ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ የአንድ ዓመት እስር እና 1,500 ብር ቅጣት ተፈረደበት
ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣም 10ሺህ ብር ቅጣት ተፈረደበት
(አዲስ ሚዲያ) ዛሬ ህዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም. የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 6ኛ ወንጀል በዋለው ችሎት የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ መስራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ አንድ ዓመት እስራትና 1,500 ብር ቅጣት ተፈረደበት፡፡ ከጋዜጠኛው በተጨማሪ ድርጅቱ ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣም የ10 ሺህ ብር ቅጣት ተፈርዶበታል፡፡
ጋዜጠኛው እና ጋዜጣው ላይ የዛሬ ፍርድ ውሳኔ የተላለፈው አዲስ አበባ መንበረ ጵጵስና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ ተፈፀመ የተባለውን ሙስና የሚያጋልጥ ዜና በጋዜጣው መሰራጨቱን ተከትሎ፤ የደብሩ እና የቤተክህነቱ ኃላፊዎች ”በጋዜጣው ስማችን ጠፍቷል” በሚል በመሰረቱት ክስለ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከፍርድ ቤቱ ቅጣት ውሳኔ በኋላም ጋዜጠኛው በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ አዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት የእስር ቅጣቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ መታሰሩ ታውቋል፡፡ በችሎቱ ላይ ከወዳጆቹ እና ጋዜጠኞች በተጨማሪ ከሳሾቹ ካህናት እና የደብሩ ኃላፊዎች ተገኝተው እንደነበር የተጠቆመ ሲሆን፤ ጋዜጠኛውም በመጨረሻ ”እውነት ትመነምናለች እንጂ አትጠፋም፤እውነቱ አንድ ቀን ይወጣል፡፡ ይህ ፍርድ የተፈረደብኝ ጋዜጣውን ለመዝጋት ታቅዶ ነው፡፡” ማለቱ ተሰምቷል፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ቀደም ሲል ሐዋሳ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ላይ የተፈፀሙ የሙስና መረጃዎችን በጋዜጣው ለህዝብ በማድረሱ ተከሶ ከፍተኛ መጉላላት፣ እስርና እንግልት እንዲሁም በባልደረባው ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው በአዲስ አበባ መንበረ ጵጵስና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈፀመ ሙስና የሚያጋልጥ ዜና በቂ መረጃ እንዳለው ለፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ቢያሳውቅም፤ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ጋዜጠኛው ለቀጣይ አንድ ዓመት በእስር ቅጣት እንዲያሳልፍ በመወሰኑ ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ለንባብ ይበቃ የነበረው ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ህትመትም እንደማይቀጥል መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ከኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት በተጨማሪ በመንግሥት እውቅና የተነፈገውና በ2004 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መብትና ጥቅም እንዲሁም በፕሬስ ነፃነት ዙሪያ ለመስራት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ እንደነበርም ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በአንድ ወር ብቻ 11,700 በላይ ዜጎችን ማሰሩን አስታወቀ
(አዲስ ሚዲያ)ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በደቡብ ክልል ኮንሶ የነበረውን የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በተፈጠረው ህዝባዊ ቁጣ ለማረጋጋት በሚል ባለፈው መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ተግባራዊ በሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ን ተከትሎ 11,607 ዜጎች መታሰራቸውን ገዥው መንግሥት አስታውቋል፡፡
ከታሰሩት መካከል ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የመብት አራማጆች፣ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ገበሬዎች፣ ሴቶች እንዲሁም በርካታ ወጣቶች እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዕድሜ የገፉ አዛውንትም የታሰሩ እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁን ተከትሎ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ መታሰራቸው ይፋ የተደረገው የታሳሪዎች ቁጥር ከዚህ ቀደም በህዝባዊ ተቃውሞው ወቅት በ10 ሺህዎች የሚገመቱ የታሰሩትን እንደማያካትት ተጠቁሟል፡፡
ገዥው መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህዝባዊ ተቃውሞውን ለማረጋጋት ቢሞክርም፤ አሁንም በተለይ በአማራ ክልል ሰሜን እና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም ምዕራብ ጎጃም ተቃውሞ እና የመንግሥት ወታደራዊ የኃይል ርምጅ በተለይም ግድያ እና የአካል ማጉደል ርምጃዎች መቀጠላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በኦሮሚያም ክልል በተለይም ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና አርሲ አካባቢ ተቃውሞች እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡
በተለይ አዋጁን ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች በወንጀል የጠረጠሩት ሰው ላይ ያለምንም ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እርምጃ እንዲወስዱ ስልጣን መስጠቱ ቢታወቅም፤ ከተጠቀሰው የ11706 እስረኞች በስተቀር ስለተፈፀመው እርምጃና ስለተጎጂዎች የተሰጠ ዝርዝር ማብራሪያም ሆነ መረጃ የለም፡፡