Daily Archives: December 21st, 2015

ጠላት ሰሪዎቹ (The Enemy Makers)

ገመቹ መረራ ፋና

gemechu merera

ብዙውን ጊዜ የራሳችንን ጠላቶች ራሳችን ጠፍጥፈን እንደምንሰራ አምናለሁ። በማድረግም ባለማድረግም (by commission and omission) የምንሰራቸው «ስህተቶች» አሉ። በተለያየ ጊዜ ያቆሰልናቸው ወይም ቆስለው እያየን በቁስላቸው አላግጠን ያለፍናቸው ሰዎች ነገ ወዳጅ ይሆኑናል ብለን የምንጠብቅ የዋሆች አይደለንም። ይሄንን ድርጊታችንን ወይም ተዓቅቦአችንን ተከትሎ የሚመጡብን ችግሮች ከመጋፈጥ ቆም ብሎ ዛሬ ላይ ምን እያደረግኩ ነው ብሎ ማሰብ ሳይበጅ አይቀርም። እስቲ በመጨረሻ ላይ የቆምንበትን/ያለንበትን ሁኔታ ከማየታችን አስቀድመን ጥቂትአብነቶች አንስተን የራሳቸውን ጠላት ጠፍጥፈው የሰሩ አካላትንን እና «ጠላቶቹን» በምሳሌነት እንመልከት፦
1. ጋሳን ፋይዝ ካናፋኒ
ይህ በብዙዎች ዘንድ የአረቡ የምንጊዜም ምርጥ የሥነ-ጽሁፍ ሰው ነው ተብሎ የሚወሰድ ፍልስጤማዊ ደራሲና የነጻነት ታጋይ ከሕልፈቱ በኋላ በ Conference of Afro-Asian Writers የ Lotus Prize for Literatureን አሸንፏል። በልጅነቱ የ1948ቱን የአረብ-እስራኤል ጦርነት ተከትሎ ከትውልድ ስፍራው ከቤተሰቦቹ ጋር ተሰዶ ወደ ሊባኖስ ከዚያም ወደ ሶርያ የኖረው ካናፋኒ በ36 ዓመት እድሜው ሞሳድ ባጠመደው የመኪና ቦምብ ከ17 ዓመቱ የወንድሙ ልጅ ጋር ቢገደልም በትንሹ የሕይወቱ ቆይታ ግን ብዙ ስራ ሰርቶ አልፏል።
Letter from Gaza በመባል በሚታወቀው ለጓደኛው ሙስጠፋ በጻፈው የመልስ ደብዳቤ ካናፋኒ አንድ ነገር ግልጽ ያደርጋል። ይህ ደብዳቤ ሶርያ በስደት እያሉ ብዙ አስቸጋሪ ጊዜያት አብረው አሳልፈው ለነበረውና ወደፊት ሃብታም የመሆን ግብ ሰንቀው ይኖሩ ለነበረው አብሮአደግ ጓደኛው ሙስጠፋ የተጻፈ የመልስ ደብዳቤ ነው። በመጀመሪያው ደብዳቤ አሜሪካ ነዋሪ የሆነው ሙስጠፋ ለካናፋኒ ለኑሮው የሚያስፈልጉትን ሁሉ ነገሮች አመቻችቶ ወደ አሜሪካ (ካሊፎርኒያ- ሳክራሜንቶ) እንዲመጣና የልጅነት ግባቸውን እንዲያሳኩ እየነገረው ነበር። በሲቪል ምህንድስና በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ስኮላርሺፕ አግኝቶ ሁሉ ነገር የተስተካከለለት ጋሳን ካናፋኒ ግን ለጓደኛው እኔ ወደ አሜሪካ አልመጣም፣ አንተ ወደ ጋዛ ና እንጂ ይለዋል። «I won’t follow you to “the land where there is greenery, water and lovely faces” as you wrote. No, I’ll stay here, and I won’t ever leave.» በዚህች መስመር እንደተጠቀሰው መቼም ከጋዛ አልወጣም ነበር ያለው። ለምን ይሆን አልመጣም ያለው? ያስብላል።
ናዲያ። ያቺ በጣም አብዝቶ የሚወዳት ናዲያ አይኑን እንደከፈተችለት ይገልጻል። ናዲያ ቆንጅዬ የ13 ዓመት ልጅ ነች። የሙት ወንድሙ ሴት ልጅ። ለበዓል ይኖርበት ከነበረችው ኩዌይት ወደ ጋዛ ሲሄድ የወንድሙ ሚስት እያነባች ልጇ ናዲያን ሄዳ ጋዛ ሆስፒታል እንዲጠይቃት ትለምነዋለች። እናቱ እና የወንድሙ ሚስት የደበቁት ነገር እንዳለ እየተሰማው ወደ ሆስፒታል ክፍሏ ይገባል። የሆስፒታሉ አልጋ ላይ ትልቅ ትራስ ተንተርሳ ጥልቅ ዝምታን በሚናገሩት እና እንባ ባዘሉ አይኖቿ ተመለከተችው። «Her face was calm and still but eloquent as the face of a tortured prophet might be. Nadia was still a child, but she seemed more than a child, much more, and older than a child, much older.» አጎቷን ያየችው ናዲያ በእጆቿ ድጋፍ ቀና ብላ ሰላም ካለችው በኋላ ተኛች። ካናፋኒም አንዲህ ይላታል «ናዲያ ብዙ ስጦታዎች ከኩዌይት ይዤልሽ መጥቻለሁ። ድነሽ ከአልጋ ስትወርጂ እቤት ትመጪና ስጦታዎችሽን ሰጥሻለሁ። ባለፈው በደብዳቤ ጽፈሽ የጠየቅሺኝን ቀይ ሱሪም ገዝቼልሻለሁ። ሱሪውን ይዤልሽ መጥቻለሁ።» ናዲያ ኤሌክትሪክ እንደያዛት ሰውነቷ ተንቀጥቅጦ ዝም አለች። አንባዋ ግራና ቀኝ ወደ ትራሱ ፈሰሰ።
«ሱሪውን አልፈለግሺውም? ምን ሆነሻል?» ብሎ ሲጠይቃት እንደምንም ጥርሷን ነክሳ ከሩቅ የመጣ በሚመስል ድምጽ «አጎቴ!» አለችው። እጇቿን ዘርግታም የሸፈናትን የሆስፒታል ብርድልብስ ገለጠችና በጣቶቿ ጠቆመቸው። ናዲያ እግሯ ከጭኗ መነሻ ጋር ተቆርጦ ነበር!! «ይሄንን ልረሳ አይቻለኝም» ይለዋል በደብዳቤው ለጓደኛው። «ያን ቀን ናዲያ እግሯን ያጣችው ታናናሽ ወንድም እና እህቶቿን ከቦንብና ከነበልባል ልታድን ራሷን ጥላ ከልላቸው ስለነበር ነው ብለው ነገሩኝ። ሮጣ ልታመልጥ እና እግሯን ልታድን ትችል ነበር። ግን ያንን አላደረገችም።» ይልና ከዚያች ቀን በኋላ ሁሉን ነገር በተለየ መልክ ማየት መጀመሩን እና ወደ ሳክራሜንቶም እንደማይመጣ፣ ይልቁንም እርሱ ራሱ እንዲመጣና ለሀገራቸው ትንሳዔ፣ ለህዝባቸው መፍትሄ እንዲሰሩ ይጠይቀዋል። ይሄ መስዋዕትነት ምንን እንደሚጨመር እንግዴህ መዘርዘር አያስፈልግም – ጉዳዩ የእስራኤል እና የፍልስጥዔም ነውና። እስከ ሕልፈተ ሕይወቱ ድረስም ለሃገሩ ሲሰራ ኖሯል። የጋሳን ካናፋኒ ስራዎች ዛሬ በብዙ ፍልስጤማውያን ልብ ውስጥ አለ።
2. ብ/ጄኔራል ታደሰ ብሩ
ጄነራሉ ሙያቸውን ከሚያከብሩ እና ለንጉሱ ታማኝ ከነበሩ ወታደሮቻቸው መካከል ግንባር ቀደሙ ነበሩ። በንጉሱ ጊዜ እንዳገለገሉት አብዛኞቹ ባለሥልጣናት እና ተሿሚዎች ለንጉሱ መልካም አመለካከት እና ታማኝነት የነበራቸው ግለሰብ ነበሩ። ይሄንንም በንጉሱ ላይ የታቀደውን መፈንቅለ መንግስት ባከሸፉበት ስራቸው እንዲሁም ኔልሰን ማንዴላን መጠበቅ እና ማሰልጠንን የሚያህል ትልቅ አደራ በመቀበል አስመስክረዋል። (እዚህ ጋር እንዴት ያንን መፈንቅለ መንግስት ያከሸፈ ግለሰብ በመልካም ይወደሳል የሚል አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይቸላል። ነገር ግን እንደወታደር እና ሃላፊነቱ እንደነበረበት ሰው ግዴታቸውን የተወጡ መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገለጽ ነበር። ከውትድርና ሳይንስ አንጻር ከታየና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ከተመዘነ ባይጥምም የሚያስማማ ነው።) የኚህ የተከበሩ ጄነራል ታማኝነት ግን አንድ ቀን ተሸረሸረ።
ከዕለታት በአንዱ ቀን በቤተመንግስት በተዘጋጀ የራት ግብዣ ላይ መኳንንቱ እና መሳፍንቱ እንዲሁም እነጄነራል ታደሰ ብሩ ታድመው ነበር። በራት ግብዣው ላይ ሰው ጨዋታ ይዞ የነበረ ሲሆን ብ/ጄኔራል ታደሰ ብሩ ጨዋታ ይዘው የነበረው ከጠ/ሚ/ሩ አክሊሉ ኃብተወልድ ጋር ነበር። የጨዋታውም ርዕስ ጄነራሉ በወቅቱ ይሰሩት ስለነበረው ስራ ነበር። ጄኔራሉ በወቅቱ በጦር ሰራዊቱ ውስጥ የጀመሩት እና በተለይ ይመሩት የነበረው አንድ ክፍል ነበር። ይህ ክፍል «የፊደል ሰራዊት» የሚባል ሲሆን በሃገራችን የተለያዩ ክፍሎች የመሰረተ ትምህርት ስልጠና ይሰጥ ነበር። በውይይቱ ወቅት ጠ/ሚ/ሩ እጅግ ያስገመታቸውን እና ለጄነራሉ መለወጥ ምክንያት የሆነውን ትዕዛዝ መሰል ምክር ለጄነራሉ ሰጡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ አክሊሉ «ታደሰ፤ ኦሮሞ ውቅያኖስ ነው ይውጠናል – ልታስተምረው እንዳትሞክር። እነሱን አንድ ክፍለዘመን ወደኋላ ይዘን መሄድ ነው ያለብን» ነበር ያሉት።
በወቅቱ በዚህ ጊዜ ተመስርቶ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እየሰራ የነበረ አንድ ማህበር ነበር፤ የመጫና ቱለማ የመረዳጃ ማህበር። ይህ ማህበር እንደ መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ያሉ የተለያዩ ትልልቅ ሰዎችን በአባልነት ያቀፈና የተለያዩ የማህበራዊ ፍትህ እና የልማት ስራዎችን የሰራ ማህበር ነበር። ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን/ክሊኒኮችን እና ሌሎች መሰል የልማት ስራ ይሰራ የነበረው ማህበሩ ለዚህ ስራው የሚረዱ ግብዓቶችን ሊሰጡ የሚችሉ ከመላው ሕብረተሰብ የተውጣጡ ሰዎችን የያዘ ሲሆን በውስጡ ደጃዝማቾችን፣ ኮሎኔሎችን፣ ዶክተሮችን ወዘተ በአባልነት ያቀፈ ማህበር ነበር። ለማህበሩ አባልነት ከተጠየቁት እና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከተጋበዙ ሰዎች መሃዘከል ደግሞ ብ/ጄኔራል ታደሰ ብሩ አንዱ ነበሩ። ጄነራሉ ግን ማህበሩ የብሄር ተኮር ፖለቲካ ያራምዳል የሚል ዕምነት ስለነበራቸው ግብዣውን ከአንዴም ሁለቴ ሳይቀበሉ ቀርተው ነበር።
ወደ ራት ግብዣው ምሽት ስንመለስ ጠ/ሚ/ሩ ያንን «ምክራቸውን» ለጄነራሉ ሲለግሱ ያላወቁት አንድ ነገር ነበር፤ ጄኔራሉ በእናታቸው ኦሮሞ መሆናቸውን። በዚህ ጊዜ ነበር እያገለገሉ ያሉት ሥርዓት አባላት ያላቸውን የነቀዘ አስተሳሰብ የተገነዘቡት እና ከዚህ በፊት የገፉትን የአባልነት ግብዣ ተቀብለው የመጫና ቱለማ ማህበርን የተቀላቀሉት። ከዚህ ቀን በኋላ በሥርዓቱ የተገፋ ሕዝብ ላሉት የኦሮሞ ሕዝብ በደርግ እስከተገደሉበት ዕለት ድረስ የታገሉ ሲሆን የማህበሩን የትግል ገጽታ በአንድ ደረጃ ከፍ እንዳደረጉ ይነገራል። (በኦላና ዞጋ የተጻፈውን «ግዞት እና ግዝት» የተሰኘው መጽሃፍ ውስጥ በስፋት ስለጄነራሉ ማንበብ ይቻላል።) ዛሬ የብ/ጄነራል ታደሰ ብሩን ትግልና መስዋዕትነትን የማያውቅና በልቡ ያላኖረ የኦሮሞ ወጣት ማግኘት ያስቸግራል።
(ምንም እንኳን ለዚህ ጽሁፍ ከላይ ከተጠቀሰው የሚበልጥ አግባብነት ባይኖረውም ጠ/ሚ/ሩ በሌላ አጋጣሚም ንጉሱ ዘንድ የቀረቡትን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኞች ተወካዮች «ንጉሱ እንኳን እናንተን የማንንም ጋላ ያናግራሉ» ብለው መናገራቸው በ «ኮሙኒስቶችም እኛን ይመስላሉና» ላይ ተጽፎልናል)
3. አህመድ ግራኝ (አህመድ ኢብን አል ጋዛሊ)
አህመድ ግራኝ ለዚያ ሁሉ ዘመቻና በቀል እንዲነሳሳ ምን አደረገው? ለዚህ ምላሽ የሚሆን በቂ ጽሁፍ በተክለ ጻድቅ መኩሪያ የታሪክ መጽሃፍት ውስጥ ይገኛል። (በእኔ እይታ ጸሃፊው እንደአብዛኞቹ የሃገሬ ታሪክ ጸሃፊዎች የሚዛናዊነት ችግር ባስተውልባቸውም በዚህ ጉዳይ ላይ ቅሬታ የሚያስቀርብ ነገር አላየሁም። ስለዚህ አንባቢ አንብቦ ይረዳው አሊያ በሌላ ጽሁፍ እመለስበታለሁ ወይም ባለሙያዎቹ ይጽፉበታል።)
4. የኛ ትውልድ
የኔ ትውልድ ያልኩት በዋነኛነት ይሄንን የCyber ትውልድ ነው። በበይነ-መረብ (ኢንተርኔት) ታግዞ የተለያዩ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በማንሳት ያለማቋረጥ የሚያፈሰው ተዋስዖ አጥፊም አልሚም ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ አይጠፋንም። ስንቶቻችን ለሰዎች እና ለነገሮች ያለንን አመለካከት በCyber ላይ ባየነው እና ባጋጠመን ነገር በአሉታዊ መልኩ ተቀይሯል? ስክሪኖች ይቁጠሩት። ይሄ «የአንተም ልክ ነህ፣ አንተም ልክ ነህ» ምክር አይደለም። ጥያቄ ሊሆን ይችላል።
በሰዎች ሳይኮሎጂ ጥናት «የመንጋ ደመነፍስ» ወይም “tribal instinct” መኖሩን ባለሙያዎቹ ይነግሩናል። ይህ ደመነፍስ በየትኛውም አለም ያለ ሲሆን ራሱን በተለያዩ ቡድኖች መኖር ውስጥ ይገልጣል፤ ክርስቲያን-ሙስሊም፣ ዲሞክራት-ሪፐብሊካን፣ ወዘተ . . .እናም ምንም እንኳን የሚፈጸመው በግለሰቦች ቢሆንም በሌላ አቻ ግለሰብ ላይ ያለማገናዘብ ከሚነገሩ/ከሚደረጉ የቃላት ጥቃቶች ይልቅ በነዚህ አይነት ቡድኖች ላይ የሚወረወሩ ያላግባብ አስተያየቶች የበለጠ ትኩረት አግኝተው ውጥረት ይፈጥራሉ። ቅራኔዎችን ያሰፋሉ። የማይታረቁ ልዩነቶችን ብሎም ጠላትነትን ይፈጥራሉ።
ከነዚህ ንግግሮች ወይም የቃላት ምልልሶች መካከል ግን አብዛኞቹ በውይይት ሊፈቱ የሚችሉ፣ የተለየ እሴት የማይጨምሩ በመሆናቸው በውይይት ሊተዉ የሚችሉ አሊያም ሊለወጡ የማይችሉ እውነታዎች በመሆናቸው ከመቀበል ውጪ አማራጭ የሌላቸው ነገር ግን «ለተቃራኒው» ቡድን እንደመሸነፍ እንዳይወሰድ በእልህ የተያዙ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ የታሪክ ልዩነት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ብንል ማጋነን/ሐሰት አይሆንም። አንድ ሰበዝ እንምዘዝ።
የሃገር/መንግስት ምስረታም (State Formation) ሆነ ግዛት ማስፋፋት (Expansion) በሰላማዊ መልኩ ወይም ኃይል ሳይጠቀሙ የሚያሳኩት ነገር አይደለም። ስለዚህ በነዚህ ሂደቶች ወቅት የሚፈጸሙ የተለያዩ ጥፋቶች አሉ። ስማቸው ከተራ ግድያ እስከ ጭፍጨፋ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሊሄድ ይችላል። ይሄ አያከራክርም ምክንያቱም «ጽጌረዳን በሌላ ስም ብንጠራው መዓዛው አይቀየርም።» የሚያከራክረው ጉዳይ ግን ያንን የታሪክ ኹነት የመቀበል ወይም ያለመቀበል እንዲሁም ለአሁኑ ትውልድ ወቀሳ ፍጆታ ማዋል ያለማዋል ላይ ነው።
እዚህ ጋር «አፍቃሬ – የቀድሞ መሪዎች» በእርግጥም አሉ ብለን ብዙ ጊዜ እንዳምን የሚያደርገን ነገር አለ። ያለፉትን መሪዎች የምንከላከልበት (Defend የምናደርግበት) አግባብ ግልጽ አይደለም። ይህ መከላከል የመጣው ከገዢው/ሃገር ከሚያስተዳድረው አካል ቢሆን ኖሮ የሕልውና ጥያቄ የሚያስነሳባቸው ብዙ ሁኔታዎች በመኖራቸው ምክንያቱ ግልጽ ይሆናል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን እንደ ግለሰብ በታሪክ የተፈጸፈሙ ድርጊቶችን መካድ ግን (ለያውም ለትምህርት/አካዳሚክ/ ዓላማ ባልሆነበት እና በማስረጃ ባልተደገፈበት ሁኔታ) ባላጋራ/ጠላት መፍጠር እንጂ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም። እውነቱን ተቀብሎ ያ ስህተት ዛሬ ላይ ጥላውን እንዳያጠላ የሚደረግበት ሁኔታ ላይ መወያየት የተሻለ ረብ አለው።
በሌላ በኩል ደግሞ «የአባት እዳ ለልጅ» የማስተላለፍ አባዜ የተጠናወተው ተዋስኦ ያለመታከት ማካሄድም ተመሳሳይ ውጤት ነው የሚኖረው – ጠላት መፍጠር። በዚህ ዘመን የሚኖር ግለሰብ ተጠያቂነት አሁን ላለበት ዘመን እና ለሚመጣው ትውልድ የተተወ እንጂ ላልነበረበት ጊዜ የሚተላለፍ መሆን የለበትም። ከላይ የተጠቀሰው ያለፈውን ስርዓትና መሪዎች የመከላከል «በሽታው» እንደ ግል ድክመት ሊቆጠር እንጂ ያለፈው አካል ላደረሰው በደል ወይም ስህተት ተጠያቂ የሚያደርገው ሊሆን አይገባም። እነኚህ ሁለቱ በየትኛውም የታሪክ ክርክሮች ውስጥ ሊተገበሩ የሚችሉ ቋሚዎች (Constants) ስለሆኑ መርሆዎች ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው።
ምናልባት ከዚህ አለፍ ስንል በቅርቡ የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ከእርሳቸው እጅግ በጣም ረዥም ጊዜ በፊት ለተፈጸመው በደል ነባሮቹን የሃገሬዎቹን ሰዎች {the Aborigins} በይፋ ይቅርታ መጠየቃቸው የሚያስተምረን ነገር ይኖር ይሆን? Let’s watch our words and stop making an enemy out of our brethren!!!

ማን አለ እንዳንተ፣ ታማኝ?

በፈቃዱ ዘ ኃይሉ

Befeqadu  Ze Hailu
የሆነ ጊዜ የሰማኋት ቀልድ ትዝ አለችኝ፤ አንዳንድ የተቃዋሚ ተወካዮች ፓርላማ ውስጥ በነበሩበት በዚያ በደጉ ጊዜ ነው አሉ፡፡ አንድ ተወካይ የሻዕቢያ መንግሥት ላይ ሊደረግ ስለሚገባው እርምጃ ሲናገሩ እንዲህ አሉ፤ “አሁኑኑ ገብተን ድምጥማጣቸውን ማጥፋት አለብን፡፡ አለበለዚያ ካደሩ አይቆረጠሙም፤ እነዚያ ወያኔዎችም ያኔ ሲመሠረቱ ሳንጨፈልቃቸው ዝም ብለናቸው ነው ዛሬ አናታችን ላይ…” አሉና ያሉበት ቦታ ትዝ ሲላቸው ድንግጥ ብለው ወደአቶ መለስ መቀመጫ አማተሩ፡፡ አቶ መለስ በጥሞና ያዳምጣሉ፤ ተወካዩ እንደደነገጡ “…ልጨርሰው ወይስ ትጨርሰኛለህ?” አሉ ይባላል፡፡

የሕወሓት/ኢሕአዴግ ወታደሮች አዲስ አበባ ደርሰው “ሲቪል” መንግሥት ከመመሥረታቸው አስቀድሞ “እኩይ” ናቸው በሚል ሲቃወማቸው የነበረ እና እስካሁንም ስክነቱ ያልተለየው አክቲቪስት ታማኝ በየነ ነው፡፡ የታማኝ የአክቲቪስትነት ሪከርድ ከኮሜዲያንነቱ የሚመዘዝ ነው፡፡ በቀልዶቹ ቢጀምርም አሁን ግን በጣም ‹ሲሪዬስ› ነው፡፡

አሁን እነቪኦኤ፣ ዶቸ ቬሊ፣ ኢሳት በየቤቱ እንደሚደመጡት ከደርግ ማክተሚያ ቀደም ብሎ ብዙ ሰው በየቤቱ ‹ድምፂ ወያነ›ን በድብቅ ያደምጥ ነበር፡፡ የፕሮፓጋንዳ ሚዲያዎች አመል ነውና ያው ውሸታቸው አይጣል ነው፡፡ ታዲያ ታማኝ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቀርቦ የምሩን ሲቀልድ ‹እዚህ ቦታ ይሄን ያክል ሻለቃ ጦር፣ እዚያ ቦታ ደግሞ ይሄን ያክል ሻለቃ ጦር ደመሰስን ይላሉ፡፡ ሲደመር ግን ይሄን ያክላል፡፡ ቆይ እኔ የምለው ወያኔዎቹ የሚደመስሱት ጦር ከጠቅላላ ጦሩ በለጠ እኮ፤ ከየት እያመጡ ነው የሚደመስሱት?› ዓይነት ቀልድ ተናግሮ አላገጠባቸው፡፡ ከዚያ በድምፂ ወያነ መልስ ተሰጠው፤ “ቁጥሩን አዲስ አበባ ስንደርስ እናወራርዳለን” የሚል፡፡ ዛቻ የሽፍትነት ዘመንም አመል ነበረች፡፡
ግንቦት 20/1983 – ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲረግጥ፣ ሲ ኤን ኤን ካነጋገራቸው ሰዎች አንዱ ታማኝ በየነ ነበር፡፡ “በመሣሪያ ተከበናል፣ ምንም ሠላም የለም…” የሚል ነገር ለጋዜጠኛው ሲነግረው ይታያል፡፡ ታዲያ ታማኝ ሁኔታውን በቀልድ ሲያስታውስ “ጓደኞቼ ከውጪ ደውለው ‹ሲ ኤን ኤን› ላይ አየንህ ሲሉኝ፣ ወዲያውኑ እንግሊዝኛዬ እንዴት ነበር?” አልኳቸው ይላል፡፡

ታማኝ ከአዲሱ ስርዓት ጋር አብሮ መኖር በማይችልበት ሁኔታ የተቀያየመው፣ ካልተሳሳትኩ የወቅቱ ባለሥልጣናት፣ እነታምራት ላይኔ በተገኙበት ስታዲዬም ውስጥ በቀለደው ቀልድ ነው፡፡ እንደማስታውሰው ቀልዱ በማንነት ላይ የተመሠረተ እና ለኢሕአዴግ የማንነት ብያኔ የማይበገር ዓይነት ቀልድ ነው፡፡

ፍቃዱ ማሕተመወርቅ፣ የቀድሞዋ ዕንቁ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነበር፡፡ በመጽሔትና ጋዜጦች አከፋፋይነትም ይታወቃል፡፡ አሁን መጽሔቱ ተዘግቶ “በታክስ ስም” ፍርድ ቤት እየተመላለሰ ይገኛል፡፡ ፍቃዱ ነጻው ፕሬስ ሲጀመር ጀምሮ ምኅዳሩን ያውቀዋል፤ እናም “እናንተ በደጉ ጊዜ ነው የመጣችሁት” እያለ ይቀልድብኛል፡፡ ያኔ (ማለትም የመጀመሪያው አንቀጼ ላይ ‹ደግ› ባልኩት፣ ለፍቃዱ ግን ‹ክፉ› ግዜ) አንድ ሰው ስርዓቱን የሚያስቀይም ንግግር ሲናገር፣ እንዳሁኑ በሕግ ሥም ፍርድ ቤት አይመላለስም፣ የደረሰበት ይጠፋና ከአራት አምስት ወር በኋላ ተመልሶ ይመጣል፡፡ እንዳይሞት እንዳይሽር ተቀጥቅጦ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ከዚያ ወዲህ ያሻሻልነው ነገር ቢኖር ፍርድ ቤት የመቅረብ ዕድል መፈጠሩ ነው ማለት ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህን ያነሳሁት ታማኝ ላይ የደረሰውም እንዲህ ያለው ነገር ነው ለማለት ነው፡፡

ታማኝ ተሰደደ፡፡ ብዙዎች ሲሰደዱ አቅላቸውን ያጣሉ፡፡ የሀገር ቤት ናፍቆት መመለስ ካለመቻሉ ጋር ተደማምሮ ይሁን፣ የሄዱበት አገር ኢሕአዴግ የማይደርስባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ የሚያዩት ነጻነት ስለሚያስቀናቸው አላውቅም ብቻ ጠርዝ ይይዛሉ፡፡ ጥቂቶች ብቻ ሚዛናቸውን በጥፍራቸው ቆንጥጠው ይቆማሉ፡፡ ታማኝ ለኔ ከጥቂቶቹ አንዱ ነው፤ ያውም በረዥም ቆይታ ይህንን ማስመስከር የቻለ፡፡ ታማኝ አሁን አክቲቪዝሙን የሚሠራው ብዙ ጊዜ የቪዲዮ ማስረጃዎችን እያቀረበ ነው፡፡ ቪዲዮዎቹን ዩቱዩብ ላይ ሳያቸው በክምችቱ እቀናለሁ፡፡ ለረዥም ጊዜ የአገር ቤት ጉዳይን እየተከታተሉ፣ ማስረጃዎችን እየሰበሰቡ የመቆየት ፅናት የገቡበትን ጉዳይ ርዝመት እና ክብደት ከመረዳት ይመነጫል፡፡

የማስረጃ ነገር ከተነሳ አይቀር፣ አሁን እነ ታማኝ ማስረጃ ዶት ኮም (masreja.com) የተባለ ድረአምባ ፈጥረዋል፡፡ ድረአምባው በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ የበላይነት ፈንታ ራሳቸው ከሕግ የበላይ ሆነው ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች ላይ ማስረጃ የሚሰበሰብበት ነው፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ እኔ በይቅርታ አምናለሁ፤ እስከዛሬ አዲሱ ያለፈውን እየቀጣ የመጣበት ዑደት ቢያንስ የእኛ ትውልድ ላይ ቢቆም እያልኩ እመኛለሁ፡፡

ይህንን በተመለከተ ጓደኛዬ ሶሊያና “ይቅርታ ከፍትሕ ጋር መጋጨት የለበትም” ብላ ሞግታኛለች፡፡ ልክ ነች፤ በወቅቱ የሰጠችኝን ምሳሌ ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር አዋህጄ ልናገር፤ “‪#‎OromoProtests‬ ላይ ልጇ የተገደለባት እናት የስርዓት ለውጥ ቢመጣ እና ለገዳዩ ወታደር ይቅርታ አድርጊለት ብትባል ፍትሕ ተደረገልኝ ብላ ታምናለች?” በወቅቱ፣ ሶሊም እኔም ጥያቄውን ከመጠየቅ በቀር መልስ መስጠት አልቻልንም፡፡ እርግጥ ነው ልጁ የሞተው የመጣው ለውጥ እንዲመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በምሳሌያችን መሠረት አወዛጋቢው ማስተር ፕላን ቢሰረዝ እንኳን ልጁ የለውጡ እሸት ተጋሪ ላይሆን አልፏል፡፡ ይቅርታ ለአገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ያስፈልግ ይሆናል፤ የቤተሰቡን አባል ወይም ወዳጁን ላጣው ግለሰብ ግን ፍትሕ ሆኖ ይሰማዋል ማለት አይቻልም፡፡ የሆነ ሆኖ፣ ለይቅርታውም ቢሆን ማስረጃውን መሰብሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ አጥፊው ጥፋቱን እንዳይክድ፣ ይቅርታ ጠይቁኝ ባዩም በማስረጃ እንዲሞግት፡፡

ማስረጃ መሰብሰብ ሕገ-ወጥ መስሏችሁ የምትፈሩ ካላችሁ አትሳሳቱ፡፡ ሕጋዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት ራሱ በፀረ-ሙስና ኮሚሽን በኩል አላግባብ የተገኘ ሀብት ካለ በሚል የባለሥልጣናቱን ሀብት ምንጭ ሳይቀር የማጣራት ማንዴት አለው፡፡ ቁርጠኝነቱ ስለሌለ አልተሳካላቸውም፤ እኛ ግን ይሳካልናል፡፡ በየቀኑ ከታችኛው እርከን (ወረዳ) እስከ ላይ ድረስ የምንጠየቃቸውን ጉቦዎች፣ ባለሀብቱና ባለሥልጣናቱ (ሁለቱም አንድ ናቸው) ኢ-ርትዓዊ በሆነ መንገድ የሚያካብቱትን ሀብት፤ ከትላልቆቹ እስከ ትናንሾቹ ሹመኞች በሕዝብ ላይ የሚፈፅሙትን ግፍ፤ ትንንሽሽም፣ ትልልቅም ሠላማዊ ተቃውሞዎች በተነሱ ቁጥር በንፁሐን ዜጎች ነፍስ ላይ የሚሰነዘሩትን የኃይል እርምጃዎች የሚያጋልጡ ማስረጃዎች ባገኘን ቁጥር ለማስረጃ ዶት ኮም በመላክ ለኢትዮጵያችን የወደፊት መልካም ዕጣ ፈንታ ሲባል እንዲከማቹ የበኩላችንን እናድርግ፡፡ ማስረጃዎቹን መሰብሰቡ ሌላው ቢቀር አጥፊዎቹን ስለሚያስፈራቸው በደላቸውን ሊያላሉልን ይችላሉ፡፡
ቪቫ ላ ታማኝ!!!

Source: http://befeqe.blogspot.se/2015/12/Tamagn-and-masreja-dot-com.html

ሰማያዊ ፓርቲ እና መድረክ በጋራ ሰላማዊ ሰልፍ ጠሩ

ሰማያዊ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አዲስ አበባ ላይ በጋራ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራታቸውን የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ነገሰ ተፋረደኝ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እና መድረክ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸው የሚታወስ ሲሆን እሁድ ታህሳስ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በጋራ ሰልፍ መጥራታቸውን አቶ ነገሰ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

Medrek Blueሰማያዊ ፓርቲና መድረክ የጠሩት ሰልፍ በዋነኛነት ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ መንግስት እየወሰደው ያለውን እርምጃ፤ እንዲሁም መንግስት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት ያቀደውን መሬቱ እንዳይሰጥ ለመቃወም ያለመ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሰልፉ ላይ በሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ መንግስት እየወሰደው ያለውን እፈና እና እርጃዎቸ እንደሚያወግዙ ምክትል ሊቀመንበሩ ተገልፆአል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ እና መድረክ በጋራ የሚያደርጉት ሰልፍ መነሻውን ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ አድርጎ፣ በቸርቺል አደባባይ የሚያልፍ ሲሆን መዳረሻው ኢትዮ-ኩባ አደባባይ መሆኑን ታውቋል፡፡ መንግስት እየወሰዳቸው ባሉ የተሳሳቱ እርምጃዎች ሀገራችን አጣብቂኝ ውስጥ መሆኗን የገለፁት አቶ ነገሰ ተፋረደኝ ሀገራችን ካለችበት ችግር ለማውጣት ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲቆሙና በሰልፉም እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሰልፉ እሁድ ታህሳስ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3 ሰዓት ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ ላይ እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ኢትዮጵያ

ኦሮሞ ነኝ!! ኢትዮጵያዊ ነኝ!! አሸባሪ አይደለሁም!!

ገመቹ መረራ ፋና

Oromo protests

*
ይኼንን የምፅፈው በብዙ ነገሮች ስለተረበሽኩ ነው፤ ጎኔን ከፍራሼ በጊዜ ባዋድድም እንቅልፍ ሊወስደኝ ስላልቻለ ከተጋደምኩበት ተነስቼ ነው። በየቀኑ የምሰማው እና የማየው ነገር እነ1984ን እና Hunger Gamesን አይነት ፊልሞች የምመለከት እንጂ የምር እየኖርኩት ያለሁት ነገር እየመሰለኝ አይደለም። መጪው ጊዜ ብሩህ አይደለም!!! ጭለማ እና አስፈሪ ሆኖብኛል።
* * *
ይሄ ሌሎች ሰዎች ላይ የደረሰ ሳይሆን በኔው በራሴው ላይ የደረሰና የኖርኩት ገጠመኝ ነው፦
አምቦ፣ ሕዳር 1998 ዓ/ም።
ከትምህርት ቤት ሲወጡ እዚያው ትምህርት ቤት በር ላይ ስለተገደሉት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች አላወራላችሁም። በሰላማዊ መንገድ ያለምንም ሁከት ተቃውሟቸውን ያሰሙ ልጆች ላይ ፊት ለፊት ጥይት ስለሚተኩሱ «ሰላም አስከባሪዎች»ም አልተርክም። አዎ የተገደሉት ከተገደሉ በኋላ በአንድ ዝም ባለ ቀን የተደረገ ነገር ነው።
በዚህ ዕለት አሁን በሕይወት የሌሉ አያቴን እያስታመምኩ ለማደር ከሰፈር ወጥቼ አያቴ ወደተኙበት ወደ አምቦ ሆስፒታል እያመራሁ ነበር። ወደዋናው የአስፓልት መንገድ ልደርስ አንድ ቅያስ ሲቀረኝ በስፍራው የነበሩት ሁለት ፌዴራል ፖሊሶች ጠሩኝ። ምርጫ አልነበረኝም፤ እየቀፈፈኝ ወደቆሙበት ጥግ ሄድኩ።
«መታወቂያ!» ሲል ጮኸብኝ አንደኛው ፌዴራል ፖሊስ ዱላውን እያሽከረከረ። አረንጓዴዋን የቀበሌ መታወቂያዬን ከኋላ ኪሴ አውጥቼ ሰጠሁት። ያሽከረክረው የነበረውን ዱላውን ትከሻዬ ላይ አሳረፈው። «ማን ይሄን ጠየቀህ?! የኦነግ መታወቂያህን አውጣ!» ሲል ጮኸብኝ።
«ኧረ የለኝም…» ንግግሬን አልጨረስኩም። የሁለተኛው ፖሊስ ዱላ አረፈብኝ። የተለያዩ መልስ የማይፈልጉ ጥያቄዎች እየጠየቁ በእግራቸው ተቀባበሉኝ። ሲበቃቸው «ሂድ ከዚህ ጥፋ፣ እናንተ ናችሁ ያስቸገራችሁት..» አሉኝ። ተነስቶ ለመሄድ የሚያስችል አቅም ግን አልነበረኝም፤ ይሄም ለሌላ ዱላ ዳረገኝ። እንደምንም ታክሲ ይዤ ሆስፒታል ደረስኩና አደርኩ። ያንን ድብደባ የማልረሳበት ሌላም ምክንያት አለኝ።
* * *
ይሄ መንገድ እየሄድኩ ሳለሁ የገጠመኝ ነገር ነው። ለተቃውሞ ድምፁን ያሰማ ሰው ደግሞ ምን ሊደርስበት ነው? መገመት ነው። ኦሮሞ ስለሆንኩ፣ ጥያቄ ስለጠየቅኩ፣ አንገቴን ቀና አድርጌ ስለሄድኩ «ኦነግ» የሚል ታፔላ በማንም እንዲሰጠኝ አልፈልግም!!! ሰው ነኝ!!! ኢትዮጵያዊ ነኝ!!! ኦሮሞ ነኝ!!! አሸባሪ ግን አይደለሁም!!! አባቶቼ ለዚህች አገር እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ደምተዋል። ቅድም አያቴ ትግራይ ድረስ ሄደው ዘምተው የሃገራቸውን ዳር ድንበር ሲያስከብሩ ተሰውተዋል። ከማንም ያልበለጥኩ፣ ከማንም ያላነስኩ የዚህች አገር ዜጋ ነኝ።
* * *
ይሄንን እና ሌሎችም ነገሮችን በጭንቅላቴ እንደሰነግኩ ነው እንግዲህ ወደ መቐለ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት የሄድኩት። እዚያ እንደደረስኩም ብዙ ሳንቆይ ነበር የብሔር ግጭት የተነሳው። በኋላ ላይ ሲጣራ አንዲት ልጅ አፍቅሮ ራሱን ባጠፋ አንድ የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ምክንያት ነበር «እኛም አንድ ኦሮሞ መግደል አለብን» ተብሎ በጠራራ ፀሃይ የተዘመተብን። እኚህ ጥቂት የተማሩ ደደቦች የፈፀሙት ድብደባና ሌሎች አስፀያፊ ድርጊቶች የትግራይን ወይም የመቐለን ሕዝብ ይገልፁት ነበር? በፍጹም!!!
ለአራት አመታት የኖርኩበት ይህ የትግራይ ሕዝብ ከተማሪው ሸሽቶ ከዩኒቨርሲቲው ጊቢ በመውጣት በደመነፍስ ወደ ሃይማኖት ተቋማት እና ሌሎች ስፍራዎች የሸሸውን የሌላ ክልል ተማሪ ምግብና መጠለያ ሰጥቶ ክፉ ቀኑን ያሳለፈለት ደግ ሕዝብ ነው!! ታምሜ ለሳምንት በተኛሁበት አጋጣሚ በአካል እንኳን ሳታውቀኝ መታመሜን ስትሰማ «ወይኔ ልጄን» ብላ በልጇ ምግብና ማር የላከችልኝን እናት ያገኘሁበት ሕዝብ ነው!! ምንም የማያውቀኝን እኔን ተቀብሎ ቤቴ ያለው እንዲመስለኝ አድርጎ የተንከባከበኝ፣ ከአባቴ ያላነሰ ገንዘብና ሞራል እየሰጠ ለአራት አመታት ከአጠገቤ ያልተለየ አባት ያገኘሁበት ሕዝብ ነው!! የዚህን ሕዝብ ደግነት በጥቂቶች ድድብና በዜሮ ላባዛው? የተወሰኑ ፖለቲከኞች አሊያም «አክቲቪስቶች» ድርጊትና ንግግር ይሄንን እውነት ይሰውርብኝ? ፈጽሞ!!!!!!
አዎ እንዲህ አይነት የደግነት ታሪኮች በሌሎች አካባቢዎችም ብትሄዱ በብዙ ትሰማላችሁ። በተቸገረ ሰው ጨክኖ «ብሔሩ ምንድነው?» የሚል ሕዝብ የትም ቦታ የለም። ስለኖርኩብትና ስላሳደገኝ ስለደጉ የኦሮሞ ሕዝብ ሌላ ጨምሬ የምናገረው ነገር የለኝም። በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች በበቂ ሁኔታ ተነግሯል። በቅርቡ፣ በጣም በቅርቡ ግን በረባውም ባልረባውም በዘር መከፋፈል ነው የማየው። የሃይማኖት ጉዳይ ሆኖበት «የክርስቲያን/የሙስሊም ስጋ አልበላም» ይል የነበረው ማህበረሰባችን «የኦሮሞ/አማራ/ትግሬ ስጋ አልበላም» የሚልበት ጊዜ የመጣ እስኪመስል ድረስ ልዩነት በባትሪ ይፈለጋል። እርስ በርስ የሚያባላን የከፋ ችግር የለብንም። እንደሌላው ዓለም የዘር (race) ችግር የለብንም፤ ሁላችንም ጥቁር ነን። ተመሳሳይ ኑሮ የምንኖር፣ የመግባቢያ ችግር የሌለብን፣ ለዘመናት ስንጋባና ስንዋለድ የኖርን ሕዝቦች ነን። አንዱ «ብሔር» ከአንዱ «ብሔር» በከፋ ሁኔታ፣ አንዱ ሃይማኖት ከሌላኛዎቹ ሃይማኖቶች በተለየ ሁኔታ በተለያዩ ሥርዓቶች የተገፋበትን ሁኔታ አይተናል። አዎ ሥርዓቶች፣ መንግስታት/ገዢዎች ያልፋሉ፣ በሌላም ይተካሉ፤ ይህ ያለና የነበረ የተፈጥሮ ሥርዓት ነው። ሕዝቦች ግን አያልፉም።
ብሔር አጣርተው አይደለም ወላጆቻችን ለጎረቤታቸው ችግር ሲደርሱ እና ሲደረስላቸው የኖሩት። ብሔር ተጠያይቀን አይደለም እዚህ የደረስነው። ብሔር ቆጥረን አይደለም ምርጥ ጓደኞቻችንን ያፈራነው። ሰውነታችንን አስቀድመን ነው!!! ዛሬ በማወቅም ባለማወቅ የሚደረጉ የብሔር የርስ በርስ ግጭት ውስጥ መግባት የለብንም። ያ እንደ ብሔርም ሆነ እንደ ሃገር የማንወጣው አዘቅት ውስጥ ነው የሚከተን። አሁን ያለንበትንም ይሁን ያለፍንበትን ልዩነት በእጅጉ የሚያስመኝ ክፉ አዘቅት ውስጥ!!!
ተዋጠልንም አልተዋጠልን ተዋልደናል። ተዋደናል። ተዛምደናል። ተጋምደናል። የተሻለችዋን ነገኣችንን ልንፈልግና ልናገኝ የምንችለው አንዲት የሁሉንም ሰው መብት እና ሰብዓዊ ክብር በምትጠብቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። ከታሪክ ልንማር ይገባል ምናምን አልልም። አይናችንን አንስተን ደቡብ ሱዳንን ማየት በቂአችን ነው። ከሱዳን እስክትገነጠል ድረስ ፅኑና የሚገርም ትግል ለዓመታት አድርጋለች። ከተገነጠለች በኋላ ግን የሆነችውን ሆናለች። የኛም የተናጠል ጉዞ መድረሻው ያው ነው። አማራ ቢገነጠል ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ሸዋ እያለ ይናከሳል። ኦሮሚያ ብትገነጠል ሸዋ፣ ሐረርጌ፣ ወለጋ፣ አርሲ እያለ ይባላል። ትግራይ ቢገነጠል ተምቤን፣ እንደርታ፣ ዓድዋ፣ ሽሬ እያለ ይጫረሳል። «ታግሎ» ሲያበቃ «ነፃ» ባወጣት «ሃገር» የሚፈጠረው ቀውስ የዳር ተመልካች መሳቂያ ያደርገዋል።
* * *
አይን የሌለው ኢፍትሃዊነትን በሚተገብር እና ግፍ በሚፈፅመው አካል ሳይሆን ዳር ሆኖ ያንን ድርጊት በሚደግፈው ሰው ልቤ ትደማለች። ከክቡሩ የሰው ልጅ ሕይወት ይልቅ በተራ የንብረት መውደም የሚብሰከሰከውን ብኩን ሳይ ነፍሴ ክፉኛ ታዝናለች። ልጁን በሞት ካጣ ወላጅ ሃዘን ይልቅ ወደፊት ምናልባት ኪሴ ሊገባ ይችላል ብሎ ለሚያስበው ሽራፊ ሳንቲም በሚቆረቆር «ሰው» ንቀቴ ይበረታል። ትናንት እርሱ ላይ ሲጫን የነበረውን የበደል ቀንበር ዛሬ ባለቀን ሆኖ ሌላው ላይ አክብዶ በሚጭነው ላይ ጥላቻዬ ይከራል። አንድ ሕሊና ያለው ሰው እንዴት በባዶ እጅ በወጣ ሰልፈኛ ላይ ቀጥታ የተተኮሰን ጥይት ደግፎ ሊናገር ይችላል? አንድ ችግር የኛን ቤት እስኪያንኳኳ ድረስ የባለቤቱን ያህል ላይሰማን ይችላል፣ ነገር ግን እንዴት በተቃራኒ ያስቆማል? አላውቅም። የዚህ አይነት አስተሳሰብ አይገባኝም።
* * *
Rabindranath Tagore «Gitanjali» በተሰኘው መድብሉ ውስጥ በጣም የምወድለት እንዲህ የምትል የልመና/የፀሎት ግጥም አለችው፦
Where the mind is without fear and
the head is held high;
Where knowledge is free;
Where the world has not been broken
up into fragments by narrow domestic walls;
Where words come out from the depth of truth;
Where tireless striving stretches its arms towards perfection;
Where the clear stream of reason has not
lost its way into the dreary desert of
dead habit;
Where the mind is led forward by Thee
into ever-widening thought and action—
Into that heaven of freedom, my Father,
let my country awake.
አሜን!!
* * *
ኦሮሞ ነኝ!! አሸባሪ አይደለሁም!!
#‎OromoProtests‬
‪#‎StopKillingCivillians‬
‪#‎StopKillingUnarmedProtesters‬

%d bloggers like this: