በተከሳሽ የፓርቲ አመራሮችና በአቃቂ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መካከል ያለው አቤቱታ ምላሽ አላገኘም
∙በቃል የቀረበው አቤቱታ ከድምጽ ክምችት ክፍል ጠፍቷል ተብሏል
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች እና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ ያሉ የሽብር ተከሳሾች በቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር መካከል ያለው አቤቱታ እስካሁን እልባት ሊያገኝ አልቻለም፡፡
ዛሬ ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች ማረሚያ ቤቱ የመብት ጥሰት እየፈጸመባቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አቤት ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዛሬ ዕለት በጉዳዩ ላይ የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪ ችሎት ቀርበው መልስ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ቀጠሮ ወቅት አቤቱታው በቃል ተሰምቶ በመቅረጸ ድምጽ ተቀድቶ እንደገና በጽሑፍ ተገልብጦ ከመልስ ጋር እንዲቀርብ ታዝዞ የነበር ቢሆንም ድምጹ ከፍርድ በቱ ድምጽ ክምችት ክፍል ሊገኝ ስላልቻለ በወረቀት ተገልብጦ መልስ እንዲሰጥበት ለማረሚያ ቤቱ አለመድረሱ ተገልጹዋል፡፡
በዚህ የተነሳም ፍርድ ቤቱ ለጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ችሎት ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ለማስቻል፣ በቀጣዩቹ ቀናት ውስጥ አቤቱታው እንደገና በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ እንዲቀርብ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ በቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦኬሎ አኳይ የክስ መዝገብ በተከሰሱ ሰዎች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የሰጡት ምስክርነት ከድምጽ ክምችት ክፍል ስለጠፋ እንደገና በሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ድጋሜ ምስክሮቹ እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም የተቀሰቀሰው እሳት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተሰማ
- ቃጠሎው ለአትክልት ልማት ከተደረገ ምንጣሮ ጋራ የተያያዘ መኾኑ ተጠቁሟል
በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ደን ውስጥ ዛሬ፣ ጥር 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ከረፋዱ 4፡30 ላይ የተቀሰቀሰው እሳት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለጸ፡፡
ቃጠሎው በቁጥጥር ሥር የዋለው ከቤተ ክርስቲያኑ በግምት ከመቶ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ በደረሰበት ኹኔታ ነው ብለዋል – እሳቱን በማጥፋት የተራዱ የዐይን እማኞች፡፡
የዳጋ እስጢፋኖስን ጨምሮ ከሌሎች የደሴቱ ገዳማት የመጡ መነኰሳት፣ የአቅራቢያው ነዋሪዎች፣ ከባሕር ዳር ከተማ በጀልባ ተጓጉዘው የደረሱ ምእመናን፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሓላፊዎች፣ የባሕር ዳር ዙሪያ ፖሊስና ልዩ ኃይል በጋራ ቃጠሎውን በማጥፋት ከፍተኛ የጋራ ርብርብ ማድረጋቸው ተገልጧል፡፡
የቃጠሎው ትክክለኛ መንሥኤ እስከ አኹን በይፋ ባይረጋገጥም፣ መሬቱን ለጌሾ ልማት ዝግጁ ለማድረግ በአንድ የገዳሙ መነኰስ የተለኰሰው እሳት በአቅራቢያው በብዛት በሚገኙት የሐረግ ተክሎችና ሸምበቆዎች መቀጣጠሉ እንደኾነ ማኅበረ መነኰሳቱን ያነጋገሩ የዐይን እማኞች ገልጸዋል፡፡
በገዳሙ ከሚገኙት ታላላቅ አገር በቀል ዛፎች ይልቅ በብዛት ተቃጥለው የሚታዩትም የሐረግና የሸምበቆ ተክሎቹ ናቸው – ‹‹አንድ አባት ጌሾ የሚያለሙበት አካባቢ ሐረግ ነበር፤ እርሱን ለማቃጠል ሲለኩሱት እሳቱ አሸንፎ ወጣ፤ ለማጥፋትም ከመነኰሳቱ አቅም በላይ ኾነ፡፡››
በአኹኑ ወቅት በስፍራው ከሚታየው ጢስና የተዳፈነ እሳት ጨርሶ መጥፋቱን ለማረጋገጥ ከሚደረግ እንቅስቃሴ በቀር የእሳት ቃጠሎው ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ከዓይን እማኞች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በጣና ሐይቅ ውስጥ ከደቅ ደሴት በስተምሥራቅ የሚገኘው የዳጋ እስጢፋኖስ የደሴት ገዳም የተመሠረተው በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ሲኾን መሥራቹም የዐፄ ይኩኖ አምላክ ወንድም አቡነ ሂሩተ አምላክ ናቸው፤ የተገደመውም በዐፄ ይኩኖ አምላክ እንደኾነ የገዳሙ አበው ይተርካሉ፡፡
በበርካታ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት ማእከልነቱ የሚታወቀው ዳጋ እስጢፋኖስ÷ የመሥራቹ የአቡነ ኂሩተ አምላክ መቋሚያ፣ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የተሣለች የእመቤታችን ምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕል፣ ብዛት ያላቸው የወርቅ፣ የብርና የነሐስ መስቀሎች ጨምሮ የዐፄ ዳዊት፣ የዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ፣ የዐፄ ሱስንዮስ፣ የዐፄ ፋሲልና ሌሎች ነገሥታት አዕፅምት፤ ዘውዶች፣ አልባሳት፣ ሰይፍና ጎራዴ የመሳሰሉ የነገሥታቱ የክብርና የወግ ዕቃዎች ተጠብቀው ይገኙበታል፡፡
የማኅበረ መነኰሳቱ ዋነኛ መተዳደርያ በተለያየ መንገድ ከሕዝብ የሚገኘው ድጋፍ ቢኾንም ቡና፣ ጌሾ፣ ሙዝና ፓፓዬ የመሳሰሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምረትም የገዳሙን አገልግሎት ይደጉማሉ ሲል የ ”ሐራ ዘተዋህዶ” ዘገባ አመልክቷል፡፡
ምርጫ ቦርድ በሶስቱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ
ዛሬ ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በአንድነት፣ በመኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲዎች ላይ ውሳሳለፉን አስታውቋል፡፡ ቦርዱ ውሳኔ ብሎ ያስተላለፈው ፤ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የውስጥ ችግራቸውን መፍታት አልቻሉም በሚል ለዛሬው ውሳኔ እሰጣለሁ ብሎ የነበረው ምርጫ ቦርድ ሁለቱ ፓርቲዎች በሁለት ሳምንት ውስጥ የውስጥ ችግራቸውን ፈትተው ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ የመጨረሻ ጊዜ ሰጥቻቸዋለሁ ሲል ገልጾአል፡፡
ቦርዱ ዛሬ ከሰዓት በሰጠው መግለጫ በአንድነትና መኢአድ ስም የተለያዩ ጉባኤዎች በመደረጋቸው ሁለቱ ፓርቲዎች ጥር 3 ያደረጉትን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አለመገኘቱን፣ አንድነት የ2004 ዓ.ም እንዲሁም የመኢአድን የ2001 ዓ.ም ደንብን እንጅ ከዛ በኋላ ያሉትን የፓርቲውን ደንቦች እንደማያውቅ በመግለጽ በሁለት ሳምንት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ችግራቸውን እንዲፈቱ የመጨረሻ ጊዜ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡
በሌላ በኩል መድረክ ረግጦ በመውጣት፣ ሌሎች ፓርቲዎች እንዲያድሙ በማድረግ፣ ቦርዱ የማያውቀው ትብብር በመመስረት በሚል በምርጫ ቦርድ ክስ የቀረበበትና ይቅርታ እንደማይጠይቅ በደብዳቤ ለገለጸው ሰማያዊ ፓርቲ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡ ማስጠንቀቂያውን የማያከብር ከሆነም ቦርዱ ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል፡፡
የቦርዱ ባለስልጣናት ‹‹ሰማያዊ ፓርቲን ህገ ወጥ ትብብር በመመስረት ስትከሱ ሌሎቹን የትብብሩን አባል ፓርቲዎች ለምን አልከሰሳችሁም?›› በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹ፓርቲዎቹ 9 መሆናቸውን የሰማሁት አሁን ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ‹‹እስካሁን ሌሎች ትብብሮችን ምርጫ ቦርድ አያውቃቸውም ብላችሁ ከሳችሁ አታውቁም›› በሚል የ9ኙን ፓርቲዎች ትብብር ህገ ወጥ ነው ካሉ ገዠው ፓርቲ ከአጋሮቹ ጋር ያለውን ግንኙነትን ለምን ህገ ወጥ ነው እንደማይሉ ለቀረበላቸው ጥያቄም ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹ኢህአዴግ እንደገዥ ፓርቲ አጋር ፓርቲዎች ሊኖሩት ይቻላል፡፡ እንደ ገዥ ፓርቲ ከአጋሮች ጋር መስራት ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮችን ቦርዱ አይመለከተውም›› ሲሉ መልሰዋል፡፡
አንድነትና መኢአድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ችግራቸውን እንዲፈቱ ተጨማሪ ጊዜ ሰጥቻለሁ ያለው ምርጫ ቦርድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ችግራቸውን ካልፈቱ ቦርዱ ተሰብስቦ ውሳኔውን አሳውቃለሁ ማለቱን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ ያመለክታል፡፡ አንድነት እና መኢአድ ምርጫ ቦርድ እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ አድርጉ ባለው መሰረት ያለፈው እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ባደረጉት ጠቅላላ ጉባኤ አንድነት ፓርቲ በድጋሚ አቶ በላይ ፈቃዱን ፕሬዘዳንት አድርጎ ሲመርጥ፤ መኢአድም እንዲሁ በተመሳሳይ ቀን ጠቅላላ ጉባዔ ያደረገ ሲሆን፤ በዕለቱ ምርጫ ቦርድ በህጉ መሰረት በሁለቱም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲገኝ የጥሪ ደብዳቤ ቢደርሰውም በሁለቱም ጉባኤ ላይ የቦርዱ ተወካይ እንዳልተገኘ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ቦርዱ አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ሁለቱም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርጉ የሁለት ሳምንት ጊዜ ሰጥቻቸዋለሁ ሲል ዛሬ በፅህፈት ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
…….
ሰማያዊ ፓርቲ ይቅርታ እንደማይጠይቅ አስታወቀ
ሰማያዊ ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤትን እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በጽሑፍ ይቅርታ ይጠይቅ በማለት የተላለፈው ውሳኔ ከሕግ አግባብ ውጪ ስለሆነ ተቃውሞውን በመግለጽ ይቅርታ እንደማይጠይቅ አስታወቀ፡፡
የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ባለፈው ሐሙስ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቦርድን ስም አጥፍቷል ብለዋል፡፡ ‹‹በተሻሻለው የምርጫ ሕግ አንቀጽ 102 (4)ሀ፣ ለ እና ሠ እንዲሁም 102 (6) ሐ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቦርዱን ሥልጣን መቀበል፣ ሕጋዊ ትዕዛዙንና መመርያውን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ቦርዱ በሚያዘጋጃቸው የጋራ የምክክር መድረኮች ወይም ሌሎች መድረኮች ላይ ወኪል የመላክ ኃላፊነት እንዳለባቸውና በሐሰት ስም ከማጥፋት መቆጠብ እንዳለባቸው ያመለክታሉ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ግን ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት ያዘጋጃቸውን የጋራ ምክክሮች እንዲበተኑ ሙከራ አድርጓል፣ እየረገጠ ወጥቷል፣ በሐሰት ቦርዱን ወንጅሏል፡፡ እንዲሁም የስም ማጥፋት ዘመቻ አድርጓል፤›› በማለት ፓርቲው በጽሑፍ ይቅርታ እንዲጠይቅ ቦርዱ ወስኗል በማለት አስታውቀዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ውሳኔውን አስመልክቶ፣ ‹‹እኛ ይህን የምንረዳው የምርጫ ቦርድ የራሱ አቋም ሳይሆን ኢሕአዴግ በቦርዱ ውስጥ ምን ያህል ሚና እንዳለው ያጋለጠ ውሳኔ መሆኑን ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
‹‹ቀደም ባሉት ጊዜያት የሰጠነው አስተያየትና ስብሰባ ረግጠን መውጣታችን ዘለፋ መስሎ ከተሰማቸው አትዝለፉን እንነጋገር ማለት መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ይቅርታ ጠይቁኝ ብሎ ማስፈራራት አገራችንን አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ይቅርታ መቀለጃ አይደለም፡፡ እኛም በዚህ ምክንያት አናስተናግደውም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በተጨማሪም በመሠረቱ እኛ አንድ ድርጅት ነን፡፡ ምርጫ ቦርድም እንዲሁ አንድ ድርጅት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ሊግባቡ የሚችሉት ደግሞ በሕግና በደንብ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ካጠፋ ወይ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳል፣ ወይም ቦርዱ ባለው ሥልጣን ችግሩ ይፈታል፡፡ ቦርዱም ካጠፋ እንዲሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ይቅርታ ጠይቀኝ ብሎ መጠየቅ ፍፁም ተቋማዊ አሠራር አይደለም፤›› በማለት ውሳኔውን ፓርቲያቸው እንደሚቃወም አስታውቀዋል፡፡
አንድነት ፓርቲ በድጋሚ በጠራው አስቸኳይ ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዘዳንቱን በመምረጥ ተጠናቀቀ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በመጪው ምርጫ ግንቦት 2007 ዓ.ም. ለመሳተፍ መወሰኑን እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ 450 ዕጩዎቹን በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ ማቅረቡን ይፋ ካደረገ በኋላ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ አድርጎ የፓርቲውን ፕሬዘዳንቱን ካለተመረጠ ምርጫው ላይ እንዳይሳተፍ አደርጋለሁ ባለው መሰረት ዛሬ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ቀበና በሚገኘው የፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት አዳራሽ ጠቅላላ ጉባዔው መካሄዱ ታውቋል፡፡ ፓርቲውን ለመምራት በዕጩነት ቀርበው የተወዳደሩት አቶ በላይ ፈቃዱ፣ አቶ አለነ ማህፀንቱ እና አቶ ዳግማዊ ተሰማ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ለፕሬዘዳንትነት የተወዳደሩት ሶስቱም ዕጩዎች በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በትምህርታቸው የማስተርስ ድግሪ፣ በፖለቲካ ተሳትፎ ሶስቱም በአንድነት ፓርቲ በተለያየ ከፍተኛ አመራርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በሙያቸውም የተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ማገልገላቸው ተጠቁሟል፡፡ በመጨረሻም በነበረው ውድድር አቶ አለነ ማህፀንቱ ራሳቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ከውድድሩ ውጭ በማድረግ በአቶ በላይ ፈቃዱና በአቶ ዳግማዊ ተሰማ መካከል በተደረገ የምረጡኝ ቅስቀሳና ውድድር የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ባደረጉት የምስጢር ድምፅ አሰጣጥ መሰረት አቶ በላይ 183 ድምፅ በማግኘት የአንድነት ፕሬዘዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ አንድነት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የጠቅላላ ጉባዔው አባላት 320 ሲሆን፤አቶ በላይም የአባላቱን 57.2 በመቶ ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል፡፡
ውጤቱን ተከትሎም ተፎካካሪያቸው የነበሩት አቶ ዳግማዊ ተሰማ ለአቶ በላይ ፈቃዱ የእንኳን ደስ ያሎት መልዕክት በማስተላለፍ መጪውን ምርጫ አንድነት ፓርቲ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በጋራ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸውና ለዚህም በፓርቲው የሚሰጣቸውን የስራ ድርሸና ተልዕኮ ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ መግለፃቸውን ከስፍራው የአዲስሚዲያ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ በመጨረሻም አቶ በላይ ፈቃዱ ፓርቲውን በፕሬዘዳንትነት ለመምራት ቃለ መሐላ መፈፃማቸው ታውቋል፡፡
በጉባዔው ላይ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዦች የተገኙ ሲሆን፤ በሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ ህግ መሰረት ሂደቱን መታዘብ የነበረበት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሂደቱን ለመታዘብ እንደማይገኝና ወኪልም እንደማይልክ ቀደም ሲል ከፓርቲው ለተደረገለት ጥሪ በደብዳቤ ማሳወቁ ተጠቁሟል፡፡ ቀደም ሲል ታህሳስ 2006 ዓ.ም. የፓርቲው ፕሬዘዳንት የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው በመልቀቅ ለፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ካስረከቡ በኋላ አቶ በላይ ፈቃዱ ያለፉት 3 ወራት የፓርቲው ፕሬዘዳንት ሆነው ማገልገላቸው አይዘነጋም፡፡









