የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ‘ሰጡ’
“ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው አሸባሪ ህወሓት/ኢህአዴግ ነው” አብርሃ ደስታ
“የጦር ችሎት በሚመስል ችሎት እየተንገላታን ነው” የሺዋስ አሰፋ
በዘለዓለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገቡ የተካተቱ ተከሳሾች በተከሰሱበት ድርጊት ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ፡፡
የሰማያዊ፣ የአንድነት እና የዓረና ትግራይ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ 10 ተከሳሾች መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህ መሰረት ከአንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ጀምሮ፣ “በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም?” የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ ለእያንዳንዳቸው የቀረበላቸው ሲሆን ብዙዎቹ ተከሳሾች ምላሻቸውን በቀጥታ ለመስጠት አለመፈለጋቸውን አሳይተዋል፡፡
1ኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ለቀረበለት ጥያቄ፣ “በአቃቤ ህግ እና በፖሊስ ተቀነባብሮ የቀረበብኝን ክስ በተመለከተ ለክሱ እውቅና ላለመስጠት ምንም አልልም፡፡ በክሱ ላይ አስተያየት በመስጠት ለጸረ-ሽብር አዋጁ እውቅና መስጠት አልፈልግም” የሚል መልስ በመስጠቱ ፍርድ ቤቱ ክሱን ክዶ ቃል እንደሰጠ አድርጎ መዝግቦታል፡፡
2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው በበኩሉ “በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት እንዳልፈጸምኩ እንኳን እኔ ከሳሾቼም በደንብ ያውቃሉ፡፡ ከሳሾቼ እኔ ድርጊቱን የመፈፀም ፍላጎቱም ሀሳቡም እንደሌለኝ ያውቃሉ” ብሏል፡፡
3ኛ ተከሳሽ ዳንኤል ሺበሽ ደግሞ፣ “እኔ ስለ ሽብር የሰማሁት ከአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢላደን እና መለስ ዜናዊ ነው፡፡ እኔ አሸባሪ አይደለሁም፤ ሀሳቡም ሆነ ፍላጎቱም የለኝም፡፡ ባህሌና እምነቴም አይፈቅድልኝም” ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
4ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታ “አሸባሪ ማለት የፖለቲካም ሆነ ሌላ ዓላማውን ሰላማዊ ዜጎችን በማሸበር ለማስፈፀም የሚሰራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው አሸባሪ ድርጅት ህወሓት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ ደግሞ የዚህ አሸባሪ ድርጅት ተቃዋሚ ነኝ” ብሏል፡፡
5ኛ ተከሳሽ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ፣ “በመጀመሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ስለሆነ የምናገረው እንዳታቋርጡኝ አደራ እላለሁ፡፡ ክሱ ቅንብር ነው፡፡ ዳኞችም ህጉ የሰጣቸው ነጻነት አይታይባቸውም፡፡ ይህ 19ኛ ወንጀል ችሎት የጦር ችሎት ነው የሚመስለኝ፡፡ ስለሆነም የጦር ችሎት በሚመስል ችሎት እየተንገላታን ነው” ሲል ተናግሯል፡፡ የሺዋስ በዳኞች በተደጋጋሚ ንግግሩ እንዲቅረጥ ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም ክሱን ክዶ ቃል ሰጥቷል በሚል ተመዝገቦለታል፡፡
6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ፣ “የተዘጋጀብኝን ክስ ያለፍቃዴ እንድተውን እየተገደድኩ ነው” ብሏል፡፡
7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን ደግሞ፣ “የተቀነባበረ ክስ ላይ ምንም ማለት አይቻልም” ብሏል፡፡
8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ፣ “ነፃ ሰው ነኝ፡፡”
9ኛ ተከሳሽ ባህሩ ደጉ “ባህሉንና ፈጣሪውን ከሚያከብር ማህበረሰብ ወጥቼ አሸባሪ ልሆን አልችልም” ሲል አስረድቷል፡፡
10ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ተፈሪ ደግሞ፣ “ድርጊቱን አልፈጸምኩም” ብሏል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾች ክሱ ላይ የተጠቀሰውን ድርጊት ክደው ቃል በመስጠታቸው አቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያሰማ ለግንቦት 13፣ 14፣ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ለተከታታይ 3 ቀናት ምስክር እንዲሰማ ቀጠሮ መሰጠቱን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክታል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ
በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱት ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ ያቀረቡት መቃወሚያ ውድቅ ተደረገባቸው፡፡ አመራሮቹ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ችሎት ቀርበዋል፡፡
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የተከሰሱት የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና ሌሎች ስድስት ተከሳሾች መቃወሚያቸው በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጓል፡፡
ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የቀረቡባቸው የተለያዩ የክስ ይዘቶች ላይ መቃወሚያቸውን አቅርበው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ የተከሳሽ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት የጠየቀውን በመቀበል ‹‹በመቃወሚያው ላይ የተነሱት ነጥቦች በአብዛኛው ማስረጃ በማሰማት ሂደት ወቅት ሊረጋገጡ የሚችሉ ስለሆኑ›› በሚል መቃወሚያቸው ውድቅ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤት በቀረበው ክስ አግባብ የክስ ሂደቱ እንዲቀጥል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች በእስር ላይ በሚገኙበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ ‹‹የመብት ጥሰት እየተፈጸመብን ነው›› በሚል አቤቱታ አቅርበው የነበር ሲሆን በአቤቱታው ላይ እስካሁን ከማረሚያ ቤቱ መልስ አለመሰጠቱ ታውቋል፡፡ አቤቱታው በጽሑፍ ተገልብጦ ለማረሚያ ቤቱ መላኩን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ ለአቤቱታው መልስ ከማረሚያ ቤቱ እየተጠበቀ እንደሆነ ተገልጹዋል፡፡
በመሆኑም ይህንኑ የማረሚያ ቤቱን መልስ ለመስማትና የክሱን ሂደት ለመቀጠል ፍርድ ቤቱ ለየካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡-ነገረ-ኢትዮጵያ
