Daily Archives: March 9th, 2016

ቅዱስ ሲኖዶስ: ፓትርያርኩ ሕግ አክብረውና መዋቅር ጠብቀው እንዲሠሩ አስጠነቀቃቸው፤ በወቅታዊ ሰላም ጉዳዮች መግለጫ አውጥቷል

• በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያስተላለፏቸው መመሪያዎችና የጠሯቸው ስብሰባዎች ሕገ ወጥ ተብለዋል
• ቋሚ ሲኖዶስ፥ የስምዐ ጽድቅን የፀረ ተሐድሶ ጽሑፍ ጨምሮ የተደረጉ መጻጻፎችን ይመረምራል
• የፓትርያርኩ ጉዞዎች፥ ስፖንሰር ተገኘ በሚል ሳይኾን በቋሚ ሲኖዶሱ ማስወሰን ይኖርባቸዋ

EOTC Holy Synod

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ መዋቅር ጠብቀው በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑና ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ በቅዱስ ሲኖዶስ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ የካቲት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ባካሔደው ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጽሑፎች ላይ ቀርበዋል ለተባሉ አቤቱታዎች የነበራቸውን አያያዝ፣ የወሰዷቸውን አቋሞችና የሰጧቸውን ምላሾች ገምግሟል፡፡

ፓትርያርኩ አቤቱታዎቹን ለመመልከት በሚል በራሳቸው የጠሯቸው የኮሌጆችና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ መምሪያዎች ሓላፊዎች ስብሰባዎች፤ ማእከላዊ አሠራርን ያልጠበቁና አድሏዊ እንደነበሩ ጉባኤው ተችቷል፡፡ ከዚኽም ጋር በተያያዘ ፓትርያርኩ፣ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በተጻፉ ደብዳቤዎች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያስተላለፏቸው የክሥና የቅስቀሳ መመሪያዎች የቅዱስ ሲኖዶስን የምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መንፈስ የሚፃረሩና ሕገ ወጥ መኾናቸውን ያረጋገጠ ሲኾን በስብሰባዎቹ ወጥተዋል የተባሉ የአቋም መግለጫዎችም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ተገልጧል፡፡

ፓትርያርኩ ዛሬ ለተጀመረው ዐቢይ ጾም ባለፈው ሳምንት ዓርብ መግለጫ በሰጡበት አጋጣሚ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ በብፁዕ ዋና ጸሐፊው አማካይነት በጠራው በዚኹ ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን በኃይለ ቃል ለማሸማቀቅ ሞክረዋል፤ ማኅበሩንም በተመለሱ ጥያቄዎችና በአሉባልታዎች ወንጅለዋል፡፡ “የማኅበሩ አባላት ናችኹ፤ ሒዱ ስላላችኹ ነው የመጣችኹት” በማለት የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ማኅበሩንም “ሀብታሞች ኾነዋል፤ ከመንግሥትም ገንዘብ ይሰበስባሉ፤ መንግሥት ይረዳቸዋል፤” እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡
ተንኮል የተሸረቡባቸውንና በክፋት የተሞሉ መረጃዎችን ሳያጣሩና ሳይመዝኑ እንደተነገራቸው የሚያስተጋቡት ፓትርያርኩ፣ እኒኽን ኃይለ ቃላት የተናገሩበት የረፋድ ወኔ ግን አብሯቸው አልዘለቀም፡፡ ስብሰባው ከቀትር በኋላ ሲጀመር አንሥቶ ከፍተኛ መደናገጥ ታይቶባቸዋል፡፡ ማእከላዊ አሠራርን ሳይጠብቁ የፈጸሟቸውን መተላለፎች፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በዝርዝር ለጉባኤው ያሰሙ ሲኾን በማኅበሩ ላይ ለሰነዘሯቸው ክሦችም ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋቸዋል፤ የማኅበሩ ዋነኛ የድጋፍ ምንጭ የአባላቱ አስተዋፅኦ መኾኑን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ በሒሳብ አሠራሩም ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከማኅበሩ ብዙ የሚማረው እንዳለም አልሸሸጉም፡፡

ለመዋቅራዊ መተላለፋቸውም ኾነ ከማኅበሩ አንጻር ለቀረቡላቸው የተጨባጭነት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ያልሰጡት ፓትርያርኩ፣ ማእከላዊ አሠራርን ባለመጠበቅ በፈጸሟቸው ተግባራት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ “አዋረዱን፤ አፈርንብዎ” እስከመባል የደረሰ ቅሬታ ቀርቦባቸዋል፤ በከፍተኛ ደረጃም ተገሥጸዋል፡፡
ፓትርያርኩ ከመዓርገ ክብራቸው አኳያ ከመሰል የደብዳቤ መጻጻፎች እንዲታቀቡ ጉባኤው በጥብቅ አስጠንቅቋቸዋል፤ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አደጋ በኮሌጆች የሚገኝበትን አስከፊነት አስመልክቶ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በዳሰሳ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ያወጣውን ጽሑፍ ተከትሎ ፓትርያርኩ የሰጧቸው መመሪያዎችና ከማኅበሩ ጋር የተመላለሷቸው ደብዳቤዎችም በቋሚ ሲኖዶሱ እንዲመረመሩ በጉባኤው ተወስኗል፡፡ በይቀጥላልም ጉባኤው፣ ፓትርያርኩ በመሰል ጉዳዮች አስፈጻሚ የአስተዳደር አካላትን በቀጥታ መሰብሰባቸው ስሕተት በመኾኑ፣ ከብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋር እየተነጋገሩና በቋሚ ሲኖዶስ እየመከሩ ሕጉን አክብረውና መዋቅሩን ጠብቀው ከአድልዎ የጸዳ አመራር መስጠት እንደሚኖርባቸውም በጥብቅ አሳስቧቸዋል፡፡

ግለ ታሪካቸውን ከማበላሸት አልፎ በክፉ ምክሮችና በሕገ ወጥ ደብዳቤዎች ቤተ ክርስቲያንን እያሳጣና እያስነቀፈ የሚገኘው የልዩ ጽ/ቤታቸው አሠራር ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን በእጅጉ አሳስቧል፤ የልዩ ጸሐፊው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃና የክፋት ተባባሪዎቹ ጉዳይም አስቸኳይ እልባት እንደሚያስፈልገው ከድንገተኛ ልዩ ስብሰባው በተጓዳኝ በስፋት የተመከረበትና አቋም የተያዘበት ወቅታዊ ነጥብ ኾኗል፡፡

Pat. Abune mathias-and-nebured Elias
የፓትርያርኩ የሀገር ውስጥም ኾነ የውጭ ጉዞ፣ ቋሚ ሲኖዶስ አስቀድሞ እያወቀው በዕቅድ መከናወን ያለበት ቢኾንም “የራሳችንን ወጪ ሸፍነን ቅዱስነታቸውን እናጅባለን” በሚሉ አማሳኝ ግብረ በላዎች ጭምር የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ያለዕቅድ እየወጣ የሚባክንበት፤ ፓትርያርኩ እንደ ርእሰ መንበር ሐዋርያዊ ተልእኳቸውንና አባታዊ ሓላፊነታቸውን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመወከል በሚያበቃ መልኩ የሚወጡበት ከመኾን ይልቅ “ስፖንሰር ተገኘ” በሚል ብቻ ከፍተኛ ስሕተት(የፕሮቶኮልም) የሚፈጸምበትና ክፋት የሚመከርበት እየኾነ እንደመጣም በጉባኤው ታይቷል፡፡

በመኾኑም ማንኛውም የፓትርያርኩ ጉዞዎችና የሚመደቡ ልኡካን፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ሲወሰን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንተ ክብርና ሉዓላዊነት እንዲኹም የመንበረ ፕትርክናውን ፕሮቶኮል በጠበቀ ደረጃ እንዲፈጸም ጉባኤው አሳስቧል፡፡
ቅዱስ ሲኖዱሱ በነበረው ድንገተኛ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በተለዩት የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ምትክ የሶማሌ/ ጅግጅጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያሬድ ደርበው እንዲሰሩ የተመደቡ ሲሆን፤ ብፁዕ አቡነ ያሬድም ከጅግጅጋው ሀገረ ስብከት በተጨማሪ የአርሲ ሀገር ስብከት አገልግሎትን ደርበው እንደሚሰሩ ተጠቁሟል፡፡

ስለ ተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከሚመለከታቸው አህጉረ ስብከት በሚመደቡ ልኡካን ተጨማሪ ማጣራት እንዲካሔድና አስፈላጊው የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንዲደረግ የወሰነው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በአገራችን ወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ላይም የመከረ ሲኾን በየካቲት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በነበረው ዕለትም በድንገተኛ ልዩ ስብሰባው ቃለ ጉባኤዎች ላይ በመፈራረም ስለሰላምና ስለወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ሙሉ መግለጫው ቀጥሎ ይመልከቱ፡-

synod-declaration-yek2008a

ምንጭ፡- ሐራ ዘተዋሕዶ

በኮንሶ የመብት ጥያቄን ተከትሎ መንግሥት በወሰደው የኃይል እርምጃ ህዝቡን አስቆጣ

በደቡብ ክልላዊ መንግሥት ከዚህ ቀደም ኮንሶ ራሱን ችሎ ልዩ ወረዳ በነበረበት ወቅት የዞን አስተዳደር ደረጃ እውቅና እንዲሰጠው ህዝቡ ቢጠይቅም፤ ከነበረበት ልዩ ወረዳ አንሶ በአዲሱ የሰገን ህዝቦች ዞን በሚል አስተዳደር ወደ ወረዳነት መውረዱን በመቃወም ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ከክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግሥት ምላሽ ሳያገኙ ቅተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ህዝቡ የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በኮንሶ ዋና ከተማ ካራት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል፡፡

Konso 1

በተቃውሞ ሰልፉ የደቡብ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይልና መከላከያ ሰራዊት በወሰዱት የኃይል እርምጃ 23 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ ህዝቡም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱትን የኃይል እርምጃ በመቃወም ዋና ከተማቸውን አቋርጦ የሚያልፈውን ከአርባ ምንጭ ጂንካ የሚወስደውን ዋና መንገድ ሙሉ ለሙሉ ዘግተው እንደነበርም ታውቋል፡፡

መንግሥት ተቃውሞን ለማስቆምና የተዘጋውን መንገድ ለማስከፈት በሚል በድጋሚ በወሰደው የኃይል እርምጃ ከዋና ከተማ ካራት በተጨማሪ በአጎራባች የገጠር ቀበሌዎች ጭምር በመዝለቅ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ የተገለፀ ሲሆን፤ በዚህም የደቤና ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሷይታ ጋራ የተባሉ ግለሰብ ወዲያው ህይወታቸው እንዳለፈና የ65 ዓመት አዛውነትንና ወጣት ተስፋዬ ማሙሽን ጨምሮ 23 ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ሰዎችም በከተማው ፖሊስ ጣቢያ እና በካራት ቴክኒክና ሙ ማሰልጠኛ ተቋም መታሰራቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

Konso 2

በመጨረሻም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተዘጋውን መንገድ በኃይል ማስከፈታቸውን የተገለፀ ሲሆን፤ ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በርካታ የክልሉ ልዩ የፖሊስ ኃይል እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢው ሰገን ወንዝ ሰፍረው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በተለይ በዋና ከተማዋ ካራት የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ የነበሩ ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ በከተማዋና አካባቢ የሰፈረው የመንግሥት የፀጥታ ኃይል በበቀል የህዝብ ንብረት ላይም ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ይህ እስከተዘገበበት ድረስም በአካባቢው የተለመደው የትራንሶፕርተና ማኀበራዊ አገልግሎት ከመስተጓገሉ በተጨማሪ አለመረጋጋቶች እንደሚስተዋሉ ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ በአካባቢው የነበረውን አለመረጋጋትና ተቃሞ በተመለከተ ከመንግሥት አካል የተገለፀ ነገር የለም፡፡

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሁለት የስራ ሀላፊዎችን ከሃላፊነታቸው አነሳ

OPDO

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከየካቲት 25 ጀምሮ ለአምስት ቀናት በአዳማ ከተማ ባካሄደው ጉባኤ ሁለት የስራ ሀላፊዎችን ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ በማድረግ እና የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የስራ ሃላፊዎቹ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገው በአመራር ችግር መሆኑን አስታውቋል።

በዚህም 1ኛ የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሞቴ የስራ አስፈጻሚ አባል እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል እንዲሁም የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ዳባ ደበሌ ሲሆኑ፥ በታየባቸው የአመራር ችግር ምክንያት ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መወሰኑን እና ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባልነት ተነስተው ነገር ግን የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው እንዲቀጥሉ ወስኗል።

2ኛ የኦህዴድ እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል እና የኦሮሚያ ክልል የእርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ጀማነ ሲሆኑ፥ እስከ ቀጣዩ የድርጀቱ ጉባኤ ድርስ ከማንኛውም የድርጅት እንቅስቃሴ መታገዳቸውን ድርጅቱ ማስታወቁን ፋና ቢሲ ዘግቧል፡፡
ምንጭ፡ http://www.fanabc.com/index.php/news/item/1428

ማኅበረ ቅዱሳን ለፓትርያርኩ መምሪያ ምላሽ ሰጠ፤ የስምዐ ጽድቅ ጽሑፍ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ የማሳወቅ ግዴታችን አካል ነው፤ ደብዳቤውም መድረክ ስለተነፈገንና ፍትሕ ስለተጓደለብን ነው

• የጋዜጣው ጽሑፎች፣ «መንፈሳዊ ኮሌጆቹ በአጠቃላይ የመናፍቃን መፈልፈያ ናቸው» አይሉም
• በጋዜጣው አጻጻፍ አንዳንድ የቃላት አጠቃቀሞች ላይ ቅሬታ ካለ ለመወያየት ዝግጁዎች ነን
• ጉዳዮቹን እንድናስረዳና የተፈጠረውንም ችግር ለመረዳት የውይይት መድረክ ይዘጋጅልን
• በተለያየ መንገድ እንደጠየቅነው፣ በአካል የመወያያ ዕድል ማጣታችን በእጅጉ ያሳዝነናል
• ለሚታረም ነገር እርምት መውሰድና ስናጠፋም ይቅርታ መጠየቅ የአገልግሎታችን መርሕ ነው
* * *
• ሰዎች እንደመኾናችንና ልንሳሳት ስለምንችል፣ በማንኛውም ደረጃ ተወያይተን የሚታረም ነገር ካለ አስፈላጊውን እርምት መውሰድ እና በትክክል ጥፋት እንዳጠፋንም ስንረዳ ይቅርታ መጠየቅ አንዱና ዋነኛው የአገልግሎታችን መርሕ ነው፡

• በሀገራችን የተከሠቱትን ማኅበራዊ ችግሮች ለመፍታት ኹሉም አካል በየዘርፉ በሚረባረብበት በዚኽ ወቅት፣ ትልቅ ሓላፊነት ያለባት የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አባትና ልጆች እንዲህ ዓይነት ደብዳቤዎችን በመጻጻፍ መጠመዳችን በእጅጉ   አሳዝኖናል፡፡

• ሕግ አውጥቶ፣ ሥርዓት ሠርቶ የሰጠን የቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በማኅበሩ አገልግሎቶች ላይ አኹንም እየተፈጠሩ ያሉት ዕንቅፋቶች እንዲታዩልንና አስፈላጊው እርምት እንዲደረግልን በታላቅ ትሕትናና አክብሮት እንጠይቃለን፡፡ (የደብዳቤውን ሙሉ ይዘት ከዚኽ በታች ይመልከቱ)

EOTC_MK 1EOTC_MK 2EOTC_MK 3EOTC_MK 4

 

ምንጭ፡- ሐራ ዘተዋሕዶ ፣ https://haratewahido.wordpress.com/2016/02/29

 

በደቡብ ክልል ሱርማ በሚገኙ የሙርሲ ማኀበረሰብ ላይ የመንግሥት ልዩ ኃይል የወሰደው እርምጃና ያለተገባ አያያዝ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አስቆጣ!

ቀኑ በትክክል ባይታወቅም ባለፈው ሳምንት የተከናወነ እንደሆነ የሚታመነውና በፖሊስ ቁጥጥር ስር ባልተገባ አያያዝ እርቃናቸውን ይታዩ የነበሩ በደቡብ ክልል በቤንች ማጂ ዞን የሚገኙ እና የደቡብ ኦሞ ዞን አጎራባች የሆኑት የሙርሲ ማኀበረሰብ በአካባቢው በመንግሥት ለማከናወን የታቀደውን የኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት ማስፋፊያ ባደረሰባቸው ተፅዕኖ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ የተሰጠ የመንግሥት ምላሽ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

human-right-abuse-ethiopia4

በተለይ በክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበሩት የሙርሲ ማኀበረሰብ አባላት ኢሰብዓዊ በሆነና ለህይወታቸው በሚያሰጋ መልኩ እር በርስ በመጠላለፍ የታሰሩበት ሁኔታ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ ይንንም በተመለከተ የስርዓቱ ደጋፊዎች ምስሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈፀመ ሳይሆን ደቡብ ሱዳን በሚል ለማስተባበል ከመሞከራቸው በስተቀር ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

Mursi HR violation

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በቁጥጥር ስር የነበሩት የሙርሲ ማኀበረሰብ እርቃናቸውን እር በርስ በአሰቃቂ ሁኔታ ካሰሯቸው መካከል የሁለቱ ፖሊስ አባላት ማንነት ከነ ምስላቸው በሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውን መለየት መቻላቸው ተጠቁሟል፡፡

ከታሰሩት ጋር ይታዩ ከነበሩት ፖሊሶች መካከል ሁለቱ ማንነታቸው የተለየ ሲሆን፤ እነሱም ኮንስታብል ደመቀ አራርሳ ወጊ የሚባል የወለንጪቲ ተወላጅ ሲሆን፤ ረዳት ኮንስታብል የኑስ ተማም ቦሬ የሚባል የዲላ ተወላጅ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ በቁጥጥር ስር የነበሩ አካላትን ጭኖ የነበረው ተሽከርካሪ ንብረትነቱ እና ፖሊሶቹ ለብሰውት የነበረው የደንብ ልብስ የደቡብ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይል እንደነበርም መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ይሁን እንጂ፤ የፖሊስን ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ በተመለከተ የረህ እስከተዘገበበት ድረስ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ የለም፡፡

በአካባቢው ከዚህ በፊት መንግሥት ያለምንም በቂ ማኀበራዊና አካባቢዊ ተፅዕኖ ግምገማ እናያለ በቂ ካሳ ከ200 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ማፈናቀሉ ከፍተኛ ትችት አስከትሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡

 

 

%d bloggers like this: