ሀብታሙ ስዩም
እና ባጭሩ የምትሉኝ በሃገሪቱ የሚሰሩ ፊልሞች ጥራት እና የታሪክ ፍሰት እምብዛም ስላልሆነ የቱርክ ፊልም እያየን እንቆይ ነው? በይ ደስም አላልሽኝ አለ ሙዚቀኛው፡፡የሀገራችን ፊልሞችና ድራማዎች ጥራትና ብቃት ከፍ እንዲል ሺ ዓመት የለፋን እንመስላለን አነጋገራችን፡፡ወገኖቼ በአስር ወር የፊልም ትምህርት ቤት የተማርኩት የመጀመሪያው ነገር የኛ ሀገር ፊልም ለውዝግብ መብቃቱ ራሱ ታላቅ ስኬቱ መሆኑን ነው፡፡
የፊልም ዕቃዎችን ለማስገባት ያለውን ጣጣ፣ጥበቡን የሚደግፍ ሁነኛ የመንግስት አካል ዕጦት፣ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት እጥረት ፤ታሪኮች የተገደቡ እንዲሆኑ የሚደረገው የእጅ አዙር ጫና ፣ሲኒማ ቤቶችን ከሚያስተዳድሩት ግልገል መንግስቱ ሃይለማሪያሞች ጋር ሁሌ የሚላተመው የኛ ፊልም የራሱን ተመልካቾች መፍጠሩ አፈር ህይወትን ፈጠረ እንደሚለው እሳቤ እጅግ የሚገርም ነው፡፡እንዲህ እየሆነ የብዙሃን የእንጀራ ቤት የሆነውን ዘውግ በአንድም ሆነ በሌላው የሚጓዳ አሰራርና ትግበራ ለኔ ምኑም አይስማማኝም፡፡
በዕቁብና በቤተሰብ ብድር ከተሰሩ ፊልሞች ውስጥ የሚገርሙ ተዋናያንን፣ተስፋ ያላቸው የቴክኒክ ባለሙያዎችን፣ መንገድ ላይ ስናያቸው ፈገግታችንን የሚያገዝፉ አዘጋጆች ተፈጥረው መገኘታቸው ሁሉ ለኔ እጡብ ነው፡፡በኢንተርናሽናል ደረጃም ሆነ በሀገር ቤት አምራቾች የተሰሩ ፊልሞችን አሰራርና ሂደት ለመታዘብ ዕድሉ ነበረኝ፡፡ጎበዛዝስት የፊልም ሰሪዎቻችን ሄሎሄ በታዘብክ ቁጥር ጉዳዩ እን የሚሊየን ብር ፊልምን በሁለት ብር እስኪርቢቶ( በትችት) ድራሹን አጥፍቶ ዞር በማለት የሚጠገን ነገር አላገኘሁበትም፡፡
ከዓመታት መውደቅ መነሳት በኃላ ቴሌቭዥኖቻችንም የአማረኛ ፈልሞችና ድራማዎችን ሀገራዊ ተፈላጊነት በማየት ከሰዓታቸው ሙዳ ሙዳውን ማከፈል ጀመሩ፡፡ይሄ ጅማሮ ደራሲያን ፣ተዋናያን የቴክኒክ ባለሙያዎች በገቢ የሚያድጉበትን ዕድል አስፍቶ ባልበላ ጎናቸው ያሳዩትን መፍጨርጨር በበላ ሆዳቸው አሳድገው እንደሚመጡ ተስፋ ሆኖኝ ነበር፡፡ይሄን መሰል ጥረታቸውን ተጨማሪ ዕድል በመስጠት እኒህ ወገኖች ለተጨማሪ ሰዎች የመንፈስም ሆነ የስጋ ጥግ እንዲሆኑ መጣር አስፈላጊም ነበር፡፡አሁን እንደሰማሁት ግን ለምዕታ ዐመት ተለፍቶበት እንዳልተወጠ ጉዳይ ‹‹ የሀገራችን ፊልም ጉዳይ በቅቶናል›› ተብሎ የቱርክና የቴሌሙንዶ ሀብታሞችን ግዛተ አጤ በሀገሬ ፊልመኞች ጉሮሮ ላይ መትከል በእጅጉ ያልታሰበበት የወጠጤ ነጋዴ ሀሳብ ሆኖብኛል፡፡
ፊልመኞቻችን ችግር የለባቸውም የሚል ክርክር አልወጣኝም፡፡አሁን ያለው የፊልመኞቻችን ችግር በጊዜ ውስጥ በባለሙያዎች መካከል በሚደረግ ውድድር እና የተማሩ ፊልም ሰሪዎች እየበዛ መምጣት ፤ሀገሪቱ በፊልም ስራ ዙሪያ የያዘቻቸው የእጅ አዙር ገደቦችና መሰናክሎች ሲከስሙ የሚቀረፍ ነው፡፡
እንኳን የኛ ሀገር ፊልም ይቅርና ሆሊውድ እንኳ አንዳንዴ እህል ውሃ የማይሉ ፊልሞች ይሰራሉ፡፡ነገር ግን ውሃ ስለጠማን እሳት እንሙቅ አይነት ውሳኔ በዚያ ሀገር የተለመደ አይደለም፡፡
የቱርክ ፊልሞችን ለናሙና ማየት ችግር የለውም፡፡ይሄን በሚያክል ምጥጥን ሰዐታቱን መሙላት ግን ለኔ መንስኤው ግልጽ ያልሆነ የስድ ውሳኔ ነው፡፡ደሞ እናውራ ከተባለ ፊልሞችን አስተርጉሞ የማሳየት ዕቅድ የሌሎችን ሀገራት ፊልሞች ለሀገራችን ተመልካች ከማቃመስ መልካም እሳቤ ብቻ የሚነሳ አይደለም፡፡ከሀገራቱ ኤምባሲዎች፣የሀገራቱን ልዕልና ለማጉላት ከሚሰሩ ድርጅቶች የሚገኘውን ፈንድና ጥቅማጥቅም ከመጠቅለል ፍላጎት የሚነሳ የትርፍ ጥረትም ነው፡፡
ከምንም በተጀመረ ጥበብ ውስጥ ሞካሪ እስካለ ድረስ የሚሞክረውን ሰው እስትንፋስ ለማርዘም ማናቸውም ከለላዎች መደረግ አለባቸው፡፡ቢያንስ ያ ሰው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ያ ሰው የእኔና የአንተን ቋንቋ ተጠቅሞ በዓለም ውስጥ ትንሽም ቢሆን ዐይንና ጆሮ እንድናገኝ እየለፋ ያለ ሰው ነው፡፡ፊልም እና ሙዚቃ የእንጀራ ጉዳይ ብቻም አይደሉም ዐለምን በእጃዙር የምታማልልበትና የሀገርህን እሳቤ በሌላ ዐለም ላይ የምትጭንባቸው ህመም አልባ መሳሪያዎች ናቸው፡፡አሜሪካ የዓለምን ልብ ያስከፈተችው በኒኩሌር ይመስልሃል፡፡እኔና አንተ አሜሪካ ሳንረግጣት ያወቅናት የጠንቋይ ዘር ስለሆን ይመስልሃል? ጥበበኞቿን ይዛ አሜሪካዊነት የተጠቀጠባቸው ሁነኛ ፊልሞችን በማስንጨፍ ነው፡፡እና ለቱርክ ፊልም ይሄን ሁሉ ጊዜ መስጠት ሀሊት እና ሀዛል ሲላቀሱ ከማየት ወዲያ የማይዘል የሞራል ልዕልናን የመጫን እርሾ የሌለበት ይመስልሃል?
ለማንኛውም ፊልሞቻችን እንከነ ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡የአንዳንድ ፊልም ሰሪዎች የዕውቀት ማነስን ሰበብ አድርጎ በማንሰራራት ላይ ያለውን ጥበብ በብላሽነት መጠቅለል የማይገናኝ አመክኒዮ ነው፡፡ስላበሳጩን ሳይሆን ስላስገረሙን የፊልም ታጋዮች ክብር ውሳኔያችንን ማጤን ግድ ይላል፡፡ ምንም ይሁኑ ምንም እንድናያቸው ጉጉት የተውልን መልካም ውጥኖችም ናቸው፡፡ለመራመድ እዳለመ – ነገር ግን እንደሚወድቅ እንደሚነሳ ልጅ እየተከተልን እየደጋገፍን እራሱን ችሎ እንዲቆም ማብቃት ይኖርብናል እንጂ እንደሞተ ሁሉ ገሸሽ አድርገነው በጉዲፈቻ ሌላ ጠብደል ከእልፍኝ ማስገባቱ ዘረሰናይ ብርሃነ ማሪያምን የሚያክል የዓለም ፊልሞችና ቴሌቭዥን የጀርባ ውስጠ ባህሪ ይገባቸዋል ከሚባሉ ሰዎች የሚጠበቅ አይደለም፡፡
ቀድሞ ነገር የጣቢያው ዓላማ የሶስተኛ ዓለም ሚዲያዎች ሊኖራቸው የሚገባውን እና ህዝቡ በድህነቱና በአለማወቁ ሰበብ የገጠሙትን የኑሮ ትንቀንቆች ድል የሚያደርግበትን መላ መጠቆም አይመስልም፡፡የጣቢያው ዓላማ የየለት ኑሯችንን የሚያፈኩ ከአንጀት ጠብ የሚሉ መሰናዶዎች ማድረስ አይመስልም፡፡ተዝናኑ ነው-በባዶ ሆድ-በባዶ ጭንቅላት ተዝናኑ-አይነት ነው፡፡
አፈር ስሆን ከማብቃቴ በፊት ዘረሰናይ፡፡አንጀሊ ረድታህ የሰራኸው ፊልም ይዘቱን ታስታውሰዋለህ? እየውልህ እሱን እና እሱን መሰል ድሃውን ህዝብ በየለቱ የሚነኩ ችግሮች በተንሰራፉበት ሀገር ነው አንተ ችግሩ ሁሉ ተቀርፎለት የመዝናኛ ያለህ ብሎ እንደለመነህ ሁሉ ለዚህ ህዝብና ሀገር የቱርክና የቴሌሙንዶ ግሳንገስ ይዘህለት የመጣህ፡፡
ከጎበዝ ዳይሬክተርነት ወደ ግደቢስ ነጋዴነት –ይሄ ነው መርመጥመጥ፡፡እንኳን ወደ ማደንዘዙ ዘመቻ በሰላም ተቀላቀልክ፡፡