Tag Archives: Ethiopia

አቶ ኃይለማርያም በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ ምክንያት መንግሥታቸው እና ፓርቲያቸው መሆኑን ቢገልፁም፤ ህዝባዊ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው

ባለፈው ህዳር አጋማሽ 2008 ዓ.ም. በድጋሚ የጀመረው የኦሮሚያ ህዝባዊ ተቃውሞ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እና ወረዳዎች ቀጥሏል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በተቃውሞው ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለው የኃይል እርምጃም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በዚህም የሟቾች ቁጥር መጨመሩ ታውቋል፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተቃውሞን ለማፈን እና ለማርገብ እየተወሰደ ባለው የኃይል እርምጃ ከሚገደሉት በተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸውና የታሰሩ ሰዎች ቁጥርም ጨምሯል፡፡ ተቃውሞን እና የርሃቡን ሁኔታ ለመዘገብ ባለፈው የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም.ወደ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ለዘገባ ተንቀሳቅሰው የነበሩት የብሉምበርግ ዘጋቢ ዊሊያም ዳቪሰን እና ለተለያየ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ወኪል ሆና የምትሰራው ጄሲ ፎርትንና አስተርጓሚያቸው በኢትዮጵያ የፀጥታ ሃይሎች ያለምንም ማብራሪያ ከአዋሽ ከተማ ወደ አዲስ አበባ በፌዴራል ፖሊስ ታጅበው እንዲመለሱ ከተደረገ በኋላ አዳር ታስረው መለቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ ጋዜጠኞቹም ለአንድ ቀን ከታሰሩ በኋላ መለቀቃቸውንም ጋዜጠኞቹ በማኀበራዊ ገፆቻቸው ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡

Halemariam Desalegn

ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት መጋቢት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. የመንግሥታቸውን የ6 ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፤ በኦሮሚያውም ሆነ በአማራ ክልል ጎንደር እና በሌሎች አካባቢዎች የተፈጠረው ችግር በመንግሥታቸው አስተዳደር ውስጥ ባለ የመልካም አስተዳደር አለመኖር፣ ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግር መሆኑን እና በሌላ አካል ላይ ጣት መቀሰር እንደማይፈልጉ በመጥቀስ ለዚህም መንግሥትና እና ፓርቲያቸው ኢህአዴግ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስተር አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ከህዝባዊ ተቃውሞው ጀርባ ኦነግ፣ አርበኞች ግንቦት 7 ፣ የኤርትራ መንግሥት እና በሀገር ቤት በይፋ የሚንቀሳቀሰውን ኦፌኮ/መድረክን ተጠያቂ ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም፤ በፓርላማው የሪፖርት ውሎ ግን የተለየ ምክንያት ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል ከሆነ የህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ማንም ላይ ማላከክ አይቻልም፣ ኦሮሚያ ስለተነሳ ሌላ ቦታ ችግር የለም ማለት አይደለም፣ ይሄ ሁሉ ባለው ብልሹ አሰራር የተፈጠረ ችግር ነው፣ ለዚህም መንግሥት ኃላፊነቱን በመውሰድ ህዝቡን ይቅርታ ይጠቃል ብለዋል፡፡ ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልል በተለይ የቅማንት ማኀበረሰብ የማንነት ጥያቄ ጋ ተያይዞ ለተፈጠረው ችግር መንግሥታቸውና ፓርቲያቸው ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ቢገልፁም ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ መንግሥት የወሰደውን እና እየወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃ ሲቃወሙ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች፣ ጋዜጠኞች እና ተማሪዎችን ጨምሮ ከ4 ሺህ በላይ ስለታሰሩት፣ ከ270 በላይ ስለተገደሉትና በርካቶች ስለቆሰሉ ዜጎች ጉዳይ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

በተለይ በኦሮሚያ ክልሉን ያስተዳድራል የሚባለውና የኢህአዴግ አባል ድርጅት የሆነው ኦህዴድ መዕከላዊ ኮሚቴ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በቅርቡ በአዳማ/ናዝሬት ባደረገው ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ አቶ ዳባ ደበሌ እና አቶ ዘለዓለም ጀማነህ የተባሉ የክልሉና የፌደራል ከፍተኛ ኃላፊዎችን ከነበሩበት የክልሉም ሆነ የፌደራል ስልጣን ማንሳቱን ይፋ ቢያደርግም ህዝባዊ ተቋውሞው ግን ይህ እስከተጠናቀረበት ድረስ ቀጥሏል፡፡
ህዝባዊ ተቃውሞ መቀጠሉን ተከትሎ መንግሥት በቅርቡ የካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም ሌሊት በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዬ ወረዳ ጎሮሶሌ ከተማ ውስጥ ሞቱማ ፈዬራ የተባለ የ20 ዓመት ወጣትና የ10ኛ ክፍል ተማሪን ጨምሮ የተለያዩ ዜጎች መገደላቸው ተጠቁሟል፡፡

ለአራት ወራት የዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በፀጥታ ኃይሉ የሚወሰደው የኃይል እርምጃዎች እንዳሳሰበቸው የገለፁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባለፈው የካቲት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. “እኛ ሽብርተኞች አይደለንም ፤ የኦሮሞ ሕዝብን መግደል አቁሙ” የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 6 ኪሎ ዋናው ግቢ አካባቢ ተነስተው ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ሲያቀኑ የነበሩ ተማሪዎች በፖሊስ ድብደባ ሰልፉ እንደተበተነ እና በርካታ ተማሪዎችም ታፍሰው መታሰራቸው ተጠቁሟል፡፡ ተማሪዎችም ሰላማዊ መሆናችንን ለመግለፅ ነጭ ጨርቅ እያውለበለብን ነበር ያሉ ሲሆን መንግሥት ለምን ሰልፉን እንደበተነ እና ተማሪዎችን እንዳሰራቸው እስካሁን የገለፀው ነገር የለም፡፡

የበዕውቀቱ ስዩም ወጎች

ከተስፋዬ ገብረአብ

Tesfaye Gebreab

በዕውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር” በሚል ርእስ ያሳተመውን መፅሃፍ አነበብኩት። እንደተለመደው ጥሩ ተራኪ ነው። በዚህ ባዲሱ መፅሃፉ በዕውቀቱ ስለማንነቱ ያሰፈረው አዲስ መረጃ ግን ቀደምት ስራዎቹን ወደ ሁዋላ ተመልሼ እንዳገላብጥ አስገድዶኛል። በዕውቀቱ ባለተሰጥኦ ነው። ተፈጥሮ ብእረኛነትን ያለስስት ያስታቀፈችው ድንቅ የዘመናችን ገጣሚ ነው። በተለይ በአጫጭር ስነግጥሞቹ የሚያነሳቸው ጭብጦች አስደማሚ ስለመሆናቸው ብዙ ተነግሮለታል። ለአብነት ሙስናን በአምስት መስመሮች ብቻ የገለፀበት መንገድ የቅኔ ችሎታውን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፣
እልፍ ከሲታዎች – ቀጥነው የሞገጉ
“ስጋችን የት ሄደ?” – ብለው ሲፈልጉ
በየሸንተረሩ – በየጥጋጥጉ
አስሰው አስሰው – በምድር በሰማይ
አገኙት ቦርጭ ሆኖ – በአንድ ሰው ገላ ላይ
የእነዚህ ስንኞች ገጣሚ እኔ ብሆን ኖሮ ፑሽኪንን እንቀው ነበር። በዕውቀቱ በእነዚህ ስንኞች ከህዝብ የዘረፉትን በቢሊዮን የሚገመት ዶላር ባንክ ውስጥ ስለደበቁ ባለስልጣኖች በቀላል መንገድ ነበር የነገረን። በዕውቀቱ ድፍረቱ የበረታ ነው። ገጣሚነቱ ቃላት አሳክቶ ቤት መምታቱ አይደለም። ነባር አስተሳሰቦችን የመሞገትና በተለየ መንገድ የማየት ልዩ ችሎታ አለው። በተለይም በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደርጋል። ኢአማኒ መሆኑ ሃይል ሆኖ ሳያግዘው አልቀረም። “ከአሜን ባሻገር” ላይ እንደነገረን ለፈጣሪ ከመስገድ የተላቀቀው ሲግመንድ ፍሮይድን ካነበበ በሁዋላ ነው። ሆኖም የአክራሪ ህብረተሰብ ባልደረባ መሆኑን በመዘንጋቱ ዋጋ ከፍሎበታል። የመፅሃፍ ቅዱስን ትረካዎች እያነሳ ከሚተርብባቸው ግጥሞቹ መካከል “ዳዊትና ጎልያድ” ይጠቀሳል።
እግዜርና ዳዊት – አብረው ተቧደኑ
ብቻውን ታጠቀ – ጎልያድ ምስኪኑ
አንዳንዱ ተገዶ – ለሽንፈት ሲፈጠር
በጥቅሻ ይወድቃል – እንኳንስ በጠጠር
ተቀባይነት አጊኝተው የቆዩ እምነቶችን ገልብጦ በማሳየት ረገድ በዕውቀቱ የተሳካለት ገጣሚ ነው። “ትንሹ ዳዊት ግዙፉን ጎልያድ አሸነፈው” ብለን እናምን ነበር። ከዳዊት ጀርባ ተሸሽጎ ጎልያድን የገነደሰውን አምላክ በፍልሚያው ውስጥ በማስገባት ነባር እምነታችን ላይ ጥያቄ ምልክት እንድናስቀምጥ ያደርገናል። ቀላል አቅም አይደለም። ሌሎች ብእረኞችም በእየሱስ ታሪክ ላይ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ያነሳሉ። ካህሊል ጊብራን ለይሁዳ ወገናዊ ሆኖ ፅፏል። እየሱስ ወደ ምድር ሲመጣ በምናውቀው መንገድ እንዲሞት ተወስኖ ከነበረ፣ ይሁዳ አሳልፎ እንዲሰጠው ተወስኖ ከነበረ ለምንድነው ይሁዳን አንደከሃዲ የምንቆጥረው? በዕውቀቱ እንዲህ ያሉ ተገላቢጦሽ እውነቶችን በኮሚክ አቀራረብ በመተረክ ረገድ የተሳካለት ገጣሚ ነው። ለአብነት ዲዮጋንን የተቸባቸው ስንኞች አስደማሚ ናቸው።
ውሻው ዲዮጋንን – እዩት ተጃጅሎ
በከንቱ ይጮሃል – “ሰው የት አለ?” ብሎ
ሰው ሰራሹን ፀሃይ – በጣቱ አንጠልጥሎ
በዕውቀቱ “ከአሜን ባሻገር” የሚል መፅሃፍ ፅፎ እስኪያሳትም ድረስ የጎጃም አማራ ይመስለኝ ነበር። “ስምና ማንነት” የምትለውን ምእራፍ ሳነብ ግን በዕውቀቱ መሰረቱ ኦሮሞ መሆኑን አወቅሁ። በመግቢያዬ እንደገለፅኩት የዚህን ወጣት ገጣሚ ስራዎች መለስ ብዬ ለማየት የተገደድኩት ከዚሁ ማንነቱ ጋር በተያያዘ ግጥሞቹን ለመመርመር ነበር። በርግጥም ከዚህ ቀደም ትርጉም አጥቼላቸው ለነበሩ ከጥቂት በላይ ስንኞቹ አሁን ምክንያት አገኘሁላቸው። ወደ ግጥሞቹ ከመግባቴ በፊት ግን በዕውቀቱ ስለማንነቱ የገለፀውን ባጭሩ ልጠቃቅስ።

አያቱ አቶ በዳዳ ይባላሉ። ጅባት እና መጫ (አምቦ) ተወልደው ጋርዱላ የተባለ አካባቢ ኖረዋል። አያቱ ጥቂት ልጆች ወልደው ሲሞቱ አባቱንና ወንድሞቹን የማሳደግ እጣ እናቱ ቀደም ሲል ከሌላ ከወለዱት ወንድማቸው እጅ ላይ ወደቀ። የአያቱ ስም የተቀየረው በዚህ ጊዜ ነበር። በዕውቀቱ ይህን ሁኔታ ሲገልፅ፣
“አባቴ በመጀመሪያ አባቱን አጣ። ቀጥሎ የአባቱን ስም አጣ።” ሲል አስፍሮአል።
በዕውቀቱ ስለ ዘር ጉዳይ አንስቶ በመፅሃፉ ከማካተቱ በፊት ከራሱ ጋር ጥቂት ሳይሟገት አልቀረም። አጎቱ አቶ አማረ፣ “ስለዘርና ስለሃይማኖት በመፃፍና በመከራከር ጊዜህን አታጥፋ” ብሎ ቢመክረውም ምክሩን ባለመቀበል ይህንን ምእራፍ ለመፃፍ እንደበቃ አስፍሮአል።

አባቱ አቶ ስዩም “በዳዳ” የሚለውን የአባታቸውን ስም ለመቀየር ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ለበዕውቀቱ ነግረውታል። የአሳዳጊ ግማሽ ወንድማቸውን ፍላጎት መጋፋት ግን አልቻሉም። በርግጥ “በዳዳ” የሚለው ቃል በኦሮምኛ ትርጉሙ፣ “የበለፀገ ወይም ሃብታም” ማለት ነው። ይህ ቃል ግን በአጋጣሚ በአማርኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ብልግና ተብለው ከተመዘገቡ ቃላት ጋር ይቀራረባል። ስለዚህ ይህንን ስም ይዞ አማሮች ወደ በዙበት ትምህርት ቤት መሄድ የሚያደርሰውን ጉዳት የአቶ ስዩም አሳዳጊ ተገንዝበውት ሊሆን ይችላል። በዕውቀቱ ግን በዚህ አይስማማም። ጉዳዩን ቀለል አድርጎ “ህያውነት ነው” ይለዋል። በዕውቀቱ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ መጠራት እንደሚፈልግ ከፅሁፎቹ ተረድቻለሁ። ለነገሩ በመፅሃፉ የአያቱን ጉዳይ ማንሳቱ በአስረጅነት እንጂ ስለዘር ጉዳይ ለመነጋገር አይደለም።

በዕውቀቱ የአያቱ ስም “ከበዳዳ ወደ መሰለ” የተለወጠበትን ምክንያት ለማወቅ ጥቂት ጉዞዎችን አድርጎአል። “በዳዳ የሚለው ስም ከአባቴ አባትነት ለምን እንዲቀየር ተፈለገ? በዘመኑ የፖለቲካ ጫና ወይስ በህያውነት” ሲል ቢጠይቅም ለዚህ ጥያቄ ግን ምላሽ አያገኝም። አዲሳባ ኗሪ የሆነ አማረ የተባለ አጎቱ ስቆ ብቻ ዝም አለው። የአጎቱ ስቆ ዝምታ በዘር ፖለቲካ ላይ ለመነጋገር ባለመፈለግ ይመስላል። አጎቱ፣ “ሰዎች በውይይት የሚግባቡበበት ዘመን እስኪመጣ አርፈህ ግጥምህን ፃፍ” ሲል ይመክረዋል።

በዕውቀቱ ግን የአጎቱን ምክር አልሰማም። በዳዳ የሚለው የአያቱ ስም ለምን እንደተቀየረ ለማወቅ ፍለጋውን ቀጠለ። ስም ቀያሪ ትልቅ አጎቱን ለመጠየቅ እስከ አለታ ወንዶ ቢጓዝም ምክንያቱን አልነገሩትም። በመቀጠል አባቱን ለመጠየቅ መንኩሳ ሄደ። አባቱ ግን ሸፋፈኑበት። ዝምታን መረጡ። በዕውቀቱ አልተዋቸውም። በዳዳን ትቶ መሰለ የሚለውን ስም ይዞ አባይን መሻገሩ ለተቀባይነቱ ጠቅሞት እንደሆን በቀጥታ አባቱን ጠየቀ። አባቱ መልስ ከመስጠታቸው በፊት ውጥረቱን ለማርገብ አክስቱ ጣልቃ ገብታ ተቆጣች። ኦሮሞ በጎጃም የተከበረ መኳንንት መሆኑን ተናግራ ጉዳዩን ቋጨችው። በመግቢያዬ እንደገለፅኩት የበዕውቀቱ ሽሽግ ማንነት በቀደምት ስነግጥሞቹ ውስጥ ተንፀባርቀው እንደሆን ለማየት መለስ ብዬ ስራዎቹን ፈታትሼ ነበር። ከምስጢራዊ ስንኞቹ መካከል ጥቂት አገኘሁ፣
በነፍሴ ሰማይ ላይ
ቢሰርቅ ጣምራ ፀሃይ
አንዱን ጋርጃለሁ
ሌላው ደምቆ እንዲታይ
“ምን ማለቱ ነው?” ብዬ ሳስብ “የአቶ በዳዳን ኦሮሞነት ሸሽጎ አያቱ ባልሆነ ስም እየተጠራ መቀጠሉን እየተቃወመ ይመስላል” አልኩ። “አንዱን ጋርጃለሁ – ሌላው ደምቆ እንዲታይ” የሚለው ኦሮሞነቴን ደብቄ ሌላ መስዬ እየታየሁ ነው የሚል ትርጉም የያዘ መሰለኝ። እንግዲህ እኔ እንደገባኝ ነው። በእውቀቱ ቢጠየቅ ግጥሞቹን የቋጠረበትን ሌላ ምክንያት ሊሰጥ ይችላል። ስለዚህ የኔን አስተያየት ስታነቡ የአንባቢ መብቴን ተጠቅሜ እንጂ የበዕውቀቱ ልብና አንጎል ውስጥ ገብቼ ያሰበውን ለማወቅ እንደማልችል ከወዲሁ ላሰምርበት እፈልጋለሁ። በዕውቀቱ በዚህ አላበቃም፣
ቀንድ አውጣ ሆይ!
ውብ ዛጎልህ አማለለኝ
ከጎጆህ ላስወጣህ ነው (ይቅር በለኝ)
‘በዝግ አለም – ሰማይ ጣራ ነው’ ይባላል
ያለውበት ነውንጂ – ያለቤት መኖር ይቻላል
እነዚህ ስንኞች ለኔ የሰጡኝ ትርጉም፣ በዕውቀቱ አቶ በዳዳን ከተሸሸጉበት ዛጎል ጎትቶ ለማውጣት መወሰኑን ነበር። በርግጥም እንደፎከረው ፈፅሞታል። ያለ ውበት መኖር እንደሚቻል ለማሳየት ሞክሮአል። አያቱ በዳዳ መሆናቸውን ሲገልፅ በከበበው ማህበረሰብ አመለካከት ውበቱ እንደሚቀንስ የግድ ያውቃል። ከዚህ በሁዋላ ሌሎች ወገኖች በዕውቀቱ ባለበት ስለ ኦሮሞ ለማንሳት ቃላት መምረጥ ሊኖርባቸው ነው። በዕውቀቱ አያቱን ከተሸሸጉበት አውጥቶ ለነፃነት ከማብቃቱ በፊት በዚሁ ቁጭት የፃፋቸው የሚመስሉ ስንኞችን ማስተዋል ችዬ ነበር። ለአብነት በአንድ ግጥሙ ኦሮሞ – አማራንና ትግሬን በገፀባህርይነት ያመጣና እንዲህ ሲል ያላግጣል፣
በታሪክ ሜዳ ላይ
አሉላ ጎበና
ወንዱን አስከትለው – ሲገድሉ ሲሞቱ
አባ ገብረሃና
እርስዎ ባይኖሩ – ምን ይውጠው ሴቱ?
ጨመረልኹ መሰል – ባባ ነፍሶ ፈንታ
እንደ አንደበትዎ – እንትንዎ መንታ
አንዱ ለቀን ሲሆን – አንደኛው ለማታ
“ባባ ነፍሶ ፈንታ” ማለቱ ባልቻ አባነፍሶ ስልብ ነበሩ ስለሚባል ሲሆን፤ “እንትንዎ መንታ” ማለቱ ደግሞ አለቃ ገብረሃናን እንደ ምላስዎ መሾል (የቀጣፊነት ችሎታ) ሁለት ብልት ይዘዋል ማለቱ ነው። ሌሎች ጦር ሜዳ ሲሞቱ እርስዎ ውሎና አዳርዎ ከሴት ጋር መዳራት ነው ማለቱ ነው። በዕውቀቱ እንዲህ በመረረ ሁኔታ ሊሳለቅ የቻለው ምን ተሰምቶት እንደሆን ባውቅ በጣም ደስ ባለኝ ነበር። በተለይ ገዢዎች ላይ ቅሬታና ቂም እየያዘ እንደመጣ የሚጠቁሙ ከጥቂት በላይ ስንኞቹን ታዝቤያለሁ። አንዷ እንዲህ ትላለች፣
አልወጣም ተራራ – ደመናውን ላብስ
ቀስተደመናውን – ሽቅብ ልቀለብስ
አልዋስም እኔ – ካቡነ ተክሌ ክንፍ -ከያ’ቆብ መሰላል
እኔ መውጣት ሳስብ – ሰማዩ ዝቅ ይላል
ዝቅ ይላል ያለው ሰማይ ስልጣን ነው። የትኛው ስልጣን እንደሆነ ግን አልገባኝም። የወያኔን ማለቱ ይሆን? ወይስ የወደቀውን የፊውዳል ስርአት አመለካከት? በእውነቱ አልገባኝም። ቁልቁል ይቀለበሳል ያለው ቀስተደመና ግን የኢትዮጵያ ባንዴራ ነው። የአቡነ ተክሌ ክንፍና የያእቆብ መሰላል ያላቸው ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ሊሆን ይችላል። በዕውቀቱ ከሁሉም ለይቶ ተክልዬ ላይ መቀለድ ይወዳል። ምክንያቱን አላውቅም። በዚህ ግጥሙ ግን በባንዴራው፣ በቤተክርስትያን እና ከፍ ባለው የአመለካከት ስልጣን ላይ ርግማኑን ያወረደ ይመስላል። ርግጥ ነው፤ ስነግጥሞች ብዙውን ጊዜ ለትርጉም ክፍት ስለሆኑ አንባቢ በራሱ መንገድ የመረዳት መብት አለው።

የበዕውቀቱ ቀደምት ግጥሞች “ከአሜን ባሻገር” ላይ ከተጠቀሱት አቶ በዳዳ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማየት ሞክሬያለሁ። በዕውቀቱ የመፅሃፉን ርእስ ለምን “ከአሜን ባሻገር” ሲል እንደሰየመው ምስጢር አልነበረም። በቀጥታ ከአያቱ ከአቶ በዳዳ ጋር ይያያዛል። እሱም በዚያው ምእራፍ ላይ እንዲህ ሲል ገልፆ ነበር፣
“የተለያዩ ባህሎችን በአንድ በገና ውስጥ እንደተወጠሩ አውታሮች ማስተናገድ በማይታወቅበት ጥንታዊ ማህበረሰብ ውስጥ ግለሰቦች የገናና ባህሎችን ምልክት አሜን ብለው ከመቀበል ያለፈ ምርጫ አልነበራቸውም።”
እና “ሉአላዊነት” የሚል ግጥሙ ብሶት ያዘለ ነበር፣
የጋራችን አለም – የጋራችን ሰማይ
የብቻችን ህመም – የብቻችን ስቃይ
ደመናው እንዴት ይታይ
ሸፍኖት ሰንደቅ አላማው
ሸፍኖት ብሄራዊ መዝሙሩ
ብሄራዊ ልቅሶውን ማን ይስማው?
ከእናቴ፣ ከአባቴ፣ ከወንድም ከእህቴ
ከወዳጅ ጠላቴ
የእንባ ጡብ ሰብስቤ
ሽቅብ ደራርቤ
የሰራሁት ህንፃ – መቸም አልፈረሰ
ሚፈርስም አይመስለኝ – ምፅአት ካልደረሰ

“ከአሜን ባሻገር”ን ሳነብ ገጣሚው ውስጡ የሚቃጠል ባህር ሆኖ ተሰማኝ። ባህሩ የእንባ ጥርቅም መሆኑን ራሱ ነው የነገረን። ምን ቢሆን ነው በዕውቀቱ ልቡ ውስጥ የእንባ ኩሬ ያጠራቀመው? ምንድነው ከውስጡ የሚጮኸው? ምንድነው በቀጥታ መናገር ያልቻለው? በአንድ ሰማይ – በአንድ አገር ስር ዜጎች አብረው እየኖሩ፤ ላንደኛው ወገን ስቃይ እንደሆነበት ሲነግረን አልገባ ብሎን ይሆን? የኦሮሞ ህዝብ ላይ ሚዛን ያጣ ወቀሳ ከሚያዥጎደጉዱ ሰዎች መሃል ተቀምጦ የውሸት ሳቅ መሳቅ ሰልችቶት ይሆን ማንነቱን ይፋ ለማድረግ የተገደደው? የትልቅ አጎቱና የአባቱ ዝምታ አስጨንቆት ይሆን የሚከተለውን ግጥም የፃፈው?
አዳኝ በንስሃ – ሰይፉ አልዶለዶመም
ታዳኝ በፀሎቱ – ካራጆች አልዳነም
ተኳሹ ቢዋልል – አልመታ ቢል ተኩሱ
ካፈሙዝ ይጠጋል – ኢላማው እራሱ
“ከአሜን ባሻገር” ላይ በዕውቀቱ ልጅነቱን በተመለከተ ጥቂት ያነሳል።
“…ከተወለድኩበት ቤት ግርጌ የሚንቆረቆረው፤ ቀይ አቧራዬን ከእግሬ ላይ ያስለቀቅሁበትን ደቦሆላ የተባለው ወንዝ የአማርኛም ሆነ የግእዝ ትርጉም እንዳለው ለማረጋገጥ ሞክሬ አልተሳካልኝም። ለካ ደቦሆላ በኦሮምኛ Daboolaa (የተከደነ) ማለት ኖሮአል?…” ሲል አስፍሮአል።

የበዕውቀቱ የትውልድ መንደር መንኩሳ ትባላለች። መንኩሳ ራሱ ቃሉ ኦሮምኛ መሆኑን አልደረሰበትም መሰለኝ አላነሳውም። “መና” ማለት “ቤት” ማለት ነው። “ኩሳ” ደግሞ “ማከማቻ” ነው። “ማከማቻ ቤት” ወይም “መጋዘን” እንደ ማለት ነው።

በዕውቀቱ በመፅሃፉ አንዳንድ ታሪካዊ ሁኔታዎችን እያነሳ ለመሞገት ሞክሮአል። አብዛኛው ጥናታዊ እና የታሪክ ትንተና ጉዳይ ነው። ፕሮፌሰር መሃመድ ሃሰን እና ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ ስለ ኦሮሞ የሰሩትን የተከበሩ ስራዎች እያጥላላ፣ ‘ይሄ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ እገሌ የተባለው ፈረንጅ በመፅሃፉ ይጠቅሰው ነበር’ ብሎ ሊሞግት ይሞክራል። ይህን መሰል ሙግት መቸም ፈረንጅ የፃፈውን የበለጠ የሚታመን ማመሳከሪያ የማድረግ የአበሻ ፀሃፊያን ልማድ ሆኖአል። የባለታሪኩ ማስታወሻ በእጅ እያለ አንድ ፈረንጅ ከአስጎብኚው የሰማውን የበለጠ ማመን ያስተክዛል።

በዕውቀቱ አጤ ምኒልክ የፈፀሙትን በጎም ሆነ ክፉ ተግባር ከጊዜው ጋር እንዲታይ፣ እርሳቸው የፈፀሙትን ሌሎችም የወቅቱ ነገስታትና መሪዎች እንደፈፀሙት ለማሳየት መሞከሩ በርግጥ ለአብሮ መኖር የሚበጅ በመሆኑ ተገቢ ነው። ‘የአኖሌ የጡት ቆረጣ ታሪክ እውነት አይደለም’ ሲል ማስተባበሉ ግን መረጃ የለውም። እንደተለመደው ‘ጡት ተቆርጦ ቢሆን ኖሮ እገሌ ይፅፈው ነበር።’ አይነት ክርክር ነው። የፕሮፌሰር መሃመድ አባስን መፅሃፍ እንኳ ያነበበ አይመስለኝም። “የቡርቃ ዝምታ” ታሪክ ቀመስ ልቦለድ እንደመሆኑ ገፀባህርያት የሚናገሩትን እንደ ደራሲው አቋም መውሰድ ልክ አለመሆኑን በዕውቀቱ አያጣውም። መቸም ችግር ነው፤ የከበበውን ስሜታዊ ማህበረሰብ ለማስደሰት ያደረገው ይሆናል።

“የጁገል ልባዊ ወግ” በሚል ርእስ የፃፍኩትን ትረካም በዕውቀቱ ይጠራጠረዋል። ለማረጋገጥ ግን ቀላል ነው። ጁገል ሄጄ ያነጋገርኳቸው እናት አመቱላ ሻሽ አቦኝ ሞተው ከሆነ ዘመዶቻቸው ይኖራሉ። የሃረሪ አዛውንቶች ታሪካቸውን ሲናገሩ ከአንድ ምንጭ እንደሚቀዳ ውሃ ይዘቱ አንድ ነው። የሃረሪ የታሪክ አባት ብዬ የጠቀስኩት አብዱሰመድ እድሪስ ተራ ሰው አይደለም። በዕውቀቱ ሊያናንቀው ሞክሯል። ስለማያውቀው ነውና አልፈርድበትም።

ይልቁን በእውቀቱ ስለ ጎጃም ነባር ጌቶች የተረከው ተነባቢ ነው። የጎጃም መስራች አባት ኢቢዶ የሚባል የቦረና ኦሮሞዎች መሆናቸውን የተሻለ ምንጭ አጣቅሶ ተንትኖአል። ኢቢዶ ከወለጋ ከብት እየነዳ ወደ ጎጃም ከገባ በሁዋላ ለጎጃም ስርወ መንግስት መሰረት መጣሉን ያብራራል። በዕውቀቱ በትረካው ደጃዝማች ጎሹ ኦሮሞ መሆናቸውን ጠቅሶ ሲያበቃ፤ የጎሹ ልጆች ኤሌምቱ፣ ዶሪ፣ ተሰማ ይባሉ እንደነበር ይገልፃል። ሁዋላ ንጉስ ተክለሃይማኖት የተባሉት እንግዲህ የተሰማ ጎሹ ልጅ ‘አዳል ተሰማ’ ናቸው። ኦሮሞ በጎጃም “መኳንንት” የመሆኑ ጉዳይ በሰነዶች የተረጋገጠ መሆኑን አብራርቶአል። በእውቀቱ በትረካው፣ ጎጃም ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎችን በመዘርዘር ግዛቱ በኦሮሞዎች እንደተመሰረተ ያብራራል። ካሰፈራቸው ስሞች መካከልም ባሶ፣ ሊበን፣ ጂጋ፣ ቡሬ፣ ሶማ፣ ዲማ፣ ኢልማና ዴንሳ፣ መጫ ይጠቀሳሉ። ባህርዳር ራሷ መጫ ስር መሆኗን ግን አልጠቀሰም። የበዕውቀቱ ትንተና ዶክተር መረራ ጉዲና “ጎጃም ኦሮሞ ነው” ከሚለው ጋር ይመሳሰላል። በእርግጥ እንዲህ ያለ ወግ ወያኔ ፊት ማውራት ጥሩ አይመስለኝም። ያላሰቡትን ማሳሰብ ይሆናል። “እንኳን ባሩድ ሸቶሽ፤ እንዲያውም ጠርሙስ አረቄ ትጨርሺያለሽ” እንዲሉ እንዳይሆን።

እንግዲህ በዕውቀቱ ስዩም በነገረን አዲስ ማንነቱ መሰረት በተለይ በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል የሰላምና የትብብር ወንዝ እንዲፈስ አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበታል። ዳር ላይ በመቆም “እገሌ ሊያጋጨን ይህን ፃፈ” እያሉ ሌላው ላይ ጣት ከመቀሰር ተላቀው እንደ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በር ከፋች ሚና መጫወት የበለጠ ውጤት ያስገኛል። በዕውቀቱ አቡነ ተክልዬን በመተረቡ የደረሰበትን የቡጢ አደጋ በማስታወስ መስጋት ያለበት አይመስለኝም። መቸም በአንክል ሳም አገር ህግ መሰረት በአያት መጠራት ደንብ ስለሆነ “ኢጆሌ በዳዳ” ማለት ቢጀምር፤ የአድናቂዎቹ ቁጥር ከግራም ከቀኝም ይጨመርለታል። ቀልዳዊ ፅሁፎች ቀልቡን ከሚስቡት “ከአሜን ባሻገር” ላይ እንደጀመረው ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም ስራ ቢሰራ መንፈሱን የሚያረካው ይመስለኛል።

በመጨረሻ የዘመናችን ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም በቋጠራት አንዲት አስቂኝ ቅኔ ልቋጭ። አስቂኝ እንኳ አይደለችም። እንደ ካራሜላ ጣፋጭ ናት። “ፍካሬ እውነት” በሚል ርእስ የቋጠራት ስትሆን፤ እንዲያው ሳስባት የኢትዮጵያን ሚዛን ያጣ ታሪክ አፃፃፍ ለማሳየት የተቋጠረች የ’ሳትዳር ወግ ትመስለኛለች።
“ሰማዩ!
እንዲህ እንደዛሬው ርቆ ሳይወረወር
ሁሉ ‘ንዳሻው ሚቆርሰው
ሁሉ ‘ንዳሻው የሚጎርሰው
ግዙፍ እንጀራ ነበር”
ብለሽ የነገርሺኝን እውነት ነው ተቀብያለኹ
ምክንያቱም ወድሻለኹ
“አያቴ
ሶስት መቶ አመታት ኖሩ
የመቶ አመት ሰው እያሉ
ብርቱ ፅኑ ነበሩ
ዝሆን በጥፊ ጣሉ
አንድ ጥይት ተኩሰው ሶስት ነብሮች ገደሉ”
ብለሽ የነገርሺኝን እውነት ነው ተቀብያለኹ
ምክንያቱም ወድሻለኹ
“አባቴ
ከሰዎች ሁሉ ይለያል
ባይኖቹ ብቻ ሳይሆን በማጅራቱም ያያል”
ብለሽ የነገርሺኝን እውነት ነው ተቀብያለኹ
ምክንያቱም ወድሻለኹ
ግና ጅል እንዳልመስልሽ አይደለሁም ተላላ
በርግጥ በጄ ብላሻለች ነፍሴ ሁሉን ተቀብላ
እውነት ማለት ከሚወዱት መስማማት‘ንጂ
አይደለምና ሌላ…
Source:- https://www.facebook.com/ttgebreab/posts/10205493725844203

ቅዱስ ሲኖዶስ: ፓትርያርኩ ሕግ አክብረውና መዋቅር ጠብቀው እንዲሠሩ አስጠነቀቃቸው፤ በወቅታዊ ሰላም ጉዳዮች መግለጫ አውጥቷል

• በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያስተላለፏቸው መመሪያዎችና የጠሯቸው ስብሰባዎች ሕገ ወጥ ተብለዋል
• ቋሚ ሲኖዶስ፥ የስምዐ ጽድቅን የፀረ ተሐድሶ ጽሑፍ ጨምሮ የተደረጉ መጻጻፎችን ይመረምራል
• የፓትርያርኩ ጉዞዎች፥ ስፖንሰር ተገኘ በሚል ሳይኾን በቋሚ ሲኖዶሱ ማስወሰን ይኖርባቸዋ

EOTC Holy Synod

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ መዋቅር ጠብቀው በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑና ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ በቅዱስ ሲኖዶስ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ የካቲት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ባካሔደው ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጽሑፎች ላይ ቀርበዋል ለተባሉ አቤቱታዎች የነበራቸውን አያያዝ፣ የወሰዷቸውን አቋሞችና የሰጧቸውን ምላሾች ገምግሟል፡፡

ፓትርያርኩ አቤቱታዎቹን ለመመልከት በሚል በራሳቸው የጠሯቸው የኮሌጆችና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ መምሪያዎች ሓላፊዎች ስብሰባዎች፤ ማእከላዊ አሠራርን ያልጠበቁና አድሏዊ እንደነበሩ ጉባኤው ተችቷል፡፡ ከዚኽም ጋር በተያያዘ ፓትርያርኩ፣ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በተጻፉ ደብዳቤዎች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያስተላለፏቸው የክሥና የቅስቀሳ መመሪያዎች የቅዱስ ሲኖዶስን የምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መንፈስ የሚፃረሩና ሕገ ወጥ መኾናቸውን ያረጋገጠ ሲኾን በስብሰባዎቹ ወጥተዋል የተባሉ የአቋም መግለጫዎችም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ተገልጧል፡፡

ፓትርያርኩ ዛሬ ለተጀመረው ዐቢይ ጾም ባለፈው ሳምንት ዓርብ መግለጫ በሰጡበት አጋጣሚ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ በብፁዕ ዋና ጸሐፊው አማካይነት በጠራው በዚኹ ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን በኃይለ ቃል ለማሸማቀቅ ሞክረዋል፤ ማኅበሩንም በተመለሱ ጥያቄዎችና በአሉባልታዎች ወንጅለዋል፡፡ “የማኅበሩ አባላት ናችኹ፤ ሒዱ ስላላችኹ ነው የመጣችኹት” በማለት የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ማኅበሩንም “ሀብታሞች ኾነዋል፤ ከመንግሥትም ገንዘብ ይሰበስባሉ፤ መንግሥት ይረዳቸዋል፤” እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡
ተንኮል የተሸረቡባቸውንና በክፋት የተሞሉ መረጃዎችን ሳያጣሩና ሳይመዝኑ እንደተነገራቸው የሚያስተጋቡት ፓትርያርኩ፣ እኒኽን ኃይለ ቃላት የተናገሩበት የረፋድ ወኔ ግን አብሯቸው አልዘለቀም፡፡ ስብሰባው ከቀትር በኋላ ሲጀመር አንሥቶ ከፍተኛ መደናገጥ ታይቶባቸዋል፡፡ ማእከላዊ አሠራርን ሳይጠብቁ የፈጸሟቸውን መተላለፎች፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በዝርዝር ለጉባኤው ያሰሙ ሲኾን በማኅበሩ ላይ ለሰነዘሯቸው ክሦችም ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋቸዋል፤ የማኅበሩ ዋነኛ የድጋፍ ምንጭ የአባላቱ አስተዋፅኦ መኾኑን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ በሒሳብ አሠራሩም ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከማኅበሩ ብዙ የሚማረው እንዳለም አልሸሸጉም፡፡

ለመዋቅራዊ መተላለፋቸውም ኾነ ከማኅበሩ አንጻር ለቀረቡላቸው የተጨባጭነት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ያልሰጡት ፓትርያርኩ፣ ማእከላዊ አሠራርን ባለመጠበቅ በፈጸሟቸው ተግባራት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ “አዋረዱን፤ አፈርንብዎ” እስከመባል የደረሰ ቅሬታ ቀርቦባቸዋል፤ በከፍተኛ ደረጃም ተገሥጸዋል፡፡
ፓትርያርኩ ከመዓርገ ክብራቸው አኳያ ከመሰል የደብዳቤ መጻጻፎች እንዲታቀቡ ጉባኤው በጥብቅ አስጠንቅቋቸዋል፤ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አደጋ በኮሌጆች የሚገኝበትን አስከፊነት አስመልክቶ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በዳሰሳ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ያወጣውን ጽሑፍ ተከትሎ ፓትርያርኩ የሰጧቸው መመሪያዎችና ከማኅበሩ ጋር የተመላለሷቸው ደብዳቤዎችም በቋሚ ሲኖዶሱ እንዲመረመሩ በጉባኤው ተወስኗል፡፡ በይቀጥላልም ጉባኤው፣ ፓትርያርኩ በመሰል ጉዳዮች አስፈጻሚ የአስተዳደር አካላትን በቀጥታ መሰብሰባቸው ስሕተት በመኾኑ፣ ከብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋር እየተነጋገሩና በቋሚ ሲኖዶስ እየመከሩ ሕጉን አክብረውና መዋቅሩን ጠብቀው ከአድልዎ የጸዳ አመራር መስጠት እንደሚኖርባቸውም በጥብቅ አሳስቧቸዋል፡፡

ግለ ታሪካቸውን ከማበላሸት አልፎ በክፉ ምክሮችና በሕገ ወጥ ደብዳቤዎች ቤተ ክርስቲያንን እያሳጣና እያስነቀፈ የሚገኘው የልዩ ጽ/ቤታቸው አሠራር ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን በእጅጉ አሳስቧል፤ የልዩ ጸሐፊው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃና የክፋት ተባባሪዎቹ ጉዳይም አስቸኳይ እልባት እንደሚያስፈልገው ከድንገተኛ ልዩ ስብሰባው በተጓዳኝ በስፋት የተመከረበትና አቋም የተያዘበት ወቅታዊ ነጥብ ኾኗል፡፡

Pat. Abune mathias-and-nebured Elias
የፓትርያርኩ የሀገር ውስጥም ኾነ የውጭ ጉዞ፣ ቋሚ ሲኖዶስ አስቀድሞ እያወቀው በዕቅድ መከናወን ያለበት ቢኾንም “የራሳችንን ወጪ ሸፍነን ቅዱስነታቸውን እናጅባለን” በሚሉ አማሳኝ ግብረ በላዎች ጭምር የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ያለዕቅድ እየወጣ የሚባክንበት፤ ፓትርያርኩ እንደ ርእሰ መንበር ሐዋርያዊ ተልእኳቸውንና አባታዊ ሓላፊነታቸውን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመወከል በሚያበቃ መልኩ የሚወጡበት ከመኾን ይልቅ “ስፖንሰር ተገኘ” በሚል ብቻ ከፍተኛ ስሕተት(የፕሮቶኮልም) የሚፈጸምበትና ክፋት የሚመከርበት እየኾነ እንደመጣም በጉባኤው ታይቷል፡፡

በመኾኑም ማንኛውም የፓትርያርኩ ጉዞዎችና የሚመደቡ ልኡካን፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ሲወሰን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንተ ክብርና ሉዓላዊነት እንዲኹም የመንበረ ፕትርክናውን ፕሮቶኮል በጠበቀ ደረጃ እንዲፈጸም ጉባኤው አሳስቧል፡፡
ቅዱስ ሲኖዱሱ በነበረው ድንገተኛ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በተለዩት የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ምትክ የሶማሌ/ ጅግጅጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያሬድ ደርበው እንዲሰሩ የተመደቡ ሲሆን፤ ብፁዕ አቡነ ያሬድም ከጅግጅጋው ሀገረ ስብከት በተጨማሪ የአርሲ ሀገር ስብከት አገልግሎትን ደርበው እንደሚሰሩ ተጠቁሟል፡፡

ስለ ተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከሚመለከታቸው አህጉረ ስብከት በሚመደቡ ልኡካን ተጨማሪ ማጣራት እንዲካሔድና አስፈላጊው የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንዲደረግ የወሰነው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በአገራችን ወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ላይም የመከረ ሲኾን በየካቲት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በነበረው ዕለትም በድንገተኛ ልዩ ስብሰባው ቃለ ጉባኤዎች ላይ በመፈራረም ስለሰላምና ስለወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ሙሉ መግለጫው ቀጥሎ ይመልከቱ፡-

synod-declaration-yek2008a

ምንጭ፡- ሐራ ዘተዋሕዶ

በኮንሶ የመብት ጥያቄን ተከትሎ መንግሥት በወሰደው የኃይል እርምጃ ህዝቡን አስቆጣ

በደቡብ ክልላዊ መንግሥት ከዚህ ቀደም ኮንሶ ራሱን ችሎ ልዩ ወረዳ በነበረበት ወቅት የዞን አስተዳደር ደረጃ እውቅና እንዲሰጠው ህዝቡ ቢጠይቅም፤ ከነበረበት ልዩ ወረዳ አንሶ በአዲሱ የሰገን ህዝቦች ዞን በሚል አስተዳደር ወደ ወረዳነት መውረዱን በመቃወም ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ከክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግሥት ምላሽ ሳያገኙ ቅተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ህዝቡ የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በኮንሶ ዋና ከተማ ካራት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል፡፡

Konso 1

በተቃውሞ ሰልፉ የደቡብ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይልና መከላከያ ሰራዊት በወሰዱት የኃይል እርምጃ 23 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ ህዝቡም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱትን የኃይል እርምጃ በመቃወም ዋና ከተማቸውን አቋርጦ የሚያልፈውን ከአርባ ምንጭ ጂንካ የሚወስደውን ዋና መንገድ ሙሉ ለሙሉ ዘግተው እንደነበርም ታውቋል፡፡

መንግሥት ተቃውሞን ለማስቆምና የተዘጋውን መንገድ ለማስከፈት በሚል በድጋሚ በወሰደው የኃይል እርምጃ ከዋና ከተማ ካራት በተጨማሪ በአጎራባች የገጠር ቀበሌዎች ጭምር በመዝለቅ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ የተገለፀ ሲሆን፤ በዚህም የደቤና ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሷይታ ጋራ የተባሉ ግለሰብ ወዲያው ህይወታቸው እንዳለፈና የ65 ዓመት አዛውነትንና ወጣት ተስፋዬ ማሙሽን ጨምሮ 23 ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ሰዎችም በከተማው ፖሊስ ጣቢያ እና በካራት ቴክኒክና ሙ ማሰልጠኛ ተቋም መታሰራቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

Konso 2

በመጨረሻም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተዘጋውን መንገድ በኃይል ማስከፈታቸውን የተገለፀ ሲሆን፤ ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በርካታ የክልሉ ልዩ የፖሊስ ኃይል እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢው ሰገን ወንዝ ሰፍረው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በተለይ በዋና ከተማዋ ካራት የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ የነበሩ ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ በከተማዋና አካባቢ የሰፈረው የመንግሥት የፀጥታ ኃይል በበቀል የህዝብ ንብረት ላይም ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ይህ እስከተዘገበበት ድረስም በአካባቢው የተለመደው የትራንሶፕርተና ማኀበራዊ አገልግሎት ከመስተጓገሉ በተጨማሪ አለመረጋጋቶች እንደሚስተዋሉ ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ በአካባቢው የነበረውን አለመረጋጋትና ተቃሞ በተመለከተ ከመንግሥት አካል የተገለፀ ነገር የለም፡፡

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሁለት የስራ ሀላፊዎችን ከሃላፊነታቸው አነሳ

OPDO

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከየካቲት 25 ጀምሮ ለአምስት ቀናት በአዳማ ከተማ ባካሄደው ጉባኤ ሁለት የስራ ሀላፊዎችን ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ በማድረግ እና የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የስራ ሃላፊዎቹ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገው በአመራር ችግር መሆኑን አስታውቋል።

በዚህም 1ኛ የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሞቴ የስራ አስፈጻሚ አባል እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል እንዲሁም የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ዳባ ደበሌ ሲሆኑ፥ በታየባቸው የአመራር ችግር ምክንያት ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መወሰኑን እና ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባልነት ተነስተው ነገር ግን የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው እንዲቀጥሉ ወስኗል።

2ኛ የኦህዴድ እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል እና የኦሮሚያ ክልል የእርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ጀማነ ሲሆኑ፥ እስከ ቀጣዩ የድርጀቱ ጉባኤ ድርስ ከማንኛውም የድርጅት እንቅስቃሴ መታገዳቸውን ድርጅቱ ማስታወቁን ፋና ቢሲ ዘግቧል፡፡
ምንጭ፡ http://www.fanabc.com/index.php/news/item/1428