የጋዜጠኞቹ እና ብሎገሮቹ አቤቱታዎች ውድቅ ተደረጉ
በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የሚገኙት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ሦስቱ ወዳጅ ጋዜጠኞች መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም ከሰዓት 8፡00 የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡
መዝገቡ ተቀጥሮ የነበረው ተከሳሾች ባቀረቧቸው ሁለት አቤቱታዎች ላይ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ በዚህም አንደኛ አቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ አለኝ ካለው ማስረጃ ዝርዝር ውስጥ 12 የኦዲዮ-ቪዲዮ ሲዲዎች አያይዞ ያቀረበ ቢሆንም፣ ሲዲዎቹ ለተከሳሾች እስካሁን ባለመድረሳቸው ተከሳሾች የቀረበባቸውን ማስረጃ ተመልክተው መልስ ለማዘጋጀት ሲዲዎቹ እንዲሰጧቸው ያቀረቡት አቤቱታ ሲሆን፣ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ 4ኛ ተከሳሽ ማህሌት ፋንታሁን እና 9ኛ ተከሳሽ ኤዶም ካሳዬ በቃሊቲ እስር ቤት አስተዳደር ላይ ከጎብኝዎቻቸው መከልከል ጋር በተያያዘ አቅርበውት በነበረው አቤቱታ ላይ ብይን መስጠት ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም ሁለቱንም አቤቱታዎች ውድቅ አድርጓል፡፡
የሲዲ ማስረጃውን በተመለከተ አቃቤ ህግ ማስረጃዎችን ኢግዚቪት ብሎ ስላስመዘገበ አሁን በዚህ ደረጃ ሲዲዎቹ ለተከሳሾች የሚደርሱበት አግባብ የለም በሚል ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን አቤቱታ እንዳልተቀበለው ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ማስረጃ በመስማት ሂደት ወቅት ማስረጃዎችን እየተመለከቱ መልስ እንዲሰጡ እንጂ ቀድሞ እጃቸው የሚደርስበት አሰራር የለም ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡
ፍርድ ቤቱ የቃሊቲ እስር ቤት አስተዳደር ላይ በሁለቱ ሴት ተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታም ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታ እና የእስር ቤቱ አስተዳደር የሰጠውን መልስ መመልከቱን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ “ለቀረበው አቤቱታ ማስረጃ ተያይዞ ያልቀረበ በመሆኑ…” በሚል አቤቱታውን ቅድቅ አድርጓል፡፡ ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ከሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2007 ጀምሮ ለሦሰት ቀናት ይሰማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ድብደባ ተፈፀመባቸው
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በዘለዓለም ወርቃገኘው የክስ መዝገብ የተከሰሱት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በመያዝ የሕግ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ድብደባ ተፈፀመባቸው፡፡ ድብደባው የተፈፀመባቸው ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ..ም. እነ አብርሃ ደስታ በነበራቸው የፍርደ ቤት ቀጠሮ ተገኝተው የሚጠበቅባቸውን የሕግ አገልግሎት ሰጥተው ከፍርደ ቤት ከወጡ በኋላ ብሔራዊ አረቄ ፋብሪካ አካባቢ ወደ አዋሳ ለሌላ የህግ አገልግሎት ለመስጠት እያመሩ በነበረበት ወቅት በማያውቁት ግለሰብ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክታል፡፡
ደብዳቢው ግለሰቡ ድብደባ ከፈፀመ በኋላ እሮጦ ለማምለጥ ሲሞክር በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ትብብር የተያዘ ሲሆን፤ በወቅቱም ደብዳቢው የአእምሮ ችግር እንዳለበት ለመምሰል ከሞከረ በኋላ የብአዴን-ኢህአዴግ አባል እንደሆነና 400 ብርም እንደተከፈለው መናገሩን እንዲሁም አዲስ አበባ ለቡ አካባቢ 105 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቶት ቤት እየሰራ እንደሆነ መግለፁን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጠበቃ ተማም ነገ አዋሳ ላይ ሌላ የነ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ የፍርድ ቤት ጉዳይ ስላለ ዛሬ የግድ ሄደው ማደር ስለነበረባቸው ደብዳቢውን እንዲለቀቅ አድርገው ወደ አዋሳ ማምራታቸው ታውቋል፡፡
ጠበቃ ተማም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በተጨማሪ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን፣ የተለያዩ ጋዜጠኞችን፣በሀገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን እና ሌሎች በርካታ የህግ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ለማኀበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከጥብቅና አገልግሎት በተጨማሪ በተለያዩ ጋዜጦች የህግ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ይፅፉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚህም ከመንግሥትና ከስርዓቱ ደጋፊዎች ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ቅጣት ተላለፈባቸው
᎐ተጨማሪ ቅጣትም ይጠብቃቸዋል፡፡
• “እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው” አብርሃ ደስታ
• “ችሎቱ ላይ ያጨበጨብነው በማፌዝ ሳይሆን በምሬት ነው” የሺዋስ አሰፋ
• “ፍትህ ተጠምተናል፣ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!” ዳንኤል ሺበሽ
በዘለዓለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ከስምንት ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነት እንዲሁም የዓረና ትግራይ ፓርቲዎች አመራሮች ‹ችሎት በመድፈር ወንጀል› ጥፋተኛ በመባላቸው ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት በሦስቱ አመራሮች ላይ እያንዳንዳቸው በሰባት ወራት እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡
የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም ተከሳሾች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸውና ንብረትም እንደተወሰደባቸው በመግለጽ አቅርበውት ለነበረው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ሙሉ ለሙሉ በመቀበል አቤቱታቸውን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ 5ኛ ተከሳሽ አቶ የሺዋስ አሰፋ በማጨብጨቡና 3ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታና 4ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሽ ሳይፈቀድላቸው ‹‹ጥሩ ፍርድ፣ ጥሩ ብይን›› በማለት አቶ የሺዋስን በመደገፍ ችሎት ደፍረዋል ተብለው ጥፋተኛ መሰኘታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ ለዛሬ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ተሰይሞ በአብርሃ ደስታ፣ በየሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽ ላይ የ7 ወራት እስራት በይኖባቸዋል፡፡ ሦስቱም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ድጋሜ ችሎት ውስጥ አጨብጭበዋል፡፡ በዚህም ድጋሜ ጥፋተኛ ተብለዋል፤ ከሁለት ቀናት በኋላም የቅጣት ውሳኔ ይወሰንባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሦስቱ ተከሳሾች ‹‹እድል ስጡን እንናገር፣ አቤቱታም አለን ተቀበሉን›› ቢሉም ፍርድ ቤቱ ሊሰማቸው አልፈለገም፡፡
በተለይ ዳንኤል ሺበሺ ‹‹ሌላ አቤቱታ አለኝ፣ ፍርድ ቤቱ ያዳምጠኝ›› ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ አሁንም ችሎቱ ላይ እያፌዛችሁ ነው በሚል ጥፋተኛ ሲላቸው ሦስቱም አመራሮች ፍርድ ቤቱን ማስፈቀድ ሳያስፈልጋቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው፡፡ ‹Already› የተደፈረ ችሎት ነው›› ሲል አብርሃ ደስታ ተናግሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ዳኞቹ ጣልቃ በመግባት፣ ‹‹የምትናገረው ነገር እንደገና ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሚወስድህ ጉዳይ ነው፤ ምርመራ ይደረግበታል›› ሲሉ አብርሃ በበኩሉ ‹‹አሁንስ ቢሆን የምናገረውን ፖሊስ እየሰማ አይደለምን?›› ሲል መልሷል፡፡ አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ ‹‹ከስምንት ወር በላይ ታፍነናል፡፡ በህግ አይደለም የተያዝነው፡፡ ደግሞ ማጨብጨባችን በችሎቱ ከማፌዝ ሳይሆን ከምሬት በመነጨ ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ መብታችን ተጥሷል፡፡ እኔ ለምሳሌ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆኔ ነው የታሰርኩት፡፡›› ብሏል፡፡
አቶ ዳንኤል ሺበሽ ድግሞ ‹‹አሁንም ችሎት ደፍራችኋል ካላችሁ ቅጣቱን ጨምሩብንና ሸኙን፡፡ በእርግጥ ዳኞች ላይ ያለውን ጫና እንረዳለን፡፡›› ሲል ችሎት ውስጥ ተናግሯል፡፡
በዚህ ሁኔታ በተከሳሾችና በችሎቱ መካከል ያለው አለመግባባት ሲጨምር ዳኞቹ መጋቢት 3/2007 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የቅጣት ውሳኔ እንደሚሰጥ በመጥቀስ ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት በፖሊስ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ከችሎት እየወጡ እያሉም አቶ ዳንኤል ሺበሽ ‹‹ፍትህ ተጠምተናል፤ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!›› እያለ ችሎቱን ለቅቆ ወጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት መውጣታቸውን ተከትሎ፣ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቱ ላይ በቀረበው አቤቱታ ዳኞች በሰጡት አስተያየት ላይ አቤቱታ አቅርቦ እንደነበር በማስታወስ አቤቱታው እንዲመዘገብለት የጠየቀው አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ‹‹በበኩሌ ያሉኝን መረጃዎች እያቀረብኩ ስነ-ስርዓቱን አክብሬ ክርክሩን አቀጥላለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ- ኢትዮጵያ
ከምርጫው ውጭ እንዲሆን የተደረገው አንድነት ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ላይ ያቀረበው ክስ ለየካቲት 27 ተቀጠረ!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በብሔራዊ ምርቻ ቦርድ አማካንነት ከግንቦቱ 2007 ዓ.ም. ሀገር አቀፍ ምርጫ ውጭ እንዲሆን መደረጉን በመቃወም በፌደራሉ ከፍኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ በፍትሐ ብሔር 11ኛ ችሎት የመሰረተው ክስ ለየካቲት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠዋት ተቀጠረ፡፡
ይህንንም በተመለከተ ፓርቲው በማኀበራዊ ሚዲያ ገፁ ላይ “ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በምርጫ ቦርድ እና በኢህአዴግ ሴራ ለእነ አቶ ትዕግስቱ አወሉ በኃይል ተላልፎ መሰጠቱ የሚታወቅ ነው። በዚህም ምክንያት ህጋዊው የአንድነት አመራር በምርጫ ቦርድ ላይ ክስ መስርተዋል፤ ፍርድ ቤቱ ልደታ በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት 11ኛ ፍትሀ ብሔር ችሎት ለየካቲት 27 ከጠዋቱ 3:30 ጉዳዩን ለማየት ቀጠሮ ሰጥተዋል፤ በመሆኑም በቅርብ የምንገኝ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች በችሎቱ ላይ በአካል በመገኘት ለህጋዊው አንድነት ያለንን አጋርነት እንድናሳይ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።” ብሏል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦር ከተመሰረተ ጀምሮ ከገዠው ህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ጠንካራ ተፎካካሪ ናቸው ተብለው የሚገመቱትንና በከደፍተኛ ደረጃ የህዝብ ተቀባይነት ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም ከዚህ በፊት የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረንስ(ኦብኮ)ን ያፈረሰ ሲሆን፤ በቅርቡ ደግሞ የግንቦቱ ምርጫ 2007 ዓ.ም. ዋዜማ ላይ አንድነት ፓርቲን እና መኢአድን በማፍረስ ምርጫ ቦርድ ያፈረሳቸውን ፓርቲዎች ስም ለፈለጋቸው ሰዎች መስጠቱን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
የዞን 9 ብሎገሮችና 3ቱ ጋዜጠኞች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ
∙ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል
በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው 6ቱ የዞን 9 ብሎገሮችና 3ቱ ጋዜጠኞች ዛሬ የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ለ20ኛ ጊዜ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ሲሆን፣ በዚህ መሰረትም ተከሳሾች ከችሎት እንዲነሱ አቤቱታ ያቀረቡባቸው ሰብሳቢ ዳኛ ሳይቀየሩ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡ በመሆኑም ከሁለተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ ጀምሮ እያንዳንዳቸው ‹‹በክሱ ላይ የተጠቀሰውን ወንጀል ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም?›› የሚል ጥያቄ እየቀረበላቸው ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
በዚህ መሰረት ሁሉም ተከሳሾች የቀረበባቸውን የሽብር ክስ እንዳልፈጸሙ ለችሎቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉን ጨምሮ ተከሳሾቹ ክሱን በተደጋጋሚ ቢያነቡትም ግልጽ ሊሆንላቸው እንዳልቻለ ቢገልጹም የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠት እንዳለባቸው ተገልጾ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ የተጠቀሰውን ክስ እንዳልፈጸመ በመግለጽ “ህግ የተከበረበት ሀገር ቢሆን ኖሮ በእኔ ቦታ ከሳሾቼ ነበሩ መቆም ያለባቸው” ብሏል፡፡ ሌሎችም እንዲሁ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡ 10ኛ ተከሳሽ ተስፋለም ወልደየስ በበኩሉ፣ “እኔ ጋዜጠኛ ነኝ፤ ጋዜጠኝነት ወንጀልም ሽብርም አይደለም፡፡ ጥፋተኛ አይደለሁም” ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ አቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያሰማ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ከመጋቢት 21-23 ቀን 2007 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት ቀጠሮ መስጠቱን የነገረ-ኢትዮጵ ዘገባ አመልክቷል፡፡




