“የስርዓቱን አረመኔያዊ እርምጃ እናወግዛለን!”- የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ጥምረት
በተቃውሞ ሰልፉ በአንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት እንዲሁም ሌሎች ዜጎች ላይ በፖሊስ የተፈፀመውን ድብደባ የ9ኙ ትብብር ፓርቲዎች ጥምረት አውግዟል፡፡ የ9ኙ የትብብር ፖለቲካ ድርጅት መኢአድ፣ሰማያዊ፣የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የከንባታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና ሌሎች አባላትን ያቀፈ የፖለቲካ ጥምረት ድብደባውን በፅኑ አውግዟል፡፡ ሙሉ መግለጫውን ከዚህ በታች ይገኛሉ፡-
የስርዓቱን አረመኔያዊ እርምጃ እናወግዛለን!
ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የተሰጠ መግለጫ
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አብሮ ስለመስራትና ሌሎቹም ትብብሩን እንዲቀላቀሉ በየጊዜው የሚወተውተው አገራችን በዚህ ዘመን በማይመጥን አምባገነንና የጭካኔ ስርዓት ውስጥ የምትገኝ መሆኑን በመረዳቱ ነው፡፡ ይህ የህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነንና ጨካኝ ስርዓት ህዳሩ 27/28 2007 ዓ.ም የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በወጡት አመራሮቻችን፣ አባላቶቻችን፣ ደጋፊዎቻችንና በየጎዳናው የተገኙት ንፁሃን ላይ ከፍተኛ ድብደባና የጅምላ እስር በመፈፀም ስርዓቱን ለመታገል የተነሳነበትን አላማ ትክክለኝነት አረጋግጦልናል፡፡
በዛሬው ዕለትም ገዥው ፓርቲ በፓርቲያቸው የውስጥ ጉዳይ ገብቶ የሚፈፅመውን ደባ፣ ምርጫ ቦርድንና የህዝብ ሚዲያን ተጠቅሞ ፓርቲውን ለመከፋፈልና አሳንሶ ለማሳየት የሚያደርገውን እኩይ ተግባር በመቃወም ሰልፍ የወጡ የአንድነት አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና የፓርቲው ጽ/ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው ቤተ ክርስትያን አካባቢ የነበሩ አዛውንት ምዕመናንን ሳይቀር በመደብደብ ጭካኔውን ዳግመኛ አሳይቶናል፡፡ ፖሊስ በትዕዛዝ በአንድነት አባላት ላይ ከፍተኛ የጭካኔ እርምጃ ወስዷል፡፡ አብዛኛዎቹንም በጅምላ አስሯል፡፡
ስርዓቱ በእነዚህ ሰላማዊ ዜጎች ላይ አሁንም የጭካኔ እርምጃውን መድገሙ ስልጣኑን የማጣት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳለ እና ከይስሙላ ያለፈ ለሰላማዊ ትግሉ ዝግጁ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ትብብራችን የስርዓቱን ጨካኝነት እያወቁም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ በስርዓቱ የማይከበረውን ህገ መንግስታዊ መርህ ተከትለው ሰልፍ ለወጡ ቆራጥ የአንድነት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች አድናቆቱን መግለጽ ይወዳል፡፡ መስዋዕትነታችሁ ለነገ ድላችን ስንቅ በመሆኑ ይበልጡን ተጠናክራችሁ በጋራ ትግላችን እንደምናጠናክርም እምነታችን ነው፡፡
በተቃራኒው ገዥው ፓርቲ ህግ የማክበርና የማስከበር ሚናውን ረስቶ ፖሊስ፣ ደህንነትንና ሌሎች ተቋማትን ለራሱ ስልጣን ማስጠበቂያ በማዋል በአንድነት አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎች ላይ የፈፀመውን ለዘመኑ የማይመጥንና በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ለጠየቁት ኢትዮጵያውያንም የማይገባ የጭካኔ እርምጃ በጥብቅ እናወግዛለን፡፡
ኢትዮጵያውያንን የማስተዳደር አቅምና ሞራል ያጣው ገዥው ፓርቲ የዜጎችን ጥያቄ በኃይል ማዳፈን የማይቻል መሆኑንና አገራችን ወደባሰ ችግር እንደሚከታት ተረድቶ ከዚህ የጭካኔ እርምጃው እንዲቆጠብ፣ እርምጃውን የወሰዱትን አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑና የታሰሩትን በአስቸኳይ እንዲፈታ እናሳስባለን፡፡ ፖሊስ፣ ደህንነት፣ መከላከያና ሌሎች ተቋማት ገዥው ፓርቲ አላፊ መሆኑን በመገንዘብና ከገዥው ፓርቲ ታዛዥነት በመውጣት ወገኖቻቸሁ ላይ እንዲህ አይነት የጭካኔና አሳፋሪ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥባችሁ ከህዝብ ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡
ያለ መስዋዕትነት ድል የለም!
ጥር 17/2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ
አንድነት ፓርቲ የጠራው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በፖሊስ ድብደባ ሲጠናቀቅ፤በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል
-“የፍትህና የነፃነት ጥያቄያችን ደም በማፍሰስ አይቀለበስም!”- አንድነት
-በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞችም ተከታታይ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች እንዲቀጥሉ ተወስኗል
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ዛሬ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አራት የክልል ከተሞች የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በፖሊስ ድብደባ ተጠናቀቀ፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ መነሻውን ቀበና ከሚገኘው የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት በማድረግ መዳረሻውን ጥቁር አንበሳ አካባቢ በሚገኘው ኢትዮ-ኩባ አደባባይ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሰልፍ በፅህፈት ቤቱ አካባቢ በተፈፀመ የፖሊስ ድብደባና እገታ ሊቋረጥ ችሏል፡፡
የተቃውሞ ሰልፉ ዋነኛ ዓላማም ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ አንድነት ወደ ምርጫው መግባቱን በመወሰን በመላ ሀገሪቱ ከ450 በላይ ዕጩዎቹን ማቅረቡን ይፋ ማድረጉን ተክትሎ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ፓርቲው ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ በሚል ፓርቲውን ከምርጫ ውድድር ለማስወጣት የሚደረገውን ተግባር ለመቃወም መሆኑን ቀደም ሲል ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ከተጠቀሰው ዓላመ በተጨማሪ በዜጎች ላይ የሚደርስ ህገወጥ እና የግፍ እስር እንዲቆም፣ የታሰሩ የህሊና እስረኞች እንዲፈጡ፣ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ እንዲኖር፣…የሚሉ ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡
መረጃዎች ከስፍራው እንደጠቆሙት ከሆነ፤ የተቃውሞ ሰልፉ ቀበና ከሚገኘው የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት የተነሳው ከ 150 በላይ የሚሆን ሰልፈኛ ከጽህፈት ቤቱ 100 ሜትር ርቀት ላይ ከሚጠብቁ ከ500 በላይ ሰልፈኞች ጋር ከመቀላቀላቀላቸው አስቀድሞ ፖሊሶች ቆርጠው በመግባት ከባድ ድብደባ አድርሰዋል፡፡ አራት ኪሎ፣ በፒያሳና የሰልፉ ማጠናቀቂያ በሆነው ኢቲዮ -ኩባ አደባባይ ይጠባበቅ የነበረው ሰልፈኛ ሊበተን መቻሉንም ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
በተፈፀመው የፖሊስ ድብደባም ከ26 በላይ የፓርቲው አባላትና አመራሮች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ከሰልፉ ጋር ምንም ንክኪ ያልነበራቸውና ቀበና መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የነበሩ የ70 ዓመት አዛውንትም ከፍተና ጉዳት ደርሶባቸው በአቅራቢያው በሚገኝ የጤና ተቋም የህክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት በክልል ከተደረጉት የተቃውሞ ሰልፎች መካከል ፓርቲው በደብረማርቆስ፣ በሸዋሮቢት እና በጋሞጎፋ ከምባ የተሳካ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አበባው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጉዳት ከደረሰባቸው የአንድነት አባላት መካከል የሚሊዮኖች ድምፅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ስለሺ ሐጎስና የፓርቲው ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኃላፊ ዳግማዊ ተሰማ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰባቸው ራሳቸውን ስተው እንደነበርና ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደነበር የዓይን እማኞች ከስፍራው አስታውቀዋል፡፡ በተመሳሳይም ……የተባሉ ነፍሰጡር በፖሊስ ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የተጠቆመ ሲሆን፤በፖሊስ ድብደባ ከተፈፀመባቸውና ጉዳት ከደረሰባቸው የፓርቲው ስራ አስፈፃሚና አባላት መካከል፡-
- አቶ አስራት አብርሃም (የህዝብ ግንኙነት ተጠባባቂ ሃላፊ)
2. አቶ ዳንኤል ተፈራ (የውጭ ጉዳይ ሃላፊ)
3. አቶ ብሩ ብርመጅ (የፖለቲካ ጉዳይ ሃላፊ)
4. አቶ ፀጋየ አላምረው (ምክትል አፈ-ጉባኤ)
5. አቶ አሻግሬ መሸሻ (የሰሜን ቀጠና ሃላፊ)
6. አቶ ሰለሞን ስዩም (የኤዲቶሪያል ቦርድ ሰብሳቢ)
7. ወ/ት ልዕልና ጉግሳ (የም/ቤት አባል)
8. አቶ ዳግማዊ ተሰማ (የም/ቤት አባል)
9. ጋዜጠኛ ስለሺ ሀጎስ (የም/ቤት አባል)
10. አቶ ስንታየሁ ቸኮል (የአዲስ አበባ የወጣቶች ጉዳይ ሃላፊ)
11. አቶ አሸናፊ አሳምረው (የወረዳ አመራር)
12. አቶ ኢሳያስ ቱሉ (አባል)
13. ወ/ት መስከረም ያረጋል (አባል)
14. አቶ ሃይሉ ግዛው (የወረዳ ሰብሳቢ)
15. አቶ አዲሱ መኮንን (የወረዳ ሰብሳቢ)
16. አቶ ሲሳይ ካሴ (አባል)
17. አቶ ወጋየሁ አድማሴ (አባል)
18. አቶ ክብረት ሃይሉ (የም/ቤት አባል)
19. አቶ ስለሺ ደቻሳ (አባል)
20. አቶ ማሩ አካሉ (አባል)
21. አቶ ክፍሉ በዳኔ (አባል)
22. አቶ ፋሲካ አዱኛ (የወረዳ አመራር)
23. ወ/ሮ ገነት ሞገስ (የወረዳ አመራር)
24. ተስፋየ ብዙነህ (አባል)
25. ሙሉጌታ ተፈራ
26.ኤፍሬም ሰለሞን(የአዲስ አበባ ስራ አስፈፃሚ)
በተቃውሞ ሰልፉ ፖሊሶች ያደረሱትን ጉዳት በቅርብ ሲከታተሉ የነበሩት የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች የአንድነት አመራሮችን እና ጉዳት ደርሶባቸው በየሆስፒታሉ የሚገኙ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎችን አነጋግረዋል፡፡ የፓርቲው አመራሮች ከአባላትና ከደጋፊዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን አንድነት በአዲስ አበባ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎችን እንደሚያደርግ ይፋ ተደርጓል፡፡ ይህንንም በተመለከተ ፓርቲው መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ ሙሉ መግለጫውን ከዚህ በታች ይመልከቱ፡-
የፍትህና የነፃነት ጥያቄያችን ደም በማፍሰስ አይቀለበስም!!!
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ፓርቲያችን አንድነት ገዥው ፓርቲ፣ ምርጫ ቦርድና የገዥው ፓርቲ ልሳን በመሆን እያገለገሉ ያሉ ሚዲያዎች በመተባበር ከምርጫ ለማስወጣትና ተለጣፊ አንድነት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ መጥራቱ የሚታወቅ ነው፡፡
የተቃውሞ ሰልፉን ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም እንደምናከናውን ለአዲስ አበባ መስተዳድር ብናሳውቅም መስተዳድሩ በ12 ሰዓት ውስጥ በፅሁፍ ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ ሰልፉ እውቅና አለው፡፡ መስተዳድሩ ግን የተጣለበትን ሃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ወደ ጎን በመግፋት የተወሰኑና የማይታወቁ ግለሰቦች ፔቲሽን ተፈራርመው አምጥተዋል በማለት ብዥታ ለመፍጠር ሞክሯል፡፡ ፓርቲያችን ህጉን ጠብቆ ህጋዊ የሆነ ሰልፍ ለማካሄድ ቢሞክርም አሁንም ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ በተደጋጋሚ እንዳየነው ፖሊስ ደንብ ማስከበር ሲገባው አድሎ ለፈፀመው አካል በመወገን ድብደባ መፈፀሙ ከወገንተኝነት ያልፀዳ መሆኑን እንድናረጋግጥ አድርጎናል፡፡
ጥያቄያችን አሁንም የፍትህ፣ የእኩልነትና ህግ እንዲጠበቅ የማድረግ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የመንግስትነት ስልጣኑን በመጠቀም የስልጣን ዘመኑን ለማስረዘም እየከወነ ያለውን ሴራ ማስቆም ነው፡፡ ጥያቄያችን የነፃነትና ያልተሸራረፈ ዴሞክራሲ ይረጋገጥ የሚል ነው፡፡ ጥቄያችን ምርጫ ቦርድ የገዥው ፓርቲ አጋር መሆኑ ቀርቶ ገለልተኛ ሚናውን ይወጣ የሚል ነው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎቻችን ደግሞ ደም በማሰስ፤ በድብደባም ሆነ በእስር ፈፅሞ አይቆሙም፡፡
በሚቀጥለው ሳምንትም በተለያዩ ከተሞችና በአዲስ አበባ የሰላማዊ ተቃውሞ ድምፃችንን ከፍ አድርገን እናሰማለን፡፡ ትግሉ ይቀጥላል፡፡
ድል የህዝብ ነው!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
አንድነት ፓርቲ እሁድ “የነፃነት ቀን ቀርባለችና ወደ አደባባይ ውጡ” በሚል ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቷል
-የሰልፉን ቅስቀሳ ተከትሎ የፓርቲው ወጣት አመራሮች ታስረዋል
.አንድነት ፓርቲ የጠራው የነገው ሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ተጠናክሮ ቀጥሏል
አንድነት ፓርቲ ለነገ እሁድ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢህአዴግና በምርጫ ቦርድ በኩል ፓርቲው ወደ ምርጫ ውድድር እንዳይገባ የሚደረገውን እንቅስቃሴና ድርጊት በመቃወም የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉን ተከትሎ ዛሬ ጥር 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃም፣ ምክትል ኃላፊው አቶ ንዋይ ገበየሁ፣ የኤዲቶሪያል ቦርድ ኃላፊው አቶ ሰለሞን ስዩም እና የፓርቲው የአዲስ አበባ ወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል እና ሌሎች አመራሮች አቶ ያሬድ አለማየሁ፣ አቶ ሲሳይ ጌትነት፣ አቶ ማቲያስ ሐረጉ በፀጥታ ይሎች መታሰራቸውና ወዳልታወቀ ስፍራ የተወሰዱ ሲሆን፤ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አቶ አስራት አብርሃም፣ አቶ ንዋይ ገበየሁ፣ አቶ ሰለሞን ስዩም እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል መፈታታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ፓርቲው ሰልፉን እንዲጠራ ያስገደደው ምርጫ ቦርድ ከሀገሪቱ የምርጫ አዋጅ ህግ አግባብ ውጭ በአንድ ወር ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ በመወሰኑ ሲሆን፤ ቅሬታ ነበረን በሚል ጥያቄ ካቀረቡት ዋነኞቹ አቶ አየለ ስሜነህ እና አቶ ኢሳይያስ ቱሉ ምርጫ ቦርድ እና ባልፈለግነው መንገድ ፓርቲውን ለሁለት ለመክፈል በመሞከሩ፣እኛ ደግሞ አንድነት አንድ ነው እንዲከፈልም ስለማንፈልግ ተመልሰን ወደ ዋናው ፓርቲያችን ቢሮ ተመልሰናል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም አንድነት ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲታዘብ ጥሪ ሲደረግለት እነ አቶ አየለ ስሜነህ ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ደብዳቤ ስላስገቡ ቦርዱ ሁለት ቦታ ለመታዘብ ወኪል መላክ እንደማይችል በጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፓርቲው ደብዳቤ መፃፉ ታውቋል፡፡
አቶ አየለ ስሜነህ በበኩላቸው እኛ ጠቅላላ ጉባኤ አልጠራንም፣ የነበርነው የአንድነት ፓርቲ አባላት ከ15 አንበልጥም፤ ነገር ግን የፓርቲው አባላት ያልሆኑ ከ60 በላይ ሰዎች በስብሰባችን ላይ ተገኝተዋል፣የሆቴል አዳራሽ ኪራይ ማን እንደከፈለ አናውቅም፣ ተከፍሎላችኋል እዛ ሆቴል ሂዱ እንባላለን፣ይሄ ሁሉ ስላላማረን እና ፓርቲያችን አንድነት አንድ ስለሆነ ወደ ፓርቲያችን ተመልሰናል ሲሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲታዘብ ለቀረበለት ጥሪ እነ አቶ አየለ ስሜነህም ጠርተውናል ሲል በፃፈው ደብዳቤ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ አቶ አየለ ስሜነህ በበኩላቸው እኛ ምንም ዓይነት ጠቅላላ ጉባኤ አልጠራንም፣በመካከላችን የነበረው ጥቂት አለመግባባት እንዲፈታ ስንል እንጂ ከፓርቲው ህልውናም ሆነ አሰራር ጋር ቅሬታም ሆነ ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራ የሚል ጥያቄ አላቀረብንም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
በአሁን ወቅት ጥያቄ ነበረን ያሉት አቶ አየለ፣ ያለንን ጥያቄ በፓርቲያችን ውስጥ ሆነን እንፈተዋለን፣ ወደ ውጪ ይዘን መውጣታችን ትክክል እንዳልነበረና እኛ ባላሰብናውና ባልፈለግነው መንገድ ፓርቲው ላይ በእኛ ስም አደጋ ለመፍጠር እየተሰራ እንዳለ ስንገዘነብ ተመልሰናል፣ መጀመሪያም ቢሆን ፓርቲው አልተከፈለም፣ እኛም ጥያቄ አቀረብን እንጂ ከፓርቲው አልወጣንም ሲሉ አክለዋል፡፡ አቶ አየለ ስሜነህ ለጋዜጠኞች የሰጡትን መግለጫ ለራሱ ለምርጫ ቦርድ ግልባጭ ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርበው የነበሩት አቶ አየለ ስሜነህ ወደ ፓርቲው መመለሳቸውን ቢያሳውቁም፤ ምርጫ ቦርድ ግን በነ አቶ አየለ ስሜነህ ስም ሌላ አካል እያደራጀ መሆኑን በመጥቀስ ፓርቲው ድርጊቱን ለማውገዝ የሰልፍ መጥራቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ፓርቲው ድርጊቱን የኢትዮጵያ ህዝብም እንዲረዳውና እንዲያወግዘው ለነገ እሁድ ጥር 17 ቀን 2007 ኣ.ም. የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉን መጥራቱን ፓርቲው አስታውቋል፡፡ ከዚህ በኋላ ፓርቲው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በመላ ሀገሪቱ ማካሄድና ነውጥ አልባ የነፃነት ትግሉን አጠናክሮ ከመቀጠል ውጭ ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንደማይጠራ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ ወደ ፓርቲያቸው ስለተመለሱት አቶ አየለ ስሜነህ እስካሁን ባይዘግብም ፓርቲው እንደተከፈለ አድርገው ከሬዲዮ ፋና እና ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በተደጋጋሚ ከሚያቀርቡት በስተቀር ምርጫ ቦርድ እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም፡፡
የነገው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ መነሻ አዲስ አበባ ቀበና መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ፊትለፊት ከሚገኘው የፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት ሲሆን፤ የሰላማዊ ሰልፉ መነሻ ሰዓት ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት መሆኑንም ታውቋል፡፡
የሰልፉ መዳረሻ ቦታ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጀርባ እና ዋናው ፖስታ ቤት ፊትለፊት በሚገኘው ኢትዮ-ኩባ አደባባይ መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት (እሁድ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም.) የተቃውሞ ሰልፉ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በደብረ ማርቆስ፣ በአርባምንጭ አካባቢ ከምባ ወረዳ፣በጂንካ እና በሸዋ ሮቢት እንደሚደረግ በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት በመወሰኑ በክልሎችም የሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ቀጥሏል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ቀኑ እንዲራዘም የመንግስት አካላትና ዲፕሎማቶች ጥረት ቢያደርጉም፤የአንድነት ፓርቲ ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ መብታችንን ከእንግዲህ ለምነን አናገኝም፣ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉም በታቀደለት መሰረት ይቀጥል ሲል መወሰኑን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ፓርቲው ከላይ ከተጠቀሱት 5 ከተሞች በተጨማሪ በተከታታይ በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞችም የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ እንደሚቀጥል ይፋ አድርጓል፡፡
መኢዴፓና ኢብአፓ በፓርቲዎች ላይ የሚፈፀመው ደባና ዛቻ እንዲቆም ጠየቁ
-
“ምርጫ ቦርድ የኢህአዴግ አምስተኛ አባል ፓርቲ ሆኗል”-ፓርቲዎቹ
የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ) እና
የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) በምርጫ ዋዜማ
ገዥው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም
በሰማያዊ፣ አንድነትና መኢአድ ላይ የሚፈፅሙትን ደባና ዛቻ
እንዲያቆሙ ጠየቁ፡፡ ፓርቲዎቹ ህዳር 7/2007 ዓ.ም ‹‹በምርጫ
ዋዜማ በፓርቲዎች ላይ የሚደርሰው ደባና ዛቻ በአስቸኳይ
ይቁም›› በሚል በጋራ ባወጡት መግለጫ ኢህአዴግ ምርጫ
ቦርድን በመሳሪያነት በመጠቀም ሰማያዊ፣ አንድነትና መኢአድ
ላይ ወከባና ዛቻ እየፈፀመ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ መግለጫው
ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጉ እያለ ለማዋከብ ቢጥርም
መኢአድና አንድነት የተዋጣለት ጠቅላላ ጉባኤ አድርገዋል
ብሏል፡፡
ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ሰማያዊ ፓርቲ አገራዊ ግዴታውን
እየተወጣ በመሆኑ፣ እንዲሁም መኢአድና አንድነት ብቃት ያላቸው
ልሂቃንን ማፍራት ስለቻሉ በተፈጠረበት ስጋት ፓርቲዎቹን
ለማጥፋት እየጣረ መሆኑንና ምርጫ ቦርድም የኢህአዴግ
አምስተኛ አባል ፓርቲ እስኪመስል ድርስ የገዥው ፓርቲ
መጠቀሚያ ሆኗል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከገዥው ፓርቲ መሳሪያነት
ወጥቶ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣም ፓርቲዎቹ
በመግለጫቸው ማሳሰባቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡




















