ፍርድ ቤቱ በብሎገሮቹና በጋዜጠኞች ላይ ተሻሻለ የተባለውን የአቃቤ ህግ ክስ ተቀበለ
ባለፉት 9 ወራት በፖሊስ ቁትጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የነበሩት 6 የዞን 9 ጦማርያንና 3 ጋዜጠኞች ላይ አቃቤ ህግ በዛሬው ዕለት ጥር 20 ቀን 2007 ዓ.ም. አሻሽዬ አቅርቤዋለሁ ያለውን የክስ ቻርጅ የልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ የወንጀል ችሎት ተቀባይ አድርጎታል፡፡
በዚህም መሰረት ተከሳሾቹ በአሸባሪነት ወንጀል እንደሚጠየቁና ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ዛሬ ጠዋት በነበረው የክስ ሂደት ወቅት ጠይቋቸው ጉዳዩን ለከሰዓት አስተላልፎት ነበር፡፡ ነገር ግን ከጥቂት ሰዓታት በፊት በነበረው የክስ ሂደት ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለ17ኛ ጊዜ ለሚቀጥለው ማክሰኞ ጥር 26 ቀን ቀጠሮ በመስጠት ተበትኗል፡፡
ስድስቱ የዞን 9 ጦማርያንና ሦስቱ ጋዜጠኞች ከባለፈው ዓመት ሚያዚያ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የከረመ ቢሆንም የክስ ሂደቱ ላይ ግን በርከት ያሉ የህግ ሂደትን ያልተከተሉ ሁኔታዎች ሲስተዋሉ መቆየቱን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡
አንድነት ፓርቲ በድብደባ ትግሉን እንደማያቆም በመግለፅ በድጋሚ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የምርጫ ቦርድ በፓርቲው ላይ የሚያሳየውን ጣልቀ ገብነትና ፓርቲውን ለማፍረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመቃወም የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ ነበር፡፡ በዕለቱም በደብረ ማርቆስ፣ በጋሞ ጎፋ ከንባ እና በሰሜን ሸዋ ሸዋሮቢት የተሳካ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጉን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ በዕለቱ በአዲስ አበባ የሰልፉ ጅማሮ ላይ ከ26 በላይ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች እና በቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ የነበሩ የ70 ዓመት አዛውንትን ጨምሮ በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው የዓይን እማኞች፣ የህክምና እና የምስል ማስረጃ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በዕለቱ በፖሊስ ከተፈፀሙ ድብደባዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና ነፍሰጡር ሴት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲው የዕለቱን ሰላማዊ ሰልፍ በፖሊስ ድብደባ እንቋረጥ ቢደረገም ፤ ለጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም. መነሻውን ቀበና ከሚገኘው የፓርቲው ጽህፈት ቤት አንስቶ በፒያሳ በዳረሻውን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጀርባ በሚገኘው የኢትዮ-ኩባ አደባባይ በድጋሚ ሰልፍ ጠርቷል፡፡ በተመሳሳይ ዕለትም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል ከተሞች በደሴ፣ በባህርዳር ፣በደብረ ታቦርና በሌሎች የክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ የጠርቷል፡፡
በተለይ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በፓርቲው አባላት፣ደጋፊዎችና ቤተክርስቲያን ለፀሎት የተቀመጡ አዘውንት ምዕመናን በፖሊስ የተፈፀመባቸውን ድብደባ በማውገዝ፣ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችንም በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ ይህንንም ሰላማዊ ትግሉ በጭፍጨፋና በውንድብና ለማቆም መሞከር ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው! ሲል አዲስ አበባ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ሙሉ መግለጫውን ከታች ይመልከቱ፡-
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
=============================
ሰላማዊ ትግሉ በጭፍጨፋና በውንድብና ለማቆም መሞከር ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው!
ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
የተሰጠ መግለጫ
================================
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት የጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሰልፍ መጥራቱ ይታወቃል። ነገር ግን ስርዓቱ ህገ ወጥ ሰልፍ ነው በማለት በአንድነት አመራሮችና አባለት ላይ ያደረሰው አሰቃቂ ድብደባ ወደር የማይገኝለት ነው። እርጉዞች፣ ህፃናት፣ አዛውንቶችና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ ደማቸው ፈሷል፤ አጥንታቸው ተሰብሯል። ሰላማዊ ሰልፉ ስርዓቱ እንደሚለው ህገ ወጥ አልነበረም፤ ስልፍ እንደምናደርግ ደብዳቤ ስንልክላቸው አንቀበለም ብለው ሲያንገራግሩ ደብዳቤውን እዚያ አስቀምጠንላቸዋል፤ ይህ ብቻ አይደለም በሬኮማንድ በድጋሚ ተልኮላቸው ተቀብለዋል። ህጉ አስተዳደሩ በአስራ ሁለት ሰዓት ውስጥ መልስ መስጠት አለበት ቢልም ከሰባ ሁለት ሰዓት በኋላ በሚዲያ “ሰልፉ ህገወጥ ነው” የሚል መግለጫ ከማውጣት ውጪ በደብዳቤ የመለሱት ነገር አልነበረም። በመሰረቱ በስብሰባና በሰልፍ አዋጁ መሰረት አንድ ፓርቲ ሰልፍ እንደሚያደርግ ለአስተዳዳሩ ማሳወቅ ነው ያለበት። አስተዳደሩ ሰላማዊ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ኃይል በመመደብ ሀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንጂ ሰልፍ መፍቀድም ሆነ መከልከል አይችልም።
አምባገነኑ የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስት የዘንድሮውን ሀገራዊ ምርጫ ሂደቱንም ጭምር በማበላሸት ጠንክራ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫው ውጪ እንዲሆኑ ለማድረግ ላይ ታች እያለ ነው። በተለይ አንድነት ፓርቲ ላይ በምርጫ ቦርድ፣ በኢቲቪ እና በሬዲዮ ፋና የሶስትዮሽ ግንባር በመክፈት በህዝቡ ዘንድ ብዥታ እንዲፈጠር፣ ምርጫው ያለጠንካራ ተዋዳደሪ እንዲካሄድ በማድረግ የምርጫውን ዋጋ ቢስነት ከማረጋገጡም በተጨማሪ ፓርቲውን ለማፍረስ ቀን ከሌሊት እየሰራ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ስርዓቱና ምርጫ ቦርድ የጥቅም ምንደኞች በማዘጋጀት ተለጣፊ አንድነትን በመጠፍጠፍ ፓርቲውን ከእውነተኛ አባላቱና ደጋፊዎቹ ለመቀማት እጅግ አሳፋሪ የሆነ የሽፍትነት ስራ በመስራት ላይ ይገኛል።
አሁንም ቢሆን አንድነት ይህን የህወሀት/ኢህአዴግ ሴራና ውንብድና በመቃወም ለሚቀጥለው እሁድ ጥር 24/2007 በአዲስ አበባና በሌሎች የተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ ሰልፍ ያድርጋል። በአዲስ አበባ ላይ የሚካሄደው ሰልፍ በተለምዶ ኢትዮ ኩባ አደባባይ (ድላችን ሀወልት) ሲሆን በትናንትናው ጥር 18/2007 ለአስተዳደሩ በደብዳቤ አስገብተናል። ይህ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሰልፍ አስተዳደሩ አሳማኝ ምክንያት አቅርቦ ተለዋጭ የጊዜ ወይም የቦታ አማራጭ እስካላቀረበ ድረስ በምንም ሁኔታ የሚታጠፍ አይደለም። አንድነት ስብሰባና ሰልፍ የማድርግ ህገመንግስታዊ መብት እስኪረጋገጥ ድረስ በህዝባዊ ንቅናቄና በሰላማዊ መንገድ ትግሉን ይቀጥላል።
ድል የሕዝብ ነው!!
ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ስልክ ቁ. ዐዐ11-1- 22-62-88
ፖ.ሣ.ቁ 4222
ሁለት ታዋቂ የአውሮፓ ኩባንያዎች በኦሞ ሸለቆ ጥጥ የተሠሩ ምርቶች አንገዛም አሉ
ዮሐንስ አንበርብር
ታዋቂዎቹ የአውሮፓ ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎች የጀርመኑ ቼቦና የስዊድኑ ኤችኤንድኤም በኢትዮጵያ ኦሞ ሸለቆ ውስጥ የተመረተ የጥጥ ምርትን የሚጠቀም የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች እንደማይገዙ መግለጻቸው ተሰማ፡፡
የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴ ለመገደብና ጥላሸት ለመቀባት የሚደረግ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች ዘመቻ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ልማት ኢንስቲትዩት በመግለጽ አጣጥሎታል፡፡
ሁለቱ ታዋቂ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎች በበርካታ የዓለም አገሮች ሰፊ ቅርንጫፍ መደብሮች እንዳሏቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በኦሞ ሸለቆ ከሚመረት ጥጥ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ማሳወቅ የጀመሩት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የምዕራብ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ተቋማት የኦሞ ሸለቆ ነዋሪዎች ከመሬታቸው በመንግሥት እንዲፈናቀሉ ተደርገው መሬቱ ለጥጥ ምርት መዋሉ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው በሚል ባናፈሱት መረጃ ነው፡፡ ሁለቱ ታዋቂ ኩባንያዎች ደግሞ የሰው ልጆችን ሰብዓዊ መብትና የአካባቢ ጥበቃ እንደሚያስከብሩ የሚያሳውቁ በመሆናቸው ነው፡፡
ኩባንያዎቹ ከሁለት ዓመት በፊት ቢሯቸውን በአዲስ አበባ ከፍተው በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎች የተመረቱ ጨርቆችን በጥሩ ዋጋ መግዛት መጀመራቸው ይታወሳል፡፡ በመጀመርያ የጀርመኑ ኩባንያ ቼቦ ነው በኦሞ ሸለቆ የሚመረት የጥጥ ምርቶች መቀበል ማቆሙን የገለጸው፡፡ በዚህ ሳምንት ኤኮ ቴክስታይል በተባለው ድረ ገጽ በጉዳዩ ላይ መረጃ የሰጠው ኤችኤንድኤም መሬት መቀራመትን (ላንድ ግራቢንግ) እንደ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለሚወስድ እንደሚቃወም ገልጿል፡፡ ድርጊቱ በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታትን የሰብዓዊ መብት መርህና የኤችኤንድኤም ድርጅትን የሰብዓዊ መብት ፖሊሲ እንደሚጥስ አክሏል፡፡ በመሆኑም በዋናነት የጨርቃ ጨርቅ ምርት ለሚያቀርብለት የቱርኩ አይካ አዲስ በዚህ አካባቢ የተመረተ ጥጥ ተጠቅሞ የሚያመርተውን ጨርቅ እንዳያቀርብለት ማሳወቁን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ልማት ኢንስቲትዩት ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎችንና ልማቱን የሚደግፍ፣ ገበያና አዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር የሚያቀርብ የመንግሥት ተቋም ነው፡፡ የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ባንተይሁን ገሠሠ በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው፣ የዚህ ዓይነቱ ዘመቻ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ነን ባዮች ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፣ የጥጥ ልማት በሚከናወንበት አካባቢ መንግሥት እንኳን ሰው ሊያፈናቅል ቀርቶ እያሰባሰበ የልማት ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በአካባቢው በጣም ጥቂት አርብቶ አደሮች ብቻ የሚኖሩበት ለእርሻ የሚመች በጣም ግዙፍ መሬት መኖሩን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ‹‹አርብቶ አደሮቹ ሳር ካለ በአካባቢው ይቆያሉ፡፡ ከሌለ አካባቢውን ለቀው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ሰው ያልሠፈረበት አካባቢ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አርብቶ አደሮቹ በአካባቢው ረግተው እንዲቆዩና ቋሚ የእርሻ መሬት ማረስ እንዲለምዱ መንግሥት እያስተባበረ እንደሚገኝና በአሁኑ ወቅትም 80 ሔክታር መሬት ላይ አርብቶ አደሮቹን በማስለመድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ለጥጥ እርሻ የተዘጋጀ 116,859 ሔክታር መሬት በአካባቢው በአሁኑ ወቅት መኖሩንና ከዚህ ውስጥ የለማው 70,867 ሔክታር ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በአካባቢው ጥጥ በማምረት ላይ የሚገኙ 22 ኩባንያዎች መኖራቸውንና በአሁኑ ወቅት ከተዘጋጀው 116 ሺሕ ሔክታር መሬት በላይ ማስተናገድ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞቹን ዘመቻ መንግሥትም፣ እኛም፣ ኤችኤንድኤምና ቼቦም ያውቁታል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ አሁንም እነዚህ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ እየገዙ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የአይካ አዲስ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጨምሮ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
“የስርዓቱን አረመኔያዊ እርምጃ እናወግዛለን!”- የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ጥምረት
በተቃውሞ ሰልፉ በአንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት እንዲሁም ሌሎች ዜጎች ላይ በፖሊስ የተፈፀመውን ድብደባ የ9ኙ ትብብር ፓርቲዎች ጥምረት አውግዟል፡፡ የ9ኙ የትብብር ፖለቲካ ድርጅት መኢአድ፣ሰማያዊ፣የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የከንባታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና ሌሎች አባላትን ያቀፈ የፖለቲካ ጥምረት ድብደባውን በፅኑ አውግዟል፡፡ ሙሉ መግለጫውን ከዚህ በታች ይገኛሉ፡-
የስርዓቱን አረመኔያዊ እርምጃ እናወግዛለን!
ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የተሰጠ መግለጫ
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አብሮ ስለመስራትና ሌሎቹም ትብብሩን እንዲቀላቀሉ በየጊዜው የሚወተውተው አገራችን በዚህ ዘመን በማይመጥን አምባገነንና የጭካኔ ስርዓት ውስጥ የምትገኝ መሆኑን በመረዳቱ ነው፡፡ ይህ የህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነንና ጨካኝ ስርዓት ህዳሩ 27/28 2007 ዓ.ም የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በወጡት አመራሮቻችን፣ አባላቶቻችን፣ ደጋፊዎቻችንና በየጎዳናው የተገኙት ንፁሃን ላይ ከፍተኛ ድብደባና የጅምላ እስር በመፈፀም ስርዓቱን ለመታገል የተነሳነበትን አላማ ትክክለኝነት አረጋግጦልናል፡፡
በዛሬው ዕለትም ገዥው ፓርቲ በፓርቲያቸው የውስጥ ጉዳይ ገብቶ የሚፈፅመውን ደባ፣ ምርጫ ቦርድንና የህዝብ ሚዲያን ተጠቅሞ ፓርቲውን ለመከፋፈልና አሳንሶ ለማሳየት የሚያደርገውን እኩይ ተግባር በመቃወም ሰልፍ የወጡ የአንድነት አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና የፓርቲው ጽ/ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው ቤተ ክርስትያን አካባቢ የነበሩ አዛውንት ምዕመናንን ሳይቀር በመደብደብ ጭካኔውን ዳግመኛ አሳይቶናል፡፡ ፖሊስ በትዕዛዝ በአንድነት አባላት ላይ ከፍተኛ የጭካኔ እርምጃ ወስዷል፡፡ አብዛኛዎቹንም በጅምላ አስሯል፡፡
ስርዓቱ በእነዚህ ሰላማዊ ዜጎች ላይ አሁንም የጭካኔ እርምጃውን መድገሙ ስልጣኑን የማጣት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳለ እና ከይስሙላ ያለፈ ለሰላማዊ ትግሉ ዝግጁ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ትብብራችን የስርዓቱን ጨካኝነት እያወቁም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ በስርዓቱ የማይከበረውን ህገ መንግስታዊ መርህ ተከትለው ሰልፍ ለወጡ ቆራጥ የአንድነት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች አድናቆቱን መግለጽ ይወዳል፡፡ መስዋዕትነታችሁ ለነገ ድላችን ስንቅ በመሆኑ ይበልጡን ተጠናክራችሁ በጋራ ትግላችን እንደምናጠናክርም እምነታችን ነው፡፡
በተቃራኒው ገዥው ፓርቲ ህግ የማክበርና የማስከበር ሚናውን ረስቶ ፖሊስ፣ ደህንነትንና ሌሎች ተቋማትን ለራሱ ስልጣን ማስጠበቂያ በማዋል በአንድነት አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎች ላይ የፈፀመውን ለዘመኑ የማይመጥንና በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ለጠየቁት ኢትዮጵያውያንም የማይገባ የጭካኔ እርምጃ በጥብቅ እናወግዛለን፡፡
ኢትዮጵያውያንን የማስተዳደር አቅምና ሞራል ያጣው ገዥው ፓርቲ የዜጎችን ጥያቄ በኃይል ማዳፈን የማይቻል መሆኑንና አገራችን ወደባሰ ችግር እንደሚከታት ተረድቶ ከዚህ የጭካኔ እርምጃው እንዲቆጠብ፣ እርምጃውን የወሰዱትን አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑና የታሰሩትን በአስቸኳይ እንዲፈታ እናሳስባለን፡፡ ፖሊስ፣ ደህንነት፣ መከላከያና ሌሎች ተቋማት ገዥው ፓርቲ አላፊ መሆኑን በመገንዘብና ከገዥው ፓርቲ ታዛዥነት በመውጣት ወገኖቻቸሁ ላይ እንዲህ አይነት የጭካኔና አሳፋሪ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥባችሁ ከህዝብ ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡
ያለ መስዋዕትነት ድል የለም!
ጥር 17/2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ















