Tag Archives: Ethiopian 2015 Election

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ለህዝባዊ ሰልፍ የመረጣቸውን 15 ከተሞች ይፋ አደረገ

  • ሰልፉ እሁድ መጋቢት 20 ቀን 2007 ዓ.ም ይደረጋል
ከግራ ወደ ቀኝ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከ(ሰማያዊ) እና አቶ ግርማ በቀለ ከ(ኦህዴህ)

ከግራ ወደ ቀኝ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከ(ሰማያዊ) እና አቶ ግርማ በቀለ ከ(ኦህዴህ)

የ9ኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍና የምርጫ ቅስቀሳ ለማካሄድ የመረጣቸውን 15 ከተሞች ይፋ አደረገ፡፡ ትብብሩ በተመሳሳይ ሰዓት በ15 ዋና ዋና የሀገሪቱ ከተሞች ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ቀደም ብሎ አሳውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በዚህ መሰረት የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር መጋቢት 20/2007 ዓ.ም በተመሳሳይ ሰዓት ሰልፉን የሚያካሂድባቸው ከተሞች የሚከተሉት ሆነዋል፡፡ እነዚህም አዳማ፣ ባህር ዳር፣ አርባ ምንጭ፣ ደብረ ታቦር፣ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ ደብረ ብርሃን፣ ወልቂጤ፣ አሰበ ተፈሪ (ጭሮ)፣ ወላይታ ሶዶ፣ ደሴ፣ ዱራሜ፣ ደብረ ማርቆስ እና ሆሳዕና ናቸው፡፡

ትብብሩ “መጋቢት 20 በፍፁም አይቀርም” በሚል ለህዝቡ የድጋፍ ሰልፍ ጥሪ ያደረገ ሲሆን፣ ከተሞቹ የተመረጡትም ፓርቲዎቹ በየአካባቢዎች ባቀረቡት እጩ ብዛት መሰረት እንደሆነ ገልጹዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የሚደረገው የድጋፍ ሰልፍ በተመረጡት ከተሞች የሚደረገው ሰልፍ በተከናወነ በሳምንቱ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፡- ነገረ-ኢትዮጵያ

የጋዜጠኞቹ እና ብሎገሮቹ አቤቱታዎች ውድቅ ተደረጉ

zone9

በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የሚገኙት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ሦስቱ ወዳጅ ጋዜጠኞች መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም ከሰዓት 8፡00 የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡

መዝገቡ ተቀጥሮ የነበረው ተከሳሾች ባቀረቧቸው ሁለት አቤቱታዎች ላይ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ በዚህም አንደኛ አቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ አለኝ ካለው ማስረጃ ዝርዝር ውስጥ 12 የኦዲዮ-ቪዲዮ ሲዲዎች አያይዞ ያቀረበ ቢሆንም፣ ሲዲዎቹ ለተከሳሾች እስካሁን ባለመድረሳቸው ተከሳሾች የቀረበባቸውን ማስረጃ ተመልክተው መልስ ለማዘጋጀት ሲዲዎቹ እንዲሰጧቸው ያቀረቡት አቤቱታ ሲሆን፣ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ 4ኛ ተከሳሽ ማህሌት ፋንታሁን እና 9ኛ ተከሳሽ ኤዶም ካሳዬ በቃሊቲ እስር ቤት አስተዳደር ላይ ከጎብኝዎቻቸው መከልከል ጋር በተያያዘ አቅርበውት በነበረው አቤቱታ ላይ ብይን መስጠት ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም ሁለቱንም አቤቱታዎች ውድቅ አድርጓል፡፡

የሲዲ ማስረጃውን በተመለከተ አቃቤ ህግ ማስረጃዎችን ኢግዚቪት ብሎ ስላስመዘገበ አሁን በዚህ ደረጃ ሲዲዎቹ ለተከሳሾች የሚደርሱበት አግባብ የለም በሚል ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን አቤቱታ እንዳልተቀበለው ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ማስረጃ በመስማት ሂደት ወቅት ማስረጃዎችን እየተመለከቱ መልስ እንዲሰጡ እንጂ ቀድሞ እጃቸው የሚደርስበት አሰራር የለም ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡
ፍርድ ቤቱ የቃሊቲ እስር ቤት አስተዳደር ላይ በሁለቱ ሴት ተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታም ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታ እና የእስር ቤቱ አስተዳደር የሰጠውን መልስ መመልከቱን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ “ለቀረበው አቤቱታ ማስረጃ ተያይዞ ያልቀረበ በመሆኑ…” በሚል አቤቱታውን ቅድቅ አድርጓል፡፡ ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ከሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2007 ጀምሮ ለሦሰት ቀናት ይሰማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ድብደባ ተፈፀመባቸው

የህግ ባለሙያና ጠበቃ ተማም አባቡልጉ

የህግ ባለሙያና ጠበቃ ተማም አባቡልጉ

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በዘለዓለም ወርቃገኘው የክስ መዝገብ የተከሰሱት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በመያዝ የሕግ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ድብደባ ተፈፀመባቸው፡፡ ድብደባው የተፈፀመባቸው ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ..ም. እነ አብርሃ ደስታ በነበራቸው የፍርደ ቤት ቀጠሮ ተገኝተው የሚጠበቅባቸውን የሕግ አገልግሎት ሰጥተው ከፍርደ ቤት ከወጡ በኋላ ብሔራዊ አረቄ ፋብሪካ አካባቢ ወደ አዋሳ ለሌላ የህግ አገልግሎት ለመስጠት እያመሩ በነበረበት ወቅት በማያውቁት ግለሰብ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክታል፡፡

ደብዳቢው ግለሰቡ ድብደባ ከፈፀመ በኋላ እሮጦ ለማምለጥ ሲሞክር በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ትብብር የተያዘ ሲሆን፤ በወቅቱም ደብዳቢው የአእምሮ ችግር እንዳለበት ለመምሰል ከሞከረ በኋላ የብአዴን-ኢህአዴግ አባል እንደሆነና 400 ብርም እንደተከፈለው መናገሩን እንዲሁም አዲስ አበባ ለቡ አካባቢ 105 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቶት ቤት እየሰራ እንደሆነ መግለፁን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጠበቃ ተማም ነገ አዋሳ ላይ ሌላ የነ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ የፍርድ ቤት ጉዳይ ስላለ ዛሬ የግድ ሄደው ማደር ስለነበረባቸው ደብዳቢውን እንዲለቀቅ አድርገው ወደ አዋሳ ማምራታቸው ታውቋል፡፡

ጠበቃ ተማም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በተጨማሪ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን፣ የተለያዩ ጋዜጠኞችን፣በሀገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን እና ሌሎች በርካታ የህግ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ለማኀበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከጥብቅና አገልግሎት በተጨማሪ በተለያዩ ጋዜጦች የህግ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ይፅፉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚህም ከመንግሥትና ከስርዓቱ ደጋፊዎች ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ቅጣት ተላለፈባቸው

᎐ተጨማሪ ቅጣትም ይጠብቃቸዋል፡፡
• “እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው” አብርሃ ደስታ
• “ችሎቱ ላይ ያጨበጨብነው በማፌዝ ሳይሆን በምሬት ነው”  የሺዋስ አሰፋ
• “ፍትህ ተጠምተናል፣ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!”  ዳንኤል   ሺበሽ

politician prisoners

በዘለዓለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ከስምንት ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነት እንዲሁም የዓረና ትግራይ ፓርቲዎች አመራሮች ‹ችሎት በመድፈር ወንጀል› ጥፋተኛ በመባላቸው ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት በሦስቱ አመራሮች ላይ እያንዳንዳቸው በሰባት ወራት እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡

የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም ተከሳሾች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸውና ንብረትም እንደተወሰደባቸው በመግለጽ አቅርበውት ለነበረው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ሙሉ ለሙሉ በመቀበል አቤቱታቸውን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ 5ኛ ተከሳሽ አቶ የሺዋስ አሰፋ በማጨብጨቡና 3ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታና 4ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሽ ሳይፈቀድላቸው ‹‹ጥሩ ፍርድ፣ ጥሩ ብይን›› በማለት አቶ የሺዋስን በመደገፍ ችሎት ደፍረዋል ተብለው ጥፋተኛ መሰኘታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ ለዛሬ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት  ተሰይሞ በአብርሃ ደስታ፣ በየሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽ ላይ የ7 ወራት እስራት በይኖባቸዋል፡፡ ሦስቱም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ድጋሜ ችሎት ውስጥ አጨብጭበዋል፡፡ በዚህም ድጋሜ ጥፋተኛ ተብለዋል፤ ከሁለት ቀናት በኋላም የቅጣት ውሳኔ ይወሰንባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሦስቱ ተከሳሾች ‹‹እድል ስጡን እንናገር፣ አቤቱታም አለን ተቀበሉን›› ቢሉም ፍርድ ቤቱ ሊሰማቸው አልፈለገም፡፡

በተለይ ዳንኤል ሺበሺ ‹‹ሌላ አቤቱታ አለኝ፣ ፍርድ ቤቱ ያዳምጠኝ›› ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ አሁንም ችሎቱ ላይ እያፌዛችሁ ነው በሚል ጥፋተኛ ሲላቸው ሦስቱም አመራሮች ፍርድ ቤቱን ማስፈቀድ ሳያስፈልጋቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው፡፡ ‹Already› የተደፈረ ችሎት ነው›› ሲል አብርሃ ደስታ ተናግሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ዳኞቹ ጣልቃ በመግባት፣ ‹‹የምትናገረው ነገር እንደገና ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሚወስድህ ጉዳይ ነው፤ ምርመራ ይደረግበታል›› ሲሉ አብርሃ በበኩሉ ‹‹አሁንስ ቢሆን የምናገረውን ፖሊስ እየሰማ አይደለምን?›› ሲል መልሷል፡፡ አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ ‹‹ከስምንት ወር በላይ ታፍነናል፡፡ በህግ አይደለም የተያዝነው፡፡ ደግሞ ማጨብጨባችን በችሎቱ ከማፌዝ ሳይሆን ከምሬት በመነጨ ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ  መብታችን ተጥሷል፡፡ እኔ ለምሳሌ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆኔ ነው የታሰርኩት፡፡›› ብሏል፡፡

አቶ ዳንኤል ሺበሽ ድግሞ ‹‹አሁንም ችሎት ደፍራችኋል ካላችሁ ቅጣቱን ጨምሩብንና ሸኙን፡፡ በእርግጥ ዳኞች ላይ ያለውን ጫና እንረዳለን፡፡›› ሲል ችሎት ውስጥ ተናግሯል፡፡
በዚህ ሁኔታ በተከሳሾችና በችሎቱ መካከል ያለው አለመግባባት ሲጨምር ዳኞቹ መጋቢት 3/2007 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የቅጣት ውሳኔ እንደሚሰጥ በመጥቀስ ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት በፖሊስ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ከችሎት እየወጡ እያሉም አቶ ዳንኤል ሺበሽ ‹‹ፍትህ ተጠምተናል፤ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!›› እያለ ችሎቱን ለቅቆ ወጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት መውጣታቸውን ተከትሎ፣ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቱ ላይ በቀረበው አቤቱታ ዳኞች በሰጡት አስተያየት ላይ አቤቱታ አቅርቦ እንደነበር በማስታወስ አቤቱታው እንዲመዘገብለት የጠየቀው አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ‹‹በበኩሌ ያሉኝን መረጃዎች እያቀረብኩ ስነ-ስርዓቱን አክብሬ ክርክሩን አቀጥላለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ- ኢትዮጵያ

በአዲስ አበባና በክልሎች በርካታ ኢትዮጵውያን ሙስሊሞች በመንግሥት እየታሰሩ መሆኑ ተሰማ

Ethio-muslims protest

ከጥር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ የኃይማኖት ነፃነት መብትና ህገ-መንግሥቱ እንዲከበር፤ በሰላማዊ መንገድ እየጠየቁ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሙስሊሙ ማኀበረሰብ  የመንግሥትን ህገወጥ እርምጃ ተቃውሞ መቀጠሉን ተከትሎ፤አሁንም በያዝነው የካቲት 2007 ዓ.ም. ከየቤቱና ከስራ ቦታ ጭምር የጅምላ እስሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የክልል ከተሞች የሚመጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የመንግሥትን ያይል እርምጃ እና የኃይማኖት ነፃነት መብታቸው እንዲከበርና መንግሥትም ከኃይማኖት ጣልቃ ገብነት እንዲወጣ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ተከትሎ ሰሞኑን የጅምላ እስር እየተካሄደ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

Anuwar mosque protest

የጅምላ እስሩ እየተከናወነ የሚገኘው መንግሥት በመጪው ምርጫ 2007 ዓ.ም. ከሙስሊሙ ማኀበረሰብ ድጋፍ እንደሌለው በመረዳቱና በርካቶችም የድምፅ መስጫ በረቀት መውሰዳቸው የደረሰው መረጃ አስደንግጦት እንደሆነ ቢጠቆምም፤ ከመንግሥት በኩል ግን እየተወሰደ ስላለው የጅምላ እስር የተሰጠ  ምንም ዓይነት ማብራሪያም ሆነ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በተለይ ሰሞኑን በተወሰደውና እየተወሰደ ባለው የጅምላ እስር ተጠናክሮ መቀጠሉን ከመጠቆም ባለፈ፤እስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደታሰሩ ግን ለማወቅ አልተቻለም፡፡

ከዚህ ቀደም መንግሥት የኢትዮጵያ ሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ጋር ሲደራደር ቆይቶ፤ በመጨረሻም በጅምላ በማሰር የሽብር ክስ መስርቶባቸው የኮሚቴው አባላት ያለምንም ፍትህ እስካሁን በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡