Category Archives: Social and Culture

ማንም ከኢትዮጵያዊነት ማማ ሊያወርደኝ አይችልም!

bedlu

በድሉ ዋቅጅራ

ሰሞኑን በፌስቡክ አድራሻዬ የጓዳ መልእክት ደረሰኝ፡፡ ‹‹አንተ በእርግጥ ማንነት አለህ? አንድ ጊዜ ኦሮሞነትህን ክደህ ጉራጌ ነኝ ትላለህ፡፡ ሌላ ጊዜ ኦሮሞ ነኝ ትላለህ፡፡ ያልገባህ ግን ጉራጌውም ሆነ ኦሮሞው ካንተ ሺህ ጊዜ የሚሻሉ ምሁራን አለው፡፡ አይፈልጉህም፡፡ የእንዳንተ አይነቱ መጠራቀሚያ ትምክህተኛ አማራ ስለሆነ እሱን ብትመርጥ ይሻልህ ነበር፡፡ . . . ›› ብሎ ይጀምርና ዋና ሀሳቡ ከዚህ ያልዘለለ አንድ አንቀጽ ይጨምራል፡፡

‹‹ሁሉም ነገር ለበጎ ነው›› እነሆ ታክቶኝ የተውኩትን ፌስቡክ እንድመለስበት አደረገኝ፡፡
ስለማንነት እኔ የማስበው እንዲህ ነው፡፡ . . . .
ትልቁ የራስ ማንነት መስፈሪያ የጎሳ ቁጭበሉ አይደለም፡፡ ሰው እንኳን ከጎሳው ከብሄራዊ መስፈሪያም የሚተርፍ ፍጡር ነው፡፡ የሰው ልጅ ነኝና ጉራጌነት ወይም ኦሮሞነት ሙሉ ማንነቴን አይገልጸውም፡፡ እንኳን ከጎሳ ከኢትጵያዊነትም ይተርፋል ማንነቴ፡፡ በኢሬቻ ላይ ስለሞቱት የምቆስለው ኦሮሞ ስለሆንኩ አይደለም፤ በቅርብ ጊዜ በአማራ ክልል በተፈጠረው ሁከት ስለተጎዱት አማራ ስላልሆንኩ የማይሰማኝ ከሆነ ሰብአዊ ፍጡር ነኝ አልልም፡፡ የሆነ የልቤ ጥግ ላይ በሶርያ ንጹሀን ላይ ስለሚደርሰው የሚደማ ክፍል አለ፡፡ ማንኛውም ሰው በአንድ ቋንቋ ተግባብቶ፣ አንድ የተለየ ባህል አዳብሮ በቋንቋውና በባህሉ ከመገለጹ አስቀድሞ ሰው በመሆኑ ይገለጽ ነበር፡፡ ፈጣሪም አዳም/አደም እና ሄዋን/ሀዋን ሲፈጥር ጎሳ ይቅርና ዜግነት አልነበራቸውም፡፡

ለእኔ ቋንቋዬ የሀሳብ መግለጫ፣ ባህሌ የአኗኗሬ መንገድ ብቻ ነው፡፡ እናቴ ጉራጌ ናት – ክስታኔ፡፡ አባቴና አባቱ ክስታንኛ አቀላጥፈው የሚናገሩትን ያህል ኦሮምኛም ይናገራሉ፡፡ በድሉ – ዋቅጅራ – ደበላ – ወልደጊዮርጊስ – ካሳ እያለ የሚዘልቀው የአባቴ ወገን መጠሪያ ሌሎችን የሚያስጨንቃቸውን፣ ግራ የሚያጋባቸውን ያህል እኔን አስጨንቆኝ አያውቅም፤ ግራም አያጋባኝም፡፡ የማያስጨንቀኝ እነሱን ስለምጠየፍ አይደለም፡፡ የማያስጨንቀኝ በማኛቸውም ማንነት ማንነቴን መበየን፣ ስለማልፈልግ ነው፡፡ እናቴ ኬርአለም ክስታኔ ናት፤ አባቴና አያቴ የኦሮሞና የጉራጌ ድብልቅ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወልደጊዮርጊስና ካሳ ትግሬ ወይም አማራ ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ እኔ ውስጥ ያለው ግን ከነዚህ ሰዎች ጎሳ በላይ ነው፡፡ እኔ ውስጥ በደም ከዝርያዎቼ ከተቀበልኩት ይልቅ፣ ካደግኩበት የኦሮሞ ማህበረሰብ ከልጅነት እስከ ጉርምስና የቀሰምኩት ይበልጣል፡፡ በወጣትነቴ ባሌ ለሶስት አመታት፣ ጎንደርና ጎጃም ለአስር አመታት ስኖር ማንነታቸውን አትመውብኛል፡፡ ባህር ተሻግሬም አውሮፓ ላይ ያን ያህል ኖሬያለሁ፡፡ ታዲያ እንዴት ነው የእኔን ማንነት በእናትና አባቴ ጎሳ (ምንም ይሁን ምን) የሚገለጸው? አዎ የክስታኝና ቋንቋን አፌን ፈትቼበታለሁ፤ እርግጥ ነው በጉራጌና በኦሮሞ ባህል ከልደት እስከ ጉርምስና ጥሪት ቋጥሬበታለሁ፤ አንድም ቀን ግን እራሴን ጉራጌ ወይም ኦሮሞ ብዬው አላውቅም፡፡ ላለፉት ሀያ አምስት አመታት ማንነትን በጎሳ የመበየን ፖለቲካ ተንሰራፍቶ እንኳን ጎሳዬን የማንነቴ መበየኛ አድርጌው፣ ወይን ሆኖ ተሰምቶኝ አላውቅም፡፡ ለዚህ ነው ጉራጌ ወይም ኦሮሞ መሆን አለመሆኔ የማያስጨንቀኝ፡፡ እኔ ከዚያ የበለጠ ሳልሸራረፍ የሚገልጠኝ ማንነት አለኝ – ኢትዮጵያዊንት፡፡

በ1991 አ. ም. የውጭ ትምህርት እድል አገኘሁና ፓስፖርት አስፈለገኝ፡፡ ኢምግሬሽን መስሪያ ቤት ሄጄ እንዲሰጠኝ አመለከት፡፡ ለወራት ጠብቅ አሉኝ፡፡ እኔ ደግሞ በሳምንት ውስጥ መሄድ ነበረብኝ፡፡ ከአንዲት ሀላፊ ዘንድ አቀረቡኝና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተጻፈልኝን የተባበሩት ደብዳቤ አሳይቼ ጉዳዩን አስርዳሁ፡፡ ያን ጊዜ ከዛሬው የተሻሉ ሀላፊዎች ነበሩ፡፡ በሳስት ቀን እንደሚደርስ ነግራኝ እራስዋ ፎርሙን ትሞላልኝ ገባች፡፡ የተጠየቅሁትን ስመልስ ትጽፋለች፡፡ የባለቤቴን ዘር/ጎሳ ጠየቀችኝ፤ ‹‹አላውቅም›› ስላት፣ ልታምን አልቻለችም – በፍጹም፡፡ ‹‹የልጅህን እናት ማንነት አታውቅም›› ከተጋባን አመት ተመንፈቃችን ነበር፡፡ ጉዳዩ ከህሊናዋ በላይ እንደሆነ ሁኔታዋ ይናገራል፡፡ ‹‹ማንነትዋን አውቃለሁ፣ የማላውቀው ጎሳዋን ነው›› ስላት፣ ስምዋን ጠየቀችኝና ስነግራት፣ ‹‹አማራ›› ብላ ፎርሙ ላይ ሞላች፡፡ ወደባህር ዳር ስመለስ ባለቤቴን ብጠይቃት፣ የኦሮሞና የአማራ ድብልቅ ልትሆን እንደምትችል ነገረችኝ፤ እርግጠኛ ግን አልነበረችም፡፡ ይህን መናገሬ ጎሳን ለማንነት መገለጫ አድሬጌ አለመቀበሌ፣ የዛሬው የጎሳ ፖለቲካ የፈጠረብኝ የጎንዮሽ ጉዳት አለመሆኑን ለማሳየት ነው፡፡

የሀገሬ ሰው በጎሳ ተደራጅቶ ለሀገሩን ችግር መፍትሄ ለመስጠት ሲሞክር ማየት፣ በተለይ በዚህ ሉላፊነት እንደሰደድ እሳት እየተዛመተ ባለበት ክፍለ ዘመን፣ ከማሳዘን አልፎ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡ በተለይ በውጭ የሚኖረው ዲያስፖራ በጎሳ እየተደራጀ፣ ‹‹የዚህ ጎሳ ተጠሪ እኔ ነኝ አንተ አይደለህም›› እየተባባለ ሲራኮት ማየት፣ ለሀገራቸው ሁለንተናዊ ታሪክ፣ አሁን ላለችበት ሁኔታ ያላቸው አረዳድ በወቅቱ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ተኮርኩሮ የገነፈለ እንደሆነ ለመገመት ምርምር አይጠይቅም፡፡ ‹‹ኦሮሞዎች ተደራጅተን የኦሮሞን መብት እናስከብር፤ አማራዎች ተደራጅተን የአማራን መብት እናስከብር፤ ጉራጌዎች ተደራጅተን የጉራጌን መብት እናስከብር፤ . . . ወዘተ. ብሎ መነሳት፣ በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ዘለቄታዊ የህዝቦች መብት መከበርንና ሰላምን አያመጠም፡፡ እያንዳንዱ ጎሳ የራሱን መብት ማስከበርን ዋና አላማው አድርጎ ከተደራጀ፣ ከሰማንያ በላይ ጎሳዎች በሚኖሩባት ሀገር የህዝቦችን መብት ተከብሮ በሰላምና በፍቅር፣ በመተሳሰብ መኖር ያዳግታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የአማራ ወይም ኦሮሞ ህዝብ መብት ሊከበር የሚችለው፣ የሀገሪቱ ህዝቦች በሙሉ የእነሱ መብት መከበር እንዳለበት አምነው ለመብታቸው መከበር ከታገሉላቸው ብቻ ነው፡፡ አንዱ ህዝብ ለሁሉም ህዝቦች፣ ሁሉም ህዝቦች ለአንዱ ህዝብ መብት ከታገሉ ብቻ ነው የኢትዮጵያ ህዝቦች መብታቸው ተከብሮ አብረው በሰላምና በፍቅር የሚኖሩት፡፡

ጎሳዊ አስተሳሰብን የሀገራችን ችግሮች መፍቻ አድርጎ ማሰብ ገኖ የወጣው በዚህ ባለንበት ፖለቲካዊ አስተዳደር ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ‹‹የሀገራችን ችግሮች ምንጭ ይህ ጎሳን መሰረት ያደረገ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ነው›› ብለው ተቃውመው የተነሱ ወገኖች እራሳቸው በጎሳ መደራጀታቸው ነው፤ ችግሩን የፈጠረውን አስተሳሰብ ህዳግ ተከትለን፣ አንድን ችግር ለመፍታት መነሳት የህልም ጉዞ ነው – እስከምንባንን እውን የሚመስል፡፡ ችግርን ለመፍታት የችግሩ ምንጭ ከሆነው አስተሳሰብ ማፈንገጥ ያሻል – ለአዲስ መፍትሄ በአዲስ መንገድ ማሰብ፡፡ ‹‹የእኔ ማንነት አዲስ የማንነት መገለጫ፣ ያልነበረ ነው›› ለማለት አይቃጣኝም፤ ግን ከወቅታዊው ጠባብ አስተሳሰብ ካሰፈነው የማንነት መገለጫ ያፈነገጠ ነው፡፡ ክስታንኛ ቋንቋዬ ነው፡፡ በክስታንኛና በኦሮምኛ ባህል ውስጥ አድጌያለሁ፡፡ ግን ሁለቱም ማንነቴን አይበይኑም፡፡ በቋንቋዬ ክስታኔ ስሆን፣ የኦሮሞ ባህሌ ይጎድላል፡፡ በባህሌ ኦሮሞ ስሆን፣ ቋንቋዬ ክስታንኛ ይጎድላል፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያዊነቴ ውስጥ እንኳን ግዝፍ የነሳ ቋንቋና ባህሌ፣ ረቂቁ ህልምና ቅዠቴ አለ፡፡ ኢትዮጵያዊ ስሆን ሙሉ እሆናለሁ፡፡

ኢትዮጵያዊ ነኝ!

ኢትዮጵያዊ ነኝ!
በላሊበላ አስቀድሼ፣ ሸህ ሁሴን ባሌ የተገኘሁ፤
በአባ ገዳ ተመራርቄ፣ መካ ላይ እርዝቅ ያገኘሁ፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!
ሳነቴ ላይ ውርጭና ጉም፣ ዳሽን ጫፍ ግግር በረዶ፤
ደሎ መና የአዋራ ጭስ፣ ዳሎል ላይ የእሳት እርጎ፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!
ጎጥ አይበቃኝ – የሀገር ስፍር፤
ጎሳ አይገልጠኝ – የሰው ስእል፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!

ኢትጵያዊ ነኝ!!
ይርጋለም ያጋጥኳትን ላም፣ ወለጋ ላይ አሰርሬ፤
ትኩስ እንገርዋን የጠጣሁ፣ አክሱም ላይ ጥገት አስሬ፤
ሰሜን ያለብኩትን ወተት፣ በአርሲ ጮጮ የሞላሁ፤
ጋምቤላ ወተቱን ንጬ፣ የሀረሪ ቆንጆ የቀባሁ፡፡
ወሰን የለሽ እግረ ፌንጣ፣
ሞተ ሲሉኝ ብን – ትር የምል፣ ሄደ ሲሉኝ የምመጣ፤
የቅዠት ምች፣ ህልም ፈቺ . . . ዳነ ሲሉኝ የማገረሽ፤
ወሰን አልባ እግረ ሞረሽ፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!

ኢትጵያዊ ነኝ!!
ጃውሌ የደንጊያ እጣን፣ ከርቤ ከጊንር ቋጥሬ፤
አቦዳይ ጫት ተዘይሬ፤
ከጂማ አባጁፋር መንደር፣ ከአዎል – በረካ ጀባ፤
ሶዶ ዋዳ ተዘፍኖልኝ – ጎዴ ላይ ቃጢራ አድሬ፤
አፋር ላይ በግመል እንገር፣ ምርቃናዬን የሰበርኩ፤
የሀገሬን ባንዲራ፣ ለአፋር ግመል ማተብ ያሰርኩ፡፡
ወሰን የለሽ እግረ ፌንጣ፣
ሞተ ሲሉኝ ብን – ትር የምል፣ ሄደ ሲሉኝ የምመጣ፤
የቅዠት ምች፣ ህልም ፈቺ . . . ዳነ ሲሉኝ የማገረሽ፤
ወሰን አልባ እግረ ሞረሽ፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!

በችግር የተተበተበው የጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት

ዮሐንስ አንበርብር

– ከ630 ሺሕ ሔክታር መሬት የለማው 76 ሺሕ ሔክታር ብቻ ነው
– መሬቱን የተረከቡ ባለሀብቶች 4.9 ቢሊዮን ብር ብድር አግኝተዋል
– የቀረጥ ነፃ መብትን ለሌላ ዓላማ ያዋሉ ተገኝተዋል

picture-11

በጋምቤላ ክልል ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የግብርና ኢንቨስትመንት በአቋራጭ ለመበልፀግ የጓጉ ባለሀብቶችን የሳበ፣ ከባንኮች የተወሰደውን ብድር ላልተገባ ዓላማ እንዲውል ያደረገና በኪራይ ሰብሳቢነት የተተበተበ እንደነበር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበ ጥናት አመለከተ፡፡
ጥናቱ እንዲካሄድ የወሰኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መሆናቸውን፣ 14 ባለሙያዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተወከሉበትና ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተውጣጡ ባለሙያዎች ያካሄዱት መሆኑን ምንጮች አመልክተዋል፡፡
በጥናቱ መሠረት ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ለ623 ባለሀብቶች 630,518 ሔክታር መሬት የተላለፈ መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ 409,706 ሔክታር በጋምቤላ ክልል መተላለፉን፣ ቀሪው 220,812 ሔክታር ደግሞ የፌዴራል የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በውክልና ከወሰደው መሬት ያስተላለፈው መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡

ከተላለፈው መሬት ውስጥ እስከ 2008 ዓ.ም. በድምሩ መልማት የቻለው 76,862 ሔክታር ብቻ መሆኑን የጥናት ውጤቱ ይጠቁማል፡፡

መሬቱ ላለመልማቱ በጥናቱ ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ባለሀብቶች ለልማቱ ትኩረት አለመስጠታቸው፣ አብዛኛው ባለሀብት መሬት የሚወስደው አልምቶ ራሱንና አገርን ለመጥቀም ሳይሆን ከባንክ ብድርና ከቀረጥ ነፃ መብት ጋር ተያይዞ የሚገኘውን ጥቅም በማጋበስ በአቋራጭ ለመክበር እንደሆነ ይገኙበታል፡፡
የመሬትና የይዞታ ካርታ መደራረብ፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላትና የመሳሰሉትም ተጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ አካባቢ ጥበቃ፣ መሬት አስተዳደርና ደን ልማት ቢሮ ከተመዘገቡ 651 ይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች ውስጥ 381 የሚሆኑት ካርታዎች በተለያየ መጠን እርስ በርሳቸው የተደራረቡ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡
መሬት ከተረከቡት 623 ባለሀብቶች የእርሻ መሣሪያ ያላቸው 226 ሲሆኑ፣ የእርሻ መሣሪያ የሌላቸው 397 መሆናቸውን ተገልጿል፡፡ ከአጠቃላይ የእርሻ ኢንቨስትመንቶቹ ውስጥ 479 የሚሆኑት ሥራ አስኪያጅ እንደሌላቸው ተጠቁሟል፡፡

ባለሀብቶቹ ከቀረጥ ነፃ መብት የመበዝበዝ አዝማሚያ እንዳላቸው የሚገልጸው ጥናቱ፣ ከ623 ባለሀብቶች ውስጥ 29 ባለሀብቶች የት እንደሆኑ ማግኘት አለመቻሉን ያስረዳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከወሰዱት መሬት በላይ ትራክተሮችን ወይም ሌሎች ተሽከርካሪዎችን እንደሚያስገቡ፣ እነዚህ ትራክተሮች እንዲሁም እንደ ፒክአፕና ሲኖትራክ ያሉ ተሽከርካዎች ደግሞ በእርሻ ቦታው እንደሌሉ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

ከሁሉም በላይ አሳዛኝ ገጽታን የያዘው ከባንክ ብድር አለቃቀቅ ጋር በታያዘዘ ጥናቱ የደረሰበት ግኝት ነው፡፡ በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ባላቸው ስምንት ወረዳዎች በተገኘው የመስክ መረጃ መሠረት ከ623 ባለሀብቶች ውስጥ 200 የባንክ ብድር አግኝተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 27 ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት፣ 161 ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጅማ ቅርንጫፍና 12 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ ጥናቱ ይዘረዝራል፡፡

ከ200 የባንክ ብድር ከተሰጣቸው ባለሀብቶች መካከል ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሁለት ተበዳሪዎች በባንክ ዝርዝር ውስጥ ያልተገኙ ቢሆንም፣ በመስክ በተደረገው ማጣራት ተበዳሪ ሆነው መገኘታቸውን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ለ200 ባለሀብቶች ለመሬት ልማት፣ ለካምፕ ግንባታ፣ ለተሽከርካሪ፣ ለማሽነሪ፣ ለሥራ ማስኬጃና ሌሎች ወጪዎች የተፈቀደላቸው ብድር 4.96 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል፡፡ እነዚሁ 200 ባለሀብቶች የተረከቡት መሬት 454,261 ሔክታር ሲሆን፣ 194 ለሚሆኑት የዚህ መሬት ባለቤቶች 1.99 ቢሊዮን ብር ብድር መለቀቁን ይገልጻል፡፡ በዚህ ብድር እስከ 2008 ዓ.ም. ብቻ 314,645 ሔክታር መሬት መልማት የሚጠቀምበት ቢሆንም፣ እስካሁን የለማው ግን 55,129 ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
ለሥራ ማስኬጃና ለሌሎች ወጪዎች በሚል ርዕስ 1.16 ቢሊዮን ብር ብድር የተለቀቀ ቢሆንም፣ ለምን ዓላማ እንደዋለ ግን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

ለካምፕ ማደራጃ ተብሎ የተለቀቀው ብድር 326,876,702 ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 180 ካምፖች በብሎኬትና በቆርቆሮ ሌሎች 19 የሚሆኑት ደግሞ በሳርና በቆርቆሮ መሠራታቸውን ይገልጻል፡፡
በልማት ባንክ ብድር 122፣ እንዲሁም በንግድ ባንክ 62፣ በድምሩ 184 ተሽከርካሪዎች ተገዝተው የተሰራጩ ቢሆንም፣ በመስክ ምልከታ የተገኙት 159 መሆናቸውን ጥናቱ ያስረዳል፡፡

‹‹የብድር ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ስናስገባ በቀጥታ በስልክ ተደውሎ ጉቦ ካልከፈልክ ለሥራ አስኪያጁ አይቀርብልህም፤›› በማለት አጥኝዎቹ ያነጋገሯቸው መግለጻቸው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

በተመሳሳይም ‹‹መሬቱን ተገኝተው ሳያዩት ውኃ ይተኛበታል፣ በስልክ ጥቆማ ደርሶናል፤›› በማለት ገንዘብ ካልተሰጣቸው ብድር  እንደማይፈቀድላቸው ጥናቱ ይጠቁማል፡፡

የጥናት ዝርዝሩ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርቡ ከኃላፊነታቸው የተነሱትን የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህርን ያካተተ ውይይት በማካሄድ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች በውል ተረክቦ የሚያስተዳድረው መሬት ውል እንዲቋረጥና ክልሎች እንዲያስተዳድሩ ወስኗል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሚና ክልሎችን ማገዝ እንዲሆን አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
ለባለሀብቶች የሚሰጥ ብድር ጠንካራ ክትትል እንዲደረግበት፣ እንዲሁም ለተባለው ዓላማ ያልዋሉ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ክትትል በማድረግ ዕርምጃ እንዲወስድ አዘዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት ለሪፖርተር ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹በውይይቱ ወቅት የተሰጡን አቅጣጫዎች አሉ፡፡ በእኛ በኩል ያሉ ችግሮችን ገምግመን የመፍትሔ ዕርምጃዎችን እንወስዳለን፤›› ሲሉ አቶ ጋትሉዋክ ገልጸዋል፡፡ (ለዚህ ዘገባ ውድነህ ዘነበ አስተዋጽኦ አድርጓል)

ምንጭ፡  ሪፖርተር ጋዜጣ

ክርስቲያንና ሙስሊም በገለምሶ

afendi-muteki

አፈንዲ ሙተቂ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ስለገለምሶው መምሬ ሙላቱ የምትተርክ አንዲት ጽሑፍ ለጥፌ ነበር፡፡ አሁን ሳስበው ግን ያቺ ጽሁፍ መሀል መንገድ ላይ ተቆርጣ የቀረች ሆና እየታየችኝ ነው፡፡ ስለዚህ ለናንተም፤ ለወገንም፣ ለታሪክ ጸሓፊያንም እንዲጠቅም ይህችኛዋን ሐተታ እጨምርበት ዘንድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በ1981 የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ይመስለኛል፡፡ ከትምህርት ቤት መልስ የጨዋታ ጓዶቼን ፍለጋ “ኒብራ” ከተሰኘው የገለምሶ ከተማ ዋነኛ ጎዳና ወረድኩ፡፡ ጓዶቼን ብዙም ርቀት ሳልሄድ ከትልቁ የጋሽ መሐመድ በከር መደብር በረንዳ ላይ አገኘኋቸው፡፡ እዚያም የኳስ ጨዋታ ሰዓታችን እስኪደርስ ድረስ በትረባና በፉገራ መናቆር ጀመርንና አንዱ ሌላውን ለማብሸቅ ይሞካክር ገባ (በጊዜው ትረባ፣ ፉገራና ለከፋ ጊዜያችንን የሚገፋልን ትልቅ መዝናኛችን ነበር)፡፡ እኛ የነበርንበትን በረንዳ በስተግራ በኩል ተጎራብቶ ወደ ታላቁ የሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድና “ሐድራ” ወደሚባለው እስላማዊ ማዕከል (መስጊዱ የሐድራ አንድ ክፍል ነው) የሚያስወጣ መንገድ አለ፡፡ መንገዱ በወቅቱ በጎርፍ ክፉኛ ተጎድቶ ስለነበር ወደ አስር የሚደርሱ የቀን ሰራተኞች ድንጋይ እየቀጠቀጡ የተቦረቦረውን የመንገዱን የመሀለኛውን ክፍል ይሞሉትና በድንጋዩ ላይ አሸዋ እየመለሱ ይደመድሙት ነበር፡፡

ይህ የምላችሁ መንገድ በጎርፍ የተጠቃው በዚያን ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ ዘወትር ክረምቱን ጠብቆ ከካምቦ ተራራ በሚወርደው ሀይለኛ ጎርፍ እየተደረመሰ አሳሩን ያያል፡፡ የከተማው ማዘጋጃ ቤት በመንገዱ ዳርና ዳር የፍሳሽ መውረጃ ቢሰራለትም ጎርፉ በጣም ከባድ በመሆኑ የተሰራለትን መውረጃ በመተው ወደ መሀል መንገድ ዘው ብሎ እየገባ መንገዱን ማበላሻሸቱ የየዓመቱ ትዕይንት ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ መኪና ይቅርና ሰዎችና የጋማ ከብቶችም በዚያ ዳገታማ መንገድ ሲወጡና ሲወርዱ መከራቸውን ነው የሚያዩት፡፡
ክረምቱ ካለፈ በኋላ መንገዱ ይጠገናል፡፡ ጥገናው የሚከናወነው በአብዛኛው በነጋዴ ግለሰቦች እንጂ በማዘጋጃ ቤቱ አይደለም፡፡ ታዲያ ከላይ በጠቀስኩትና ወሩንና ቀኑን በዘነጋሁት የ1981 አንደኛው ዕለት መንገዱን የሚያስጠግነው ግለሰብ ከወትሮው የተለየ ሆነብኝና በደንብ አየሁት፡፡

ሰውየው ቄስ ነው፡፡ መንገዱ ደግሞ ወደ መስጊድ የሚያስወጣው ትልቁ መንገድ ጎዳና፡፡ ቄሱ ወደ መስጊድ የሚያስወጣውን ትልቁን መንገድ ያስጠግናል!! አጃዒብ! በልጅነት አዕምሮዬ ተገረምኩ፡፡ በጣም ተደመምኩ፡፡ እናም በአቅራቢያችን የነበሩትን ጋሽ መሐመድ በከርን ስለሰውየውና ስለመንገድ ጥገናው ጠየቅኳቸው፡፡
“ዛሬ መንገዱን የሚያስጠግነው ቄስ ነው እንዴ?”
“አይ ቄሱ ሳይሆን ቤተክርስቲያን ነው”
“የቱ ቤተክርስቲያን?”
“መድኃኒ ዓለም ቤተክርስቲያን ነዋ! በገለምሶ ስንት ቤተክርስቲያን ነው ያለው?”
“ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል? የመስጊድን መንገድ ነው እንዴ ቤተክርስቲያን የሚያስጠግነው?”
“እንዴት ሊሆን አይችልም? እነርሱስ ቢሆኑ የኛ ሰዎች አይደሉም እንዴ? እኛስ ቤተ ክርስቲያናቸው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ቢጠቃ ዝም ብለን እናያለን እንዴ?”

ጋሽ መሐመድ የነገረኝ ነገር እውነት መሆኑን በደንብ ያረጋገጥኩት በአስር ሰዓት ገደማ ቄሱ ለሰራተኞቹ ክፍያ በፈጸሙበት ወቅት ነው፡፡ በነጋታውም እኒያ ቄስ ሰራተኞችን አሰማርተው መንገዱን ሲያስጠግኑ ነበር የዋሉት (እኚያ ቄስ የአካባቢያችን ተወላጅ አልነበሩም፤ ለዚህም ነው ስማቸውን ያልያዝኩት፡፡ ሆኖም ቀጠን ብሎ ዘለግ ያለው ሰውነታቸው፣ ጠይም መልካቸውና ሰልካካ አፍንጫቸው እስከ አሁን ድረስ ይታወሱኛል፤ ብዙ ጊዜም ሰማያዊ ቀለም ያለው ቆብ ነው በራሳቸው ላይ የሚያደርጉት)፡፡

ልብ ያለው ይበል! እንዲህ አይነት ታሪክ በገለምሶ ተፈጽሟል፡፡ የገለምሶ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ወደ ሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድ የሚያስወጣውን መንገድ በራሷ ገንዘብ አስጠግናለች፡፡ በገለምሶ የክርስቲያንና ሙስሊሙ ፍቅር እስከዚህ ድረስ ነበር፡፡ ዛሬ በአካል እዚያ ባልኖርም ይህ የጥንት ፍቅራችን አሁንም ድረስ እንዳልቀዘቀዘ ቤተሰቦቼ ያወጉኛል፡፡

“የሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድስ ለክርስቲያኖችና ለቤተክርስቲያኒቷ ምን አድርጎ ያውቃል?” ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም መቼስ! እንዲያ ከሆነ የሚከተለውን ታሪክ ላጋራችሁ፡፡

የሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድ “ሐድራ” የሚባለው እስላማዊ ማዕከል አንዱ ክፍል ነው- ከላይ እንደጠቀስኩት፡፡ ይህ ሐድራ የሚባለው ማዕከል ከትልቁ መስጊድ ሌላ የቁርአን መማሪያ (ቁርአን ጌይ)፣ የዒልሚ መማሪያ (ቤይተል ዒልሚ)፣ የሴቶች መማሪያና መስገጃ፣ የዚክሪና አውራድ ማድረጊያ፣ የአዛውንቶችና የሽማግሌዎች መኖሪያና ሌሎች በርካታ ቤቶች አሉት፡፡ እንዲሁም “ቤይቱል ሐድራ” የሚባለውና የሁሉም እንግዶች ማረፊያ የሆነው ቤት (በስፋቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲውን ልደት አዳራሽ የሚያክል) በዚሁ ሐድራ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ እነዚህ ቤቶች ሁሉ ከዓመት እስከ ዓመት ተመሳሳይ አገልግሎት ነው የሚሰጡት፡፡ በመውሊድ ጊዜ ግን አገልግሎታቸው ይቋረጥና በበዓሉ ለመታደም የሚመጡትን እንግዶች ያስተናግዳሉ፡፡ በየቤቶቹ ውስጥ ሰለዋትና መንዙማ ይደረጋል፡፡

በገለምሶ የሚከበረው መውሊድ ሞቅ ደመቅ ያለ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ የሚታደሙ እንግዶች ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍለሀገራት ይመጣሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ከጎረቤት ሀገራት ጭምር (ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና የመን) በርካታ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ እነዚህን እንግዶች ለማስተናገድ በትንሹ አስራ አምስት በሬዎችና ሶስት ግመሎች ይታረዳሉ፡፡ ግመሎችና በሬዎቹን የሚገዙት ግን የሐድራው ሰዎች አይደሉም፡፡ ድሮ በሼኽ ዑመር አሊዬ እጅ የተማሩ ሼኮችና ሌሎች የሼኽ ዑመር ወዳጆች ናቸው ከብቶቹን የሚያመጡት፡፡

ታዲያ የሐድራው ሀላፊዎችና የመስተንግዶ መሪዎች ወደነርሱ የሚመጡትን ከብቶች በሙሉ አያርዷቸውም፡፡ በቅድሚያ አንድ ወይም ሁለት በሬ ለሴቶች ይሰጥና የከተማው ሴቶች ከልዩ ልዩ ክፍለ ሀገራት የሚመጡ ወይዛዝርትን እንዲያስተናግዱበት ይደረጋል (በሐድራ ውስጥ ሴትና ወንድ መቀላቀል ክልክል ነው፤ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ምግባቸውን ለየራሳቸው ነው የሚያዘጋጁት፤ ደግሞም የሁለቱም ጾታ ሰዎች ከተፈቀደላቸው ክልል ውጪ መውጣት የለባቸውም)፡፡

በማስከተልም አንድ በሬ ለስጋ ደዌ በሽታ ተጠቂዎች ይሰጣል፡፡ እንዲህ የሚደረግበትን ምክንያት በትክክል ባላውቅም በዘመኑ በነበረው ልማድ የተነሳ የበሽታው ተጠቂዎች መሸማቀቅ ሳይደርስባቸው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተናግዱ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ይመስለኛል፡፡ በሬዎቹ ለሴቶችና ለስጋ ደዌ ህሙማኑ የሚላኩት ግን ለግብዣና ለፌሽታ ብቻ አይደለም፡፡ በመስተንግዶው የሚታደሙት ሰዎች ሰለዋት ስለሚያደርጉና የነቢዩን ገድል በመንዙማ ስለሚያወድሱ ነው፡፡ እንዲያ የማያደርግ ጀመዓ ለመውሊድ ከመጣው በሬ አንዳች ድርሻ የለውም፡፡

ነገር ግን ይህ መመሪያ የማይመለከተው አንድ ክፍል አለ፡፡ የገለምሶ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን! በዓሉን የማታከብር ሆኖም ከመውሊድ በሬዎች የራሷ ድርሻ የነበራት ብቸኛ አካል እርሷ ነበረች፡፡ ለዚያውም ለርሷ የሚደርሳት አንድ በሬ ብቻ አይምሰላችሁ! ሁለት በሬዎችን ነው በየዓመቱ የምታገኘው፡፡
የዚህ ምክንያት ለረጅም ጊዜ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ዕድሜዬ ከፍ ካለ በኋላ ግን ምክንያቱን የሐድራው መሪ የሆኑትን ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅን ጠይቄ ከአንደበታቸው ተረዳሁ (ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ የሐድራው መስራች የነበሩት የሼኽ ዑመር አሊዬ ልጅ ናቸው- አሁን ዕድሜአቸው ከዘጠናው ተሻግሮ ወደ መቶ ዓመት እየተጠጋ ነው)፡፡

ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ ሁለት በሬዎች በየዓመቱ ለቤተክርስቲያን የሚሰጥበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ነበር ያስረዱኝ፡፡

“እነዚህ ክርስቲያኖች ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ እንደኛው የአዳም ልጆች ናቸው፡፡ በሀይማኖት ብንለያይም የአንድ ሀገር ሰዎች ነን፡፡ ከዚያም አልፎ የአንድ ከተማ ነዋሪዎች ነን፡፡ በሬዎቹ ወደኛ የሚመጡት በዓላችንን በደስታ ለማክበር እንድንችል ነው፡፡ እኛ በሬዎቹን አርደን በዓላችንን በደስታ ስናከብር ክርስቲያን ወገኖቻችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ እስልምናችን ጎረቤቶቻችንንም ማስደሰት እንዳለብን ያዘናል፡፡ ስለዚህም ነው በሬዎቹን ወደ ቤተክርስቲያን የምንልከው”፡፡

እንዲህ ዓይነቱን ውብ ባህል ምንድነው የምትሉት? “መቻቻል” ነው የሚባለው ወይስ ሌላ ስም አለው? እኔ ግን “መቻቻል” አልለውም፡፡ ይህ በተመን የማይመነዘር ፍቅር ነው እንጂ “መቻቻል” የሚለው ዘመን ወለድ ታፔላ የሚለጠፍለት አይሆንም፡፡ “መቻቻል” ሲባል አንዱ ወገን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሌላውን የሚያስከፋ ድርጊት በሚፈጽምበት ጊዜ ሌላኛው ወገን በትዕግስት ችሎ ማለፍ ይገባዋል የሚል እድምታ ያለው ይመስለኛል፡፡ በኔ ከተማ ግን ፍቅር ሰባኪ የሆኑት ሼኮች እና ቄሶች ክፋት ሊፈጸም የሚችልባቸውን ሽንቁሮች ሁሉ ቀድመው የደፈኗቸው በመሆኑ “መቻቻል” የሚባለው አነጋገር እዚያ ዘንድ ተራ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ በዚያች እትብቴ በተቀበረባት መሬት ያየሁትና የሰማሁት “ፍቅር” ነው እንጂ “መቻቻል” አልነበረም፡፡

በኔዋ የገለምሶ ከተማ እንዲህ ዓይነት ፍቅር ነበረን፡፡ በሌላው ኢትዮጵያስ ቢሆን? ዲግሪው (መጠኑ) ይለያይ ይሆናል እንጂ ተመሳሳይ ታሪኮች ሞልተዋል፡፡ እንዲህ በህብረት የኖረውንና ፍቅርን የተቋደሰውን ህዝብ የፖለቲከኞች ወሬ ሆድና ጀርባ ሊያደርገው ከቶ አይቻለውም፡፡ ፖለቲከኞች በሌሎች ሀገራት በስለት እንኳ ተፈልጎ የማይገኝ ይህንን ውብ ባህላችንን በዓለም ዙሪያ ቢያስተዋውቁልን ነው የሚያምርባቸው፡፡
እኛ አንድ ነን፡፡ ወንድማማቾች ነን፡፡ ፍቅር ነን፡፡ ክብር ነን፡፡ ህብር ነን፡፡ ሰሞነኛ ወሬ አያለያየንም፡፡
—–
ተፃፈ በአፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 21 ቀን 2005

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ

(አዲስ ሚዲያ) የበርካታ ዓለም አቀፍ የሩጫ ውድድር ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ሆኖ ተመረጠ፡፡ ምርጫው የተደረገው ጥቅምት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ በጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ሲሆን፤ በውድድሩም አቶ ተፈራ ሞላ እና አቶ ዳኛቸው ሽፈራው ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ በመጨረሻም የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በመወከል የተወዳደረው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ከነበሩት አምስት ድምፆች መካከል የዘጠኙን በማገኘት በማሸነፉ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን እንዲመራ በፕሬዘዳንት ተመርጧል፡፡

haile-gebreselassie

አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ    ( ፎቶ ክሬዲት ቢቢሲ)

ከአትሌት ሻለቃ ኃይሌ በተጨማሪ ለስራ አስፈፃሚነት አትሌት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም በእጩነት ቀርበው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለስራ አስፈፃሚነት አሸናፊ ሆኖ የተመረጠው አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም መሆኑ ታውቋል፡፡

ቀደም ሲል ለሀገሪቱ የአትሌቲክ ውጤት መውረድ ከፌዴሬሽኑ በተጨማሪ በጋራ ሲሰራ የነበረው የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኀበር አመራር የነበሩት አትሌት መሰረት ደፋር እና አትሌት ስለሺ ስህን በተለይ ከአትሌቶች ተመሳሳይ ቅሬታ ሲቀርብባቸው የነበረ ቢሆንም፤ በአዲስ ስራ አስፈፃሚ ውስጥ በድጋሚ አባል እንዲሆኑ መደረጉም ተጠቁሟል፡፡

በተለይ ባለፈው በለንደን ኦሎምፒክ እና በቀርቡ በተካሄደው የሪዮ ዲ ጄኔሪዮ ኦሎምፒክ የአትዮጵያ አትልቲክስ ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ውድድር ባልተለመደ መልኩ እየቀነሰ በመሄዱና ብት ያላቸው ተወዳዳሪዎች ለውድድር ለምን አልተጋበዙም በሚል የስፖርቱ ደጋፊና አፍቃሪ እንዲሁም አትሌት ኃይሌ እና አትሌት ገብረእግዚአብሔርን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ስመ ጥር አትሌቶች በይፋ ቅሬታ ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡

የአትሌት ኃይሌ ለፕሬዘዳንት መመረጥና የአትሌት ገብረእግዚአብሐየር ለስራ አስፈፃሚነት መመረጥ ከስፖርቲ ደጋፊና አፍቃሪ ኢተዮጵያውያን በተጨማሪ ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማኀበርም የእንኳን ደስ ያላችሁ ድጋፍ ተችሯቸዋል፡፡

የጣይቱ ልጆች ፤የኢትዮጵያ ደም መላሾች

dr-admasu-gebeyehu

አድማሱ ገበየሁ (ዶ/ር፣ ኢንጂነር)
(ጥቅምት 25 ቀን 2009 ዓ.ም)

ጣይቱ አሰኔ በወሎ ክፍለ-ሀገር በቦረና አውራጃ በጫቀታ ወረዳ ልዩ ስሙ ጅሩ ጉጣ ከተባለው ቀበሌ ተወለደች። ገና ልጅ እንዳለች ባሻ ዘለቀ ላቀውን አገባች። ዘለቀ የተወለደው በወሎ ክፍለ-ሀገር፡ ቦረና አውራጃ፡ ጫቀታ ም/ወረዳ፡ ልዩ ስሙ ገዛዛ አቦ ከተባለው ቀበሌ ነው። ጣይቱና ዘለቀ ሁለቱም የጫቀታ ተወላጆች ሲሆኑ መኖሪያቸው ጅሩ ጉጣ (ከጣይቱ ትውልድ ቦታ) ነበር።
የጣይቱ አሰኔ አባት አሰኔ ወዳጅ (አባ ጨፍልቅ) ይባላሉ። አባ ጨፍልቅ የንጉሥ ሚካኤል ባለሟልና የአንድ ክፍለ ጦር አዛዥ ነበሩ። አባ ጨፍልቅ አድዋ ጦርነት ላይ ሲዋጉ ጥይት አልቆባቸው አንድ ጠላት በአለንጋ መተው ገድለዋል ይባላል። ይህንን በተመለከተ፡
“ሰው ሁሉ የሚገል በጎራዴ ነው፤
ሰው ሁሉ የሚገል በመሣሪያ ነው፤
የእኛ አሰኔ ወዳጅ በአለንጋው ነው።”
የሚል ተገጥሞላቸዋል። አባጨፍልቅ “የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ባሕር ጠረፍ ነው።” ይሉ እንደነበር ይነገራል። አባ ጨፍልቅ በዘወትር ፀሎታቸው “ድንበር አልፎ የገባውን ጠላት (ጣልያና ፈረንሳይን) ሳናባርር ሞትን እንዳትልክብኝ፣ ያዝልኝ።” ይሉ ነበር ይባላል።

ጣይቱ በ1904 ዓ.ም በላይ ዘለቀን ወለደች። ከሁለት ዓመት በኋላም በ1906 ዓ.ም እጅጉ ዘለቀን ወለደች። እጅጉ እንደተወለደ የጣይቱ ባለቤት ባሻ ዘለቀ ከቤተሰብ ተለይቶ ወደ ዳር አገር ዘመተ። ብዙም ሳይቆይ ጣይቱ መሸሻ አደምን አገባች። መሸሻ አደም የተወለደው በወሎ ክፍለ-ሀገር፡ ቦረና አውራጃ፡ በሜታ ም/ወረዳ፡ ልዩ ስሙ ወርቄ አቦ በተባለው ቀበሌ ነው። ጣይቱ ሦስተኛ ልጅ አያሌው መሸሻን በ1908 ዓ.ም ከመሸሻ ወለደች።
ጣይቱ ሁለት ባሎች አከታትላ ብታገባም አብራ ለመኖር ግን አልታደለችም። የበፊተኛው ማለትም ዘለቀ ላቀው ከልጅ ኢያሱ ሠራዊት ጋር ተቀላቀለ። በጥቅምት ወር 1909 ዓ.ም ደግሞ የአያሌው አባት መሸሻ አደም የንጉሥ ሚካኤልን የዘመቻ ጥሪ ተቀብሎ ሰገሌ (ሸዋ ደብረ ብርሃን አጠገብ) በተደረገው ጦርነት ለመሳተፍ ዘመተ። ግን አልተመለሰም በዚያው ቀረ።

ስለ ጣይቱ ልጆች (በላይ፡ እጅጉና አያሌው) ታሪክ መነሻ ለማግኜት ይረዳ ዘንድ ስለ ባሻ ዘለቀ ማወቅ ይጠቅማል። ባሻ ዘለቀን ለመዝመት ያነሳሳው ልጅ ኢያሱ የኢትዮጵያን ወሰን መልሶ እስከ ባሕር ጠረፍ ለማድረስ ብርቱ ምኞት እንደነበረው ከአማቱ (ከጣይቱ አባት ከሀሰኔ ወዳጅ) ይሰማ ስለነበር ነው። ልጅ ኢያሱ ከመንገሡ በፊት ጣልያንና ፈረንሳይን ከአገራችን በማባረር ጠረፋችንን ለማስከበር አስቧል የሚል ወሬ በስፋት ይሰማ ነበር። ይንንም ለማሳካት ልጅ ኢያሱ ከጀርመንና ከቱርክ ጋር ተፈጣጥሟል ተብሎም ተወርቶ ነበር። ባሻ ዘለቀ ላቀው ከልጅ እያሱ ሠራዊት ጋር ተቀላቀለ። ከልጅ ኢያሱ ጋር ሆኖ በአፋር፡ በጅቡቲ መስመር (ሶማሌ)፡ እና በሐረር አካባቢ ሲንቀሳቀስ ቆዬ።

መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም የመስቀል ዕለት ባሻ ዘለቀ ከልጅ ኢያሱ ጋር ሐረር ነበር። አኩለ ቀን ሲሆን “የሸዋ ሰው አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ አድርጎ አዲስ መንግሥት አቋቁሟል፤ ወይዘሮ ዘውዲቱን ንግሥት፤ ደጃማች ተፈሪን ደግሞ አልጋ ወራሽ አድርጎ ሾሟል” ተብሎ ተነገረ። ብዙም ሳይቆይ የኢያሱ አባት ንጉሥ ሚካኤል የልጃቸውን ሥልጣን ለማስመለስ ወደ ሸዋ ዘምተዋል የሚል መልእክት ደረሰ። የልጅ ኢያሱም ሠራዊት ከንጉሥ ሚካኤል ሠራዊት ጋር ለመቀላቀል ገሠገሠ። ይሁን እንጂ ንጉሥ ሚካኤል በለስ እንዳልቀናቸውና እንደተማረኩ ተረጋገጠ።

ለባሻ ዘለቀ ሌላ ተጨማሪ መርዶ ደረሰው። “መስከረም 22 ቀን 1909 ዓ.ም. በቤተ መንግሥት ሹም ሽር ሆኖ የሰላሌው ገዢ ደጃዝማች ካሣ ኃይሉ በግዛታቸው በሰላሌና በላስታ ላይ እንሳሮና መራቤቴ፣ ደራ፣ ሚዳ፣ ቦረና ተጨምሮላቸው ራስ ተባሉ።” የሚል መረጃ ደረሰው። ባሻ ዘለቀ ወደ ቦረና ቢመለስ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ገመተ። ያለው አማራጭ እስከመጨረሻው ከልጅ ኢያሱ አለመለየት ነው ብሎ ወሰነ።

ባሻ ዘለቀ ከልጅ ኢያሱ ጋር በወሎና በትግራይ አካባበቢ ለአምስት ዓመታት ያህል ሲንቀሳቀስ ቆዬ። ልጅ ኢያሱ ተይዞ ኮረማሽ ታሰረ፤ ብዙም ሳይቆይ በኅዳር 29 ቀን 1914 ዓ.ም ወደ ፍቼ ተዛውሮ በሰላሌ ገዢ በራስ ኃይሉ ጠባቂነት እንዲታሰር ተደረገ። ከልጅ ኢያሱ መታሰር በኋላ ባሻ ዘለቀ ወደ ቦረና ሄዶ የዘመድ አዝማድ ከለላ ማግኘትን መረጠ። በጫቀታ ወረዳ ልዩ ስሙ ጣቀት መደሎ ከተባለው ቀበሌ ተቀምጦ እንዳለ አንድ ሰው በእጁ ጠፋበት (ሞተበት)። ከዚያም ሸፈቶ በጎጃም ክፍለ ሀገር በቢቸና አውራጃ በእነማይ ወረዳ ልዩ ስሙ ለምጨን ከተባለው ቀበሌ እንደተቀመጠ ከደብረማርቆስ በታዘዘ ጦር ተገደለ።

በላይ ዘለቀና እጅጉ ዘለቀ አባታቸው ሲሞት ገና የ10 እና የ12 ዓመት ልጆች ነበሩ። እድሜያቸው ከፍ ሲልና አካላቸው ሲጠነክር አባታቸውን በጥቆማ መርቶ ያስገደለውን ግራዝማች ደርሰህ የተባለውን ሰው ገድለው ጫካ ገቡ። የእናታቸው ልጅ ታናሽ ወንዳማቸው አያሌውም በሽፍትነቱ ተቀላቀላቸው።
ሦስቱ ወንድማማቾች በሽፍትነት በአባይ ወንዝ ዳርቻ ባለው በርሃ በመንቀሳቀስ ከየዘመዱ ስንቅ እያሰባሰቡ ጥቂት ዓመታት እንዳሳለፉ የጣልያን ጦር ደብረማርቆስ መግባቱ ተሰማ። እነበላይም የእናትና የአባታቸውን ወገን ሰብስበው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተመካከሩ። ጣልያን በ1928 ዓመት አገራችንን ሲወር የጣይቱ ልጆች በላይ ዘለቀ 24፡ እጅጉ ዘለቀ 22፡ እና አያሌው መሸሻ 20 ዓመታቸው ነበር። የአክስታቸው ልጅ ሺፈራው ገርባውም 17 ዓመቱ ነበር።

በላይም ዘለቀም እንዲህ ሲል ጠየቀ። “ፋሽስት ጣልያን እየገፋ መጣ። ንጉሡም ከማይጨው ሸሽተው አዲሰ አበባ ከገቡ በኋላ፤ የሚወልዷቸውንና የሚወዷቸውን ይዘው፤ የሚችሉትን ያህል የኢትዮጵያን ገንዘብ ዘርፈው፤ ያልቻሉትን ለዘራፊ አጋልጠው፤ ከነቤተሰቦቻቸው ከድተው ባሕር ማዶ ሄዱ ይባላል። ስለዚህ እኛስ ይህንን የመጣ እንግዳችንን እንዴት ነው የምናስተናግደው አስኪ መላ አምጡ።” ብሎ ጠየቀ። በመጨረሻም ከብዙ ምክክር በኋላ የተሰበሰበው ቤተሰብና ዘመድ ዝማድ በሙሉ ጠላትን ለመፋለም ወሰነ።

እነ በላይ በመቀጠልም በየአካባቢው ላሉት ሽፍቶች መልእክት ላኩ። “ሽፍትነትም ወግ የሚኖረው አገር አማን ሲሆን ነው። ሁላችንንም የሚያጠፋ የከፋ የውጭ ጠላት መጥቶብናል። ሁላችንም አንድ ልብ ሆነን ልንመክተው ይገባል። የሚያድኑን ደመኞቻችን ከጠላት የከፉ አይሆኑም። የእኛው ወገኖች ናቸው። ሽማግሌ እየላክን አገር አማን ሲሆን የጉማ ሥርዓት ፈጽመን (ማንኛውም የሚጣልብን ካሳ ክሰን) ለመታረቅ መቁረጥ አለብን። ደመኞቻችንም እኛም (ሽፍቶቹ) አንድ ላይ ካልሆንን ከምድር በጠመንጃና በመድፍ ከሰማይ በሮቢላ የመጣብንን ጠላት መመከት አንችልም። እንግዳችን በተደጋጋሚ አገራችንን የደፈረው ጠላታችን ጣልያን ነው። ሕፃን፡ ሴት፡ ሽማግሌ የማይለይ አረመኔ ነው። ሃሳባችንን የወደዳችሁ ሁሉ የሚቀጥለው እሁድ … እኛ ዘንድ መጥታችሁ እንመካከር” የሚል ደብዳቤ ከእነ አንባቢው ላኩ። (ሚስጢሩን ጠላት እንዳይደርስበት በማሰብ የመሰብሰቢያ ቦታው ስም የሚነገረው በቃል ብቻ ነበ፡፡)

በስብሳው ቀን በተባለው ቦታ የአካባቢው ሽፍታ ሁሉ ልቅም ብሎ መጣ። በላይም ዘለቀም እንዲህ ሲል ተናገረ። “እኛ የጣይቱ ልጆች፡ ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ በሙሉ የአባይን ወንዝ ይዘን፡ የአለቱን ድንጋይ ተንተርሰን፡ አሸዋውን ለብሰን፡ ዋሻውንና ተራራውን ምሽግ አድርገን፡ የመጣውን ጠላት ለመመለስ ወስነናል። ከዚህ ፍንክች አንልም። እናት ሀገራችን ስትደፈር ከማየት ሞታችንን እንመርጣለን። የፈራህ ልቀቀን። ለአገር ለወገንህ ለመሰዋት የምትፈልግ ሁሉ እኛን ተከተለን።” ብሎ በጣይቱ ልጆች፡ ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ስም ቁርጥ ያለ ጥያቄ አቀረበ። ከዚያም ተሰበሰበው ሽፍታ ሁሉ ገባላቸው። ሽፍታው ሁሉ ላይከዳ መሣሪያውን እንዳጎረሰ አጋድሞ ዮሔ ቢሰት ዮሔ አይሳተኝ በማለት እየማለ ቃል ገባላቸው። በወቅቱ እስከ 200 የሚደርስ የሽፍቶች ሠራዊት አሰባሰቡ። በላይ ዘለቀንም የጎበዝ አለቃ አድርገው መረጡት። በኋላም ሌሎች ሽፍቶች ካያለበት እየወጡ ገቡላቸው።

ከበላይ ጋር ሆነው ጣልያንን ለመፋም ቆርጠው የተነሱት ጀግኖች ለጣልያን ካደሩት ባንዶች ጋር ተደጋጋሚ ፍልሚያ አደረጉ። ተደጋጋሚ በለስም ቀናቸው። ባደረጓቸው ጦርነትም ከገደሏቸውና ከማረኳቸው ባንዶች ላይ ብዙ መሣሪያ ገፈፉ። በርካታ ምርኮኞችንም ወደ አርበኛነት ለወጧቸው። ቀስ በቀስም የቦረና፡ የደራ፡ የደብረ ጉራቻ፡ የእንሳሮ፡ ሕዝብ አነ በላይን ተቀላቀለ። አብዛኛው የምሥራቅ ጎጃም ሕዝብም በትግሉ ተቀላቀለ፤ አርበኞችንም አቅፎ ደግፎ ያዘ።

patriot-belay-zeleke

በላይ ዘለቀ በውጊያ ለተማረኩት ባንዳዎች የሚያደርጋቸው ንግግሮች የብዙ ባንዳዎችን አሰላለፍ ለወጠ። ንግግሩም፡- “እናንተ ከጣልያን ታዛችሁ አገራችሁን በመክዳት በተደረገው ጦርነት ከሞት ተርፋችሁ የተማረካችሁ፣ ኢትዮጵያዊ የሆናችሁ ወገኖቻችን ሁሉ፣ አሁን በእኛ በኩል ምረናችኋል። እናት ሀገርህና ወገንህን የምትል ተከተለን፣ ወይም አርሰህ ብላ። ነገር ግን ሁለተኛ ለጠላት ገብተህ ብትገኝ ነገ እኛገኝሃለን።” የሚል ነበር። በዚህ አቀራረብም በየካቲት ወር 1929 ብቻ ደረቤን፡ ቅንቧትን፡ ባሰን፡ ሊበንን፡ ድድሜትን፡ ደጀንን፡ አምበልን፡ በጠቅላላው አስከ ጨሞጋ ያለውን አሣምነው እንዲከተላቸው አድርገዋል። በ1933 ዓ.ም ጦርነቱ ሊያበቃ ሲቃረብ የነበላይ ጦር በ102 ጦር አዛዦች የሚመራ 111, 000 ሠራዊት ነበረው። በሠራዊቱም ውስጥ የማዕረግ ስም የተሰጣቸው አርበኞች 986 ደርሰው ነበር።

በ1930 ዓ.ም የጣልያን ሠራዊት የበላይን ሚስት ሸክሚቱ አለማየሁንና እህቷን ዘውዲቱ አለማየሁን ገድለው ልጁን የሻሽወርቅ በላይን ማርከው ወሰዷት። ለበላይ ዘለቀም ልጁን ማግኘት ከፈለገ ማድረግ ያለበትን የሚያሳውቅ መልእት በጣልያን መንግሥት ስም ላኩለት።

በላይም ለጣልያን መንግሥት መልእክት የሰጠው መልስ እንደሚከተለው ነበር።“ይድረስ ለጣልያን መንግሥት ሰላም ላንተ ይሁን። የላክልኝን እንግዶች እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማን በአክብሮት ተቀብዬ በማስተናገድ ሥፍራ ሥፍራ ሰጥቻቸዋለሁ። ላንተ ግን ትርጁማን (አስተርጓሚ) ብለህ የላከውን እሌላ ቦታ ስትልክ እንዳይቸግርህ መልሼ ልኬልሃለሁ። ልጅህን እመልስልሃለሁ ለምትለው፣ ለአንድ ልጅ ብዬ እናት ሀገሬን ኢትዮያን ከድቼ ከአንተ ጋር አልታረቅም። ከዛሬ ጀምሮ በእኔ በኩል ያለውን ምኞትህን አንሳ። እኔን ፈልገህ ማጥፋት እንጂ አንዲት ልጅ ወስዶ ማስጨነቅና ማጉላለላት ደስ የሚልህ ከሆነ እንደፈለግህ አድርጋት። ሲሆን ለሷም የፈጠራት አምላክ እግዚአብሔር ፍቃዱ ከሆነ ከአንተው እጅ ላመጣት እችል ይሆናል። ጎጃምን በእንደራሴነት ልስጥህ የምትለው አንተ የሰው አገር ሰው ከምትሰጠኝ እኔው ሀገሬን አስተዳድረው የለምዎይ። የቦለቲካ ወሬህን ከምትነዛ የኢትዮጵያ አርበኛ እየቆማመጠ ለአሞራ ከሚሰጥህ፣ በዱር በገደሉ ወድቀህ ከምትቀር በመጣህበት መንገድ አገርህ ግባ!” ይላል።

የሻሽርቅ በላይም በ1930 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣልያ ማርኮ እስከ ሮማ ተወስዳ በደረሰባት እንግልትና ሥቃይ ምክኒያት እግሯ ሽባ ሆነ። ከዚያም ወደ ቢቸና ተመልሳ በጣልያን ካምፕ በከባድ ጥበቃ ስር ሆነች። በግንቦት ወር 1932 ዓ.ም በታሰረች በሁለት ዓመቷ በአባቷ ብርታት ከቢቸና እስር ቤት አመለጠች።

በመስከረም ወር 1933 ዓ.ም ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ከንጉሡ የተላከው ደብዳቤ አመጡ። መልእክቱም፡- “ይድረስ ለልጅ በላይ ዘለቀ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን ሥራህንና ጥንክርናህን ሰምቻለሁ። በጣም የሚያስደስትና የሚያኮራ ሥራ በመሥራትህ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። እኔም በመንገድ ላይ ነኝ። መጣሁ አይዞህ ጠንክር። የእግዚአብሔር ፍቃዱ ከሆና በዋናው ቤተመንግሥቴ ለመግባት የበቃሁ እንደሆነ ውለታህን በእጥፍ አድርጌ እመልሳለሁ። እስከዚያው ሰው ላክና መሣሪያ ከዚህ ከከሰላ አስወስድ። በተረፈ ጠንክር አይዞህ!” የሚል ነበር።
ጣልያን ተሸንፎ በ1933 ዓ.ም ከአገራችንን ሲወጣ የጣይቱ ልጆች በላይ ዘለቀ 29፡ እጅጉ ዘለቀ 27፡ እና አያሌው መሸሻ 25 ዓመታቸው ነበር። የአክስታቸው ልጅ ሺፈራው ገርባው ደግሞ 22 ዓመቱ ነበር።

በላይ ዘለቀ በደማርቆስ ከተማ ከንጉሡ ጋር በተገናኘ ጊዜ የሚከተለውን ተናግሮ ነበር። “በአምስቱ ዓመት የጠላት ወረራ ዘመን ውስጥ ከጣልያን ፋሽሽት ጋር በሰልፉ ያይዋቸውን ወንድሞቼን ይዤ በምዋጋበት ጊዜ እንደሥራ ችሎታቸውና እንደየአገልግሎታቸው የማዕረግ ስም ሰጥቻለሁ። ስለሆነም ሕዝቡን ለማስተባበርና ጦሩን ለማጠናከር፣ የጠላትንም ቅስም ለመስበርና ለማጥቃት ችያለሁ፤” ሲል ተናገረ።
ንጉሡም የበላይን ንግግር ካዳመጡ በኋላ፤ “አንተ የማዕረግ ስም የሰጠኸውን እኔ ከመጨመር በስተቀር አልቀንስም፤ መርቄልሃለሁ። ለእኔ የትናንትናው ሰልፍህና ሁኔታህ ብቻ ይበቃኛል። ደስታዬ ወሰን የለውም። በዋናው ቤተመንግሥቴ እንደገባሁ ያንተን ውለታ እመልሳለሁ፤” ሲሉ ተናገሩ። ቀጥለውም “አዲስ አበባ አብረኽኝ እንሂድ፤ አድርሰኝ፤” ሲሉ ንጉሡ ተናገሩ።

በላይም “እኔ አሁን አብሬዎት አልሄድም። ያለኝም እረፍት አሁን ነው። በጦር ሜዳም፡ በየበረሃው አጥንታቸው ረግፎና ተከስክሶ፣ ደማቸው ፈሶ፣ ሥጋቸው ለአሞራ ሲሳይ በመሆን ለአገራችን ሲሉ የተሰውትን የወንድሞቼን አጽም ከየረገፈበት ሰብስቤ በሥርዓት አስቀብራለሁ። ስለዚህ ከእርስዎ ዘንድ ወደፊት በጥቅምት ወር እመጣለሁ።” ብሎ ተናገረ። ንጉሡም “ጥሩ ሃሳብ ነው። መልካም ነው። እኔም ሃሳብህን እደግፋለሁ፤” ብለው ተናገሩ።

ጥቅምት ወር 1934 ዓ.ም በላይ፡ እጅጉና አያሌው አዲስ አበባ መጡ። ከዚያም የኢያሱን ልጅ ዮሐንስ ኢያሱን ለማንገሥ አድማችኋል በማለት በክቡር ዘበኛ ወታደሮች ተይዘው ታሰሩ። ጉዳዩ ሲጣራ እነበላይ በሤራው እንደሌሉበት ተረጋገጠ። ከጥቅምት እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ ዘጠኝ ወር ሙሉ ከአዲስ አበባ እንዳይወጡ በግዞት ቆዩ። በመጨረሻም ንጉሡ ቀደም ብለው ደብረማርቆስ ከበላይ ዘለቀ ጋር ሲገናኙ ለሠራዊቱ አዛዦች በበላይ ዘለቀ የተሰጣቸውን ማዕረግ መርቄያለሁ ያሉትን ለወጡት (ካዱ)። በአርበኛ መሪዎች የተሰጠው ማዕረግ ሁሉ ተቀነሰ። አስከነአካቴውም አንዳንዶቹ የተሰጣቸው ማዕረግ ሙሉ በሙሉ ተሰረዘ። ለበላይ ዘለቀም የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሰጠው። ንጉሡ ደብረማርቆስ ሲደርሱ የገቡትን ቃል፡ አዲስ አበባ ሲገቡ መቀየራቸው (መካዳቸው) የጣይቱን ልጆች በጣም አስከፋ፤ አስቆጣ።

የጣይቱ ልጆችም አዲስ አበባ የመጡበት ጉዳይ ባለመሳከቱ እያዘኑ አኩርፈው ወደ ቢቸና ተመለሱ። በኋላም ንጉሡ በላይን አዲስ አበባ እንዲመጣ ቢልኩበት አሁን አይመቸኝም አልመጣም ብሎ ቀረ። እነበላይ የመጣው ቢመጣ ወደ ንጉሡ ላለመሄድ ወስኑ። የቅርብ ዘመድና ወዳጅ ያካተተ ሠራዊት አሰባስበው በተጠንቀቅ ሲጠባበቁ ቆዩ። (እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት በጠላት ጊዜ የነበረው ያ ሁሉ ሠራዊት ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው የአርበኞን በ1933 ዓ.ም መበተኑን ነው።

እንደታሰበውም በመጋቢት ወር 1935 ዓ.ም ከንጉሡ የታዘዘ በርካታ ሠራዊት ያለው ጦር እነበላይን ሶማ ደጋ ከተባለው ትልቅ ተራራና አምባ ላይ እንደመሸጉ ከበባቸው። ከንጉሡ ለሠራዊቱ የተሰጠው ትዕዛዝ፡ እነበላይን ከተቻለ ይዘው እንዲያመጡ ካልተቻለ ደግሞ ባሉበት እንዲደመሰሱ ነበር። የነበላይ ሠራዊት አሥር እጥፍ ቁጥር ካለው ከንጉሡ ሠራዊት ጋር ለ15 ቀናት ሌት ከቀን ተዋጋ። እነበላይ ጊዜው በረዘመ መጠን የውሃ ጥም ቢበረታባቸውም የያዙት ቦታ አመቺ በመሆኑ በርትተው ሲከላከሉ ሰነበቱ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከንጉሡ ለበላይ የተላከ ደብዳቤ መጣ። ደብዳቤውም፡ “ይድረስ ለደጃዝማች በላይ ዘለቀ ሰላም ለአንተ ይሁን። በሰደድናቸው ዳኞች በሊጋባ በቀለ፡ በፊታውራሪ ይልማ በሺ፡ እና በአቶ ዳዊት አማካኝነት እንድትመጣ። እኛ በክፉ አናይህም። በክፉ ብናይህ ውድ ልጃንን ልዑል መኮንን ይሁንብን።” የሚል የመሃላ ደብዳቤው ላይ “ሞኣ አንበሳ ዘዕምነ ነገደ ይሁዳ እኛ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ስዩመ እግዚአብሔር” የሚል ማህተም ያለበትን ደብዳቤ ላኩ።

ይሁን እንጂ መተማመን ስለጠፋ ጦርነቱ እንደገና ተቀሰቀሰ። በሁለቱም ወገን ብዙ ሰዎች ሞቱ። እጅጉ ዘለቀ በከባድ ሁኔታ ግራና ቀኝ ታፋውን ተመታ። የጋሜዎች አዛዥ የነበረውም ልጅ ሺፈራው ገርባው ሞተ። በመጨረሻም በላይ የወንድሙን የእጅጉን ሕይዎት ለማትረፍ ሲል እጁን ለመስጠት ወሰነ።
በግንቦት ወር 1935 ዓ.ም አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ 12 ሚኒስትሮች ለሦስት ወር ያህል በዋናው ቤተመንግሥት ሲመረመሩ ቆይተው ውሣኔ ተሰጠ። ውሳኔውም፡- አንደኛ፡ በላይ ዘለቀና እጅጉ ዘለቀ ቢቸና ተወስደው እንዲሰቀሉ። ሁለተኛ፡ አያሌው መሸሻና ሌሎች 15 የጦር አዛዦች በእድሜ ይፍታህ እንዲታሰሩ ተወሰነባቸው። ንጉሡም በሚኒስትሮች የተሰጠውን ውሳኔ አፀደቁት፡፡

በፍርዱ መሠረት በላይና እጅጉ ለመሰቀል ወደ ጎጃም ጠቅላይ ግዛት ሲጓዙ እንዳለ አባይ ሲደርሱ የጎጃምና የቦረና ሕዝብ አንጎራጉሯል ማለትን ስለሰሙ እረብሻ እንዳይፈጠር በማለት የአባይ ውሃ ሞልቶ አላሻግረን ብሎ ከለከለን አሰኙ። ከአባይ መልሰው አምጥተው በወሊሶ ከተማ በደጃዝማች በቀለ ወያ እጅ እንዲታሰሩ ላኳቸው። ቀጥሎም በቤተመንግሥት ግቢ ውስጥ እንዲታሠሩ ተደረገ። በታኅሳስ ወር 1937 ዓ.ም ከእስር ቤት ሰብረው ወደ ጎጃም ሲሄዱ ተያዙ። ከዚያም በላይ ዘለቀ በ33 ዓመቱ፣ እጅጉ ዘለቀ ደግሞ በ31 ዓመቱ ጥር 12 ቀን 1937 ዓ.ም አድስ አበባ ውስጥ ተሰቀሉ።

ስለእነ በላይ መሰቀል በርካታ ግጥሞች ተገጠሙ በዘፈንም ተሰምተዋል፤ ከነዚህም አንዱ እንዲህ የሚል ነበር።
“ተሰቀለ ቢሉኝ ሽጉጡ ነው ብዬ፣
ተሰቀለ ቢሉኝ ጠመንጃ ነው ብዬ፣
ተሰቀለ ቢሉኝ ዝናሩ ነው ብዬ፣
ለካስ በላይ ኖሯል ትልቁ ሰውዬ!”
ሌላው ደግሞ፡-
“አሁን ምን ያደርጋል እኔ ባበጃጅ፣
መማርህ ነበረ ላገር የሚበጅ፤”
እንዲሁም፡
ሰው ማለት፣
ሰው የሚሆን ነው፣
ሰው የሌለ ዕለት።

ወራሪ ጠላትን ለአምስት ዓመታት ያለመታከት ሌት ከቀን ወጥረው መግቢያ መውጫ ያሳጡት ጀግኖች የጣይቱ ልጆች በራሳችን መሪዎች እንደዋዛ በአደባባይ ተሰቀሉ። በዚህም ከጣይቱ ልጆች ጋር ሆነው ጣልያኖችንና ባንዳዎችን አሸንፈው አገራችንን ለድል ያበቁት አርበኞች ሁሉ በሁኔታው በጣም ተሸማቀቁ። አርበኝነትም በይፋ በአደባባይ የሚያስፎክር ጀብዱ መሆኑ ቀረ። እነበላይ ከተሰቀሉ በኋላ በርካታ አርበኞች በተሰጣቸው ማዕረግ እንዳይጠሩ ለቤተሰብና ለዘመድ አዝማድ አሳወቁ። በመሆኑም በቦረና ውስጥ በጣልያን ወረራ ጊዜ በተሰጠ የአርበኝነት ማዕረግ የሚጠራ አልነበረም። ከነበላይ ወዲያ ብሎ ሁሉም እርም ብሎ እርግፍ አድርጎ ተወው።

የጣይቱ ልጆች የትውልድ ሐረግ

በላይ ዘለቀ (የአርበኞች ጠቅላይ አዛዥ) ጥር ወር 1937 ዓ.ም በተወለደ በ33 ዓመቱ ተሰቀለ። እጅጉ ዘለቀ (የአርበኞች ምክትል ጠቅላይ አዛዥና የበረንታ ጦር አዛዥ) ጥር ወር 1937 ዓ.ም በተወለደ በ31 ዓመቱ ተሰቀለ። ሺፈራው ገርባው (የጋሜዎች አዛዥ) መጋቢት ወር 1935 በንጉሡ በታዘዘው ጦር ተገደለ። አያሌው መሸሻ (የመትረየስ ተኳሾች አዛዥ) ከ 1934 ዓ.ም ጀምሮ ለሰላሳ ዓመታት ቦንጋ በእስርና በግዞት ቆይቶ በ1964 ዓ.ም ተለቆ፣ በ1983 ዓ.ም አረፈ።

ጣይቱ አሰኔ … አባቷን አሰኔ ወዳጅን፤ ወንድሟን ለገሠ አሰኔን፣ ባሎቿን ዘለቀ ላቀውንና መሸሻ አደምን፣ ልጆቿን በላይ ዘለቀን ፡ እጅጉ ዘለቀን በሞት ተነጠቀች። ከሞት የተረፈው ሦሰተኛውና የመጨረሻው ልጇም አያሌው መሸሻ በእድሜ ልክ አሥራት ተፈርዶበት ወህኒ ቤት ገባ (1964 ዓ.ም ሲፈታም በሕይዎት አልነበረችም።) ጣይ እስከ ሕይወቷ መጨረሻ ድረስ ሁለት ስሜቶች ሲፈራረቁባት ነበር። በአንድ በኩል በቤተሰቦቿ በደረሰው እልቂት ምክኒያት ቀኑ ሲጨልምባትና ሃዘኑም ሲበረታባት ለጉድ የፈጠረኝ ምነው እኔን ቢያስቀድመኝ ትላለች። በሌላ ቡል ደግሞ የቤተሰቦቿ የአርበኝነት ገድል ልቧን በኩራት ይሞላዋል። ጣይቱ ባለፈችበት ሁሉ ከሕዝብ የሚሰጣት ከበሬታ በልጅቿ አኩሪ ታሪክ ምክኒያት በመሆኑ ፈጣሪን ታመሰግነናለች። ሞት ላይቀር! እንደደኔ ማን የታደለ እናት አለ ትላለች ጣይቱ፤ ወዲያው ደግሞ እንደ ሰው ልጅ ሳይዘሉ፡ ሳይጨፍሩ …. ትልና ለቅሶዋን ታቀልጠዋለች።

ጣይቱ ነፍስ ያወቁ ዘመዶቿን ብታጣም የልጅ ልጆቿን ማሳግን ሥራዬ ብላ ተያያዛው ነበር። የልጅ ልጆቿም የአባቶቻቸውን ታሪክ እንዲያውቁ የተቻላትን ያህል ሞክራለች። ስለ ጦርነቱና ስለ ልጆቿ ገድል በራሷ ብዙም ልትነግራቸው አትችልም ነበር። ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት አብረው ዘምተው የነበሩ ዘመድ አዝማድ ወደ ሠፈሯ ሲመጡ ስለ ልጆቿ የአርበኝነት ገድል ለልጅ ልጆቿ እንዲያወጉላት ታደርግ ነበር። በተጨማሪም እሷ በራሷ ለልጅ ልጆቿ ያስተማረቻቸው ቁም ነገር ነበረ። ይኸውም የልጇን የትውልድ ሐረግ ለልጅ ልጆቿ ማሳወቅ ነበር። በመሆኑም የሚከተለውን የጣይቱን ልጆች የትውልድ ሐረግ መረጃ ያገኘሁት ጣይቱ ካሳደገቻቸው ከየሻሽ-ወርቅ በላይ ዘለቀና ከመንግሥቴ አያሌው መሸሻ ነው። እኔም በራሴ በኩል ከአባቴና ከእናቴ ማረጋገጫ የሚሆነኝ መረጃ አግኝቻለሁ።

በጣይቱ አሰኔ በኩል ያለው የትውልድ ሐረግ (ከበዳሳ አንስቶ እስከ ጣይቱ ልጆች) እነደሚከተለው ነው።
(1) በዳሳ፡ (2) ዋጁ፡ (3) ሜታ፡ (4) ገረሱ፡ (5) አቡ፡ (6) ጃርሶ፡ (7) ቢቂሊ፡ (8) ባቦ፡ (9) ድምቶ፡ (10) ወዳጅ (ወዳይ)፡ (11) አሰኔ (እንሰኔ)፡ (12) ጣይቱ፡ (13) በላይ፡ እጅጉና አያሌው፡፡

በዘለቀ ላቀው በኩል ያለው የትውልድ ሐረግ (ከዋዩ አንስቶ እስከ በላይና እጅጉ) እነደሚከተለው ነው።
(1) ዋዩ፡ (2) ጫንጮ፡ (3) ቂልጡ፡ (4) ገልገል፡ (5) ሃጌ፡ (6) ላቀው፡ (7) ዘለቀ፡ (8) በላይና እጅጉ፡
መሸሻ አደም በኩል ያለው የትውልድ ሐረግ (ከበዳሳ አንስቶ እስከ አያሌው) እነደሚከተለው ነው።
(1) በዳሳ፡ (2) ዋጁ፡ (3) ሜታ፡ (4) ገረሱ፡ (5) አቡ፡ (6) ጃርሶ፡ (7) ቢቂሊ፡ (8) ባቦ፡ (9) ዲዶ፡ (10) ጎበና፡ (11) ቦሩ፡ (12) ይመር፡ (13) አደም፡ (14) መሸሻ፡ (15) አያሌ፡፡
የሺፈራው ገርባውም የትውልድ ሐረግ (በእናቱ በአያህሉሽ ዘለቀ በኩል) እንደሚከተለው ነው።
(1) ዋዩ፡ (2) ጫንጮ፡ (3) ቂልጡ፡ (4) ገልገል፡ (5) ሃጌ፡ (6) ላቀው፡ (7) አያህሉሽ ዘለቀ (የዘለቀ ላቀው እህት፡) (8) ሺፈራው፡ (የሽፈራው የትውልድ ቦታ ወሎ ክፍለ-ሀገር፡ ቦረና አውራጃ፡ ወግዲ ወረዳ፡ መነ-ዲጋ ቀበሌ ነው።)
የራሴ የትውልድ ሐረግና የተወለድኩበት አካበባቢ
አስቲ ከአያቴ ከየሺ ሰምቤ (የአባቴ እናት) ስለራሴ የትውልድ ሀረግ የሰማሁትን ልንገራችሁ። አያቴ ከመቶ ዓመት በላይ ኖራለች። በርካታ ዘመዶቻችን እየመጡ የትውልድ ሐረጋቸውን እንድትነግራቸው ይጠይቋት ነበር። ዋነኛ መነሻቸው የቅርብ ዘመዳሞች እንዳይጋቡ ለመከላከል ነው። አያቴም ጥርት አድርጋ ትቆጥርላቸው ነበር። በዚህም ረክተው ይመለሱ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ዘመዶቼ ከገጠር አዲስ አበባ ሲመጡም ለልጆቼ የሚነግሩት የትውልድ ሐረጋችንን ነበር። እንግዲህ ወደራሴው ልመልሳች፡፡
እኔ ራሴ (አድማሱ ገበየሁ) ከጣይቱ አሰኔ ጋር በ10ኛው ወዳጅ በሚባለው እገናኛለሁ፤ ከአንደኛው ማለትም ከበዳሳ ጀምሮ 14ኛ ትውልድ ላይ ነኝ፡፡እንዲሁም ከአያሌው መሸሻ ጋር በ13ኛው አደም በሚባለው እገናኛለሁ፤ ከአንደኛው ማለትም ከበዳሳ ጀምሮ 17ኛ ትውልድ ላይ ነኝ፡፡ በሌሎችም በተቀሩት በሁለቱ አያቶቼ በኩል ትውልድ ሐረጌ (1) በዳሳ፡ (2) ዋጁ፡ (3) ሜታ፡ ከሚባሉት ጋር ይገናኛል።
ይህ የትውልድ ሀረግ የሚያሳየው እኔ (አድማሱ ገበየሁ) በማንኛውም አቅጣጫ (በአራቱም አያቶቹ በኩል) ኦሮሞ መሆኔን ነው።
ዘመዶቼ የሚኖሩበትና እኔም በልጅነቴ ያደግሁበትና የተማርሁበት አካባቢ የሚገኘው በደቡብ ምዕራብ ወሎ ነው።

(1) የተወለድኩት ቦረና ወረዳ ውስጥ ዲቢ የሚባል አካባቢ ነው። መንደራችን መነ ገጃ (ፊንጫ) እየተባለ የሚጠራ ሲሆን፡ በርካታ ዘመዶቻችን የሚኖሩባቸው ጎረቤቶቻችን ደግሞ መነ-ከተሜ፡ መነ-ደርሶ፡ መነ-ቱፋ፡ መነ-ደግሉ ይባላሉ።እስከ 8ኛ ክፍል የተማርኩት መካነሰላም ከተማ የሚገኘው ቦረና ትምህርት ቤት ነው።
(2) ቦረና ወረዳ ውስጥ በርካታ የገጠር አካባቢዎች አውቃለሁ፤ ተዘዋውሬም ጎብኝቻለሁ። እነሱም፡- ሜታ (ጅሩ መነቡኮ፡ ወቦ፡ መነዶዩ፡ ወርቄ አቦ፡ ተዋ፡ ወርቄ አቡ፡ በታ፡ መነደጋ፡ አይቻል ቦነያ፡ መስካቤ፡) ወግሎ፡ (ዶክስ፡ መስካቤ፡ ቢሊ፡ ሴፋጢራ፡ አቡ አደሬ፡ ዲቢ ጪሪ፡ ዶንቆሮጫካ፡) ደምቢ፡ (ሰምቦ፡ ሶዬ፡ ደራሜ፡ ወርቄ መስቀሌ፡) አያና፡ ይባላሉ።

(3) በወግዲ ወረዳ (ሌንጮ፡ ለሚ፡ ጫቀታ፡ ጎረንጅ፡) አልፎ አልፎም ቢሆን ዘመዶች አሉኝ። በመሐል ሳይንት (ከደንቆሮ ጫካ እስከ ድንሳ፡) እና በለገሂዳ ወረዳ (አስከ ወለቃ ወንዝ፡) ጥቂት ዘመዶች አሉኝ።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ በእነብሴ ሳር ምድር፡እናርጅ እናውጋ፡ እና ሸበል በረንታ ወረዳዎች (በአባይ ወንዝ ዳርቻዎች አከካባቢ) አልፎ አልፎም ቢሆን ዘመዶች አሉኝ።

ከላይ በጠቀስኳቸው አካባቢዎች የሚኖሩት ዘመዶቼ ሁሉ የትውልድ ሀረጋቸው የሚቋጠረው ሜታ በሚባለው ግንድ ነው። እስከ አያቶቼ ትውልድ ድረስ ያሉት መስማትና መናገር የሚችሉት ኦሮምኛ ቋንቋን ነበር። የአባቴ ትውልድ ትንሽ ትንሽ ኦሮምኛ መስማትና መናገር ይችል ነበር። ከእኔ ትውልድ ጀምሮ ኦሮምኛ መስማትና መናገር የሚችል ማግኜት በጣም አስቸጋሪ ነው። የእኔ ትውልድ (ሁላችንም ማለት ይቻላል) መስማትና መናገር የምንችለው አማርኛ ብቻ ነው።

ለአሁኑ ይህን ያህል ካልሁ፣ ወደፊት ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለኝን አስተያየትና አቋም ይዤ እቀርባለሁ።