Daily Archives: March 16th, 2016

በኮንሶ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ሁለት ሰዎቸ ተገደሉ

በደቡብ ክልል ከዚህ ቀደም በልዩ ወረዳ አስተዳደር የነበረና በአሁን ወቅት የሰገን አካባቢ ዞን ስር ወደ ወረዳ አስተዳደርነት እንዲወረድ የተደረገው የኮንሶ ማኀበረሰብ አባላት የዞን አስተዳደር መዋቅር እንዲፈቀድላቸው መጠየካቸውን ተክትሎ በመንግሥት ተጣቂዎች በተወሰደ እርምጃ በግብርና የሚተዳደሩ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል፡፡

እሁድ መጋቢት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀትር ላይ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉት አቶ ሞሌ አዛዥ እና አቶ ፋንታዬ ጊዮርጊስ በግብርና ሙያ የሚተዳደሩ ጎልማሶች እንደሆኑ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ከተገደሉት በተጨማሪ 3 ሰዎች በፀኑ የቆሰሉ ሲሆን፤ ማኀበረሰቡም የተገደሉ 2 አስከሬኖች ይዞ ወደ ካራት አደባባይ በመውጣት ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማቱ ታውቋል፡፡

Konso Protest Ethiopia

የአዲስ ሚዲያ መረጃዎች እንዳረጋገጡት፤ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ አሁንም በኮንሶ በርካታ የደቡብ ልዩ ፖሊስ ኃይል የደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች በኮንሶ ዋና ከተማ ካራት እና በተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች ጭምር እንደሰፈሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የህዝባዊ ተቃውሞ ዋነኛ ምክንያት 55ሺህ የኮንሶ ማኀበረሰብ ስምና ፊርማ ያለበት ስምምነት ወደ ዞን አስተዳደር እንደግ የሚል ጥያቄ ከደቡብ ክልል እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስገባታቸውና መንግሥትም በሐረገ-መንግሥቱ መሰረት ተገቢውን መልስ ሳይሰጥ ከልዩ ወረዳነት ወደወረዳነት በማውረድ ጥያቄያቸው ምላሽ ባለማግኘቱ በተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ተቃውሞንም ተከትሎ የኮንሶ ባህላዊ ንጉስ ካላ ገዛኸኝ ወልደ ዳዊትን ጨምሮ ከ200 ያላነሱ የአካባቢው ዜጎች መታሰራቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ መንግሥት የሰጠው ይፋዊ ምላሽ ባይኖርም በአካባው ከፍተና ውጥረት መኖሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የደረሰውን የሰብዓዊ ጉዳት አስመልክቶ በ33 ወረዳዎች ብቻ 103 ዜጎች መገደላቸውን የሚገልፅ ገለልተኛ የምርመራ ሪፖርት ይፋ ሆነ

HRCO-logo-150x150

ከህዳር አጋማሽ 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ተጀምሮ በነበረው እና መላው ኦሮሚያ ክልልን ያዳረሰው ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ የደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት ልዩ የምርመራ ሪፖርት መግለጫ ይፋ ሆነ፡፡ ልዩ መግለጫው ይፋ የሆነው መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው የሰመጉ ዋና ጽህፈት ቤት ሲሆን፤ መግለጫውም የ103 ዜጎች ህይወት መጥፋቱን አስታውቋል፡፡

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ይባል የነበረውና በኋላም የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ(ሰመጉ) እየተባለ የሚጠራው ብቸኛው ሀገር በቀል መነግሥታዊ ያልሆነ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሲሆን፤ ባለፉት አራት ወራት በተጀመረውና እስካሁንም በቀጠለው የኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ የሰብዓዊ ጉዳት ቀዳሚውን ልዩ መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡ ሰመጉ በ140ኛው የተቋሙ ሪፖርት “የኦሮሚያ ክልል በ18 ዞኖች እና በ342 ወረዳዎች የተከፋፈለ ሲሆን ሰመጉ ከ9 ዞኖች ውስጥ በ33 ወረዳዎች ብቻ ባደረገው የመስክ ምርመራ ባገኘው ውጤት መሰረት 103 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 57 ሰዎች በጥይት የመቁሰል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡” ብሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተገደሉትና ከቆሰሉት በተጨማሪ በ22 ሰዎች ላይ ማሰቃየት እና ድብደባ መፈፀሙን፣ 84 ሰዎች መታሰራቸውን እንዲሁም 12 ሰዎች የደረሱበት ወይም ያሉበት አለመታወቁንም ጠቁሟል፡፡

TPLF victims in Oromia region

ሰመጉ 34 ገፅ ባለው ልዩ መግለጫው እንዳስታወቀው ከሆነ፤ የደረሰው የሰብዓዊ ጉዳት ምርመራ የሚያካትተው ከህዳር 2 ቀን እስከ የካቲት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. የደረሱ የሰብዓዊ ጉዳቶች ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በተለይ በምርመራ ወቅት ድርጅቱ የጋጠሙትን ችግሮችም የጠቀሰ ሲሆን በተለይም የገንዘብ ፣ የሰው ኃይልና የምርመራ መሳሪያ እጥረት፣ በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ውጥረት የተሞላበት በመሆኑ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ቀውስ እንደልብ ተዘዋውሮ ለመስራት አለመቻል፣የመንግሥት የደህንነት እና የፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ጫና እና ክትትል ማድረጋቸው፣ ሕዝቡ ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ በመግባት ማንንም ሰው አለማመን እና መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን ዋነኞቹ መሆናቸው ጠቅሷል፡፡

በክልሉ አሁንም በተለያዩ ቦታዎች ተቃውሞች መቀጠላቸውንም በመጥቀስ፣ ማንኛውም የሰብዓዊ መብት የሚመለከተው አካል የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት እንዲያከብር፣ እንዲያስከብርና እንዲያስጠበቅ ጫና እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡

ሙሉ መግለጫውን ከዚህ ቀጥሎ ያለውን መስፈንጠሪያ (ሊንክ) በመጠቀም ያገኙታል፡- http://ehrco.org/wp-content/uploads/2016/03/The-Human-Rights-Council-HRCO-140th-Special-Report-Amharic-Scanned-March-14-2016.pdf

%d bloggers like this: