Daily Archives: November 12th, 2016

እነ በቀለ ገርባ ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች አልተሰሙም፤ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተጠርጣሪዎችን አሟልቶ አላቀረበም

‹‹እሰነጥቅሃለሁ ተብያለሁ›› አቶ በቀለ ገርባ

bekele-gerba-et-al

በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ለእስር ተዳርገው የሽብር ክስ የቀረበባቸው የኦፌኮ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ከሦስት ወራት በኋላ እንደገና ወደ ችሎት ሲመለሱ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ቀጠሮ በመያዝ የነበር ቢሆንም፣ በእስር የሚገኙበት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ተጠርጣሪዎችን አሟልቶ ባለማቅረቡ ምክንያት ምስክሮቹ ሳይሰሙ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ህዳር 2 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት ላይ እንደተመለከተው በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ከተካተቱት ተጠርጣሪዎች (22 ሰዎች) መካከል 5ቱን ማረሚያ ቤቱ አላቀረባቸውም፡፡ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ህዳር 2 ቀን 2009 ዓ.ም ለፍርድ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸው ‹4ቱ ተጠርጣሪዎች በቂሊንጦ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ አደጋ ተከትሎ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስደው ስላልተመለሱ› ማቅረብ አልቻለም፡፡ ማረሚያ ቤቱ ሸዋሮቢት እንደሚገኙ ያመለከታቸው ተጠርጣሪዎች ገላና ነጋሪ፣ ገመቹ ሻንቆ፣ ደረጀ መርጋ እና ቶምሳ አብዲሳ ናቸው፡፡

ሆኖም ግን ማረሚያ ቤቱ በስም ጠቅሶ ሸዋሮቢት ስለሆኑ ማቅረብ አለመቻሉን ከጠቀሰው ሌላ አንድ ተጠርጣሪ ችሎት አለመገኘቱን በማጣራት ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪውን ለምን እንዳላቀረበ የማርሚያ ቤቱን ተወካይ ጠይቋል፡፡ ሆኖም የዕለቱ ጉዳይ አስፈጻሚ ምክትል ሰርጀንት ዘውዱ ወልደማርያም ተጠርጣሪው በእርግጥ የት እንደሚገኝ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ ይህ የት እንዳለ ያልታወቀው ተጠርጣሪ ጭምሳ አብዲሳ ይባላል፡፡

በዛሬው የችሎት ውሎ ተጠርጣሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ጠበቆችም ተሟልተው አለመቅረባቸው ታውቋል፡፡ የብዙዎቹ ተጠርጣሪዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ ወንድሙ ኢብሳ አልቀረቡም፡፡ ተከሳሾችም ጠበቃቸው ከቀጠሮ በፊት ደንበኞቻቸውን ለማነጋገር ወደቂሊንጦ ሄደው ማግኘት እንደማይችሉ ተነገሯቸው መመለሳቸውን ከማወቃቸው ውጭ በዛሬው ችሎት ለምን እንዳልቀረቡ እንደማያውቁ ለችሎቱ ተናግረዋል፡፡ በችሎት የቀረቡት ሌሎች ጠበቆችም ቢሆን ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ደንበኞቻቸውን በነጻነት ስለጉዳያቸው ለማነጋገር እንዳይችሉ እንቅፋት እየፈጠረባቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ችሎቱ ዛሬ የተሰየመው የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት መሆኑን በመጥቀስ አቃቤ ህግ ከአጠቃላይ 42 ምስክሮቹ መካከል አምስቱ መቅረባቸውን በመግለጽ ምስክሮቹ ቀርበው እንዲሰሙለት ጠይቋል፡፡ ሆኖም ግን ተከሳሾቹ ሁሉም ተሟልተው ባልተገኙበት ሁኔታ ምስክር ሊሰማ እንደማይገባ ጠቅሰው ተቃውመዋል፡፡ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ በጋራ የቀረበባቸው ፍሬ ነገር ስላለ በተናጠል ምስክሮች ቢደመጡ መብታችንን ይነካል በሚል በጠበቆቻቸው አማካኝነት አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል አቶ በቀለ ገርባ አሁን ጉዳያቸውን እየየ የሚገኘው ችሎት በክስ መቃወሚያቸው ላይ ጉዳያቸው በፌደራል ፍርድ ቤት ሳይሆን በኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች ሊታይ ይገባል በሚል ያነሱትን ህገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄ በጣሰ መልኩ ሐምሌ 25 ቀን 2008 ዓ.ም መቃወሚያቸውን ውድቅ ማድረጉን በማስታወስ፣ በፍርድ ቤቱ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ስላላቸው ችሎት ቀርበው ክርክር ለማድረግ እንደማይፈልጉ ቀደም ብለውም ገልተጸው እንደነበር ጠቅሰው በዛሬው ችሎት ላይም ፖሊስ በጉልበት እየደበደበ እንዳቀረባቸው አስረድተዋል፡፡

አቶ በቀለ ሌሎችንም ተከሳሾች በመወከል እንዳስረዱት ከዚህም በኋላ ችሎት የሚቀርቡ ከሆነ ተገደው እየቀረቡ እንዳሉ ችሎቱ እንዲያውቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ያደረገባቸውንና በክስ መቃወሚያ የጠቀሱትን ይህንኑ የህገ-መንግስት ጉዳይ ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው ወደ ፌደሬሽን ምርድ ቤት የመውሰድ ሀሳብ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡

ፖሊስ በጉልበት መኪና ውስጥ ካስገባን በኋላ ‹‹እሰነጥቅሃለሁ›› የሚል ዛቻ እንደደረሰባቸው፣ ይህን የተናገረውን ፖሊስ ችሎት ፊት ጠቁመው በማሳየት ጭምር ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህን ዛቻ ያደረሰውን ፖሊስ ችሎቱ አንድም ጥያቄ ሳያቀርብለት አልፎታል፡፡

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎ ያልቀረቡ ተከሳሾችን ማረሚያ ቤት እንዲያቀርብ፣ 7ኛ ተከሳሽ ጭምሳ አብዲሳን ማረሚያ ቤት ለምን እንዳላቀረባቸው ምክንያት እንዲያስረዳ እንዲሁም የኦሮምኛና ስዋህሊ ቋንቋዎች አስተርጓሚዎች እንዲመደቡ ትዕዛዝ በመስጠት ተከሳሾቹ ተሟልተው ሲቀርቡ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለህዳር 6 ፍርድ 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤት ማንኛውም ተከሳሽ በቀጠሮው ዕለት የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አክብሮ መገኘት እንዳለበትም ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

በዛሬው የችሎት ውሎ የኦሮምኛ ቋንቋ አስተርጓሚ ችሎቱ ባለማቅረቡ ከተከሳሾች መካከል አቶ በቀለ ገርባ በአጋዥነት ሲያስተረጉሙ ውለዋል፡፡ የዛሬውን ችሎት ከተከሳሽ ቤተሰቦች በተጨማሪ የዲፕሎማቲክ ኮሚኒቲ ተወካዮችና ጋዜጠኞች ተከታትለውታል፡፡
ምንጭ፡- EHRP.

ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ በድጋሚ ታሰረ

“ኮማንድ ፖስቱ ሊያናግርህ ይፈልጋል”

befekadu-hailu

ከተለያዩ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ከዞን፱ ጦማሪያን ስብስብ ጋር በመሆን ሽልማቶችን ያገኘው ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ህዳር 02 ቀን 2009ዓ.ም ጠዋት ከቤቱ በፀጥታ ኃይሎች ወደ ፖሊስ ጣብያ ተወስዷል።

ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፈቃዱ ሚያዝያ 17 ቀን በ2006ዓ.ም ከሌሎች የዞን፱ ጦማሪያን እና ሶስት ጋዜጠኖች ጋር በመሆን በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሲሆን ከአንድ አመት ከስድስት ወር የእስር ቆይታ በኋላ የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የተከሰሰበትን የሽብር ወንጀል ወደ አመፅ ማነሳሳት ቀይሮ በ20ሺ ብር ዋስ እንዲወጣ ፈቅዶለት ነበር። በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያልተደሰተው አቃቤ ህግ በበፍቃዱ ላይና ሌሎች ፍርድ በቤቱ ነፃ የለቀቃቸው የዞን፱ ጦማሪያን (ሶልያና ሽመልስ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አጥናፉ ብርሃኔና አቤል ዋበላ) ላይ ይግባኝ የጠየቀ ሲሆን የፊታችን ማክሰኞ ህዳር 06 ቀን 2009 ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ በጠየቀው ይጋባኝ ላይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በፈቃዱ ኃይሉ ከእስር ከተፈታ አንድ አመት በኋላ ዛሬ ጠዋት ላይ በመኖሪያ ቤቱ እያለ “ኮማንድ ፖስቱ ሊያናግርህ ይፈልጋል” በሚል በፀጥታ ሀይሎች ሊወሰድ ችሏል።

ጋዜጠኛ እና ጦማሪ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች በፍቃዱ ኃይሉ ከእስር ከተፈታ በኋላ በአጭር ጊዜ ተወዳጅ በሆነችውና ከ10 እትም በኋላ ከገበያ በወጣችው ውይይት መፅሄት ላይ በዋና አዘጋጅነት ይሰራ እንደነበር ይታወቃል።
ምንጭ፡- EHRP.

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ለ3ኛ ጊዜ ለብይን ተቀጠረ

‹ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ግንቦት ሰባት ከተባለው አሸባሪ ቡድን አመራሮች ጋር ግንኙነት አድርገሃል› በሚል የሽብር ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ለ3ኛ ጊዜ ለብይን ቀጠሮ ተሰጥቶበታል፡፡

Getachew Shiferaw

ጥቅምት 21 ቀን 2009 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች ጉዳዩን በጽህፈት ቤት የተመለከቱት ሲሆን፣ ዳኞቹ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ለህዳር 28 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡

በሌሎች መዝገቦች ከዛሬ ቀደም ቀጠሮ የነበራቸውን ተከሳሾች ሳያቀርብ የቆየው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጋዜጠኛ ጌታቸውን ጨምሮ ሌሎች በዕለቱ ቀጠሮ ያላቸውን ተከሳሾች ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡

ተከሳሹ ጌታቸው ሺፈራው ጉዳዩ ሲታይ የቆየው 14ኛ ወንጀል ችሎት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ላይ ጉዳዩን የሚያየው ችሎት 4ኛ ወንጀል ችሎት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም ቀደም ሲል በነበረው ችሎት በአንድ ዳኛ ይታይ የነበረው የክስ ጉዳዩ በአሁኑ ችሎት በሦስት ዳኞች የሚታይ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው የቀረበበትን ክስ መከላከል ይገባዋል ወይስ መከላከል ሳያስፈልገው በነጻ ይሰናበት የሚለውን ብይን ለመስማት ፍርድ ቤት ቀጠሮ ሲሰጥ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው፡፡ ተከሳሹ ላይ አቃቤ ህግ ከሰነድ ማስረጃዎች ሌላ የሰው ምስክር አላቀረበበትም፡፡

ጌታቸው ታህሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ለእስር ከተዳረገበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ጉዳዩን በእስር ቤት ሆኖ እየተከታተለ ይገኛል፡፡
ምንጭ፡- EHRP.

%d bloggers like this: