Daily Archives: April 16th, 2016

በጋምቤላ ከደቡብ ሱዳን በመጡ ታጣቂዎች 170 ያህል ኢትዮጵያውያን ተገደሉ

(አዲስ ሚዲያ)ትናንት አርብ ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት ጀምሮ ከሰዓት በኋላም የቀጠለው በሺህዎች የሚቆጠሩና የታጠቁ ደቡብ ሱዳን ቡማ ግዛት ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ የሙርሌ ማኀበረሰብ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት በጋምቤላ የሚገኙ ህፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 170 ኢትዮጵያውያን የኑዌር ማኀበረሰብ አባላትን መግደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ዋቢ በማድረግ ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡

Murle South Sudan

ታጣቂዎቹ በብዛት የኔዌር ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት በጋምቤላ ክልል ዞን 3 ጂካው እና ኒኔኛንግ ወረዳ የካጃክ አስር የኑዌር መንደር በመሄድ ጥቃት ማድረሳቸው የተገለፀ ሲሆን፤ በተለይ የግድያ ሰለባው የሆኑት በዋናነት ህፃናት እና ሴቶች መሆናቸውንም ከጥቃቱ የተረፉ እማኞች ተናግረዋል፡፡ በጥቃቱም በርካታ ዜጎች መቆሰላቸውና እስካሁን ቁጥራቸው ያልተገለፀ በርካታ ህፃናትም ታግተው መወሰዳቸው ተጠቁሟል፡፡

እንደእማኞች ገለፃ ከሆነ፤ በጥቃቱ ወቅት በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ለጋምቤላ ክልላዊ መንግሥትና በአካባቢው በቅርብ ርቀት ለሚገኙ የፌደራል መንግሥት ፌደራል ፖሊስና መከላከያ የድረሱልን ጥሪ ቢያደርጉም ምላሽ እንዳላገኙ እና ጠዋት የጀመረው ጥቃትም እስከ ከሰዓት ድረስ መዝለቁን ያልተለመደ እንደነበርና በወቅቱ መንግሥት ምላሽ ባለመስጠቱም የብዙ ሰዎች ህይወት መጥፋቱም እንዳሳዘናቸው በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡

“በእጃችን ራሳችንን የምንከላከልበት እንኳ በቂ መሳሪያ ባለመኖሩና የመንግሥትን ምላሽ በማጣታችን ለአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች የድረሱልን ጥሪ በማሰማታችንና ትብብር ስላደረጉልን ታጣቂዎቹ እያደረሱ ያሉትን አደጋ ለመቀነስ ችለናል:: በዚህም ከደቡብ ሱዳን ታጣቂዎችም ከ51 ያላነሱ ሰዎችን ገድለናል፣ የተወሰኑ የተዘረፉ ከብቶቻችንን አስመልሰናል፤ ነገር ግን የታገቱ ህፃናት ልጆቻችንን እና የተዘረፉ ከብቶቻችንን ማስመለስ አልቻልንም “ ብለዋ፤ሌላኛው በህይወት የተረፉ አንድ አባት፡፡

ስማቸውን እንዲገለፅ ያልፈለጉና ከጥቃቱ የተረፉ ግለሰብ እንደተናገሩት ከሆነ፤ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ሰርገው በመግባት ጥቃት ያደርሱ እንደነበር ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፤ የትናንትናው ግን በወታደራዊ የደንብ ልብስ በብዛት ታጥቀው ገብተው የዚህ ዓይነት የከፋ ጉዳት ሲያደርሱ የመጀመሪያቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በትናንትናው ግድያም 170 ኢትዮጵያውያን እና 51 የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎችን ጨምሮ ወደ 221 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡

በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግሥት በበኩሉ በስሩ ባሉ ፋናቢሲ እና ኢቢሲ በመሳሰሉ መገናኛ ብዙኃን እንዳስታወቀው ከሆነ፤ በጋምቤላ ከደቡብ ሱዳን መንግሥትም ሆነ ከመንግሥት ተቃዋሚ ታጣቂዎች ምንም ንክኪ የሌላቸው “ወንበዴዎች” 140 ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን እና ከጥቃት አድራሽ ደቡብ ሱዳናውያን ደግሞ 60 ያህል ሰዎች መገደላቸውን ቢያስታውቅም፤ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃም ሆነ የሰጠው መግለጫ የለም፡፡

ታጣቂዎቹ  ከደቡብ ሱዳን ድረስ ድንበር ጥሰው በመግባት ለምን ኢትዮጵያውያንን እንገደሉ፣ ህፃናቱን እንዳገቱና ከብቶቻቸውን እንደዘረፉ የተገለፀ ነገር የለም፡፡

በያዝነው 2008 ዓ.ም. ባለፉት ወራት በተለያየ ጊዜ በዚሁ በጋምቤላ ክልል የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ በርካታ ዜጎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የትናንቱ ግድያ የጠፈፀመው ግን ከደቡብ ሱዳን በመጡ ታጣቂዎች እንደነበርና ይህንንም ከተገደሉ ሰዎች ማረጋገጥ እንደተቻለ ተጠቁሟል፡፡

“የሰርቆ አደሮች” ስብሰባ

Daniel Kibret

ዲ/ን ዳንኤል ክብረት

ሰሞኑን በአዲስ አበባ አንድ ትልቅ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የአዲስ አበባ ደረጃ አንድ ሌቦች ስብሰባ አድርገው ነበር፡፡ የስብሰባው መሪ ቃል ‹የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ሌቦች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?› የሚል ነው፡፡ ስብሰባው እንደተጀመረ አንደኛው የታወቀ ሌባ እጁን አወጣና ‹መፈክሩ ላይ የተጠቀስንበት ስም ትክክል አይደለም። ገጽታችንን የሚያበላሽ ነው› ሲል አስተያየት ሰጠ፡፡ ጭብጨባ አዳራሹን ሞላው፡፡

‹ታድያ ምን ይሁን፤ መቼም ሌባ መሆናችን ርግጥ ነው› አሉ ሰብሳቢው፡፡
‹ጠየም አድርጉት፤ እንደ ባለጌ ጥፊ ድርግም አይደረግም› አሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ፡፡
‹እኮ ምን እንባል› አሉ ሰብሳቢው፡፡
‹ሌሎቹ ሠርቶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ ወቶ አደር፣አርሶ አደር ከተባሉ እኛም ‹ነጥቆ አደር› ነው መባል ያለብን›
ይኼው ጸደቀ፡፡

‹የሕዝቡ ምሬት ጨምሯል፡፡ ሕዝቡ በሌቦች መማረሩን በተደጋጋሚ እየገለጠ ነው፡፡ አንድ ቀን መሣሪያ ቢያጣ እንኳን አካፋና ዶማ ይዞ መነሣቱ አይቀርም፡፡
ከተንተከተከ እሳቱ ጨምሮ
ክዳኑን ይገፋል የፈላበት ሽሮ
ሲባል አልሰማችሁም፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ ለሁላችን መግቢያ ቀዳዳው ጠባብ ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ እኛው ራሳችን መፍትሔ ማምጣት አለብን› አሉ ሰብሳቢው፡፡

‹ስንናገር ለይተን መናገር አለብን፡፡ ሌባ ሁሉ አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ ኩሩ ሌባና ልክስክስ ሌባ፤ ጨዋ ሌባና ባለጌ ሌባ፤ ሸቃጭ ሌባና ኢንቨስተር ሌባ፤ ነጥቆ ሂያጅና ነጥቆ ገንቢ፤ ገፋፊ ሌባና ለካፊ ሌባ፣ እየተባለ የሚዘረዘር ብዙ ዓይነት ሌባ ነው ያለው፡፡ በስመ ሌባ ሁላችንም መሰደብ የለብንም› አሉ አንድ የታወቁ ሌባ፡፡

ሰብሳቢው የተገረሙ ይመስላሉ፤ አገጫቸውን በእጃቸው ይዘው ‹እኔም የእናንተን ያህል ባይሆንም መቼም በዚሁ ስም ተጠርቼበታለሁ፡፡ አሁን የዘረዘርከው ግን ምንድን ነው?› አሉት፡፡

ሰውዬው ዕውቀት በመጠየቁ ወንበሩ ላይ ተገላብጦ ተቀመጠና፣ ጉሮሮውን ጠራርጎ ‹መቼም ዕውቀት ማካፈል ደስ ይለኛል፡፡ ኩሩ ሌባ ማለት ከሚሊዮን በታች የማይነካ፤ ዝም ብሎ በመቶውም በሺውም የማይልከሰከስ ነው፡፡ ልክስክስ ሌባ ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ ጨዋ ሌባ ማለት ደግሞ ሲሰርቅ በሕጉ መሠረት የሚሰርቅ ማለት ነው፡፡ ሰነድ አዘጋጅቶ፣ ጨረታ አጫርቶ፣ ማስታወቂያ አሠርቶ፣ ቃለ ጉባኤ አያይዞ፤ ዕቃ ገቢ አድርጎ የሚሰርቅ ማለት ነው፡፡ ባለጌ ሌባ ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ ኢንቨስተር ሌባ ገንዘብ የሚቦጭቀው ከትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ብቻ ነው፡፡ መጉመድ እንጂ መጉረስ የማያውቅ ቆፍጣና። መጉረድ እንጂ መቁረጥ ያልለመደ ጀግና፤ መቦጨቅ እንጂ መንጨት የማያውቅ ሆደ ሰፊ ማለት ነው፡፡ ሸቃጭ ሌባ ግን ከገቢውም፣ ከወጭውም፣ ከሱቁም፣ ከኅብረት ሱቁም የሚቀነጣጥብ ቀነጣጣቢ ነው፡፡ ነጥቆ ሂያጅና ነጥቆ ገንቢ ስለሚባሉት የሌባ ዓይነቶች በደንብ መግለጥ አለብኝ፡፡ ‹ነጥቆ ሂያጅ ሌባ› ማለት ካገኘ በኋላ እዚህ ሀገር የማይቀመጥ ሌባ ነው፡፡ ይኼ ዓይነቱ ሌባ ለሀገሪቱ ዕድገት ዕንቅፋት ነው፡፡ የሀገርን ገቢ ወደ ባዕድ ሀገር የሚያሸሽ ከሐዲ ሌባ ነው፡፡ የሀገር ፍቅር ስሜት ፈጽሞ የሌለው ሌባ ነው፡፡ እዚሁ ነጥቆ እዚሁ መብላት ሲገባው ሀገሩን ከድቶ ወጥቶ የሚበላ፡፡ እኛ ‹ወጥቶ በል ሌባ› ብለነዋል፡፡ ‹ነጥቆ ገንቢ ሌባ› ግን አገር ወዳድ ሌባ ነው፡፡ እዚሁ ነጥቆ እዚሁ ፎቁንም፣ ፋብሪካውንም፣ ሆቴሉንም፣ እርሻውንም ይገነባል፡፡ ለሀገሩም አጥብቆ ያስባል፡፡ እዚሁ ነጥቆ እዚሁ የሚሊዮን ብሩን መኪና ያሽቃብጠዋል፤ እዚሁ የመቶ ሺ ብር ውስኪ ያወርዳል፡፡

ነጥቆ ገንቢ ሌባ ደግ ሰው ነው፡፡ ሃይማኖተኛ ከሆነ ከነጠቀው ገንዘብ ወይ ለቸርች ወይ ለገዳም ይሰጣል፡፡ ነዳያን ያበላል፡፡ ድኻ ይረዳል፡፡ ሃይማኖተኛ ካልሆነ ደግሞ ለወጣት ማኅበራት ይለግሳል፤ ለቀበሌ ቲሸርት ያሠራል፤ በዓል ስፖንሰር ያደርጋል፤ እንዲህ ያለው ነጥቆ ገንቢ ሌባ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡ ግን ምን ያደርጋል የሀገራችን ሕግና የኢንቨስትመንት ዐዋጁ በቂ ማበረታቻ ለዚህ ሀገር ወዳድ ሌባ አይሰጥም፡፡
በመጨረሻ የማብራራላችሁ ‹ገፋፊ ሌባና ለካፊ ሌባ› ስለሚባሉት ነው፡፡ ገፋፊ ሌባ ማለት ሥጋ ሲበላ አጥንት የማያስቀር፤ እንጀራ ሲበላ ሞሰብ የማይተርፈው፤ ሻይ ሲወስድ ከነ ብርጭቆው፤ የደራሲውን ድርሰት ወስዶ የደራሲውን ስም የሚያጠፋ፤ሚስቱን መንጠቁ ሳያንሰው ባሏን የሚገል፤ በመሬትህ ላይ ባለ ዘጠኝ ፎቅ ሊሠራ አንተን በዘጠነኛው የኮንዶሚኒየም ፎቅ ላይ የሚወረውርህ፣ ሃምሳ ዓመት የኖርክበትን ቤት ወስዶ ከከተማው ሃምሳ ኪሎ ሜትር አውጥቶ የሚጥልህ ማለት ነው፡፡ ለካፊዎቹ ሌቦች ዝም ብለው ነው፡፡ እዚህም እዚያም ለኮፍ ለኮፍ ነው የሚያደርጉት፡፡›

ሰውዬው ማብራሪያውን ሲጨርስ አድናቂዎቹ እየሳቁ አጨበጨቡ፡፡ ሰው የልቡን ሲነግሩት የኮረኮሩት ያህል ይስቃል ይባል የለ፡፡

‹ታድያ አሁን መፍትሔው ምንድን ነው› አሉ ሰብሳቢው ነገሩ ውስብስብ ብሎባቸው፡፡ አንዱ እጁን አወጣ፡፡
‹ለችግሩ መባባስ ዋነኞቹ ተጠያቂዎች ከመሐልና ከታች ያሉት ሌቦች ናቸው፡፡ አሁን እኔ ኩሩ ሌባ ነኝ፡፡ ልስረቅ አልስረቅ ሰፊው ሕዝብ አያውቅም። እይውልዎት፣ መንደር መንገድ ላይ ያለችውን ዛፍ የሚቆርጠውን እንጂ ደን ውስጥ ያለውን ዛፍ የሚቆርጠውን ማንም አያየውም። አሁን ለኛ ችግር የሆኑብን የመንደር ዛፍ ቆራጮች ናቸው። ለካፊ ሌቦች ከስኳሩም፣ ከጨውም፣ ከድንቹም፣ ከሸማቾቹም ይቀነጣጥቡና ሕዝቡን ያነሣሡታል፡፡ ሕዝቡኮ ስኳሩ ወደ ሸማቾች ከገባ በኋላ አለቀ ሲሉት እንጂ መጀመሪያውኑ ወደ ሸማቾች ባልመጣው ስኳር ላይ አይበሳጭም፡፡ ሃምሳ ኩንታሉን ወስደን ሃምሳውን ኩንታል ሩብ ሩብ ኪሎ ብናከፋፍለው ‹ተመስገን› ብሎ ነው ወደ ቤቱ የሚሄደው፡፡ ሥራው ግልጽነት ያለው እንዲመስል ደግሞ የመጣውን ሃምሳ ኩንታል ከሴቶች፣ ከወጣቶችና ከአዛውንት የተመረጡ ኮሚቴዎችን አሰልፎ እኩል እንዲያካፍሉ ማድረግ ነው፡፡ ›

‹ልክ ነው፡፡› አለ አንዱ ሰርቆ አደር ኢንቨስተር ‹ሰው መብራት ተቆራረጠብን አለ እንጂ የመብራቱን ኬብል እነማን ናቸው ከውጭ የሚያስገቡት ብሎ ጠየቀ? ዱቄቱ ወደ ሸማቾች በብዛት አልመጣም አለ እንጂ ዱቄቱን እነ እገሌ ብቻ ለምን ከውጭ ያስመጣሉ?ብሎ ጠየቀ፤ አልጠየቀም፡፡ ኮንደሚኒየም በትክክል አልደረሰኝም አለ እንጂ እነ እገሌ የከተማ ቦታ በካሬ 300 ሺብር የሚጫረቱት ብሩን ከየት ቢያመጡት ነው ብሎ ጠየቀ፤አልጠየቀም፡፡ ‹እገሌና እገሌ የተባሉ ዋና አከፋፋዮች ለምን አስወደዱብን፣ ለምን አሳነሱን› አለ እንጂ ‹ግን እነርሱ የውጭ ምንዛሬ ከየት እያገኙ ነው ዕቃውን ከውጭ የሚያመጡት?› ብሎ መች ጠየቀ፤ ስለዚህ ችግሩ እታች ያሉት አቀባባይ ሌቦች አሠራሩን ስላላወቁበት ነው ማለት ነው፡፡ አያችሁ ሕዝቡ የዋሕ ነው፡፡ በጥፍርህ ስትቧጭረው ‹ጥፍሩን ቁረጡልኝ› ነው የሚለው፡፡ ሰውዬውኮ የቧጨረው ጥፍር ስላለው አይደለም። በጥፍሩ እንዲቧጭር የሚያዝ ጭንቅላት ስላለው ነው፡፡ ሕዝቡ ‹ጥፍሩን አስቆርጦ› ወደ ቤቱ ይገባል። ለተወሰነ ጊዜ ቧጫሪው ዝም ይላል፡፡ ቆይቶ ግን ጥፍሩ ሲያድግ መቧጨሩን ይቀጥላል፡፡

መጀመሪያ ጥፍሩን ያሳደገው፤ ተቧጨር ብሎ መብት የሰጠው ማን ሆነና፡፡ አሁንም ያስቸገሩን ራሶቹ አይደሉም፡፡ ጥፍሮቹ ናቸው፡፡› እንደ ድጓ አድራሽ በሊቃውንት ፊት ዕውቀቱን ያስመሰከረ መስሎት ትከሻውን ሰበቀ፡፡

ሰብሳቢው ግራ እየገባቸውም ቢሆን ‹ሐሳቡን እንጠቅልለው፤ የመቋጫ ሐሳብ አምጡ› አሉ፡፡
ሁለት ሰዎች ተረዳድተው ያዘጋጁትን የአቋም መግለጫ ይዘው ወጡ፡፡ እነርሱ የአቋም መግለጫውን ሲያቀርቡ ተሰብሳቢዎቹ ወረቀትና ስክርቢቶ አዘጋጁ፡፡ አንደኛ፡- ኅብረተሰቡ ስርቆትን እንዲጠየፍ ስለ ስርቆት በመገናኛ ብዙኃን ትምህርት ይሰጥ (ይኼ ሲነበብ አንድ አምስቱ በቲቪና ሬዲዮ የሚቀርበውን ማስታወቂያ ለመሥራት እንዴት ከባለ ሥልጣናቱ ጋር እንደሚሠሩ ተንሾካሾኩ፤ አንድ ሁለቱ ደግሞ በእነርሱ ሬዲዮ ጣቢያ ይህን ፕሮግራም ለመሥራት የስፖንሰር ገንዘብ ሲቦጭቁ ታያቸው)

ሁለተኛ፡- በየቀበሌውና በየደረጃው ሕዝቡ ሌቦችን እንዲያጋልጥ ይደረግና ርምጃ ይወሰድ (የተወሰኑት ተሰብሳቢዎች ለቀበሌ ስብሰባዎች ሞንታርቦ፣ ውኃና ኮፍያ ያለ ጨረታ ለማቅረብ ተጠቃቀሱ)

ሦስተኛ፡- ሌብነትን የተመለከተ ዜማ በታዋቂ አርቲስቶች እንዲዘጋጅ ይደረግ (አርት ነክቶናል የሚሉ ነጥቆ አደር አርቲስቶች የሚዘጋጀውን የፀረ ስርቆት ቅስቀሳ ከእነርሱ እንዳይወጣ ዘየዱ)

አራተኛ፡- ስለ ስርቆት አስከፊነት የሚያስተምር ቢል ቦርድ በመላ ሀገሪቱ ይተከል (የማስታወቂያ ድርጅት ያላቸው ተሰብሳቢዎች ይቺ ፕሮጀክት ከኛ አታልፍም ብለው ማሉ) አምስተኛ፡- የፀረ ስርቆት ቀን በየዓመቱ ይከበር። (ቲሸርትና ኮፍያ፣ መድረክና መስተንግዶ የሚያቀርቡ ተሰብሳቢዎች ዓመታዊ ገቢ ተገኘ ብለው ጮቤ ረገጡ፡፡)

ተሰብሳቢዎቹ ሲወጡ የአዳራሹ ዘበኛ በኀዘን ለጓደኛቸው ‹በሬ ሞተና ፍትሐት ሲፈታ ከበሮው ድምጹ እንዳይሰማ ‹ትሽ፣ ትሽ፣ ትሽ› ይል ጀመር፡፡ ከዚያ በፊት ‹እድም፣ እድም፣ እድም› ሲል ይሰሙት የነበሩት ጽናጽንና መቋሚያ ‹ምነው ዛሬ ያለወትሮህ ድምጽ እንዳይሰማ ‹ትሽ፣ ትሽ፣ ትሽ› ትል ጀመር› ብለው ቢጠይቁት ‹የሞተው በሬ፤ የሚመታው የበሬ ቆዳ ሆኖብኝኮ ነው፡፡ እንዴት ከበሬ ቆዳ ተሠርቼ በሬ ሞተ ብዬ ከበሮ ልምታ› አላቸው ይባላል ብለው ተረቱ፡፡

%d bloggers like this: