Daily Archives: July 2nd, 2016

መንግሥት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 አካባቢ 6 ያህል ነዋሪዎች ገድሎ ከ3 ሺህ ያላነሱ ነዋሪዎችን ቤት አፈረሰ

(አዲስ ሚዲያ) በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፈለ ከተማ ወረዳ 1 በተለምዶ ሐና ማርያም፣ ፉሪ፣ ቀርሳ፣ ኮንቱማ እና ማንጎ ጨፌ አካባቢ ነዋሪዎች ላይ መንግሥት በወሰደው የኃይል ርምጃ አንዲት ነፍሰጡር እናት እና አንድ ቄስን ጨምሮ 6 ያህል ሰዎች ሲገደሉ፤ ከ 3 ሺህ ያላነሱ የመኖሪያ ቤቶች በዶዘር እየፈረሰ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ መንግሥት የኃይል ርምጃውን የወሰደው ሐሙስ ሰኔ 23 እና ትናንት አርብ ሰኔ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆን፤ በአካባቢው ህፃናት፣ ሴቶች እና ነፍሰጡር የሆኑ እናቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸው ታውቋል፡፡ በተለይ አንዲት ነፍሰጡር እናት በቤቷ ተኝታ እያለ፤ ቤቷ በዶዘር ሲፈርስ እዛው መገደሏም ተሰምቷል፡፡

NFSL demolishing In Addis

የቤቶቻቸውን በክረምት መፍረስና የመንግሥትን የኃይል ርምጃ የተቃወሙና በጉዳዩ ዙሪያ የሌሉትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውም የተገለፀ ሲሆን፤ የአካባቢው ወንዶች እየፈረሱ ባሉ ቤቶች አካባቢ እንዳይገኙ አካባቢው በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መውደቁ ታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ከቤቶቻቸው መፍረስ በተጨማሪ የመንግሥትን ግድያ እና እስር በመፍራት ከአካባቢው መሰደዳቸው ተጠቁሟል፡፡

መንግሥት የነዋሪዎቹን ቤት በክረምቱ የዝናብ ወቅት ጠብቆ ለምን ማፍረስ እንደወሰና እንደጀመረ ባይታወቅም፤ እንዲፈርሱ የተወሰኑ ቤቶችን የማፍረስ ስራው እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ በአካባቢውም ቤቶቻቸው በዶዘር እንዲረስ የተደረጉባቸው ሰዎች ንበርትም አብሮ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን መደረጉን የአካባቢው ሴቶች ይናገራሉ፡፡

ቀደም ሲል ረቡዕ ሰኔ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. መንግሥት ወደ 30 ሺህ የሚጠጋ የነዋሪዎችን ቤት “ህገወጥ ነው፣ መፍረስ አለበት” በሚል መወሰኑን ተከትሎ ቅሬታ በመቅረቡ፣ የአካባቢው ወረዳ 1 አስተዳደር ነዋሪውን በቦታውና በቤቶቹ ጉዳይ እንነጋገር ብሎ ሰብስቦ እያወያየ ሳለ፤ በጎን አፍራሽ ግብረ ኃይልና የፀጥታ ኃይል ልኮ ማፍረስ በመጀመሩ በተፈጠረ አለመግባባት የወረዳው ስራ አስፈፃሚ እና ፖሊሶች መገደላቸውን፣ ከነዋሪዎችም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸው ይታወሳል፡፡

ከቤቶቹ መፍረስ ጋር በተያያዘ የሰብዓዊ መብት ጉባዔ (ሰመጉ)፤ መንግሥት ከ19 ሺህ ያላነሱ ቤቶችን ማፍረሱን በመጠቆም፤ እየተወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃ እንዲያቆምና ቤቶቹን አፍርሶ ነዋሪዎቹን ለጎዳና ህይወት ከመዳረግ ይልቅ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠይቋል፡፡

 

በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አወዳይ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት 4 ሰዎች ተገደሉ

(አዲስ ሚዲያ)በምስራቅ ሐረርጌ ዞን አወዳይ ከተማ ትናንት ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት በመንግሥት ኃይሎች እና በህዝቡ መካከል በተፈጠረ ግጭት የ9 ዓመት ህፃንን ጨምሮ 4 ያህል ነዋሪዎች በከተማው አስተዳደርና በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው የሚገኘው የሐሮማያ ሆስፒታል በበኩሉ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 4 መሆኑን እና የቆሰሉ 3 ሰዎች በሆስፒታሉ የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው ተጠቁሟል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 6 እንደሆነ እና በፅኑ የቆሰሉት ደግሞ 4 እንደነበሩ ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡

Aweday firing

በዕለቱ የግጭቱ መነሻ እንደሆነ የተነገረው በአወዳይ ከተማ ውስጥ ያለ አንድ የሞባይል ስልክ መሸጫ ሱቅና አጠገቡ ያለው የፍራሽ መሸጫ ሱቅ ባልታወቀ ምክንያት በመቃጠላቸው የተነሣ የአከባቢው ህዝብ እሳቱን ለማጥፋት ጥረት ቢያደርግም ሊሳካ ባለመቻሉ በአከባቢው ያሉትን የባለሥልጣናት ለእርዳታ ቢማፀኑም ቆመው ከመሳቅ ባለፈ ምንም እርዳታ ባለማድረጋቸው የተበሳጩ ነዋሪዎች “ድሮም እናንተ የምታደርጉልን ነገር የለም” ስለዚህ ከዚህ ሂዱ ብለው በመናገራቸው የፀጥታ ኃይሎች በስልክ ወደ ቦታው መጠራታቸውንና ግጭቱ መከሰቱን የአካባቢውን ነዋሪ ዋቢ በማድረግ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የነጋዴዎቹን ሱቅ ቃጠሎ ተከትሎ በህዝቡና በመንግሥት በተለይም በአካባቢው አስተዳደር አካለትና የፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የአወዳይ ቀበሌ 02 ሊቀመንበር አቶ አብዲ ኢድሪስ በቃጠሎው ስፍራ የነበሩ ነዋሪዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ የ9 እና የ13 ዓመት ህፃናት ቆሰሉ፡፡ በሊቀመንበሩ የቆሰሉ ህፃናትም ወደ አካባቢው የጤና ተቋም ቢወሰዱም ወዲያው ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች በቁጣና በጩኸት ወደቆሰሉ ህፃናት ሲመጡ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ እና የፌደራል ፖሊስ በድንገት ወደስፍራው በመምጣት፣ አንድ የፌደራል ፖሊስ አባል ተኩስ ከፍቶ 3 ወጣቶች ወዲያው ሲገደሉ፤ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችም በፅኑ መቁሰላቸውን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኝ ተናግረዋል፡፡

Aweday town protest

በመንግሥትና በህዝቡ መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በአወዳይ የሐረር መንገድ ዝግ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ይሁን እንጂ በግጭቱ ዙሪያ እስካሁን ከመንግሥት አካል የተሰጠ መግለጫም ሆነ ማብራሪያ ማግኘት አልተቻለም፡፡

%d bloggers like this: