Category Archives: Human Rights

አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በሽብር ተከሰሱ

 

Bekele Gerba

የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የሽብር ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ባለፈው ሰኞ ሚያዝያ 10/2008 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ሚያዝያ 14/2008 ዓ.ም በፌደራል አቃቤ ህግ ክስ የቀረበባቸው 22 ተከሳሾች ክሳቸው ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በንባብ ተሰምቷል፡፡

በአቶ ጉርሜሳ አያናው መዝገብ የተከፈተው ክስ ላይ እንደተመለከተው የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በአራተኛ ተከሳሽነት ስማቸው ተቀምጧል፡፡ ተከሳሾቹ በ2001 ዓ.ም የወጣውን የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 የተለያዩ አንቀጾችን በመተላለፍ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፣ ተከሳሾች ለ122 ሰዎች ጉዳት፣ ለንብረት ውድመት፣ ለመሰረተ ልማት መስተጓጎል፣ ለትምህርት መስተጓጎል ተጠያቂዎች ናቸው ሲል አቃቤ ህግ በክሱ ላይ አመልክቷል፡፡

ተከሳሾች በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሽብርተኛ ተብሎ በተፈረጀው ኦነግ ውስጥ በአመራርነትና በአባልነት በመሳተፍ የሽብር ወንጀልን መፈጸማቸውን ክሱ በንባብ ሲሰማ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ተከሳሾች በአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ምክንያት የተቀሰቀሰውን የህዝብ ተቃውሞ በማነሳሳትም ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

በዚህ መዝገብ የተካተቱት ተከሳሾች ዝርዝር የሚከተለው ነው፡-
1. ጉርሜሳ አያናው
2. ደጄኔ ጣፋ
3. አዲሱ ቡላላ
4. በቀለ ገርባ
5. አብደታ ነጋሳ
6. ገላና ነገረ
7. ጭምሳ አብዲሳ
8. ጌቱ ግርማ
9. ፍራኦል ቶላ
10. ጌታቸው ደረጄ
11. በየነ ሩዶ
12. ተስፋዬ ሊበን
13. አሸብር ደሳለኝ
14. ደረጄ መርጋ
15. የሱፍ አለማየሁ
16. ሂካ ተክሉ
17. ገመቹ ሸንቆ
18. መገርሳ አስፋው
19. ለሚ ኤዴቶ
20. አብዲ ታምራት
21. አብደላ ከመሳ
22. ሀራኮኖ ቆንጮራ፣ ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ ዛሬ ክሳቸው በንባብ ሲሰማ አንዳቸውም ጠበቃ አልነበራቸውም፡፡ ከተከሳሾች መካከል ሰባቱ አማርኛ ቋንቋ እንደማይችሉ ገልጸው ክሱን እንዳልሰሙ ተናግረዋል፡፡ 22ኛ ተከሳሽ በበኩሉ ኦሮምኛም አማርኛም እንደማይችል አስረድቶ፣ ኪስዋህሊ ቋንቋ አስተርጓሚ እንዲመደብለት ጠይቋል፡፡

ፍ/ቤቱም አስተርጓሚ እንዳላቀረበ ገልጾ በቀጣይ ማክሰኞ ሚያዝያ 18/2008 ዓ.ም አስተርጓሚ በመመደብ ተከሳሾች የሚያመለክቱት አቤቱታ ካለ ሊቀበል እንደሚችል ገልጾ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾች ከችሎት ወጥተው ወደመኪና ሲጫኑ በጋራ መዝሙር ያሰሙ ነበር፡፡

ምንጭ፡-EHRP

 

ሜዲትራኒያን ባህር ላይ በሰጠመችው ጀልባ አደጋ ምክንያት ከሞቱት መካከል ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል

(አዲስ ሚዲያ) ትናንት እሁድ ሚያዝያ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት 400 ያህል ስደተኞችን ጭና ከግብፅ ወደ ጣሊያን ስታመራ የነበረች ጀልባ ሜዴትራንያን ባህር ላይ በመስጠሟ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ ፡፡

Meditreanian sea Boat sinks

በጀልባዋ ሲጓዙ የነበሩት አብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ሲሆኑ የተወሰኑ ኤርትራውያን ስደተኞች እንደሚገኙበት እየተነገረ ሲሆን፤ የሶማሊያ መንግሥት በበኩሉ 200 ያህል ዜጎቹ በአደጋው መሞታቸውን አስታውቋል፡፡ ከሞቱት መካከል ኢትዮጵያውያን እናት እና ልጅን ጨምሮ በርካታ ወጣቶችም በአደጋው ህይወታቸው እንዳለፈ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በጀልባው ላይ ሲጓዙ ከነበሩት መካከል ከ200 ያላነሱት ኢትዮጵያውያን እንደነበሩም ተጠቁሟል፡፡

በተለይ በጉዞ ላይ እያሉ የአደጋው ሰለባ የሆኑት ከህዳር አጋማሽ 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ እየተደረገ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ መንግሥት እየወሰደ ያለውን ወታደራዊ የኃይል እርምጃ በመፍራት አብዛኛው ከባሌ፣ከሐረር እና ድሬዳዋ አካባቢ የተሰደዱ ኢትዮጵያውን እንደሆኑ ቤተሰቦቻቸውን ዋቢ በማድረግ የኢሳት ዘግቧል፡፡

የጀልባዋን መስጠም ተከትሎ በአቅራቢያ የደረሱት ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ሰራተኞች ከ27 ያላነሱ የአደጋው ሰለባ ሰዎችን ህይወት ማትረፍ መቻላቸው የተገለፀ ሲሆን፤ ከሞቱት መካከልም የተወሰኑ አስከሬኖችን አውጥተዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን በአጠቃላይ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ እና ምን ያህሉ እንደተረፉ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም፡፡

በጋምቤላ ከደቡብ ሱዳን በመጡ ታጣቂዎች 170 ያህል ኢትዮጵያውያን ተገደሉ

(አዲስ ሚዲያ)ትናንት አርብ ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት ጀምሮ ከሰዓት በኋላም የቀጠለው በሺህዎች የሚቆጠሩና የታጠቁ ደቡብ ሱዳን ቡማ ግዛት ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ የሙርሌ ማኀበረሰብ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት በጋምቤላ የሚገኙ ህፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 170 ኢትዮጵያውያን የኑዌር ማኀበረሰብ አባላትን መግደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ዋቢ በማድረግ ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡

Murle South Sudan

ታጣቂዎቹ በብዛት የኔዌር ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት በጋምቤላ ክልል ዞን 3 ጂካው እና ኒኔኛንግ ወረዳ የካጃክ አስር የኑዌር መንደር በመሄድ ጥቃት ማድረሳቸው የተገለፀ ሲሆን፤ በተለይ የግድያ ሰለባው የሆኑት በዋናነት ህፃናት እና ሴቶች መሆናቸውንም ከጥቃቱ የተረፉ እማኞች ተናግረዋል፡፡ በጥቃቱም በርካታ ዜጎች መቆሰላቸውና እስካሁን ቁጥራቸው ያልተገለፀ በርካታ ህፃናትም ታግተው መወሰዳቸው ተጠቁሟል፡፡

እንደእማኞች ገለፃ ከሆነ፤ በጥቃቱ ወቅት በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ለጋምቤላ ክልላዊ መንግሥትና በአካባቢው በቅርብ ርቀት ለሚገኙ የፌደራል መንግሥት ፌደራል ፖሊስና መከላከያ የድረሱልን ጥሪ ቢያደርጉም ምላሽ እንዳላገኙ እና ጠዋት የጀመረው ጥቃትም እስከ ከሰዓት ድረስ መዝለቁን ያልተለመደ እንደነበርና በወቅቱ መንግሥት ምላሽ ባለመስጠቱም የብዙ ሰዎች ህይወት መጥፋቱም እንዳሳዘናቸው በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡

“በእጃችን ራሳችንን የምንከላከልበት እንኳ በቂ መሳሪያ ባለመኖሩና የመንግሥትን ምላሽ በማጣታችን ለአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች የድረሱልን ጥሪ በማሰማታችንና ትብብር ስላደረጉልን ታጣቂዎቹ እያደረሱ ያሉትን አደጋ ለመቀነስ ችለናል:: በዚህም ከደቡብ ሱዳን ታጣቂዎችም ከ51 ያላነሱ ሰዎችን ገድለናል፣ የተወሰኑ የተዘረፉ ከብቶቻችንን አስመልሰናል፤ ነገር ግን የታገቱ ህፃናት ልጆቻችንን እና የተዘረፉ ከብቶቻችንን ማስመለስ አልቻልንም “ ብለዋ፤ሌላኛው በህይወት የተረፉ አንድ አባት፡፡

ስማቸውን እንዲገለፅ ያልፈለጉና ከጥቃቱ የተረፉ ግለሰብ እንደተናገሩት ከሆነ፤ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ሰርገው በመግባት ጥቃት ያደርሱ እንደነበር ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፤ የትናንትናው ግን በወታደራዊ የደንብ ልብስ በብዛት ታጥቀው ገብተው የዚህ ዓይነት የከፋ ጉዳት ሲያደርሱ የመጀመሪያቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በትናንትናው ግድያም 170 ኢትዮጵያውያን እና 51 የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎችን ጨምሮ ወደ 221 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡

በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግሥት በበኩሉ በስሩ ባሉ ፋናቢሲ እና ኢቢሲ በመሳሰሉ መገናኛ ብዙኃን እንዳስታወቀው ከሆነ፤ በጋምቤላ ከደቡብ ሱዳን መንግሥትም ሆነ ከመንግሥት ተቃዋሚ ታጣቂዎች ምንም ንክኪ የሌላቸው “ወንበዴዎች” 140 ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን እና ከጥቃት አድራሽ ደቡብ ሱዳናውያን ደግሞ 60 ያህል ሰዎች መገደላቸውን ቢያስታውቅም፤ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃም ሆነ የሰጠው መግለጫ የለም፡፡

ታጣቂዎቹ  ከደቡብ ሱዳን ድረስ ድንበር ጥሰው በመግባት ለምን ኢትዮጵያውያንን እንገደሉ፣ ህፃናቱን እንዳገቱና ከብቶቻቸውን እንደዘረፉ የተገለፀ ነገር የለም፡፡

በያዝነው 2008 ዓ.ም. ባለፉት ወራት በተለያየ ጊዜ በዚሁ በጋምቤላ ክልል የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ በርካታ ዜጎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የትናንቱ ግድያ የጠፈፀመው ግን ከደቡብ ሱዳን በመጡ ታጣቂዎች እንደነበርና ይህንንም ከተገደሉ ሰዎች ማረጋገጥ እንደተቻለ ተጠቁሟል፡፡

እነ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ ጥፋተኝነት ሲበየንባቸው፣ አቶ በቀለ ገርባ እና ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው

በእነ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ ከ600 ቀናት በላይ ፍርድ ቤት ሲመላሱ የቆዩት ተከሳሾች ላይ ዛሬ ብይን ተሰጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ፣ ሰለሞን ግርማ ፣ መምህር ተስፋዬ ተፈሪ ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱት ባህሩ ደጉ እና ዬናታን ወልዴ በነጻ ተሰናብተዋል፡፡

Zelalem Workagegnehu

በተመሳሳይ የክስ ፋይል አብረው የተከሰሱት የፓቲካ ፓርቲ አመራሮች ( አብርሃ ደስታ ፣ ሃብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሸዋስ አሰፋ) እና መምህር አብርሃም ሰለሞን መከላከል ሳያስፈልጋቸው ነጻ መባላቸው ይታወሳል፡፡

Bekele Gerba

ለአራት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ማእከላዊ ምርመራ የከረሙት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው እና አብረው የታሰሩ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስና የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ተጨማሪ አንድ ሳምንት ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ እስካሁን ድረስ በሽብር ከመጠርጠር ውጪ ክሳቸው በውል ያልታወቀው ፣ አቶ በቀለ ገርባ ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውን ጨምሮ ኦሮሚያ ላይ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡

Getachew Shiferaw

ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ቀርበው ለዛሬ ክሳቸው እዲነበብ የተቀጠሩት 33 በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ አካባ ኦነግ ተዋጊነት የተጠረጠሩት እነ ሃብታሙ ሚልኬሳ ዛሬም ክሳቸው ሳይሰማ ለሚያዝያ 20 ሌላ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ተላልፏል፡፡

ምንጭ፡- EHRP

እነ ኦኬሎ ኦኳይ ጥፋተኛ ተባሉ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ መጋቢት 28ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት የቀድሞው የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር ኦኬሎ ኦኳይ እና አብረዋቸው የተከሰሱት ስድስት ተከሳሾች ጥፋተኛ ናቸው ብሎ ውሳኔ አስተላለፈ።ፍርድ ቤቱ የቅጣት አስተያየት ለመስማት ሚያዚያ 17 ቀጠሮ ስጥቷል፡፡

Okello Akuay

በሰኔ ወር 2006ዓ.ም የሽብር ክስ ተመሰርቶባቸው ክሳቸው እየታየላቸው የሚገኙት እነ ኦኬሎ ኦኳይ በየካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ለማስተላለፍ ለዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ ተቀጥረው ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ዛሬ በችሎት ከተሰየሙት ሶስት ዳኞች መካካል የቀኝ ዳኛ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ታደሰ የፍርድቤቱን ውሳኔ በንባብ አሰምተዋል፡፡

ዳኛ ሣሙኤል ታደሰ ወደ አንድ ስዓት በቆየው የፍርድ ውሳኔ ንባባቸው እንዳመለከቱት አቶ ኦኬሎና ስድስቱ ተከሳሾች የጋምቤላ ህዘቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) አባል በመሆን እና የጋምቤላ ክልልን ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ከአሜሪካ ገንዘብ በማሰባሰብ እና የሽብር ቡድን ማስተባበራቸውን በንባባቸው ጠቅሰዋል፡፡

አቃቤ ህግ በነኦኬሎ ላይ ከዘረዘራቸው ክሶች መካከል ከኤርትራ መንግስት ጋር የሽብር ድርድር በማድረግ እና ከኦነግ እና ግንቦት 7 አመራሮች ጋር በተለይ ከሞት ፍርደኛው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር መገናኘት እንደሚገኙበት ዳኛ ሳሙኤል አስታውሰዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶችን ለሽብር ተግባር መመልመል፣ ወታደራዊ ስልጠና መስጠት በክሳቸው ላይ መጠቀሱን ዳኛው ተናግረዋል፡፡

ከክስ ንባብ መስማት በኃላ ወደ ሁለት አመት ያህል ፍርድቤት የተመላለሱት እነ ኦኬሎ አኳይ የክስ መቃወሚያ ካቀረቡበት ጊዜ አንስቶ ለውሳኔ እስከተቀጠሩበት ጊዜ ያለው ሂደት በዳኛው ተብራርቶ ቀርቧል፡፡
የእነ ኦኬሎ የክስ መቃወሚያ በፍርድ ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ መደረጉን እና የተከሰሱበትን ክስ ክደው መከራከራቸውን ያስታወሱት ዳኛ ሳሙኤል በመቀጠል አቃቤህግ ምስክሮቹን አቅርቦ ማሰማቱን አስረደተዋል፡፡
ለወራት ከዘለቀው የምስክሮች መሰማት ሂደት በኃላ ፍርድቤቱ ተከሳሾቹን እንዲከላከሉ መወሰኑን ዳኛው ጠቅሰዋል፡፡ ተከሳሾቹ በምርመራ ወቅት በከፍተኛ ጫና እና ድብደባ ውስጥ እንዳለፉ ማስመዝገባቸውን ዳኛው ጠቁመዋል፡፡

የግራና የቀኙን ክርክር ያዳመጠው እና የቀረቡለትን ማስረጃዎች የመረመረው ፍርድ ቤት በሁሉም ተከሳሾች ላይ የጥፋተኛ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

አንደኛ ተከሳሽ ኦኬሎ አኳይ በሰው እና መማስረጃ የጋምቤላን ክልል ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆን የአመራር ሰጪ ውሳኔዎችን ሲመራ በመቆየቱ አቃቤህግ በሰው እና በማስረጃ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳ ዳኛው በውሳኔው አመልክተዋል፡፡ተከሳሹ በበኩሉ የተከሳሽነት ቃል ከማሰማት በስተቀር መከላከያ ምስክሮችም ይሁን ሰነዶችን አቅርቦ በበቂ ሁኔታ እንዳልተከላከለ ዳኛው ገልፀዋል፡፡
ቀሪዎቹም ተከሳሾች በምርመራ ወቅት ለፖሊስ ቃላቸውን ተገደው ስለመስጠታቸው ያሰረዱ እንጂ የቀረበባቸውን ክስ የሰው ምስክር እና የሰነድ ማስረጃ አቅርበው እንዳልተከላከሉ በዳኛው ተገልጿል፡፡
“[ተከሳሾቹ] ምስክሮቻቸው ማዕከላዊ አብረዋቸው የነበሩ፣ በሌላ ወንጀል ተጠርጥረው ያሉ እና ተዓማኒነታቸው ጥርጣሬ ውስጥ የሚገባ ከመሆኑ በተጨማሪ ከዋናው ክስ እና የክስ ማስረጃ ጋር የማይገናኙ በመሆናቸው ክሳቸውን በደንብ አልተከላከሉም” ሲሉ ዳኛው ገልፀዋል፡፡

ክሱ መታየት ያለበት በፀረ ሽብር አዋጁ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ፍርድቤቱ መርምሮ በአንደኛ ተከሳሽ የተመሰረተው ጋህነን፣ የጋምቤላ ህዝብን ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል ከተለያዩ የሽብር ቡድኖች ጋር የስልጠና ትብብር መጠየቃቸው በአቃቤ ህግ የተረጋገጠ ነው ብለዋል ዳኛው፡፡ ሆኖም ድርጊቱ የአገሪቷን አንድነት የማፈራረስ ሙከራን የሚያቋቁም እንደሆነ የገለፁት ዳኛው በዚህም መሰረት ተከሳሾቹ በፀረ ሽብር አዋጁ ሳይሆን የወንጀል ህጉን 241 በመተላለፋቸው በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ 149(1) የጥፋተኝነት ውሳኔ ማስተላለፉን ተናግረዋል፡፡

መጋቢት 28/2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት የጥፋተኝነት የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው ሰባት ሰዎች ሲሆኑ፣ እነዚህም ኦኬሎ አኩዋይ፣ ዴቪድ ኦጅሉ፣ ኡቻል አፒዮ፣ ኡማን ኒኮዮ፣ ኡጅሉ ቻም፣ ኡታካ ኡዋር እና ኡባንግ ኡቡንግ ናቸው፡፡

ምንጭ፡- EHRP