Daily Archives: July 15th, 2016

እነ በቀለ ገርባ ላቀረቡት የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ምላሽ ለመስጠት ዳግም ቀጠሮ ሰጠ

– አቶ ደጀኔ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት እንዲችሉ ፍርድቤቱ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
– አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ደጀኔ ጣፋ በሀኪም የታዘዘላቸውን መድሃኒት እንዳያገኙ መደረጋቸውን ለችሎት በድጋሚ አቤት ብለዋል፡፡
– አቶ ጉርሜሳ አያኖ ጆሮቸውን ሰለታመሙ ህክምና እንዲያገኙ ፍርድቤቱን ጠይቀዋል፡፡
– ተከሳሾች ቅሊንጦ ማረሚያቤት ሲገቡ ማረሚያቤቱ የወሰደባቸው 825 ብር እንዲመለሰላቸው ጠይቀው፡ ማረሚያ ቤቱ ምንም ብር አልተረከብኩም ብሏል፡፡

Bekele-June-27-court-150x150

ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች አመራሮች(22 ተከሳሾች) ዛሬ ሐምሌ 8 ቀን 2008 ዓ.ም ችሎቱን ከሚመሩት ሶስት ዳኞች መካከል ዳኛ ታደለ ተገኝ ስልጠና ላይ በመሆናቸው የተከሳሾችን አቤቱታ እና የማረሚያ ቤቱን ምላሽ መርምረው ብይን መስራት እንዳልቻሉ ዳኛ ሳሙኤል ታደሰ ለተከሳሾች አስረደተዋል፡፡

ፍርድቤቱ ብይኑን ለመሰጠት ማክሰኞ ሐምሌ 12 ቀን 2008 ዓ.ም ከሰዓት በኃላ ቀጥሯል፡፡
የአቶ ደጀኔ ጣፋ እናት አዲስ አበባ ድረስ መጥተው በጡረታ መታወቂያ ልጃቸውን ለማየት እንደተከለከሉ ያሰረዱት የተከሳሽ ጠበቃ ፍርድቤቱ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ፍርድቤቱ በተለየ ሁናቴ የአቶ ደጀኔ ጣፋ እናት ስም ከነአባት በዝርዘር ጠይቆ ለማረሚያ ቤቱ ጉብኝት እንደፈቀድላቸው ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡

አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ደጀኔ ጣፋ በሀኪም የታዘዘላቸውን መድሃኒት እንዳያገኙ መደረጋቸውን ለችሎት በድጋሚ አመልክተዋል ፤በሌላ በኩል አቶ ጉርሜሳ አያኖ ጆሮቸውን ታመው ህክምና ቢጠይቁ ከህመም ማስታገሻ ውጪ ምንም እርዳታ እንዳልተሰጣቸው እና ለከፍተኛ ህመም መጋለጣቸውን አስርድተዋል፡፡ ፍርድቤቱ ህክምናን በተመለከተ ተከሳሾቹ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ትዕዛዝ ለማረሚያ ቤቱ ስጥቷል፡፡

በተያያዘ የተከሳሾችን አቤቱታ ሲሰማ የዋለው ችሎት ተከሳሾች ክስ ተመስርቶባቸው ከማዕከላዊ ፖሊስ ምርመራ ወደ ቅሊንጦ ማረሚያቤት ሲገቡ ማረሚያቤቱ የወሰደባቸው 825 ብር እንዲመለሰላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተከሳሾች ብራቸውን ቆጥረው ለማረሚያ ቤቱ እንዳስረከቡ ምስክሮች አሉን ቢሉም ማረሚያ ቤቱ ምንም ብር አልተረከብኩም ብሎ ለፍርድቤቱ ደብዳቤ ልኮ አስታውቋል፡፡

ምንጭ፡-የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴን የተመለከተ መረጃ ለኤርትራ መንግስት ያቀበሉ ዘጠኝ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

በታሪክ አዱኛ

በኢትዮጵያ ድንበር ስለሚገኙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ኤርትራውያን ስደተኞች እንቅስቃሴ ለኤርትራ መንግስት መረጃ ያቀበሉ ዘጠኝ ግለሰቦች በፅኑ እስራት ተቀጡ።

Ethiopian federal high court

ተከሳሾቹ 1ኛ ካሃሳ መስፍን፣ 2ኛ አብደላ ኢብራሂም፣ 3ኛ ልኡል መሃሪ፣ 4ኛ ፍስሃይ ተክለገብረስላሴ፣ 5ኛ ጎይቶም ይደጎ ተስፋይ፣ 6ኛ ጎበዘይ ገብረስላሴ፣ 7ኛ ገብረሚካኤል ገብረማርያም፣ 8ኛ ብርሃኔ ምረጽ ይልማ እና 9ኛ ትኩህ ንጉሴ ገብረ መድን ይባላሉ።

ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያሉ ተከሳሾች የኤርትራ ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ ከ6ኛ እስከ 9ኛ ያሉ ተከሳሾች ደግሞ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

ተከሳሾቹ ከጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም እስከ 2006 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ከኤርትራ መንግስት የመረጃ ሰራተኞች ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት በመፍጠር በኢትዮጵያ ድንበር የሚገኙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የኤርትራ ስደተኞች እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለኤርትራ መንግስት አቀብለዋል ይላል የአቃቤ ህግ ክስ።

በተጨማሪም 2ኛ ተከሳሽ በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም አራት ኤፍዋን ቦምቦችን በአካባቢው ለሚገኙ ግለሰቦች ለመሸጥ ሲዘጋጅ በቁጥጥር ስር ውሏል።

በተመሳሳይ 8ኛ ተከሳሽም የመሳሪያ ጥይቶችን እና አምስት ቦምቦችን ሸሽጎ መያዙንም ክሱ ያስረዳል።

በዚህም መሰረት አቃቤ ህግ የሃገሪቱን ሚስጥራዊ መረጃ በማቀበል እና ስለላ ወንጀል ክስ መስረቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ ድርጊቱን ክደው የተከራከሩ ቢሆንም አቃቤ ህግ የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ኤጀንሲ የሰነድ ማስረጃና የሰው ምስክር አቅርቦ አሰምቷል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎትም ተከሳሾቹን ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

ችሎቱ ከ7ኛ እና ከ8ኛ ተከሳሾች ውጪ ያሉትን ተከሳሾች በ3 አመት ከ4 ወር እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

7ኛ ተከሳሽ የደም ግፊት ህመምተኛ መሆኑን በማስረጃ በማቅረቡ አንድ ማቅለያ ተይዞለት በሶስት አመት ጽኑ እስራት ሲቀጣ፥ 8ኛ ተከሳሸ ደግሞ በአራት አመት ከስድስት ወር እስራትና በ500 ብር እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

በተከሳሾቹ እጅ ላይ የተያዙ ቦምቦች ለመንግስት ገቢ እንዲሆኑ ፍርድ ቤቱ አዟል።

በአጠቃላይ ሁሉም ተከሳሾች ለአምስት አመት ከማንኛውም ህዝባዊ መብታችው እንዲታገዱ ችሎቱ ወስኗል።
ምንጭ፡- ፋናቢሲ (የሐምሌ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ዘገባ), http://www.fanabc.com/index.php/news/item/17450

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል

*ጌታቸው ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደርጓል

Getachew Shiferaw

ከሽብር ቡድን አመራሮች ጋር በፌስቡክና በስልክ ግንኙነት በመፍጠር መረጃዎችን አስተላልፏል በሚል የሽብር ክስ የቀረበበት የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የእምነት ክህደት ቃሉን ለፍርድ ቤት ሰጥቷል፡፡

አርብ ሐምሌ 8 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው ጋዜጠኛ ጌታቸው ቀደም ሲል ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ውድቅ መሆኑን ተከትሎ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ በችሎቱ ተጠይቆ ‹‹የቀረበብኝን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛም አይደለሁም›› ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡

መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ተከሳሹ ቀደም ሲል ያቀረበው የክስ መቃወሚያን መርምሮ ብይን ለመስጠት ሲሆን፣ ጉዳዩን የሚያየው 14ኛ ወንጀል ችሎት የተከሳሹን መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ችሎቱ የመቃወሚያ ብይኑን በንባብ ከማሰማት ይልቅ በጥቅሉ “የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ አድርገነዋል” ሲል ለተከሳሹ ገልጹዋል፡፡

”በአጭሩ የክስ አቀራረቡ ከተጠቀሰው የወንጀሉ ክፍል አለመጣጣምን በተመለከተ የቀረበው መቃወሚያ አልተቀበልነውም፤ ዝርዘሩን ማስረጃ ስንመዝን እናየዋለን፡፡ የቀረበው ክስ ግልጽ አይደለም የተባለውን በተመለከተም፣ ክሱን ስንመለከተው በተብራራ መልኩ የቀረበ መሆኑን ስለተገነዘብን ውድቅ አድርገነዋል” በማለት የመቃወሚያው ውድቅ መሆንን ችሎቱ በቃል ለተከሳሹ አስረድቷል፡፡

ችሎቱ ተከሳሹ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲሰጥ ወንጀሉን አልፈጸምኩም፣ ጥፋተኛም አይደለሁም ማለቱን ተከትሎ የአቃቤ ህግን አስተያየት የጠየቀ ሲሆን፣ አቃቤ ህጉ በበኩሉ ከክስ ማመልከቻ ጋር ያያያዘው የሰነድ ማስረጃ ተመርምሮ ብይን እንዲሰጥለት አመልክቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም የሰነድ ማስረጃውን መርምሮ ብይን ለማሰማት ለሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ ከሳሽ ያቀረበበት የሰው ማስረጃ እንደሌለ በችሎቱ ተገልጹዋል፡፡

ምንጭ፡- EHRP

በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተለያየ የአፍሪካ ሀገራት እየታሰሩ መሆኑ ቢታወቅም፤ በርካታ ወጣቶች አሁንም በመሰደድ ላይ መሆናቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ

በተለያዩ የምዕራብና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ቁጥራችዉ በትክክል ሊታወቅ ያልቻለ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ መሆናቸውንና በርካታ ወጣቶች ከሀገሪቱ በመሰደድ ላይ እንደሚገኙ የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) ሐሙስ አስታወቀ ። ባለፉት ስድስት ወራቶች ብቻ በተለያዩ 10 የአፍሪካ ሀገራት ለዚሁ ችግር ተጋለጠዉ የነበሩ 1ሺ 657 ኢትዮጵያዉያንን ወደ ሀገር ቤት መመለስ እንደቻለም ድርጅቱ ገልጿል።

የዓለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት ስደተኞቹን ወደ ሀገር ለማመላለስ ጥረትን ቢያደርግም አሁንም ድረስ በርካታ ወጣቶች ከሀገሪቱ በመሰደድ ላይ መሆናቸው ስጋትን እየፈጠረ መምጣቱን አክሎ አመልክቷል።

iom-logo

በተያዘዉ ሳምንት በዛሚቢያ በህገ-ወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለዉ የተላለፋባቸዉን የእስር ቅጣት የጨረሱና ወደ ሀገር መመለስ ያልቻሉ 14 ታዳጊ ህፃናት ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን የስደተኞች ተቋም ገልጿል። በማላዊ ፣ ዛሚቢያ ፣ ታንዛኒያ እና ሌሎች ሀገራት ቁጥራቸዉ በትክክል ሊታወቅ ያልቻለ ስደተኞች በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን የእስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸዉ የሚመልሳቸዉ ባለመኖሩ ለችግር ተጋልጠዋል ። የማላዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከ120 የሚበልጡ ኢትዮጵያዉያን በእስር ቤት እየደረሰባቸዉ ያለን ስቃይ በመቃወም ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸዉ እንዲመለሱ በመጠየቅ ዘመቻን መክፈታቸዉ ይታወሳል።

የምዕራብና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራትን በመጠቀም ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ደቡብ አፍሪካ የመግባት እቅድ እንዳላቸዉ የተለያዩ አካላት ይገልፃሉ። ሰሞኑን የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ታዳጊ ህፃናት በርካታ ኢትዮጵያዉያን በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ እስር ቤቶች በስቃይ ላይ መሆናቸዉን እንዳስታውቁ ድርጅቱ በችግሩ ዙሪያ ባወጣዉ ሪፖርት አመልክቷል።

የስደተኛ ድርጅቱ ለችግር ተጋልጠዉ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ለመመለስ እያደረገ ባለዉ ጥረት ባለፉት 6 ወራቶች ብቻ 1 ሺ 657 ስደተኞች ከ10 የፍሪካ ሀገራት ሊጓጓዙ ችለዋል። መንግስት በተለያዩ ሀገራት ለችግር ተጋልጠዉ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም ።
ምንጭ፡- ኢሳት

በጎንደር በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 ያላነሱ ሰዎች ሲገደሉ፤ በአካባቢው ውጥረቱ እንደቀጠለ ነው

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኘው ጎንደር ከተማ፤ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት ጀምሮ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 ያላነሱ ዜጎች መገደላቸው ተጠቆመ፡፡ መረጃዎች እንደሚመለክቱት ከሆኑ፤ 10 ያህል ንፁሃን ዜጎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ ርምጃ መገደላቸውን ተከትሎ፤ ህዝቡ በወሰደው የአፀፋ እርምጃ 9 የፌደራል ፖሊስ እና 1 የመከላከያ ሰራዊት አባል ተገድለዋል፡፡

በስፍረው የሚገኙ የዓይን እማኞች በበኩላቸው የተገደሉ ሶወች ቁጥር ከተጠቀሰው እንደሚልቅ ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ በግጭቱ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ እስካሁን ከገለልተኛ አካልም ሆነ ከመንግሥት የተሰጠ ማረጋገጫ የለም፡፡

Gonder Protest

ባለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በህዝቡ መካከል በተፈጠረ ግጭት በጎንደር ለሁለት ተከታተይ ቀናት የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደሌሎች አጎራባች ከተሞች መዛመቱ ተሰምቷል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞውም ሐሙስ ወደ ዳባርቅ ከተማ የተዛመተ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ወደ ሳንጃ ወረዳ እና ወደ ሌሎች አጎራባች ከተሞችና ወረዳዎች መዛመቱ እየተነገረ ነው፡፡

car buring in Gondar

በተፈጠረው ግጭትም የሰው ህይወትን ጨምሮ የህወሃት እና የደጋፊው ናቸው የተባሉ ንብረቶች መውደምንም አስከትሏል፡፡
የግጭቱ መንስኤ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የአማራ ማንነትና ተያያዥ መብታቶቻችን ይከበሩልን የሚል ጥያቄን ለትግራይ ክልላዊ መስተዳደርና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲያቀርቡ የነበሩ ተወካይ ኮሚቴዎችን ከሚኖሩበት ጎንደር ከተማ የትግራይ ክልልና የፌደራሉ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና የደህንነት አባላት ለማፈን እና ለማሰር በወሰዱት የኃይል እርምጃ በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተለይ ከወልቃይት የአማራ ማንነት ተወካይ ኮሚቴዎች መካከል ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፤ ሊያግቷቸው የመጡ የፀጥታ ኃይሎችን “ህጋዊ ከሆናችሁ በቀን መምጣት ትችላላችሁ፤ ካልሆነ በሌሊት እኔ እጄን ለማንም አልሰጥም” ማለታቸውን ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባት፤ ህዝቡ የመንግሥት ኃይሎችን የሌሊት እገታና ሌሎች 4 የኮሚቴ አባላትን እስርና እገታ በመቃወም ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት እንደተፈጠረ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

በጎንደር በተፈጠረው አለመረጋጋት የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥታት ዜጎቻቸው ወደጎንደርና አቅራቢያው ከመሄድ እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል፡፡ እስራኤል በበኩሏ በጎንደር የሚገኙ 6 ሺህ ቤተ እስራኤላውያንን እና በስፍራው የሚገኙ በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ ተወካዮችን ደህንነት በተመለከተ ከፍተኛ ቁጥጥር ወደሚደረግበት ስፍራ ጥበቃ እያደረገችላቸው መሆኑን የኢየሩሳሌም ፖስት ዘገባ አመልክቷል፡፡

በጎንደር ግጭቱ ለጊዜው የተረጋጋ ቢመስልም፤ አሁንም በአካባቢው በመንግሥትና በህዝቡ መካከል ከፍተኛ ውጥረት መኖሩ እየተገለፀ ነው፡፡

%d bloggers like this: