የአዋሽ ወንዝ ሊሞላ ስለሚችል የአካባቢው ወረዳዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጠ
በዚህ ሳምንት ውስጥ እንደሚጥል በተተነበየ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ አማካይነት የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል፣ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡
ኮሚሽኑ ለሪፖርተር የላከው የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክት እንደሚገልጸው፣ ከሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በስተቀር በአብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እስከ ሚያዝያ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ሊጥል እንደሚችል፣ ከብሔራዊ የሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ መረጃ ማግኘቱን ይጠቁማል፡፡
ከአዋሽ ተፋሰስ ባለሥልጣን በተገኘው ሌላ መረጃ መሠረትም የአዋሽ ወንዝ በቀጣዩ ሳምንት ሊሞላ ስለሚችል፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ጐርፍ በተፋሰሱ ባሉ አካባቢዎች ሊከሰት እንደሚችል መረጃዎች የሚያመለክቱ መሆኑን፣ በኮሚሽኑ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉነህ ወልደ ማርያም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በበቾ ወረዳ፣ በዓለም ጤና ወረዳ (ሁምቡሌና ጐሮ አካባቢዎች)፣ በስሬ ወረዳ፣ በወንጂ በተለይም በቆቃ ግድብ አካባቢ የሚኖሩ፣ በመርቲ ወረዳ፣ በመተሃራ (ፈንታሌ)፣ በአሚባራ፣ በዱለቻ፣ በገላአሎ፣ በገዋኔ፣ በተንዳሆ ግድብ አካባቢ የሚኖሩ፣ በአሳይታና በአፋምቦ ወረዳዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጐርፍ ሊከሰትባቸው ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡
የተጠቀሱት አካባቢዎች የመስተዳደር አካላትም በአካባቢዎቹ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከወንዙ በማራቅ ከጉዳት መጠበቅ እንዲችሉ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉም አሳስቧል፡፡
ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተከሰተው የጐርፍ አደጋ ከ20 ሰዎች በላይ መሞታቸው ይታወሳል፡፡
ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በ2008 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወራት እንደ አዲስ የተቋቋመና በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን የመከላከልና የቅድመ ማስጠንቀቅ ሥራ የማከናወን ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም ሲሆን፣ ተጠሪነቱም በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ
በጋምቤላ ክልል በድጋሚ በ21 ዜጎች ላይ ግድያ ተፈጸመ
ባለፈው ሳምንት ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ በጋምቤላ ክልል የደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የፈጠረው ሐዘን ሳይሽር፣ በድጋሚ ሌላ አሰቃቂ ግድያ በ21 ዜጎች ላይ ተፈጸመ፡፡
ሐሙስ ሚያዝያ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በጋምቤላ ክልል ጀዊ ስደተኞች ካምፕ የሚኖሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች፣ 21 ሰዎች ገድለው ሰባት ሰዎች ማቁሰላቸውን ሪፖርተር ከሥፍራው የደረሰው መረጃ አመልክቷል፡፡
የግድያው ምክንያት ሐሙስ ረፋድ ላይ በጋምቤላ ከተማ ከሚገኙ ስድስት ካምፖች አንዱ በሆነው ጀዊ ስደተኞች ካምፕ ውኃ የሚያመላልስ ቦቴ ተሽከርካሪ፣ ብስክሌት ይጫወቱ የነበሩ ሁለት ሕፃናት ስደተኞች ላይ አደጋ ማድረሱ ነው፡፡ በድንገተኛው የተሽከርካሪ አደጋ የሕፃናቱ ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ስደተኞቹ ይህ አደጋ ሆን ተብሎ የደረሰ ነው በማለት ወዲያውኑ በኢትዮጵያውያን ላይ አደጋ ማድረስ ጀመሩ፡፡
በአደጋው እስካለፈው ዓርብ ድረስ የ21 ሰዎች አስከሬን ተሰብስቦ ወደ ጋምቤላ ሆስፒታል የተጓጓዘ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል የጋምቤላ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ስደተኞቹ ደቡብ ሱዳናውያን ድንጋይ፣ ገጀራና ጦር በመጠቀም በሥፍራው በአሸዋ ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ መፈጸማቸው ተነግሯል፡፡ ጭፍጨፋው የተካሄደበት ቦታ ጫካማ በመሆኑ ራሳቸውን ለማዳን ወደ ጫካ የሸሹ ሰዎች በመኖራቸው፣ በወቅቱም ያልተገኙ ሰዎች ስለነበሩ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የቆሰሉ ሰዎች ጋምቤላ ክልል ውስጥ በምትገኘው ቦንጋ ከተማ ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህ ጭፍጨፋ የተሽከርካሪ አደጋን ምክንያት ያድርግ እንጂ፣ የክልሉ ነዋሪዎች መሰንበቻውን በክልሉ የተከሰቱት ጭፍጨፋዎች ከዚህ ቀደም ታይተው በማይታወቁ መንገዶች የተፈጸሙ በመሆናቸው ከፍተኛ ሥጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡
ጋምቤላ ሚያዝያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት በደረሰው ጭፍጨፋ የ182 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ ከዚህ ቀደም ባሉት ቀናት ከነበረው ግድያ ጋር በድምሩ የ208 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ታውቋል፡፡ 72 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ይታወቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ 36 ሕፃናት በዕለቱ ታፍነው ሲወሰዱ ቀደም ባሉት ቀናት ከተወሰዱት ጋር የታፈኑት ሕፃናት ቁጥር 108 ደርሷል፡፡ ከ2,000 በላይ ከብቶች ተነድተዋል፡፡ ይህ ዘግናኝ ክስተት መላ ኢትዮጵያውያን ለከፍተኛ ሐዘን ዳርጎ ባለበት ወቅት፣ በድጋሚ በሳምንቱ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ መከሰቱ ብዙዎችን አስቆጥቷል፡፡
ለሚያዝያ 7 ቀን ጥቃት መንግሥት አፀፋዊ ዕርምጃ በመውሰድና ሕፃናቱን ለማስለቀቅ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ዓርብ ሚያዝያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ ታፍነው የተወሰዱ ሕፃናት ያሉበት ቦታ ተለይቷል፡፡ አቶ ተወልደ ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰው ጥቃት ከጀርባው የፖለቲካ አጀንዳ መኖር አለመኖሩ፣ ጥቃቱን ያደረሰው አካል ማንነት እየተመረመረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ይህንን ግድያ በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ሕዝቡን ለማረጋጋት በተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ ላይ እንዳሉ ገልጸው፣ በሁለተኛው ግድያ ዙሪያ ሙሉ የተሟላ መረጃ እንደሌላቸውም ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ችግሩ የተከሰተው በተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት ለበቀል በተነሱ ስደተኞች መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ 272,648,300 የተለያዩ አገሮች ስደተኞችን ታስተናግዳለች፡፡ ከዚህ ውስጥ በጋምቤላ ክልል የሚገኘውና ይህ ጭፍጨፋ የተፈጸመበት ጀዊ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ 48,648 ስደተኞች ይገኛሉ እንደሚገኙ እና ስደተኞችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ስደተኞችና ስደት ተመላሾች ባለሥልጣን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ በሪፖርተር የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን በመጠቆም ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
በተለይ የትናንት በስቲያውን ግድያ ተከትሎ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ተቃውሞ በማሰማት የ21 ኢትዮጵያውያንን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደሚገኙበት ጀዊ ሲያቀኑ ከመከላከያ ሰራዊትና ከፖሊስ ግጭት በመፈጠሩ በኢትዮጵያውያኑ ግድያ ተቃውሞ ሲያሰሙ ከነበሩት መካከል ቢያንስ 2 ሰዎች በፀጥታ ኃይሉ በተወሰደ ርምጃ እንደተገደሉ የኢሳ ዘገባ አመልክቷል፡፡ አካባቢው ይህ እስከተዘገበበት ድረስ አለመረጋጋት እንደሚታይበት የአከባቢው ነዋሪዎች ይናራሉ፡፡
ምንጭ፡-ሪፖርተር ጋዜጣ እና ኢሳት
አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በሽብር ተከሰሱ
የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የሽብር ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ባለፈው ሰኞ ሚያዝያ 10/2008 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ሚያዝያ 14/2008 ዓ.ም በፌደራል አቃቤ ህግ ክስ የቀረበባቸው 22 ተከሳሾች ክሳቸው ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በንባብ ተሰምቷል፡፡
በአቶ ጉርሜሳ አያናው መዝገብ የተከፈተው ክስ ላይ እንደተመለከተው የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በአራተኛ ተከሳሽነት ስማቸው ተቀምጧል፡፡ ተከሳሾቹ በ2001 ዓ.ም የወጣውን የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 የተለያዩ አንቀጾችን በመተላለፍ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፣ ተከሳሾች ለ122 ሰዎች ጉዳት፣ ለንብረት ውድመት፣ ለመሰረተ ልማት መስተጓጎል፣ ለትምህርት መስተጓጎል ተጠያቂዎች ናቸው ሲል አቃቤ ህግ በክሱ ላይ አመልክቷል፡፡
ተከሳሾች በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሽብርተኛ ተብሎ በተፈረጀው ኦነግ ውስጥ በአመራርነትና በአባልነት በመሳተፍ የሽብር ወንጀልን መፈጸማቸውን ክሱ በንባብ ሲሰማ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ተከሳሾች በአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ምክንያት የተቀሰቀሰውን የህዝብ ተቃውሞ በማነሳሳትም ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
በዚህ መዝገብ የተካተቱት ተከሳሾች ዝርዝር የሚከተለው ነው፡-
1. ጉርሜሳ አያናው
2. ደጄኔ ጣፋ
3. አዲሱ ቡላላ
4. በቀለ ገርባ
5. አብደታ ነጋሳ
6. ገላና ነገረ
7. ጭምሳ አብዲሳ
8. ጌቱ ግርማ
9. ፍራኦል ቶላ
10. ጌታቸው ደረጄ
11. በየነ ሩዶ
12. ተስፋዬ ሊበን
13. አሸብር ደሳለኝ
14. ደረጄ መርጋ
15. የሱፍ አለማየሁ
16. ሂካ ተክሉ
17. ገመቹ ሸንቆ
18. መገርሳ አስፋው
19. ለሚ ኤዴቶ
20. አብዲ ታምራት
21. አብደላ ከመሳ
22. ሀራኮኖ ቆንጮራ፣ ናቸው፡፡
ተከሳሾቹ ዛሬ ክሳቸው በንባብ ሲሰማ አንዳቸውም ጠበቃ አልነበራቸውም፡፡ ከተከሳሾች መካከል ሰባቱ አማርኛ ቋንቋ እንደማይችሉ ገልጸው ክሱን እንዳልሰሙ ተናግረዋል፡፡ 22ኛ ተከሳሽ በበኩሉ ኦሮምኛም አማርኛም እንደማይችል አስረድቶ፣ ኪስዋህሊ ቋንቋ አስተርጓሚ እንዲመደብለት ጠይቋል፡፡
ፍ/ቤቱም አስተርጓሚ እንዳላቀረበ ገልጾ በቀጣይ ማክሰኞ ሚያዝያ 18/2008 ዓ.ም አስተርጓሚ በመመደብ ተከሳሾች የሚያመለክቱት አቤቱታ ካለ ሊቀበል እንደሚችል ገልጾ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾች ከችሎት ወጥተው ወደመኪና ሲጫኑ በጋራ መዝሙር ያሰሙ ነበር፡፡
ምንጭ፡-EHRP