Category Archives: News

የዛሬው የአዲስ አበባ የታክሲ አድማ፤ ታሪክ ራሱን ሊደግም ይሆን?

ብስራት ወልደሚካኤል

የዛሬ 42 ዓመት በየካቲት 11 ቀን 1966 ዓ.ም. በቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ዘመን በሊትር የ10 ሳንቲም የነዳጅ ጭማሪን (50 በመቶ ጭማሪን)ተከትሎ የታክሲ ባለንብረቶች እና ሾፌሮች የታሪፍ ማሻሻያ ጭማሪ ቢጠይቁ ተቀባይነት በማጣታቸው የታክሲ አድማ ተደርጎ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ዕለት የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር በጠራው አድማ የሀገሪቱ መምህራን በሙሉ ስራ አቁመው ነበር፡፡ ይህም እየተቀጣጠለ ከአዲስ አበባ ወደ ሌሎች ከተሞች ሳይዳረስ በሚል የወቅቱ መንግሥት የነዳጅ ጭማሪውን መሰረዙን ይፋ አደረገ፡፡

Addis taxi strike

ይሁን እንጂ ተቃውሞው እንደሰደድ እሳት ተቀጣጠለ፤ከዛም መፍትሄ ይሆናል በሚል የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃብተወለድ ልክ የዛሬ 42 ዓመት የካቲት 21 ቀን 1966 ዓ.ም. ከስልጣናቸው እንዲሰናበቱ ተደረ፡፡ ይሄም መፍትሄ አልሆነም፤ይልቅ የመምህራን ማኀበርና የታክሲ የተቃውሞ አድማ ወደ ወታደሩ ዞረ፤ከዛም ንጉሱንም ዘውዳዊ ስርዓቱን ላይመለስ እስከነ አካቴው አሰናበተው፡፡ ልብ በሉ ይህ ሁሉ ልክ የዛሬ 42 ዓመት የነበረ የአዲስ አበባ ታክሲ አድማ ምን እንዳስከተለ፡፡ ይሄ ሁሉ 4ኛ ወሩን ያስቆጠረውና እስካሁንም የቀጠለውን የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ በተጨማሪ መሆኑ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በጎንደርም ተቃውሞዎች እያገረሹ መንገድ እስከመዝጋት እንደደረሱ እየተሰማ ነው፡፡

ዛሬ ከ42 ዓመት በኋላ በዘመነ ኢህአዴግ የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የመንግሥትን አዲስ መመሪያ በመቃወም የተደረገው የታክሲ አድማ በጠዋቱ ጀምሯል፡፡ ይህ እስከተፃፈበት ድረስም የአዲስ አበባው የታክሲ አድማ እንደቀጠለ ነው፡፡ አድማውም ለ ሁለት ተከታታይ ቀናት እንደሚደረገ የታቀደ ቢሆንም፤ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ግን አድማው ሊቀጥል እንደሚችል ነው፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ የአዲስ መመሪያ ዋና ሰለባዎች የታክሲ ሾፌሮች በመሆናቸው ነው፡፡

Flyers

New Addis Ababa Transport regulation

እስካሁን ባለው አድማም በከተማው የመንግሥት የመስሪያ ቤት የትራንስፖርት አገልግሎት አውቶቡስ፣ የግለሰቦች የጭነት ተሸከርካሪዎች (በግድ ተሳፋሪ እንዲጭኑ እየጠደረጉ) ከሚሰጡት አገልግሎት በስተቀር የተለመዱት የሚኒባስ ታክሲዎች አድማ መትተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ህዝብ ብዛትና ከተጠቃሚው ብዛት እንዲሁም ቀድሞም ከነበረው የትራንስፖርት እጥረት አንፃር የታክሲዎች አድማ የሚያስከትለው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡መንግሥት በስሩ ባሉ መገናኛ ብዙኃን በጠዋት ዜና እወጃው የአዲሱን የአዲስ አበባ ትራንሰፖርት ደንብ መመሪያ ትግበራ ለ3 ወራት ማራዘሙን ቢገልፅም፤የታክሲዎች አድማ ግን ቀኑን ሙሉ ቀጥሎ ውሏል፡፡

ምንም እንኳ ሀገር አቀፍ ምርጫ ከተደረገ 100 ቀናት ቢያልፉትም፤ የዛ “ምርጫ” ኢህአዴግ 100% የህዝብ ድምፅ “በምርጫ” አሸንፊያለው የሚለው መዝሙር ሳያባራ በየአቅጣጫው ጠንከር ያለ ተቃውሞ መምጣቱ ምናልባትም አማራጭ ሐሳብ ያለመኖርና እንዲኖር ያለመፈለጉ ያመጣው መዘዝም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በርግጥ የዛ ተዓምረኛው “ የ100% ምርጫ” ውጤት መዘዝ ገና ብዙ ክስተቶችን በመላው ሀገሪቱ ሊያስተናግድ እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡

የዛሬው የአዲስ አበባ የታክሲ ተቃውሞ አድማ ወደ ሌሎች የግልና መንግሥታዊ ተቋማት አድማሱን አስፍቶ የዛሬ 42 ዓመቱን ታሪክ ይደግመው ይሆን?

Public service Bus as a taxi in Addis

በተለይ ከዓለም ገበያና ሀገሪቱ ነዳጅ ከገዛችበት 365 % (ነዳጁ ከተገዛበት ወደ 4 እጥፍ) ክፍያ የተጫነበት ተጠቃሚው ህዝብ ትክክለኛ መረጃ ቢኖረው ከታክሲ አድማው ይልቅ የተሳፋሪው አለመቅደሙ አስገራሚ ቢሆንም፤የዛሬው የታክሲዎች አድማ ሌላም ቁጣ ይቀሰቅስ ይሆን ወይስ እንደተለመደው በማስፈራሪያ አሊያም ደንብ ቁጥር 208/2003 ተከትሎ ወጥቷል የተባለው አዲሱ መመሪያ ተሰርዟል በሚል ወደስራቸው ይመለሱ ይሆን?

ሁሉንም ጊዜ ያሳየናል፡፡

በኢትዮጵያ ለተከታታይ አራት ወራት የቀጠለው ተቃውሞ ላይ የሚፈፀመው ግድያና እስር መቀጠሉ አስመልክቶ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አስታወቀ

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች አራተኛ ወሩን ይዞ የቀጠለውን የኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ መንግሥት በፀጥታ ኃይሉ በወሰደው የኃይል እርምጃ ሰዎች መደላቸውን፣ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን እና መታሰራቸውን እንዲሁም ታግተው የደረሱበት ያልታወቁ ሰዎች መኖራቸውን በመግለፅ መግለጫ አወጣ፡፡

Oromia region protest 1

ሂውማን ራይትስ ዎች በመግለጫው “አጠቃላይ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር ለማረጋገጥ አልቻለም ምክንያቱም በኢትዮጵያ ያለው እንቅስቃሴ እና በነጻነት የመዘገብ ሁናቴ የተገደበ በመሆኑ ነው፡፡ ተሟጋቾች በተለይ ከማህበራዊ ድረ-ገፆችን መሰረት በማድረግ ባገኟቸው የቪዲዮ፣ የፎቶ እና የድረ-ገጽ ላይ ጽሁፎች መረጃዎች መሰረት ከኖቬምበር 12 ቀን ጀምሮ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ያለው መረጃ እንሚጠቁመው በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል፤ በርካቶቹ የት እንሚገኙም አይታወቀም፤ የሚገመተው በሃይል እንዲሰወሩ መደረጉን አስታውቋል፡፡

Oromia region protest 2

እ.አ.አ.ከህዳር ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በስፋት እየተካሄደ ያለውን ሰላማዊ ተቃውሞ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይል በጉልበት እያፈነው እንደሚገኝ ሂውማን ራይትስ ዎች አስታወቀ፡፡ ከ2016 ዓ.ም. መነሻ ጀምሮ በእየለቱ ሰዎች እንደሚገደሉ እና በዘፈቀደ እንደሚታሰሩ በመግፅ፤ የወታደራዊ ሰራዊትን ያካተተው የጸጥታ ሃይል ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ላይ የሚገኙ በርካታ ሰዎችን ቀጥታ በመተኮስ ገድሏል፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረው ያለምንም ክስ እንደታገቱ ይገኛሉ፡፡ ባለፉት ሳምንታት የተቃውሞው ድግግሞሽ የቀነሰ መስሎ ቢታይም አፈናው ግን ቀጥሏል፡፡” ይላል ፤በመግለጫው፡፡
የተቋሙን ሙሉ መግለጫ (በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ) ለማግኘት የሚከተለውን ሊንክ ይጠቀሙ፤

ምንጭ፡ https://www.hrw.org/am/news/2016/02/21/287126
https://www.hrw.org/news/2016/02/22/ethiopia-no-let-crackdown-protests

በኦሮሚያ ክልል ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ አሁንም ቀጥሏል፤ እየተገደሉ እና እየቆሰሉ ያሉ ዜጎችም መጠንም ጨምሯል

በህዳር አጋማሽ በምዕራብ ሸዋ የጀመረው ተቃውሞ በአብዛኛው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት በነበሩ ተቃውሞች ህፃናት እና ኣዛውንቶችን ጨምሮ ከ130 ያላነሱ ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተጠቁሟል፡፡ በተለይ በምዕራብ አርሲ አጄ አካባቢ በነበረው ተቃውሞውም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ህዝቡ ላይ የወሰዱትን የኃይል እርምጃ ተከትሎ 11 ያህል የመንግሥት ወታደሮች መገደላቸው ታውቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገሪቱ የፖለቲካ እስረኞች ከሚበዙበት ወህኒ ቤቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት የአምቦ ወህኒ ቤት በእሳት የመቃል አደጋ ደርሶበታል፡፡ የቃጠሎው መንስኤ እና ቃጠሎውን ተከትሎ ስለደረሰው ጉዳት ከመንግስትም ሆነ ከገለልተኛ አካል የተገለፀ ነገር የለም፡፡

Dembi dolo

በዛሬው የካቲት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ሐረርጌ መቻራ ከተማ በነበረው ተቃውሞ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልተለዩ በርካታ ሰልፈኞች መገደላቸውና ከ15 በላይ ዜጎች ደግሞ በፅኑ ቆስለው ገለምሶ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞን ተክተሎ በክልሉ እየታሰሩ ያሉ ወጣቶች ቁጥርም በከፍተኛ ደረጃ የቸመረ ሲሆን፤ በትናንትናው ዕለትም ዋና ፅህፈት ቤቱ 6 ኪሎ አዲስ አበባ አፍንጮ በር የሚገኘው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ/መድረክ ዋና ፅሕፈት ቤት በመንግሥት የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች ቁጥጥር ስረ ወድቆ በቢሮው የነበሩት ተደብድበው መታሰራቸውንም የፓርቲው የመረጃ ማኀበራዊ ገፅ አመልክቷል፡፡ በወቅቱ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲናም ወደ ቢሯቸው እንዳይገቡ ተከልክለው እንደነበር የፓርቲው ገፅ አስታውቋል፡፡

Oromo protest 2

በተለይ በምዕራብ አርሲ በነበረው ተቃውሞ የአካባቢው ሽማግሌዎች ለተቃውሞ የወጡና የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ንቁ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ በርካታ ወጣቶችን በመሰብሰብ በሚደረገው ተቃውሞ በሌሎች ብሔሮች አካልም ሆነ ንብረት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳትና ጥቃት እንዳትፈፅሙ፣ ተቃውሞ በምንግሥትና በስርዓቱ ላይ እንጂ በየትኛውም የህዝብ አካላ ላይ አይደለም፡፡ ይህን ተላልፎ የተገኘም የእና አካል አይደለም፤ሊሆንም አይችልም ሲሉ ቃል ማስገባታቸው ታውቋል፡፡ በክልሉ ያለው ተቃውሞ በአርሲ፣ በወለጋ፣ በነጌሌ፣ በሱሉልታ፣ በምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ተጠናክሮ መጠሉ ታውቋል፡፡ይሁን እንጂ መንግሥት ምዕራብ ወለጋን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የመከላከያ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን እና ሰራዊት የጫኑ ተሸከርካሪዎች በሰፊው ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል፡፡

እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ተከላከሉ ተባሉ

*ተከሳሾች 200 የሰው መከላከያ ምስክሮች አሉን ብለዋል

የኢትዮ-ኤርትራ ድንበርን አቋርጠው ኤርትራ የሚገኘውን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ወታደራዊ ክንፍ ሊቀላቀሉ ከአዲስ አበባ ተነስተው ሲጓዙ ማይካድራ የሚባል የድንበር ከተማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሶ የፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የመሰረተባቸው እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡

ዛሬ የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾቹ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ወ/ሪት እየሩሳሌም ተስፋው፣ አቶ ፍቅረማርያም አስማማው እና አቶ ደሴ ካህሳይ አቃቤ ህግ ያቀረበባቸውን ክስ በሰነድና በአንድ የሰው ምስክር ማስረጃዎች አስረድቷል በሚል ተከሳሾች መከላከል ይገባቸዋል ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

Birhanu Tekleyared, et.al

ተከሳሾች 14ኛ ወንጀል ችሎት እንዲቀየርላቸው አቤቱታ አቅርበው እንደነበር በማስታወስ ይህ ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ችሎቱ ብይኑን እንዳያሰማ ቢጠይቁም፣ ችሎቱ ‹‹አቤቱታው ቶሎ ብይን እንዲሰጣችሁ የሚጠይቅ ነው፣ በመሆኑም ብይኑ ተሰርቷል›› ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡ በዚህም ተከሳሾች ብይኑ አይሰማብን የሚለውን ጥያቄ ባለመቀበል ችሎቱ ብይኑን በንባብ አሰምቷል፡፡

እነ ብርሃኑ ተከላከሉ መባላቸውን ተከትሎ መከላከያ ማስረጃዎች ያቀርቡ ከሆነ በሚል ፍርድ ቤቱ ጠይቆ፣ ተከሳሾች 200 የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች በጋራ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም መከላከያ ማስረጃዎችን ለማድመጥ ለመጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች እያዘጋጁት የነበሩት የተከሳሽነት ቃል ጽሁፍ በማረሚያ ቤት ፖሊሶች እንደተወሰደባቸው ለፍርድ ቤቱ በመግለጽ ከዚህም በኋላ ተመሳሳይ ለችሎት የሚቀርቡ ማስረጃዎችን ማዘጋጀት እንዲችሉ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ችሎት የቀረቡት እነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን እና እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጠኝ 14ኛ ወንጀል ችሎት እንዲቀየርላቸው አቤቱታቸውን በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ብይን ለማሰማት ለየካቲት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ መሰጠቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

እነ ሀብታሙ አያሌው ከእስር እንደሚፈቱ ተጠቆመ

በፌደራል አቃቤ ህግ ይግባኝ ተጠይቆባቸው ጉዳያቸውን በእስር ቤት ሆነው እየተከታተሉ የሚገኙት የቀድሞው አንድነት፣ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲዎች አመራሮችና መምህር አብርሃም ሰለሞን ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ እንደሚጽፍ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታውቋል፡፡

Politiciansበቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በደል እየተፈጸመብን ነው በሚል አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ እና አቶ ዳንኤል ሺበሽ የካቲት 1 ቀን 2008 ዓ.ም ባሰሙት አቤቱታ ላይ ማረሚያ ቤቱ መልስ እንዲሰጥ ለየካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም ተቀጥሮ በነበረው መሰረት ችሎት የቀረቡት ሦስቱ ይግባኝ መልስ ሰጭዎች ከማረሚያ ቤቱ መልስ ሳይሆን “ነገ መፈቻችሁ ይጻፍላችኋል” የሚል መልስ ከዳኛ ዳኜ መላኩ ተነግሯቸዋል፡፡

ይግባኝ መልስ ሰጭዎቹ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሽና መምህር አብርሃም ሰለሞን የስር ፍርድ ቤት ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በነጻ እንዲሰናበቱ መወሰኑን ተከትሎ ከእስር መፈታት ነበረባቸው የሚለውን ውሳኔ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን የአሁኑ የመፈታት ውሳኔም የዚሁ ውጤት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ዳኛ ዳኜ መላኩ ለአቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ እና ለአቶ ዳንኤል ሺበሽ “ነገ ለአምስታችሁም መፈቻችሁን እንልካለን፤ ሰኞ የሚኖራችሁን ቀጠሮ ከቤት መጥታችሁ ትከታተላላችሁ” ሲሉ እንደነገሯቸው የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡ አምስቱ ይግባኝ መልስ ሰጭዎች በስር ፍርድ ቤት ነጻ ከተባሉ ሰባት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተከሳሾቹ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ከእስር አለመፈታታቸው ታውቋል፡፡