Tag Archives: TPLF/EPRDF democracy

መድረክ ከኢህአዴግ ጋር በአስቸኳይ መወያየት እፈልጋለሁ አለ

በምርጫው ሂደት ላይ ቅሬታዎች አሉኝ ብሏል

የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና

የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና

የግንቦቱ ምርጫ ሂደት ላይ ቅሬታዎች እንዳሉት የገለፀው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤ በጉዳዩ ላይ ከገዥው ፓርቲ ጋር በአስቸኳይ መወያየት እንደሚፈልግ አስታወቀ፡፡

መድረኩ ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በምርጫ ታዛቢዎችና አስፈፃሚዎች አመራረጥና በምርጫው ለሚሳተፉ ፓርቲዎች ከመንግስት በሚሰጠው የድጐማ ገንዘብ ክፍፍል ላይ ቅሬታ እንዳለው ጠቁሟል፡፡

ምርጫውን ለማስፈፀምና ለመታዘብ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ገለልተኛ የሆኑ ሠዎች መመረጥ ያለባቸው ቢሆንም በቅርቡ የተመረጡት አስፈፃሚዎች አብዛኞቹ የገዥው ፓርቲ አባላት መሆናቸው እየታወቀ “የማንም ፓርቲ አባላት አይደለንም” እያሉ ፈርመው ወደ አስፈፃሚነቱ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል ሲል ፓርቲው ቅሬታውን ገልጿል፡፡

መንግስት ለፓርቲዎች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጐማ በተመለከተም ገንዘቡ ለሚመለከታቸው ፓርቲዎች ብቻ በአግባቡ እንዲከፋፈል ጠይቋል፡፡ “ከመንግሰት ካዝና ወጥቶ ታማኝ ለሚባሉ ፓርቲዎች እየተከፋፈለ ያለው ገንዘብ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን” ብሏል መድረኩ፡፡ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ያልሆነው መድረኩ፤ ጉዳዩ ከፖለቲካ ሙስና ተለይቶ አይታይም ብሏል፡፡

ቦርዱ፤ ፓርቲዎች በፓርላማና በክልል ምክር ቤት ባላቸው መቀመጫ እንዲሁም በሚያቀርባቸው እጩዎች ብዛትና የሴቶች ተሳሣትፎን መሠረት አድርጐ ገንዘቡን ለማከፋፈል መወሰኑን የተቃወመው ፓርቲው፤ በተለይ የምክር ቤት መቀመጫ የሚለው መስፈርት ኢህአዴግን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው ብሏል፡፡

“በምክር ቤት መቀመጫ ብቻ ኢህአዴግ 55 በመቶውን ድርሻ ያገኛል፤ ቀሪው 45 በመቶ 59 ፓርቲዎች የሚከፋፈሉት ይሆናል” ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ኢህአዴግ በድልድሉ የደረሰውን 10ሚ.ብር የጋራ ምክር ቤቱ አባል ለሆኑ ፓርቲዎች ማከፋፈሉ ይታወሳል፡፡

የመድረክን ተቃውሞና ቅሬታ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደምሰው በንቲ በበኩላቸው፤ የህዝብ ታዛቢዎቹ ምርጫ የተከናወነው ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ራሳቸው የፓርቲ ተወካዮች በተገኙበት፣ ተአማኒነት ባለው መልኩ በመሆኑ የቀረበው ቅሬታ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ውድቅ አድርገዋል፡፡ ከገንዘብ ክፍፍሉ ጋር ተያይዞ ከመድረክ በመግለጫ መልክ ቅሬታ መቅረቡ አግባብ አይደለም ያሉት ኃላፊው፤ ቦርዱ ክፍፍሉን በተመለከተ ፓርቲዎች ሃሳብ እንዲያቀርቡ በማሰብ እንጂ ሳያማክር በራሱ የማከፋፈል መብት አለው ብለዋል፡፡

(ምንጭ: አዲስ አድማስ ጋዜጣ)

ጎበዝ ጠንከር ነው!

        ግርማ ሰይፉ  (የአንድነት ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት)

ግርማ ሰይፉ
(የአንድነት ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት)

ምርጫ ቦርድ ማንም ይዘዘው ማንም ወይም በግል ተነሳሽነት እያደረገ ያለው ነገር የኢትዮጵያን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ከምን ጊዜውም በለይ ወደኋላ ለመመለስ እንደሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊረዳው ይገባል፡፡ ምርጫ ቦርድ ምርጫ እንዲያሰተዳድር በተሰጠው ኃላፊነት የፓርቲዎች አስተዳደሪ ለመሆን እየቃጣው ያለ ተቋም ነው፡፡ ስናከብረው ለመከበር ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ለዚህ ተቋም መጠናክር የበኩላችንን መወጣት አለብን ብለን የተነሳን ፓርቲዎችን ጭምር እየገፉ አለቆቹን ለማስደሰት ደም ተግቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህን የሚያደርጉትን ሰዎች ደግሞ በህዝብ ፊት ለብይን እንዲቀርቡ በግልፅ ማጋለጥ ይኖርብናል፡፡

ትላንትና ዶ/ር አዲሱ በሚዲያ ቀርቦ የተናገረው በምንም መልኩ አንድነትን አይመጥንም፡፡ የተቀሩት የቦርድ አባላትም ይመጥነናል ካሉ ትዝብት ላይ ይወድቃሉ፡፡ የምርጫ ቦርድ አባላት ሳያገባቸው እንፈትፍት ሲሉ መፈተፍቱን ለእኛ ተዉልን ነው ያልናቸው፡፡ ዶ/ር አዲሱ በሚዲያ የቦርድ ውሳኔ ሊሆን ይችላል ብሎ ካቀረበ በኋላ ዛሬ ታህሳስ 28 ቀን 2007 ቦርድ ተሰብስቦ ውሳኔ ሰጥቶዋል፡፡ ይህን ውሳኔ እንገራችሁ ብለው በስልክ ከጠሩን በኋላ የአንድነት ፓርቲ የወረዳ አባላት የሆኑትንም በተመሳሳይ መልክ ጠርተው ነበር፡፡ ለነገሩ ይህ አካሄድ አንድነትን ስለማይመጥን በፅሁፍ እንዲገልፁልን ነግረናቸው ተመልሰናል፡፡ ለማንኛውም ዶ/ር አዲሱ የሰጠው መግለጫ ይህ መግለጫ እንዲሰጥ የወሰኑትን ጨምሮ ለተቀሩት የቦርድ አባላት ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው፡፡ ቦርዱ ተሰብሰቦ ምንም ዓይነት ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ውሳኔውን ሚዛን የሚያሳጣ መግለጫ ለመስጠት ምን እንዳጣደፋቸው መገመት ቀላል ነው፡፡ በልባቸው የሚደግፉትን ፓርቲ ለማንገስ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፡፡

ልክ የዛሬ አምስት ዓመት አንድነት ላይ ተመሳሳይ ግብ ግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የዚህ ተልዕኮ ፈፃሚዎች ዛሬ ላይ ሆነው ምን እንደተጠቀሙ ሲያሰላስሉ ምን እንደሚሰማቸው ባላውቅም ዛሬ በዚህ ተግባር ላይ የተሰለፉት አባላት ደግሞ ምን እንደሚያደርጉ መጠበቅ ነው፡፡ ለመማር ያልተፈጠረን ሁሉ ምን ማድረግ ይቻላል? ማንም ተላላኪና ላኪ ሆኖ ቢያገለግልም ዛሬ የተሰማኝ ነገር አንድነት በምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን እንደዚህ ዓይነት ተቋማት በምን ያህል ደረጃ ለመዋረድ ዝግጁ እንደሆኑ ለመረዳት የሚያስችል ነው፡፡ አሁንም ትግሉ መራራ፣ የሚያስከፍለው መስዋህትነትም ውድ ሊሆን እንኳን ቢችል የአንድነት አባላት በድል እንደሚወጡት ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ እሩቅ እንደሆነ አውቀን ለጀመርነው ትግል አቋራጭ እንደማንፈልግ መግለፅ ይኖርብናል፡፡

ውድ የአንድነት አባላት ለቀጣይ አንድነት ከምርጫ ቦርድ አሻጥር ለማላቀቅ ለምናደርገው ትግል ቀበቶ ጠበቅ ነው፡፡ ከሰማይ በታች አንድነት ለመፍታት የማይችለው ፈታኝ ነገር ምርጫ ቦርድም ሆነ በውሰጥችን ያሉት ዙንቢዎች ሊያቀርቡ አይችሉም፡፡ ጎበዝ ጠንከር ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ገመና (ክፍል 2)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
(ከዝዋይ እስር ቤት)

temesegen dበዚህ አውድ ለማቅረብ የተገደድኩበትን ዘግናኝ ታሪክ፣ ወደር በሌለው አስከፊነቱ የተነሳ ለንባብ ባላበቃው በወደድኩ ነበር፡፡ ግና! ይህ መንግስታዊ የጭካኔ ተግባር፣ ዛሬም በምስኪን ዜጎች ላይ እየተፈፀመና ብዙዎችን ሰለባ እያደረገ በመሆኑ ህዝቡ ይህን ሊሸሸግ እየተሞከረ ያለውን መከራ ተረድቶ ሥርዓቱን በአደባባይ ዓመፅ “ሃይ!” ይል ዘንድ ትርክቴን ለማጠናቀር ተገድጄያለሁ፡፡ ለእስር ያበቃኝ የጋዜጠኝነት ሙያዬም ተጨማሪ ዕዳ ጭኖብኛል፡፡

“ጄል-ኦጋዴን”

ጄል ኦጋዴን በሱማሌ ክልል ርዕሰ-መዲና የሚገኝ፤ ለ800 እስረኞች ታቅዶ በ1992 ዓ.ም የተገነባ እስር ቤት ነው፡፡ የግቢውን ዙሪያ ከከበበው አጥር በግምት 15 ሜትር ፈንጠር ብሎ ሌላ ተደራቢ የድንጋይ አጥር ተበጅቶለታል፡፡ እስከ ሚያዝያ 24 1999 ዓ.ም ድረስ እስር ቤቱ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ካሉ መሰል ማጎሪያዎች ብዙም የተለየ አልነበረም፡፡ በዚህ በተጠቀሰው ቀን የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ታጣቂዎች፣ አቦሌ እና ሰንደሬ ወታደራዊ ካምፖችን ጨምሮ፣ በነዳጅ ዘይት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ቻይናውያን ባለሙያዎች መኖሪያ ሰፈር ላይ የሰነዘሩትን ከባድ ጥቃት ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞች ብቻ የሚታጎሩበት እስር ቤት ከሆነ ወዲህ ግን በዋይታ የሚናወፅና በደም ጅረት የሚጥለቀለቅ ምድራዊ ሲኦል ለመሆን በቅቷል፡፡ መንግስት በጥቃቱ ከዘጠኙ ቻይናውያን ጋር 74 ሲቪል ዜጎችና ወታደሮች መገደላቸውን ቢያምንም፤ የአካባቢው የአይን እማኞች ከሰራዊቱ ብቻ እስከ 300 እንደተሰዉ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኦብነግ እንደ አል-ቃይዳ እና አል-ሸባብ የአባላቱን አስከሬን ትቶ የመሸሽ ልምድ ስለሌለው በቡድኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት በትክክል ለማወቅ አዳጋች እንደሆነ ቀጥሏል፡፡

የሆነው ሆኖ ከዚህ ጥቃት በኋላ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የሚመራ አምስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያካተተ የደህንነትና (ጄነራል ሳሞራ የኑስ እና ጌታቸው አሰፋ ያሉበት) የፀጥታ ኮሚቴ ተቋቁሞ የሚከተሉትን (ዛሬም ድረስ እየተተገበሩ ያሉ) አስቸኳይ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ ‹‹ከጅጅጋ ውጭ ባሉ በክልሉ ማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል ተሽከርካሪ እንዳይንቀሳቀስ፣ ትዕዛዙን ጥሶ የተገኘ ከነጭነቱም ሆነ ተሳፋሪዎቹ በከባድ መሳሪያ እንዲመታ፤ አብዛኛውን ህዝብ በፍጥነት ከመኖሪያ ቀዬው በማፈናቀል ለቁጥጥር ወደሚያመቹ ከተሞች ማስፈር (በ2006 ዓ.ም መጀመሪያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ካሳ ተክለብርሃን 2300 መንደሮችን ወደ ተመረጠ ቦታ ማስፈሩ እንደተሳካ መናገሩን ልብ ይሏል)፤ ወታደራዊ መኪና ላይ ምንም አይነት የደፈጣ ጥቃት ከደረሰ በአቅራቢያው የሚገኝ መንደርን ያለርህራሄ ማውደም (ለማሳያ ያህልም ፍልቼ፣ ቃሙዳ፣ ሳስባኒ፣ ሁለሌ፣ ለንካይርተ፣ ቻለሌን… የመሳሰሉ ከተሞች ወደ ፍርስራሽነት መቀየራቸውን መጥቀስ ይቻላል) እና ከአንድ ሻምበል ያነሰ ኃይል ለአስቸኳይ ጉዳይም ቢሆን ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ›› የሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚህ በኋላም ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ሳሞራ የኑስ በክልሉ የሚገኘውን የደቡብ ምስራቅ ዕዝ ወታደራዊ አዛዦችን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ሰብስቦ ማብራሪያ ሰጥቶ ሲያበቃ ውሳኔውን ያለምንም ማቅማማት ተግባራዊ እንዲያደርጉት በጥብቅ አሳስቧል፡፡

ደቡብ ምስራቅ ዕዝ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት (ከ1993 ዓ.ም) በኋላ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሰፈረ ሲሆን እስከ ታህሳስ 1999 ዓ.ም ድረስ በሜ/ጀነራል ባጫ ደበሌ ሲመራ ቆይቷል፡፡ ከታህሳስ 1999 እስከ 2000 ዓ.ም ደግሞ ብርጋዴር ጄነራል ስዩም አስተዳድሮታል፤ በዚሁ ዓመት ከጥቅምት እስከ ሚያዚያ ድረስ ባሉት ጊዜያትም በብ/ጄነራል ሙሉጌታ በርሄ ስር የቆየ ሲሆን፤ ከሚያዚያ 2000 ዓ.ም አንስቶ አሁን ድረስ እየተመራ የሚገኘው በሌ/ጄነራል አብርሃም ወ/ማርያም (ቅፅል ስሙ ‹‹ኳርተር››) እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ዕዝ ውስጥ በዋናነት ሶስት ክፍለ ጦሮች (12ኛ፣ 13ኛ እና 32ኛ) ክልሉን ሶማሊያ ድንበር ድረስ እንዲቆጣጠሩት ተመድበዋል፡፡ ሰፈራቸውን ነገሌ ቦረና ያደረጉት 43ኛ እና 44ኛ ክፍለ ጦሮችም፣ ኦጋዴን ድረስ እንዲንቀሳቀሱ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በአናቱም የአግአዚ ኃይል በቀድሞ ምክትል አዛዡ ብ/ጄኔራል ገ/መድህን ፈቀደ (‹‹ወዲ ነጮ››) ስር ሆኖ አልፎ አልፎ በተደራቢነት እየተላከ በነዋሪዎቹ ላይ በደረሰው ጅምላ ጭፍጨፋ እና ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፈ ስለመሆኑ ከወታደራዊ መረጃ ምንጮቼ ሰምቻለሁ፡፡ ይህም ሆኖ ለደረሱ እልቂቶችና ጭፍለቃዎች በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂ ተደርገው የሚጠቀሱት ከጄነራል ሳሞራ፣ ከጀኔራል ‹‹ኳርተር›› እና ከክልሉ ፕሬዝዳንት በተጨማሪ በብ/ጄነራል በየነ ገ/እግዚአብሔር (‹‹ወዲ አንጥር››) የተመራው 12ኛ ክ/ጦር እና በብ/ጄነራል ፀጋዬ ገ/ጨርቆስ (‹‹ጀብጀብ››) ዕዝ ስር የነበረው 13ኛ ክ/ጦር እንደሆነ ይነገራል፡፡ ኦብነግ በስፋት ይንቀሳቀስባቸዋል ተብለው የሚታሰቡት፡- ደገሃቡር፣ ቀብሪደሃር፣ ዋርደር፣ ጎዴ እና ቪቅ ከተሞች መደበኛ የጦር ቀጠናዎች ከሆኑ 15 አመት ያለፋቸው በመሆኑ፣ ከሌሎች የክልሉ አውራጃዎች በተለየ ሁኔታ የችግሩ ቀጥተኛ ተጠቂ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም የሚፈፅማቸውን ኢ-ህገ መንግስታዊ ድርጊቶች ለመሸፈን እንደ ቀይ መስቀል፣ ዓለም-አቀፍ ሚዲያዎች፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችና መሰል ተቋማት ከጅጅጋ ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ በኃይል አግዷል፡፡ ይህ ኩነትም በ ዙ-23 እና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ተደብድበው ከምድረ-ገፅ የጠፉ መንደር ነዋሪዎች፣ የቤት እንስሳት እና ቁሳዊ ንብረቶች በአንድነት ተቃጥለው መውደማቸውን ዛሬም ድረስ በምስጢርነት ሸሽጎ ለማቆየት አስችሎታል፡፡

የሆነው ሆኖ የመከላከያ ሰራዊቱ እና በክልሉ ከ70-80 በመቶ በሚሆኑ አካባቢዎች ላይ መንቀሳቀስ የቻለው ኦብነግ፣ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ከባድ ውጊያ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ግጭቱ አሁንም ሳያበራ የመቀጠሉ ምክንያት አማፂው ቡድን ያን ያህል ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ አይደለም፤ ይልቁንም የጄነራሎቹ እጅ በዘወርዋራ ስላለበት መሆኑን ወታደራዊ ምንጮቼ ያስረግጣሉ፡፡ ‹‹የኦብነግ ህልውና በተለይም ለከፍተኛ መኮንኖች ዋነኛ ንግድ (ቢዝነስ) ነው›› ይላሉ፡፡ የክልሉ መንግስት ‹‹የመረጃ እና ፀጥታ ባጀት›› በሚል ሽፋን በዓመት የሚመድበውን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የህዝብ ሀብት እንዲያወራርዱ አዛዦቹ አይገደዱም፡፡ መከላከያ ራሱም ‹‹የመረጃ እና የበረሃ ፍሳሽ›› በሚል የሚበጅተው አመታዊ ወጪ በብዙ ሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ በጀት እስከ ኃይል አመራሮች ድረስ ወርዶ እንደየድርሻቸው መጠን የሚመዘበርበት አሰራርም ተዘርግቶለታል፡፡ እናም ጀነራሎቹ ኦብነግ ሙሉ በሙሉ ተወግዶ የገቢ ምንጫቸው እንዳይደርቅም ሆነ፤ ከአቅም በላይ ተጠናክሮ በብቃት ማነስ እንዳያሳጣቸው (እንዳያስወቅሳቸው) ተቆጣጥረው ለመዝለቅ የቻሉበትን ቀመር እንዲከተሉ ይህ የገቢ ምንጭነት ገፊ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡

ሌላው ቀርቶ ከመከላከያ ሠራዊቱ እና ከፌዴራል ፖሊስ በተጨማሪ በቀጥታ የክልሉ አስተዳደር የሚያዝዘውና ‹‹ልዩ ኃይል›› ተብሎ የተቋቋመው ታጣቂ ቡድን ዛሬም ድረስ የሎጅስቲክ አቅርቦቱን ያለጨረታ ጠቅላላ የያዘችው የሜ/ጀነራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስ (በአሁኑ ወቅት ጀነራል አበባውን ተክቶ የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ነው) ባለቤት ሃዋ መሆኗ በራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ (በነገራችን ላይ ክልሉን የሚያስተዳድሩት በህዝብ የተመረጡት ሳይሆኑ ‹‹የፀጥታ አማካሪ›› በሚል በየወረዳው የተመደቡ የሻለቃ ወይም የሻምበል አዛዦች ከጀርባ ሆነው ነው፡፡ ለነርሱ ያልተመቸ ኃላፊን በሌላ እስከመቀየር ድረስ የሚንጠራራ ስልጣን አላቸው፡፡ የፕሬዚዳንት አብዲና እና የጄነራል ‹‹ኳርተር››ን የ‹‹ሥራ ግንኙነት›› መመልከቱ ጉዳዩን ፍንትው አድርጎ ለመረዳት ያስችላል፡፡ በርግጥም አስራ ሦስት ፕሬዚዳንቶች የተፈራረቁበት ክልል ዛሬ እንዲህ በጨካኙ አብዲ መርጋት መቻሉ እንቆቅልሽ ሊሆን አይችልም)፡፡

‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ከደረቅ ወንጀለኞች ማረሚያነት፣ በኦብነግ አባልነት የሚጠረጠሩ ንፁሃንን ወደማሰቃያ እስር ቤት እንዲቀየር የተደረገበት መግፍኤ ከላይ የጠቀስኩትን (የ1999 ዓ.ም የኃይል ጥቃትን) ተከትሎ ሟቹ አምባ-ገነን ጠ/ሚኒስቴር በደህንነት ኮሚቴው ስም የሰጠው ትዕዛዝ ነው፡፡ መቼም ዕድል ፊቷን አዙራበት ወደዚህ ግቢ የተላከ ምስኪን፣ በቀን አንድ መናኛ እንጀራ እየተወረወረለት፣ በ‹‹ምርመራ›› ስም የተወለደበትን ቀን ከመርገም አልፎ ዘላለማዊ ዕረፍት የሚያጎናፅፈው መልአከ-ሞት ቶሎ መጥቶ እንዲገላግለው እስከመናፈቅ ለሚያደርስ ስቀየት (ቶርቸር) ይዳረጋል፡፡ እስር ቤቱ የተገነባው 800 ታሳሪዎችን ታሳቢ ተደርጎ ቢሆንም፣ ወደምድራዊ ገሃነም ከተቀየረ ወዲህ ግን ከ5000 በላይ ሰዎች የሚታጎሩበት የሰቆቃ ግቢ ሆኗል፡፡ ሁሉም ታሳሪዎች ከጠዋት 2፡30 እስከ 7፡00 ሰዓት ድረስ አንድ ቦታ ተሰብስበው ክብርን፣ ሞራልን እና ሰብዕናን የሚያጎድፍ ግፍ ይፈፀምባቸዋል፡፡

ogadenበተለይም ሴት እስረኞች በየተራ እንዲቆሙ ይደረግና ወንዱ አንድ በአንድ እየተነሳ ሴተኛ አዳሪ መሆኗን፣ እሱ እና ጓደኞቹ ከእርስዋ ጋር ግብረ-ስጋ ግንኙነት መፈፀማቸውን፣ ወዘተ እንዲናገር ይገደዳል፡፡ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኖ ካልተገኘም በጨካኝ ታጣቂዎቹ ፍዳውን ይበላል፡፡ ሁኔታውን መራር የሚያደርገው ደግሞ ‹‹ስብሰባው›› ሲጠናቀቅ፣ ሰብሳቢው እስረኞቹ ወደየክፍላቸው እንዲገቡ ትዕዛዝ የማይሰጥ መሆኑ ነው፤ ይልቁንም ወፋፍራም ዱላ ጨብጠው ዙሪያውን ለከበቡት ፖሊሶች በአይኑ ምልክት ያስተላልፋል፤ ይሄኔ በያዙት ቆመጥ ከአቅራቢያቸው ያገኙትን ሁሉ መቀጠቀጥ ይጀምራሉ፤ እስረኛውም ከዱላው ውርጅብኙ ለማምለጥ ባገኘው አቅጣጫ ይተራመሳል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በየቀኑ የተለመደ በመሆኑ የዕለቱ ፕሮግራም ሊገባደድ በተቃረበ ቁጥር፣ ሁሉም ለመሸሽ ዝግጁ ሆኖ ይጠባበቃል፤ ከድብደባው ማምለጡ ግን ብዙም የሚሳካ አይሆንም፡፡

በ‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ሴት እስረኞችን አስገድዶ መድፈር፣ ሙዝ ልጦ እንደመብላት ቀላል ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በዚህም በርካቶች በየጊዜው ለውርጃ ወደሆስፒታል ሲላኩ ይስተዋላል፡፡ አልፎ አልፎ እዚያው ለመውለድ የሚገደዱ እህቶችም አሉ፡፡ አብዛኞቹ ሴት እስረኞች ፀጉራቸውን ከማሳደግ ይልቅ መላጨትን ይመርጣሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ የሚፈፀምባቸው ስቅየት የበሰበሱ ቆሻሻዎችንና ፈሳሽ-ሰገራዎችን ፀጉራቸው ላይ መደፋትን ስለሚያካትት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እዚህ ቦታ ሴቶች አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ እና ልብሶቻቸውን እንዲያወልቁ ከተደረገ በኋላ እርቃናቸውን የሚገረፉበት ጊዜም እንዳለ ከአይን እማኞች ሰምቻለሁ፡፡ ከሁሉ የከፋው ደግሞ ንፅህናን ካለመጠበቅና በምግብ እጥረት የሚነዛው ወረርሽኝ ነው፡፡ በ2004ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ በሽታው ተከስቶ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ 700 ያህል ሰዎች በሞት መቀጠፋቸው ይነገራል፡፡ በወቅቱ አስከሬን ቶሎ ስለማይነሳ እስረኞቹ ከአስከሬኑ ጋር እስከ 3 ቀን ድረስ ጋር ለመቆየት ይገደዱ ነበር፡፡

በ‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ግቢ ከሚገኙ ማጎሪያዎች መካከል 3ኛ፣ 4ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ክፍሎች ‹‹የቅጣት ቤት›› ሲሆኑ፤ አሰራራቸውም ሶስት በሶስት ሜትር የሆነ እጅግ በጣም ጠባብ፤ ውስጣቸውም ሃምሳ ሳንቲ-ሜትር ጥልቀት ባለው ውሃ የተሞላ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክፍልም የግድ ከ25 እና ከዚያ በላይ እስረኞች እንዲይዝ ስለሚደረግ ለቅጣት ወደግቢው የተላከ እስረኛ ለሳምንት ያህል እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር ለመሰንበት ይገደዳል፡፡ በአናቱም የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደዚህ ግቢ እየተላኩ ስቅየትም ሆነ ግድያ እንደሚፈፀምባቸው ሰምቻለሁ፡፡ በግቢው ለአራት ወራት ገደማ ያሳለፈው ሀሰን፣ በውል በማያስታውሰው በአንድ የተረገመ ቀን 3 ወታደሮች ሲረሸኑ ማየቱንና ከመካከላቸው አንዱም ‹‹እባካችሁ አትግደሉኝ! የ3 ልጆች አባት ነኝ!›› እያለ ሲማፀን መስማቱን ያስታውሳል፡፡

እስረኞቹ ላይ የጭካኔ ተግባር የሚፈፅሙት ደግሞ ከዚህ ቀደም ‹‹አል-ኢትሀድ አል-ኢስላሚያ›› በሚል ስም ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ፤ በኦብነግ ተሸንፎ ከኦጋዴን የተባረረው አማፂ ቡድን አባላት የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች መንግስት ምህረት አድርጎላቸው ወደ ሰላማዊ ህይወት ከተመለሱ በኋላ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዛኛውን አሰባስቦ ‹‹ልዩ ኃይል›› ብሎ አደራጅቷቸው ሲያበቃ፤ ከኦብነግ ጋር ተያይዞ የሚጠረጠሩ እስረኞች ላይ ያሻቸውን እንዲፈፅሙ ባልተፃፈ ሕግ ስልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም የቀድሞ ሽንፈታቸውን ለመበቀል እንደ መልካም አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ዛሬ በክልሉ ከተሞች በሚገኙ የተለያዩ የእስር ቤት ግቢዎች ውስጥ የጅምላ መቃብር መመልከት አስገራሚነቱም አስደንጋጭነቱም እየቀረ የመጣው ከዚህ አኳያ ይመስለኛል፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች የጦር ሄሊኮፕተር ይዘው ስርዓቱን መክዳታቸውን መንግሥት አመነ

helicopterባለፈው አርብ ታህሣሥ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ከድሬዳዋ የአየር ኃይል ምድብ የጦር ልምምድ ላይ የነበሩት የኢትዮጵያ  የአየር ኃይል አብራሪዎች እና አንድ መካኒክ በስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት በመክዳት ኤም አይ-35 የሆኑ ሁለት ዘመናዊ የጦር ሄሊኮፕተሮችን ይዘው ኤርትራ መግባታቸው ተረጋገጠ፡፡ ይሄንንም የኢትዮጵያ መንግስት መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ታህሣሥ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ማመኑን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡ አብሪዎቹ  ሻምበል ሳሙኤል ግደይ፣ መቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝ እና የሄሊኮፕተሩ ቴክኒሻን ፀጋብርሃን ግደይ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

አብራሪዎቹ ይዘዋቸው የጠፉት የጦር ሄሊኮፕተሮች የአንዱ  ዋጋ 36 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር  የሚገመት ሲሆን፤በኢትዮጵ  ከ720 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡ እንደ ኢሳት ዘገባ ከሆነ የአርብ ዕለቱን ጨምሮ ባለፉት 6 ወራት  ውስጥ ብቻ 11 የመከላከያ ሚኒስቴር የአየር ኃይል አብራሪዎችና ባለሟሎች ከድተው ስርዓቱን በኃይል ለመጣል ወደ ሚታገሉ ታጣቂዎች መቀላቀላቸው ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ቢሮ ታሸገ

ethi-mihedarየኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ዛሬ መስከረም 23 ቀን 2007 ዓ.ም ለምሳ ከቢሮ እንደወጡ መታሸጉን ዋና አዘጋጁ አቶ ጌታቸው ወርቁ ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ገለጹ፡፡ እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ ህትመት ካቋረጥንበት ነሐሴ 14 ቀን ጀምሮ ወደ ተለያዩ ማተሚያ ቤቶች ሄደን ለማተም ጥረት ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ነገር ግን ከ2 ሳምንት በፊት ማተሚያ ቤት አግኝተን ዝግጅታችንን ካጠናቀቅን በኋላ ወደ ህትመት ልንገባ ስንል ፊውዝ ተቃጠለ በሚል ሰበብ ልትታተም አልቻለችም፡፡ አሁንም ወደ ሌላ ማተሚያ ቤት በመሄድ ለማተም ተስማምተው ዝግጅት በምናደርግበት ሰዓት ከማዕከላዊ ተደውሎ ትፈለጋላችሁ እንድትመጡ የሚል የስልክ መልዕክት እንደደረሳቸው አቶ ጌታቸው ገልጸው፣ ለምን እንደተፈለጉ ቢጠይቁም በስልክ አልነግርክም ማዕከላዊ ቢሮ ቁጥር 75 አቶ አለበል ብለህ እንድትመጣ እንደተባሉ እሳቸውም ሰኞ እንደሚመጡ ለደዋዩ እንደገለጹላቸው ነገር ግን በዛሬው ዕለት ለምሳ እንደወጡ ቢሮዋቸው እንደታሸገ ለፍኖተ ነፃነት ገልጸዋል፡፡