በኢትዮጵያ የጥራት ጉድለት የተገኘባቸው 69 ሚሊየን ኮንዶሞች ተገኙ
በያዝነው 2008 ዓ.ም. ሁለተኛ አጋማሽ የጥራት ጉድለት የተገኘባቸው 69 ሚሊየን ኮንዶሞች ሊወገዱ ነው።
ከግሎባል ፈንድ በተገኘ ከ2 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የተገዙት ኮንዶሞች፥ በኢትዮጵያ የምግብ መድሃኒትና ጤና አጠባበቅ ቁጥጥር ባለስልጣን ፍተሻ የጥራት ችግር እንዳለባቸው ተጋግጧል።

ኮንዶሞቹ ከሁለት ወራት በፊት በተደረገ ፍተሻ መያዛቸው ነው የተገለጸው። የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና ዳይተሬክር አቶ መስቀሌ እንደተናገሩት፥ የኮንዶሞቹ አቅራቢ ድርጅት ለግዢ የወጣውን ገንዘብ እንዲተካ የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል።
ኮንዶሞች ለገበያ ከመቅረባቸው በፊት ጥብቅ የጥራት ፍተሻ እንደሚደረግላቸው ያነሱት ዳይሬክተሩ፥ ይህ ስራም ጥራቱ ተረጋግጦ ገበያ ላይ ከዋለ በኋላ በአያያዝ ምክንያት ሊደርስ የሚችል ችግርንም እስከ መፈተሽ ድረስ የሚከናወን ነው ብለዋል ሲል ፋናቢሲ ዘግቧል፡፡
ጥራት የጎደላቸው 69 ሚሊዮን ኮንደሞች በአንድ የህንድ ኩባንያ አማካኝነት በኢትዮጵያ መሰራጨታቸውን በተመለከተ ቀደም ሲል ዋዜማ ሬዲዮ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የተሰራጩት ኮንዶሞች ጫፋቸው የተቀደዱ፣ ፈሳሽ እና አየር ማሳለፍ የሚችሉ፣በላዩ ላይ ያለው ማለስለሻ ቅባት ከሰውነት ፈሳሽ ጋር ሲደባለቅ የጤና ችግር የሚፈጥር እንደሆነ በተደረገ ምርመራ መረጋገጡ ተጠቁሟል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በነበረው ተቃውሞ ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች ይፋ አደረገ
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ ከህዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከ400 በላይ የሚሆኑ ሰልፈኞችን የገደሉ ሲሆን ከአስር ሺህ በላይ የሚቆጠሩትን ደግሞ ማሰራቸውን አስታውቋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ “የኢትዮጵያ መንግስት የተፈጸሙ ግድያዎችን፣ እስራቶችንና ሌሎች የመብት ጥሰቶች በአስቸኳይ ተአማኒነት ያለውና ገለልተኛ የሆነ ማጣሪያ እንዲካሄድ ድጋፍ ማድረግ አለበት።” ሲል ባለ 61 ገፅ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

ድርጅቱ ሰኔ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው ባለ 61 ገጽ ሪፖርት “ጭካኔ የተሞላበት አፈና’ – የግድያ እና የእስራት ምላሽ፤ ለኢትዮጵያ የኦሮሞ ተቃውሞ” የሚል ነበር፡፡ መንግሥትም በነበረው ተቃውሞ ያልተመጣጠነ ርምጃ መውሰዱን በመግለፅ ድርጊቱን አውግዟል፡፡ ሪፖርቱ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ እንዲሁም ሀሳባቸውን በነጻነት በሚገልጹ ዜጎች ላይ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን፣ ከ125 በላይ የሚሆኑ የተቃውሞ ሰልፎች ተሳታፊዎችን፣ ጉዳዩን በአንክሮ ሲከታተሉ የቆዩ ግለሰቦችን፣ በተለያዩ ጊዜያት የመብት ጥሰት የተካሄደባቸውና ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ያካተተ ቃለ መጠይቅ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡
በመንግሥት የተቋቋም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮምሽን ይህንን የኦሮሚያ ክልል ተቋውሞ ተከትሎ በተወሰደ ርምጃ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 173 ብቻ መሆናቸውን እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው ርምጃም “ተገቢና ተመጣጣኝ” ነው ሲሉ ኮሚሽነሩ ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ሰኔ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. “ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” እና ለጋዜጠኞች ገልፀዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ተገቢና ተመጣጣኝ ያሉት ርምጃ የተወሰደው በመከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ እና በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል መሆኑንም ለጋዜጠኞች ጠቁመዋል፡፡

መንግሥታዊ ያልሆነው ሀገር በቀል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፤ በኦሮሚያ ክልል በነበረው ተቃውሞ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው ርምጃ ተገቢና ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ቀደም ሲል ይፋ ባደረገው ዝርዝር ሪፖርት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በነበረውን ተቃውሞ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ፤ ሀገር በቀል የሆነው የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ባለፈው መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በ140ኛው የተቋሙ ሪፖርት “የኦሮሚያ ክልል በ18 ዞኖች እና በ342 ወረዳዎች የተከፋፈለ ሲሆን ሰመጉ ከ9 ዞኖች ውስጥ በ33 ወረዳዎች ብቻ ባደረገው የመስክ ምርመራ ባገኘው ውጤት መሰረት 103 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 57 ሰዎች በጥይት የመቁሰል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡” ብሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተገደሉትና ከቆሰሉት በተጨማሪ በ22 ሰዎች ላይ ማሰቃየት እና ድብደባ መፈፀሙን፣ 84 ሰዎች መታሰራቸውን እንዲሁም 12 ሰዎች የደረሱበት ወይም ያሉበት አለመታወቁንም በመግለፅ ሪፖርቱን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
ሙሉውን የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት እዚህ https://www.hrw.org/news/2016/06/15/ethiopia-protest-crackdown-killed-hundreds ያገኙታል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የቀረበበት ክስ ተሰርዞ በነጻ እንዲሰናበት አመልክቷል
ከሽብር ቡድን አመራሮች ጋር በፌስቡክና በስልክ ግንኙነት በመፍጠር መረጃዎችን አስተላልፏል በሚል የሽብር ክስ የቀረበበት የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ክሱ ተሰርዞለት በነጻ እንዲሰናበት በክስ መቃወሚያው አምልክቷል፡፡

ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው ጋዜጠኛ ጌታቸው አራት ገጽ ያለው የክስ መቃወሚያውን ለችሎቱ አስገብቷል፡፡
ተከሳሹ የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀጽ 7(1)ን በመጥቀስ አቃቤ ህግ ያቀረበበት ክስ “በማናቸውም መልኩ በሽብር ተግባር መሳተፍ” የሚለው፣ አንድ ሽብርተኛ ተብሎ የተሰየመን ድርጅት ስም መጥራት፣ የሽብር ድርጅቱ በሚጠቀምበት ሚዲያ መጠቀም ወይም የሽብር ድርጅት አባል ነው የተባለን ሰው ለሽብር ድርጅቱ አንዳችም ፋይዳ በሌለው ነገር ላይ ማነጋገር ሁሉ ይጨምራል በሚል ተለጥጦ መቅረብ እንደሌለበት በመቃወሚያው ላይ አመልክቷል፡፡
ተከሳሽ አቃቤ ህግ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ስለነበሩ ክስተቶች የሽብር ድርጅት አመራር ናቸው ላላቸው ሰዎች መረጃ ማስተላለፍን በሽብር ድርጅቱ ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ እንደሆነ አድርጎ ማቅረቡ ስህተት ብቻ ሳይሆን ከህጉ አላማም በእጅጉ የራቀ ነው ሲል ተከሳሹ ተቃውሟል፡፡
ስለሆነም የአዋጁን አንቀጽ 7(1) ጠቅሶ ክሱን ማቅረብ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉ አንቀጽ 112 ላይ በወንጀል ጉዳይ በሚቀርብ ክስ ስለ ወንጀሉ እና የወንጀሉ ሁኔታ ስለሚሰጠው ዝርዝር ወንጀለኛው የፈጸመውን ተግባር ወንጀል ከሚያደርገው ሕግ አነጋገር ጋር የተቀራረበ መሆን አለበት የሚለውን አስገዳጅ ድንጋጌ የሚጥስ በመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ መጠቀሱ አግባብ አይደለም ተብሎ ክሱ እንዲሰረዝለት አመልክቷል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው በሁለተኛነት ያቀረበው መቃወሚያ የህጋዊነት መርህን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ ህገ-ወጥነቱ በህግ ያልተደነገገን ድርጊት ወይም ግድፈት እንደወንጀል ሊቆጥረውና ቅጣት ሊወስንበት እንደማይገባ በማስታወስ በክሱ ዝርዝር ላይ የተመለከቱ በህግ ወንጀል ናቸው ተብለው ያልተደነገጉ ድርጊቶችን ጠቅሶ ክሱ እንዲሰረዝለት የሚጠይቀውን መቃወሚያ አስገብቷል፡፡
ተከሳሹ በሦስተኝነት ያቀረበው የመቃወሚያ ነጥብ የተከሰሰበትን ወንጀል ለይቶ በማወቅ መልስ ለመስጠት እንዲያስችለው ግልጽ ሊሆኑለት የሚገቡ ነጥቦችን በመጥቀስ ነው፡፡ በዚህ መቃወሚያ ስር ተከሳሹ ከሽብር ቡድኑ ተልዕኮ እንደተቀበለ ከመጠቀሱ በቀር ተልዕኮው ምን እንደሆነ፣ መቼ፣ ከማን እና በምን አይነት መንገድ ተልዕኮውን እንደተቀበለ ከሳሽ ግልጽ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡ ተከሳሹ ‹‹የሽብር ቡድኑ በሚጠቀምበት ሚዲያ›› በሚል የቀረበበት ክስ በህግ ቋንቋ ምን ማለት እንደሆነም አልተገለጸም ሲል ጠቃውሟል፡፡
በመሆኑም ከሳሽ እነዚህና ሌሎች በመቃወሚያው ላይ የተመለከቱ ነጥቦችን ግልጽ እንዲያደርግ፣ ይህን ማድረግ የማይችል ከሆነ ግን ክሱ ተሰርዞ በነጻ እንዲሰናበት ተከሳሹ ለችሎቱ በመቃወሚያው ላይ አመልክቷል፡፡
ችሎቱ አቃቤ ህግ ተከሳሹ ያቀረበውን የክስ መቃወሚያ ተመልክቶ መልስ እንዲሰጥበት ለመጠባበቅ ለሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡-EHRP
ኦብነግ የኢትዮጵያን መንግሥት በጭፍጨፋ ከሰሰ
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ የመንግሥት ወታደሮችና የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይል ጥቃት አድርሰው ሃምሣ አንድ ሰው ገድለዋል ሲል የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ሰኔ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ስሞታ አሰምቷል፡፡

ሶማሌ ክልል ውስጥ ጃማ ዱባድ በሚባል መንደር ሰሞኑን የመንግሥት ወታደሮችና የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይሎች በመንደርተኞች ላይ ጥቃት አድርሰው 51 ሰው ገድለዋል ሲል የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር – ኦብነግ ከስሷል፡፡
“የመንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች በሌሎች አካባቢዎችም በተለያዩ የቅርብ ጊዜያት ከሦስት መቶ በላይ ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል” ያሉት የኦብነግ ቃል አቀባይ አቶ ሃሰን አብዱላሂ ድርጅታቸው ጉዳዩን ለዓለምአቀፍ ተቋማት ለማድረስ ማስረጃዎችን እያጠናቀረ መሆኑን ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የቪኦኤ የሶማሊኛ ዝግጅት ክፍል ወደ አካባቢው ደውሎ ያነጋገራቸው የጎሣ መሪ ወታደሮቹ ስድስት ሕፃናትና ሴቶችንም ጨምሮ ሃያ አራት ሰዎችን መግደላቸውን አመልክተዋል፡፡ ሌሎች ምንጮች ደግሞ ወታደሮቹ መንደሪቱን ማቃጠላቸውንና አሥር ሰዎች የገበቡበት እንደማይታወቅ ጠቁመዋል፡፡ ስለጉዳዩ ከክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግሥቱ የተሰጠ መግለጫ የለም፡፡
ምንጭ፡- VOA Amharic service
እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ መከላከል አትችሉም ተባሉ
ማህሌት ፋንታሁን
የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል በዋለው ችሎት እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ( ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ኢየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማው እና ደሴ ካህሳይ) አቃቢ ህግ ያቀረበባቸውን ክስ በሰነድና በአንድ የሰው ምስክር ማስረጃዎች አስረድቷል በሚል ተከሳሾች መከላከል ይገባቸዋል ሲል ፍርድ ቤቱ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ውሳኔውን ተከትሎም መከላከያ ማስረጃዎች ያቀርቡ እንደሆነ በሚል ፍርድ ቤቱ ጠይቆ፣ ተከሳሾች 200 የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች በጋራ እንደሚያቀርቡ አሳውቀው ነበር፡፡ ከዛ በኋላ በነበሩ ቀጠሮዎችም ምስክሮቻቸውን በዝርዝር አስገብተው ነበር፡፡ እንዲሁም ከዛሬ ግንቦት 30 እስከ ሰኔ 8 ቀን 2008ዓ.ም. ድረስ ምስክሮቻቸውን እንዲያሰሙ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም፤ የቀጠሯቸው ቀን ሳይደርስ፤ ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ቀርበው ጭብጥ እንዲያሲዙ ተጠይቀዋል። እነሱም የምስክርነት ጭብጥ ምስክሮች መሃላ ሳይፈፅሙ መያዝ እንደሌለበት ለፍቤቱ አስረድተው ውሳኔውን ለመስማት ለዛሬ ተቀጥረው ነበር።

ይሁን እንጂ አራት ወር ሙሉ ፍርድ ቤቱ ሲሰጥ ከነበረው ትዕዛዝ በተለየ “መከላከያ ምስክር ማሰማት የለባችሁም ስለዚህ ለፍርድ ብይን ሃምሌ 13, 2008 ቅረቡ” የሚል ውሳኔ አስተላልፏል።
ምንጭ፡-ከማህሌት ፋንታሁን ፌስቡክ ገፅ የተወሰደ