ችሎት እንዲቀየርላቸው አቤቱታቸውን በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ብይን ለማሰማት ለየካቲት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ መሰጠቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

እነ ሀብታሙ አያሌው ከእስር እንደሚፈቱ ተጠቆመ

በፌደራል አቃቤ ህግ ይግባኝ ተጠይቆባቸው ጉዳያቸውን በእስር ቤት ሆነው እየተከታተሉ የሚገኙት የቀድሞው አንድነት፣ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲዎች አመራሮችና መምህር አብርሃም ሰለሞን ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ እንደሚጽፍ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታውቋል፡፡

Politiciansበቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በደል እየተፈጸመብን ነው በሚል አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ እና አቶ ዳንኤል ሺበሽ የካቲት 1 ቀን 2008 ዓ.ም ባሰሙት አቤቱታ ላይ ማረሚያ ቤቱ መልስ እንዲሰጥ ለየካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም ተቀጥሮ በነበረው መሰረት ችሎት የቀረቡት ሦስቱ ይግባኝ መልስ ሰጭዎች ከማረሚያ ቤቱ መልስ ሳይሆን “ነገ መፈቻችሁ ይጻፍላችኋል” የሚል መልስ ከዳኛ ዳኜ መላኩ ተነግሯቸዋል፡፡

ይግባኝ መልስ ሰጭዎቹ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሽና መምህር አብርሃም ሰለሞን የስር ፍርድ ቤት ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በነጻ እንዲሰናበቱ መወሰኑን ተከትሎ ከእስር መፈታት ነበረባቸው የሚለውን ውሳኔ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን የአሁኑ የመፈታት ውሳኔም የዚሁ ውጤት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ዳኛ ዳኜ መላኩ ለአቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ እና ለአቶ ዳንኤል ሺበሽ “ነገ ለአምስታችሁም መፈቻችሁን እንልካለን፤ ሰኞ የሚኖራችሁን ቀጠሮ ከቤት መጥታችሁ ትከታተላላችሁ” ሲሉ እንደነገሯቸው የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡ አምስቱ ይግባኝ መልስ ሰጭዎች በስር ፍርድ ቤት ነጻ ከተባሉ ሰባት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተከሳሾቹ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ከእስር አለመፈታታቸው ታውቋል፡፡

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የምስክርነት ቃሉን ሰጠ

*”የህሊና እስረኛ ነኝ” እስክንድር ነጋ

Eskinder Nega

በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ 18 ዓመት እስር ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የመከላከያ ምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል፡፡

በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ አንደኛ ተከሳሽ ለሆነው አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ መከላከያ ምስክር ሆኖ ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ከእስር ቤት የቀረበው ጋዜጠኛ እስክንድር ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም ምስክርነቱን ሊያሰማ ችሏል፡፡

Zelalem Workagegnehuያለጠበቃ በግሉ የሚከራከረው ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ጋዜጠኛ እስክንድር እንዲያስረዳለት የሚፈልገው ጭብጥ ጡመራ ምንድነው፣ ከወንጀል ጋርስ ግንኙነት አለው ወይ፣ እና ሰብዓዊ መብት እና ዴሞክራሲ ላይ ስልጠና ስለሚሰጡ ድርጅቶችና የስልጠናው ይዘትን በተመለከተ እንደሆነ ቢያስታውቅም በጭብጡ ላይ አቃቤ ህግ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ በዚህም አቃቤ ህግ ጡመራ ምንድነው፣ ወንጀልስ ነው ወይ የሚለው በምስክር ሳይሆን በህግ ድንጋጌዎች የሚረጋገጥ እንደሆነ በመግለጽ ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከሰማ በኋላ ጡመራ ወንጀል ስለመሆን አለመሆኑ የተያዘውን ጭብጥ ውድቅ በማድረግ ስለ ስልጠናውና አሰልጣኝ ተቋማት የተመዘገበው ጭብጥ ላይ ምስክሩ እንዲመሰክሩ ብይን ሰጥቷል፡፡

ብይኑን ተከትሎ ምስክሩ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ችሎት ፊት የቀረበ ሲሆን በመጀመሪያ በፍርድ ቤቱ የቀረቡለትን ጥያቄዎች መልሷል፡፡ ምስክሩ ሙሉ ስሙን፣ እድሜውን፣ ስራውንና ለምን እንደመጣ፣ እንዲሁም ከተከሳሾች ጋር ስለመተዋወቁ ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል፡፡ እስክንድር ‹‹ስራ›› ተብሎ ሲጠየቅ፣ ‹‹ጋዜጠኛ ነበርኩ›› ብሏል፡፡ ‹‹አሁንስ›› የሚል ጥያቄ ፍርድ ቤቱ አቅርቦለት፣ ‹‹አሁን የህሊና እስረኛ ነኝ›› ሲል መልሷል፡፡

ተከሳሹ ዘላለም ወርቃገኘሁ በዋና ጥያቄ ተከሳሹ ውጭ ሀገር ሊወስደው ነበር ተብሎ በክሱ ላይ ስለተጠቀሰው ስልጠና ምስክሩ እንዲያብራሩለት ጠይቋል፡፡ ምስክሩም ‹‹ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትንም የሚያሳትፍ ስልጠና በሰብዓዊ መብት፣ በሚዲያ ‹ኢቲክስ›፣ እና በዴሞክራሲ ላይ ይሰጣሉ፡፡ ድርጅቶቹ የተለያዩ ቢሆንም በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ መርሃቸው ተመሳሳይና ዓለም አቀፍ ነው›› በማለት መስክሯል፡፡

ድርጅቶቹን በስም መጥቀስና የሚገኙበትንም ሀገር ለፍርድ ቤቱ መግልጽ ይቻል እንደሆነ ምስክሩ ተጠይቆ ‹‹የተቋማቱ መገኛ ምዕራቡ ዓለም ነው፡፡ በዴሞክራሲ የዳበሩ ሀገራት ነው ዋና መቀመጫቸው፡፡ ሲ.ፒጄ፣ ፍሪደም ሀውስ፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል እና አርቲክል 19 የመሳሰሉትንም በስም መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኔም ከነዚህ ተቋምት ውስጥ በአንዱ የተሰጠ ስልጠና አዲስ አበባ ላይ ተካፍየ ነበር፡፡ ስልጠናው ስለ ሰብዓዊ መብት፣ ስለ ሚዲያ፣ ስለ ዴሞክራሲ የሚያስተምር ነው፡፡ ስልጠናው ከሽብር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ ይህ እንደማስረጃ መቅረቡ ኢትዮጵያን ትዝብት ውስጥ የሚከትና የሚያሳዝን ነው›› ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መቼ እንደታሰረ በመስቀለኛ ጥያቄ ተጠይቆ ‹‹መስከረም 2004 የሀሰት ክስ ቀርቦብኝ፣ በግፍ ተፈርዶብኝ ታስሬ እገኛለሁ›› ሲል መልሷል፡፡ እስክንድር ነጋ ጥቁር ሱፍ በደብዛዛ ሸሚዝ ለብሶ፣ ሙሉ ጥቁር መነጸር አድርጎና ነጠላ ጫማ ተጫምቶ ችሎት ፊት ቀርቧል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ምስክሩ ምስክርነቱን ማጠቃለሉን ተከትሎ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡለት የጠራቸው ሌላኛው ምስክር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በተደጋጋሚ እንዲቀርቡለት ትዕዛዝ እንዲሰጥለት የጠየቀ ቢሆንም እስካሁን አለመቅረባቸው መንግስት ግለሰቡን ለማቅረብ ፍላጎት እንደሌለው ያሳያል ሲል ቅሬታውን አሰምቷል፡፡ ‹‹አሁን የተረዳሁት ነገር ከሳሼ የሆነው መንግስት አቶ አንዳርጋቸውን ከሚያቀርብ እኔን በነጻ መልቀቅ እንደሚቀለው ነው›› ብሏል ተከሳሹ፡፡

ተከሳሹ ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንደተገናኜ አቃቤ ህግ መጥቀሱን በማስታወስ ምስክሩ መቅረባቸው ያለውን ተገቢነት አስረድቷል፡፡ ‹‹ምስክሩ እንዲቀርቡልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ፍርድ ቤቱ ከምስክሩ ጋር በተገናኘ ያለውን የክሱ ፍሬ ነገር አውጥቶ በቀሪው ላይ ብይን ይስጥልኝ›› ብሏል ተከሳሹ አቶ ዘላለም፡፡

ፍርድ ቤቱም ምስክሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት ምስክርነታቸውን ለመስማት በሚል ለየካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ኢትዮጵያ

%d bloggers like this: