ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የምስክርነት ቃሉን ሰጠ
*”የህሊና እስረኛ ነኝ” እስክንድር ነጋ

በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ 18 ዓመት እስር ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የመከላከያ ምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል፡፡
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ አንደኛ ተከሳሽ ለሆነው አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ መከላከያ ምስክር ሆኖ ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ከእስር ቤት የቀረበው ጋዜጠኛ እስክንድር ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም ምስክርነቱን ሊያሰማ ችሏል፡፡
ያለጠበቃ በግሉ የሚከራከረው ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ጋዜጠኛ እስክንድር እንዲያስረዳለት የሚፈልገው ጭብጥ ጡመራ ምንድነው፣ ከወንጀል ጋርስ ግንኙነት አለው ወይ፣ እና ሰብዓዊ መብት እና ዴሞክራሲ ላይ ስልጠና ስለሚሰጡ ድርጅቶችና የስልጠናው ይዘትን በተመለከተ እንደሆነ ቢያስታውቅም በጭብጡ ላይ አቃቤ ህግ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ በዚህም አቃቤ ህግ ጡመራ ምንድነው፣ ወንጀልስ ነው ወይ የሚለው በምስክር ሳይሆን በህግ ድንጋጌዎች የሚረጋገጥ እንደሆነ በመግለጽ ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከሰማ በኋላ ጡመራ ወንጀል ስለመሆን አለመሆኑ የተያዘውን ጭብጥ ውድቅ በማድረግ ስለ ስልጠናውና አሰልጣኝ ተቋማት የተመዘገበው ጭብጥ ላይ ምስክሩ እንዲመሰክሩ ብይን ሰጥቷል፡፡
ብይኑን ተከትሎ ምስክሩ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ችሎት ፊት የቀረበ ሲሆን በመጀመሪያ በፍርድ ቤቱ የቀረቡለትን ጥያቄዎች መልሷል፡፡ ምስክሩ ሙሉ ስሙን፣ እድሜውን፣ ስራውንና ለምን እንደመጣ፣ እንዲሁም ከተከሳሾች ጋር ስለመተዋወቁ ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል፡፡ እስክንድር ‹‹ስራ›› ተብሎ ሲጠየቅ፣ ‹‹ጋዜጠኛ ነበርኩ›› ብሏል፡፡ ‹‹አሁንስ›› የሚል ጥያቄ ፍርድ ቤቱ አቅርቦለት፣ ‹‹አሁን የህሊና እስረኛ ነኝ›› ሲል መልሷል፡፡
ተከሳሹ ዘላለም ወርቃገኘሁ በዋና ጥያቄ ተከሳሹ ውጭ ሀገር ሊወስደው ነበር ተብሎ በክሱ ላይ ስለተጠቀሰው ስልጠና ምስክሩ እንዲያብራሩለት ጠይቋል፡፡ ምስክሩም ‹‹ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትንም የሚያሳትፍ ስልጠና በሰብዓዊ መብት፣ በሚዲያ ‹ኢቲክስ›፣ እና በዴሞክራሲ ላይ ይሰጣሉ፡፡ ድርጅቶቹ የተለያዩ ቢሆንም በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ መርሃቸው ተመሳሳይና ዓለም አቀፍ ነው›› በማለት መስክሯል፡፡
ድርጅቶቹን በስም መጥቀስና የሚገኙበትንም ሀገር ለፍርድ ቤቱ መግልጽ ይቻል እንደሆነ ምስክሩ ተጠይቆ ‹‹የተቋማቱ መገኛ ምዕራቡ ዓለም ነው፡፡ በዴሞክራሲ የዳበሩ ሀገራት ነው ዋና መቀመጫቸው፡፡ ሲ.ፒጄ፣ ፍሪደም ሀውስ፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል እና አርቲክል 19 የመሳሰሉትንም በስም መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኔም ከነዚህ ተቋምት ውስጥ በአንዱ የተሰጠ ስልጠና አዲስ አበባ ላይ ተካፍየ ነበር፡፡ ስልጠናው ስለ ሰብዓዊ መብት፣ ስለ ሚዲያ፣ ስለ ዴሞክራሲ የሚያስተምር ነው፡፡ ስልጠናው ከሽብር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ ይህ እንደማስረጃ መቅረቡ ኢትዮጵያን ትዝብት ውስጥ የሚከትና የሚያሳዝን ነው›› ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መቼ እንደታሰረ በመስቀለኛ ጥያቄ ተጠይቆ ‹‹መስከረም 2004 የሀሰት ክስ ቀርቦብኝ፣ በግፍ ተፈርዶብኝ ታስሬ እገኛለሁ›› ሲል መልሷል፡፡ እስክንድር ነጋ ጥቁር ሱፍ በደብዛዛ ሸሚዝ ለብሶ፣ ሙሉ ጥቁር መነጸር አድርጎና ነጠላ ጫማ ተጫምቶ ችሎት ፊት ቀርቧል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ምስክሩ ምስክርነቱን ማጠቃለሉን ተከትሎ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡለት የጠራቸው ሌላኛው ምስክር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በተደጋጋሚ እንዲቀርቡለት ትዕዛዝ እንዲሰጥለት የጠየቀ ቢሆንም እስካሁን አለመቅረባቸው መንግስት ግለሰቡን ለማቅረብ ፍላጎት እንደሌለው ያሳያል ሲል ቅሬታውን አሰምቷል፡፡ ‹‹አሁን የተረዳሁት ነገር ከሳሼ የሆነው መንግስት አቶ አንዳርጋቸውን ከሚያቀርብ እኔን በነጻ መልቀቅ እንደሚቀለው ነው›› ብሏል ተከሳሹ፡፡
ተከሳሹ ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንደተገናኜ አቃቤ ህግ መጥቀሱን በማስታወስ ምስክሩ መቅረባቸው ያለውን ተገቢነት አስረድቷል፡፡ ‹‹ምስክሩ እንዲቀርቡልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ፍርድ ቤቱ ከምስክሩ ጋር በተገናኘ ያለውን የክሱ ፍሬ ነገር አውጥቶ በቀሪው ላይ ብይን ይስጥልኝ›› ብሏል ተከሳሹ አቶ ዘላለም፡፡
ፍርድ ቤቱም ምስክሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት ምስክርነታቸውን ለመስማት በሚል ለየካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ኢትዮጵያ
በጋምቤላ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ40 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተሰማ
ባለፈው ሳምንት ጥር 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል በተከሰተው የብሔር ግጭት ከ40 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተሰምቷል፡፡ የግጭቱ መንስኤ እስካሁን በገለልተኛ አካል ባይታወቅም ግጭቱ በክልሉ ነዋሪ በሆኑ አኝዋክና ኑዌር ማኀበረሰብ መካከል በተፈጠረ ግጭት እንደሆነ ይነገራል፡፡

የማዕከላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩሉ የሟቾች ቁጥር 14 ነው ግጭቱም በቁጥጥር ስር ውሏል ቢሉም፤ የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ኢታንግ ወረዳ አስተዳደር አቶ ኦኬሎ ኦባንግ በበኩላቸው ብዙ ሰዎች እንደሞት እንደሚነገርና በአሁን ወቅት የሟቾችን ቁጥር በርግጠኝነት መግለፅ እንደማይቻል ለብሉንበርግ ተናግረዋል፡፡
ለግጭቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሎ የተገመተው በአካባቢው የደደቡብ ሱዳን አማፂ መሪ ሬክ ማቻር ደጋፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ከ264 ሺህ በላይ የኑዌር ጎሳዎች በክልሉ ኢታንግ ወረዳ መስፈራቸውና በአካባቢው ማኀበራዊ መስተጋብር ላይ ተፅዕኖው እየበረታ ነው በሚል እንደሆነም ቢነገርም ከመንግሥትም ሆነ ከዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት ስደተኞቹ አሳድረዋል ስለተባለው ተፅዕኖ የተገለፀ ነገር የለም፡፡
የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች እና በማኀበረሰቡ መካከልም አለመግባባቶች እንደተፈጠሩ በዚህም በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውን እና የመኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
ከግጭቱ ጋ በተያያዘም በርካታ ሰዎች በክልሉ ዋና ከተማ ጋምቤላ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውንና ጉዳት የደረሰባቸው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
እነ ጌታቸው ሽፈራው ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው
*”ከቤተሰቦቻችን ጋር እንዳንገናኝ ተደርገናል” ተጠርጣሪዎች
*”6 ቀን ደንበኛየን ለማግኘት ተመላልሼ ተከልክያለሁ” የጋዜጠኛ ጌታቸው ጠበቃ አምሃ መኮንን

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከታህሳስ 15/2008 ዓ.ም ጀምሮ በማዕካለዊ ወንጀል ምርመራ በእስር ላይ የሚገኙት እነ ጌታቸው ሺፈራው ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በእነ ዳንኤል ተስፋየ ስም በተከፈተው የምርመራ መዝገብ ስር የተካተቱት ሦስት ተጠርጣሪዎች አቶ ዳንኤል ተስፋየ፣ አቶ ሸዋታጠቅ ኃ/መስቀል እና ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ሲሆኑ፣ ተጠርጣሪዎች ዛሬ ጥር 14/2008 ዓ.ም ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ቀርበው ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ብሎ ጠይቆ የ27 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋ፡፡
ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ የጠየቀበትን ምክንያት ለፍርድ ቤት ያስረዳ ሲሆን ‹‹የቴክኒክ ማስረጃዎችን ከብሄራዊ ደህንነትና መረጃ ኤጀንሲ ጠይቀን ማስመጣትና ተጨማሪ ግብረ አበሮችን መያዝ ይቀረናል›› ብሏል፡፡
ተጠርጣሪዎች ከተያዙበት ቀን ጀምሮ በማንም እንዳይጎበኙ መከልከላቸውን በማስረዳት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ‹‹ከተያዝኩ ጀምሮ ቤተሰቦቼን አይቼ አላውቅም፡፡ እስር ላይ ሆኜ በቀን ለ10 ወይም 15 ደቂቃዎች ነው የጸሐይ ብርሃን የማገኘው፤ ይሄ እንዲስተካከልልኝ ፍርድ ቤቱን እጠይቃለሁ›› ሲል ያመለከተ ሲሆን፣ አቶ ሸዋታጠቅ ኃ/መስቀል በበኩሉ፣ ‹‹ቤተሰቦቼን ያየኋቸው ዛሬ ችሎት ስመጣ ከርቀት ነው፤ ቤተሰቦቼን እንዳይ ይፈቀድልኝ›› በማለት እያነባ ጠይቋል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ደግሞ በጠበቃው በኩል ያለውን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል፡፡ ጠበቃው አቶ አምሃ መኮንን ለስድስት ቀናት ማዕከላዊ ደንበኛቸውን ለማነጋገር ቢመላለሱም ከበር ላይ እንዲመለሱ በመደረጋቸው ከደንበኛቸው ጋር ሳይነጋገሩ ፍርድ ቤት መቅረባቸው አግባብ አለመሆኑንና ድርጊቱ ህገ-መንግስቱን የሚጣረስ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹‹ደንበኛየን ያገኘሁት አሁን ነው፡፡ ደንበኛየ የምንፈልገውን ነገር ሳናገኝ ከጠበቃህ ጋር አናገናኝህም ተብሏል፡፡ ይህ በህገ-መንግስቱ የተሰጠውን መብት የጣሰ ተግባር ነው፡፡ አሁንም ደንበኛየ፣ ከዚህ በኋላ እኔን ሳያነጋግር ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ፍርድ ቤቱ እንዲመዘግብልኝ እፈልጋለሁ›› ሲሉ ጠበቃ አምሃ መኮንን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው እስካሁን በቤተሰብም ሆነ በጓደኞቹም እንዳይጠየቅ መከልከሉ የህግ አግባብ የሌለው የመብት ጥሰት ነው ብለዋል ጠበቃ አምሃ፡፡
ጠበቃ አምሃ ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ የጠየቀበት ምክንያት ደንበኛቸው የዋስትና መብቱ ተከብሮለት ሊከናወን እንደሚችል በማስረዳት የዋስትና መብት እንዲከበርለት ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን በሁሉም ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ለየካቲት 11/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከሦስት ወራት በላይ በማዕከላዊ በእስር ላይ የሚገኙት በጋሞ ጎፋ አርባምንጭ የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪዎች እነ ሉሉ መሰለ እና አየለች አበበ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ‹የመጨረሻ› ነው የተባለለትን ተጨማሪ የ28 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ኢትዮጵያ
በኦሮሚያ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው፤ በመንግሥት የኃይል እርምጃ የተገደሉ ዜጎች ቁጥርም ከ140 በላይ ደርሷል
በኦሮሚያ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ አሁንም በተለያዩ ከተሞች እንደቀጠለ ነው፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶች ተዝግተዋል፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉት ዜጎች ቁጥር ከ140 በላይ መድረሱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ ከሰላማዊ ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ ከተሳተፉት እና በቤታቸው እንዲሁም በመንገድ ላይ ሲጓዙ የተገደሉትን 140 ዜጎችን ጨምሮ ከ350 በላይ ሰዎች ሲቆስሉ ከ4 ሺህ በላይ ዜጎች በእስር ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በተለይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በጅምላ እየወሰዱት ባለው እስር በድጋሚ የታሰሩት የኦፌኮ/መድረክ አመራር አቶ በቀለ ገርባ ልጅ የሆነው እና በአዳማ ዩኒቨርስቲ የ5ኛ ዓመት የህግ ተማሪ የሆነው ናዖል በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ ተማሪዎች ከሚማሩበት የትምህርት ተቋም ተይዘው መታሰራቸውም ተሰምቷል፡፡
ህዝባዊ ተቃውሞው አሁንም በተለያዩ ከተሞች በተለይም በምዕራብ ኢትዮጵያ በወለጋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል በምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ፣ በአርሲ ፣ በምስራቅ ሸዋ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች እንደቀጠለ ነው፡፡ በመንግሥት የሚገደሉ፣ የሚታሰሩና የሚጎዱ ዜጎችም ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
የኦፌኮ/መድረክ ዋና ፀሐፊ አቶ በቀለ ነጋዓ እስካሁን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከደረሰባቸው ተደጋጋሚ ማስፈራሪያና ዛቻ በኋላ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ የተንቀሳቃሽ ስልካቸው ተነጥቆ ፣ ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡ ተደርጎ እስካሁንም በቁም እስር ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ህዝባዊው ተቃውሞ ባለፈው ህዳር 2008 ዓ.ም. አዲሱን የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ትግበራን በመቃወም መጀመሩ ይታወሳል፡፡
መንግሥት በበኩሉ ለተቃውሞ የወጡትን ፀረ-ህዝብ፣ ፀረ-ሰላም፣ አሸባሪዎች ብሎ መወንጀሉን እና ህዝባዊው ተቃውሞውን በቁጥጥር ስር አውየዋለሁ በሚል ተደጋጋሚ መግለጫ ቢሰጥም፤ ተቃውሞው በያዝነው ሳምንት በተለያዩ የሀገሪቱ ኦሮሚያ ክልሎች ተጠናክሮ መቀጠሉ የታወቀ ሲሆን፤ በተለይ በሐረርጌ አካባቢ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ እና ሐረር የሚወስዱ ዋና መንገዶች በተቃውሞው ተዘግተው እንደነበር ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
እነ ሀብታሙ አያሌው ለጥር 10 ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል
አቃቤ ህግ በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብርተኝነት ክስ መስርቶባቸው በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ተበይኖላቸው አቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቆባቸው ጉዳያቸውን በእስር ላይ ሆነው እየተከታተሉ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በድጋሜ ለጥር 10 ቀን 2008 ዓ.ም ተቀጥረዋል፡፡

ዛሬ ታህሳስ 29 ቀን 2008 ዓ.ም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በእነ ሀብታሙ አያሌው ላይ የተጠየቀው ይግባኝ ላይ ብይን ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም ዳኛ ዳኜ መላኩ ‹‹የምንመረምረው ነገር አለ›› በሚል ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡
ይግባኝ የተጠየቀባቸው ተከሳሾች ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሺ እና አብርሃም ሰለሞን ሲሆን፣ ሁሉም ተከሳሾች ነሀሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በስር ፍርድ ቤት ነፃ ቢባሉም እስካሁን በእስር ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
ምንጭ፡ ነገረ ኢትዮጵያ