እነ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ ጥፋተኝነት ሲበየንባቸው፣ አቶ በቀለ ገርባ እና ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው
በእነ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ ከ600 ቀናት በላይ ፍርድ ቤት ሲመላሱ የቆዩት ተከሳሾች ላይ ዛሬ ብይን ተሰጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ፣ ሰለሞን ግርማ ፣ መምህር ተስፋዬ ተፈሪ ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱት ባህሩ ደጉ እና ዬናታን ወልዴ በነጻ ተሰናብተዋል፡፡
በተመሳሳይ የክስ ፋይል አብረው የተከሰሱት የፓቲካ ፓርቲ አመራሮች ( አብርሃ ደስታ ፣ ሃብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሸዋስ አሰፋ) እና መምህር አብርሃም ሰለሞን መከላከል ሳያስፈልጋቸው ነጻ መባላቸው ይታወሳል፡፡
ለአራት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ማእከላዊ ምርመራ የከረሙት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው እና አብረው የታሰሩ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስና የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ተጨማሪ አንድ ሳምንት ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ እስካሁን ድረስ በሽብር ከመጠርጠር ውጪ ክሳቸው በውል ያልታወቀው ፣ አቶ በቀለ ገርባ ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውን ጨምሮ ኦሮሚያ ላይ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡
ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ቀርበው ለዛሬ ክሳቸው እዲነበብ የተቀጠሩት 33 በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ አካባ ኦነግ ተዋጊነት የተጠረጠሩት እነ ሃብታሙ ሚልኬሳ ዛሬም ክሳቸው ሳይሰማ ለሚያዝያ 20 ሌላ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ተላልፏል፡፡
ምንጭ፡- EHRP
እነ ኦኬሎ ኦኳይ ጥፋተኛ ተባሉ
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ መጋቢት 28ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት የቀድሞው የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር ኦኬሎ ኦኳይ እና አብረዋቸው የተከሰሱት ስድስት ተከሳሾች ጥፋተኛ ናቸው ብሎ ውሳኔ አስተላለፈ።ፍርድ ቤቱ የቅጣት አስተያየት ለመስማት ሚያዚያ 17 ቀጠሮ ስጥቷል፡፡
በሰኔ ወር 2006ዓ.ም የሽብር ክስ ተመሰርቶባቸው ክሳቸው እየታየላቸው የሚገኙት እነ ኦኬሎ ኦኳይ በየካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ለማስተላለፍ ለዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ ተቀጥረው ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ዛሬ በችሎት ከተሰየሙት ሶስት ዳኞች መካካል የቀኝ ዳኛ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ታደሰ የፍርድቤቱን ውሳኔ በንባብ አሰምተዋል፡፡
ዳኛ ሣሙኤል ታደሰ ወደ አንድ ስዓት በቆየው የፍርድ ውሳኔ ንባባቸው እንዳመለከቱት አቶ ኦኬሎና ስድስቱ ተከሳሾች የጋምቤላ ህዘቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) አባል በመሆን እና የጋምቤላ ክልልን ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ከአሜሪካ ገንዘብ በማሰባሰብ እና የሽብር ቡድን ማስተባበራቸውን በንባባቸው ጠቅሰዋል፡፡
አቃቤ ህግ በነኦኬሎ ላይ ከዘረዘራቸው ክሶች መካከል ከኤርትራ መንግስት ጋር የሽብር ድርድር በማድረግ እና ከኦነግ እና ግንቦት 7 አመራሮች ጋር በተለይ ከሞት ፍርደኛው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር መገናኘት እንደሚገኙበት ዳኛ ሳሙኤል አስታውሰዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶችን ለሽብር ተግባር መመልመል፣ ወታደራዊ ስልጠና መስጠት በክሳቸው ላይ መጠቀሱን ዳኛው ተናግረዋል፡፡
ከክስ ንባብ መስማት በኃላ ወደ ሁለት አመት ያህል ፍርድቤት የተመላለሱት እነ ኦኬሎ አኳይ የክስ መቃወሚያ ካቀረቡበት ጊዜ አንስቶ ለውሳኔ እስከተቀጠሩበት ጊዜ ያለው ሂደት በዳኛው ተብራርቶ ቀርቧል፡፡
የእነ ኦኬሎ የክስ መቃወሚያ በፍርድ ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ መደረጉን እና የተከሰሱበትን ክስ ክደው መከራከራቸውን ያስታወሱት ዳኛ ሳሙኤል በመቀጠል አቃቤህግ ምስክሮቹን አቅርቦ ማሰማቱን አስረደተዋል፡፡
ለወራት ከዘለቀው የምስክሮች መሰማት ሂደት በኃላ ፍርድቤቱ ተከሳሾቹን እንዲከላከሉ መወሰኑን ዳኛው ጠቅሰዋል፡፡ ተከሳሾቹ በምርመራ ወቅት በከፍተኛ ጫና እና ድብደባ ውስጥ እንዳለፉ ማስመዝገባቸውን ዳኛው ጠቁመዋል፡፡
የግራና የቀኙን ክርክር ያዳመጠው እና የቀረቡለትን ማስረጃዎች የመረመረው ፍርድ ቤት በሁሉም ተከሳሾች ላይ የጥፋተኛ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ ኦኬሎ አኳይ በሰው እና መማስረጃ የጋምቤላን ክልል ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆን የአመራር ሰጪ ውሳኔዎችን ሲመራ በመቆየቱ አቃቤህግ በሰው እና በማስረጃ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳ ዳኛው በውሳኔው አመልክተዋል፡፡ተከሳሹ በበኩሉ የተከሳሽነት ቃል ከማሰማት በስተቀር መከላከያ ምስክሮችም ይሁን ሰነዶችን አቅርቦ በበቂ ሁኔታ እንዳልተከላከለ ዳኛው ገልፀዋል፡፡
ቀሪዎቹም ተከሳሾች በምርመራ ወቅት ለፖሊስ ቃላቸውን ተገደው ስለመስጠታቸው ያሰረዱ እንጂ የቀረበባቸውን ክስ የሰው ምስክር እና የሰነድ ማስረጃ አቅርበው እንዳልተከላከሉ በዳኛው ተገልጿል፡፡
“[ተከሳሾቹ] ምስክሮቻቸው ማዕከላዊ አብረዋቸው የነበሩ፣ በሌላ ወንጀል ተጠርጥረው ያሉ እና ተዓማኒነታቸው ጥርጣሬ ውስጥ የሚገባ ከመሆኑ በተጨማሪ ከዋናው ክስ እና የክስ ማስረጃ ጋር የማይገናኙ በመሆናቸው ክሳቸውን በደንብ አልተከላከሉም” ሲሉ ዳኛው ገልፀዋል፡፡
ክሱ መታየት ያለበት በፀረ ሽብር አዋጁ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ፍርድቤቱ መርምሮ በአንደኛ ተከሳሽ የተመሰረተው ጋህነን፣ የጋምቤላ ህዝብን ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል ከተለያዩ የሽብር ቡድኖች ጋር የስልጠና ትብብር መጠየቃቸው በአቃቤ ህግ የተረጋገጠ ነው ብለዋል ዳኛው፡፡ ሆኖም ድርጊቱ የአገሪቷን አንድነት የማፈራረስ ሙከራን የሚያቋቁም እንደሆነ የገለፁት ዳኛው በዚህም መሰረት ተከሳሾቹ በፀረ ሽብር አዋጁ ሳይሆን የወንጀል ህጉን 241 በመተላለፋቸው በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ 149(1) የጥፋተኝነት ውሳኔ ማስተላለፉን ተናግረዋል፡፡
መጋቢት 28/2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት የጥፋተኝነት የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው ሰባት ሰዎች ሲሆኑ፣ እነዚህም ኦኬሎ አኩዋይ፣ ዴቪድ ኦጅሉ፣ ኡቻል አፒዮ፣ ኡማን ኒኮዮ፣ ኡጅሉ ቻም፣ ኡታካ ኡዋር እና ኡባንግ ኡቡንግ ናቸው፡፡
ምንጭ፡- EHRP
የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ይከበር!
ዞን 9
የዜጎች ከሀገር ሀገር የመንቀሳቀስ መብት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ሆነ ኢትዮጵያ አባል ሆና በፈረመቻቸው አህጉር አቀፍ እና ዓለማቀፍ ድንጋጌዎች የተጠበቀ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 32/1 ላይ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ . . . ከሀገር የመውጣት ነጻነት አለው” በማለት ተደንግጓል፡፡ ኢትዮጵያ ፈራሚ አባል የሆነችበት ‘ዓለም አቀፉ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን’ በበኩሉ ማንኛውም ግለሰብ ሕጋዊ ማዕቀብ ካልተጣለበት በስተቀር ወደፈለገው ቦታ የመንቀሳቀስ ከሀገር መውጣትን የሚጨምር መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ በኢትዮጵያ ህግም ብቸኛ ገደብ የሚያስቀምጠው የኢምግሬሽን አዋጅ ቁጥር 354/2003 በአንቀጽ 7 ላይ “ማንኛውም ሰው ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ሊታገድ የሚችለው በሕግ መሠረት በፍርድ ቤት ሲታዘዝ ብቻ ነው” በማለት የመንቀሳቀስ መብት ገደብን በማያሻማ መልኩ ያስቀምጠዋል፡፡
እንደሚታወሰው የዚህ የጡመራ መድረክ አባል የሆነው ዘላለም ክብረት በወንጀል ተጠርጥሮ ታስሮ የነበረ ቢሆንም ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በራሱ ተነሳሽነት ክሱ እንዲቋረጥ በማድረጉ ከማሕሌት ፋንታሁን፣ ከአስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ከኤዶም ካሳዬና ከተስፋለም ወልደየስ ጋር ሐምሌ 01/2007 ከእስር ተፈትቷል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው የሕግ አግባብ መሠረት ከሀገር እንዳይወጣ የሚያደርግ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ክልከላም የለበትም፡፡ ይሁንና ሕዳር 05/2008 ዘላለም ለቡድኑ የተበረከተ ሽልማትን ለመቀበል ወደ ፈረንሳይ፣ ፓሪስ ለማቅናት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቢገኝም የጉዞ ሰነዱ (ፓስፖርቱ) ተነጥቆ ከሀገር እንዳይወጣ ተከልክሏል፡፡ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች እንደተገለጸው ጦማሪው የጉዞ ሰነዱ እንዲመለስ እና የመንቀሳቀስ መብቱ እንዲከበር ያደረገው ሙከራ ከመጉላላት በቀር ምንም መፍትሔን አላስገኘም፡፡ እንዲያውም በአግባቡ ምላሽ የሚሰጥ መንግሥታዊ አካል መጥፋቱን ለመታዘብ ችለናል፡፡ በዚህም ምክንያት የተለያዩ ዕድሎችን ተጠቅሞ መማርም ሆነ መሥራት እንዳይችል ሁኗል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ይህንን የመብት ጥሰት ‹ጉዳዩ ከአቅሜ በላይ ነው› በሚል ምክንያት ሊያስቆም አልቻለም፡፡
በሌላ በኩል ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ በታኅሣሥ 01/2008 ዓ.ም. ለትምህርት ወደ አሜሪካ ለመሔድ በሞከረችበት ወቅት የጉዞ ሰነዷን ተቀምታ ከሐገር መውጣት እንደማትችል የተነገራት ሲሆን፤ ለምን የጉዞ ሰነዷን እንደተነጠቀች በተደጋጋሚ ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት መምሪያ ጥያቄ ብታቀርብም እስከ አሁን ድረስ ምላሽ ማግኘት አልቻለችም፡፡
እንዲሁም ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ በጥር 11/2008 ዓ.ም. ወደ ጀርመን ሃገር ለስድስት ሳምንታት የጋዜጠኝነት ልምድ ለመቅሰም ያገኘውን አጋጣሚ ለመጠቀም ያደረገው ሙከራም በተመሳሳይ የጉዞ ሰነዱን ያለምንም ሕጋዊ ምክንያት በመነጠቁ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ይባስ ብሎም ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ ለስድስት ሳምንታት ወደ ጀርመን ሃገር በመሔድ በጀርመኑ የመንግስት ቴሌቪዥን ጣቢያ የቀረበለት የልምድ ልውውጥ ላይ ተሳትፎ ወደ ሃገሩ ሲመለስ በየካቲት 26/2008 ዓ.ም. በተመለሰበት ወቅት ‹ከሃገር እንዴት ልትወጣ ቻልክ› ከሚል ከባድ ዛቻና ማስፈራሪያ ጋር የጉዞ ሰነዱን ሊነጠቅ ችሏል፡፡
ይህንን ሕገ ወጥ ድርጊት ለማረም ሁሉንም ሕጋዊ መንገዶች አሟጠን የምንጠቀም ሲሆን፤ ሕግ አስፈጻሚው አካል ግን ይህንን ስህተቱን ማረም የሚጀምርበት ተጨማሪ ዕድል አግኝቷል፡፡ ዘላለም ክብረት የዘንድሮው The Nelson Mandela Fellowship ወይም በቀድሞው አጠራር Young African Leaders initiative (YALI) አሸናፊ ሆኗል፡፡ የኔልሰን ማንዴላ ፌሎውሽፕ የአሜሪካው ፕሬዝዳነት ባራክ ኦባማ ወጣት አፍሪካውያን አህጉራቸውን የሚጠቅሙ መሪዎች እንዲሆኑ የሚያግዛቸውን ክህሎት እንዲጨብጡ በማሰብ እ.ኤ.አ. 2010 ይፋ ያደረጉት መርሐ-ግብር ሲሆን፤ በዚህ ስድስት ሳምንታት በሚፈጀው መርሐ-ግብር በየዓመቱ በርካታ አፍሪካውያን ለራሳቸውም ለአህጉራቸውም ጠቃሚ የሆነ ዕውቀት ገብይተው ተመልሰዋል፡፡ የዘንድሮው ውድድር አሸናፊ የሆኑት ሌሎች ኢትዮጵያውያን እና ዘላለም ክብረት በመጋቢት እና ሚያዝያ ወር ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው በሰኔ አጋማሽ ወደ አሜሪካ እንደሚያቀኑ የመርሐ-ግብሩ የጊዜ ሰሌዳ ያሳያል፡፡
እኛም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጉዳዩ ሕጋዊ መልክ ይይዛልና ይሻሻላል ብለን ተስፋ ብናደርግም ነገሮች ግን እየተባባሱ እና የመብት ጥሰቱም እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይሄም ድርጊት ዜጎች በሃገራቸው ሕግን አምነው ለመኖር አለመቻላቸው ማሳያም ነው፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው የአስፈጻሚ አካል ያለምንም የሕግ አግባብ የጉዞ ሰነዳቸውን ተቀምተው የሚገኙ ጦማሪዎችና ጋዜጠኞች መብታቸው ተከብሮላቸው የጉዞ ሰነዶቻቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲመለሱላቸው እንዲያደርግ እና የመንቀሳቀስ መብታቸውን እንዲያከብር እንጠይቃለን፡፡
ሕገ መንግሥቱ ይከበር!