Tag Archives: Tigray Regional State

በጎንደር በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 ያላነሱ ሰዎች ሲገደሉ፤ በአካባቢው ውጥረቱ እንደቀጠለ ነው

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኘው ጎንደር ከተማ፤ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት ጀምሮ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 ያላነሱ ዜጎች መገደላቸው ተጠቆመ፡፡ መረጃዎች እንደሚመለክቱት ከሆኑ፤ 10 ያህል ንፁሃን ዜጎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ ርምጃ መገደላቸውን ተከትሎ፤ ህዝቡ በወሰደው የአፀፋ እርምጃ 9 የፌደራል ፖሊስ እና 1 የመከላከያ ሰራዊት አባል ተገድለዋል፡፡

በስፍረው የሚገኙ የዓይን እማኞች በበኩላቸው የተገደሉ ሶወች ቁጥር ከተጠቀሰው እንደሚልቅ ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ በግጭቱ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ እስካሁን ከገለልተኛ አካልም ሆነ ከመንግሥት የተሰጠ ማረጋገጫ የለም፡፡

Gonder Protest

ባለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በህዝቡ መካከል በተፈጠረ ግጭት በጎንደር ለሁለት ተከታተይ ቀናት የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደሌሎች አጎራባች ከተሞች መዛመቱ ተሰምቷል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞውም ሐሙስ ወደ ዳባርቅ ከተማ የተዛመተ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ወደ ሳንጃ ወረዳ እና ወደ ሌሎች አጎራባች ከተሞችና ወረዳዎች መዛመቱ እየተነገረ ነው፡፡

car buring in Gondar

በተፈጠረው ግጭትም የሰው ህይወትን ጨምሮ የህወሃት እና የደጋፊው ናቸው የተባሉ ንብረቶች መውደምንም አስከትሏል፡፡
የግጭቱ መንስኤ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የአማራ ማንነትና ተያያዥ መብታቶቻችን ይከበሩልን የሚል ጥያቄን ለትግራይ ክልላዊ መስተዳደርና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲያቀርቡ የነበሩ ተወካይ ኮሚቴዎችን ከሚኖሩበት ጎንደር ከተማ የትግራይ ክልልና የፌደራሉ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና የደህንነት አባላት ለማፈን እና ለማሰር በወሰዱት የኃይል እርምጃ በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተለይ ከወልቃይት የአማራ ማንነት ተወካይ ኮሚቴዎች መካከል ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፤ ሊያግቷቸው የመጡ የፀጥታ ኃይሎችን “ህጋዊ ከሆናችሁ በቀን መምጣት ትችላላችሁ፤ ካልሆነ በሌሊት እኔ እጄን ለማንም አልሰጥም” ማለታቸውን ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባት፤ ህዝቡ የመንግሥት ኃይሎችን የሌሊት እገታና ሌሎች 4 የኮሚቴ አባላትን እስርና እገታ በመቃወም ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት እንደተፈጠረ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

በጎንደር በተፈጠረው አለመረጋጋት የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥታት ዜጎቻቸው ወደጎንደርና አቅራቢያው ከመሄድ እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል፡፡ እስራኤል በበኩሏ በጎንደር የሚገኙ 6 ሺህ ቤተ እስራኤላውያንን እና በስፍራው የሚገኙ በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ ተወካዮችን ደህንነት በተመለከተ ከፍተኛ ቁጥጥር ወደሚደረግበት ስፍራ ጥበቃ እያደረገችላቸው መሆኑን የኢየሩሳሌም ፖስት ዘገባ አመልክቷል፡፡

በጎንደር ግጭቱ ለጊዜው የተረጋጋ ቢመስልም፤ አሁንም በአካባቢው በመንግሥትና በህዝቡ መካከል ከፍተኛ ውጥረት መኖሩ እየተገለፀ ነው፡፡

የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ…

ከዚህ ቀደም በቤጌምድር (ጎንደር) ጠቅላይ ግዛት የነበሩና ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የትግራይ ክልል ስር ያሉት የወልቃይት ጠገዴ ማኀበረሰብ “እኛ አማራ ነን፣ ያለፈቃዳችን ተገደን ነው ወደ ትግራይ የተካለልነው፣ የአማራ ማንነት ጥያቄያችን ተመልሶ ወደነበርንበት ጎንደር አማራ እንጠቃለል” የሚል ጥያቄን ቢያነሱም፤ ከመንግሥት በኩል እስካሁን ምላሽ አላገኙም፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ማኀበረሰብ አባላት ተገደው ያለፈቃዳቸው ወደ ትግራይ እንድንጠቃለል ተደርገናል ከሚለው ጥያቄ በተጨማሪ አማራ በመሆናችን ብቻ በትግራይ ክልል አስተዳደር ከፍተኛ በደል ተፈፅሞብና፤እየተፈፀመብንም ይገኛል በማለት የቀደመው የአማራ ማንነታችን ተመልሶ ወደነበርንበት ጎንደር አስተዳደር አማራ ክልል ለመጠቃለል አንዱ ምክንያታቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልፁ ይስተዋላል፡፡

Wolkite Tegedie

እንደ ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴዎች አገላለፅ፤የነበረው የወልቃይት ጠገዴ አስተዳደር ወሰን ክልልም በሰሜን ተከዜ ወንዝ፣ በሰሜን ምዕራብ ኤርትራ፣ በምስራቅ የቀድሞው ትግራይ ጠቅላይ ግዛት ፣ በምዕራብ ሱዳን በደቡብ የቀድሞው ቤጌምድር (የአሁኑ ጎንደር) አስተዳደር አካል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አካባቢውም በአሁን ወቅት በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን በሚል አስተዳደር ስር በ3 ወረዳዎች የተዋቀሩት ቃፍታ ሁመራ፣ ወልቃይት እና ጠገዴ ወረዳዎች በቀድሞ ቤጌምድር (ጎንደር) ጠቅላይ ግዛት ወልቃይት ጠገዴ አውራጃ አስተዳደር እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ቀደምት የአስተዳደር ሰነዶችን እና የአማራ ማንነትን ያረጋግጣሉ የሚሏቸው መረጃዎችን አያይዘው በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ጥያቄ ቢያቀርቡም ከሚመለከተው አካል እስካሁንም ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

በተለይ የወልቃይት ጠገዴ ማኀበረሰብ ተወካዮች የአማራ ማንነት ጥያቄ ይዘው ላለፉት 25 ዓመታት ጀምሮ ጥያቄ ያቀርቡ እንደነበር እንደሚያውቁ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲአዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አስታውሰዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ይህን ያስታወሱት ባለፈው ከኦሮሚያ እና በሌሎች ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ በተያያዘ መድረክ በዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ላይ ነበር፡፡
የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላቱም በተለያየ ጊዜ በተለያየ መገናኛ ብዙኃን እንደገለፁት ከሆነ፤ አማራ ሆነው ሳለ ሳይወዱ በግድ ወደ ትግራይ መጠቃለላቸውን፣ ልጆቻቸውም ከአፍ መፍቻ አማርኛ ውጭ ተገደው በትግርኛ እንዲማሩ መደረጉን፣ የአካባቢው ህዝብ ከአማርኛ በተጨማሪ አረብኛ እና ትግርኛም ባላቸው የድንበር ግንኙነት አማካኝነት መናገር ቢችሉም፤ ባህላቸውን እና ማንነታቸውን የሚገልፁበት ቋንቋ አማርኛ መሆኑን እና የማንነት ስነ ልቦናቸውም አማራ እንደሆነ፤ ይህንንም ላለፉት 25 ዓመታት በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ተቋማት ጥያቄ ሲያነሱ ግድያ፣ እስራት፣ ድብደባ፣ ማስፈራራትና ስደት እንደደረሰባቸው፣ ከጥያቄው ጋር በተያያዘ የትግራይ ክልል መስተዳደር ግድያን ጨምሮ የተለያዩ በደሎችንም ይፈፅም እንደነበርና አሁንም እየፈፀመ እንደሆነ ሲያነሱ ይደመጣል፡፡

የአማራ ማንነት ፈቃዳችን ሳይጠየቅ ተገደን እንድንጠቃለል ተደርገናል ለሚሉት የትግራይ ክልል መስተደዳደርና በፌደራሉ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄን የሚያቀርቡ ተወካዮች በአዲስ አበባም ለተወሰኑ ቀናት በፖሊስና ደህንነት አባላት ታግተው መለቀቃቸው የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮን ጨምሮ በተለያየ መገናኛ ብዙኃን የተዘገበ ሲሆን፤ በተለይ የትግራይ ክልል አስተዳደርና እና የክልሉ ምዕራባዊ ዞን የመንግሥት ኃላፊዎች አሁንም ከፍተኛ ማስፈራሪያ እና ዛቻ እየፈፀሙ መሆኑን የኮሚቴው አባላት ገልፀዋል፡፡ አዲሱን የአስተዳደር ክልል መዋቅር የመሰረተው ኢህአዴግ መንግሥት እና የትግራይ ክልል መስተዳደር ቀድሞ የነበረውን የአማራ ስነ ህዝብ ስብጥር፣ ባህል እና ማንነትን ለማጥፋትና መቀየር ላለፉት 25 ዓመታት ሙሉ ሲሰሩ ተቃውሞ ብናቀርብም ሰሚም አላገኘንም፣ እንደወንጀለኛም ተቆጥረናል ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ ከዛ በተጨማሪ የእኛ የአማራ ማንነት እንደሌለ ተቆጥሮና ተክዶ ልጆቻችን በአማር እንዳይማሩና እንዳይናገሩ፣ በአማራ ማንነታቸው እንዲያፍሩና የነበረውን የአማራ ማንነት ባህል እንዳያንፀባርቁ ተደርገዋል፤ በግድም የትግርኛ ቋንቋ እንዲነገሩ፣ የትግራይ ማንነት ባህልን ብቻም እንዲያንፀባርቁ ተደርገዋል፤ይህም ህገ-መንግሥቱን እንደሚፃረር ብናነገርም የከፉ በደሎች ተፈፅመውብናል ይላሉ፡፡

በተለይ አካባቢውን በተመለከተ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን የትግራይ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ የነበሩትና የአጼ ዮሐንስ 4ኛ የልጅ ልጅ የሆኑት ልዑል መንገሻ ስዩም ወልቃይት ጠገዴ በሳቸው ዘመንም ሆነ ከዛ በፊት ወልቃይት ጠገዴ በትግራይ አስተዳደር ስር እንዳልነበር እንደሚያውቁ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ገልፀው ነበር፡፡ የትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን አስተዳደር ሃላፊ በኩላቸው ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ እንደሆነ እና ከዛ ጋ ተያይዞ የሚነሳ የማንነት ጥያቄ የህዝቡ እንዳልሆነ ከመግለፃቸው በተጨማሪ የአማራ ማንነት ጥያቄ የሚያነሱ ተወካዮች የሚቃወም ሰልፍም በአካባቢው ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአማራ ማንነት ጥያቄን ለሚያነሱ ማኀበረሰብ አባላትና ተወካዮች ጥያቄያቸው መፍትሄ አሊያም ህዝባዊ ውሳኔ ያገኝ ዘንድ ባሉበት ወልቃይት ጠገዴ ህዝባዊ ስብሰባና ሰልፍ ቢጠይቁም በትግራይ ክልልም ሆነ በክልሉ ምዕራባዊ ዞን አስተዳደር ሊፈቀድ ባለመቻሉ የማኀበረሰቡ ተወካዮች ህዝባዊ ስብሰባዎቻቸውን በአጎራባች የአማራ ክልል ከተሞች ለማድረግ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስለ ኦሮሚያው ተቃውሞ እና ስለ ጎንደር የቅማንት ማኀበረሰብ ማንነት ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ችግር ቢገልፁም፤ ስለ ወልቃይ ጠገዴ አማራ ማንነት ጥቄን ግን ሳያነሱት ከማለፋቸው በተጨማሪ በጥቅሉ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ከማንነት ጋር በተያያዘ ያልተመለሰ ጥያቄ የለም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አዲስ ሚዲያ ባለው መረጃ መሰረት የብሔረሰብ ማንነት እና የራስ አስተዳደር ጋ በተያያዘ በትግራይ ወልቃይት ጠገዴን እና በኣማራ ክልል ምላሽ አግኝቷል ከተባለው የቅማንት ማኀበረሰብ ማንነት ጥያቄ በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ከክልሎቹ እስከ አዲስ አበባው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ እስካሁንም ምላሽ ያላገኙ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡

%d bloggers like this: