(አዲስ ሚዲያ) በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፈለ ከተማ ወረዳ 1 በተለምዶ ሐና ማርያም፣ ፉሪ፣ ቀርሳ፣ ኮንቱማ እና ማንጎ ጨፌ አካባቢ ነዋሪዎች ላይ መንግሥት በወሰደው የኃይል ርምጃ አንዲት ነፍሰጡር እናት እና አንድ ቄስን ጨምሮ 6 ያህል ሰዎች ሲገደሉ፤ ከ 3 ሺህ ያላነሱ የመኖሪያ ቤቶች በዶዘር እየፈረሰ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ መንግሥት የኃይል ርምጃውን የወሰደው ሐሙስ ሰኔ 23 እና ትናንት አርብ ሰኔ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆን፤ በአካባቢው ህፃናት፣ ሴቶች እና ነፍሰጡር የሆኑ እናቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸው ታውቋል፡፡ በተለይ አንዲት ነፍሰጡር እናት በቤቷ ተኝታ እያለ፤ ቤቷ በዶዘር ሲፈርስ እዛው መገደሏም ተሰምቷል፡፡
የቤቶቻቸውን በክረምት መፍረስና የመንግሥትን የኃይል ርምጃ የተቃወሙና በጉዳዩ ዙሪያ የሌሉትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውም የተገለፀ ሲሆን፤ የአካባቢው ወንዶች እየፈረሱ ባሉ ቤቶች አካባቢ እንዳይገኙ አካባቢው በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መውደቁ ታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ከቤቶቻቸው መፍረስ በተጨማሪ የመንግሥትን ግድያ እና እስር በመፍራት ከአካባቢው መሰደዳቸው ተጠቁሟል፡፡
መንግሥት የነዋሪዎቹን ቤት በክረምቱ የዝናብ ወቅት ጠብቆ ለምን ማፍረስ እንደወሰና እንደጀመረ ባይታወቅም፤ እንዲፈርሱ የተወሰኑ ቤቶችን የማፍረስ ስራው እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ በአካባቢውም ቤቶቻቸው በዶዘር እንዲረስ የተደረጉባቸው ሰዎች ንበርትም አብሮ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን መደረጉን የአካባቢው ሴቶች ይናገራሉ፡፡
ቀደም ሲል ረቡዕ ሰኔ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. መንግሥት ወደ 30 ሺህ የሚጠጋ የነዋሪዎችን ቤት “ህገወጥ ነው፣ መፍረስ አለበት” በሚል መወሰኑን ተከትሎ ቅሬታ በመቅረቡ፣ የአካባቢው ወረዳ 1 አስተዳደር ነዋሪውን በቦታውና በቤቶቹ ጉዳይ እንነጋገር ብሎ ሰብስቦ እያወያየ ሳለ፤ በጎን አፍራሽ ግብረ ኃይልና የፀጥታ ኃይል ልኮ ማፍረስ በመጀመሩ በተፈጠረ አለመግባባት የወረዳው ስራ አስፈፃሚ እና ፖሊሶች መገደላቸውን፣ ከነዋሪዎችም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸው ይታወሳል፡፡
ከቤቶቹ መፍረስ ጋር በተያያዘ የሰብዓዊ መብት ጉባዔ (ሰመጉ)፤ መንግሥት ከ19 ሺህ ያላነሱ ቤቶችን ማፍረሱን በመጠቆም፤ እየተወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃ እንዲያቆምና ቤቶቹን አፍርሶ ነዋሪዎቹን ለጎዳና ህይወት ከመዳረግ ይልቅ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠይቋል፡፡