Tag Archives: Ethiopia

አልወድቅም ያለው ደመራ

 

Abel-Wabella

አቤል ዋበላ

ሁለት ተከታታይ ደመራዎችን ያበራኹት ቂሊንጦ ዞን አንድ ነበር፡፡ በእስር ቤት ሀይማኖታዊ እና ብሔራዊ በዓላት እንደሁኔታው እንደአቅሚቲ ይከበራሉ፡፡ ዛሬ በዚህች አጭር ማስታወሻ ላጫውታችኹ የወደድኩት በዚያ ካሳለፍኳቸው በዓላት አንዱ የሆነውን የ2007 ዓ.ም. የደመራ በዓል ነው፡፡

ቂሊንጦ ያለው እስረኛ በሙሉ ያልተፈረደበት የቀጠሮ እስረኛ ነው፡፡ ያው ሁሉም እንደሚያውቀው ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎችን መርምሮ ውሳኔ እስኪሰጥ አመታት መፍጀቱ የተለመደ ነው፡፡ ስለዚህ በእስር ቤቱ አመታትን ያሳለፉ ሲኒየር የቀጠሮ እስረኞችን ማግኘት የተለመደ ነው፡፡ አምና ለበዓል የተደረገው ዘንዶሮ እንዳይቀርባቸው እስረኞቹ ኮሚቴ አቋቁመው ተፍ ተፍ ይላሉ፡፡ በመዋጮም በጨረታም ብር ይሰበስባሉ፡፡ ከውጭ ተገዝተው የሚመጡ ዕቃዎችን እንዲያስገቡ የማረሚያ ቤቱን ኃላፊዎች እንዲማልዱ ትልልቅ ሰዎች ተመልምለው ይላካሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ በሙስና የተከሰሱ ሰዎች በማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ዘንድ ተሰሚነት ስለሚኖራቸው የሚላኩት እነርሱ ናችው፡፡ እነርሱም ተስማምተው ደጅ ከጠኑ፣ ከቦጨቁትም በጥቂቱ ዘግነው ስለሚሰጡ በስኬት ይመለሳሉ፡፡

በዚያ አመት ማረሚያ ቤቱ ለደመራ ታስበው የተገዙ ችቦዎችን አላስገባም በማለቱ እስረኛው ሲያጉረመርም ትዝ ይለኛል፡፡ አንዳንዱ እስረኛ እስር ቤት መሆኑን ይዘነጋዋል፡፡ እስኪ አላስገባም ይበሉና እንተያያለን በማለት ሲዝቱ ሳይ ግርም አለኝ፡፡ ጸብ ቢነሳ ወዴት መሮጥ እንዳለብኝ ማሰቤ አልቀረም፡፡ በዚያን ወቅት ከማዕከላዊ ከመጣኹ ገና ሁለት ወሬ ስለነበር የእስረኛውን ስነ ልቦና ስላልተረዳው አንድ ግርግር እንዳይፈጠር መስጋቴ አልቀረም፡፡ እየቆየው ስሄድ ባዶ ጉራ እንደሆነች ገባኝ፡፡

በኋላ ምልጃው ከውጭ የመጣውን ባያሰገባም የማረሚያ ቤቱ ውጨኛው ግቢው ውስጥ ከሚገኙ ዛፎች የሚነድ ነገር ተሰብስቦ ደመራው እንዲዘጋጅ የሚፈቅድ ይሁንታን አስገኘ፡፡ የተወሰኑ ልጆች ተመርጠው ከኛ ዞን ወጥተው የሚነድ ነገር ለመልቀም ከአጃቢ ፖሊስ ጋር ወደዋናው ጊቢ ወጡ፡፡

መስከረም ከክረምቱ ብዙም ያልተለየ ስለሆነ ብዙም ያልደረቀውን ማገዶ ይዘው መጡ፡፡ ከዚያ ወፈር ያለውን ስር የሌለው ልጅ-እግር ዛፍ መኸል አቁመው ደመራ የሚስል ነገር ሠሩልን፡፡ ቆፍረው ቢቀብሩትም አመሻሽ ደርሶ ሳንሎክሰው እንዳይወድቅ ስጋት ውስጥ ገባን፡፡

በአይነ ቁራኛ ሲጠበቅ ሰዓቱ ደረሰ፡፡ ከእስረኛው መካከል ካህናት እና ዲያቆናት አልታጡም፡፡ ለስርዓተ ጸሎቱም ደመራውንም ለመሎከስ ተዘጋጁ፡፡ ጸሎቱ አብቅቶ ደመራው ጋዝ ተርክፍክፎበት መንደድ ጀመረ፡፡ ወፍራሙም ዲያቆን ከበሮውን አንስቶ ይደቃው ጀመር፡፡

በደመራ ትውፊት ደመራው መሀል ከላይ የአደይ አበባ በመስቀል ቅርጽ የሚታሰርበት ያለው አውራ ነዶ ወዴት እንደሚወድቅ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ ታዳሚው ወዴት እንደሚወድቅ ሳይመለከት አይበተንም፡፡ ከልጅነት ጀምሮ እንዳስተዋልኩት ደመራው ወዴትም ይውደቅ ወዴት አመቱ የደስታ ነው፤ አመቱ የሰላም እና የብልጽግና ነው፤ የሚል በጎ በጎ ምኞት ይሰነዘራል እንጂ ወደሰሜን ከወደቀ ሀዘን ወደደቡብ ከወደቀ ደስታ የሚል የተደነገገ አሉታዊ ትርጓሜውም፡፡ የኛም ደመራ ለዚህ ወግ በቅታ ወዴት እንደምትወድቅ መጠበቅ ጀመርን፡፡ እስረኛውም ወደመውጫው በር ወድቆለት አመቱ የፍቺ ዓመት ነው እያለ ለማሳለፍ ተዘጋጅቷል፡፡ የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶችም ወዴት ይወደቅ ብቻ ቶሎ ይውደቅና ቆጥረውና ቆልፈውብን ለመሄድ ጓግተዋል፡፡

ቢጠበቅ ቢጠበቅ ወደታች በጥልቀት ይቅበሩት አልያም እንጨቱ እርጥብ ስለሆነ ብቻ ባልታወቀ ምክንያት ሳይወድቅ ቆየ፡፡ በዙሪያው ያለው ርብራብ ተቃጥሎ ወደአመድነት ተለውጧል፡፡ ከመሬት ትንሽ ከፍያለው ወደባቱ አከባቢ እሳት እንደበላው ያስታውቃል፡፡ ዲያቆኑም ደክሞት መዝሙር መምራቱን አቁሟል፤ ፖሊሶቹ እየተቁነጠነጡ ነው፤ ደመራው አልወደቀም፡፡ ሁሉም ሰው ግራ ገብቶት ትውፊቱን ላለመተው በግርምት ይተያያል፡፡

አንድ መላኩ የሚባል በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥሮ የገባ እስረኛ አለ፡፡ ፍርድ ቤቱ መታመሙን እርግጠኛ ባይሆንም የአእምሮ ህመምተኛ ሆኗል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲሶርደር እንዳለበት በግልጽ ያስታውቃል፡፡ ዝርዝሩን ለባለሙያዎች እንተወው፡፡ ቆሻሻ ሲያነሳ እና ሲጥል ነው የሚውለው፡፡ ሰው ሰለማይተናኮል እስረኛው ሁሉ ወዳጁ ነው፡፡ የተደራጀ ነገር ባያወራም ከመታሰሩ በፊት ኮሚክ ነገር እንደነበር ያስታውቃል፡፡ አንዳንዴ ሲለው እንግሊዘኛ ይሞካክራል ይሄን ጊዜ እስረኛው “ፓ! መሌ እኮ የተማረ ነው” ብሎ ያደንቀዋል:: ብቻ ምን አለፋቹኽ መሌ ራሱ ተረኩ ብዙ ነው፡፡

የመሌን ታሪክ መጥቀሴ አለነገር አይደለም፡፡ በዚያ ቀን እስረኛው እና ፖሊሱ ተፋጥጦ ትውፊት ላለማፍረስ የደመራውን በራሱ መውደቅ ሲጠባበቅ የመሌን ትኩረት ይስባል፡፡ መዝሙር የለ፤ እንቅስቃሴ የለ ፡፡ የሚስቅ የሚጫወት ሰውም አይታይም፡፡ ሰው ሁሉ ያን በእሳት የተበላ እንጨት በጉጉት ይመለከታል፡፡ መሌ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው? ቀጥ ብሎ ሄደና ደመራውን አንዴ በእርግጫ ሲለው በአፍጢሙ ድፍት አለ፡፡ መጻኢውን ጊዜ ለመተንበይ የፈለጉ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ቢናደዱም አብዛኛው እስረኛ ፖሊሶቹን ጨምሮ በሳቅ እያውካካ የበዐሉ ፍጻሜ ሆነ፡፡

ዛሬ እቤቴ ቁጭ ብዬ ሳስብ ያ በእሳት ተበልቶ ሳይወድቅ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የቆየ እንጨት የወያኔ መንግስት ይመስለኛል፡፡ (At least metaphorically) እንደመሌ ያለ በካልቾ ብሎ እስኪያደባያው ድረስ የሚጠብቅ ይመስለኛል፡፡ የመሌን ድርሻ የሚወስድ ማን ይሆን?

ኦሕዴድ ሊቀመናብርቱን አነሳ

ዮሐንስ አንበርብር

workineh-gebeyehu-and-muktar-kedir

– የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እየተካሄደ ነው

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ሰሞኑን ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው፣ የድርጀቱን ሊቀመንበር አቶ ሙክታር ከድርንና ምክትል ሊቀመንበሯን ወ/ሮ አስቴር ማሞን ከኃላፊነት ማንሳቱን አስታወቀ፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ማክሰኞ መስከረም 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት ላይ በፌስቡክ ገጹ እንዳሳወቀው፣ ሁለቱ አመራሮች ያቀረቡትን ጥያቄ በመቀበል ከድርጅቱ ኃላፊነት እንዲነሱ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡ በምትካቸውም የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ የሆኑን አቶ ለማ መገርሳን የኦሕዴድ ሊቀመንበር አድርጎ ሲመርጥ፣ በፌዴራል መንግሥት የትራንስፖርት ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን ደግሞ የኦሕዴድ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ ሁለቱ የድርጅቱ ሊቀመናብርት ከኃላፊነት የተነሱት ባቀረቡት ጥያቄ መሆኑን ቢገልጽም፣ የሪፖርተር ምንጮች ግን ሁለቱ ሊቀመናብርት በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው በኦሮሚያ ተስፋፍተው ዓመቱን ሙሉ ለዘለቁ ግጭቶችና የኅብረተሰቡ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ያልቻሉ ናቸው በማለት ሲወቅሳቸው እንደነበርና ሁለቱም አመራሮች ራሳቸውን መከላከል አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ለማ መገርሳ ወጣት ከሚባሉት የኦሕዴድ አመራሮች ውስጥ አንዱ ሲሆኑ፣ ኦሕዴድን የተቀላቀሉት በ1983 ዓ.ም. እንደሆነና የትውልድ ቦታቸውም ወለጋ መሆኑን ምንጮች አክለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደሆኑም ይታወቃል፡፡

የኦሕዴድ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው በወ/ሮ አስቴር ማሞ ምትክ የተሾሙት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የፌዴራል ትራንስፖርት ሚኒስትር ሲሆኑ የትውልድ ቦታቸው ሻሸመኔ ነው፡፡

አቶ ሙክታርና ወ/ሮ አስቴር ከድርጅቱ ኃላፊነት ቢነሱም፣ አቶ ሙክታር የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ጨፌ ኦሮሚያ በጥቅምት ወር መጀመርያ ላይ እስከሚሰበሰብ ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በኦሕዴድ የቆየ የአሠራር ልማድ መሠረት የድርጀቱ ሊቀመንበር የክልሉ ፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ያገኛል፡፡ በዚህ አሠራር የሚቀጥል ከሆነ ጨፌው በጥቅምት ወር መጀመርያ ላይ ሲሰበሰብ አቶ ለማ መገርሳን የክልሉ ፕሬዚዳንት አድርጎ ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ወ/ሮ አስቴር ማሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ክላስተር አስተባባሪና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትርነታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በጥቅምት ወር መጀመርያ ሳምንት ላይ አዲስ ካቢኔ እስኪያዋቅሩ ድረስ ይቀጥላሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እየተካሄደ መሆኑን የድርጅቱ መግለጫ ያመለክታል፡፡ በዚህ ስብሰባም ሹም ሽሮች እንደሚኖሩ እየተነገረ ነው፡፡ የደኢሕዴን ምክትል ሊቀመንበርና የትምህርት ሚኒትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በበኩላቸው ከፌዴራል ተቋማት የተወጣጡ የኢሕአዴግ መካከለኛ አመራሮችን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በማወያያት ላይ ናቸው፡፡
ምንጭ፡-ሪፖርተር ጋዜጣ

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አቶ አንዱዓለም አራጌ 5 ዓመት እስር እንደዋዛ

ጋዜጠኛና ጦማሪ እስክንድር ነጋ እና የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝ ፖለቲከኛ አቶ አንዱአለም አራጌ በሽብር እና በሃገር ክህደት ወንጀል ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው እስር ቤት ከገቡ መስከረም 3 ቀን 2009 ዓ.ም ድፍን አምስት ዓመት ሆናቸው፡

እስክንድር “ንፁህ ስለሆንኩኝ፣ የቀረበብኝ ማስረጃ የሌለ በመሆኑ እንዲሁም ፍርድቤቶችን የሚያህሉ የተከበሩ ተቋማት የበቀል የአፈናና የጭቆና መድረክ መሆን ስለሌለባቸው በነፃ እንድለቀቅ የተከበረውን ፍርድቤት እጠይቃለሁ” ብሎ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ይግባኙን በነሐሴ 2004 ዓ.ም ያቀረበ ቢሆንም የከፍተኛው ፍርድቤት የፈረደበትን የአስራ ስምንት ዓመት ፅኑ እስራት እና አምስት አመታት ህዝባዊ መብቶች እግድ ጠቅላይ ፍርድቤቱም አፅንቶበት የፍርዱን ሩብ አመታት በእስራት አሳልፏል፡፡

በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አዲስ አበባ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አምስት አመታትን በእስር ሲያሳልፍ ዘንድሮ የ48 አመት ጎልማሳ የሚሆነው ጦማሪው እስክንድር ነጋ በየኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ መንግስት ለሰባተኛ ጊዜ ሲታሰር በበርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብተ ተሟጋች ድርጅቶች እስራቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሆን ደምፃቸውን ከፍ አድርገው አምስቱንም አመታት ለኢትዮጵያ መንግስት ውትወታቸውን አስምተዋል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፍርድቤት የችሎት ሂደቱን በመከታተል ላይ እያለ በግንቦት ወር 2004ዓ.ም ፔን አሜሪካ ከተባለ አለማቀፍ ድርጅት በአደገኛ የመገናኛ ብዙሐን ድባብ ውስጥ ሆኖ በመፃፍ ላደረገው አስታዋፅኦዖ “የመፃፍ ነፃነት ሽልማትን” አግኝቷል፡፡ በዚሁ አመት አለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተማጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እስክንድር ነጋ የህሊና እስረኛ ስለመሆኑ አውጇል፡፡

ለሰባተኛ ጊዜ ለእስር በተዳረገ በአንድ አመት ከአራት ወራት ጊዜ ውስጥ በታህሳስ 2005ዓ.ም ደግሞ የሂውማን ራይትስ ዎች የነፃ ንግግር ሽልማት አሸናፊ ከመሆኑ በተጨማሪ በ36ተኛው አለማቀፍ የፀሃፊዎች ፌስቲቫል ላይ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ “የአንድ ስብዓዊነት ሽልማት” አሸናፊ ሆኗል፡፡

በጋዜጠኝነት ሙያው በሚሰራው ስራ የኢትዮጵያ የፀረ ሽብር አዋጅ ቀደምት ሰለባ የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር በ1997 ዓ.ም የተደረገውን አገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ መንግስት በአገር ክህደት፣ አመፅ በመቀስቀስ፣ህገ መንግስት እና ህግ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል በመናድ ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት የፈረደበት ቢሆንም አንድ አመት ከአምስት ወራት እሰራት በኃላ ክሱ ተቋርጦ መለቀቁ ይታወሳል፡፡

የኢንተርናሽናል ወመንስ ሚዲያ አሶሴሽን “የብርቱ ጋዜጠኛ” ሽልማት አሸናፊ የጋዜጠኛ እስክንድር ባለቤት ጋዜጠኛ ሰርክዓለም ፋሲልም የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ ከባለቤቷ ጋር በተመሳሳይ ክስ በአንድነት ታስራ በቃሊቲ እስር ቤት ሳለች የመጀመሪያ እና ብቸኛ ልጃቸውን ናፍቆት እስክንድርን ተገላገላለች፡፡

የያኔው ስድስተ አመት ህፃን ልጁን ከትምህርትቤት ወደ ቤት እያመጣ ሳለ በድንገት ያለምንም ማስጠንቀቂያ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው እስክንድር ነጋ እነሆ ዛሬ አብረውት ከተከሰሱት 23 አባሪዎቹ ጋር አምስት አመትን ሲደፍን የቀደሞ የአንድነት ፓርቲ ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንዷለም አራጌም የእድሜ ልክ እስራቱን በቃሊቲ ማረሚቤት እየገፋ ይገኛል፡፡

‹ምርጫ 97ን›› ተከትሎ ወህኒ ከወረደው የቅንጅት አመራር አንዱ የነበረው የያኔው ወጣት የአሁኑ ጎልማሳ፣ በብዙዋች ዘንድ የሰላማዊ ትግል አርበኛ ተበሎ የሚወደሰውአንዷለም አራጌ የቅጥት ማቅለያ እንዲያቀርብ በፍርድቤት ሲጠየቅ አንዷለም አራጌ እንዲህ ብሎ ነበር ማቅለያውን ያቀረበው፡፡ “እኔም ለልጆቼ፣ ለወገኖቼ፣ ለአገሬ እና ለራሴ በመረጥኩት ሰላማዊ ትግል ስታገል ቆይቻለሁ፡፡ የበደልኩት ህዝብ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ወንጀል ሰርቻለሁ ብዬ አላሰብም፡፡ ውስጤ ፍፁም ሠላማዊ ነው ከሳሾቼ የሚስጡኝን የግፍ ፅዋ ለመጠጣት ዝግጁ ነኝ፡፡”

አቶ አንዷለም አራጌ “ያልተሄደበት መንገድ” የሚል የመጀመሪያ መጸሐፉን በእስር ላይ ሆኖ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለአንባቢያን አደርሷል፡፡ በ2007 ዓ.ም ሰኔ ወር ደግሞ “የሀገር ፍቅር እዳ” የተሰኘው ሁለተኛ መጽሐፋ ዳግም ለህትመት በቅቷል፡፡

እስካሁንም ድረስ በእስር ላይ የሚገኙት እነዚህ የሰላማዊ ትግል አርበኞ አዲሱን አመት 2009 ዓ.ም የተቀበሉት አምስተኛ አመታቸውን በማሰብ ነው፡፡

እስክንድር ነጋ እና አንዷዓለም አራጌ በፍትህ እጦት አመታትን በእስር እንዲያሳልፉ ሲገደዱ እስራቸው አገሪቷ በዓለም አቀፍ ህግ መደረክ ተገዢ እሆናለሁ ብላ ቃል የገባችባቸውን የቃልኪዳን ሰነዶች ሁሉ የናደ ሰለመሆኑ የሰበዓዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ሲሞግቱ አምስት አመታት አልፈዋል፡፡

ዛሬም አስራቸው ህገ መንግስቱን የጣሰ፣ አላግባብ፣ ኢፍታዊ እና የሰብዓዊ መብቶቻቸውን ያላከበረ ነው ፡፡ አንዱአለም በተለምዶው ቅጣት ቤት ተብሎ የሚጠራው ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ክፍል ውስጥ ታስሮ ሲገኝ እስክንድር በቃሊቲ የተለያዩ ዞኖች ታስሯል፡፡ ሁለቱም እስረኞች ከቅርብ ቤተሰብ ውጪ ማንም እንዳይጠይቃቸው የተከለከሉ ሲሆን ከእስራቸው እስከ አያያዛቸው ኢሰብአዊነትን እያስተናገዱ አምስት አመት አስቆጥረዋል፡፡
ምንጭ፡- EHRP

በደብረ ታቦር ማረሚያ ቤት ቃጠሎ በእስረኞች ላይ ጉዳት ደረሰ

በባህር ዳር በአበባ እርሻዎችና በሌሎች ንብረቶች ውድመት ደርሷል

– የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አሳስቦኛል አለ

በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ደብረ ታቦር ማረሚያ ቤት በደረሰ ቃጠሎ በእስረኞች ላይ ጉዳት ደረሰ፡፡ የመከላከያ ሠራዊት እስረኞች እንዳያመልጡ ዙሪያውን ከቦ እንደነበርና ሊያመልጡ የነበሩ በርካታ እስረኞች መሞታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የእሳት አደጋው የተከሰተው ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ እስረኞቹ ከአደጋው ለማምለጥ መሞከራቸውን አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አካባቢውን በፍጥነት የከበበው የመከላከያ ሠራዊት እስረኞቹ እንዳያመልጡ ሲተኩስ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

debre-tabor-prison-fire

በእሳት አደጋው ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት በማረሚያ ቤቱ ላይ መድረሱንና ሊያመልጡ በነበሩ እስረኞች ላይም ጉዳት እንደደረሰ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ማረሚያ ቤቶች መምርያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር መንጌ ከበደ ቃጠሎው የተነሳው በኤሌክትሪክ መስመሮች መገናኘት መሆኑን ገልጸው፣ ሊያመልጡ የነበሩ ሁለት እስረኞች መገደላቸውንና ከእስረኞች ደግሞ ሁለት መቁሰላቸውን አስረድተዋል፡፡
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተስፋፋ የሚገኘው አመፅ፣ ከመንግሥት ጋር ቁርኝት አላቸው በተባሉ የግል ባለሀብቶች ንብረቶችና የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጉዳት እያደረሰ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ኢስመራልዳ (Esmeralda Farms) የተባለው በባህር ዳር የሚገኘው የኔዘርላንድ ባለሀብቶች የአበባ እርሻ በእሳት ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡
መቀመጫውን በኔዘርላንድ ያደረገው የአበባ ኩባንያው ዋና ቢሮ ባወጣው መግለጫ፣ በፖለቲካ ተቃውሞው ምክንያት በባህር ዳር የሚገኘው የአበባ እርሻ (ኮንዶር ፋርም) በእሳት ሙሉ በሙሉ መውደሙንና የኩባንያው አጠቃላይ ኢንቨስትመንት አሥር ሚሊዮን ዩሮ እንደሆነም አስታውሷል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኘው ቢሮ ጋር መገናኘት አለመቻሉን የሚገልጸው መግለጫው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጃችን በቀውሱ ምክንያት ከአካባቢው በመልቀቃቸው መረጃዎችን ማግኘት አልተቻለም፤›› ብሏል፡፡

በመንግሥት ላይ የተነሳው ተቃውሞ በአካባቢው በሚገኙ የአበባ እርሻዎች ላይ ጉዳት ማድረስ መቀጠሉንና አሥር ያህል የአበባ እርሻዎች መቃጠላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ኮንዶር ፋርም የተባለው የአበባ እርሻ ሲቃጠል በአካባቢው የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች የነበሩ ቢሆንም፣ ጉዳቱን ያደረሱት ከፀጥታ ኃይሎች ቁጥር በብዛት የሚበልጡ በመሆናቸው ማዳን አለመቻሉን ኩባንያው ገልጿል፡፡
መጋዘኖች፣ የማቀዝቀዣ ክፍሎች፣ ትራክተሮች፣ የጭነት ተሽከርካሪዎች፣ ኮንቴይነሮችና ማሸጊያዎች በሙሉ በእሳት መውደማቸውን አስታውቋል፡፡

‹‹ሁሉም ጠፍቷል፡፡ የአሥር ሚሊዮን ዩሮ ኢንቨስትመንትና የረጅም ዓመታት ጥረት በአንድ ቀን ወድሟል፤›› ሲል በመግለጫው የደረሰውን ጉዳት አመልክቷል፡፡

ሌላው በየመኑ ባለሀብት መሐመድ አልካሚን የተቋቋመውና ከ500 በላይ ሠራተኞች የነበረው የአበባ እርሻ ይገኝበታል፡፡
ለባህር ዳር ከተማ የውኃ አቅርቦት ምንጭ የሆነው እንፍራንዝ ከተማ አካባቢ የሚገኘው የጥቁር ውኃ የውኃ ማጠራቀሚያ ጋንም ቃጠሎ ደርሶበታል፡፡ ይህም በከተማዋና በአካባቢዋ የውኃ አቅርቦት ላይ እጥረት እንደሚያስከትል እየተነገረ ነው፡፡
በተያያዘ ዜና በክልሉ ውስጥ ያለው ተቃውሞ እየተባባሰና በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች እያሳዩ ነው፡፡

በተለይም ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለማስቆም የፀጥታ ኃይሉ ሕግ እንዲያስከብር ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ከገለጹ ጀምሮ ሰዎች መሞታቸውን፣ የዘር ጥቃት ተፈጸመባቸው የተባሉ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገር እየተሰደዱ መሆናቸው እየተገለጸ ነው፡፡

በተለይ በአምባ ጊዮርጊስ፣ በደብረ ታቦር፣ በመተማ ዮሐንስና በአጎራባች አካባቢዎች የሰው ሕይወት መጥፋቱን የሚገልጹ ቁጥሮችም እየጨመሩ ስለመውጣታቸው መረጃዎች እየጠቆሙ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት በኩል እስካሁን ምንም ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልተሰጠም፡፡

ሪፖርተር ከምንጮች ማረጋገጥ እንደቻለው በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የመከላከያ ሠራዊት እየገባ ሲሆን፣ የከባድ መሣሪያ ተሽከርካሪዎች መታየታቸውን ለማወቅ ችሏል፡፡

የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ በክልሉ ምዕራባዊ አካባቢዎች ሁከት መከሰቱን ተናግረዋል፡፡ በአንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች የተነዛ መረጃ ሕዝቡን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መምራቱንና በተፈጠረው ሁከትም በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ግጭት እያሳሰበው መምጣቱን ጠቁሞ፣ ሁሉም ወገኖች ከማንኛውም ግጭት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ዓርብ ነሐሴ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹በአገሪቱ የማኅበራዊ ፖለቲካው የሰው ሕይወት ማጥፋት፣ በንብረቶች ላይ ውድመት ማስከተል፣ እንዲሁም የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት እስከማቋረጥ ደረጃ መድረሱ አሳሳቢ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሊቀመንበሯ አክለው ሁሉም ወገኖች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ በማመዘን ለሕግ መከበር እንዲተጉ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብትና የዴሞክራሲ ባህልና መርሆችን እንዲያከብሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ

በአዲስ አበባ አቃቂ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በደረሰ የእሳት አደጋ ከ25 ያላነሱ እስረኞች ህይወት አለፈ

(አዲስ ሚዲያ)ዛሬ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አበባ አቃቂ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ከ25 ያላነሱ እስረኞች መሞታቸው ተጠቆመ፡፡ በጥበቃ ላይ የነበሩ ወታደሮችም ከእሳቱ ለማለጥ የሞከሩ እስረኞች ላይ ሲተኩሱ እንደነበር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ከቃጠሎው በፊት በነበረው ተኩስ ምን ያህል እስረኞች ላይ ጉዳት እንደደረሰ እስካሁን ማረጋገጥ ባይቻልም፤ በነጋታው ጠዋት በነበረው የእሳት አደጋ ከ25 ያላነሱ ሰዎች መሞታቸውን ከቅዱስ ጳውሎስ፣ ሜክሲኮ በሚገኘው ፖሊስ ፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ እና የካቲት 12 ሆስፒታል ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቃጠሎው ጉዳት የደረሰባቸውና በህይወት የተረፉትም አብዛኞቹ ፖሊስ ሆስፒታልና የካቲት 12 ሆስፒታል በጥበቃ ስር ሆነው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

Addis Ababa Akaki Kilinto Prison

በወህኒ ቤቱ ታስረው ከሚገኙት መካከል ስመጥር እና ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸው በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ያሉበት ሲሆን በተለይም፤ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ፖለቲከኞች፣ የመብት አራማጆች እና ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት ይታወቃል፡፡

በያዝነው 2008 ዓ.ም. ብቻ ከአዲስ አበባ አቃቂ ከሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በተጨማሪ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች የሚገኙባቸው ጎንደር፣ አምቦና ደብረ ታቦር ወህኒ ቤት በተመሳሳይ መልኩ የእሳት አደጋ ሰለባ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ በነበሩ አደጋዎች መንስኤ እና ጉዳትን በተመለከተ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም ከመግለፅ መቆጠቡ ይታወቃል፡፡

በተለይ የአቃቂ ቂሊንጦውን እሳት ቃጠሎ ተከትሎ በርካታ የታሳሪ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች እና ደጋፊዎች ስጋት እንዳደረባቸው በተለያየ መድረክ ከመግለፅ በተጨማሪ በአዲስ አበባና አጎራባች አካባቢ ያሉ ሰዎች የቤተሰቦቻቸውን ደህንነት ለማጣራት ሙከራ ቢያደርጉም በወህኒ ቤቱ አስተዳደር እንዳልተፈቀደ ተረጋግጧል፡፡ በወህኒ ቤቱ የታሰሩ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ከተለያዩ የክልል ከተሞች የመጡ ሰዎችም ወደ እስር ቤቱ ግቢም ሆነ ከግቢ ውጭ በቅርብ ርቀት እንዳይጠጉ በመከልከላቸው ወደየመጡበት መመለሳቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

በአደጋው የደረሰውን ጉዳትና ምክንያት በተመለከተ የወህኒ ቤቱ አስተዳደርም ሆነ መንግሥት እስካሁን የሰጡት መረጃ የለም፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ ሰዎች አደጋው በመንግሥት ሆን ተብሎ የተቀነባበረና የፖለቲካ እስረኞችን ለመጉዳት የታሰበ የገዥው ስርዓት የተለመደ ስልት እንደሆነ የሚገልፁ ቢኖሩም፤ ስለ አደጋውና አጠቃላይ መረጃ ከገለልተኛ አካልም ሆነ ከመንግሥት ለማወቅ አልተቻለም፡፡