Category Archives: Human Rights

የመኢአድ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ዘመነ ምህረት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ፓርቲው ገለፀ

AEUO

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የፓርቲያቸው ምክትል ፕሬዝደንት እና የሰሜን ቀጠና ኃላፊ የሆኑት አቶ ዘመነ ምህረት እጅግ ዘግናኝ ድብደባ ደርሶባቸው ሲል ፓርቲው ጥር 15 ቀን 2007 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡ አቶ ዘመነ የመኢአድን ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ወደ መኖሪያቸው ጎንደር ከተማ ከተመለሱ በኋላ ከፍተኛ የደህንነት ክትትልና ጫና ይደረግባቸው እንደነበር ለፓርቲያቸው አሳውቀው ነበር ያለው ፓርቲው ጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም ጎንደር ከሚገኘው መኖሪያው ቤታቸው ከባቤታቸውና ከህፃን ልጃቸው ፊት የፖሊስ ልብስ በለበሱ አካላት ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን ግልጾአል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፓርቲው አባላት ባደረጉት ክትትል አቶ ዘመነ አዘዞ የሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ውስጥ እንደሚኙ አረጋግጠናል ያለው መግለጫው የሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይገመት ከፍተኛ ስቃይና ሰቆቃ ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡

ከአቶ ዘመነ በተጨማሪ ጠቅላላ ጉባኤውን ተሳትፈው የተመለሱት የፓርቲው የማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ አቶ እያሱ ሁሴን 3 አመት ተፈርዶባቸው እስር ቤት እንደሚገኙ፣ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ፣ መ/አ ጌታቸው መኮንን፣ አቶ ጥላሁን አድማሴ የተባሉትን ጨምሮ ሌሎችም የፓርቲው አመራሮች ለእስር መዳረጋቸውን ያወሳው መግለጫው በአመራርና አባላቶቻቸው ላይ የሚደረገው እስር መኢአድ ምርጫውን ተጠቅሞ በገዥው ፓርቲ ላይ ጫና ማሳደር ስለሚችል እንደሆነ ተገልጾአል፡፡

በሌላ በኩል በአባላቶቻቸው ላይ በሚደርሰው በደልና ጫና ባሻገር ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ከምርጫ 2007 እንዳይሳተፍ የኢህአዴግ ቀኝ እጅ ሆኖ በመስራት ላይ እንዳለ ያወሳው መግለጫው ፓርቲው በምርጫው እንዳይሳተፍ ከተደረገ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል፡፡ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ በፓርቲው ላይ የሚፈጽመውን በደል ተከትሎ ፓርቲው በሚደርገው ትግልም ህዝቡ ከጎኑ እንዲቆም ጥሪ ማቅረቡን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በኤርትራ የታሰሩ 6 ጋዜጠኞች ተፈቱ

Eritrean_J

የኤርትራ  መንግስት ባለፈው የካቲት 2001 ዓ.ም. በርካታ ጋዜጠኞች በጅምላ ካሰረቻቸው መካከል በረከት ምስግና፣ ይርጋዓለም ፍስሃ፣ ባሲሎስ ዘሞ፣ ንጉሴ ክፍሉ፣ግርማይ አብርሃም እና ጴጥሮስ ተፈሪ ከ6 ዓመታት እስር በኋላ መፈታታቸውን ድንበርየለሹ የጋዜጠኞች ቡድን (Reporters without Border)  ይፋ አድርጓል፡፡

ጋዜጠኞች በሬዲዮ ባና፣ በሬዲዮ ዛራ እና በሬዲዮ ድምጺ ሃፋሽ ይሰሩ የነበረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ወቅት ከታሰሩት ጋዜጠኞች መካከል ባለፈው መጋቤት 2005 ዓ.ም. 7 ጋዜጠኞችን እንዲሁ የኤርትራ መንግስት በዋስ መፍታቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ እና ስዩም ፀሐዬን ጨምሮ 16 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን አስታውሷል፡፡

ሰሞኑን ከእስር ስለተፈቱት ጋዜጠኞች ያሉበት ሁኔታና የቴንነት ጉዳይን በተመለከተ እስካሁን ለማወቅ እንዳልተቻለና ይህንንም ለማወቅ ክትትል እንደሚያደርጉ የተቋሙ የአፍሪካ ጉዳይ ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡

በተለይ በአፍሪካ ጋዜጠኞችን በማሰር ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር ኤርትራ ቀዳሚ ሀገር እንደሆነች እና ለጋዜተኞች ከማይመቹ የዓለማችን ሀገራት እጅግ አደገኛ በሚል ዝርዝር ውስጥ መግባቷ ይታወሳል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ባህሪ ያላት ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ መንግስት ስልጣን ላይ ያሉት አካላት በትጥቅ ትግል ወደ ስልጣን እንደመጡ አይዘነጋም፡፡

በአዲስ አበባ ኮልፌ የሚገኙ የአባት ጡረተኛ አርበኞች መኖሪያቸው እንዲፈርስ ተደረገ

Ethiopian elders patrioties

በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 09 እና 10 ውስጥ ከኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ በቀድሞ መንግስት በተሰጣቸው ካምፕ ውስጥ ሲኖሩ የነበሩ ከ500 በላይ የአባት ጡረተኛ አርበኞች ቤታቸው በመንግስት እንዲፈርስ በመደረጉ ከነቤተሰቦቻቸው ሜዳ ላይ መበተናቸውን ገለፁ፡፡

በተለምዶ ኮልፌ ልኳንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውንና ከጥንት ጀምሮ የአባት ጡረተኞችና የአርበኞች መኖሪያ የሆነውን የወታደር ካምፕ ቦታው ተከልሎላቸው የሰሩት ራሳቸው አርበኞቹ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ የገለፁ ሲሆን፤ ፈጽሞ ባላሰቡበትና ባልተዘጋጁበት ሁኔታ መኖሪያ ካምፓቸው ያለ ምንም ተለዋጪ ማረፊያ መሳሪያ በታጠቁ ወታደሮች እንዲፈርስ መደረጉ እንዳስደነገጣቸው  መናገራቸውን የኢሳት ዘገባ አመልክቷል፡፡  ነዋሪዎቹ  ውሳኔውን በመቃወም እስከ ፍትህ ሚኒስቴር ድረስ አቤቱታ ቢያቀርቡም  ሰሚ እንዳላገኙ ተጠቁሟል።

ካምፕ የሚገነው ቤታቸው ፈርሶ ሜዳ ላይ ከተበተኑትና የላስቲክ ድንኳን ሰርተው ከተጠለሉት ነዋሪዎች መካከል የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ህመምተኞችና በርካታ ህጻናት እንደሚገኙበት ኢሳት በዘገባው አስታውሷል። የአካባቢው መስተዳድር አካላት ነዋሪውን ሊያነጋግሩ ሲመጡ የአርበኞቹ  ልጆች ባንዲራ እያውለበለቡ አባቶቻቸው በሞቱላትና ወደነሱ ባስተላለፉዋት ሀገራቸው የመኖር መብት ሊነፈጉ እንደማይገባና ያለ አማራጭ መኖሪያ ሜዳ ላይ መውደቅ እንደሌለባቸው አቤቱታ ቢያቀርቡም፤ የመስተዳድሩ አካላት ወጣቶቹ ባንዲራ በመያዛቸው ቁጣቸውን በመግለፅ ያለምንም መፍትሔ መመለሳቸውን ነዋሪዎቹ በሀዘን መናገራቸው ተጠቁሟል። አሁንም ነዋሪው የመንግስት ያለህ፣ያገር ያለህ እያለ ተማፅኖውን እያሰማ እንደሚገኝ የጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም.የኢሳት ዘገባ አመልክቷል።

በተከሳሽ የፓርቲ አመራሮችና በአቃቂ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መካከል ያለው አቤቱታ ምላሽ አላገኘም

∙በቃል የቀረበው አቤቱታ ከድምጽ ክምችት ክፍል ጠፍቷል ተብሏል

politician prisoners

በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች እና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ ያሉ የሽብር ተከሳሾች በቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር መካከል ያለው አቤቱታ እስካሁን እልባት ሊያገኝ አልቻለም፡፡

ዛሬ ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች ማረሚያ ቤቱ የመብት ጥሰት እየፈጸመባቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አቤት ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዛሬ ዕለት በጉዳዩ ላይ የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪ ችሎት ቀርበው መልስ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ቀጠሮ ወቅት አቤቱታው በቃል ተሰምቶ በመቅረጸ ድምጽ ተቀድቶ እንደገና በጽሑፍ ተገልብጦ ከመልስ ጋር እንዲቀርብ ታዝዞ የነበር ቢሆንም ድምጹ ከፍርድ በቱ ድምጽ ክምችት ክፍል ሊገኝ ስላልቻለ በወረቀት ተገልብጦ መልስ እንዲሰጥበት ለማረሚያ ቤቱ አለመድረሱ ተገልጹዋል፡፡

በዚህ የተነሳም ፍርድ ቤቱ ለጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ችሎት ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ለማስቻል፣ በቀጣዩቹ ቀናት ውስጥ አቤቱታው እንደገና በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ እንዲቀርብ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ኦኬሎ አኳይ

 አቶ ኦኬሎ አኳይ

በተመሳሳይ በቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦኬሎ አኳይ የክስ መዝገብ በተከሰሱ ሰዎች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የሰጡት ምስክርነት ከድምጽ ክምችት ክፍል ስለጠፋ እንደገና በሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ድጋሜ ምስክሮቹ እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ ደህንነቱ አደጋ ላይ መሆኑ ተገለፀ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶበት የሶስት ዓመት እስር የተፈረደበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ደህንነቱ አደጋ ላይ መሆኑ የቅርብ ቤተሰቦቹ ገለፁ፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን፣ በዝዋይ ወህኒ ቤት ኮማንደር ቢኒያም ተብሎ በሚጠራው የወህኒ ቤቱ አስተዳዳሪ ጠዋትና ማታ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰበት እንደሚገኝና በተጨማሪነትም በቀን ለአምስት ጊዜ ያህል ሌሊትን ጨምሮ በሰበብ አስባቡ ከክፍሉ እየተጠራ እንደሚወሰድ የቅርብ ቤተሰቦቹ አስታውቀዋል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን፣ በኮማንደር ቢኒያም እየተጠራ “እንገልሃለን፣ ከዚህ አንተ ሳይሆን ሬሳህ ነው የሚወጣው” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰበት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ዛቻው እና ማስፈራሪያው እየደረሰበት የሚገኘው በቅርቡ ለንባብ ባበቃው “የኢትዮጵያ መንግስት ገመና” በሚለው መጣጥፉ እንደሆነ የቅርብ ቤተሰቦቹ አያይዘው ገልፀዋል፡፡ ከያዝነው ሳምንት ጀምሮም ምግብ እንዳይገባለትም ሆነ በቤተሰብ፣ በወዳጅ እና በስራ በባልደረቦቹ እንዳይጎበኝ መደረጉን ፍኖተ ነፃነት ዘግቧል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን፣ ፍትህ ጋዜጣ ላይ በፃፋቸው ፅሁፎች የተነሳ የሶስት ዓመት እስር ተፈርዶበት ከጥቅምት ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡