በሽብር ወንጀል የተከሰሱት የነ መሪ ጌታ ዲበኩሉ አስማረ የፍርድ ቤት ውሎ
ቴዎድሮስ አስፋው
“እየተመገብንና እየጠጣን ያለው አሸዋ ነው” ተከሳሾች
~”ስሜ መሪጌታ ዲበኩሉ አስማረ እንጂ ወይዘሪት ዲበኩሉ አስማረ አይደለም”
~የመቃወሚያ ብይን ለመስጠት 9 ወር ፈጅቷል
በፀረ ሽብር አዋጅ አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 1 ተጠርጥረው በነ አቶ ክንዱ የክስ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው 8 ተከሳሾች መጋቢት 3 ቀን 2010ዓ.ም የክስ መቃወሚያ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 6 ቀን 2010ዓ.ም ተቀጥሮ በነበረው መስረት ተከሳሾች የሚመለከታቸው አካላት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ችሎቱ በሚካሄድበት የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት አዳራሽ ውስጥ የተገኙ ቢሆንም ችሎቱ ግን ዘግይቶ 5 ሰዓት ላይ ነው የጀመረው።
የመሀል ዳኛው ዳኛ በመጓደሉ ምክንያት መዘግየታቸውን ገልፀው ዘግይተው በመጀመራቸው ይቅርታ በመጠየቅ ከሳሽ ዐቃቤ ህግ የተከሳሽ ጠበቆች እንዲሁም ተከሳሾች መኖራቸው በስም ጥሪ በሚያረጋግጡበት ግዜ 6ኛ ተከሳሽ መሪጌታ ዲበኩሉ አስማረን ወይዘሪት ዲበኩሉ ሰመረ ብለው በመጥራታቸው ተከሳሹ ስሜ መሪጌታ ዲበኩሉ ሰመረ እንጂ ወይዘሪት ዲበኩሉ አስማረ አይደለም በማለት ስማቸው እንዲስተካከልለት ጠይቀዋል።
በዚህም መሰረት ዳኛው መዝገቡ ላይ ወ/ት ተብሎ መመዝገቡን ገልፆ ለስህተቱ ይቅርታ ጠይቋል። በመጨረሻም የክስ መቃወሚያ ብይኑን በዳኛ መጓደል ምክንያት እንዳልሰሩት በመግለፅ ተለዋጭ ቀጠሮ ለመስጠት የተከሳሽ ጠበቆችና ተከሳሾች አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ከ2ኛ እስከ 6ኛ እና የ10ኛ ተከሳሾች ጠበቃ መዝገቡ በዚህ ሳምንት ብቻ ብይን ለመስጠት ለ3ኛ ግዜ መቀጠሩን በመግለፅ የአሁኑ ቀጠሮ የመጨረሻ እንዲሆን ጠይቀዋል። 7ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ እንየው መዝገቡ እየተጓተተ ያለው በኔ የመቃወሚያ ብይን ነው ይህም 9 ወር መፍጀቱ አሳዛኝ ነው ብሏል። ከዚህ በተጨማሪ 10ኛ ተከሳሽ ለገሰ ወልደሃና በማረሚያ ቤቱ የሚቀርብልን ምግብና መጠጥ አሸዋ ያለበት በመሆኑ በተደጋጋሚ ግዜ እንዲስተካከልልን ለአስተዳደሩ ብናቀርብም መልስ ማግኘት ስላልቻልን ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይስጥልን ሲል አቤቱታውን በጽሁፍ ጭምር አቅርቧል።
የመሀል ዳኛው ፍርድ ቤቱ በማረሚያ ቤቱ የውስጥ አስተዳደር ጣልቃ የማይገባ ቢሆንም የምግብና የመጠጥ አቅርቦቱን በሚመለከት አስተዳደሩን ጠርተን እናናግራለን ዛሬ ከሰዐትም አጠቃላይ የፍትህ አካላት ውይይት ያለ በመሆኑ በዚሁ አጋጣሚ መልስ እንደሚያገኝ ገልፀዋል። ቀጠሮውንም በሚመለከት ለቀጣዩ ሳምንት ለመጋቢት 13 ጠዋት ላይ እንዲሆን በመወሰን የመጨረሻ እንደሚሆን ገልፀዋል።
የተከሳሾች ስም ዝርዝር
1ኛ. ክንዱ ዱቤ
2ኛ. ዘመነ ጌጤ
3ኛ. ደበበ ሞገስ
4ኛ. ዘራይ አዝመራው
5ኛ. ገብረስላሴ ደሴ
6ኛ. መሪጌታ ዲበኩሉ ሰመረ
7ኛ. ሀብታሙ እንየው
10ኛ. ለገሰ ወልደ ሃና ናቸው
8ኛ እና 9ኛ ተከሳሾች ክሳቸው መቋረጡ በፍርድ ቤቱ ተገልፆል።
አቶ አበበ ካሴ በእስር ቤት ስለደረሰበት ግፍ ተናገረ
ዳንኤል ተስፋዬ
~ “በግብረሰዶም ወንጀል ከተፈረደባቸው እና ከአህምሮ እመምተኞች ጋር ከአንድ አመት በላይ አንድ ላይ አንድታሰር ተደርጌያለሁ”
~ በደረሰብኝ ኢ-ሰባዊ ድርጊት ኩላሊቴ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። ሽንቴንም መቆጣጠር አልችልም…”
~”ከወልቃይት ማንነት ጋር በተያያዘ አሁንም በማረሚያ ቤት ሀላፊዎች ድብደባ እየፈፀሙብኝ ነው…”
በግንቦት 7 ስም ተከሶ 7 ዓመት ተፈርዶበት አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ቃሊቲ የሚገኘው የአበበ ካሴ በእስር ቤት በደል እየተፈፀመበት እንደሚገኝ ገልፆአል።
ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኘው አበበ ካሴ በቃሊቲ ማ /ቤት ከፍተኛ ስቃይና ድብደባ እንደደረሰበት ተናገረ። ከዝዋይ ማረሚያ ቤት ወደ ቃሊቲ ከተዛወረ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት ሱፐር ገብረ ህይወት፣ ኦፌሰር መካሻ፣ ኦፌሰር ጥላሁን እና ሌሎችም የማረሚያ ቤቱ አመራሮች ከፍተኛ ድብደባ እንደፈፀሙበት ገልፆአል።
ስነ ልቦና እና አካላዊ ጉዳት እንዲደርስበት ግበረ ሰዶም ተከሰው ከተፈረደባቸው እና የአህምሮ ህመምተኞች ለብቻቸው ከሚተሰሩበት ማቆያ እንዳሰሩትም ተናግሯል። “ከወልቃይት ማንነት ጋር በተያያዘ እዚህ ሆነህ ወጣቶች እንዲደራጁ፣ እንዲያምፁ፣ በወልቃይት ጉዳይ ህዝብ አቋም እንዲይዝ መልህክት አስተላልፈሃል” በሚል ድብደባ ተፈፅሞብኛል ብሏል።
“እስር ቤት ውስጥ በደረሰበት ድብደባ ኩላሊቴ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኛል። ሽንቴንም መቆጣጠር አልችልም” ብሏል። ይህን መረጃ ያጠናቀረው ዳንኤል ተስፋየ አበበ ከፍተኛ የሆነ የወገብ ህመም እና ድካም እንዳለበት መታዘብ ችሏል።
በሌላ ክስ 20 አመት ተፋርዶበት ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፍርድ ቤት ቅጣቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ትህዛዝ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት መሰጠቱን አበበ ገልጿል። አቶ አበበ ካሴ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በደረሰበት ድብደባ እና ስቃይ 20 የእግሩ እና የእጁ ጥፍሮቹ ሙሉ በሙሉ መነቀላቸው፣ ብልቱ መኮላሸቱ፣ በኤሌክትሪክ ንዝረት በተፈፀመበት ግርፋት ለ11 ወራት ያህል አንድ ጎኑ ደንዝዞ እንደነበር በዚህም ምክንያት የእግሩ ጡንቻዎች መሸማቀቃቸው መግለፁ ይታወሳል።
የዋልድባ ገዳም መነኮሳት አባ ገብረ-ሥላሴ ስና አባ ገብረ-ኢየሱስ የፍርድ ቤት ውሎ
ሀብታሙ ምናለ
የፌደራሉ ከፍተና ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት፤ የካቲት 30 ቀን 2010 ዓ. ም. በዋለው ችሎት የዋልድባ መነከሳት ባቀረቡት “የሰብዓዊ ጥሰት በማረሚያ ቤቱ ተፈፅሞብናል ፍርድ ቤቱ ተትዕዛዝ ይስጥልን!” ብለው ያቀረቡትን አቤቱታ ሰምቶ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ለመስማት ሲኾን ማረሚያ ቤቱም ምላሽ የሚለውን በደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡
ፍርድ ቤቱ ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን ምላሽ እንደተመለከተው እና ውሳኔ እንደሚሰጥ አሳውቋል፡፡ አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም “የተከሰስነውም የታሰርነው አንድ ላይ ቢኾነም እኔን ያለምንም ምክንያት ወደ ዞን አምስት በተለምዶ ጨለማ ወይም ቅጣት ቤት ወደሚባለው አዘዋውረውኛል፡፡ ተቀጥቼ ከኾነ ጥፋቴ ተነግሮኝ፤ ቅጣቴ ምን ያህል ቀን እንደኾነ አውቄ ቅጣቴን ልቀበል፤ ያለምንም ጥፋት ዝም ብዬ ነው፡፡ እየተሰቃየኹ ያለኹት ብዙ በደል ደርሶብናል፡፡ ከአመት በላይ ልብስ ሳንቀይር ቆይተን በቅርብ ቀን አንድ ምዕመን ልብስ አምጥቶልኝ እኔ ለመቀየር ችያለሁ፡፡
ነገር ግን አባ ገብረሥላሴ ከተያዙ ጀምሮ ምንም ልብስ ቀይረው አያውቁም። ሰዎች ልብስ ሲያመጡ ማስገባት አይቻልም፡፡ እያሉ እያስመለሱ ከአንድ ዓመት በላይ በአንድ ልብስ ብቻ ሳናወልቅ ቆይተናል፡፡ ኹለታችንም አብረን በአንድ ዞን የነበርነው ያለምክንያት በታትነውናል፡፡ ሰዎች ሊጠይቁን ሲመጡ የተለያየ ዞን በመኾናችን ጠያቂዎቻችን እክል እየገጠማቸው ነው፡፡ ወደነበርኩበት ዞን ልመለስ” ብለው ጠይቀዋል፡፡
ዳኞቹም፡- “ልብስ ለምን አይገባም?” ብለው የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ሲጠይቁ መልስ መስጠት ባለመቻላቻው “ልብስ ማነው የሚያመጣላችሁ?” ብለው ዳኞች ሲጠይቁ ችሎቱን ሲከታተሉ ከነበሩት ወጣቶች መካከል ለአንዳቸው የሚኾን የምንኩስና ልብስ ገዝተው ይዘው ነበር፡፡ ልብሱን ሲያቀርቡ ዳኞቹ፡- “ጠባቂዎቹን ፈትሹና ስጧቸው!” ቢልም ፍቃደኛ አለመኾናቸውን ሲያሳዩ ዳኞቹ በቁጣ “ተቀበሉና ፈትሻችሁ ስጡ!” በማለት ሲያዙ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ወታደራዊ ሰላምታ በመስጠት ወደ ዳኞቹ ተጠግቶ ሊናገር ሲል ዳኞቹ፡- “የተባልከውን ብቻ አድርግ! ምንም ሌላ አያስፈልግም!” በማለት ልብሱ ተፈትሾ ለአባ ገ/ሥላሴ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም ያቀረቡትን አቤቱታ እና የተሰጠውን መልስ አይተው ውሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት 5 ቀን 2010ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ መጋቢት 18 መደበኛ የክስ የሚቀጥል እና ምስክር እንደሚሰማባቸው ይታወቃል፡፡
የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር፥ የመብት ተሟጋች እና ጦማሪ ስዩም ተሾመ በማዕከላዊ እስር ቤት የመብት ጥሰት ተፈፀመበት
(ዳጉ ሚዲያ) የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር፥ የመብት ተሟጋች፥ የኢትዮ ቲንክታንክ እና ማኀበራዊ ገፅ ጦማሪ ስዩም ተሾመ ከሚኖርበትና ይሰራበት ከነበረው ወሊሶ ከትማ በፀጥታ ኃይሎች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እስር ቤት ከፍተኛ ስቃይና እንግልት እንደተፈፀመበት ተጠቆመ።
ከየካቲት 9 ቀን 2010 ዓ. ም. ጀምሮ በድጋሚ ለ6 ወራት የሚቆይ የአቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በተደረገ ሳምንት ሳይሞላው ስዩም ተሾመ ከመኖሪያ ቤቱ ታፍኖ ማዕከላዊ በሚባለው የፌደራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል ከፍተኛ ምርመራ እየተደረገበት ሲሆን፤ የአገዛዙ መርማሪዎች አካላዊ ጥቃት በመፈፀምና በማስገደድ የሚጠቀማቸውን የኮምፒዩተርና የኢንተርኔት አገልግሎት የይለፍ ቃሎች(ፓስ ወርድ) መወሰዱም ታውቋል። መርማሪ ፖሊሶችም የፍርድ ቤት ክስ በመመስረት ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ በጠየቁት መሰረት እንደተፈቀደላቸውም ለማወቅ ተችሏል። ስዩም ተሾመን ማዕከላዊ ምርመራ በመሄድ ለመጎብኘት የሞከሩ ወዳጆቹ፥ የመብት ተሟጋቾችና የስራ ባልደረቦቹ እንዳይጎበኙት መከልከላቸውም ታውቋል።
ስዩም ባለፍው ለ10 ወራት ተግባራዊ ተደርጎ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመሳሳይ መልኩ ከመኖሪያ ቤቱ በገዥው ስርዓት የፀጥታ ኃይሎች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በምርመራ ወቅት ከፍተኛ የአካል ጥቃት ተፈፅሞበት እንደነበርና ከተወሰኑ ወራት እስር በኋላ መለቀቁ ይታወሳል።
በሞያሌ 10 ያህል ሰላማዊ ዜጎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተገደሉ
(ዳጉ ሚዲያ)ትናንት ቅዳሜ መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ፥ቦረና ዞን የሞያሌ ከተማ በገዥው መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት የፀጥታ አባላት 10 ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ 11 ያህሉ መቁሰላቸውን የዓይን እማኞችን እና የከተማውን ከንቲባ ዋቢ በማድረግ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ዘግቧል።
ግድያውን በተመለከተ በአስቸኳይ አዋጁ መሰረት የመላ ሀገሪቱን አጠቃላይ የጠጥታ እና የተፈጥሮ ሃብትን በበላይነት እየተቆጣጠረ ያለው የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት በበኩሉ በተፈጠረ የመረጃ ስህተት ምክንያት 9 ሰላማዊ ዜጎች በስሩ ባሉ የፀጥታ ኃይሎች 9 ሰላምዊ ዜጎች መገደላቸውን እና 12 ያህል መቁሰላቸውን አስታውቋል።
ግድያው የተፈፀመው በከተማው በተለምዶ ሸዋበር በሚባል ሰፈር ሲሆን፤ በወቅቱ በአካባቢው ምንም ዓይነት ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ባልነበረበትና ዜጎች በተለመደ ሰላማዊ መደበኛ ዕለታዊ እንቅስቃሴ እያሉ ግድያው በጅምላ መፈፀሙን የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል። በተለይ ጥቃቱ በሚፈፀምበት ወቅት በመዝናኛ ስፍራ የነበሩ፥ በምግብ ቤትና በሱቅ ግብይት ላይ የነበሩና መንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እንደሚገኙበት ተጠቁሟል።
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ ም የታወጀው እና ለ6 ወራት የሚቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ባሉ የተለያዩ ከተሞች በርካታ ሰላማዊ ዜጎች በኮማንድ ፖስቱ የፀጥታ አባላት መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የሞያሌው የጅምላ ግድያ ተጨማሪ ጥቃት መሆኑ ታውቋል። የጅምላ ጥቃቱን ተከትሎም በርካታ የከተማው ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ተሰደዋል።
ቀደም ሲል የመብት ተሟጋች ኢትዮጵያውያን፥ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፥ ዓለም አቀፍ ይሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፥ የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮፓ ህብረት አባላት እና የገዥው መንግሥት አካል የሆኑ በርካታ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ እንዳይደረግ ተቃውመውት እንደነበር አይዘነጋም። ይሁን እንጂ አዋጁን ተከትሎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግድያ እና እስር ተጠናክሮ መቀጠሉ ታውቋል።