የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የሰላማዊ ዜጎች እስር ቢኖርም፤ በአንዳንድ ቦታዎች አሁንም ተቃውሞች እንደቀጠሉ ናቸው
(አዲስ ሚዲያ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓም ተግባራዊ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች በጅምላ እየታሰሩ ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል እስሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ በቅርብ ርቀት የምትገኘው ሰበታ ከተማ ብቻ ከ አንድ ሺህ በላይ ተጠርጣሪ ናቸው ያላቸውን ነዋሪዎችን ማሰሩን ራሱ መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን፤ በሌሎችም የኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከተሞችና ወረዳዎችም በተመሳሳይ መልኩ እስሩ መቀጠሉን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን እና ጎንደር ዞን መንግሥት የነዋሪዎቹን ትጥቅ ለማስፈታት ወደ ወረዳዎች እና ገጠር ቀበሌዎች የፀጥታ ኃይሉን ቢያሰማራም ከህዝቡ የአፀፋ ርምጃ በመወሰዱ በርካታ ወታደሮችና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ህዝባዊ ተቃውሞው ከተጀመረበት ቀን አንስቶ የመንግሥት የፀረ አገዛዝና ጭቆና ተቃውሞ እንደቀጠለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በአፋር ክልልም እንዲሁ የሰላማዊ ዜጎች እስሩ የቀጠለ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በአፋርኛ በማዜም የምትታወቀው ድምፃዊት መፈራ መሐመድ ላሌን ጨምሮ አስር ሰላማዊ ዜጎች በአሳይታ ከተማ መታሰራቸው ታውቋል፡፡
ድምፃዊት መፈራ መሐመድ ላሌ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያ ትግበራ ላይ መንግሥት እንደ ኢሳት፣ ኦ.ኤም.ኤን. የመሳሰሉ መገናኛ ብዙኃን መከታተልና መረጃ መለዋወ ላይ መመሪያው እገዳ ጥሏል፡፡ በተጨማሪ ያልተፈቀደ ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ፣ ለህዝብ አገልግሎት አለመስጠት፣ በትምህርትና በስፖርት ማዘውተሪያ አድማ ማድረግ በክልከላው ተካተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር የመንግሥትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትግበራባለመቀበል በድጋሚ ለ3ኛ ጊዜ ከቤት ያለመውጣት አድማ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ አስቀድሞ በኢትዮጵያ የመንግሥትን በደልና ብልሹ አሰራር ለመቃወምና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ቀድሞም ቢሆን ለዓመታት ፈፅሞ የተከለከሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
መንግሥት ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ዓመት ያህል ያለማቋረጥ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቀጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማርገብ በሚል ባለፈው መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ተግባራዊ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ኢንተርኔትን በተለይም ማኀበራዊ ሚዲያ፣ በውጭ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተዘጋጅተው ለህዝቡ አማራጭ የመረጃ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ ያሉ እንደ ኢሳት፣ ኦ ኤም ኤን ያሉ መገናኛ ብዙኃን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዳይሰራጩ ከማፈን በተጨማሪ ህዝቡም መረጃ መለዋወጥና መስማትም እንደሌለበት በአዋጁ መከልከሉ ይታወሳል፡፡
አዋጁን ተከትሎ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ክልል ኮንሶ ፣ ጋሞ ጎዳ ዞን፣ በአፋርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል (ኦጋዴን) የተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች በመዘዋወር ድንገት ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ የተለያዩ የወርቅ ጌጣጌጦችን፣ ገንዘብ፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ ከመወስድ በተጨማሪ ጠርጥረንሃል ያሉትን ሰው ያለምንም ፍርድ ቤት ማዘዣ እየደበደቡ በመውሰድ ወዳልታወቀ ስፍራ እንደሚያስሯቸው ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ምክንያት ከወትሮ በተለየ መልኩ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ ነዋሪው በፍርሃት ድባብ ውስጥ እንደሚገኙ በመጠቆም በማኀበራዊና ንግድ እንቅስቃሴዎች ላይም አለመረጋጋቶች እንደሚስተዋሉ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
መንግሥትበአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት አፈና እና ቁጥጥሩን አጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ ዋነኞቹ የህዝባዊ ተቃውሞ አስተባባሪዎች መካከል የአማራ ተጋድሎና የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች ከመንግሥት ርምጃ ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን የሚችል አዳዲስ የትግል ስልቶችንም በቅርቡ ሊጀምሩ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡ በተለይ በውጭ የሚኖሩ የመንግሥትን አገዛዝ የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያን በስልጣን ላይ ካለው ገዥው ስርዓት ለውጥ በኋላ በኢትዮጵያ ሊመሰረት ስለሚገባው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ትግበራ በቪዥን ኢትዮጵያ እና በኦሮሞ ማኀበረሰብዓለም አቀፍ የህግ ባለሙያዎች ማኀበር አስተባባሪነት ከወዲሁ በሰሜን አሜሪካ ዋሸንግተን ዲሲ እበእንግሊዝ ለንደን ምክክር መጀመራቸው ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ አቃቂ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በደረሰ የእሳት አደጋ ከ25 ያላነሱ እስረኞች ህይወት አለፈ
(አዲስ ሚዲያ)ዛሬ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አበባ አቃቂ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ከ25 ያላነሱ እስረኞች መሞታቸው ተጠቆመ፡፡ በጥበቃ ላይ የነበሩ ወታደሮችም ከእሳቱ ለማለጥ የሞከሩ እስረኞች ላይ ሲተኩሱ እንደነበር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ከቃጠሎው በፊት በነበረው ተኩስ ምን ያህል እስረኞች ላይ ጉዳት እንደደረሰ እስካሁን ማረጋገጥ ባይቻልም፤ በነጋታው ጠዋት በነበረው የእሳት አደጋ ከ25 ያላነሱ ሰዎች መሞታቸውን ከቅዱስ ጳውሎስ፣ ሜክሲኮ በሚገኘው ፖሊስ ፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ እና የካቲት 12 ሆስፒታል ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቃጠሎው ጉዳት የደረሰባቸውና በህይወት የተረፉትም አብዛኞቹ ፖሊስ ሆስፒታልና የካቲት 12 ሆስፒታል በጥበቃ ስር ሆነው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
በወህኒ ቤቱ ታስረው ከሚገኙት መካከል ስመጥር እና ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸው በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ያሉበት ሲሆን በተለይም፤ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ፖለቲከኞች፣ የመብት አራማጆች እና ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት ይታወቃል፡፡
በያዝነው 2008 ዓ.ም. ብቻ ከአዲስ አበባ አቃቂ ከሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በተጨማሪ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች የሚገኙባቸው ጎንደር፣ አምቦና ደብረ ታቦር ወህኒ ቤት በተመሳሳይ መልኩ የእሳት አደጋ ሰለባ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ በነበሩ አደጋዎች መንስኤ እና ጉዳትን በተመለከተ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም ከመግለፅ መቆጠቡ ይታወቃል፡፡
በተለይ የአቃቂ ቂሊንጦውን እሳት ቃጠሎ ተከትሎ በርካታ የታሳሪ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች እና ደጋፊዎች ስጋት እንዳደረባቸው በተለያየ መድረክ ከመግለፅ በተጨማሪ በአዲስ አበባና አጎራባች አካባቢ ያሉ ሰዎች የቤተሰቦቻቸውን ደህንነት ለማጣራት ሙከራ ቢያደርጉም በወህኒ ቤቱ አስተዳደር እንዳልተፈቀደ ተረጋግጧል፡፡ በወህኒ ቤቱ የታሰሩ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ከተለያዩ የክልል ከተሞች የመጡ ሰዎችም ወደ እስር ቤቱ ግቢም ሆነ ከግቢ ውጭ በቅርብ ርቀት እንዳይጠጉ በመከልከላቸው ወደየመጡበት መመለሳቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
በአደጋው የደረሰውን ጉዳትና ምክንያት በተመለከተ የወህኒ ቤቱ አስተዳደርም ሆነ መንግሥት እስካሁን የሰጡት መረጃ የለም፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ ሰዎች አደጋው በመንግሥት ሆን ተብሎ የተቀነባበረና የፖለቲካ እስረኞችን ለመጉዳት የታሰበ የገዥው ስርዓት የተለመደ ስልት እንደሆነ የሚገልፁ ቢኖሩም፤ ስለ አደጋውና አጠቃላይ መረጃ ከገለልተኛ አካልም ሆነ ከመንግሥት ለማወቅ አልተቻለም፡፡
የሪዮ ኦሎምፒክ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ገመና
ብስራት ወልደሚካኤል
ኢትዮጵያ ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው የ2016ቱ የብራዚሉ የበጋ ሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ 35 ስፖርተኞችን በ3 ዘርፍ በማሳተፍ 8 ሜዳሊያ በማግኘት ከዓለም ተወዳዳሪዎች 44ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡ በበርካታ ዓለም አቀፍና የኦሎምፒክ ውድድሮች ኢትዮጵያ በምታገኛቸው ድሎች ትበልጣት የነበረችውና በአፍሪካ የቅርብ ተቀናቃኟ ኬንያ በበኩሏ 13 ሜዳሊያ በማግኘት 15ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች፡፡
ኢትዮጵያ ለ13ኛ ጊዜ የበጋ በሪዮ ኦሎምፒክ ውድድር የተሳተፈችው በሶስት የውድድር ዘርፍ በተለይም በአትሌቲክስ ሩጫ፣ ዋና እና ብስክሌት ውድድር ሲሆን፤ ሜዳሊያ ያገኘችው በሩጫው የአትሌትክስ ዘርፍ ብቻ ነው፡፡ በዚህም 1 ወርቅ፣ 2 ብር እና 5 ነሐስ ያገኘች ሲሆን በአጠቃላይ 8 ሜዳሊያ አግኝታ ተመልሳለች፡፡ ባለፈው የለንደኑ 2012ቱ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በ2 ስፖርት ዘርፍ 35 ተወዳዳሪዎችን በማሰለፍ 3 ወርቅ፣ 2 ብር እና 2 ነሐስ በአጠቃላይ 7 ሜዳሊያ በማግኘት በዓለም 23ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀች ሲሆን፤ በቤጂንጉ የ2008 ኦሎምፒክ በ1 ስፖርት ዘርፍ 27 ተወዳዳሪዎችን በማሰለፍ 4 ወርቅ፣ 1 ብር እና 2 ነሐስ አጠቃላይ 7 ሜዳሊያ በማግኘት 18ኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው፡፡ ይህም የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ውድድር፣ ተሳትፎ፣ ብቃት እና ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ እየቀነስ መሄዱን ቢያሳይም፤ በተለይ በአትሌቲክስና በሌሎች ፌዴሬሽኞች እንዲሁም በኦሎምፒክ ኮሚቴና በስፖርት ፌዴሬሽን በኩል ከመገናኛ ብዙኃኝ ፍጆታ ባለፈ ለስፖርቱ መሻሻል ትኩረት እንዳልተሰጠው ያሳያል፡፡
ኬንያ በ2012 የለንደኑ ኦሎምፒክ በ4 ስፖርት ዘርፍ 47 ተወዳዳሪዎችን አሳትፋ 2 ወርቅ፣ 4 ብር እና 6 ነሐስ በአጠቃላይ 12 ሜዳሊያ በማግኘት ከዓለም 28ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን፤ በ2008ቱ የቤጂንግ ኦሎምፒክ በ5 ስፖርት ዘርፍ 48 ተወዳዳሪዎችን በማሳተፍ 6 ወርቅ፣ 4 ብር እና 4 ነሐስ በአጠቃላይ 14 ሜዳሊያ 13ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋይታወሳል፡፡ በርግጥ አብዛኞች የኢትዮጵያ ድሎች በአትሌቶች የግል ጥረት እንጂ በፌዴሬሽነች ስራ ጥረት እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ቅሬታን መፍጠሩ የሚታወቅ ሲሆን፤ በሪዮ ኦሎምፒክም በተለይ በስመ ጥር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሳይቀር ባልተለመደ መልኩ ከፍተኛ ተቃውሞና ቅሬታ መሰማቱ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ በ3 የውድድር መስክ በአጠቃላይ 38 ተወዳዳሪዎችን ለኦሎምፒክ ውድድሩ ብታስመዘግብም፤ እስካሁን ለምን እንደሆነ በይፋ የታወቀ ነገር ባይኖርም ውድድሩ ላይ ለመሳተፍ የጠጓዙት ግን 35 ተወዳዳሪዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ተወዳዳሪዎችን አስቀርቶ በምትካቸው ከስፖርቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ልዑካን ይዞ መሄድ እና ስፖርቱን በፖለቲካዊ ዝምድና እና ማዕቀፍ ውስጥ መውደቁ አዲስ ባይሆንም፤ የሪዮ ኦሎምፒክ በሀገር ቤት የተገደበውን ፖለቲካዊ ፈር የለቀቀ ሙስና ለአደባባይ የበቃበት ክስተት አሳዛኝ ትዝታን አስፍሮ አልፏል፡፡ ይህ ክስተት ምንም እንኳ በሪዮ ኦሎምፒክ አዲስ ባይሆንም ከምን ጊዜውም ይበልጥ በተለይ ገዥውን ስርዓት በዓለም አደባባይ ያጋለጠ ነበር፡፡
የሪዮ ኦሎምፒክ ውድድር ውጤት ለኢትዮጵያ አስደሳች ባይሆንም፤ በዓለም የኦሎምፒክ መድረክ አሳዛኝ፣ አስደሳችና አሳፋሪ አዳዲስ ክስተቶች በኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ለዓለም አደባባይ በቅቷል፡፡ በተለይ ስፖርታዊ ቅርፅም ሆነ ብቃት የሌለው ሮቤል ኪሮስ፣ አባቱ የውሃ ዋና ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት በመሆናቸው፣ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ፕሬዘዳንት አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያምና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ አማካኝነት ብቃት ያላቸውን ተወዳዳሪዎችና የዋና አሰልጣኑ አበበ ቢቂላን ሀገር ቤት ጥለው ባላቸው የስጋና ፖለቲካዊ ዝምድና ብቻ በዓለም መድረክ ሀገርን ወክሎ እንዲወዳደር በማድረግ ሀገሪቱንም ልጁንም የዓለም መሳቂያ ማድረግ ችለዋል፡፡ በአትሌቲክ ፌሬሽንም ተመሳሳይ ቅሬታ ያለ ሲሆን፤ በተለይ የማራቶን አሰልጣኙ ሐጂ አዲሎ በጀት የለንም በሚል ከሪዮ ኦሎምፒክ እንዲቀሩ ተደርጉ፤ ከስፖርቱ ጋ ምንም ግንኙነት የሌላቸው እንደነ ሚሚ ስብሃቱ ያሉ የስርዓቱ ደጋፊ ሰዎች በኦሎምፒክ ኮሚቴ ወጪ እንዲጓዙ መደረጉም ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ አሰልጣኙ ሐጂ አዲሎ አትሌቶቹ በውድድሩ ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ለማገዝ በራሱ ሙሉ ወጪ ብራዚል ሪዮ ኦሎምፒክ እንደሄደ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተለይ ሮቤል ኪሮስን የተለያዩ የስፖርት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም ስፖርታዊ ብቃትና ቅርፅ አልባ መሆኑን በመታዘብ ሮቤል ዓሳ ነባሪው የሚል ስም በመስጠት ግርምታቸውን ለዓለም ህዝብ አሰራጭተው ነበር፡፡ በተለይ በሀገር ቤት በዋና ውድድር ለኦሎምፒክ ማጣሪያ በጥሩ ብቃትና ተክለ ቁመና አንደኛ ሆኖ ያለፈው የአዲስ አበባው አብዱልመሊክ በዋና ፌዴሬሽኑ እና በኦሎምፒክ ኮሚቴው አማካኝነት ያለምንም ምክንያት በሪዮ ኦሎምፒክ እንዳይሳተፍ ሲደረግ፤ በምትኩ ብቃትና ቅርፅ አልባው ሮቤል ኪሮስ፤ በአባቱና በኦሎምፒክ ኮሜቴው አማካኝነት እንዲሄድ መደረጉ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ወደ ኦሎምፒኩ ውድድር መሄድ ያለበት ተወዳዳሪ እንዲቀር ከመደረጉ በተጨማሪ የውሃ ዋና አሰልጣኙ ዋናተኞች እንዲያሰለጥኑ በሪዮ ኦሎምፒክም ዋናተኞች ይዘው በዛውም ልምድ ቀስመው ለቀጣይ ዓለም አቀፍ በቃት ያላቸው ተወዳዳሪዎችን ማፍራት እንዲችሉ በሚል አሰልጣን አበበ ቢቂላ በማስታወቂያ በተደረገ ውድድ አልፈው ከሚሰሩበት ጋምቤላ ተጠርተው፣ የሪዮ ኦሎምፒክ ግብዣ ቢመጣላቸውም፤ የውሃ ዋና ፌሬሽን ፕሬዘዳንት በሆኑት የሮቤል አባት አቶ ኪሮስ ሃብቴ እና በኦሎምፒክ ኮሚቴው ፕሬዘዳንት አቶ ብርሃነ ኪዳነ ማርያም አማካኝነት አዲስ አበባ እንዲቀሩ ተደርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ያለ ብቃት ኦሎምፒክ ላይ እንዲሳተፍ የተደረገው ሮቤል ኪሮስ አሰልጣን አበበ ቢቂላ የኦሎምፒክ ጉዞውን እንዲሰርዝና አዲስ አበባ እንዲቀር የ10 ሺህ ብር ቼክ ጉቦ መስጠቱን፣ አሰልጣኙም ጉዳዩን ለዋና ፌሬሽን፣ ለኦሎምፒክ ኮሜቴ፣ ለስፖርት ኮሚሽን እና ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ጋር ድረስ ቢያሳውቁም ምላሽ ሳያገኙ መቅረታቸው ሌላ ጥያቄን የሚያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡
በውድድሩ በሮቤ፣ በአባቱ አቶ ኪሮስና በኦሎምፒክ ፖለቲካው ና ስጋዊ ዝምድና ምክንያት ሀፍረት ውስጥ የወደቀችው ሀገር፤ በአልማዝ አያና የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ውድድር በአዲስ ክብረወሰን አንደኛ ሆና የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣቷ ብዙዎችን አስደስቷል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አትሌቷ በ5 ሺህ ሜትርም ተወዳድሯ ለሀገሯ የነሐስ ሜዳሊያንም በማምጣት ከማስደሰቷ በተጨማሪ ሁለት ወርቅ ባለማምጣቴ ህዝቡን ይቅርታ እጠይቃለሁ ያለችው ንግግር ይበልጥ የብዙዎችን ልብ ሰብሯል፡፡
አትሌት አልማዝ አያና ብቃት ብቻ ሳይሆን ትህትና እና ብሔራዊ ፍቅርን አንድ ላይ አንግባ በግሏ በአንድ የኦሎምፒክ ውድድር ብቻዋን ሁለት ሜዳሊያ ማምጣቷ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብም ከፍተኛ አድናቆትና ክብርንም አጎናፅፏታል፡፡ በርግጥ በአንድ ኦሎምፒክ ሁለት ሜዳሊያ ስታመጣ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ባትሆንም፤የሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያውያን በብዙ የሀዘን እና የመከፋት እንዲሁም በውጤት ላይ ስጋት ውስጥ በነበሩበት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡
ሌላው በኢትዮጵያዊው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ አማካኝነት ከስፖርቱ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት የሳበነ፣ የተከፉና የተገፉ ኢትዮጵያውያንን በሁለት ነገሮች ያስደሰተ፤ ግን ደግሞ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለአፍሪካ ታሪክ አዲስ የሆነ፤ በኦሎምፒክ ታሪክ ደግሞ ሁለተኛ የሆነ አሳዛኝ ክስተት በሪዮ ኦሎምፒክ አደባባይ ታይቷል፡፡ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ የኦሎምፒኩ መዝጊያ በሆነው በወንዶች ማራቶን ውድድር ሁለተኛ ሆኖ በማሸነፍ ለሀገሩ የብር ሜዳሊያ ቢያስገኝም፤ በሀገር ቤት መንግሥት በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ግድያ፣ እስር፣ ስቃይና እንግልት በመቃወም ለዓለም አደባባይ አሳይቷል፡፡ ተበድለናል የሚለውን ገላጭ ምልክቱን በፕሬስ መግለጫ እና በሽልማት ስነ ስርዓቱም ላይ ደግሞታል፡፡
የአትሌት ፈይሳ ያልተጠበቀው የተቃውሞ ክስተት ገዥውን ስርዓት ሀፍረት ውስጥ ቢከተውም፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውንን በተለይም በገዥው ስርዓት ግፍና በደል የተፈፀመባቸውን እንዲሁም ለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት የቆሙትን በሙሉ አስደስቷል፡፡ በመጨረሻም አትሌቱ ውድድሩን ሁለተኛ ሆኖ በሚያጠናቅቅበት ወቅት እጁን በመስቀለኛ አጣምሮ በተለይም ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቃውሞ በኋላም የኦሮሞ ተቃውሞ አሁን ደግሞ በአማራ ተቃውሞም ታስረናል፣ ተጨቁነናል፣ ተበድለናል፣ ነፃነት እንፈልጋለን የሚል መልዕክት ያለውን ምልክት እያሳየ ውድድሩ ሲያሸንፍ ታይቷል፡፡ ድርጊቱ ባለስልጣናቱን እና የስርዓቱን ደጋፊዎች እጅግ አስደንግጧል፡፡
አትሌት ፈይሳም በኦሎምፒኩ መድረክ የተገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ለምን ያንን ምልክት እንደተጠቀመ ሲጠየቅ፤ ሀገር ቤት በተለይ መንግሥት በኦሮሚያ በርካቶችን እየገደለ፣ እያሰረ ያለውን ድርጊት መቃወሙን ለመግለፅ እንደሆነ፣ ያቀረበውን ተቃውሞ ተከትሎ ሀገር ቤት ቢመለስ መንግሥት እንደሚገድለው፣ ምናልባት ባይገድለው እንኳ እንደሚያስረው አሊያም ከሀገር እንዳይወጣ ሊያደርገው እንደሚችል ስለሚሰጋ ወደ ሀገር ቤት እንደማይመለስ በማስታወቅ ለጊዜው ብራዚል ቀርቷል፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እና የልዑካን ቡድን አባላቱ ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸው ታውቋል፡፡
በውጭ የሚገኙ የተለያዩ የኢትዮጵያውያን መገናኛ ብዙኃንም ቃለመጠይቅ ያደረጉለት ሲሆን፤ አትሌቱም የቅርብ ጓደኞቹና አብረውት የተማሩ ሳይቀሩ በባሌ፣ በአርሲ፣ እንዲሁም በተለያየ የኦሮሚያና አማራ ክልል ሰዎች እየተገደሉ እና እየታሰሩ መሆኑን በመግለፅ፤ ድርጊቱንም በመቃወም ምልክቱን እንዳሳየና ህዝቡም በአንድነት ተባብሮ ስርዓቱን ማስወገድ እንዳለበት እምነቱን ሲገልፅ ተሰምቷል፡፡ በተለይም ህዝቡ በዘር ከመከፋፈል ይልቅ ሁሉም ተባብሮ ስርዓቱን ማስወገድ እንዳለበት በአፅንዖት ሲናገር ተሰምቷል፡፡
በተለይ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ደጋፊዎች የአትሌት ፈይሳ የኦሎምፒክ ማራቶን ድል የብር ሜዳሊያ እንዲሰረዝ የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ላይ ጫና ለማድረግ ቢሞክሩም፤ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ በበኩሉ የአትሌቱን ሜዳሊያ ሊነጥቅም ሆነ ምንም ዓይነት ርምጃ እንደማይወስድ ይፋ አድርጓል፡፡ በመጨረሻም የኢትዮጵያ መንግሥት አትሌቱ ወደ ሀገሩ መመለስ እንደሚችል እና ላሳየው ተቃውሞ ምምልክት በማሳየቱ ምንም እንደማይደርስበት ቢያሳውቅም፤ አትሌቱ ግን ወደ ሀገር ቤት መመለስ ለደህንነቱ አደጋ እንዳለው በመግለፅ ለጊዜ ብራዚል ሪዮ ዲ ጄኔሪዮ መቅረቱ ተረጋግጧል፡፡
በ2016ቱ የሪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ውጤት:
ውጤት የተወዳዳሪ ስም የውድድር ዓይነት እና ርቀት የተገኘው ሜዳሊያ
1ኛ. አልማዝ አያና በሴቶች 10,000 ሜትር ወርቅ
2ኛ. ገንዘቤ ዲባባ በሴቶች 1,500 ሜትር ብር
2ኛ. ፈይሳ ሌሊሳ በወንዶች ማራቶን ብር
3ኛ. ጥሩነሽ ዲባባ በሴቶች 10,000 ሜትር ነሐስ
3ኛ. ታምራት ቶላ በወንዶች 10,000 ሜትር ነሐስ
3ኛ. ማሬ ዲባባ በሴቶች ማራቶን ነሐስ
3ኛ. አልማዝ አያና በሴቶች 5,000 ሜትር ነሐስ
3ኛ. ሐጎስ ገብረህይወት በወንዶች 5,000 ሜትር ነሐስ
አጠቃላይ ድምር 8 ሜዳሊያ
በተለይ በኦሎምፒክ ውድድር ዘርፍ ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ የወድድር መስክ ዕድሎች ውስጥ አብዛኛውን ለምን መጠቀም እንደማትፈልግ እስካሁን ግልፅ ባይሆንም፤ በውጤትም ሆነ በውድድር ዘርፍ እንዲሁም ውጤት ማነስ ብዙ ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ስፖርቱ አጠቃላይ በፖለቲካ መዋቅር የተሳሰረ በመሆኑ እና በብቃት ሳይሆን በፖለቲካ ሹመት ከየክልሉ በሚመጡ ሹመኞች እና ለፖለቲካ ስርዓቱ ታማኝ የተባሉ ብቻ ከፌዴሬሽን፣ ኦሎምፒክ ኮሜቴ እና ስፖርት ኮሚሽን ስለሚሞሉ ስርዓቱ እስካለ ስፖርቱ ላይ የተለየ አዎንታዊ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል እሙን ነው፡፡ ምክንያቱም ከወረዳ እስከ ፌደራል ድረስ ባሉ የስፖርት ፌዴሬሽን እና ስፖርት ኮሚሽን የሚመለከታቸው ሰዎች ባላቸው የትምህርት ዝግጅት፣ ዕውቀት፣ ብቃት፣ ልምድና ተነሳሽነት ኃላፊነት የሚቀመጡ ሳይሆን ባላቸው የፖለቲካ ወገንተኝነት ብቻ የሚሾሙ አንዳንዶቹ ስለ ስፖርት ስራና አስፈላጊነት ምን እንደሆነ እንኳ የማያውቁ የፖለቲካ ሹመኞች የኃላፊነት ቦታውን ይዘው እንዳሉ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ብቃቱ ያላቸው የስፖርት አመራር ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ተወዳዳሪዎችም ነፃ የወድድር ተሳትፎ ሊያገኙ የሚችሉባቸው ዕድሎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመነመኑ መጥተዋል፡፡ ስለዚህ ሀገሪቱ ኦሎምፒክን ጨምሮ በሁሉም የስፖርት ዘርፎች ውጤታማ እንድትሆን በአጠቃላይ የስርዓት ለውጥ ካልመጣ አሁን ባለው አሰራር የሚሾሙ ሰዎች ቢቀያየሩ እንኳ የተለየ ውጤት መጠበቅ አስቸጋሪ ነው፡፡
በ2016ቱ የሪዮ ኦሎምፒክ አጠቃላይ ውጤት አሜሪካ 121 ሚዳሊያ (46 ወርቅ፣ 37 ብር እና 38 ነሐስ)፣ እንግሊዝ 67 ሜዳሊያ (27 ወርቅ፣ 23 ብር እና 17 ነሐስ)፣ ቻይና 70 ሜዳሊያ (26 ወርቅ፣ 18 ብር፣ 26 ነሐስ)፣ ራሽያ 56 ሜዳሊያ (19 ወርቅ፣ 18 ብር እና 19 ነሐስ) እንዲሁም ጀርመን 42 ሜዳሊያ (17 ወርቅ፣ 10 ብር እና 15 ነሐስ) በማግኘት እንደ ቅደም ተከተላቸው ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል፡፡
የበጋው የሪዮ ኦሎምፒክ 207 የዓለም ሀገሮች የተውጣጡ 11,303 ተወዳዳሪዎች የተሳተፉበት ዓለም አቀፍ ዝግጅት ባለፈው እሁድ ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በመዝጊያው የማራቶን ውድድር በሰላም ተጠናቋል፡፡ በቀጣይም በ2018 የክረምት ኦሎምፒክ በደቡብ ኮሪያዋ ፓዮንቻን የሚካሄድ ሲሆን፤ የ2020ው የበጋው ኦሎምፒክ ውድድር ደግሞ በጃፓኗ መዲና ቶክዮ እንደሚዘጋጅ ይጠበቃል፡፡
በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ አድማሱን እያሰፋ ቀጥሏል፤ በኦሮሚያ ኢኮኖሚ ተኮር ተቃውሞ እንደሚጀመር ይፋ ተደረገ
ብስራት ወልደሚካኤል
(አዲስ ሚዲያ)የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄን መነሻ አድርጎ በጎንደር ፋሲል ከተማ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ፤ የተለያዩ የሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ወረዳና ከተሞችን ጨምሮ ወደ ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም እንዲሁም ወደ ሰሜን ወሎ መቄት እና ሸዋ ሮቢት መስፋፋቱን እማኞች ለአዲስ ሚዲያ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ነሐሴ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ከተማ፣ ነሐሴ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ቡሬ ወምበራ ወረዳ ቡሬ ከተማ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር በተለያዩ ወረዳዎች እና ከተሞች ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ተቃውሞዎች እና የመንግሥት የኃይል ርምጃዎችም የቀጠሉ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
በጎንደር፣ ባህርዳር እና ደብረማርቆስ ከተሞች ከቤት ያለመውጣት ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞች የተደረጉ ሲሆን ከነሐሴ 22-25 ቀን 2008 ዓ.ም. ደግሞ በተመሳሳይ ምልኩ በደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር ከተማ ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ እንደሚደረግ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በአማራ ክልል ባሉ ሰሞንኛ ተቃውሞች በተለይ በማክሰኝት፡በገደብዬ፡በእንፍራንዝ፣ በአብደራፊ፣ በአርማጭሆ፣ በፍኖተ ሰላም፡ቡሬ፡ ጅጋ እና ማንኩሳ በተባሉ ወረዳዎች ህዝባዊ ተቃውሞዎች የበረቱባቸው መሆኑን ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡ በነኚህ ስፍራዎች የነበሩ ተቃውሞች መካከልም የተወሰኑ በማኀበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጩ መዋላቸውን ለመታዘብ ተችሏል፡፡
በነበሩ የአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞች ሁለት ሰላማዊ ሰዎች በመንግሥት መገደላቸው የተጠቆሙ ሲሆን፤ በተለይ በሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ ወረዳዎች በነበሩ ተቃውሞች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በኦሮሚያ ክልልም ህዝባዊ የፀረ አገዛዝ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞች የቀጠሉ ሲሆን፤ በዚህም በምዕራብ ሐረርጌ መሰላ ወረዳ በሚገኙ ዋልተሲስ እና ጎሮ በተባሉ መንደሮች በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ አራት ሰላማዊ ዜጎች በመንግሥት በተወሰደ የኃይል ርምጃ መገደላቸው ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገሪቱ ያለውን የመንግሥትን ግድያ፣ እስርና እና አፋና በመቃወማቸው በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ እስረኞች በተለይም እነ አቶ በቀለ ገርባ በሀገሪቱ ከነሐሴ 19-21 ቀን 2008 ዓ.ም. ብሔራዊ የሀዘን ቀን በሚል ታስቦ እንዲውል ያደረጉት ጥሪ ከወዲሁ በተለያዩ ደጋፊዎቻቸው ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ታውቋል፡፡
የመንግሥት የኃይል ርምጅና ግፍ በመቃወም በሚደረግ ብሔራዊ የሀዘን ቀንም ፀጉር መላጨት፣ ጥቁር ልብስ መልበስ፣ ጥቁር ባንድራ(ጨርቅ) ማውለብለብ፣ ሻማ ማብራት፣ በተቃውሞ ትግሉ የተገደሉ ሰላማዊ ዜጎች ቤተሰቦችን መጎብኘት እና ተሰብስቦ ህዝባዊ ውይይት በማካሄድ እንዲተገበር ጥሪ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ባሉ ዜጎች ከወዲሁ ተግባራዊ መደሩ የሚያመለክቱ የተለያዩ ምስሎች በማኀበራዊ ሚዲያዎች ላይ መሰራጨታቸውን ማየት ተችሏል፡፡
በኦሮሚያ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ካለው የፖለቲካና ማኀበራዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ከጳጉሜ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የኢኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞችም እንደሚተገበሩ የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች እና የመብት አራማጆች ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞው ምን ላይ እንደሚያተኩር በዝርዝር የተቀመጠ ነገር ባይኖርም፤ ወደፊት ይፋ እንደሚደረግ የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡
በታቀደው መሰረት በኦሮሚያ የኢኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ መንግሥት በክፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ይጠበቃል፡፡ በተለይም መንግሥት ከክልሉ በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪና የሀገሪቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆኑት እንደ ቡና፣ የጫት፣ የአበባ፣ የቁም እንሰሳትና፣ የቆዳና ሌጦ እንዲሁም የምግብ ነክ የሆኑ የብግርና ምርቶች እንዲሁም ወርቅና የመሳሰሉ የማዕድን ሃብቶች ከክልሉ እንዳይወጡና ወደ ማዕከላዊም ሆነ የክልሉ ገበያ ንግድ ላይ የማይውሉ ከሆነ ምን አልባትም በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ፈተና በመንግሥት ላይ ሊደርስ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የኢኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞ በቀጣይ ወደሌሎች ክልሎች በተለይም አማራ እና ደቡብ ክልል የሚዛመት ከሆነ ደግሞ የመንግሥት 90% የገቢ ምንጭ በማድረቅ ስርዓቱን ሙሉ ለሙሉ አደጋ ላይ እንደሚጥለው ይገመታል፡፡ በተለይ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል ብቻ የሀገሪቱን 54% የሆነውን ህዝብ ቁጥር እንደሚሸፍኑ እና ከ65% የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪና የገቢ ምንጭም መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ከባለፈው ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ የተቀጣጠለው የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ መላው ኦሮሚያ ክልልን በማዳረስ፤ ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ አማራ ክልል ተዛምቷል፡፡ በሁለቱም ክልሎች ዘገባው እስከተጠናቀረበት ድረስ ህዝባዊ ተቃውሞዎቹ በተለያዩ ወረዳዎችና ከተሞች ቀጥሏል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በሁለቱም ክልሎች ባሉ የተለያዩ ቦታዎች መደበኛ የመንግሥት ስራን ጨምሮ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋቶች እየታዩ ነው፡፡
አስረኛ ወሩን ባስቀጠረው ህዝባዊ ተቃውሞ በሁለቱም ክልሎች ከ650 በላይ ሰላማዊ ዜጎች በመንግሥት በተወሰደ የኃይል ርምጃ ሲገደሉ፣ ከ 1,250 ያላነሱ ዜጎች ቆስለው በግምት ከ35,000 በላይ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ እና የቆሰሉ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ስማቸውና ምስላቸው በሰፊው በማኀበራዊ ሚዲያ እየተገለፀ ይገኛል፡፡ በሁለቱም የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ህዝባዊ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ የወጣው ህዝብ አንዱ ለሌላው በተለያዩ ጊዜና ቦታ ያሳዩት የርስ በርስ አጋርነት፤ መንግሥትን ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ እንደጣለው ባለስልጣናቱ በስራቸው ባሉ መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ የተደመጡ ሲሆን፤ በዚህም ስጋት እንዳደረባቸው ባለስልጣናቱና ደጋፊዎቻቸው በይፋ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎችና ከሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች መረዳት ተችሏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ ፤የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ”የጋራ ልማት የተቀናጀ ማስተር ፕላን” በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ገበሬዎች የሚያፈናቅልና ለጎዳና ህይወት የሚዳርግ ነው በሚል ቀደም ሲል የነበረውን ተቃው ከዓመት በኋላ በማገርሸት በምዕራብ ሸዋ ጊንጪ ከተማ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በአማራ ክልል ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ ህዝባዊ ወኪሌ ኮሚቴ አባላት ላይ መንግሥት በሌሊት በመኖሪያቸው አካባቢ የፀጥታ ኃይሎችን በመላክ የኃይል ርምጃ መውሰዱን ተከትሎ በጎንደር ከተማ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
መንግሥት በወሰደው የኃይል ርምጃ ስለደረሱ አጠቃላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች በተመለከተ በመንግሥት ጉዳዩን ለመሸፋፈን ከመሞከር በዘለለ ትክክለኛውን ቁጥርና የጉዳት መጠለን ለመናገር አልደፈረም፡፡ ቀደም ሲል ሀገር በቀል በሆነው የሰብዓዊ መብት ጉባዔ (ሰመጉ) እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች (HRW) አማካኝነት በተወሰኑ ወረዳዎችና አካባቢዎች የተደረጉ ምርመራዎች ይፋ ከመደረጋቸው በስተቀር አጠቃላይ በደረሱ የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶች የተደረገ ምርመራም ሆነ ሪፖርት የለም፡፡ ይህን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ምት ኮሚሽን ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲደረግ በይፋ ጥያቄ ቢያቀርብም በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት በበኩሉ የመንግሥታቱን ድርጅት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
በጎንደር የሰላማዊ ሰው ግድያ የቀጠለ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠርቷል
(አዲስ ሚዲያ) ዛሬ ነሐሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ መንግሥት ሰላማዊ ዜጎችን ተኩሶ 1 ወጣት መግደሉን ተከትሎ ዳግም ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሷል፡፡ በሌላ የከተማዋ አካባቢም በተመሳሳይ መልኩ በመንግሥት በተወሰደ ወታደራዊ የኃይል ርምጃ የቆሰሉ እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡ እንደ መብት አራማጆች ከሆነ፤ ነጭ ለብሰው በመንቀሳቀሳቸው ብቻ ዛሬ በጎንደር የተገደሉ ዜጎች ቁጥር 4 ደርሷል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ከተገደለው አንድ ሰላማዊ ዜጋ በስተቀር ሌሎች ጉዳቶችን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
የዓይን እማኞች እንደተናገሩት፤ዛሬ ግድያው የተፈፀመው የጎንደር ህዝብ በመንግሥት ቀጥተኛ ትዕዛዝ በግፍ የተገደሉባቸውን ሰላማዊ ሰዎችን ለመዘከር ነጭ የመልበስ መርሃ ግብርን ተከትሎ ነጭ ለብሶ ሲንቀሳቀስ የነበረ ወጣት በድብደባ ሲገደል፣ ሌሎች 3 ሰላማዊ ዜጎች ደግሞ ከወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ጋብ ብሎ የነበረው የጎንደር ህዝባዊ ተቃውሞ ዳግም ተቀስቅሷል፡፡
ህዝቡም ዛሬ በግፍ የተገደለ ወጣት አስከሬን በአደባባይ ይዞ በመዞር ተቃውሞውን እያሰማ ይገኛል፡፡ ጎንደር ባለፈው ሳምንት እሁድ ጀምሮ ለ3 ቀናት ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
በከተማው ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄን ተከትሎ መንግሥት አስተባባሪ የኮሚቴ አባለት ላይ የወሰደውን የኃይል ርምጃ ተከትሎ በነበሩት የፀረ አገዛዝ የህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች በመቀጠላቸው ስጋት የገባው መንግሥት፤ በርካታ የታጠቁ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ እና የፌደራል ልዩ የፀጥታ ኃይሎችን በከተማው ማስፈሩ ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ በኦሮሚያ እስካሁንም ድረስ የቀጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ትናንት ነሐሴ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ደንቢዶሎ አንድ ሰላማዊ ወጣት በመንግሽት አልሞ ተኳሾች መገደሉ የታወቀ ሲሆን፤ በምስራቅ ሷ ዝዋይ ከተማ እቤቱ የነበረ አንድስ ሰላማዊ ዘጋም በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ወታደራዊ ርምጃ መገደሉ ታውቋል፡፡
ለነገ ጠዋት በአዲስ አበባ መዳረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጋበዘበት ህዝባዊ ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቷል፡፡የተቃውሞ ሰልፉ ዋነኛ ዓላማ፤ መንግሥት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚወስደውን ግድያ ህዝቡ በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልል ተቃውሞው የቀጠለ ሲሆን፤ መንግሥት በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ግድያና የፀረ አገዛዝ ተቃውሞ፤ ነገ እሁድ ጠዋት ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ታላቅ የተባለለት የተቃውሞ ሰልፍ መዘጋጀቱን የተቃውሞ አስተባባሪዎችና የመብት አራማጆች አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በሀገር ቤት እየጠፈፀመ ያለውን የመንግሥት ግድያ፣ እስራትና አገዛዝ ድርጊትን በመቃወም በተለያዩ የአሜሪካ፣ አውሮፓ እና አፍሪካ ሀገሮችና ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞ እያደረጉ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
መንግሥት ሰላማዊ ዜጎችን በአደባባይ መግደሉ እንዳሳሰበው በመጠቆም ምርመራ ማድረግ እንደሚፈልግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቢያስታውቅም አገዛዙ የመንግሥታቱ ድርጅትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራን እንደማይቀበልና ከላከው ምላሽ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ጉዳዩ ያሳሰባቸው የአሜሪካና የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት መንግሥት እየፈፀመ ያለውን ግድያ በማውገዝ ጉዳዩን በጥብቅ እየተከታተሉት እንደሆነ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
ከህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት በወሰደውና እየወሰደ ባለው ወታደራዊ የኃይል ርምጃ በኦሮሚያ ክልል በነበሩት ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ከ500 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ፤ ሁለተኛ ወሩን ባስቆጠረው የአማራ ክልል ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ደግሞ ከ100 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው ታውቋል፡፡