ምርጫ 2007 እና የ‹‹ተመራጩ›› አምባገነን ጉዞ
ጌታቸው ሺፈራው
በየ ዘመኑ የመንግስት ስርዓቶች ይቀያየራሉ፡፡ የህዝብ አመለካከት አድማስና የሚፈልገው ስርዓትም እንዲሁ፡፡ ይህን ሁሉ በሚገባው መንገድ ለመምራት ደግሞ ገዥዎች ለወቅቱ ሁኔታ የሚያወጣቸውን የአገዛዝ ስርዓት ይዘረጋሉ፡፡ በተለይ ከህዝብም ሆነ ከሌላ አካላት ስልጣንና ህይወታቸውንም እያጡ የሚገኙት አምባገነኖች ስልጣናቸውን ለማቆየት የሚደረግን ብልጣብልጥ መንገድ ሁሉ መከተላቸው የተለመደ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምርጫ ዘመናዊ ፖለቲካ መለኪያ ነው፡፡ ነገር ግን ምርጫ አምባገነኖችን ስልጣን የሚያሳጣ በመሆኑ በሙሉ ልባቸው ወደ ምርጫ መግባትን አይደፍሩም፡፡ ከዚህ ይልቅ በስመ ምርጫ፣ አምባገነንነታቸውን፣ አፋኝነታቸውን ያጠናክራሉ፡፡ እነዚህን አብዛኛዎቹ ብልጣብልጦች ምርጫን እየጠሉ በስመ ምርጫ ስልጣናቸውን የሚያራዝሙ አምባገነኖች ‹‹ተመራጭ አምባገነኖች›› ይሏቸዋል፡፡
ይህ አይነት ስርዓት ከአፍሪካዎቹ ዚምባብዌ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ዩናጋዳ እስከ ቱርክ ኢራንና ሩሲያ ድረስ ያለውን የብልጣብልጦች ‹‹መንግስት›› የሚያጠቃልል ነው፡፡ በእርግጥ በአፍሪካው በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ገዥው ፓርቲ ደህንነትና መከላከያ ሰራዊቱን በቀኝ እጁ ምርጫን ደግሞ በግራው አንጠልጥሎ ወደ ‹‹ምረጡኝ›› የሚገባበትና ያልፈለገው ነገር ሲከሰት ‹‹ጨዋታ ፈረሰ!›› የሚልበት በመሆኑ ‹‹ተመራጭ አምባገነን/አፋኝ›› የሚባለውን መስፈርትም ብዙም የሚያሟላ አይደለም፡፡ ብልጣብልጥነትን ይልቅ ግትርነት፣ ማን አለብኝነት፣ አሊያም እኔ ከሞት ሰርዶ አይብቀል አይነት የአህያዋ አስተሳሰብ የተጠናወተው ነው ማለት ይቀላል፡፡
ምርጫው ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው፣ በህዝብ ገንዘብ አባላት፣ ተለጣፊ ተቃዋሚዎችን፣ ሚዲያ አደራጅቶ አማራጭ አልባ ‹ተመራጭ›› ከመሆን እስከ ማጭበርበር፣ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ቢሸነፍ በሀይል የምርጫ ድምጽ በመንጠቅ ምርጫውን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የሚቆጣጠረው ስልጣን ላይ ያለው ‹‹ተመራጭ›› አምባገነን/አፋኝ ስርዓት አይነተኛ ባህሪ ነው፡፡
ህገ መንግስት፣ ፍርድ ቤት፣ ምርጫ ቦርድ፣ ሚዲያ (የግል የሚባሉትን ይጨምራል)፣ ተቃዋሚዎቹም እንዳይንቀሳቀሱ ነገር ግን ለእርዳታ ለጋሾች የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዳለ፣ ህዝብም አማራጭ እንዳለው ነገር ግን እንደማይመርጣቸው ለማሳየት ተቋማትን እያዳከመ ለመግዛት ይጥራል፡፡ እነዚህ ተቋማት ስርዓቱ የሚፈልገው ግብ ይደርስ ዘንድ የቲፎዞነት ሚና ከተወጡ ደግሞ በማያሸልመው እየሸለመ፣ በማያስደጉመው ተግባራቸው እየደጎመ በአሯሯጭነት ያስቀጥላቸዋል፡፡ ይህን በእኛ አገር በግልጽ የምናስተውለው ነው፡፡ ኢህአዴግ ፓርቲም መንግስትም ሆኖ የህዝብን ሀብት ‹‹የጋራ ምክር ቤት›› ውስጥ ተካተው ለምርጫው በአሯሯጭነት ለተሰለፉት፣ አብዛኛው የፓርቲው ካቢኔ በአንድ ሰው ለተያዘባቸው ፓርቲዎች ከ100 ሺህ እስከ 390 ሺህ ብር አከፋፍሏል፡፡ በምርጫ ሊቀናቀኑት የሚችሉትን ግን አመራሮቻቸውን እያሰረ፣ ጽ/ቤት እንዳያገኙ፣ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ እንዳያካሂዱ በሀይል እያገደ ከአሁኑ ምርጫውንና እድሜውን ለመወሰን እየጣረ ነው፡፡
እንደ አጠቃላይ ግን ተመራጭ አምባገነንነት/አፋኝነት በምርጫ ስም የሌለን ምርጫ ምርጫ እንዳለ፣ ያላሸነፉትን ምርጫ አጭበርብረውም ሆነ ድምጽ ቀምተው በህጋዊ መንግድ እንዳሸነፉ፣ ነጻ ያልሆኑትን ተቋማት ነጻ እንደሆኑ በማስመሰል ስልጣናቸውን በማራዘም የተካኑ ስርዓቶች መገለጫ ነው፡፡ ብልጣብልጥ ነው ባይባልም ኢህአዴግ ይህን ስልት በዋነኛነት እየተከተሉት ከሚገኙት አፋኞች መካከል የግንባር ቀደምነቱን ቦታ ለመያዝ እየተንደረደረ ነው፡፡
‹‹ተመራጩ›› ኢህአዴግና ምርጫ 2007
ለኢህአዴግ ምርጫ 2007 ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ወሳኝ ይመስለኛል፡፡ በአንድ በኩል ለዴሞክራሲ ጭላንጭል በር ከፍቶ የነበረው ምርጫ 97 በአሳዛኝ መልኩ ካለቀ በኋላ ህዝቡ ላይ የተፈጠረውን የምርጫ ፍዘት (apathy) በማጠናከር ነገር ግን ለተወሰነው የማህበረሰብ ክፍል በምርጫ የሚያምን፣ ተመርጦም የሚመራ ለማስመሰል ይጠቀምበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛውን በጀት የሚሰበስብበትን አሁን አሁን የኢህአዴግን ሪፖርት ሳይቀር (የኢኮኖሚ እድገት….የመሳሰሉትን የስታስቲክ ባለስልጣን የተጋገረ ሪፖርት) እንደሪፖርት ማየት የተገደደውን የ‹‹ዓለም አቀፍ›› ማህበረሰብ ለማሞኘትም ይጠቀምበታል፡፡ ምርጫ ለስልጣኑ አደጋ እንደሆነ በምርጫ 97 በደንብ ተምሮበታልና እውነተኛ ምርጫ ግን እንዲኖር ይፈቅዳል ማለት ዘበት ነው፡፡
ያም ሆኖ የ2007 ዓ.ም ምርጫ ለኢህአዴግ አስፈላጊ የሆነውን ያህል መስቀለኛ መንገድ ላይም የሚጥል ነው፡፡ በአንድ በኩል ቀደም ብሎ ያወጀውን የ‹‹አውራ ፓርቲ››ነት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ዘንድ ‹‹ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ›› ያደረገ ተብሎ ቅቡልነት ለማግኘት ይጠቅመዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝብንም ሆነ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ‹‹ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ አድርጌ አሸንፌያለሁ›› ብሎ እንደሚያሞኘው ለምርጫ የሚያበቃ ምህዳር መዘርጋቱ እራሱን አጋልጦ መስጠት ይሆንበታል፡፡
በመሆኑም በህዝቡም ሆነ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ቢቻል ነጻና ፍትሃዊ የሚመስል ‹‹ምርጫ›› እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ነጻና ፍትሃዊ በሚመስል ምርጫ ውስጥም አደጋ የሚያደርሱበት አካላት ላይ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለበት፡፡ ለገዥው ፓርቲ በምርጫው ቀጥተኛ አደጋዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ከፓርቲዎቹ ባሻገር ሲቪክ ማህራት፣ ሚዲያ፣ ነጋዴው ማህበረሰብ፣ ሌላው ህዝብ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በምርጫው ወቅት ተጽዕኖ ከማሳደር ጀምሮ ለስልጣኑ አደጋ አድርጎ ይቆጥራቸዋል፡፡ ነገር ግን ዋነኛዎቹ ተቀናቃኞች ተቃዋሚዎች እንደመሆናቸው ትልቁን ስራ የሚሰራው በእነሱ ዙሪያ ነው፡፡
ተቃዋሚዎቹ በምርጫ 1997 ኢህአዴግን ካስበረገጉት ማግስት ኢህአዴግ መስራት የጀመረው ‹‹ተቃዋሚዎችን ከህዝብ መነጠል፣ ተቃዋሚዎችን ራቁታቸውን ማስቀረት…..›› በሚል አዲስ ‹‹ስልት›› ነው፡፡ በምርጫ 97 ሲቪክ ማህበራት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለምርጫ ስርዓቱ የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ምርጫ 97 በኋላ እነሱን የሚያስቆምበት መላ ዘየደ፡፡ የሲቪህ ማህበራት አዋጅ በመሳሪያነት የተጠቀመበት አንዱ ስልት ነው፡፡ ሲቪክ ማህበረሰቦች ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ቢኖርም ይህ ሁሉ ከስልጣኑ የማይበልጥበት ገዥው ፓርቲ በአዋጁ መሰረት እንዳይንቀሳቀሱ በማገድ ‹‹ተቃዋሚዎችን ራቁታቸውን›› የሚያስቀርበት እንደ አንድ ትልቅ ስልት ወሰደው፡፡ በእርግጥ ይህ ከስልጣን ጥማት የመነጨው የገዥው ፓርቲ ስልት ተቃዋሚዎቹን ብቻ ሳይሆን አገሪቱንም ጭምር ራቁቷን የማስቀረት ስልት ነው፡፡
ሚዲያ ተቃዋሚዎች መግለጫ የሚያወጡበት፣ ፖለቲከኞች በቃለ መጠይቅም ሆነ በአስተያየት መልክ ሀሳባቸውን ለህዝብ የሚያደርሱበት፣ ስለ ፓርቲዎችና እንቅስቃሴዎቻቸው ዜናዎች የሚተላለፉበት በመሆኑ ኢህአዴግ የተቃዋሚዎች ጋሻ አድርጎ ይወስዳቸዋል፡፡ ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ ልሳኖቻቸው አድርጎ ይከሳቸዋል፡፡ በመሆኑም የሚዲያ አዋጅ በማውጣት ሚዲያዎቹ በስርዓቱ ላይ ጠንከር ያለ ትችት እንዳይሰነዘር በስም ማጥፋትና በመሳሰሉት ማጥመድ ጀመረ፡፡ ይህ አልበቃ ሲልም ጋዜጠኞችን በማስፈራራት አገር ጥለው እንዲሰደዱ አደረገ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማተሚያ ቤት እንዳያገኙ ተደረገ፡፡ በቅርቡ ደግሞ የራሱን መዋቅር በማደራጀት በተለይ የግል ጋዜጦችና መጽሄቶች ወደ ክፍለ ሀገር እንዳይከፋፈሉ አከፋፋዮችን በራሱ አደረጃጀት ማዋቀሩ ተሰምቷል፡፡ ይህ አማራጭ መረጃን ለህዝብ የሚያደርሱ ሚዲያዎችን በማፈን ተቃዋሚዎችን ‹‹ራቁታቸውን የማስቀረት›› ለ40ና 50 አመት የታቀደው የ‹‹አውራነት›› በአጭር ጊዜ ደግሞ የ2007 ቅድመ ዝግጅት አንዱ አካል ነው፡፡
ይህ ሁሉ ግን በቂ አይደለም፡፡ ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራርና አባላትን፣ የሲቪክ ማህበራትና የኃይማኖት መሪዎችን፣ አርሶ አደሮችን፣ ነጋዴዎችን፣ መምህራንን፣ ተማሪዎችን…..በአጠቃላይ ከተቃዋሚዎች ጋርም ሆኖም ይሆን በግል ስርዓቱን የተቃወመ አሊያም ይቃወማል ተብሎ የታሰበን ‹‹ከህዝብ የሚነጥልበት›› አዋጅ አስፈላጊ ነበር፡፡ ለዛም ሲባል የጸረ ሽብር ህጉ ወጣ፡፡ በዚህ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር፣ ጋዜጠኛ፣ የኃይማኖትና የሲቪክ ማህበረሰብ መሪ፣ አርሶ አደር ‹‹አሸባሪ›› ተብሎ በሚከሰስበት ህግ በርካቶች ለእስር ተዳርገዋል፡፡
በአንጻሩ በዚሁ ህግ የታሰሩት አውሮፓውያን በወራት ውስጥ ተለቀዋል፡፡ ምንም ለውጥ አያመጡም የተባሉት የተገንጣይ ቡድን አባላት በፓርላማ አሸባሪ ተብለው አዋጁ ይቅርታ የሚሰጥበት ምንም አንቀጽ ሳይኖረው፣ ፓርላማውም ‹‹አሸባሪነታቸውን›› ሳይሽር በጓዳ እርቅ ወደ አገር ቤት ገብተዋል፡፡ በዚህ ህግ የከሰሷቸውን እነ አንዳርጋቸው ጽጌን በሚሊዮን ዶላር ከየመን እንዳላመጡ በድንገት አዲስ አበባ የተገኙትን ‹‹አሸባሪዎች›› በ24 ሰዓት ‹‹ውጡልን!›› ብለው ለምነዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው አዋጅ፣ ህግ….ተብሎ ለስርዓቱ መግዢያ መሳሪያ፣ መጠቀሚያና ያለ አማራጭ ‹‹ማስመረጫ›› መሆኑን ነው፡፡
የጸረ ሽብር አዋጅ ከየትኛውም አዋጅ በላይ ‹‹ተቃዋሚዎችን ራቁታቸውን ማስቀረት›› የተሰኘውን የኢህአዴግ ስልት ለማስፈጸም መጠቀሚያ መሳሪያ ሆኗል፡፡ እነ አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ አበበ ቀስቶ፣ …. ተቃዋሚዎቹ ጋር እየሄደ ስለ ሰላማዊ ትግል ያስተምር የነበረውና ስለ ለውጥ ትንታኔ የሚሰጠው እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታየ፣ ርዕዮት ዓለሙ…… በማሰር ተቃዋሚዎችን ራቁት የማስቀረት ስልት ለመተግበር ሞክሯል፡፡ የተቀውሞ ጎራው፣ ሚዲያው ተቀዛቀዘ ሲባል እንደገና ሲጠናከር ደግሞ ሀብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታ፣ የሽዋስ አሰፋ፣ ዳንኤል ሺበሽ፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና ጋዜጠኞችን አስሮበታል፡፡ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ በየ ክፍለ ሀገሩ የሚገኙ የአንድነት፣ የመኢአድ፣ የሰማያዊና የአረናን ጠንካራ አመራሮችና አባላት በጸረ ሽብር ህጉ እየከሰሰ እያሰረ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባም ሆነ በየ ክፍለ ሀገሩ የሚገኙ ጠንካራ አባላትንና አመራሮች ላይ የሚደረገው እርምጃ አሁንም እንደሚቀጥል ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምርጫ የሚመስል ምርጫ አካሂዶ በህዝብ ዘንድም ሆነ በለጋሾች ‹‹ተመራጭ›› ለመምሰል ነው፡፡
የቀድሞው የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ድኤታ አቶ ኤርምያስ ለገሰ በመጽሃፉም ኢህአዴግ በ1997 ውድድሩን ቀድሞ ክፍት ማድረጉ በአመራሩ ዘንድ ስህተት መሆኑ እንደታመነበት ጽፏል፡፡ ምርጫ 2007 ዓ.ም እንደ 1997 ዓ.ም ይሆናል ባይባልም ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜም (ለአንድ ሳምንትም ይሁን ወር) ምርጫውን ምርጫ ለማስመሰል የተወሰኑ ክርክሮች እንዲኖሩ ማድረግ፣ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባዎችን በመጠኑ መፍቀዱ የማይቀር ነው፡፡ በእነዚህ ቀናትም ቢሆን ግን በተለያዩ ብሶቶች የተወጠረው ህዝብ በእሱ ላይ እንደሚነሳበት ያውቃል፡፡ በመሆኑም እስከዛው ህዝብን ያደራጃሉ የሚባሉት ተቃዋሚዎች መዳከም (ራቁታቸውን መቅረት) አለባቸው፣ ሚዲያዎችም ከገበያ መውጣት ይገባቸዋል፡፡ በእነሱ ምትክ ደግሞ ስመ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ እየተከፈላቸው ተቃዋሚዎችን የሚያብጠለጥሉ ሚዲያዎች ወደ ገበያው እንደሚመጡ ይደረጋል፡፡ እንዲህ ከሆነ ብቻ ነው ኢህአዴግ ‹‹ተመርጦ›› ለቀጣዮቹ 40ና 50 አመታት ሊገዛ የሚችለው፡፡ ይህ ደግሞ ኢህአዴግ ከአቶ መለስ የወረሰው እውነተኛውን አማራጭ አሳጥቶ በግድ የመመረጥ የ‹‹ተመራጭ›› አፋኝነት ‹‹ሌጋሲ›› ነው፡፡
እነ ሙባረክ፣ ቤል አሊ፣ ኮምፓወሬ በዚህ ብልጣብልጥነት በርከት ላሉ ጊዜያት ስልጣን ላይ ቆይተው በመጨረሻ ያላሰቡት ደርሶባቸዋል፡፡ ከብልጣብልጥነት ይልቅ ግትርነቱ የሚያጠቃው የኢህአዴግ እንደሌሎቹ ‹‹ቀን እስኪጥለው›› ድረስ የ‹‹ተመራጭ›› አፋኝነቱ ጉዞ እንደቀጠለ ነው፡፡ እንደ ‹‹ተመራጩ አፋኝ›› ስርዓት እቅድ ከሆነ ደግሞ ለ50 አመታት ይቀጥላል፡፡
ከታሳሪ ዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገ መንግስታችንን ያክብሩ!
ግልጽ ደብዳቤ ”ለጠቅላይ ሚኒስትር” ኃይለማርያም ደሳለኝ
ከታሳሪ ዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገ መንግስታችንን ያክብሩ!
ሠላም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!? እንዴት ነዎት? ያስታውሱ ከሆነ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢከፊሉ የዚህ ማስታወሻ ፀሃፊዎች ‘ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ’
“ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እባክዎትን የተለያዩ የመንግስት አካላት የሕገ መንግስታችንን ድንጋጌዎች እየጣሱ ነውና እርስዎም በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 74/13/ መሠረት ሕገ መንስቱን የማስከበርና የማክበር ግዴታ ስላለብዎት ሕገ መንግስቱን ያክብሩ”በማለት አንዲት አጭር ደብዳቤ ፅፈንልዎት ነበር፡፡
ድንገት በተለያዩ ምክንያቶች የጻፍንልዎትን ደብዳቤ ካላነበቡት ወይም ማስታወስ ካልቻሉ ዛሬ ይሄን ማስታወሻ ስለምንፅፍልዎት ግለሰቦች አንድ ሌላ ማስታወሻ እንስጥዎ፡ ከ6ወራት በፊት /በሚያዚያ 2006 ዓ.ም/ ሶስት ጋዜጠኞችንና ስድስት ጦማሪያንን ‘ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር ወንጀል ጠርጥሬያችኋለሁ’ በማለት መንግስትዎ ልማታዊ ርምጃ (አብዮታዊ ርምጃ እንደሚባለው) ወስዶ ነበር፡፡
እኛም የዚህ ማስታወሻ ፀሃፊዎች የዚህ ‘ልማታዊ ርምጃ’ ሰለባ የሆንን ግለሰቦች ነን፡፡በርግጥ ከሁለት ዓመታት በፊት ‘ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገ መንግስቱን’ ያስከብሩልን በማለት ጥያቄ ያቀረብንልዎት ግለሰቦች ‘ከ6 ወራትበፊት ሕገ መንግስቱን ለመናድ ሞክራችኋል’ በማለት መንግስትዎ ሲያስረን ሕገ መንግስቱ እንዲከበር ጠይቀን ሕገ መንግስቱን ለመናድ በመሞከር ወንጀል ተጠርጥረን ስንታሰር እስሩ በጣም ግራ አጋብቶን ነበር፡፡በዚህ ያልቆመው መንግስትዎ ክሱን ‘ሕብረተሰቡንና ሀገሪቱን ለማሸበር አቅዳችኋል ሞክራችኋል አሲራችኋል…’ በማለት ወደ ‘ሽብርተኝነት’ያሳደገው ሲሆን እርስዎም ከዚህ ጋር በተያያዘ ሃሳብዎትን ሲሰጡ ስለተመለከትንዎ ትንሽ ቅሬታ ይዘን መጣን፡፡
በቅድሚያ አሁን ያለንበትን ሁኔታ በትንሹ ብናስረዳዎት ቅሬታችንን ለመረዳት ያስችልዎታልና አንዳንድ ጉዳዮችን እንንገርዎት፡፡
ይሄን ማስታወሻ በምንፅፍልዎት ወቅት ከታሰርን ከ 200 ቀናት የተቆጠሩ ሲሆን፣ነገር ግንጉዳያችን ገና በቅድመ ክስ (Pre Trial) የክርክር ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ይሄ የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም መንግስትዎ እንኳን ለእኛ ለተከሳሾች ለከሳሽ አካልም ግልፅ ያልሆነ ክስ በማቅረቡ ነው፡፡ ይሄንንም ስንል ልትፈፅሙት ነበር የተባለው ‘የሽብርተኝነት ድርጊት’ ሳይጠቀስ ‘በቃ የሽብርተኝነት ድርጊት ልትፈፅሙ ነበር’ በማለት በጨበጣ ስለመጣብን ነው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንግዲህ የብዙ ድብደባ፣ ዛቻ እና ስድብ ሰለባዎች ከሆንን በኋላምየቀረበው ይሄ ክስ ነው ከ6 ወራት በኋላም ተከሳሾች ከሳሾቻችንምሳንረዳው በየቀጠሮው እየታሸ ነው የሚገኘው፡፡ ‘የተፋጠነ ፍትህ’ ሕገ መንግስትዊ መብት ነውና የተፋጠነ ፍትህ ይሰጠን፣ እርስዎምይሄን ሕገ መንግስታዊ መብት ያክብሩ እያልንዎት አይደለም ‘ሕገ መንግስቱ ተከብሮ እያለ ሕገ መንግስቱ ይከበር በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ’በማለት ‘ጥፋት የሚያሳምን’ ( አንዱ የዚህ ደብዳቤ ጸሃፌ ጦማሪ ጥፋት ብሎ አንዲፈርም የተገደደው ህገ መንግስቱ ተከብሮ እያለህገመንግስቱ ይከበር ማለቴ ጥፋት ነው ብሎ መሆኑ መንግስትዎን መልክ ግልጽ አድርጎ ያሳያል) መንግስት አለዎትና ይህ ጥያቄ አንደሚበዛብዎትእናውቃለን፡፡
ይልቁንም ቀላልና ግልፅ ቅሬታን ነው ይዘን የመጣነው፡፡ ይሄውም የኢፌድሪ ሕገ መንግስትበአንቀፅ 20/3/ ላይ
‘የተከሠሡ ሰዎች[…] በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር[…]መብት አላቸው::’
በማለት የደነገገ ሲሆን፣ ይሄንን ሕገ መንግስታዊ መብትም ማንኛውም የመንግስት አካል እንዲሁም ግለሰብ የማክበር ግዴታ አለበት፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር እርስዎና መንግስትዎም በተደጋጋሚ ‘ሕገ መንግስቱ ሳይሸራረፍ እናስከብራለን’ ይላሉና ይሄን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ የምታውቁት ይመስለናል፡፡ ነገር ግን ከታሰርን ወዲህ ስለእኛ የእስር ጉዳይ በተጠየቁባቸውጊዜያት ይሄን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ በመጣስ ‘ፍርድዎትን’ በተደጋጋሚ ሲሰጡ ታዝበናል፡፡ እናስረዳዎ፡- ሐምሌ 12/2006 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣሚ መግለጫ ላይ ስለእኛ እስር ጉዳይ ለቀረበልዎት ጥያቄ ሲመልሱ፡-
‘ከአስመራ እስከ ሞቃዲሾ የተዘረጋው የሽብር ሰንሰለት ውስጥ አንዴከገቡ በኋላ ብሎገር ነኝ፣ ጋዜጠኛ ነኝ ማለት ዋጋ የለውም’
በማለት ብዙ ነገሮችን ተናገሩ፡፡ ይሔውልዎት ስህተትዎ፡-
1. የክሳችን ዋነኛ ጭብጥ በሃገርውስጥ ‘የሽብርተኛ ድርጅት በማቋቋም ‘የሽብርተኝነት’ ተግባራትን ለመፈጸም አሲረዋል፡ አቅደዋል… የሚል እንጂ፣ እርስዎም እንደሚሉት ‘ሰንሰለት’ ምናምን አይደለም፣
2. እሺ አሸባሪዎችም ይበሉን፣ነገር ግን ሕገ መንግስቱ እንደሚደነግገው በፍርድ ቤት ‘ጥፋተኝነታችን’ እስሚረጋገጥ ቢጠብቁስ ምናለበት? ይህ የሚያመለክተው እርስዎም እንደ ማእከላዊ መርማሪዎች ነፃ ሆኖ የመገመት (presumption of innocence) መብታችንን እያከበሩልን እንዳይደለ ነው፡፡
ይሄ ነገር የሆነው በድንገት ሊሆን ይችላል ብለንዝም ብንልም እርስዎ ግን በድጋሚ ጥቅምት 6/2007 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባል ለቀረበልዎ ጥያቄሲመልሱ፡-
“የብሎገር ጭምብልአጥልቆና በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ተሸሽጎ ከተከሳሽነት ማምለጥ አይቻልም፡፡ ሽብርተኝነትን መዋጋታችን ይቀጥላል…” እያሉ እርስዎ ያሉትን የብሎገር ጭምብል አውልቀውና ተሸሸጉበት ያሉትን የጋዜጠኝነት ሙያመሸሸጊያ አፍርሰው ባንዴ ‘የአሸባሪነት’ ካባ ደረቡልን፡፡
ክቡር ጥቅላይ ሚኒስቴር፣ እያልን ያለነው የአንድ ሰው ‘አሸባሪነት/ወንጀለኝነት’ የሚረጋገጠው በፍርድ ቤት እንደሆነ ሕገ መንግስቱ ደንግጎ እያለ፣ እርስዎ ግን ነፃ ሆኖ የመገመት መብታችን ወደ ጎን ብለው እንደ ከሳሽም እንደፈራጅም በመሆን ‘አሸባሪዎች’… እያሉን ይገኛሉ ነው፡፡
ምናልባት ‘ስራ አስፈጻሚው ከሳሽ ነውና እኔም የስራ አስፈጻሚው አካል መሪ ስለሆንኩ የፈለኩትን አስተያየት የመስጠት መብት አለኝ’ ብለው ከሆነ፣ ሕገ መንግስቱን የማክበር ጉዳይ ‘ርስዎን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች ላይ የተጣለ ግዴታነው፡፡ እርስዎ ‘L’e’tat, c’est moi’ ይሉት አይነት የራስ ግምት ውስጥዎ ከሌለ በስተቀር እንዲህ በግልፅ እየጠየቅንዎት ‘ሕገ መንግስትቱን አላከብርም’ በማለት ገና ዋነኛ ክርክሩ እንኳንያ ልተጀመረ ክስን (ዋነኛ ክርክር ካለው) መሠረት በማድረግ ከዚህ በኋላ እኛን ‘አሸባሪዎች’ አይሉንም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ይህን ተመሳሳይ ምላሽ “በእርግጠኝነት አሸባሪ ናቸው” በሚል ቃና ለቢቢሲ ለኢንቢሲ ለመሳሰሉት አለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማትም መስጠትዎን ሰምተናል፡፡
ሌላው ልናስታውስዎ የምንፈልገው ጉዳይ እንደኛ አይነት የተራገበ( በሰፊው በታወቀ የአደባባይ)የፍርድ ጉዳይ ([un] popular case) ላይ የመንግስት አካላት አስተያየት (say) ያለውን ተፅእኖ እንዲያስቡት ነው፡፡እርስዎ በምክር ቤት ቀርበው የአሸባሪነት ፍርድ ከበየኑብን (አሁን እያደረጉት እንዳሉት) ፍርድ ቤትም ሆነ ሌሎች የመንግስትዎ አካላትምን ሊያስቡ እንደሚችሉ አስተውለውታልን?!
ይሄን ሁሉ ስንልዎ እንዲያው ሕጉን ያክብሩልን ለማለት ያክል ነው እንጅ፣ ከሽብርተኝነትጋር የሚያገናኘን ቅንጣት ያክል እውነት /A segment of fact/ እንደሌለና የሰው ልጆች መልካምና ደስተኛ ሕይወት እንዲኖራቸውከመመኘትና ለአገራችን ያገባናል ከማለት ያለፈ ሕይወትም ፍላጎትም እንደሌለን እኛም እናውቀዋለን እርስዎና መንግስትዎም ያውቁታል፡፡ነገር ግን ካለፉት ስድስት ወራት አንስቶ ጨዋታውን በግድ ካልተጫወታችሁ ተብለናልና እየተጫወትን ነው፡፡ የአሁኑ ጥያቄያችን ግን በጣም ቀላል ነው፣ ጨዋታው ገና በደንብ እንኳን ሳይጀመር ውጤቱን እይወስኑት ነው፡፡
እርስዎ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የስልጣን ደረጃ በወጡ ሰሞን አብዛኞች የዚህ ማስታወሻፀሃፊዎች መጠነኛ ለውጥና ማሻሻዎች ያደርጋሉ የሚል ተስፋ ሰንቀን “The First 100 Days” ወዘተ እያልን ብዙ ጠብቀንዎት ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በሚበልጥ ግዜ እንደተመለከትንዎ ግን ተስፋችን ፍሬ ሊያፈራልን አልቻለም፡፡ አሁንም አዲስ ተስፋ ሰንቀን ግን ፡- “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር እባክዎትን ሕገ መንግስቱን ያክብሩ! የእኛንም መብት ያክብሩልን” እንላለን፡፡
‘’የብሎገር ካልሲ አድርጎ፣ የጋዜጠኝነት ጫማ ተጫምቶ የሽብረተኝነት ሰንሰለት ውስጥ ከገቡ በኋላ ሕገ መንግስቱን ያክብሩልኝ ማለት ዋጋ የለውም!’’በማለት ተስፋችን ዋጋ እንደማያሳጡት ተስፋ አለን፡፡
ከአክብሮት ጋር
ጦማርያን ጋዜጠኞች
ጦማሪያን፡- ዘለዓለም ክብረት ጋዜጠኞች፡- ኤዶም ካሳዬ
ናትናኤል ፈለቀ ተስፋዓለም ወልደየስ
በፈቃዱ ኃይሉ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ
አጥናፍ ብርሃኔ
አቤል ዋበላ
ማህሌት ፋንታሁን
ምንጭ፡- ዞን 9 (ኢትዮጵያ)
እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉት ክሣቸው ተሰማ
- ከአልሸባብና ደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት ነበራቸው ተብሏል
- መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል
በጅሃድ ጦርነት እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም በጅማ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች፤ ሰሞኑን ፍ/ቤት ቀርበው ክሣቸው ከተሰማ በኋላ የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ባለፈው ረቡዕ ክሣቸው በንባብ የተሰማው 7 ተጠርጣሪዎች፡- ጃፋር መሃመድ መሃሙድ ኑር፣ መሃመድ ሣኒ፣ መህዲን ጀማል፣ መሃሙድ አባቢያ፣ አንዋር ትጃኔ እና ሼክ ከማል አባጪብሳ ሲሆኑ በዋና ወንጀል ፈፃሚነት መሠረታቸውን ጅማ አካባቢ አድርገው፣ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተጠቁሟል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ የሽብር ቡድንና በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ጋር ግንኙነት ነበራቸውም ብሏል – የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ፡፡ 1ኛ ተከሣሽ ጃፋር መሃመድ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖታዊ ጦርነት ለማወጅና እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም የሚያስችለውን ስልጠና ከደቡብ አፍሪካ ወስዶ በመምጣት፣ ጅማ አካባቢ ለአላማው ማስፈፀሚያ ቦታ በመምረጥ አባላትን በመመልመል ሲንቀሳቀስ ነበር ተብሏል፡፡
ተከሳሹ በደቡብ አፍሪካ ይገኛል ከተባለው አሸባሪ ቡድን የተላከለትን 80ሺህ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ተቀብሎ ለመሣሪያ መግዣ እንደተጠቀመበት የክስ መዝገቡ አመልክቷል፡፡ በጅማ አካባቢ ኮዳ በተባለ ጫካ ውስጥ የመለመላቸው ግለሰቦች ለ6 ቀናት ስልጠና እንደወሰዱና እንቅስቃሴው በፀጥታ ኃይሎች እንደተደረሰበት ሲረዳ፣ ወደ ሶማሊያ ሄዶ ከአልሻባብ ጋር ለመቀላቀል ሙከራ ሲያደርግ በግንቦት 2006 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋሉን የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡
በመዝገቡ የተካተቱት ቀሪዎቹ 6 ተጠርጣሪዎች አባል በመሆን፣ የሽብር ተልዕኮ በመቀበልና እስላማዊ መንግስት የመመስረት አላማቸውን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ በፈፀሙት በሽብር ቡድን ውስጥ የመሳተፍ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ፍ/ቤቱ ክሱን በንባብ ካሰማ በኋላ፣ የተከሳሾች ጠበቃ በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ለህዳር 10 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡- አዲስአድማስ ጋዜጣ
ኢትዮጵያውያን በቤልጂየም ብራሰልስ የአውሮፓ ህብረት ዋና ጽህፈት ቤት ፊትለፊት የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ
ዛሬ አርብ ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ ገዥው ስርኣት በዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወም የአውሮፓ ህብረት ዋና ፅህፈት በሚገኘው ቤልጂየም ብራሰልስ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ፡፡ ሰልፈኞቹ መንግስት በሽብር ስም አስሮ ክስ የመሰረተባቸውን እና የፈረደባቸውን የኢትዮጵያ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞችን ፎቶ ግራፎችን በመያዝ፣ በተለያየ የሀገሪቱ አካባቢ በመንግስት የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባ የሆኑ ዜጎችን በማሰብና በሀገሪቱ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በግልፅ በመኮንን፤ የአውሮፓ ህብረት ሀገራትም እንዲህ ዓይነት ድርጊቱ በዜጎቹ ላይ ከሚፈፅም ስርዓት ጋር ትብብር ማድረጋቸው አቁመው ፖሊሲያቸውንና አቋማቸውን እንዲመረምሩ የሚጠይቅ ደብዳቤም ለህብረቱ ፅህፈት መግባቱን በስፍራው የነበሩ ምንጮች አስታውቃል፡፡
ሰልፈኞቹ ተቃውሟቸውን በብራሰልስ የአውሮፓ ህብረት ዋና ፅህፈት ካደረጉ በኋላ በከተማው ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመሄድ በሀገሪቱ እየተፈፀመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማውገዛቸውን ተሰምቷል፡፡ የተቃውሞ ሰልፉን አስመልክቶ ከአውሮፓ ህብረትም ሆነ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘውን ዝርዝር ምላሽ በተመለከተ መረጃው እንደደረስን እናቀርባለን፡፡
ኢህአዴግ በክልል የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ማሰርና መደብደቡን ቀጥሏል
የታሰሩ አመራሮች የአንድነት፣መኢአድ፣ ሰማያዊ እና አረና ፓር እና የሲቪክ ተቋም አመራር ይገኙበታል፡፡ እነኚህም ከአንድነት ከሰሜን ጎንደር ምዕራብ አርማጭሆ አቶ አንጋው ተገኝ፣ አቶ አባይ ዘውዱ፣ አቶ እንግዳው ዋኘው እንዲሁም ከመተማ አቶ በላይነህ ሲሳይ እና አቶ አለባቸው ማሞ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም.፤ ከበመቀሌ የአንድነት አባል የሆነው አቶ ሺሻይ አዘናው ደግሞ ጥቅምት 26 2007 ዓም ተይዘው እስካሁን ባልታወቀ ስፍራ በመንግስት ፀጥታ ኃይሎች ታፍነው መሰወራቸው ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ ወቅት ሌሎች የአንድነት አመራሮች ከወረታ አቶ አለበል ዘለቀ፣ከምዕራብ ጎጃም ደጋ ዳሞት ወረዳ አቶ ጥላሁን አበበ በመንግስት ፀጥታ ይሎች ታፍነው ወዳልታወቀ ቦታ መታሰራቸው ፓርቲው አስታውቋል፡፡ ሌላው የአንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን አመራሮች አቶ ማሞ ጎሙ፣ አቶ ወኖ መናሳ እና አቶ አልታዬ አቦታ በመንግስት የደህንነት ኃይሎች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸውና የህክምና ዕርዳታም እየተደረገላቸው እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ አንድነታ ፓርቲ ድርጊቱን በመቃወምና በማውገዝ ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. መግለጫ ማውጣቱ ታውቋል፡፡
ከመኢአድ የቀድሞው የፓርቲው ዋና ፀሐፊነ አመራር ተስፋዬ ታሪኩ ከጎጃም ደጀን በፀጥታ ኃይሎች ታፍነው መወሰዳቸው እንዲሁም ከሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ የሰሜን ጎንደር የዞን አመራር የሆኑት አቶ አግባው ሰጠኝ ጎንደር ከተማ ውስጥ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በተመሳሳይ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ታፍነው ወዳልታወቀ ስፍራ እንደሰወሯቸው ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል፡፡ በተያያዘ ዜና ከአረና ትግራይ ፓርቲ ደግሞ በትግራይ ክልል የሚገኙ አመራሮቹና አባሎቹ ቀሺ ብርሃኑ ቀባዕ፣ኣቶ ኣያሌው ጣዕምያለው፣,አቶ ሓለፎም ገብረዝጊ እና ቀሺ ገብረእግኣብሄር ካሳዬ ጥቅምት 26 ቀን 2007 ዓ.ም.በተመሳሳይ በፀጥታ ኃይሎች ታፍነው መወሰዳቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡ የኢህአዴግ መንግስት መጪውን ምርጫ 2007 ዓ.ም. ከወዲሁ ታሳቢ በማድረግ ከላይ የተጠቀሱ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ወጣት አመራሮችን ማሰር፣ መሰወርና መደብደቡን አጠናክሮ መቀጠሉ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የመግባባት፣ አንድነትና ሰላም (ሰላም) ማህበር የተሰኘው የሲቪክ ተቋም ስራ አስኪያጅ አቶ ፋንታሁን ብርሃኑ ጥቅምት 23 ቀን 2007 ዓ.ም.መታሰራቸው ተጠቁሟል፡፡ አቶ ፋንታሁን ማኀበራቸው በህግ የተፈቀደለትንና የቆመለትን ዓላማ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ተይዘው መታሰራቸውን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ ያመለክታል፡፡
በተለይ የፓርቲዎቹ ወጣት አመራሮች ላይ በተከታታይ እየደረሰ ያለውን እስርና ድብደባ ምክንያት በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ጥረት ቢደረግም አልተሳካም፡፡ በተለይ ከሚያዚያ 2006 ኣ.ም. ጀምሮ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን፣ ብሎገሮችን እና ወጣት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በጅምላ ማሰሩን አጠናክሮ መቀጠሉን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡