የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የሰላማዊ ዜጎች እስር ቢኖርም፤ በአንዳንድ ቦታዎች አሁንም ተቃውሞች እንደቀጠሉ ናቸው
(አዲስ ሚዲያ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓም ተግባራዊ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች በጅምላ እየታሰሩ ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል እስሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ በቅርብ ርቀት የምትገኘው ሰበታ ከተማ ብቻ ከ አንድ ሺህ በላይ ተጠርጣሪ ናቸው ያላቸውን ነዋሪዎችን ማሰሩን ራሱ መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን፤ በሌሎችም የኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከተሞችና ወረዳዎችም በተመሳሳይ መልኩ እስሩ መቀጠሉን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን እና ጎንደር ዞን መንግሥት የነዋሪዎቹን ትጥቅ ለማስፈታት ወደ ወረዳዎች እና ገጠር ቀበሌዎች የፀጥታ ኃይሉን ቢያሰማራም ከህዝቡ የአፀፋ ርምጃ በመወሰዱ በርካታ ወታደሮችና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ህዝባዊ ተቃውሞው ከተጀመረበት ቀን አንስቶ የመንግሥት የፀረ አገዛዝና ጭቆና ተቃውሞ እንደቀጠለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በአፋር ክልልም እንዲሁ የሰላማዊ ዜጎች እስሩ የቀጠለ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በአፋርኛ በማዜም የምትታወቀው ድምፃዊት መፈራ መሐመድ ላሌን ጨምሮ አስር ሰላማዊ ዜጎች በአሳይታ ከተማ መታሰራቸው ታውቋል፡፡

ድምፃዊት መፈራ መሐመድ ላሌ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያ ትግበራ ላይ መንግሥት እንደ ኢሳት፣ ኦ.ኤም.ኤን. የመሳሰሉ መገናኛ ብዙኃን መከታተልና መረጃ መለዋወ ላይ መመሪያው እገዳ ጥሏል፡፡ በተጨማሪ ያልተፈቀደ ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ፣ ለህዝብ አገልግሎት አለመስጠት፣ በትምህርትና በስፖርት ማዘውተሪያ አድማ ማድረግ በክልከላው ተካተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር የመንግሥትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትግበራባለመቀበል በድጋሚ ለ3ኛ ጊዜ ከቤት ያለመውጣት አድማ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ አስቀድሞ በኢትዮጵያ የመንግሥትን በደልና ብልሹ አሰራር ለመቃወምና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ቀድሞም ቢሆን ለዓመታት ፈፅሞ የተከለከሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
መንግሥት ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ዓመት ያህል ያለማቋረጥ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቀጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማርገብ በሚል ባለፈው መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ተግባራዊ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ኢንተርኔትን በተለይም ማኀበራዊ ሚዲያ፣ በውጭ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተዘጋጅተው ለህዝቡ አማራጭ የመረጃ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ ያሉ እንደ ኢሳት፣ ኦ ኤም ኤን ያሉ መገናኛ ብዙኃን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዳይሰራጩ ከማፈን በተጨማሪ ህዝቡም መረጃ መለዋወጥና መስማትም እንደሌለበት በአዋጁ መከልከሉ ይታወሳል፡፡
አዋጁን ተከትሎ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ክልል ኮንሶ ፣ ጋሞ ጎዳ ዞን፣ በአፋርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል (ኦጋዴን) የተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች በመዘዋወር ድንገት ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ የተለያዩ የወርቅ ጌጣጌጦችን፣ ገንዘብ፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ ከመወስድ በተጨማሪ ጠርጥረንሃል ያሉትን ሰው ያለምንም ፍርድ ቤት ማዘዣ እየደበደቡ በመውሰድ ወዳልታወቀ ስፍራ እንደሚያስሯቸው ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ምክንያት ከወትሮ በተለየ መልኩ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ ነዋሪው በፍርሃት ድባብ ውስጥ እንደሚገኙ በመጠቆም በማኀበራዊና ንግድ እንቅስቃሴዎች ላይም አለመረጋጋቶች እንደሚስተዋሉ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
መንግሥትበአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት አፈና እና ቁጥጥሩን አጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ ዋነኞቹ የህዝባዊ ተቃውሞ አስተባባሪዎች መካከል የአማራ ተጋድሎና የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች ከመንግሥት ርምጃ ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን የሚችል አዳዲስ የትግል ስልቶችንም በቅርቡ ሊጀምሩ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡ በተለይ በውጭ የሚኖሩ የመንግሥትን አገዛዝ የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያን በስልጣን ላይ ካለው ገዥው ስርዓት ለውጥ በኋላ በኢትዮጵያ ሊመሰረት ስለሚገባው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ትግበራ በቪዥን ኢትዮጵያ እና በኦሮሞ ማኀበረሰብዓለም አቀፍ የህግ ባለሙያዎች ማኀበር አስተባባሪነት ከወዲሁ በሰሜን አሜሪካ ዋሸንግተን ዲሲ እበእንግሊዝ ለንደን ምክክር መጀመራቸው ታውቋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዜጎቹ የጉዞ ክልከላ አወጣ
የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለይ በአማራና ኦሮምያ ክልሎች ሁከቱ አሁንም ቀጥሎ በመቶዎች ለሚቆጠሩ መሞት፥ በሺዎች ለሚገመቱ ሌሎች መታሠር፥ መጎዳትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት እየደረሰ ባለበት ሁኔታ፥ ዜጎቹ አስፈላጊ ካልሆነ በቀር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄዱ አስጠንቅቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ ተግባራዊ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ደንግጓል። ጥቅምት 4 በወጣ መመሪያም ግለሰቦች መገናኛ ብዙሃን ሲከታተሉ፥ በስበሰባዎች ሲካፈሉ፥ ከባዕዳን መንግሥታት ወይም ድርጅቶች ጋር ሲገናኙ እንዲሁም የሰዓት እላፊውን ሲተላለፉ ቢገኙ ያለፍርድ ቤት ማዘዣ ተይዘው ሊታሠሩ እንደሚችሉ ያብራራል። መመሪያው በተጨማሪም፥ የዩናይትድ ስቴትስና የሌሎች ባዕዳን ሃገሮች ዲፕሎማቶች፥ ከኢትዮጵያ መንግሥት አስቀድመው ፈቃድ ሳያገኙ ከአዲስ አበባ ከተማ 40 ኪሎ ሜትር ውጪ እንዳይጓዙ ይከለክላል። ይህም ኤምባሲው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎችን የመርዳት አቅሙን ክፉኛ ይጎዳል ብሏል።
የኢንተርኔትና የቴሌፎን አገልግሎቶች አልፎ አልፎ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ውሱን በመደረጋቸው ወይም ሙሉ በሙሉ ስለሚቋረጡ፥ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዜጎቹን የመርዳት አቅሙን ያግዳል ሲልም አብራርቷል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ አሜሪካውያን አማራጭ የመገናኛ ዘዴ እቅዶችን እንዲያዘጋጁ፥ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸውም አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ይህን እንደሚመስል እንዲያሳውቁም የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው በዚሁ ማስጠንቀቂያው ጠይቋል።
አሜሪካውያን ሰልፎች ከሚካሄዱባቸውና ሕዝብ በብዛት ከሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ራሣቸውን እንዲያርቁ፥ የሚሄዱባቸውን አካባቢዎች በደንብ እንዲቃኙና ደህንነታቸው የሚጠበቅበት መሆኑን እንዲያረጋግጡም መክሯል። መንግሥት ሰልፎቹ ሰላማዊ ቢሆኑ እንኳ ምላሹ በኃይል ሊሰጥና ጥይት ሊተኩስ እንደሚችልም አስታውሱ ብሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች ስለ ደህንነታቸው በንቃት እንዲከታተሉና አመጻ ሊፈጠርባቸው ከሚችሉ አካባቢዎች መውጣት በሚፈልጉበት ጊዜ ካደገኛ ሥፍራ ፈጥኖ መውጪያ ዘዴዎቻቸውን አስቀድመው ማዘጋጀት እንዳለባቸውም አሳስቧል።
የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመጨረሻም፥ የአሜሪካ መንግሥት ሠራተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ኦሮሚያን፥ አማራን፥ ሱማሌን፥ ጋምቤላን፥ ኢትዮጵያና ኬንያ የሚዋሰኑበትን ድንበር አካባቢ ማለትም ደቡብ ግዛቱን እንዲሁም ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚዋሰኑበትን ሰሜኑን ግዛት ጨምሮ ወደ በርካታ አካባቢዎች እንዳይሄዱ አስጠንቅቋል። ወደተጠቀሱት አካባቢዎች ከሥራ ጋር የተያያዙ ጉዞዎች ፍቃድ የሚያገኙትም በሁኔታዎች መሠረት ይሆናል ብሏል። ወደ አዲስ አበባ በሚደረጉ ጉዞዎችና ከተማ ውስጥ በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ላይ ግን ምንም እገዳ የለም ካለ በኋላ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመገናኛ ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ ግን፥ አሜሪካውያን ዜጎች በጉዞ መርሃ-ግብሩ ማለትም በ STEP አማካይነት መመዝገብን ጨምሮ፥ የሞባይል ቴሌፎን ቁጥሮቻቸውን፥ አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲ በማስመዝገብ የደህንነት መረጃዎችን በጹሑፍ መልዕክት ሊያገኙ ይችላሉ ብሏል ሲል የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይም የእስራኤል መንግሥትም ዜጎቿ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደረጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቋ ታውቋል፡፡
የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል መንግሥት ለተቃዋሚዎችና ለሲቪክ ማኅበራት ሰፊ የፖለቲካ ዕድል እንዲሰጥ ጠየቁ
ብርሃኑ ፈቃደ
– ፖለቲካዊ አለመግባባቶች በምክክር እንዲፈቱና ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የመንግሥት የቤት ሥራ መሆኑን አሳሰቡ
– ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በአገሪቱ ጉዳይ ተነጋገሩ

ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ የገቡት የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በፖለቲካ መስክ ለተቃዋሚዎችም ሆነ ለሲቪክ ማኅበራት ሰፊ ዕድል እንዲሰጥ ጠየቁ፡፡ የፖለቲካ አለመግባባቶች በውይይትና በምክክር እንዲፈቱም አሳሰቡ፡፡
መርከል ማክሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንደተናገሩት፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መደመጥ አለባቸው፡፡ ሲቻልም በተወካዮች ምክር ቤት ጭምር እንዲሳተፉ በማድረግ ድምፃቸው እንዲሰማ፣ ውይይትና ክርክር እንዲያደርጉ መንገዱን ማመቻቸት ይገባል፡፡
‹‹መነጋገር በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በተነጋገርንበት ወቅት ገልጫለሁ፡፡ የሲቪክ ተቋማትን ማሳተፍና በጠረጴዛው ዙሪያ እንዲገኙ መጋበዝ ይገባል፡፡ ጥሩ ትምህርት ቤቶች ሠርታችኋል፡፡ ከጎበኘኋቸው የአፍሪካ አገሮች ይልቅ እዚህ ብዙ ጥሩ ነገሮች ተሠርተዋል፡፡ ነገር ግን ለወጣቶች ሥራ መፍጠር ካልቻላችሁ የተሠራው ሁሉ ምንም ትርጉም አይኖረውም፤›› ያሉት መራሒተ መንግሥት መርከል፣ ‹‹ከአገሪቱ ግማሽ ያህሉ ሕዝብ በወጣቶች የተገነባ ነው፡፡ ወጣቶች ደግሞ ስሜታቸውን ባገኙት መንገድ መግለጽ ይፈልጋሉ፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎችና በሌሎችም የሚሰማቸውን ለመግለጽ ይፈልጋሉ፡፡ ቅሬታውቸውን ሲገልጹም ትዕግሥት ላይኖራቸው ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ በውይይትና በመነጋገር ጥሩ የመፍትሔ ሐሳቦች እንደሚመነጩ ሲመክሩም፣ በአገራቸው የፖለቲካ ሥርዓት በውይይትና በመነጋገር አብዛኞቹ ለውጦች እንደሚመነጩ አብራርተዋል፡፡ በዚህም አገር የቱንም ያህል አስቸጋሪና ከባድ ቢሆን በመነጋገር ችግሮችን መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡
መንግሥት እንዲህ ያሉ አሳሳቢ ችግሮችን ለመፍታት ወጣቶችን በኢኮኖሚ መስክ በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንደሆኑ ከማድረግ ባሻገር፣ ነፃ ሚዲያም ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ህልውና ወሳኝ እንደሆነ በመግለጽ መንግሥት ትኩረትም ቦታም እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
‹‹ዴሞክራሲያችን እንጭጭና ያልጠነከረ በመሆኑ በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ በየፈርጁ ያሉብንን ችግሮች ከማመን ተቆጥበን አናውቅም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በአገሪቱ ይበልጥ የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያሰፉ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ከመራሒተ መንግሥት መርከል ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት አስታውቀዋል፡፡ አሳታፊና ለበርካቶች ዕድል የሚፈጥሩ፣ ለሲቪክ ማኅበራትም ቦታ የሚሰጡ ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ጠቁመዋል፡፡ በምርጫ ሥርዓቱ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉም አስታውቀዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የመርከል ማብራሪያዎች በአብዛኛው በፓርላማው በፕሬዚዳንቱ ከቀረበው የመንግሥት የሥራ ዕቅድ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ነበሩ፡፡
ወጣቶች ሥራ በማጣት በዚህም ሳቢያ በተፈጠረባቸው መከፋትና ተስፋ መቁረጥ መንግሥት ላይ ተቃውሞ ማሰማታቸው ተገቢ እንደሆነ ያመኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት የተነሳበትን ተቃውሞ ትክክለኛ መሆኑን እንደሚቀበልም አስታውቀዋል፡፡ ከ15 ሚሊዮን ያላነሱ ወጣቶች በሥራ ፍለጋና በትምህርት ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ መንግሥት የሥራ ዕድሎችን በሚፈለገው መጠን ማሟላት እንዳልቻለ አምነዋል፡፡
ይሁንና ተቀባይነት ያላቸውን ተቃውሞች ተገን በማድረግ የተከሰቱት ብጥብጦችና ንብረት የማውደም ዕርምጃዎች ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል፡፡ በርካታ ፋብሪካዎች፣ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የገነቧቸው ኢንዱስትሪዎችና ሀብቶች መቃጠላቸውን በመግለጽ፣ እንዲህ ያሉትን ብጥብጦች ጉዳት ያስከተሉት ‹‹ከውጭ ጠላቶች›› ጋር የሚያብሩና ‹‹መሣሪያ የታጠቁ›› አካላት ናቸው በማለት በአገሪቱ የተቀጣጠለውን ፖለቲካዊ ቀውስ ለማብረድ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገግ በኋላም በአገሪቱ አንድም ብጥብጥ እንዳልተከሰተ ጠቁመዋ፡፡
የተከሰቱትን ግጭቶችና ብጥብጦች ለመቆጣጠር የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት ዕርምጃ ተመጣጣኝነትን በሚመለከት ተጠይቀውም፣ ‹‹መሣሪያ ካነገቱ ታጣቂዎች ጋር መነጋገር የሚቻለው በመሣሪያ ብቻ ነው፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ይሁንና የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት ዕርምጃ ተመጣጣኝ ስለመሆኑና ከሚፈቀድላቸው በላይ ኃይል ስለመጠቀማቸው ምርመራ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡
በተከሰተው ቀውስ ምክንያት የሟቾች ቁጥር ከ500 በላይ ስለመድረሱ የተጠየቁት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ግጭቶቹን የሚያባብሱት የታጠቁ ሰዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሟቾችን ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅበው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩንም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እያጣራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከሰቱ ግጭቶች የሟቾች ቁጥር 190 ያህል እንደደረሰ፣ ከዚህም ቀደም በተከሰተው ግጭት በኦሮሚያ 178 ሰዎች፣ በአማራ ክልል ደግሞ 120 ሰዎች መሞታቸውን ኮሚሽኑ ይፋ እንዳደረገ በመጥቀስ ከጀርመን ጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የተቀሰቀሱ ግጭቶችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች የሚወስዷቸው ዕርምጃዎች ተመጣጣኝነት ላይ የሚነሱትን ክሶች መነሻ በማድረግም፣ መንግሥታቸው የጀርመንን ድጋፍ እንደሚሻና ሥልጠና እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡ ብጥብጥን ለመቆጣጠርና ግጭቶች ደም አፋሳሽ ከመሆናቸው በፊት በሠለጠነ መንገድ ለመቆጣጠር የፀጥታ ኃይላቸውን ጀርመን እንድታሠለጥንላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ የተቀበሉት መርከል፣ ድጋፍ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱ መሪዎች በተሰጠው መግለጫ ወቅት መራሒተ መንግሥት መርከል ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ስለሚያደርጉት ውይይት አጀንዳ ምንም ዓይነት ማብራሪያ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች በፀጥታና በደኅንነት ጉዳዮች፣ ስደተኞችን በተመለከቱ ተግባራትና በሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በሁለትዮሽ ውይይታቸው ወቅት መነጋገራቸው ታውቋል፡፡
ጀርመን በኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ የተቃዋሚ ቡድኖች መካከል እንደ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ያሉት የሚገኙባት እንደመሆኗ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለቱ መሪዎች ተነጋግረው እንደሆነ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ፣ መሪዎቹ እንዲህ ባሉ ነጥቦች ላይ በተናጠል እንዳልተነጋገሩ ገልጸዋል፡፡
መራሒተ መንግሥት መርከል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉትን ውይይት አጠናቀው፣ በጀርመን ድጋፍ በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባውንና በቀድሞው የታንዛኒያ መሪ ጁሊየስ ኔሬሬ ስም የተሰየመውን የፀጥታና የደኅንነት መሥሪያ ቤት መርቀዋል፡፡ ስድስት ያህል የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግረው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከመራሒተ መንግሥት መርከል ጋር በአገሪቱ በተካሄዱ ተቃውሞዎችና የመንግሥት ምላሽ፣ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡
አገሪቱ በወሳኝና አሳሳቢ ጊዜ ላይ እንዳምትገኝ የገለጹት ዶ/ር መረራ መንግሥት እንደወትሮው ‹‹የተቀባባና የተሽሞነሞነ መግለጫውን›› ትቶ ትክክለኛ ለውጥ በአፋጣኝ እንዲያመጣ፣ የሚደረጉ ለውጦችም ወደፊት በታሳቢነት ሳይሆን አሁኑኑ ሊደረጉ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ አንገላ መርከል የአገሪቱ ተቃዋሚዎች፣ ሲቪክ ማኅበራትና ሌሎችም የሚገኙበትን ሁኔታ እንደሚገነዘቡና በሚደርስባቸው ጫናም ሐዘኔታ እንዳደረባቸው ዶ/ር መረራ ገልጸዋል፡፡
አንገላ መርከል ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ወደፊት እንደሚጠብቁ የገለጹት ዶ/ር መረራ፣ እሳቸውን ጨምሮ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን፣ የሴቶች ማኅበራት ተወካዮች በተገኙበት ከመራሒተ መንግሥት መርከል ጋር መነጋገራቸው በማውሳት ሪፖረተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን ሊያባብሰው ይችላል ተባለ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተለያዩ ቦታዎች ይሰፍራል ተብሎ የሚጠበቀው የመከላከያ ሰራዊት ከዚህ በፊት ይወስድ የነበረውን የሃይል ዕርምጃ በማጠናከር ተጨማሪ አፈናን አግባራዊ እንደሚያደርግ የስብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ገልጸዋል።
በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግስት ከዜጎቹ የተነሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በሃይል ለመቆጣጠር ፍላጎት እንዳለው ማሳያ ነው ሲሉ በድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆርን ገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን ያወሳው ሂውማን ራይትስ ዎች ጥያቄ ያላቸው አካላት ምላሽን ካላገኙ ተቃውሞ ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል አሳስቧል።
ለአለም አቀፉ ማህበረሰ ስጋት እየሆነ የመጣው የጸጥታ ሃይሎች እርምጃና ተቃውሞ ቀጣይ የሚሆን ከሆነም ሃገሪቱ ሊቀለበስ ወደ ማይችል የሰብዓዊ መብት ቀውስ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ሂውማን ራይትስ ዎች በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
በርካታ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰብዓዊ መብት ረገጣን ሊያባብስ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለስድስት ወር የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊት ሊነሳ እንደሚችል የመንግስት ባለስልጣናት መግለጻቸውን ብሉምበርግ ማክሰኞ ዘግቧል።
“የስድስት ወሩ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሙሉ ለሙሉ ላያስፈልገን ይችላል ሲሉ ለዜና አውታሩ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከተቀመጠው ጊዜ በፊት ችግሮቹን ልንቆጣጠር እንችላለን ብለዋል።
ምንጭ፡-ኢሳት
በዲላ ከተማ በተቀሰቀሰ ደም አፍሳሽ ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት አለፈ
ዮናስ ዓብይ እና ውድነህ ዘነበ
ባለፈው ሳምንት ዓርብ መስከረም 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን የተቀሰቀሰው ደም አፍሳሽ ግጭት፣ ለበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ምክንያት ሆነ፡፡
ከጌድዮ ዞን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ባለፈው ዓርብ ከቀኑ 4፡30 ሰዓት ተጀምሮ እስከ ቅዳሜ ድረስ በቀጠለው ደም አፍሳሽ ግጭት የ63 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ይጠቁማሉ፡፡ ከጌዲዮ ብሔረሰብ አባላት 52 ሰዎች፣ ከሌሎች ክልሎች መጥተው በዲላ ከተማ ከሚኖሩ ውስጥ ደግሞ 11 የሚደርሱ ግለሰቦች ሕይወት ማለፉን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በዚህ ግጭት መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ የሕዝብና የጭነት ተሽከርካሪዎችና የቤት መኪኖች በእሳት ጋይተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ግን ቁጥሩ የተጋነነ ነው ይላል፡፡
የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አህመድላዲን ጀማል በተቀሰቀሰው ግጭት የሰው ሕይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
ነገር ግን ምክትል ኮሚሽነሩ እንደገለጹት፣ የሟቾችን ቁጥርና የደረሰውን የንብረት ውድመት የሚያጣራ ግብረ ኃይል ወደ ሥፍራው በመላኩና ሪፖርቱን ባለማጠናቀቁ፣ የሟቾችንም ሆነ የደረሰውን የንብረት ውድመት በቁጥር ማስደገፍ አይቻልም፡፡
መስከረም 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ከረፋዱ 4፡30 ሰዓት ላይ የጌዲዮ ተወላጅ የሆኑ ሰዎች በተለይ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የመጡ የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥፋት መፈጸማቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ምንጮች እንደገለጹት የጥቃቱ ማጠንጠኛ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ሰዎች በዞኑ ውስጥ ሀብትና ንብረት ማፍራታቸው፣ በአንፃሩ ደግሞ የጌዲዮ ብሔረሰብ አባላት በድህነት ውስጥ ነን በሚል ምክንያት ለዓመታት በአካባቢው የሚኖሩ የሌሎች ክልል ተወላጆች ከአገር እንደሚወጡ መጠየቃቸው ነው፡፡
በዚህ ሳቢያ የከተማው ነዋሪዎች ቤቶቻቸውና ንብረቶቻቸው ከመውደማቸውም በተጨማሪ ግድያ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ከከተማ እንዲወጡ የተደረጉም አሉ፡፡
ለዚህ ግጭት መነሻ የሆነው በዲላ ከተማ ‘ታይዋን’ ተብሎ በሚጠራው የገበያ ሥፍራ አካባቢ በጌዲዮ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየንና በከተማው ነጋዴዎች መካከል የመሬት ይገባኛል ጥያቄ በፍርድ ቤት እልባት ማግኘቱ ነው፡፡
በሁለቱ አካላት መካከል ሲካሄድ የቆየው የፍርድ ቤት ክርክር ለከተማው ነጋዴዎች መወሰኑ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ በውሳኔው የተነሳም የአካባቢው ነዋሪዎች ቁጣ ወደ ደም አፍሳሽ ግጭት ተቀይሯል፡፡
የእዚህ ግጭት ሰለባ የሆኑ የዲላ ከተማ ነጋዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በከተማ ከሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች አባላት መካከል 11 የሚሆኑ ሞተዋል፡፡ እንዲሁም ከጌዲዮ ወገኖች 52 ያህል መገደላቸውን አስረድተዋል፡፡
የደቡብ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሂክማ ኬይረዲን ለሪፖርተር እንገደለጹት ግን አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 23 ሲሆን፣ ግጭቱም ብሔር ተኮር አይደለም፡፡
በዚህ ግጭት የዲላ ከተማን ሲሶ ያህሉን እሳት በልቶታል፡፡ ‹‹ፌዴራል ፖሊስ ቅዳሜ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ባይደርስ ሁላችንም እናልቅ ነበር፤›› በማለት የግጭቱን አስከፊነት ነጋዴው ገልጸዋል፡፡
የጌዲዮ ዞን መቀመጫ የሆነችው ዲላ ከአዲስ አበባ ከተማ 369 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ዞኑ በአጠቃላይ 1,347.04 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡
ዞኑ የኢትዮጵያ ስፔሻሊቲ ቡና (ይርጋ ጨፌ) ይመረትበታል፡፡ በዞኑ ዲላ፣ ጨለልቅቱ፣ ይርጋ ጨፌና ወናጎ አጎራባች አካባቢዎች ግጭቱ ተንሰራፍቶ ነበር፡፡
የፖሊስ ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት የክልሉ ሰላም ወደነበረበት ተመልሷል፡፡ ችግሩንም የፈጠሩ አካላትም በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው፡፡ እስከ ማክሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ሰላም ቢሰፍንም በከተማው የንግድ እንቅስቃሴ አለመጀመሩ ታውቋል፡፡
ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ