Daily Archives: December 4th, 2015

ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የቀረበውን የአቃቤ ህግ ይግባኝን ውድቅ አደረገ

ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ምስክር ሆነው እንዳይቀርቡ ያቀረበውን ይግባኝ ዛሬ ህዳር 23 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውድቅ አደርጎታል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በእነ ዘመነ ካሴ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ድረስ ለተጠቀሱት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ተጠይቆ የነበር ቢሆንም ማረሚያ ቤቱ በተደጋጋሚ ሳያቀርባቸው ቀርቷል፡፡

Andaregachew Tsigie
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ምስክርነት በተጠሩበት ወቅት የፌደራል አቃቤ ህግ “አቶ አንዳርጋቸው በእነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ እና በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መዝገብ ላይ ክስ ቀርቦባቸው በእድሜ ልክና በሞት እንዲቀጡ ተወስኖባቸው የህዝባዊ መብታቸው የተሻረ በመሆኑ በምስክርነት ሊቀርቡ እንደማይችሉ መቃወሚያ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው እንዲቀርቡላቸው የጠየቁት ለዋስት አሊያም ልዩ አዋቂ ምስክር ሆነው ሳይሆን ነበሩበት የተባለውን ጉዳይ ለመናገር በመሆኑ ለምስክርነት ሊቀርቡ ይገባል” በሚል የፌደራል አቃቤ ህግ ያቀረበውን ተቃውሞ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
የልደታ ፍርድ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሀምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ቀርበው ምስክርነት እንዲሰጡ ከወሰነ በኋላ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት “ትዕዛዝ አልደረሰኝም፣ የተፃፈው ለቃሊቲ ሳይሆን ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት የሚል ነው” እና ሌሎችም ምክንያቶች በማቅረብ በተደጋጋሚ አቶ አንዳርጋቸውን ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡ በስተመጨረሻም ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም ማረሚያ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ቃሊቲ እንደሌሉ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ከተከሰሱት መካከል አቶ ደናሁን ቤዛ (3ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን (4ኛ ተከሳሽ) ውጭ ያሉት የፍትህ ሂደቱ እየተጓተተባባቸው በመሆኑ የአንዳርጋቸው ፅጌ ምስክርነት ቀርቶ በሌሎች መረጃዎች ውሳኔ እንዲሰጥላቸው ሲጠይቁ ሁለቱ ተከሳሾች ግን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሊመሰክሩላቸው እንደሚገባ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡
በዚህም መሰረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለፀረ ሽብር ግብረ ኃይልና አቶ አንዳርጋቸውን ጠይቀውታል ለተባሉት የብሪታኒያ አምባሳደር ደብዳቤ መፃፋቸው ይታወቃል፡፡ ይሁንና ተከሳሾቹ ለሶስቱ አካላት ደብዳቤውን በፃፉበት ማግስት የፌደራል አቃቤ ህግ ከወራት በፊት ለልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ መመስከር አይገባቸውም ብሎ አቅርቦት የነበረውን መከራከሪያ መሰረት በማድረግ አቶ አንዳርጋቸው ምስክር እንዳይሆኑ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቆ ነበር፡፡
የአቃቤ ህግን ይግባኝ ያየው ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ዛሬ ህዳር 23 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት “አንድ ሰው ለምስክርነት ይቅረብ አይቅረብ በሚል ይግባኝ ሊጠየቅበት አይገባም፡፡ ካስፈለገ ግለሰቡ የሰጡት ምስክረነት መረጃው ተመዝኖ የሚሰጠው ፍርድ ላይ ይግባኝ ሊባል ይችላል፡፡ እኛም ጉዳዩን ለማጣራት ምስክርነቱ እንዲቋረጥ አድርገን የነበር ቢሆንም አሁን ግን እንዲቀጥል ወስነናል፡፡ የአቃቤ ህግን ይግባኝም አልተቀበልነውም” ሲል ይግባኙን ውድቅ አድርጓል፡፡ አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ምስክር መሆን የለባቸውም ብሎ ያቀረበው ክርክር በፍርድ ቤት ውድቅ ሲሆንበት ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
በእነ ዘመነ ካሴ መዝገብ ከተከሰሱት በተጨማሪ በእነ ዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት ጠርቷቸዋል፡፡ በሌሎች የክስ መዝገቦች ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ተገናኝታችኋል የተባሉ ተከሳሾችም አቶ አንዳርጋቸውን የመከላከያ ምስክር አድርገው ሊጠሯቸው እንደሚችሉ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ባሉ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ላይ መንግሥት በወሰደው የኃይል እርምጃ ከ5 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ በርካቶች ቆስለዋል

ህዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ጊኒጪ ከተማ እንደገና የተጀመረው አዲሱን የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ትግበራን የተቃወሙ ተማሪዎች ላይ መንግሥት በወሰደው የኃይል እርምጃ እስካሁን የ5 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ እና በርካታ ተማሪዎችም መጎዳታቸው ታውቋል፡፡ በተለይ እንደ አዲስሚዲያ ምጮች ከሆነ፤ የተማሪዎች ተቃውሞ በምዕራብ ኢትዮጵያ በጊኒጪ፣ በአምቦ፣ በምዕራብ ወለጋ የተቀጣጠለው ተቃውሞ ሌሎችንም የምዕራብ ሸዋ ከተሞችን አዳርሶ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ሐረማያ ዩኒቨርስቲ መድረሱ ታውቋል፡፡

Sululta 1

በተለይ በሐረማያ ዩኒቨርስቲ ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጥያቄ ባነሱ ተማሪዎች ላይ መንግሥት በወሰደው የኃይል እርምጃ 1 ተማሪ ሲገደል፣ ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቁ በርካቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡ በተለይ ህዳር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ሐረማያ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በዩኒቨርስቲው ክልኒክ እና በሐረር ሆስፒታል የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ከነበሩት መካከል በዩኒቨርስቲው ክልኒክ የህክምና እርዳታ ሲደረግለት የነበረ አንድ ተማሪ ህይወቱ ማለፉን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተማሪዎች ላይ እየወሰዱ ባሉት የኃይል እርምጃ በምዕራብ ወለጋ ግሊሶ ከተማ ሌላ አንድ ተማሪ መገደሉ የተጠቆመ ሲሆን፤ እስካሁን በፀጥታ ኃይሉ የተገደሉ ተማሪዎች ቁጥርም 5 መድረሱ ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በሱሉልታ ጫንጮ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ባነሱት ተመሳሳይ ጥያቄ በርካታ ተማሪዎች በመንግሥት በተወሰደባቸው የኃይል እርምጃ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ተቃውሞው በኦሮሚያ ክልል ካሉ አንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ የተቀጣጠለ ሲሆን፤ በተለይ በጫንጮ አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መንግሥት በወሰደው የኃይል እርምጃ የአንደኛ ደረጃ ህፃን ተማሪዎች ላይ ሳይቀር ጉዳት መድረሱን ምስልን አስደግፈው የአካባቢው ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

Sululta

መንግሥት በተማሪዎች ላይ እየወሰደ ባለው የኃይል እርምጃ ከክልሉ ተወላጆች በተጨማሪ በርካታ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፤ ተቃውሞው ወደክልሉ ሌሎች ከተሞች እና ዩኒቨርስቲዎችም እየተዛመተ በመሆኑ በየአካባቢው ከተሞች ባሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርስቲዎች ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ ቁጥጥር ላይ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ ተቃውሞው ወደባሌ መዳወላቡ ዪኒቨርስቲም መዛመቱ መዛመቱን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ በበቾ እና በቱሉቦሎ ከተማ እንደዚሁም በደቡብ ሸዋ ወሊሶ አካባቢ በዲላላ ከተማ ውስጥ ያሉ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተቃውሞ እያደረጉ እንደሆነም የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዘገባ አመልክቷል፡፡ የተቃውሞው ዋነኛ ምክንያትም መንግሥት ይፋ ያደረውና እስካሁንም ከህዝብ ጋር ያልተመከረበትና ተግባራዊ ለማድረግ ከመንቀሳቀስ በስተቀር በምስጢር ተይዟል የተባለለት አዲሱ የአዲስ አበባ እና የአካባቢው የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የጋራ የተቀናጀ ማስተር ፕላን በአካባቢው ያሉ ገበሬዎችን ያለ በቂ ካሳ ያፈናቅላል፣ የአካባቢው ኦሮሞ ማኀበረሰብ ባህልና ቋንቋ ያጠፋል እና ኦሮሚያ ክልልን ለሁለት ይከፍላል የሚሉ ጥያቄዎች እንደሚገኙበት ለአዲስ ሚዲያ የደረሱ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ አዲሱ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ባለፈው ግንቦት 2006 ዓ.ም. ተቀስቅሶ በነበረው ተመሳሳይ የተማሪዎች ተቃውሞ ከ40 በላይ ወጣቶች ሲገደሉ፤ በርካቶች መጎዳታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህንንም ተከትሎ ተቃውሞውን አነሳስታችኋል ተብለው የታሰሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አሉ፡፡ በተለይ ዛሬ ህዳር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ልደታ ምድብ ችሎት ከግንቦት 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ ከነበሩት 6 ተማሪዎች መካከል 5ቱን ጥፋኛ ሲል መበየኑን እና እንዲከላከሉ ለማክሰኞ ጥር 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱን ታውቋል፡፡ ጥፋተኛ ተብለው እንዲከላከሉ ከተበየነባቸው ተማሪዎች መካከል አበበ ኡርጌሳ፣ መገርሳ ወርቁ፣ አዱኛ ኬሶ፣ቢሊሱማ ዳመነ እና ተሾመ በቀለ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከተማሪ ተሾመ በቀለ በስተቀር የቀሪዎቹ አራቱን ተከሳሾች የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ መደረጉንም የአዲስ ስታንዳርድ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በጎንደር የ17 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን መንግሥት ሲያምን፤ አንዱን የገደልኩት እኔ ነኝ ብሏል

በጎንደር ህዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በእስር ቤት ላይ በደረሰ ቃጠሎ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተነገረ፡፡ መንግሥት ከቃጠሎው ወቅት አንድ ሰው መግደሉን ሲያምን ሌሎቹ 16 ሰዎች ህይወት የጠፋው በቃጠሎው ወቅት ከ እስር ቤቱ ለማምለጥ ሲጋፉ ነው ብሏል፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ለመንግስት ሚድያ በሰጠው መግለጫው በህዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ወህኒ ቤት ከቀኑ 7፡30 ሰዓት አካባቢ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ እስረኞች ከቃጠሎው ለመውጣት በተደረገው ግፊያ የ16 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ አንድ ሰው ሊያመልጥ ሲል ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መገደሉን አምኗል፡፡

Gonder prison
እንደ ዓይን እማኞች ከሆነ ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቁጥር ከ42 በላይ እንደሚሆን እና መንግሥት ቁጥሩን ዝቅ በማድረግ በእጁ የጠፉትን ቁጥር ወደ አንድ ብቻ ማሳነሱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ እንደ ዓይን እማኞች ገለፃ ከሆነ በቃጠሎው ወቅት መንግሥት በእስረኞች ላይ ጠከታታይ ተኩስ ከፍቶ እንደነበርና የእስረኞችንም ህይወት ለማትረፍ ማንም ወደ አቅራቢያው እንዳይጠጋ የጥብቃ ኃይሎች እና ፖሊሶች ማንም የውጭ ሰው እንዳይጠጋ ሲያስፈራሩ እንደነበር ጠቁመው፤ ከሞቱት መካከል አብዛኛው በመንግሥት እጅ የተገደሉ እንጂ ከእስር ቤት ከእሳት ለማምለጥና ለመውጣት ሲጋፉ እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡
ከሞቱት በተጨማሪ በቃጠሎው በርካታ እስረኞች ጉዳት እንደደረሰባቸውና በጎንደር ሆስፒታል የህክምና እርዳታም እየተደረገላቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ የቃጠሎውን መንስኤና የተጎዱትንም ሆነ የሞቱን በተመለከተ እስካሁን በገለልተኛ አካል የተጣራ ነገር አለመኖሩ ታውቋል፡፡
በተለይ በሰሜን ጎንደር ዞን ከቃጠሎው በፊት ባሉት ቀናት የቅማንት ማኀረሰብ ባነሱት የመብት ጥያቄ ፖሊስ በወሰደው የኃይል እርምጃ እስካሁን በገለልተኛ አካልም ሆነ በመንግሥት ተጣርቶ ይፋ ባይደርግም በርካታ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውና የተወሰኑትም ምስሎቻቸውም በማኀበራዊ ሚዲያ ይፋ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

የወህኒ ቤቱ ኃላፊ በቃጠሎውም ሆነ በመንግሥት ኃይሎች እርምጃ የሞተ ሰው የለም በሚል ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ 16ቱ በቃጠሎው ወቅት በተፈጠረ መገፋፋት ሲሞቱ አንዱ ግን ሊያመልጥ ሲል በወህኒ ቤቱ ጥበቃ አባላት መገደሉን በማመን እስካሁን 17 ሰዎች መሞታቸውን አምነዋል፡፡ በተለይ በዞኑ ሰሜን ጎንደር መንግሥት በህዝቡ ላይ እየወሰደ ስላለው የኃይል እርምጃ እና በጎንደር ወህኒ ቤት በቃጠሎው እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር መደበቅና መቀነስ የተበሳጩ የጎንደር ዩኒቨርስቲ በተለይ ማራኪ እየተባለ በሚጠራው ግቢ የተማሪዎች ተቃውሞ መቀስቀሱን ተሰምቷል፡፡ በአሁን ወቅትም ተቃውሞው ወደሌሎች የዩኒቨርስቲው ግቢ እና ወደ ሌሎች የክልሉ ተቋማት ሊስፋፋ ይችላል በሚል ስጋት ዩኒቨርስቲው በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ተከቦ ጥብቅ ቁጥር እየተደረገበት መሆኑንም የአዲስ ሚዲያ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

 

%d bloggers like this: