አንድነት እና መኢአድ የፊታችን ሐሙስ ውህደት ሊፈራረሙ ነው
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ነገ ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ቅድመ ውህደት ሊፈራረሙ ነው፡፡ ፓርቲዎቹ እስካሁን በተናጠል የሚደረገው ፖለቲካ ትግል ለሀገሪቱም ሆነ ለህዝቧ እንዲሁም ለራሳቸው አዋጭ አለመሆኑን በማመን ተዋህደው አንድ ጠንካራ የፖለቲካ ማኀበር መስርቶ ለመታገል የሚያስችላቸውን ስምምነት በመጨረስ ቅድመ ውህደቱን ለመፈራረም ቀነ ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ዋናው የውህደት ስምምነት የሚጠናቀቀው የሁለቱም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ ተደርጎ ሲፀድቅ ሲሆን፤ከዚህ ቀደም የሁለቱም ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ውህደቱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ውሳኔ ማሳለፋቸው አይዘነጋም፡፡ በዚህም ምክንያት ስምምነቱ ተጠናቆ የፊታችን ሐሙስ ድርድሩን ሲያካሂዱ የነበሩት አካላትና የሁለቱም ፓርቲ አመራሮች በተገኙበት የአንድነት ፓርቲ ፕሬዘዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው እና የመኢአድ ፕሬዘዳንት አቶ አበባው መሐሪ ፓርቲያቸውን በመወከል ስምምነቱን እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱም ፓርቲዎች የፕሮግራም ልዩነት እንደሌላቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለይ አንድነት ፓርቲ ከዚህ ቀደም ከብርሃን ፓርቲ ጋር በመዋሃድ በፖለቲካው እንቅስቃሴ ለውጥ መፍጠር ችሏል፡፡ አሁን ደግሞ ከመኢአድ ጋር በመዋሃድ ጠንካራ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡ የውስጥ አዋቂ ምንጮች እንዳረጋገጡት ከሆነ አንድነት ከመኢአድ በተጨማሪ ከሌሎችም ፓርቲዎች ጋር ውህደት ለመፍጠር አንድ ግብረኃይል በማቋቋም ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑንና በቅርቡም ሌሎች ፓርቲዎችም አብረውት ሊዋሃዱ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ አንድነት ከመድረክ አባል ፓርቲዎች ጋር በግንባር ተጣምሮ እስካሁን ቢቆይም በአባላቱ የሚጠበቀው ለውጥ ባለመምጣቱ ውህደት ላይ ማተኮሩ ይነገራል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚመለክተው ከሆነ፤ በአሁን ወቅት ተመዝግበው የእውቅና ሰርተፍኬት የተሰጣቸው 66 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከአራት ፓርቲዎች ውጭ ሌሎቹ ከምርጫ ወቅት በስተቀር የት እንዳሉና ምን እየሰሩ እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ህዝቡ በተለያየ ጊዜ በጥቂቱም ቢሆን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ከተናጥል ይልቅ አንድ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ሆነው እንዲቀርቡ በተደጋጋሚ መጠየቁ ይታወሳል፡፡
በጉጂ ዞን ያለው ውጥረት እስካሁንም አለመብረዱ ተገለፀ
በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል በሚገኘው ጉጂ ዞን ባለፈው መጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. በኦዶ ሻኪሶ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና ከዞኑ ከተማ መስተዳደር ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ሁለት ወጣቶች በፌደራል ፖሊስ መገደላቸውን ተከትሎ የፈጠረው ውጥረት እስካሁንም አለመብረዱ ተገለፀ፡፡ እንደምንጮች ገለፃ ከሆነ የ9ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ብስራት ኃይሌ እና በግብርና ሙያ የሚተዳደረው ወጣት ሀለቄ ሮባ በከተማው የዕለት ስራውን ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ ሳለ በፌደራል ፖሊስ በተወሰደ የጥይት ተኩስ እርምጃ ወዲያው ህይወታቸው አልፏል፡፡
በፌደራል ፖሊስ ተገደሉ ከተባሉት ተማሪዎች በተጨማሪ በከተማው ማንነቱ ባልታወቀ አካል በተተኮሰ ጥይት አንድ የፌደራል ፖሊስ ላይ ከፍተኛ አደጋ በመድረሱ ወዲያው ወደ አዲስ አበባ ለህክምና መላኩን እና በከተማውም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሌሎች ነዋሪዎች ላይ በፖሊስ በተወሰደ የኃይል እርምጃ ቆስለው በከተማው ሆስፒታል ህክምና እርዳታ ያገኙም እንዳሉበት የአዲስሚያ ምንጮች ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በጉጂ ዞን ባሉ 15 ወረዳዎች እና በሶስቱ ከተማ መስተዳደሮች ነጌሌ ቦረና፣ ክብረ መንግስትና ኦዶሻኪሶ በነዋሪውና በመንግስት ኃላፊዎች መካከልበተፈጠረ አለመግባባት እስካሁን ውጥረቱ አለመርገቡ እና ችግሩ በዞኑ ባሉ ገጠሮች ድረስ መዛመቱም ተጠቁሟል፡፡ የግጭቱ መንስኤም ተማሪዎቹ ለአስተዳዳሪዎቹ ባነሱት የመጠጥ ውሃ፣ የመብራትና ተያያዥ የመብት ጥያቄዎች መሆኑንም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በዚህ ዙሪያ የመንግስት ኃላፊዎች እስካሁን ምንም የሰጡት ማስተባበያም ሆነ መልስ ባይኖርም፤ በወጣቶቹ መገደል በተፈጠረው ውጥረት የአካባቢው የመንግስት ሹማምንት ዛሬ እሁድ መጋቢት 7 ቀን 2006 ኣ.ም. ከጠዋቱ 3 ሰዓት በጉጂ ዞን አንድነት ፓርቲ የገንዘብና ንብረት ክፍል ኃላፊ የሆኑትን አቶ ዮሐንስ ኢብሶን ተማሪዎቹ ላነሱት ጥያቄ ምክንያት ናቸው በማለት መንግስት ማሰሩ የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡
በኦሮሚያ ሻኪሶ ሁለት ተማሪዎች በፌደራል ፖሊስ በመገደላቸው ውጥረት መንገሱ ተሰማ
በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል በሚገኘው ጉጂዞን ኦዶ ሻኪሶ ከተማ በተማሪዎችና በከተማው አስተዳደር መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የፌደራል ፖሊስ ጣልቃ በመግባት በወሰደው የኃይል እርምጃ አንዲት ሴት እና አንድ ወንድ በአጠቃላይ ሁለት ተማሪዎች ህይወት በማለፉ እና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በመቁሰላቸው የኦዶ ሻኪሶ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ተጠቁሟል፡፡ 
የግጭቱ መንስኤ ተማሪዎቹ “በከተማውና አካባቢው የመጠጥ ውሃ አገልግሎት የለም፣ አንድ ባለ 25 ሊትር ጀርካን ውሃ በ 7 ብር እየተሸጠ ነው፣ በቂ የመብራት አገልግሎትም የለም፣ ከህዝቡ ሚሰበሰበው ግብር እና ከመንግስት የሚመደበው በጀት እስካሁን ምን ላይ እየዋለ ነው? ህብረተሰቡም እኛ ምበውሃጥም እየተጎዳን አስተዳደሩ እስከዛሬ ለምን ዝም አለ?” የሚሉ ጥያቄዎች በመነሳታቸው፤ የአስተዳደር አካላት ተማሪዎቹን “እናንተ ምን አገባችሁ፣ አርፋችሁ ተማሩ፤ካልሆነ እርምጃ እንወስዳለን” የሚልምላሽ በመሰጠቱ ተማሪዎችን እንዳስቆጣ የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የፌደራል ፖሊስ ድንገት ጣልቃ በመግባት ተቃውሞ በሚያሰሙ ተማሪዎች ላይ እርምጃ በመውሰዱ የከተማው ነዋሪዎችም ተቃውሞውን መቀላቀላቸው የአዲስሚዲያ ምንጮች ከስፍራው ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የከተማውና የአካባቢው ነዋሪ ከፌደራል ፖሊስ ጋር መፋጠጡን፣ ይህ እስከተዘገበበት ሰዓት ድረስም በከተማው የጦር መሳሪያ ተኩስ ሁሉ እየተሰማ መሆኑንም ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሟቾቹ ሁለቱ ተማሪዎች አስከሬን በሆስፒታል እንደሚገኝ እና ወላጆችም ወደሆሲፒታሉ እንዳይገቡ በፌደራል ፖሊስ መከልከላቸው እንዲሁም በከተማው ተወስኖ የነበረው ቁጣም ወደ ገጠሩ ነዋሪበ መስፋፋት በርካቶች በቁጣወደ ከተማው እየገቡ መሆኑንም ምንጮች አስረድተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በከተማው ከፍተኛው ጥረት መንገሱም ተጠቁሟል፡፡
እንደምንጮች ገለፃ ከሆነ ችግሩ የተፈጠረው የኦዶ ሻኪሶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው አስተዳደሩ ጥያቄያቸውን በቀጥታ ወደ ፖለቲካ በመቀየር የፌደራል ፖሊስ ተጠርቶ በቀጥታ የኃይል እርምጃ በመውሰዱ የሁለት ተማሪዎች ህይወት ወዲያው በማለፉ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ በአሁን ሰዓትም በከተማው በተለያዩ ቦታዎች የእሳት ቃጠሎ፣ የህንፃዎች መስታወት መሰባበር፣ ሌሎች ንብረቶች እየወደሙ መሆናቸውን እንዲሁም ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ እየተሰማ መሆኑንም ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ አዲስሚዲያ ይህንን ለማጣራት የኦሮሚያ ፖሊስ አዛዥ ናቸው ወደተባሉት ኮማንደር አበበ እና የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዳ ሮቤ ጋር ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረገም ለጊዜው አልተሳካም፡፡ ኦዶ ሻኪሶ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የወርቅ ማዕድን ከሚመረትባቸው አካባቢዎች ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡
መኢአድና አንድነት በባህርዳር ከተማ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጠሩ
ዛሬ የካቲት 6 ቀን 2006 ዓ.ም. በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት መኢአድና አንድነት በጋራ ሰላማዊ ሰልፍ ጠሩ፡፡ ፓርቲዎቹ ሰላማዊ ሰልፉን የጠሩት የፊታችን ካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. በባህርዳር ከተማ ሲሆን ፤ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ባለፈው የብአዴን/ኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርና ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን አማራን ህዝብ በማጥላላት ስድበ አዘል ንግግር ማድረጋቸውን በመቃወም ነው፡፡
ፓርቲዎቹ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከሆነ አቶ አለምነው መኮንን የሚባሉት የብአዴን/ኢህአዴግ አመራር ህዝብን በመዝለፍና በማዋረድ በይፋ ህግ የጣሱ ቢሆኑም እስካሁን ፓርቲያቸውም ሆነ እራሳቸው ህዝቡን ይቅርታ አልጠየቁም፡፡ ይህም የሚያሳየው ለህዝብ ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ በመሆኑ ለፍርድ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ ይገባል፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የፊታችን የካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ከተጠራው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በተጨማሪ በሌሎችም የሀገራችን ከተሞች የተቃውሞ ሰልፉ ይቀጥላል፣ ህዝብን እየናቁ ህዝብን ማስተዳደርም ሆነ መምራት አይቻልም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
በመግለጫው እንደተገለፀው የሰልፍ ማሳወቂያው ደብዳቤ በሁለቱም ፓርቲዎች ለሚመለከተው የባህርዳር ከተማ መስተዳደር ገቢ መደረጉምን ገልፀዋል፡፡ የባህርዳርና አካባቢው ህዝብም በነቂስ በመውጣት በተቃውሞ ሰልፉ ላይ እንዲገኝ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዛሬ ታሰሩ
የአንድነትለዲሞክራሲናለፍትህፓርቲ(አንድነት)ብሔራዊምክርቤትአባልየሆኑት እና ለረጅም ጊዜ ፓርቲውን በዋና ፀሐፊነት ያገለገሉት አቶአስራትጣሴ ዛሬ ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ታሰሩ፡፡አቶ አስራትበክስሂደትላይየነበረውየአኬልዳማዶክመንተሪበድጋሚበኢትዮጵያቴሌቪዥንመታየቱንተከትሎበአዲስጉዳይመጽሔትላይከፃፉትአስተያየትጋርበተያያዘ “ዘለፋአዘልጽሑፍ” ፅፈዋልበሚልፍርድቤትቀርበውእንዲያስረዱትዕዛዝበተላለፈባቸውመሰረት ዛሬ ችሎት ተገኝተው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የፌደራልመጀመሪያፍርድቤት ለቀጣይ 7 ቀንከታሰሩ በኋላ በድጋሚእንዲቀርቡበማለትየእስርትዕዛዝሰጥቶባቸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራን ጨምሮ ሌሎች አራት ወጣት አመራሮች ኢህአዴግ ለማሰር መዘጋጀቱም መጠቆሙን በፍኖተ ነፃነት ተዘግቧል፡፡