ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የሽብርተኝነት ክስ ተመሰረተበት
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው

የፌደራል አቃቤ ህግ ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም በተጻፈ የክስ ማመልከቻ የሽብር ክስ የመሰረተበት የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ የቀረበው ክስ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) ላይ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት መተላለፍ የሚል ነው፡፡
ተከሳሹ ከ24/05/2006 ዓ.ም እስከ 13/04/2008 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ግንቦት ሰባት ከተባለ የሽብር ድርጅት አመራሮች ጋር በማህበራዊ ድረ ገጽ በተለይም ፌስቡክ እና ስልክ ግንኙነት በመፍጠር ለሽብር ቡድኑ ተልዕኮ የተለያዩ መረጃዎች በማስተላለፍና በሽብር ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል ፈጽሟል ሲል አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ጠቅሷል፡፡
በአቃቤ ህግ ክስ ላይ እንደተመለከተው ተከሳሽ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በህግ ተመዝግቦ በሀገር ውስጥ ህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርገው ሰማያዊ ፓርቲ አባላት ጋር ያደረገው የመልዕክት ልውውጥ ክስ ሆኖ ቀርቦበታል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ከተለያዩ ውጭ ሀገር ከሚገኙ ሚዲያዎች ባለሙያዎች በተለይም ኢሳት ጋር ያደረጋቸው ቃለ-መጠይቆችና የመረጃ ልውውጦችም በሽብር ክስነት ቀርበውበታል፡፡ ተከሳሹ በሽብርተኝነት ክስ ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ቤተሰቦቻቸውን እንዴት ማገዝ ይቻላል በሚል ከዳያስፖራ አባላት ጋር በማህበራዊ ድረ ገጽ የተለዋወጣቸው መልዕክቶችም በክሱ ላይ ተካተው ቀርበዋል፡፡
በአጠቃላይ ጌታቸው ‹‹…በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር እየተገናኘ መረጃ በመሰብሰብ በውጭ ሀገር ለሚገኙ የሽብር ቡድኑ አመራሮች መረጃ በማስተላለፍ….›› በሽብር ድርጅት ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ለአምስት ወራት በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት ክስ ተመስርቶበት ቂሊንጦ በእስር ላይ ይገኛል፡፡ ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም የቀረበበት ክስ በፍርድ ቤት ሊነበብለት ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የዕንቁ መፅሔት አምደኛ፣ የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ መስራች አባልና የጊዜያዊ አስተባባሪው አመራር እንዲሁም አዲስ ሚዲያ ተባባሪ እና በራሱ የማኀበራዊ ገፅ ብሎገር እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ምንጭ፡- EHRP.
ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ 5 ዓመት ከ4 ወር ቅጣት እስር ተበየነበት
( አዲስ ሚዲያ) የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በዘለዓለም ወርቅአገኘሁ ላይ 5 ዓመት ከ4 ወር የእስር ቅጣት ተበየነበት፡፡ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ የደ ብርሃን ድረ-ገፅ ተባባሪ ብሎገር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ድህረ-ምረቃ ተማሪ የነበረ ሲሆን፤ በውጭ ሀገር የኢንተርኔት ደህንነት ስልጠና ለመውሰድ ማመልከቱ “ለሽብር ተግባር ተሰናድተዋል” በሚል በተመሰረተበት ክስ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ሲል መበየኑ ታውቋል፡፡

በዘለዓለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ ዘለዓለምን ጨምሮ 10 ተከሳሾች ከሰኔ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ ሆነው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታየ የነበረ ቢሆንም፤ የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አመራር አባላት የነበሩት አቶ ሃታሙ አያሌው እና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበረው የሺዋስ አሰፋ፣ የዓረና ትግራይ/መድረክ አመራር አባል አቶ አብርሃ ደስታ እንሁም መምህር አብርሃም ሰለሞን በተመሰረተባቸው ክስ በነፃ መሰናበታቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ አቶ አብርሃ ደስታ ይህ ዜና እስከተዘገበበት ድሰር አሁንም በእስር ላይ ይገኛል፡፡
እነ ጌታቸው ሽፈራው ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው
*”ከቤተሰቦቻችን ጋር እንዳንገናኝ ተደርገናል” ተጠርጣሪዎች
*”6 ቀን ደንበኛየን ለማግኘት ተመላልሼ ተከልክያለሁ” የጋዜጠኛ ጌታቸው ጠበቃ አምሃ መኮንን

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከታህሳስ 15/2008 ዓ.ም ጀምሮ በማዕካለዊ ወንጀል ምርመራ በእስር ላይ የሚገኙት እነ ጌታቸው ሺፈራው ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በእነ ዳንኤል ተስፋየ ስም በተከፈተው የምርመራ መዝገብ ስር የተካተቱት ሦስት ተጠርጣሪዎች አቶ ዳንኤል ተስፋየ፣ አቶ ሸዋታጠቅ ኃ/መስቀል እና ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ሲሆኑ፣ ተጠርጣሪዎች ዛሬ ጥር 14/2008 ዓ.ም ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ቀርበው ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ብሎ ጠይቆ የ27 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋ፡፡
ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ የጠየቀበትን ምክንያት ለፍርድ ቤት ያስረዳ ሲሆን ‹‹የቴክኒክ ማስረጃዎችን ከብሄራዊ ደህንነትና መረጃ ኤጀንሲ ጠይቀን ማስመጣትና ተጨማሪ ግብረ አበሮችን መያዝ ይቀረናል›› ብሏል፡፡
ተጠርጣሪዎች ከተያዙበት ቀን ጀምሮ በማንም እንዳይጎበኙ መከልከላቸውን በማስረዳት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ‹‹ከተያዝኩ ጀምሮ ቤተሰቦቼን አይቼ አላውቅም፡፡ እስር ላይ ሆኜ በቀን ለ10 ወይም 15 ደቂቃዎች ነው የጸሐይ ብርሃን የማገኘው፤ ይሄ እንዲስተካከልልኝ ፍርድ ቤቱን እጠይቃለሁ›› ሲል ያመለከተ ሲሆን፣ አቶ ሸዋታጠቅ ኃ/መስቀል በበኩሉ፣ ‹‹ቤተሰቦቼን ያየኋቸው ዛሬ ችሎት ስመጣ ከርቀት ነው፤ ቤተሰቦቼን እንዳይ ይፈቀድልኝ›› በማለት እያነባ ጠይቋል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ደግሞ በጠበቃው በኩል ያለውን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል፡፡ ጠበቃው አቶ አምሃ መኮንን ለስድስት ቀናት ማዕከላዊ ደንበኛቸውን ለማነጋገር ቢመላለሱም ከበር ላይ እንዲመለሱ በመደረጋቸው ከደንበኛቸው ጋር ሳይነጋገሩ ፍርድ ቤት መቅረባቸው አግባብ አለመሆኑንና ድርጊቱ ህገ-መንግስቱን የሚጣረስ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹‹ደንበኛየን ያገኘሁት አሁን ነው፡፡ ደንበኛየ የምንፈልገውን ነገር ሳናገኝ ከጠበቃህ ጋር አናገናኝህም ተብሏል፡፡ ይህ በህገ-መንግስቱ የተሰጠውን መብት የጣሰ ተግባር ነው፡፡ አሁንም ደንበኛየ፣ ከዚህ በኋላ እኔን ሳያነጋግር ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ፍርድ ቤቱ እንዲመዘግብልኝ እፈልጋለሁ›› ሲሉ ጠበቃ አምሃ መኮንን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው እስካሁን በቤተሰብም ሆነ በጓደኞቹም እንዳይጠየቅ መከልከሉ የህግ አግባብ የሌለው የመብት ጥሰት ነው ብለዋል ጠበቃ አምሃ፡፡
ጠበቃ አምሃ ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ የጠየቀበት ምክንያት ደንበኛቸው የዋስትና መብቱ ተከብሮለት ሊከናወን እንደሚችል በማስረዳት የዋስትና መብት እንዲከበርለት ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን በሁሉም ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ለየካቲት 11/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከሦስት ወራት በላይ በማዕከላዊ በእስር ላይ የሚገኙት በጋሞ ጎፋ አርባምንጭ የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪዎች እነ ሉሉ መሰለ እና አየለች አበበ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ‹የመጨረሻ› ነው የተባለለትን ተጨማሪ የ28 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ኢትዮጵያ
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ታሰረ
የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ዛሬ ታህሣሥ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት ለስራ ከቤቱ ሲወጣ በፌደራል ፖሊሶችና በደህንነት ሰዎች ተይዞ ታስሯል። የፀጥታ ኃይሉ መኖሪያ ቤቱን ከፈተሹ በኋላ ፣ጋዜጠኛውን ወደ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል ማዕከላዊ መስደው ማሰራቸው ቢገለፅም፤ መንግሥት ጋዜጠኛውን ለምን እንዳሰረ የገለፀው ነገር የለም፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ከመሆኑ በተጨማሪ የእንቁ መፅሔትም ፀሐፊ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት በመንግሥት ኃይሎች ከፍተኛ ማስፈራሪያና ዛቻ ይፈፀምበት እንደነበርም ታውቋል፡፡ጌታቸው ነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣን እና ደረ- ገፅን ጨምሮ በተለያዩ ድረ-ገፆችና የራሱ ማኀበራዊ ገፅ ላይ የተለያዩ ሐሳቦችን ይፅፍ እንደነበርም ይታወቃል፡፡
ከጋዜጠኛ ጌታቸው በተጨማሪ በተደጋጋሚ ሲታሰሩና ሲፈቱ የነበሩት ሶስቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት መካከል ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርምያስ ፀጋዬ እና ቴዎድሮስ አስፋው ዛሬ መታሰራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ባለፈው ቅዳሜ ታህሣሥ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት አዲስ አበባ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ የታሰረውና የኦሮሚያ ሬዲዮናቴሊቪዥን ዜና አንባቢ ጋዜጠኛ ፈቃዱ ምረከና አለመፈታቱ ታውቋል፡፡ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ጋዜጠኛ ፈቃዱ ምርከናም ሆነ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በምን ምክንያት እንደታሰሩ ከመንግሥት በኩል የተገለፀ ነገር የለም፡፡

ከጋዜጠኛ ፈቃዱ እና ጌታቸው በተጨማሪ በርካታ ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙና በዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች ድርጅቶች፤ ኢትዮጵያም ጋዜጠኞችን በማሰር ከአፍሪካ የሁለተኛ ደረጃን ተቀዳጅታ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የዞን 9 ብሎገሮች የ2015 የዓመቱን የፕሬስ ነፃነት ሽልማት ተቀበሉ
በአሜሪካ ኒዮርክ ከተማ ዋና ቢሮውን ያደረገው ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (Committee to Protect Journalists) በዘንድሮው የ2015 የዓመቱ የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ላበረከቱት አስተዋፅዖ ኢትዮጵያውያኑ ዞን 9 ብሎገሮች ሽልማት ተቀበሉ፡፡ በስፍራው ማክሰኞ ህዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በተከናወነው ምሽት የዞን 9 አባላት መካከል እንዳልካቸው ኃይለሚካኤል እና ሶሊያና ሽመልስ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡

ሀገር ቤት የሚገኙት ቀሪዎቹ የዞን 9 አባለት ከአንድ ዓመት እስር ቆይታ በኋላ ቢለቀቁም ከሀገር እንዳይወጡ የጉዞ እገዳ የተጣለባቸውና የጉዞ ሰነድ የተነጠቁም እንዳሉ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ለፕሬስ ነፃነት በሀገሪቱ ውስጥ ላበረከቱት አስተዋፅዕ ሲፒጄን ጨምሮ መቀመጫውን በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረገው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የዓለም አቀፍ ተሸላሚ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በዕለቱ በእንግድነት የተገኘችው በቅርቡ የተፈረደባትን እስር አጠናቃ ከእስር የወጣችው ርዕዮት ዓለሙ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላታል፡፡ በያዝነው ዓመት የሲፒጄ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ከኢትዮጵያውያኑ ዞን 9 በተጨማሪ ሶሪያዊ እና ማሌዥያዊ ጋዜጠኛ እና አክቲቪስቶችም ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በተመሳሳይ ከ አምስት ዓመት በፊት የቀድሞው የአውራምባ ታየምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ዳዊት ከበደ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ሲፒጄ ዓለም አቀፍ የሃዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲሆን፤በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት በፕሬስ ነፃነት እና በጋዜጠኞች ላይ የሚወስደውን አፈና አጥብቆ በመኮነን ይታወቃል፡፡