በተከሳሽ የፓርቲ አመራሮችና በአቃቂ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መካከል ያለው አቤቱታ ምላሽ አላገኘም
∙በቃል የቀረበው አቤቱታ ከድምጽ ክምችት ክፍል ጠፍቷል ተብሏል
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች እና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ ያሉ የሽብር ተከሳሾች በቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር መካከል ያለው አቤቱታ እስካሁን እልባት ሊያገኝ አልቻለም፡፡
ዛሬ ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች ማረሚያ ቤቱ የመብት ጥሰት እየፈጸመባቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አቤት ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዛሬ ዕለት በጉዳዩ ላይ የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪ ችሎት ቀርበው መልስ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ቀጠሮ ወቅት አቤቱታው በቃል ተሰምቶ በመቅረጸ ድምጽ ተቀድቶ እንደገና በጽሑፍ ተገልብጦ ከመልስ ጋር እንዲቀርብ ታዝዞ የነበር ቢሆንም ድምጹ ከፍርድ በቱ ድምጽ ክምችት ክፍል ሊገኝ ስላልቻለ በወረቀት ተገልብጦ መልስ እንዲሰጥበት ለማረሚያ ቤቱ አለመድረሱ ተገልጹዋል፡፡
በዚህ የተነሳም ፍርድ ቤቱ ለጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ችሎት ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ለማስቻል፣ በቀጣዩቹ ቀናት ውስጥ አቤቱታው እንደገና በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ እንዲቀርብ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ በቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦኬሎ አኳይ የክስ መዝገብ በተከሰሱ ሰዎች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የሰጡት ምስክርነት ከድምጽ ክምችት ክፍል ስለጠፋ እንደገና በሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ድጋሜ ምስክሮቹ እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ ደህንነቱ አደጋ ላይ መሆኑ ተገለፀ
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶበት የሶስት ዓመት እስር የተፈረደበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ደህንነቱ አደጋ ላይ መሆኑ የቅርብ ቤተሰቦቹ ገለፁ፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን፣ በዝዋይ ወህኒ ቤት ኮማንደር ቢኒያም ተብሎ በሚጠራው የወህኒ ቤቱ አስተዳዳሪ ጠዋትና ማታ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰበት እንደሚገኝና በተጨማሪነትም በቀን ለአምስት ጊዜ ያህል ሌሊትን ጨምሮ በሰበብ አስባቡ ከክፍሉ እየተጠራ እንደሚወሰድ የቅርብ ቤተሰቦቹ አስታውቀዋል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን፣ በኮማንደር ቢኒያም እየተጠራ “እንገልሃለን፣ ከዚህ አንተ ሳይሆን ሬሳህ ነው የሚወጣው” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰበት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ዛቻው እና ማስፈራሪያው እየደረሰበት የሚገኘው በቅርቡ ለንባብ ባበቃው “የኢትዮጵያ መንግስት ገመና” በሚለው መጣጥፉ እንደሆነ የቅርብ ቤተሰቦቹ አያይዘው ገልፀዋል፡፡ ከያዝነው ሳምንት ጀምሮም ምግብ እንዳይገባለትም ሆነ በቤተሰብ፣ በወዳጅ እና በስራ በባልደረቦቹ እንዳይጎበኝ መደረጉን ፍኖተ ነፃነት ዘግቧል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን፣ ፍትህ ጋዜጣ ላይ በፃፋቸው ፅሁፎች የተነሳ የሶስት ዓመት እስር ተፈርዶበት ከጥቅምት ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
ምርጫ ቦርድ በሶስቱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ
ዛሬ ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በአንድነት፣ በመኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲዎች ላይ ውሳሳለፉን አስታውቋል፡፡ ቦርዱ ውሳኔ ብሎ ያስተላለፈው ፤ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የውስጥ ችግራቸውን መፍታት አልቻሉም በሚል ለዛሬው ውሳኔ እሰጣለሁ ብሎ የነበረው ምርጫ ቦርድ ሁለቱ ፓርቲዎች በሁለት ሳምንት ውስጥ የውስጥ ችግራቸውን ፈትተው ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ የመጨረሻ ጊዜ ሰጥቻቸዋለሁ ሲል ገልጾአል፡፡
ቦርዱ ዛሬ ከሰዓት በሰጠው መግለጫ በአንድነትና መኢአድ ስም የተለያዩ ጉባኤዎች በመደረጋቸው ሁለቱ ፓርቲዎች ጥር 3 ያደረጉትን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አለመገኘቱን፣ አንድነት የ2004 ዓ.ም እንዲሁም የመኢአድን የ2001 ዓ.ም ደንብን እንጅ ከዛ በኋላ ያሉትን የፓርቲውን ደንቦች እንደማያውቅ በመግለጽ በሁለት ሳምንት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ችግራቸውን እንዲፈቱ የመጨረሻ ጊዜ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡
በሌላ በኩል መድረክ ረግጦ በመውጣት፣ ሌሎች ፓርቲዎች እንዲያድሙ በማድረግ፣ ቦርዱ የማያውቀው ትብብር በመመስረት በሚል በምርጫ ቦርድ ክስ የቀረበበትና ይቅርታ እንደማይጠይቅ በደብዳቤ ለገለጸው ሰማያዊ ፓርቲ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡ ማስጠንቀቂያውን የማያከብር ከሆነም ቦርዱ ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል፡፡
የቦርዱ ባለስልጣናት ‹‹ሰማያዊ ፓርቲን ህገ ወጥ ትብብር በመመስረት ስትከሱ ሌሎቹን የትብብሩን አባል ፓርቲዎች ለምን አልከሰሳችሁም?›› በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹ፓርቲዎቹ 9 መሆናቸውን የሰማሁት አሁን ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ‹‹እስካሁን ሌሎች ትብብሮችን ምርጫ ቦርድ አያውቃቸውም ብላችሁ ከሳችሁ አታውቁም›› በሚል የ9ኙን ፓርቲዎች ትብብር ህገ ወጥ ነው ካሉ ገዠው ፓርቲ ከአጋሮቹ ጋር ያለውን ግንኙነትን ለምን ህገ ወጥ ነው እንደማይሉ ለቀረበላቸው ጥያቄም ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹ኢህአዴግ እንደገዥ ፓርቲ አጋር ፓርቲዎች ሊኖሩት ይቻላል፡፡ እንደ ገዥ ፓርቲ ከአጋሮች ጋር መስራት ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮችን ቦርዱ አይመለከተውም›› ሲሉ መልሰዋል፡፡
አንድነትና መኢአድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ችግራቸውን እንዲፈቱ ተጨማሪ ጊዜ ሰጥቻለሁ ያለው ምርጫ ቦርድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ችግራቸውን ካልፈቱ ቦርዱ ተሰብስቦ ውሳኔውን አሳውቃለሁ ማለቱን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ ያመለክታል፡፡ አንድነት እና መኢአድ ምርጫ ቦርድ እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ አድርጉ ባለው መሰረት ያለፈው እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ባደረጉት ጠቅላላ ጉባኤ አንድነት ፓርቲ በድጋሚ አቶ በላይ ፈቃዱን ፕሬዘዳንት አድርጎ ሲመርጥ፤ መኢአድም እንዲሁ በተመሳሳይ ቀን ጠቅላላ ጉባዔ ያደረገ ሲሆን፤ በዕለቱ ምርጫ ቦርድ በህጉ መሰረት በሁለቱም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲገኝ የጥሪ ደብዳቤ ቢደርሰውም በሁለቱም ጉባኤ ላይ የቦርዱ ተወካይ እንዳልተገኘ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ቦርዱ አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ሁለቱም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርጉ የሁለት ሳምንት ጊዜ ሰጥቻቸዋለሁ ሲል ዛሬ በፅህፈት ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
…….
የአንድነት ፓርቲ ሁለት አባላት ድብደባ ተፈፀመባቸው
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ የሴቶች ጉዳይ ምክትል ኃላፊ ወይንሸት ስለሺ እና የፓርቲው አባል መሳይ ትኩ ባልታወቁ ሰዎች መደብደባቸው ተሰማ፡፡ ወጣት መሳይ ትኩ ባለፈው እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. አንድነት ፓርቲ የጠራውን ጠቅላላ ጉባኤውን አጠናቆ ወደ ቤቱ ሲጓዝ አዲስ አበባ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ባልታወቁ ሰዎች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመበት ፓርቲው አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የነበረችና በፓርቲው ንቁ ተሳትፎ እያደረገች የምትገኘው የሴቶች ጉዳይ ምክትል ኃላፊ ወይንሸት ስለሺ ጥር 6 ቀን 2007 ኣ.ም. ከረፋዱ 5፡30 ላይ አዲስ አበባ በተለምዶ ነፋስ ስልክ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ባልታወቁ ሁለት ሰዎች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባት የፍኖተ ነፃነት ዘገባ አመልክቷል፡፡ ወይንሸት ነፍሰጡር መሆኗንና ሆዷ ላይም ከፍተኛ ድብደባ በመፈፀሙ በአሁን ወቅት ራሷን ስታ ሆስፒታል የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ሁለቱም የፓርቲው አባላት በፓርቲው እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸው በመግለፅ፤ በተለይ ወጣት መሳይ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ አንድነት መጪውን 2007 ኣ.ም. በሚደረገው ምርጫ እንዳይሳተፍ የሚደረገውን ሴራ ቀድሞ በማጋለጡ የተወሰደበት እርምጃ እንደሆነ የፍኖተ ነፃነት ዘገባ አመልክቷል፡፡ ወይንሸትም በፓርቲው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ አስመራጭ ኮሚቴ ሆና ከማገልገሏ በተጨማሪ በፓርቲው ላይ የሚደረጉ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን በማውገዝ አስተያየት መሰንዘሯ ለተፈፀመባት ድብደባ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ የፓርቲው ልሳን መረጃ አመልክቷል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ይቅርታ እንደማይጠይቅ አስታወቀ
ሰማያዊ ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤትን እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በጽሑፍ ይቅርታ ይጠይቅ በማለት የተላለፈው ውሳኔ ከሕግ አግባብ ውጪ ስለሆነ ተቃውሞውን በመግለጽ ይቅርታ እንደማይጠይቅ አስታወቀ፡፡
የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ባለፈው ሐሙስ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቦርድን ስም አጥፍቷል ብለዋል፡፡ ‹‹በተሻሻለው የምርጫ ሕግ አንቀጽ 102 (4)ሀ፣ ለ እና ሠ እንዲሁም 102 (6) ሐ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቦርዱን ሥልጣን መቀበል፣ ሕጋዊ ትዕዛዙንና መመርያውን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ቦርዱ በሚያዘጋጃቸው የጋራ የምክክር መድረኮች ወይም ሌሎች መድረኮች ላይ ወኪል የመላክ ኃላፊነት እንዳለባቸውና በሐሰት ስም ከማጥፋት መቆጠብ እንዳለባቸው ያመለክታሉ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ግን ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት ያዘጋጃቸውን የጋራ ምክክሮች እንዲበተኑ ሙከራ አድርጓል፣ እየረገጠ ወጥቷል፣ በሐሰት ቦርዱን ወንጅሏል፡፡ እንዲሁም የስም ማጥፋት ዘመቻ አድርጓል፤›› በማለት ፓርቲው በጽሑፍ ይቅርታ እንዲጠይቅ ቦርዱ ወስኗል በማለት አስታውቀዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ውሳኔውን አስመልክቶ፣ ‹‹እኛ ይህን የምንረዳው የምርጫ ቦርድ የራሱ አቋም ሳይሆን ኢሕአዴግ በቦርዱ ውስጥ ምን ያህል ሚና እንዳለው ያጋለጠ ውሳኔ መሆኑን ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
‹‹ቀደም ባሉት ጊዜያት የሰጠነው አስተያየትና ስብሰባ ረግጠን መውጣታችን ዘለፋ መስሎ ከተሰማቸው አትዝለፉን እንነጋገር ማለት መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ይቅርታ ጠይቁኝ ብሎ ማስፈራራት አገራችንን አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ይቅርታ መቀለጃ አይደለም፡፡ እኛም በዚህ ምክንያት አናስተናግደውም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በተጨማሪም በመሠረቱ እኛ አንድ ድርጅት ነን፡፡ ምርጫ ቦርድም እንዲሁ አንድ ድርጅት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ሊግባቡ የሚችሉት ደግሞ በሕግና በደንብ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ካጠፋ ወይ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳል፣ ወይም ቦርዱ ባለው ሥልጣን ችግሩ ይፈታል፡፡ ቦርዱም ካጠፋ እንዲሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ይቅርታ ጠይቀኝ ብሎ መጠየቅ ፍፁም ተቋማዊ አሠራር አይደለም፤›› በማለት ውሳኔውን ፓርቲያቸው እንደሚቃወም አስታውቀዋል፡፡






