Daily Archives: July 5th, 2016

ለውጥን እንደ ሰማይ መና

ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com

Ethiopian Parlama building

አንድ ሰው ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዓላማ እና ግቦች አሉት። እነኚህን ግቦች የሚያስቀምጥበት እና ለማሳካት የሚፈልግበት ደግሞ አንድ ምክንያት ይኖረዋል። እዚያ ምክንያታዊነት ላይ እንዲደርስ ያስቻለው ደግሞ የቆመበት እና የሚከተለው መርሕ ነው። እነኚህ ጉዳዮች ተያያዥነት ቢኖራቸውም አንዱ ከሌላው የሚለይበት የራሳቸው የሆነ ልዩነቶች አሏቸው።

ወደ አገራችን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ስንመጣ ትኩረታቸው ግብ ላይ እንጂ ዓላማ፣ መርሕ እና ምክንያታዊነት ላይ ነው ለማለት አያስደፍርም። አስገራሚው ነገር ፖለቲካውን በቅርበት ለሚከታተል ሰው፣ አብዛኞቹ ግባቸው ሥልጣን የመቆጣጠር እና የበላይነትን መጎናፀፍ ግብ እንጂ ቆመንለታል ላሉት ዓላማ፣ መርሕ እና ምክንያት ሲሆን አይስተዋልም። ይህ ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመጣ የሚፈለገው ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እስካሁን እንዳይመጣ ከፊል መንስኤ ሆኗል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ችግሩን በጨረፍታ መዳሰስ ነው።

ትችትን መድፈር

ምንም እንኳ ብቃታቸው፣ሚናቸውና እና ዓላማቸው የተለያየ ቢሆንም፣በአሁን ሰዐት በአገሪቱ 50 ያህል የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ። ይህ አሐዝ ከ7 ያላነሱ በትጥቅ ትግል እንቀስቃሴ የሚያደርጉትን ሳያካትት ነው። ምንም እንኳ ጥቅል ድምዳሜ ለመስጠት ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም፣ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ብንመረኮዝ ገዥው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን ጨምሮ አብዛኞቹ የፖለቲካ ንቅናቄ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ ተክለቁመና ላይ አልደረሱም ወይም ለመድረስ ዕድሉን አላገኙም። ምክንቱም በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ የለም። ይህ የተደረገው በሥልጣን ላይ ባለው ገዥው ስርዓት ነው። ነገር ግን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም መጠነኛም ቢሆን የራሳቸው ድርሻ አላቸው።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ስኬታማ እንዳይሆኑ ቀዳሚውን ድርሻ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የሚወስድ ቢሆንም፣ ተፎካካሪዎች ስለራሳቸውም ሆነ ስለድርጅቶቻቸው ድክመቶች በግልጽ ሲነጋገሩም ሆነ በአደባባይ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ሲወያዩ አይስተዋልም። በርግጥ ያን መድረክ በቀላሉ ማግኘት አይችሉ ይሆናል። ነገር ግን ችግሩን ቦታ ሰጥተውት ሲጠቀሙና ድክመቶቻቸውን ሲያርሙ አይታይም። ከድክመቶቻቸው መካከልም ዓላማና መርህ ላይ ያለመቆም ችግር አንዱ ነው።

በተለይ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን የስርዓት ለውጥ መኖር እንዳለበት እያመኑ፣ ነገር ግን ደግሞ በሥልጣን ላይ ላለው አካል መጠንክር የሚሠሩ ጥቂት አይደሉም። በተለይ ከወረቀት ባለፈ ከጊዜው እና ከተቀናቃኛቸው ጋር ሊገዳደር የሚችል ስትራቴጂ ነድፎ ወደመሬት ያለማውረድና ፖሊሲና ፕሮግራማቸውን በተለያየ ዘዴ ወደ ሕዝቡ የማስረፅ ችግር አለ። እነዚህን የተቃዋሚውን ችግሮች ለትችት ማቅረብ የተቃውሞውን ጎራ እንደመጉዳት ስለሚቆጠር ልምዱ የለም።

ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ግን ከተቃዋሚዎች በተሻለ፣ ለይስሙላም ቢሆን አልፎ አልፎ አሁን የመልካም አስዳደር እንደሚለው እነዚህ ችግሮች አሉብኝ የማለት ልማድ አለው። እርግጥ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ችግር እንዳለ በደፈናው ቢያምንም፣ የተጠቀሱ ችግሮች ግን ለኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ቅዱስ የሆኑ የሥልጣን መሠረቱ ናቸው። ምክንያቱም የሚከተለው ርዕዮተዓለም “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” እና የምጣኔሀብት “ልማታዊ መንግሥት” ፍልስፍና የተጠቀሱ ችግሮችን ለማረም የሚያስችሉ አይደሉም፤ ይልቁኑ ያባብሱታል እንጂ። ምናልባት በውጫዊ ጫና ምክንያት ስርዓቱ ችገሮቹን ለማረም አንዲት ርምጃ ወደፊት ቢጓዝ፤ ስርዓቱ ታሪክ ብቻ ሆኖ እንደሚቀር መሪዎቹ ጠንቅቀው ያውቁታል። ስለዚህ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ም ቢሆን ለተሻለ ለውጥ ከልብ አምኖ ራሱን የመተቸት ወይም ትችትን የመቀበል ልማድ አለው ማለት አይቻልም። በመሆኑም በሁለቱም ጎራ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች የትችትን ፋይዳ የማይቀበሉ በመሆናቸው ዴሞክራሲያዊ መርሕ አላቸው ማለት አይቻልም።

ራስን ከመገምገም አንፃር ሲታይ፤ ስርዓቱ ራሱን የሚያወዳድረው በአቅራቢያ ካሉ እንደነ ታንዛኒያ፣ኬንያ፣ ጋና ወይም ሞርሽየስ ጋር አሊያም ዘመኑን ከሚመኑ የተሸሉ ስርዓቶች ጋር ሳይሆን ሞተው ከተቀበሩ ስርዓቶች ጋር ነው፡፡ ስለሆነም 17 ዓመት የገዛውን ደርግን 25 ዓመታት ሙሉ ከራሳቸው ጋር አወዳድረው አልጠገቡም፣ ኮንነውና አኮስሰው አልጨረሱም። በዚህም ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ራሱን ብቻ አይደለም ከሙታን ጋር እያወዳደረ ያለው፣ ተፎካካሪውን እና ሕዝቡንም ጭምር እንጂ።

የራስን መለያ ምልክት ማኖር

ምንም እንኳ በበጎ ባይሆንም ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የራሱን መለያ ምልክት (ብራንድ) አኑሯል። እዚህ ላይ የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ አመራሮች የራሳቸውን በጎ መለያ ምልክት የማኖር ችግር ይስተዋላል። በተለይ ለስርዓት ለውጥ የሚታገሉ አመራሮችና አባላት በሕዝቡ ዘንድ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን ያህል የተወገዘ ተግባር ባይኖራቸውም፤ በጎ ምልክት በማኅበረሰቡ አዕምሮ ስሎ የማኖር ዘዴን እየተጠቀሙ ነው ለማለት ያስቸግራል። በርግጥ በጣም ጥቂቶች በፖለቲካው መስክ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በጎ ምልክት ያላቸው ቢሆንም፣ ከከተማ የዘለለ ዕውቅና እና ድጋፍ እንዲኖራቸው ከዓላማቸው እና ከመርሓቸው ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል የራሳቸውን ምልክት የማኖር ክፍተት አለ።

የራስን በጎ መለያ ምልክት የግድ በፖለቲካ መስክ ብቻ ላይሆን ይችላል። በተለይ ማኅበራዊ ክንፍ በመመሥረት፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ላይም ትኩረት ቢሰጡ ለፖለቲካው እንቀስቃሴም የበለጠ ይጠቅማቸዋል፤ ሕዝቡን በቅርብ የማግኘት ዕድል ያገኛሉ። ለምሳሌ በአባላት የሚደረግ የደም ልገሳ፣ አገር በቀል የሕፃናት እና አረጋውያን እንክብካቤና መጠለያን ሄዶ መጎብኘት እና ያቅምን ያህል ድጋፍ ማድረግ፣ እንዲሁም የአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ በግልም ሆነ በድርጅት ሥም ብሎም ሌሎች ሙያዊ የበጎ ፈቃድ ነጻ አገልግሎት መስጠት፣… የመሳሰሉት ላይ ቢሳተፉ ተደራሽነታቸውም ሆነ ተቀባይነታቸው እየጨመረ በጎ ምልክትን እያኖሩ የመሄድ ዕድላቸው ሰፊ ይሆን ነበር። በርግጥ ይህ ሥራ የሲቪክ ተቋማት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አንዱ ሥራ ቢሆንም፣ ፖለቲከኞች እንደ አንድ ዜጋ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ ሕዝቡጋ በቀላሉ ከመድረስ በተጨማሪ፣ ነገ የመንግሥትን ሥልጣን ቢይዙ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚከተሏቸውን ፖሊሲዎችም ከሕዝብ አገር በቀል ዕውቀትና ልምድ ጋር እንዴት ማስተሳሰር እንዳለባቸው እና በቀጥታ የሕዝቡን ችግር የበለጠ ለመረዳት ትልቅ ግብኣት ሊሆናቸው ይችላል።

ራስን ችሎ መቆም

ብዙውን ጊዜ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አለመኖር ወይም አለመጎልበት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ስርዓቱ ቢሆንም፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም የራሳቸው ሚና እንዳላቸው ሲገልጹ አይስተዋልም። ስርዓቱ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዳይኖሩ አድርጓል በሚል ይወቀሳል። ከዴሞክራሲ ተቋማት በተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ የመገንባት ሒደት ችግር ላይ ገዥውም ሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የማይተናነስ ድርሻ እንዳላቸው።

የአገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች በተለይ ተቀናቃኝ አካል የሚያቀርባቸውን አማራጭ ሐሳቦችም ሆኑ ትችቶች እነርሱን ጭምር የሚጠቅም እንኳ ቢሆኑ፤ እንዲፈሩና በአሉታዊ ጎን ብቻ እንዲመለከቱ ቀፍድዶ ስለያዛቸው በሐሳብ የበላይነት የሚያምን ነጻ ማኀበረሰብ እንዳይኖር በማድረግ ረገድ ትልቅ አገራዊ ጉዳት አስከትሏል። ለዚህም ነው፤ ከጥቂት አመራሮቻቸው በስተቀር ከሌላው ማኅበረሰብ ያልተለየ አንዳንዶችም የባሰ ጎስቋላ ሕይወት እየመሩ እንኳ ከለውጥ ይልቅ የሚደግፉት ስርዓት ልዩ ጥቅም እንደሰጣቸው አድርገው የሚቆጥሩት። ይህ የመንጋ አስተሳሰብ ውጤት ነው፤ ራሳቸውን ችለው እንዳይቆሙ በማድረግ በፖለቲካው፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው የበለጠ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደረጋቸው።

በገዢው ፓርቲ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርቶች በኩል ብዙውን ጊዜ ለእንቀስቃሴያቸው አስፈላጊ የሆነ የፋይናንስ እና የሰው ኃይል ችግር አለ። ያን ችግር ለመፍታት በአቅራቢያቸው ከማኅበረሰቡ ጋር ቀጥታ ትስስርን በመፍጠር ሌላ አማራጭ ከማየት ይልቅ፣ ፈራ ተባ እያሉ በሚያዋጡ ጥቂት አባሎቻቸው እና ዳያስፖራው ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በርግጥ የፖለቲካ ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የፖለቲካ ድርጅቶች የንግድ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ የሚያስገድድ ቢሆንም፤ ይህ ግን ለገዥው ስርዓት የሚሠራ እንዳልሆነ በየአባል ድርጅቶቹ (በአባላት ባለቤትነት ሥም) የሚያስተዳድራቸው የንግድ ኩባንያዎች ማስረጃዎች ናቸው። ተፎካካሪዎች ያን ዕድል ባያገኙ እንኳ፤ ከኢትዮጵያውያን የተለያየ ዘዴን በመጠቀም ቢያንስ በፖለቲካው መስክ ራሳቸውን ችለው ሲንቀሳቀሱ አይታይም።

የፖለቲካ ድርጅቶች በፋይናንስ ራሳቸውን ችለው አለመቆማቸው ዓላማቸውን በተወሰነ የጊዜ ገደብ ከግብ እንዳያደርሱ አንዱ እንቅፋት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከጊዜውና አገር ውስጥ ካለው ማኅበረሰብ ፍላጎትና አቅም ጋር አብረው እንዳይጓዙ የፈጠረው የፋይናንስ ችግር በሐሳብ ደረጃም የዳያስፖራው ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ይህ ማለት ግን የዳያስፖራው ድጋፍ አያስፈልግም፣ አይጠቅምም ማለት አይደለም፤ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በፋይንናስም በሐሳብም ሙሉ ለሙሉ ጥገኛ መሆን በቀጥታ የሀገር ውስጥ እንቅስቃሴ ራሱን ችሎ እንዳይቆም ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የደጋፊውን እና የአባላቱን ድርሻ በግልፅ ለይቶ ግንዛቤ በማስጨበጥ መንቀሳቀስ የራስ መተማመንን ይፈጥራል፡፡

መተባበር፣ መተማመን እና መከባበር

በሐሳብ አለመስማማት ወይም በፖለቲካ ርዕዮተዓለም አብሮ አለመጓዝ አንዱ ሌላውን እንደ አንድ አገር ዜጋ ሳይሆን እንደጠላት ማየት፣ ለፓርቲ ታማኝነት እያስመሰለው ይገኛል። ይህ ልምድ ገዥው ስርዓት ተቀናቃኞቹን የሥልጣን ተፎካካሪ አድርጎ ከመመልከት ይልቅ በጠላትነት የመፈረጅ አንዱ መለያ ፀባዩ ከሆነ ይኸው ሁለት ዐሥርት ዓመታት አልፈዋል። ምንም እንኳ በግፍ ባያስሩና ባያስፈርዱም ይህን ባሕል ተፎካካሪዎቹም ይጋሩታል።
በተፎካካሪዎች ዕርስበርስ ያለው መተባበር፣ መከባበርና መተማመንም አለመኖር ችግርን በጋራ አለመጋፈጥ ብቻ ሳይሆን ያላቸውንም የሰው፣የጊዜ እና የገንዘብ ሀብት በአግባቡ እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል። ይህ ማለት ግን ከቆሙለት ዓላማና መርህ ውጭ የግድ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” የሚለውን የተሳሳተ መንገድ መከተል ማለትም አይደለም፡፡ መተባበርንና አብሮ መስራት መፍጠር ያለበት የያዙት ዓላማና የቆሙለት መርህ እንጂ የተቀናቃኝ አካል ተቃዋሚ ስለሆነ አይደለም፡፡
የርዕዮተዓለም ልዩነት መኖር የጋራ ተቀናቃኝን ለመቋቋም ተባብሮ መሥራትን እና መከባበርን አይከለክልም። በተለያየ ርዕዮተዓለም በጋራ ሰርቶ ውጠየታማ መሆንን ዴሞክራሲ በዳበረባቸው አገሮች በተለይ እንደ ጀርመን፣ ስዊድን እና እስራኤልን ማንሳት ይቻላል።

ርስበርስ መተባበር አለመኖሩ አለመተማመኑን ፈጥሯል። ያለመተማመኑ ደግሞ አለመከባበርን አስከትሏል። በተለይ ፖለቲካው ከሐሳብ የበላይነት ይልቅ በመንጋ ቲፎዞ ማዕቀፍ ውስጥ መውደቁ ርስበርስ ከመከባበር ይልቅ በመካከላቸው መናናቅና ጥርጣሬን በማስፈን ለጋራ መብትና ጥቅም እንኳ በጋራ ባለመቆም ፖለቲካው እንዳይዘምን ጥላ አጥልቶበታል። ምክንያቱም ፖለቲካው የሚመነዘረውና የሚተረጎመው ከምክያታዊነት እና ከቆሙለት መርህ ይልቅ በስሜት ስለሆነ፤ ዛሬም ድረስ የሐሳቦችን ጠቀሜታና ጉዳት ከማየት ይልቅ ሐሳቡን የሚሰነዝረው “እሱ ማን ነው?” የሚል ኋላ ቀር የግለሰብ ተክለ ስብዕና አምልኮ ላይ የመጠመድ ዝንባሌ ይታያል፡፡ ይህ ችግር በገዥውም ሆነ በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ሊሂቃን እና ደጋፊዎች የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሐሳቡ ጥራት ይልቅ የግለሰቡ ማንነት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ፣ የጎደላቸውን ከሌሎች አጋሮቻቸው መሙላት እንደሚችሉ ባለመገንዘብ ለራስ የሚሰጥ እጅግ የገዘፈ ትልቅ ግምት፤ ሰጥቶ አለመቀበል፣ አለመተባበር፣ አለመተማመን እና አለመከባበርን አስከትሏል።

ቀድሞ መተንተን እና መተንበይ

የነበሩ ተሞክሮዎችን በማጥናትና በመረዳት የእንቅስቃሴዎች ውጤትን ቀድሞ መተንበይ እንዳለ ሁሉ፣ ሊመጣ የሚችለውንም አሉታዊና አዎንታዊ ችግርንም ከግምት ማስገባት አስቀድሞ ክፍተቶችን ለመቀነስ ይረዳል። ይህ እንቅስቃሴዎችን በዕቅድ መሠረት ማስኬድ ብቻ ሳይሆን መተንተን እና መተንበይ የተሻለ ውጤት ከማስመዝገብ በተጨማሪ ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል የተለያየ አቅጣጫን ሊያመላክት ይችላል። ይሄ ብዙ ሲሠራበት አይታይም። ምክንያቱም ቀድሞ መተንተን እና መተንበይ የቻለ የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ መሪ የግድ በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ በሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ብቻ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ አይጠብቅም፡፡

ከፊት ሊመጣ የሚችለውን ውጤትን በተመለከተ፤ እንኳን ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በሌለበት አገር ቀርቶ፣ በሠለጠነ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ በሕግ የበላይ የተረጋገጠበት አገር የወቅቱ አስተዳደር ተፎካካሪ እንደመሆኑ መጠን በቀናነት ዕድሉን ይሰጣል ተብሎ አይታሰብም። ስለዚህ እንቅስቃሴዎችና የነበሩ ልምዶች ቀጣዩን ጊዜ ለመተንተንም ሆነ ለመተንበይ በቂ ግብኣት መሆናቸው አምኖ ያለመጠቀም ችግር አለ። በተለይ የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅቶች ነገሮች ቀድመው ተንብየው ባለመዘጋጀታቸው ውጤቱ ላይ ሲደረስ የመረበሽና ያለመረጋጋት ስሜት ይታያል። ይህ ሥልጣን ላይ ያለው አካል ከሚፈጥረው ችግር በተጨማሪ በራስ ስንፍናም የሚፈጠር ነው።

ከጊዜው ጋር አብሮ መዘመን

የአባላትም ሆነ የመሪዎች ከጊዜው ጋር አብሮ መዘመን፤ የአገሪቱን የፖለቲካ እንቅስቃሴ አብሮ ያዘምነዋል። በተለይ አመራሮቻቸው ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን ማንፀባረቅ፣ አባላቱን በመረጃ መረብ ማግናኘትና ወቅታዊ መረጃን በፍጥነት መለዋወጥ ግልጽነት ያለውን አሠራር ለመከተል ያስችላል።

ቢቻል ሁሉም አመራር ከማኅበረሰቡ ጋር በቀላሉ ሊያገናኛቸው የሚችሉ ዝሙን ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ቢጠቀሙ ተደራሽ ከመሆናቸው በተጨማሪ ራሳቸውም አዳዲስ መረጃና ዕውቀትን የመቅሰም ዕድላቸው የሰፋ ነው። በዚህም ራሳቸውን በመረጃ አበልፅገው ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን ከማኅበረሰቡ ቀጥተኛ ግብረመልስ ከማግኘት በተጨማሪ አዳዲስ ደጋፊና ተከታይ የማፍራት አጋጣሚም ይኖራቸዋል። በተለይ ከኮምፒዩተርና ቴሌፎን ቴክኖሎጂዎች ጋር ራስን ማስማማትና ማላመድ ራስን በዕውቀት ለማበልፀግም ይረዳል። እዚህ ላይ በገዥውም ይሁን በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች ከሕዝቡ ይልቅ በይበልጥ ራሳቸውን ብቻ የሚያደምጡ በመሆናቸው ራሳቸውን ለሕዝቡ ግልጽ አድርገው ሲቀርቡ አይታይም።

በቴክኖሎጂ አጠቃቀም በኩል አብዛኛው የገዠውም ሆነ የተፎካካሪ ድርጅት መሪዎች ተመሳሳይ ባሕርይ ነው ያላቸው። ሁለቱም ማኅበራዊ ሚዲያውንም ሆነ ዝሙን የመረጃ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ፈት ወጣቶች የሚጠቀሙበት አድርገው ይቆጥሩታል፤ በዚህም ጠቃሚ ነገሮችን እንዲያጡ አድርጓቸዋል።

በተለይ በአሁን ሰዐት የአውሮፓም ሆነ የአሜሪካ መሪዎች በተጨማሪ የጎረቤታችን ኬንያ መሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካና የእስያ ሀገራት መሪዎች ዘመን ያፈራውን ቴክኖሎጂ ራሳቸውን ከማኅበረሰቡ ጋር በቀጥታ በማገናኘት ከሚሰጣቸው ፖለቲካዊ ፋይዳ በተጨማሪ ለአገራቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የበለጠ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ገፋፍቷቸዋል። በኢትዮጵያ ግን ገዥው ስርዓት ቴክኖሎጂውን ራሱ በአግባቡ ተጠቅሞ ማኅበረሰቡም የበለጠ እንዲጠቀም ከመጋበዝ ይልቅ፤ አፋኝ ሕጎችን ማውጣቱና መተግባሩ ሳያንስ ቴክኖሎጂውን በሌላ ፀረ-ቴክኖሎጂ መሣሪያ ለማፈን እና ለማዘግየት ሥራ ላይ ሲያውል ይስተዋላል። በዚህም አገሪቱም ሆነች ሕዝቡ ዓለም ከደረሰበት ዘመን ጋር አብሮ እንዳይጓዝ እንቅፋት ፈጥሯል።

በዚህ መሠረት በፖለቲካው እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፎ ያላቸው አካላት ዓላማቸው ግቡን ይመታ ዘንድ በቆሙለት መርሕ መሠረት ትችቶችን ከግብታዊ ስሜት በፀዳ መልኩ ለመስማት መድፈር፣ ራስን ችሎ መቆም፣ በጎ የሆነ የራስን ምልክት ማኖር፣ በሐሳብ የበላይነት ማመን፣ ርስ በርስ መተባበር፣ መተማመን፣ መከባበር፣ መጪውን ጊዜና ውጤት አስቀድሞ መተንተን እና መተንበይ እንዲሁም ከጊዜው ጋር አብሮ መዘመን የተሻለ ውጤት እንድናይ ያስችለናል የሚል እምነት አለኝ። አለበለዚያ የራሳችንን ጉድፍና በሽታ ደብቀን የሌላ ድክመት ላይ መንጠልጠል የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በሰው ልጅ ጥረት ለሰው የሚመጡ መሆናቸው ቀርቶ፤ ለውጥን እንደሰማይ መና ለመጠበቅ መገደዳችን አይቀሬ ነው፡፡   ምክንያቱም በሀገሪቱ ያሉ ችግሮች መነሻቸው የፖለቲካው አለመዘመን ውጤት ስለሆነ፤ መፍትሄውም ከነበረው ተሞክሮና ልምድ በተለየ መልኩ ሁሉንም ሊያሳትፍና ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የፖለቲካ ለውጥ ነው፡፡

%d bloggers like this: