በስኳርና በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ሙስና የተጠረጠሩ ታስረው ፍርድ ቤት ቀረቡ
ታምሩ ጽጌ
በ184 ሚሊዮን ብር ሙስና የተጠረጠሩ ብርጋዴር ጄኔራል ተካተዋል
የስኳር ኮርፖሬሽን የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታሰሩ
በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የመንግሥት ኃላፊዎችን፣ ነጋዴዎችንና ባለሀብቶች በቁጥጥር ሥር ማዋል የጀመረው ፌዴራል ፖሊስ፣ ከሁለት የስኳር ፋብሪካዎችና ከአንድ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ሦስት ተጠርጣሪዎችን አስሮ ፍርድ ቤት አቀረበ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በቁጥጥር ሥር አውሎ ሐሙስ ሐምሌ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ካቀረባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ፣ በ184,008,000 ብር የተጠርጣሩት ብርጋዴር ጄኔራል ኤፍሬም ባንጌ ናቸው፡፡ ብርጋዴር ጄኔራሉ የተጠቀሰውን ገንዘብ ለግላቸው በመዋላቸው ኦሞ ኩራዝ አምስት ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በሁለት ዓመት እንዲዘገይ ማድረጋቸውንም አስረድቷል፡፡
ሌላው በቁጥጥር ሥር የዋሉት የቀድሞ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ በጋሻው ናቸው፡፡ በመንግሥት የተጣለባቸውን አደራ ወደ ጎን በመተው ኦአይኤ ለተባለ ኮንትራክተር በትውስት አርማታና ሲሚንቶ መስጠታቸውን፣ ከሰጡ በኋላም ከተከፋይ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ባለመቀነሱ፣ ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡
አቶ ዮሴፍ ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት ሌላም ጉዳት አድርሰዋል ያለው መርማሪ ቡድኑ፣ የአገዳ ምንጠራ ሥራ በአንድ ሔክታር 25,000 ብር ለባቱ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተሰጥቶ እያለ ሥራውን ከባቱ በመንጠቅና በአንድ ካሬ ሜትር 72,150 ብር ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በመስጠት፣ በሕዝብና መንግሥት ላይ ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ሥራ አስኪያጁ በተመሳሳይ የአገዳ ምንጣሮ ላይ፣ ሥራው ሳይከናወን አሥር ሚሊዮን ብርና 20 ሚሊዮን ብር ለተለያዩ ግለሰቦች በመክፈልም ጉዳት ማድረሳቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ቡድን መሪ የነበሩት አቶ ካሳዬ ካቻ ደግሞ 26,771,681 ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው ታስረዋል፡፡
ተጠርጣሪው ሳትኮን ኮንስትራክሽን ለተባለ ኩባንያ ከመካኒሳ እስከ ዓለም ገና ለሚሠራ መንገድ፣ 400 በርሜል ወይም 23,456,481 ብር ግምት ያለው አስፋልት በውሰት መስጠታቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ አቶ ካሳዬ በውሰት የሰጡትን አስፋልት በሦስት ወራት ውስጥ ማስመለስ ሲገባቸው ባለማስመለሳቸው፣ በመንግሥት ላይ የ26,771,681 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
አቶ ካሳዬ በጠበቃቸው አማካይነት በሰጡት ምላሽ፣ ለሳትኮን በትውስት የተሰጠው አስፋልት በባለሥልጣን ተፈቅዶ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ድርጅቱም በወቅቱ ባለመመለሱ በፍትሐ ብሔር ክስ ተመሥርቶበት በሒደት ላይ መሆኑን በማስረዳት ሊጠየቁ እንደማይገባቸው ገልጸዋል፡፡ መጠየቅ አለባቸው ቢባል እንኳን በዋስ ሆነው በውጭ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ የጠየቁ ቢሆንም፣ መርማሪ ቡድኑ ተቃውሟል፡፡
ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ብይን የዋስትና መብት ጥያቄውን በማለፍ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ኤፍሬምና አቶ ዮሴፍ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ቀደም ብሎ ከቀረቡ ተጠርጣሪዎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ ካሳዬ ላይ የተጠየቀውን 14 ቀናት በመፍቀድ፣ ለነሐሴ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ያለመከሰስ መብት ያላቸውን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታን አቶ አለማየሁ ጉጆን ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸውን በማንሳቱ በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የስኳር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ደስታ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ አቶ ኪሮስ በኮርፖሬሽኑ የቤቶችና የመስኖ ዘርፍ ልማት ዋና ዳይሬክተር እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደሪፖርተር ዘገባ ከሆነ፤ በአጠቃላይ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ቁጥር እስከ ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት ድረስ 51 ደርሷል፡፡
የመኢአድ አመራር የነበሩት አቶ ማሙሸት አማረ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰሱ
በታምሩ ጽጌ

አቶ ማሙሸት አማረ
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አመራር የነበሩትና ከሁለት ዓመታት ወዲህ ለሌሎች አመራሮች ጋር በተፈጠረ ልዩነት ከአባልነት የራቁት አቶ ማሙሸት አማረ፣ የሽብርተኝነት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
አቶ ማሙሸት የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (4)ን ተላልፈው የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማሴር መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ አቶ ማሙሸት በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. መልምለው ያደራጇቸውንና በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩ የሽብር ቡድን ታጣቂዎችን አስተባብረው፣ በአማራ ክልል በተመረጡ ቦታዎች የሽብር ድርጊቱን እንዲፈጽሙ ማዘጋጀታቸውን በክሱ ገልጿል፡፡ አቶ ማሙሸት ኃላፊነት ወስደው እንቅስቃሴውን ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነው ለመምራት ኬንያ ለመሄድ ሞያሌ ከተማ እንደገቡ፣ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው የክስ ዝርዝር ላይ ገልጿል፡፡
ተከሳሹ በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ሽመልስ ለገሰ በተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን አባል አማካይነት እንደተመለመሉ የሚገልጸው ዓቃቤ ሕግ፣ ተልዕኮ በመቀበል ከቡድኑ በሚላክላቸው ገንዘብ የጦር መሣሪያ በመግዛትና ማሠልጠኛ በማመቻቸት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተነስቶ የነበረውን ሁከት እንዲቀጥል ሲያደርጉ እንደነበር ገልጿል፡፡
በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በምርጫ ሳይሆን በትጥቅ ትግል ከሥልጣን ማስወገድ እንዲቻል፣ በውጭና በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጥምረት በመፍጠር የሽብር ተግባር መፈጸም እንዳለባቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመቀበል መስማማታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ አባላት በመመልመልና በማደራጀት ለሥልጠና ወደ ኤርትራ እንዲልኩም ተልዕኮ እንደተሰጣቸው አክሏል፡፡
ተከሻሹ በ2007 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ለቡድኑ አባላትን መልምለውና ወታደራዊ ቤዝና ማሠልጠኛ ወዳላት ኤርትራ በሁመራ በኩል መላካቸውን፣ በታኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም. ከተለያዩ አካባቢዎች 11 የሽብር ቡድን አባላትን ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሰብስበው መንግሥትን ከሥልጣን ማስወገድ የሚቻለው በሕዝባዊ አመፅ መሆኑን፣ አመጽ ለመፈጸም ደግሞ የጦር መሣሪያ ስለሚያፈልግ እያንዳንዱ አባል ሌላ አባላት በመመልመል፣ በማደራጀትና በማስፋፋት የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል አንዱን ብሔር በሌላኛው ብሔር ላይ እንዲነሳ ማድረግ እንዳለባቸው ተልዕኮ መስጠታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡
ተከሳሹ በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. ሰሜን ሸዋ ውስጥ ለሽብር ቡድኑ ወታደራዊ ቤዝ የሚሆን ቦታ በመምረጥ፣ ከደብረ ብርሃንና አዲስ አበባ የተመለመሉ ዘጠኝ አባላትን ወደ ማሠልጠኛ በመላክ ሥልጠና ማስጀመራቸውንም ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡
በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. አቶ ማሙሸት ዘመነ ምሕረቱ ከተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን አመራርና ለገሰ ወልደሀና ከተባለ የቡድኑ አባል ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመሰብሰብ፣ በጎንደር ተቀስቅሶ የነበረውን ሁከት እንዲስፋፋና እንዲቀጥል ሰሜን ሸዋ ጫካ ውስጥ በመግባት፣ በአካባቢው የሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችና የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጥቃት እንዲደርስ ተልዕኮ መስጠታቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
በአጠቃላይ አቶ ማሙሸት የሽብርተኛነት አዋጅ ቁጥር 652/2001ን በመተላለፍ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም የማቀድ፣ የመዘጋጀት፣ የማሴርና የማነሳሳት ሙከራ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ክስ ቀረቦባቸዋል፡፡ ተከሳሹ ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሲሆኑ፣ በግላቸው ጠበቃ ማቆም አለማቆማቸውን ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ምላሽ እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፦ ሪፖርተር
የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የቀረበበት የዶ/ር መረራ አቤቱታ ለመጪው ዓመት ተቀጠረ
በታምሩ ጽጌ

ዶ/ር መረራ ጉዲና
የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመጥቀስ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን መከልከሉን የተቃወሙት መረራ ጉዲና (ዶ/ር)፣ ጉዳያቸው የሕገ መንግሥት ትርጉም ስለሚያስፈልገው የአጣሪ ጉባዔውን ውሳኔ እንዲጠይቁ ተነገራቸው፡፡ ውሳኔውን የሚሰሙት በሚቀጥለው ዓመት ነው፡፡
ሦስት የተለያዩ የወንጀል ክሶች የተመሠረቱባቸው ዶ/ር መረራ በክሶቹ የተጠቀሱባቸው የሕግ አንቀጾች የምስክሮችና የማስረጃ ዝርዝሮች እንዳይደርሳቸው የማይከለክሉ መሆኑን በመግለጽ፣ ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/01 አንቀጽ 32ን በመጥቀስ እንዳይሰጣቸው መከልከሉን ተቃውመው ነበር፡፡
ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1)ሀ፣ ለ፣ 38(1)፣ 27(1)፣ 238(1) እና (2)ን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 12(1)፣ 2(1) የወንጀል ሕግ 486(ለ) ማለትም በጋራ በመተባበር፣ ወንጀል ለማድረግ በማደም፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ወንጀል ለማድረግ በመስማማት፣ የሐሰት ወሬ በማውራትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመጣስ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ሳለ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 32 በመጥቀስ የምስክሮች ዝርዝር እንዳይሰጣቸው መከልከሉ ተገቢ ያልሆነና ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቀረበለትን የመቃወሚያ አቤቱታ የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም?›› በማለት ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አጣሪ ጉባዔ የላከው ቢሆንም፣ ውሳኔው ሊደርስ ባለመቻሉ ለቀጣይ ዓመት ጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የምስክሮች ዝርዝር ‹‹ለተከሳሽ ሊሰጥ ይገባል ወይስ አይገባም?›› የሚሉ ጥያቄዎች የተነሱት በዶ/ር መረራ ክስ ብቻ አለመሆኑን የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ በርካታ የክስ መዝገቦች ላይ ጉዳዩ በመነሳቱ ቀደም ብሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም የሚለውን ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሷል፡፡ ምክር ቤቱ ግን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ መላኩን ከመግለጽ ውጪ ያለው ነገር ስለሌለ ውሳኔውን መጠበቅ የግድ እንደሚል አስረድቷል፡፡
የዶ/ር መረራ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ዶ/ር መረራ ከታሰሩ ዘጠኝ ወራት ሞልተዋቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ደግሞ የዓመቱን ሥራ ሊያጠናቅቅ የቀረው ከ15 ቀናት አይበልጥም፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በራሱ የመተርጎም ሥልጣን ስላለው ተርጉሞ ወይም የምክር ቤቱ ውሳኔ የሚፈጥንበት ሁኔታ ካለ ተባብሯቸው፣ ወደሚቀጥለው ዓመት ከመተላለፉ በፊት ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ዶ/ር መረራ በክርክር መቃወሚያቸው ምክንያት ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለትርጉም መላኩን አስታውሶ፣ የመቃወሚያ ሐሳባቸውን ለማንሳት ፈልገው ከሆነ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡ የዶ/ር መረራ ጠበቆች ተመካክረው ምላሽ ሲሰጡ መቃወሚያ ያቀረቡት ሕጉ በሚፈቅድላቸው መሆኑን በመጠቆምና ፍርድ ቤቱም ትዕዛዝ እንደሰጠበት ተናግረው፣ መቃወሚያቸውን እንደማያነሱ ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም ዶ/ር መረራ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንኳን ሳይሰጡ እየተጉላሉ መሆኑን ገልጸው፣ ጉዳዩ በአጭር ቀናት ውስጥ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ መቃወሚያችሁን አንሱ የሚል ጥያቄ አለማቅረቡን ገልጾ፣ እሳቸው በራሳቸው ተነሳሽነት መቃወሚያቸውን እያነሱ ስለመሆናቸው ለማወቅ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ዶ/ር መረራም ሆኑ ሌላ ተከሳሽ እንዲመላለስና እንዲጉላላ ፍላጎት እንደሌለው በመንገር፣ መዝገቦችን የሚያስተናግደው ክስ በተመሠረተበት ጊዜ (ዕድሜ) ቅደም ተከተል ከመሆኑ አንፃር የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ መጠበቁ ለተከሳሹም ሆነ ለፍርድ ቤቱ ጥቅም ስላለው፣ ለጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. መሸጋገሩ የግድ መሆኑን በማስረዳት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የዶ/ር መረራ ጠበቃ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም፣ የጥብቅና ፈቃድና ውክልና እያላቸው ማረሚያ ቤት ደንበኛቸውን እንዳይጎበኙና እንዳያነጋግሩ እንደከለከላቸው ላቀረቡት ጥያቄ፣ ማረሚያ ቤቱ እንዲያገናኛቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ዘገባው ይሪፖርተር ነው።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ
1. የመሬት መብት ተሟጋቹ ኦሞት አግዋ ቀሪ መከላከያ ምስክራቸውን ያሰሙት ባሳለፍነው ሰኔ ወር ነበር፡፡
የመሬትና አካባቢ ጥበቃ አክቲቪስት ኦሞት አግዋ ሰኔ 05 ቀን 2009 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ቀሪ ሁለት የመከላከያ ምስክሮችን አስደምጠዋል፡፡ ምስክሮቹ በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የጋመቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ኦኬሎ አኳይ እና አቶ ሳምሶን አባተ የተባሉ ምስክር ናቸው፡፡
ምስክሮቹ በዋናነት ኦሞት አግዋን የሚያቋቸው በ1996 ዓ.ም ጋምቤላ ክልል በተነሳ ግጭት በክልሉ መንግስት በተቋቋመ የሰላም ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆነው ግጭቱን ለማብረድና ግጭቱን በመሸሽ የተሰደዱ ዜጎችን ለማስመለስ መልካም ስራ መስራታቸውንና ተከሳሹ “የጋምቤላ ሰለምና ልማት ጉባኤ” የሚባል ምግባረ ሰናይ ድርጅትም መስርተው ሲሰሩ እንደሚያውቁ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀሪ ሦስት የተከሳሽ መከላከያ ምስክሮችን ከዝዋይ እና ሸዋ ሮቢት የፌደራል እስር ቤቶች ሲቀርቡ ለመስማት በሚል ለሐምሌ 20 ቀን 2009 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።
2. የኦፌኮ አባላትና አመራሮች እነ ጉርሜሳ አያና ላይ ይሰጣል የተባለው ብይን አሁንም በቀጠሮ መጓተቱ ቀጥሏል
የሽብር ክስ በቀረበባቸው የኦፌኮ አመራሮችና አባላት እነ ጉርሜሳ አያኖ (በቀለ ገርባ) መዝገብ ላይ ሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም ብይን ለማሰማት የመጨረሻ ቀጠሮ ተሰጥቶ የነበር ቢሆንም ብይኑ ‹‹ተሰርቶ አላለቀም›› በሚል ሌላ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ለብይን በሚል ቀጠሮ እየተሰጠባቸው አራት ወራት ያህል ያስቆጠሩት እነ ጉርሜሳ አያኖ (22 ሰዎች)፣ ብይኑን ትሰማላችሁ ተብለው ለሰኔ 15 ቀን 2009 ቀጠሮ ቢሰጣቸውም በዕለቱ ቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር ተከሳሾቹን ፍርድ ቤት ሳያቀርባቸው ቀርቷል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ እንደገና ተከሳሾች ባልቀረቡበት ሁኔታ ለሐምሌ 06 ቀን 2009 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
3. በእነ ንግስት ይርጋ መዝገብ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ባለመቅረባቸው ተከሳሾች በቀጠሮ እየተጉላሉ ነው
በአክቲቪስት ንግስት ይርጋ የክስ መዝገብ በሽብር የተከሰሱት ተከሳች ላይ አቃቤ ህግ አሉኝ የሚላቸውን ምስክሮች ባለማቅረቡ በተደጋጋሚ ቀጠሮ ተከሳሾች መጉላላት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ችሎት ቀርበው የነበሩት ተከሳሾች ምስክር ሳይሰማባቸው እንደገና ምስክር ለመጠባበቅ ለሐምሌ 11 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ተከሳሾች በተደጋጋሚ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ቀጠሮ መሰጠቱን በመቃወም አቤቱታ አሰምተዋል፡፡ በዚህም 5ኛ ተከሳሽ የሆነው በላይነህ አለምነህ “እኛ የታሰርነው እና ድርጊቱ ተፈፀመ የተባልነው ባህርዳርና ጎንደር ቢሆንም ምስክር እየተጠበቀ ያለው ግን ከአዲስ አበባ ነው፡፡ ይህ እንዴት ይሆናል? በባለፈው ቀጠሮ ምስክር ረጅም ቀጠሮ እየተሰጠን ያለው አቃቤ ህግ ምስክሮችን እስኪያሰለጥን ድረስ ነው ወይ ብለን አስተያየት ሰጥተን ነበር፡፡ ፍርድ ቤት አቃቤህ ግን ማዘዝ ከቻለ ለምንድነው ሃይ የማይለው?” ሲል ተናግሯል፡፡
4. ዶ/ር መረራ ጉዲና ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደርጓል
*የምስክሮች ማንነት ይገለጽ በሚለው መቃወሚያ ላይ ብቻ ብይኑ አልተሰራም፤ ጉዳዩ ለህገ-መንገስታዊ ትርጉም ለፌደሬሽን ምክር ቤት ተልኳል ተብሏል፡፡
በፌደራል አቃቤ ህግ ሦስት የተለያዩ ክሶች የቀረቡባቸው የኦፌኮ ፕሬዚደንት ዶ/ር መረራ ጉዲና በቀረቡባቸው ክሶች ላይ ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያዎች አብዛኞቹ ውድቅ ሲደረጉ አንዱ ብቻ ለህገ-መንግስታዊ ትርጉም ለፌደሬሽን ምክር ቤት መላኩን ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም ጉዳዩን ለማየት የተሰየመው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት አስታውቋል፡፡
ዶ/ር መረራ መቃወሚያቸው ውድቅ መደረጉን ከችሎቱ ከሰሙ በኋል፣ ‹‹የተከሰስሁት ፖለቲካዊ ክስ ነው፡፡ እኔ የተከሰስሁት ለኦሮሞ ህዝብ፣ ለኢትዮጵያ ህዝቦች በመከራከሬ ነው፡፡ ይህንን እናንተ ዳኞችም፣ የኢትዮጵያ ህዝብም ያውቃል፡፡ እኔ የተከሰስሁት በሀገራችን ሀቀኛ ፌደራላዊ ስርዓትና ፍትህ እንዲሰፍን በመከራከሬ ነው›› ሲሉ አስተያየታቸውን አሰምተዋል፡፡
ችሎቱ የፌደሬሽን ምክር ቤት የተላከለትን የትርጉም ስራ ሰርቶ መላኩን ለመጠባበቅ በሚል ለሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
5. ጋዜጠኞችና አርቲስቶች ሙዚቃና ግጥሞችን ዩ ቲ ዩብ ላይ ጭነዋል በሚል የሽብር ክስ ቀርቦባቸዋል
ሁከትና አመጽ የሚያስነሱ ዜና፣ ግጥምና ሙዚቃ በማዘጋጀት ዩ ቲ ዩብ ላይ እንዲጫን አድርገዋል በሚል ሰባት ሰዎች የሽብር ክስ የቀረበባቸው ባሳለፍነው ሰኔ ወር ነበር፡፡
በፌደራል አቃቤ ህግ ክሱ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች ኦሊያድ በቀለ፣ ኢፋ ገመቹ፣ ሞይቡሊ ምስጋኑ፣ ቀነኒ ታምሩ፣ ሃይሉ ነጮ፣ ሴና ሰለሞን እና ኤልያስ ክፍሉ ናቸው፡፡ አቃቤ ህግ ተከሳሾችን የጸረ-ሽብር አዋጁን አንቀጽ 4 መተላለፍ ክስ ያቀረበባቸው ሲሆን፣ ተከሳሾቹ ሰኔ 23 ቀን 2009 በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19 ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሱ ተነቦላቸዋል፡፡
6. ሁለት ጋዜጠኞች የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ባሳለፍነው ሰኔ ወር ከእስር ተፈተዋል
የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው እና የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ አዘጋጅና ባለቤት ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ የተበየነባቸውን የእስር ቅጣት አጠናቀው ከእስር ተፈተዋል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው አመጽ በማነሳሳት ጥፋተኛ ተብሎ የተበየነበትን የአንድ አመት ከስድስት ወር እስሩን ጨርሶ ከቃሊቲ እስር ቤት የተፈታው ሰኔ 16 ቀን 2009 ዓ.ም ሲሆን፣ በስም ማጥፋት ክስ የአንድ አመት እስር ተበይኖበት የነበረው ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ደግሞ በአመክሮ ከሸዋሮቢት እስር ቤት የተፈታው ባሳለፍነው ሳምንት ነው፡፡
ምንጭ፦ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት
የኦሮሚያ ክልልን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ አንጻር ሲቃኝ

ውብሸት ሙላት
በዚህ ዓመት የሚጸድቁት ዋና ዋና አዋጆችን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች የ2009 ዓ.ም. የሥራ ዘመናቸውን ሲጀምሩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ አሳውቀዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የምርጫ ሕጉና የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ የሚኖረውን ልዩ ጥቅም የሚመለከቱት ከሚወጡት ውስጥ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡
የምርጫ ሕጉን በተመለከተ እስካሁን ለሕዝብ የደረሰ ነገር የለም፡፡ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምን በተመለከተ ግን የበርካታ ሰውን ትኩረት የሳበ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የመንግሥት አይደሉም የተባሉ ረቂቅ አዋጅና የጥናት ሰነዶች በማኅበራዊ ሚዲያ መሠራጨታቸውም ይታወሳል፡፡ በያዝነው ሳምንት ደግሞ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተዘጋጀና የጸደቀ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የመራው መሆኑን ተዘግቧል፡፡ ለወትሮው ከሚወጡት ሕጎች ለየት ባለ መልኩ ረቂቁን የሚመለከት ዘለግ ያለ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
ሕገ መንግሥቱ ጸድቆ ሥራ ላይ ከዋለ ሃያ ሁለት ዓመታት ሊሆነው ሁለት ወራት የማይሞሉ ጊዜያት ቢጎድሉትም፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀስ 5 ላይ የሰፈረውና ዝርዝሩ በሌላ ሕግ እንደሚወሰን ተስፋ የተጣለበት፣ ክልሉ በአዲስ አበባ ላይ የሚኖረው የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ‘ጃሮ ዳባ ልበስ’ ተብሎ ኖሮ ገና በዚህ ዓመት ሕግ ሊወጣለት ነው፡፡ ለረቂቅ አዋጁ መነሻ የሆነው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ የሚከተለው ነው፡፡
“የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የምትገኝ በመሆኗ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ይላል፡፡
ይኽ ጽሑፍ ከላይ የተገለጸውን ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ ተመርኩዞ የወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ምጥን ቅኝት ያደርጋል፡፡ ዋና ትኩረቱም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅሞች ተብለው በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት ሐረጋትን በአጠቃላይ ከሕገ መንግሥቱ መንፈስ ላይ በመመርኮዝ ረቂቅ አዋጁን መፈተሽ ነው፡፡ በመሆኑም፣በረቂቁ ላይ የተቀመጡ ግልጽነት የጎደላቸውን፣ዘርዘር ማለት የሚያስፈልጋቸውን፣መካተት ሲገባቸው ያልተካተቱ ጉዳዮችን እና በልዩ ጥቅም ሥር ሊወድቁ የማይችሉ ነጥቦችን ይመለከታል፡፡ ስለሆነም፣የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ያላቸውን መብት የዚህ ጽሑፍ አካል አይደለም፡፡
ረቂቁ በአጭሩ ፤
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በ25 አንቀጾች እና በአራት ክፍሎች ተቀነብቦ በአጭሩ የቀረበ ነው፡፡ በረቂቅ አዋጁ መሠረት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ በሦስት ክፍል የተቀመጡ ልዩ ጥቅሞች ይኖሩታል።
የመጀመሪያው ከአገልግሎት አቅርቦት ጋር የተያያዘ ልዩ ጥቅም ነው፡፡ በመሆኑም፣ ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር ለሚፈልጉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአፋን ኦሮሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የማደራጀት ግዴታ አለበት።
አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ በመሆኗ በከተማዋ የሚሰጠው የጤና አገልግሎት በከተማዋ ዙሪያ ያሉ የክልሉ ተወላጆችን ታሳቢ ያደረገ ይሆናል፤ ከዚህ ባለፈም ከአማርኛ በተጓዳኝ አፋን ኦሮሞ በከተማ አስተዳደሩ የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንደሚያገለግል ተገልጿል።
የኦሮሞ ሕዝብን ማንነት የሚያንጸባርቁ አሻራዎች በከተማዋ በቋሚነት እንዲኖሩ በከተማዋ፥ አደባባዮች፣ ጎዳናዎች፣ ሠፈሮች እና የመሳሰሉት ቦታዎች እንደ አስፈላጊነቱ በቀድሞ የኦሮሞ ስማቸው ሊጠሩ እንደሚችሉ በረቂቁ ላይ ተቀምጧል።
የከተማው አስተዳደርም የኦሮም ሕዝብን ባህልና ታሪክ የሚያንፀባርቁ የባህልና ታሪክ ማዕከላት፣ ቲያትር፣ ኪነ ጥበባትና የመዝናኛ ማዕከላት የሚገነቡበትና የሚተዋወቁበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታ ተጥሎበታል። እንዲሁም፣ የከተማዋ መጠሪያዎች “ፊንፊኔ” እና “አዲስ አበባ” በሕግ ፊት እኩል ተቀባይነት እንዳላቸው በረቂቁ ላይ ሰፍሯል።
ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም አንጻር ደግሞ በረቂቁ ላይ የተካተቱት ሦስት ፈርጆች አሏቸው፡፡ የመጀመሪያው የኦሮሚያ ክልል እና የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የሚያገኛቸው የሚመለከቱ ናቸው፡፡
በዚህም መሠረት፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተለያዩ መንግሥታዊ ሥራዎች እና ሕዝባዊ አገልግሎቶች መስጫ የሚውሉ ሕንጻዎች የሚሠሩበትን መሬት የከተማው መስተዳድር ከሊዝ ነጻ እንዲያገኙ ይደረጋል። በአዲስ አበባ ጋር በተያያዘ በዙሪያ ያሉ ወጣቶች በተቀናጀ ሁኔታ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሌሎች በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉት አካባቢዎች አዲስ አበባ የሚሠራቸው ሥራዎች ለዙሪያ ወጣቶች የሥራ ዕድል የማመቻቸት ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ አርሶ አደሮች በተደራጀ መለክ ምርቶቻቸውን የሚሸጡባቸውን የገበያ ማዕከላት አቋቁሞ ለአርሶ አደሮች እና ማኅበሮቻቸው ያቀርባል።
ከዚህ በተጨማሪም በከተማው የሚኖሩ የኦሮሚያ ክልል ሠራተኞች በመንግሥት ወጪ ከሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የማገኘት አርሶ አደሩ ለልማት ተነሺ ሲሆን፥ በቂ ካሳ የማግኘትና በዘላቂነት የማቋቋም ግዴታ ይኖርበታል፡፡ የካሳና የማቋቋሙ ጉዳይ ከአሁን በፊት የተነሱትም ሊጨምር ሊጨምር ይችላል፡፡
በሁለተኛው ፈርጅ የሚካተቱት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል (በተለይም በዙሪያው ከሚገኘው ዞን) የሚያገኛቸውን የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም የሚመለከት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ፣ ለከተማው ልማት የግንባታ ማእድናት ማግኛ ሥፍራዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ የአየር ብክለት እንዳያስከትሉ እና ለደን ልማት ወይም ለሌሎች ልማቶች መዋል እንዲችሉ እንዲያገግሙ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማከሚያና ማስወገጃ ቦታዎች እንዲሁም መልሶ መጠቀሚያ ስፈራዎች አስተዳደሩና ክልሉ በጋራ ባጠኗቸወ ቦታዎችና ሳይንሳዊ መስፈርቶችን ባሟሉ ሁኔታዎች እንዲተዳደሩ እንደሚደረግ ረቂቁ ስለሚያመለክት የማዕድናት ማውጫ ቦታ እና የቆሻሻ ማስወገጃ እና ማከሚያ ቦታ ክልሉ ያቀርባል ማለት ነው፡፡
በሦስተኝነት የምናገኛቸው የከተማ መስተዳድሩ በራሱ ድንበር ውስጥ በሚያከናውናቸው ተግባራት ምክንያት በዙሪያው ባሉ ነዋሪዎች የሚደርሰውን የጎንዮች ጉዳት በተመለከተ እና በተለይም የውሃ አቅርቦት ከሚያገኝበት አካባቢ ለሚኖረው ሕዝብ የሚኖረበትን ግዴታ የሚመለከት ነው፡፡ በአጭሩ ከአካባቢ ጥበቃ እና ውሃ ለወጣበት ወይንም ለሚያልፍበት አካባቢ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ከማዳረስ ግዴታን የሚመለከት ነው፡፡
በዚህም መሠረት በመስተዳድሩ ዙሪያ ባሉ ከተሞችና ቀበሌዎች ደህንነቱ ሳይጠበቅና ቁጥጥር ሳይደረግበት በሕግ ከተቀመጠው ደረጃ በላይ ወደ ክልሉ በተጣሉ ወይም በፈሰሱ ቆሻሻዎች ምክንያት በሰው፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ለደረሰው ጉዳት በሕግ አግባብ ከአስተዳደሩ ካሳ የማግኘት መብት እንዳለቸው ረቂቁ ይገልጻል፡፡ የመጠጥ ውሃን በተሚመለከት ደግሞ የከተማ መስተዳድሩ በአብዛኛው ውሃ የሚያገኘው ከኦሮሚያ ክልል በመሆኑ ጉድጓዱ የሚቆፈርበት፣ ግድብ የሚለማበት ወይም የውሃ መስመሩ አቋርጠው የሚያልፍባቸው የክልሉ ከተሞችኛ አና ቀበሌዎች ለሚኖሩ ነዋሪዎች በአስተዳደሩ ወጪ የመጠጥ ዉሃ የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡
አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል የተከበበች በመሆኑ፣የተቀናጀ የትራንስፖርት አገልግሎትም መሥጠት ይጠበቅባታል፡፡ ከላይ የተገለጹትን ልዩ ጥቅሞች ለማስፈጸም የሚገለግል አንድ ተቋም ከከተማው መስተዳድር እና ከክልሉ ምክር ቤት በእኩል ቁጥር የተወከሉ ሰዎች የሚገኙበት ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥት የሆነ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ረቂቁ ላይ ተገልጿል፡፡ ረቂቅ አዋጁ በአጭሩ ከላይ የቀረበውን ይመስላል፡፡
በመቀጠል ሕገ መንግሥቱ “ልዩ ጥቅም” በማለት ቀድሞ የተቀመጠው ምን እንደሆነ እንመለከታለን፡፡
ሕገ መንግሥቱ ቀድሞ ያሰበው፤
ቀድመው በፌደራል ሥርዓት የማይተዳደሩ አገራት በተለይም ገና እንደ አዲስ ሲመሠረቱ ከሚያሳስቧቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው የዋና ከተማ ነገር ነው፡፡ በተለይም፣ ዋና ከተማው አንድን ክልል አላግባብ እንዳይጠቅም ወይንም እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቃል፡፡
በዚህም መሠረት፣ ከተማው ለሚገነባበት ወይንም በዋና ከተማነት የተመረጠው ቦታ ቅርብ የሚሆነው ክልል ወይንም ሌላ ከተማ፣ የበለጠ ተጠቃሚ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በምሳሌነት የአውስትራሊያን ብንወስድ ዋና ከተማዋ ሲዲኒ (የኒውሳውዝ ዌልዝ ክልል ዋና ከተማ) ወይንም ሜልቦርን (የቪክቶሪያ ክልል ዋና ከተማ) እንዳይሆን ያደረገችው እና ከሲዲኒ ከተማ ከመቶ ማይልስ ባላነሰ እርቀት ላይ እንዲቆረቆር የተወሰነው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
ዋና ከተማ የሚሆንበት ክልል ወይንም ቅርብ የሆነ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ኗሪዎች በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድሎች ይኖሯቸዋል፡፡ በሌላ ክልል ሊፈጠር የማይችል ዕድል እና ተጠቃሚነት ማለት ነው፡፡ አዲስ አበባ ዋና ከተማ በመሆኗ በአቅራቢያዋ ለሚገኙ ከተሞች ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገችው ማለት ነው፡፡
ይሁን እንጂ፣ አዲስ አበባ ቀድማ የተቆረቆረች እና ዋና ከተማም የነበረች በመሆኗ በሽግግር ወቅቱ (ከ1983-1987 ዓ.ም.) ክልል 14 ተብላ ከሌሎች ክልሎች ጋር እኩል ሥልጣን የነበራት ብትሆንም፣ ሕገ መንግሥቱ የቀድሞውን አወቃቀር አልመረጠም፡፡ ይልቁንም፣ ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግሥት እንዲሆን መርጧል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ረቂቅ በነበረበት ወቅት ከተዘጋጀው ማብራሪያ መረዳት የሚቻለውም፣ አዲስ አበባ የበርካታ ዓለም ኣቀፍ ተቋማት መቀመጫ ስለሆነችና የፌደራሉም መንግሥት በራሱም ስለ ዓለም አቀፍ ተቋማቱም በአግባቡ ኃላፊነቱን መወጣት በሚያስችለው መንገድ መዋቀር የቀድሞው አወቃቀር የተቀየረ መሆኑን ነው፡፡
በተለምዶ፣ዋና ከተማ የሚሆነው ቀድሞ የነበረ እና የሕዝብ ቁጥሩም ከፍተኛ ከሆነ ሌላው ከተማው ቀድሞ የነበረና ትልቅ ሆኖ የኗሪውም ብዛት ከፍተኛ ከሆነ የኗሪውን መብቶች በሚገድብ መልኩ ርዕሰ ከተማ መቆርቆር ብዙም አልተለመደም፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት ሞስኮ እና በርሊን ናቸው፡፡ በሩሲያ ከቀድሞው ዋና ከተማ ከሴንት ፒተርስበርግ ወደ ሞስኮ ሲዛወር፣ በጀርመን ደግሞ ከቦን ወደ በርሊን ሲቀየር ቀድመው የነበሩና በርካታ ሕዝብ ስለነበራቸው ከክልል ጋር እኩል ሥልጣን እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ትልቅ ከተማ ሲሆኑ የክልልነት ደረጃ መስጠት የተለመደ ነው፡፡ የሕዝብ ቁጥሩ አናሳ ሲሆን ደግሞ ለማእከላዊው ተጠሪ ማድርግ የተለመደ ነው፡:
ይሁን እንጂ፣የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የርእሰ ከተማዋን አስተዳደር በተመለከተ ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግሥት ከመሆን በዘለለ በሌሎች አገራት ያልተለመደ ወይንም የተለየ መንገድ ተከትሏል፡፡ ይኼውም አዲስ አበባ የምትገኝበት ክልል ከከተማው የተለየ ጥቅም እንዲኖረው መደንገጉ ነው፡፡ ይህ ልዩ ጥቅም ምን እንደሆነ በግልጽ ባይቀመጥም ሕገ መንግሥቱ ሲጸድቅ ከነበረው ውይይት እና በቃለጉባኤ ከተያዘው የተወሰኑ ነጥቦችን መረዳት ይቻላል፡፡
በውይይቱ ወቅት በግልጽ ከተነሱት ጉዳዮች አንዱ በከተማ መስተዳድሩ ውስጥ ካሉ ፋብሪካዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል ፍሳሽ በመልቀቅ ክልሉና ነዋሪዎች ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ፣ከተማዋ መስፋቷ ስለማይቀር በዙሪያው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ላይ የሚደርሰው መፈናቀልን ጋር የተገናኘ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ እንዲሁም የከተማውን ዙሪያና ከተማውን በተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም እንደሚገናኝም ተወስቷል፡፡ ከአጽዳቂ ጉባኤያተኞች አንዱ የነበሩት፣ አቶ ተሰማ ጋዲሳ የተባሉ ግለሰብ ስለጉዳዩ ሲያስረዱ ከተማዋ የኦሮሚያ ክልልም ዋና ከተማ በመሆኗ መስተዳድሩ ለክልሉ ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ባሻገር፣ የጽሕፈት ቤት አቅርቦትንና የመሳሰሉትን የሚመለከት እንደሆነ ገልጻዋል፡፡ ሌላው አስተዳደራዊ ጉዳዮችንም የሚመለከት ተነስቷል፤ምንም እንኳን ዝርዝር ነገር ባይኖረውም፡፡ የረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ማብራሪያም ከቃለጉባኤው ጋር በይዘቱ ተመሳሳይ ነው፡፡
ስለሆነም፣የክልሉ ልዩ ጥቅም እንዲከበር መነሻ የሆነው፣ አዲስ አበባ ኦሮሚያ ውስጥ መገኘቷ፣ ከተማዋ ወደ ፊት የመስፋቷ ጉዳይ አይቀሬ መሆኑ፣ ከተማዋ ከክልሉ የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶችን ማገኘቷ፣የክልሉ ዋና ከተማ መሆኗ እና በከተማ መስተዳድሩ ውስጥ የሚፈጸሙ የተለያዩ ድርጊቶች በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ሊያደርሱት የሚችሉት ጉዳት መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከእዚህ ሌላ፣ሕገመንግሥቱ ላይ “ማኅበራዊ አቅርቦትን” የሚል ሃረግ ስላለው ይህንን ትርጉም መሥጠት ያስፈልጋል፡፡
ከረቂቅ አዋጁ የምንረዳው የትምህርት፣የቋንቋ አጠቃቀም፣የሕክምና አገልግሎትን በሚያካትት መንገድ ተዘርዝሯል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተካተቱት ውስጥ በተወሰነ መለክ ግለጽነት የሚጎድላቸው፣በጣም በጥቅሉ በመቀመጣቸው ዝርዝር መሆንን የሚጠይቁ፣በሌላ መልኩ ደግሞ በልዩ ጥቅም ውስጥ ያልታሰቡ ነገር ግን የተካተቱ እንዲሁም የአዋጁ አካል እንዲሆኑ የሚጠበቁ ነገር ሳይካተቱ የታለፉ ጉዳዮች ስላሉ በቅድም ተከተላቸው የተወሰኑትን እንመልከት፡፡
ግልጽነት የሚጎደላቸው ፤
በረቂቁ ላይ ከተቀመጡት እና የከተማ መስተዳድሩ በዙሪያው በሚገኘው ዞን ውስጥ ማከናወን ካለበት ተግባራት አንዱ “የተፋሰስ ልማት” ነው፡፡ የከተማ መስተዳድሩ የውሃ ጉድጓድ በሚቆፍርበት፣በሚያመነጭበት፣መስመሮቹ በሚያልፉበት አካባቢ የተፋሰስ ልማት በራሱ ወጭ የሚያከናውንበት ሁኔታ እንደሚያመቻች ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የተፋሰስ ልማት ማለት የአካባቢው ቅርጽ እዳይቀየር ለማድረግ መልሶ መገንባት ነው? ወንዞችን ማጎልበት ነው? ደን መትከል ነው? ይዘቱ አይታወቅም፡፡
በተጨማሪም መስተዳድሩ “ያመቻቻል” ማለት ግዴታ አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነት አገላለጽ ኋላ ላይ ለማስፈጸም ያዳግታል፡፡
ከዚሁ ጋር መነሳት ያለበት ውሃ የሚወጣበት ወይንም የሚያልፍበት ከተማ፣ቀበሌ፣በአስተዳደሩ ወጪ ውሃ የማቅረብ ግዴታ የሚመለከተው ነው፡፡ ከገፈርሳ ለሚመጣው ውሃ፣ለቡራዩ ከተማ በሙሉ ማቅረብን ወይንስ ለሚገኝበት ቀበሌ ወይንስ መስመሩ የሚያልፍበትን አካባቢ የቱን እንደሚመለከት ግልጽነት ይጎድለዋል፡፡ ከገፈርሳ የሚነሳው ውሃ ጀሞ ወደ ሚባለው ሠፈር ቢሄድና በመካከል በሰበታ ከተማ የሚተዳደርን መንደር ቢያቋርጥ የከተማ መስተዳድሩ ውሃ የማዳረስ ግዴታው ለመንደሩ ወይንስ ለቀበሌው ወይንስ ለሰበታ ከተማ በሙሉ ነው?
ሌላው ግልጽ መሆን ያለበት ነገር በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ወጣቶች በከተማው ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል መጠቀም እንዳለባቸው ቢገለጽም እንደማንኛውም ሠራተኛ እኩል ተወዳድረው ነው? ወይንስ በድጋፍ እርምጃ መልክ (Affirmative Action) መልክ ነው፡፡ በጥቃቅን እና አነስተኛ ማደራጀትን ይጨምራል ወይስ በቅጥር ብቻ ነው?
በረቂቁ ላይ ከተካተቱት በጎ ነጥቦች አንዱ አፋን ኦሮሞ በመስተዳድሩ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን መወሰኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ሁለትና ከእዚያ በላይ ቋንቋዎች በአንድነት ሥራ ላይ ሲውሉ የሚፈጠር ችግር አለ፡፡ ይኸውም፣ መስተዳድሩ አገልግሎት ሲሰጥ አፋን ኦሮሞ አስተርጓሚዎችን በየመሥሪያ ቤቱ በመመደብ አልበለዚያም በአማርኛ አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞች እንዳሉ ሁሉ በትይዩ እኩል በአፋን ኦሮሞ አገልግሎት የሚሰጡ ተጨማሪ የሠው ኃይል መቅጠር ይጠበቅበታል፡፡ ካልሆነም ደግሞ ሁለቱንም ቋንቋ ብቻ የሚችሉ መሆን አለባቸው ማለት ነው፡፡
እያንዳንዳቸው አማራጮች የራሳቸው ጥቅምና ጉዳት፣ መስተዳድሩንና ክልሉን ለግጭት ስለሚዳርጉ፣እንዲሁም የሕገመንግሥት ጥያቄም ስለሚያስነሱ በአዋጁ ላይ በምን ዓይነት ሁኔታ ሥራ ላይ መዋል እንዳለበት መቀመጥ ይገባዋል፡፡
ረቂቁ ላይ ከተቀመጡ የመስተዳድሩ ግዴታዎች አንዱ ለክልሉ አርሶ አደሮች የገበያ ማእከላት ማመቻቸትን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ በርካታ ክፍተቶች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው መስተዳድሩ ማዘጋጀት ያለበት ባዶ ቦታ ላይ (Open Market) ወይንስ ሕንጻ ነው የሚለው ሲሆን ቀጥሎ የሚመጣው ደግሞ ለክልሉ አርሶ አደሮች በሙሉ የመሆኑ ነገር ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ለሚገኝ ብሔሩ ምንም ይሁን ምን፣ለሁሉም ገበሬ በፈለጉት መንገድ ቢደረጁ ከቦታ እና ከሌሎች ግብኣት አንጻር ማሳካት የሚቻል አይመስልም፡፡ ከአርሶ አደሮቹ ብዛት፣ከምርታቸው መለያየት አንጻር የከተማ መስተዳድሩ በምን መልኩ ይተገብረዋል በዙሪያው ላሉት አርሶ አደሮች ቢሆን ተጠየቃዊ ይሆናል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተቀመጡት ጉዳዮች አንዱ የአዋጁን አተገባበር የሚከታተልና የሚስፈጽም ምክር ቤት መቋቋሙ ነው፡፡ የምክር ቤቱ ተጠሪነት ለፌደራል መንግሥቱ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ በተለምዶ መንግሥት በመባል የሚታወቀው አስፈጻሚው አካል ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ የከተማ መስተዳድሩ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥቱ (በብዙ መልኩ ለአስፈጻሚው) ሆኖ ሳለ፣ የከተማውን እና የክልሉን ጉዳይ የሚመለከተውን ምክር ቤት ተጠሪነት ለፌደራል መንግሥት ማድረግ ተገቢነት አይኖረውም፡፡ የፌደራልና የክልል ጉዳዮችን የሚያስተባብር ወይንም የሚያሳልጥ ተቋም ቢኖር ለዚያ፤ አልበለዚያም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢሆን ይመረጣል፡፡
ልዩ ጥቅም ሳይሆኑ የተካተቱ፤
በረቂቁ ውስጥ መካተት የሌለባቸው ነገር ግን የተካተቱ ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ የመጀመሪው የመስተዳድሩ የራሱ የውስጥ ጉዳይ ሲሆን ሁለተኛው ግን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚጠይቅና በልዩ ጥቅምነትም መካተቱ አጠራጣሪ የሆነ ነው፡፡
ቀዳሚው፣ በከተማው ክልል ውስጥ የሚኖሩ ብሔራቸው ምንም ይሁን ፣በተለያዩ ምክንያት በልማት ሲነሱ ካሳ መክፈልና ማቋቋምን በተመለከተ ኦሮሚያ ክልልን የሚመለከት ባለመሆኑ በልዩ ጥቅም ውስጥ መካተት የለበትም፡፡ ከተማ መስተዳድሩ በልማት ምክንያት ስለሚፈናቀሉ ሰዎች በራሱ የማቋቋምና ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ወደ ሌላ ክልልም ማስፈርም የለበትም፡፡ ሌሎች መፍትሔዎችን መከተል ይገባዋል፡፡ በመሆኑም በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደ ኦሮሚያ ልዩ ጥቅም መወሰድ የሚገባው አይደለም፡፡
ሁለተኛው ጉዳይ የአፋን አሮሞ የሥራ ቋንቋነትን የሚመለከት ነው፡፡ በቅድሚያ፣ የኦሮሚያ ክልል በከተማ መስተዳድሩ ላይ ሊኖሩት ከሚችሉት ልዩ ጥቅሞች ውስጥ ሊካተት መቻሉ አጠራጣሪ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ውሳኔው ተገቢ መሆኑ ባያጠራጥር እንኳን የሕገመንግሥት ጥያቄ ማስነሳቱ ግን አይቀርም፡፡ መነሻው ደግሞ፣ የፌደራል መንግሥቱ በተቋማቱ በሥሩ ለሚገኙ መስተዳድሮች የሥራ ቋንቋው አማርኛ እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ ላይ መደንገጉ ነው፡፡ በመሆኑም፣አዋጁ ከመጽደቁ በፊት ሕገመንግሥቱን ማሻሻል ይገባል፡፡
መካተት ሲኖርባቸው ያልተካተቱ፤ ረቂቁ ላይ መካተት የነበረባቸው ነገር ግን ያልተካተቱ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱን ብቻ እንመለከት፡፡ በመጀመሪያ፣ አዋጁ መተግበር ሲጀምር በመስተዳድሩ እና በክልሉ መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን ለመፍታት የታሰበ ተቋም አለመኖሩ ነው፡፡
የአካባቢ ብክለትን ለሚመለከት አለመግባባት ፍርድ ቤትን መጠቀም እንደሚቻል ተቀምጧል፡፡ ከዚያ ውጭ ባሉት ጉዳዮች ሊነሱ የሚችሉ አለመግባባቶችን፣ከፖለቲካዊ ውሳኔ ባለፈ፣ በየትኛው ተቋም ይፈታሉ? በሚቋቋመው ምክር ቤት እንዳይባል እኩል አባላት ከክልሉም ከመስተዳድሩም ስለሚወከሉበት በስምምነት ከመጨረስ ባለፈ ዳኝነት መሥጠት አይቻላቸውም፡፡ በፌደሬሽን ምክር ቤት እንዳሆን አንድም ጉዳዩ የሕገመንግሥት ላይሆን ይችላል፡፡ አንድም፣ከአዲስ አበባ መስተዳድር ወኪል በሌለበት ተቋም የሚሠጠው ውሳኔ ተገቢ አይሆንም፡፡
ሌላው፣ ከተማዋ ከፌደራሉ በተጨማሪ የክልሉም በርእሰ ከተማ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በከተማዋ ላይ ምን ዓይነት መብቶች እንዳሉት የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ከመስተዳድሩ የሚያገኛቸውን ጥቅሞች እንጂ በራሱ ማከናወን ስለሚችላቸው ሁኔታዎች አልተቀመጠም፡፡ የከተማው መሥተዳድር ተጠሪነቱ ለፌደራሉ ስለሆነ የፌደራሉ መንግሥት መብቶቹን በራሱ ሊወስን ይችላል፡፡ የክልሉ ግን ሁልጊዜም በመስተዳድሩ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ የፌደራሉ፣የመስተዳድሩ እና የክልሉ መንግሥት ከተማዋን በተመለከተ በተለይም ግንባታን በሚመለከት የሚኖራቸው ግንኙነት በአዋጁ መቀመጥ አለበት፡፡ በሌሎች የፌደራል ከተሞች ላይ ይህንን የሚያሳልጥ፣’ስታንዳርድ’ የሚያስቀምጥ ‘ብሔራዊ የዋና ከተማ የፕላን ኮሚሽን’ አላቸው፡፡
በሦስተኛነት መቀመጥ ያለበት የከተማው የጸጥታ አጠባበቅ እና የክልሉን ግንኙት የሚመለከት ነው፡፡ የፌደራሉ እና የከተማ መስተዳድሩ የፖሊስ ግንኙነት በአዋጅ ተለይቷል፡፡ የፌደራል እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ጥበቃ የሚከናወነው በፌደራል ፖሊስ ሲሆን የመስተዳድሩን ደግሞ በአዲስ አበባ ፖሊስ ነው፡፡ በከተማው ውስጥ የሚገኙ የክልሉ ተቋማትን ጥበቃ የሚያደርገው ማን እንደሆነ እንዲሁም የሦስቱም መንግሥታት የፖሊስ ግንኙነት መታወቅ አለበት፡፡ እዚሁ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ኦሮሚያ ክልልን የሚመለከቱ ነገር ግን በዋና ከተማው ላይ ሰላማዊ ሰልፎች ሲኖሩ ጥበቃ የሚደረግበትን፣ማወቅ ያለበት ተቋም ማን እንደሆነ ወዘተ መገለጽ ይኖርበታል፡፡
በጥቅሉ፣አዋጁ ከመጽደቁ በፊት በአግባቡ መፈተሽን ይፈልጋል፡፡ የርዕሰ ከተማ አስተዳደር ውጥረት እንደሚኖርበት ይታወቃል፡፡ በአንድ በኩል የፌደራል መንግሥቱ እንደ ብሔራዊ ከተማ፣መገለጫ መውሰድ፣ ብሔራዊ ውክልናና እና የባህል መለያ እንዲሆን ስለሚፈለግ፤ በሌላ ጎኑ ደግሞ የአካባቢው ሕዝብ ደግሞ ቅድሚያ ለራሱ በማሰብ በራስ መንገድ ማስተዳደር እና የራሱ መገልጫ እንድትሆን የመፈለጉ ጉዳይ ሁልጌዜም የማይጠፋው ውጥረት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ሲሆን ደግሞ፣የክልልም ይጨመርበታል፡፡
የፌደራል ሥርዓት የሚከተሉ አገራት ዋና ከተሞቻቸውን ከሦስቱ በአንዱ መንገድ ማዋቀራቸው የተለመደ ነው፡፡ አንደኛው፣ ዋና ከተማው ከክልል ጋር በእኩልነት እንዲቋቋም በማድረግ እኩል ሥልጣን እንዲኖረው በማድረግ ነው፡፡ ሞስኮ፣በርሊን፣ቪየና እና ብራሰልስ በዚህ መልኩ የተቋቋሙ በመሆናቸው ለፌደራሉ መንግሥት ተጠሪነት የለባቸውም፡፡ በሽግግር ወቅቱ ጊዜ፣አዲስ አበባም፣ክልል ዐስራ አራት ተብላ የክልልነት ደረጃ ነበራት፡፡
ሁለተኛው መንገድ ደግሞ፣ የፌደራሉ መንግሥት መቀመጫ በአንድ ወይንም ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች ውስጥ ሆኖ የሚቋቋምበት ሥርዓት ነው፡፡ የፌደራሉ መንግሥት የሚያስተዳድረው መሬት ወይንም ግዛት የለም፡፡ ደቡብ አፍሪካ፣ሲውዘርላንድ፣እና ካናዳ ይሄንን ዓይነት አካሄድ መርጠዋል፡፡
ሦስተኛው በፌደራሉ መንግሥት ሥር የሚገኝ ከተማ እና ለዚህም የሚሆን የተለየ ግዛት በመከለል የሚቋቋሙ ከተሞች ናቸው፡፡ የከተሞቹም ተጠሪነት ለፌደራሉ መንግሥት ይሆናል፡፡ በርካታ አገራት ዋና ከተሞቻቸውን በዚህ መንገድ ነው ያቋቋሙት፡፡ አዲስ አበባም ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ክልልነቷ ቀርቶ የፌደራል ከተማ መሆኗ ይታወቃል፡፡
የፌደራል ከተሞች ከሌሎች ክልሎች (የፌደሬሽኑ አባላት) የሚለዩባቸው የአስተዳደር ጠባይ አሏቸው፡፡ የአዲስ አበባ ደግሞ ከክልልም ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ካሉ የፌደራል ዋና ከተሞችም የሚለያት ባሕርይ ስላላት ይህንኑ የሚመጥን ብሎም አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት በሚመች መልኩ ከኦሮሚያ ክልልም ጋር ሆነ ከፌደራሉ ጋር የምትተዳደርበት እና የምትመራበት ሕግ ነው የሚያስፈልጋት፡፡