ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ለ3ኛ ጊዜ ለብይን ተቀጠረ
‹ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ግንቦት ሰባት ከተባለው አሸባሪ ቡድን አመራሮች ጋር ግንኙነት አድርገሃል› በሚል የሽብር ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ለ3ኛ ጊዜ ለብይን ቀጠሮ ተሰጥቶበታል፡፡

ጥቅምት 21 ቀን 2009 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች ጉዳዩን በጽህፈት ቤት የተመለከቱት ሲሆን፣ ዳኞቹ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ለህዳር 28 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡
በሌሎች መዝገቦች ከዛሬ ቀደም ቀጠሮ የነበራቸውን ተከሳሾች ሳያቀርብ የቆየው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጋዜጠኛ ጌታቸውን ጨምሮ ሌሎች በዕለቱ ቀጠሮ ያላቸውን ተከሳሾች ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡
ተከሳሹ ጌታቸው ሺፈራው ጉዳዩ ሲታይ የቆየው 14ኛ ወንጀል ችሎት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ላይ ጉዳዩን የሚያየው ችሎት 4ኛ ወንጀል ችሎት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም ቀደም ሲል በነበረው ችሎት በአንድ ዳኛ ይታይ የነበረው የክስ ጉዳዩ በአሁኑ ችሎት በሦስት ዳኞች የሚታይ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው የቀረበበትን ክስ መከላከል ይገባዋል ወይስ መከላከል ሳያስፈልገው በነጻ ይሰናበት የሚለውን ብይን ለመስማት ፍርድ ቤት ቀጠሮ ሲሰጥ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው፡፡ ተከሳሹ ላይ አቃቤ ህግ ከሰነድ ማስረጃዎች ሌላ የሰው ምስክር አላቀረበበትም፡፡
ጌታቸው ታህሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ለእስር ከተዳረገበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ጉዳዩን በእስር ቤት ሆኖ እየተከታተለ ይገኛል፡፡
ምንጭ፡- EHRP.
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የሰላማዊ ዜጎች እስር ቢኖርም፤ በአንዳንድ ቦታዎች አሁንም ተቃውሞች እንደቀጠሉ ናቸው
(አዲስ ሚዲያ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓም ተግባራዊ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች በጅምላ እየታሰሩ ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል እስሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ በቅርብ ርቀት የምትገኘው ሰበታ ከተማ ብቻ ከ አንድ ሺህ በላይ ተጠርጣሪ ናቸው ያላቸውን ነዋሪዎችን ማሰሩን ራሱ መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን፤ በሌሎችም የኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከተሞችና ወረዳዎችም በተመሳሳይ መልኩ እስሩ መቀጠሉን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን እና ጎንደር ዞን መንግሥት የነዋሪዎቹን ትጥቅ ለማስፈታት ወደ ወረዳዎች እና ገጠር ቀበሌዎች የፀጥታ ኃይሉን ቢያሰማራም ከህዝቡ የአፀፋ ርምጃ በመወሰዱ በርካታ ወታደሮችና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ህዝባዊ ተቃውሞው ከተጀመረበት ቀን አንስቶ የመንግሥት የፀረ አገዛዝና ጭቆና ተቃውሞ እንደቀጠለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በአፋር ክልልም እንዲሁ የሰላማዊ ዜጎች እስሩ የቀጠለ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በአፋርኛ በማዜም የምትታወቀው ድምፃዊት መፈራ መሐመድ ላሌን ጨምሮ አስር ሰላማዊ ዜጎች በአሳይታ ከተማ መታሰራቸው ታውቋል፡፡

ድምፃዊት መፈራ መሐመድ ላሌ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያ ትግበራ ላይ መንግሥት እንደ ኢሳት፣ ኦ.ኤም.ኤን. የመሳሰሉ መገናኛ ብዙኃን መከታተልና መረጃ መለዋወ ላይ መመሪያው እገዳ ጥሏል፡፡ በተጨማሪ ያልተፈቀደ ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ፣ ለህዝብ አገልግሎት አለመስጠት፣ በትምህርትና በስፖርት ማዘውተሪያ አድማ ማድረግ በክልከላው ተካተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር የመንግሥትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትግበራባለመቀበል በድጋሚ ለ3ኛ ጊዜ ከቤት ያለመውጣት አድማ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ አስቀድሞ በኢትዮጵያ የመንግሥትን በደልና ብልሹ አሰራር ለመቃወምና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ቀድሞም ቢሆን ለዓመታት ፈፅሞ የተከለከሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
መንግሥት ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ዓመት ያህል ያለማቋረጥ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቀጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማርገብ በሚል ባለፈው መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ተግባራዊ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ኢንተርኔትን በተለይም ማኀበራዊ ሚዲያ፣ በውጭ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተዘጋጅተው ለህዝቡ አማራጭ የመረጃ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ ያሉ እንደ ኢሳት፣ ኦ ኤም ኤን ያሉ መገናኛ ብዙኃን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዳይሰራጩ ከማፈን በተጨማሪ ህዝቡም መረጃ መለዋወጥና መስማትም እንደሌለበት በአዋጁ መከልከሉ ይታወሳል፡፡
አዋጁን ተከትሎ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ክልል ኮንሶ ፣ ጋሞ ጎዳ ዞን፣ በአፋርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል (ኦጋዴን) የተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች በመዘዋወር ድንገት ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ የተለያዩ የወርቅ ጌጣጌጦችን፣ ገንዘብ፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ ከመወስድ በተጨማሪ ጠርጥረንሃል ያሉትን ሰው ያለምንም ፍርድ ቤት ማዘዣ እየደበደቡ በመውሰድ ወዳልታወቀ ስፍራ እንደሚያስሯቸው ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ምክንያት ከወትሮ በተለየ መልኩ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ ነዋሪው በፍርሃት ድባብ ውስጥ እንደሚገኙ በመጠቆም በማኀበራዊና ንግድ እንቅስቃሴዎች ላይም አለመረጋጋቶች እንደሚስተዋሉ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
መንግሥትበአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት አፈና እና ቁጥጥሩን አጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ ዋነኞቹ የህዝባዊ ተቃውሞ አስተባባሪዎች መካከል የአማራ ተጋድሎና የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች ከመንግሥት ርምጃ ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን የሚችል አዳዲስ የትግል ስልቶችንም በቅርቡ ሊጀምሩ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡ በተለይ በውጭ የሚኖሩ የመንግሥትን አገዛዝ የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያን በስልጣን ላይ ካለው ገዥው ስርዓት ለውጥ በኋላ በኢትዮጵያ ሊመሰረት ስለሚገባው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ትግበራ በቪዥን ኢትዮጵያ እና በኦሮሞ ማኀበረሰብዓለም አቀፍ የህግ ባለሙያዎች ማኀበር አስተባባሪነት ከወዲሁ በሰሜን አሜሪካ ዋሸንግተን ዲሲ እበእንግሊዝ ለንደን ምክክር መጀመራቸው ታውቋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን ሊያባብሰው ይችላል ተባለ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተለያዩ ቦታዎች ይሰፍራል ተብሎ የሚጠበቀው የመከላከያ ሰራዊት ከዚህ በፊት ይወስድ የነበረውን የሃይል ዕርምጃ በማጠናከር ተጨማሪ አፈናን አግባራዊ እንደሚያደርግ የስብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ገልጸዋል።
በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግስት ከዜጎቹ የተነሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በሃይል ለመቆጣጠር ፍላጎት እንዳለው ማሳያ ነው ሲሉ በድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆርን ገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን ያወሳው ሂውማን ራይትስ ዎች ጥያቄ ያላቸው አካላት ምላሽን ካላገኙ ተቃውሞ ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል አሳስቧል።
ለአለም አቀፉ ማህበረሰ ስጋት እየሆነ የመጣው የጸጥታ ሃይሎች እርምጃና ተቃውሞ ቀጣይ የሚሆን ከሆነም ሃገሪቱ ሊቀለበስ ወደ ማይችል የሰብዓዊ መብት ቀውስ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ሂውማን ራይትስ ዎች በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
በርካታ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰብዓዊ መብት ረገጣን ሊያባብስ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለስድስት ወር የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊት ሊነሳ እንደሚችል የመንግስት ባለስልጣናት መግለጻቸውን ብሉምበርግ ማክሰኞ ዘግቧል።
“የስድስት ወሩ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሙሉ ለሙሉ ላያስፈልገን ይችላል ሲሉ ለዜና አውታሩ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከተቀመጠው ጊዜ በፊት ችግሮቹን ልንቆጣጠር እንችላለን ብለዋል።
ምንጭ፡-ኢሳት
በዲላ ከተማ በተቀሰቀሰ ደም አፍሳሽ ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት አለፈ
ዮናስ ዓብይ እና ውድነህ ዘነበ
ባለፈው ሳምንት ዓርብ መስከረም 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን የተቀሰቀሰው ደም አፍሳሽ ግጭት፣ ለበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ምክንያት ሆነ፡፡
ከጌድዮ ዞን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ባለፈው ዓርብ ከቀኑ 4፡30 ሰዓት ተጀምሮ እስከ ቅዳሜ ድረስ በቀጠለው ደም አፍሳሽ ግጭት የ63 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ይጠቁማሉ፡፡ ከጌዲዮ ብሔረሰብ አባላት 52 ሰዎች፣ ከሌሎች ክልሎች መጥተው በዲላ ከተማ ከሚኖሩ ውስጥ ደግሞ 11 የሚደርሱ ግለሰቦች ሕይወት ማለፉን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በዚህ ግጭት መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ የሕዝብና የጭነት ተሽከርካሪዎችና የቤት መኪኖች በእሳት ጋይተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ግን ቁጥሩ የተጋነነ ነው ይላል፡፡
የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አህመድላዲን ጀማል በተቀሰቀሰው ግጭት የሰው ሕይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
ነገር ግን ምክትል ኮሚሽነሩ እንደገለጹት፣ የሟቾችን ቁጥርና የደረሰውን የንብረት ውድመት የሚያጣራ ግብረ ኃይል ወደ ሥፍራው በመላኩና ሪፖርቱን ባለማጠናቀቁ፣ የሟቾችንም ሆነ የደረሰውን የንብረት ውድመት በቁጥር ማስደገፍ አይቻልም፡፡
መስከረም 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ከረፋዱ 4፡30 ሰዓት ላይ የጌዲዮ ተወላጅ የሆኑ ሰዎች በተለይ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የመጡ የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥፋት መፈጸማቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ምንጮች እንደገለጹት የጥቃቱ ማጠንጠኛ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ሰዎች በዞኑ ውስጥ ሀብትና ንብረት ማፍራታቸው፣ በአንፃሩ ደግሞ የጌዲዮ ብሔረሰብ አባላት በድህነት ውስጥ ነን በሚል ምክንያት ለዓመታት በአካባቢው የሚኖሩ የሌሎች ክልል ተወላጆች ከአገር እንደሚወጡ መጠየቃቸው ነው፡፡
በዚህ ሳቢያ የከተማው ነዋሪዎች ቤቶቻቸውና ንብረቶቻቸው ከመውደማቸውም በተጨማሪ ግድያ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ከከተማ እንዲወጡ የተደረጉም አሉ፡፡
ለዚህ ግጭት መነሻ የሆነው በዲላ ከተማ ‘ታይዋን’ ተብሎ በሚጠራው የገበያ ሥፍራ አካባቢ በጌዲዮ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየንና በከተማው ነጋዴዎች መካከል የመሬት ይገባኛል ጥያቄ በፍርድ ቤት እልባት ማግኘቱ ነው፡፡
በሁለቱ አካላት መካከል ሲካሄድ የቆየው የፍርድ ቤት ክርክር ለከተማው ነጋዴዎች መወሰኑ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ በውሳኔው የተነሳም የአካባቢው ነዋሪዎች ቁጣ ወደ ደም አፍሳሽ ግጭት ተቀይሯል፡፡
የእዚህ ግጭት ሰለባ የሆኑ የዲላ ከተማ ነጋዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በከተማ ከሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች አባላት መካከል 11 የሚሆኑ ሞተዋል፡፡ እንዲሁም ከጌዲዮ ወገኖች 52 ያህል መገደላቸውን አስረድተዋል፡፡
የደቡብ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሂክማ ኬይረዲን ለሪፖርተር እንገደለጹት ግን አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 23 ሲሆን፣ ግጭቱም ብሔር ተኮር አይደለም፡፡
በዚህ ግጭት የዲላ ከተማን ሲሶ ያህሉን እሳት በልቶታል፡፡ ‹‹ፌዴራል ፖሊስ ቅዳሜ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ባይደርስ ሁላችንም እናልቅ ነበር፤›› በማለት የግጭቱን አስከፊነት ነጋዴው ገልጸዋል፡፡
የጌዲዮ ዞን መቀመጫ የሆነችው ዲላ ከአዲስ አበባ ከተማ 369 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ዞኑ በአጠቃላይ 1,347.04 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡
ዞኑ የኢትዮጵያ ስፔሻሊቲ ቡና (ይርጋ ጨፌ) ይመረትበታል፡፡ በዞኑ ዲላ፣ ጨለልቅቱ፣ ይርጋ ጨፌና ወናጎ አጎራባች አካባቢዎች ግጭቱ ተንሰራፍቶ ነበር፡፡
የፖሊስ ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት የክልሉ ሰላም ወደነበረበት ተመልሷል፡፡ ችግሩንም የፈጠሩ አካላትም በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው፡፡ እስከ ማክሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ሰላም ቢሰፍንም በከተማው የንግድ እንቅስቃሴ አለመጀመሩ ታውቋል፡፡
ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ
በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ፤ ህዝባዊ ተቃውሞውም አድማሱን እያሰፋ ቀጥሏል
(አዲስ ሚዲያ)በኢትዮጵያ ለተከታታይ አስር ወራት የፈጀው የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከትናንት ቅዳሜ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለ6 ወር ተግባራዊ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዝርዝር ጉዳይን በተመለከተ ወደፊት ይገለፃል ከማለት በስተቀር አጠቃላይ ይዘቱን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡
በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስተሩ በሚመራ ኮማንድ ፖስት ስር የህግ አስከባሪዎችም መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የፌደራል የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል፣ የአካባ ሚሊሻዎች እና ንብረት ጠባቂ የፀጥታ ኃይሎች የሚያካትት መሆኑን ደግሞ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ አብራርተዋል፡፡ አስቸኳይ አዋጁ በአጠቃላይ ሀገሪቱ ላይ ተግባራዊ መደረጉንም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር መሰረት የተጠረጠረ ማንኛቸውም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊታሰር እንደሚችል፣ ቤቶችና አካባቢዎችም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብርበራ ሊካሄድባቸው እንደሚችልም እና ማንኛውም ዓይነት መገናኛ ብዙኃን ሊዘጋ እንደሚችልም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተቃውሞን ሊገልፁ የሚችሉ ምልክቶችን መጠቀምንም አዋጁ እንደሚከለክል፣ አዋጁን ተላልፎ የተገኘም ቅጣት እንደሚጠብቀው አስታውቀዋል፡፡
በተለይ ከህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ እንዲሁም ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል የተነሱ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞች መንግሥት በወታደራዊ ኃይል ግድና፣ እስርና አፈና ለማስቆም መሞከሩን ተከትሎ ያለማቋረጥ ተቃውሞዎቹ ተጠናክረው መቀጠላቸው ስርዓቱን ስጋት ላይ ጥሎታል፡፡ በተለይ እንደ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ከሆነ ከሀገሪቱን አጠቃላይ ህዝብና የቆዳ ስፋት 62% የሚሸፍነው የሀገሪቱ ህዝብ በአደባባይ የስርዓት ለውጥ እንደሚፈልግና በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት መገዛት ለከፍተኛ ግድያ፣ እስር፣ በደልና ጭቆና እንደዳረገው በአደባባይ እየገለፀ ይገኛል፡፡ ለህዝቡ ጥያቄ የመንግሥት ምላሽ ግድያ፣ እስርና ማሰቃየት መሆኑ ደግሞ ህዝቡን የበለጠ እንዲቆጣና የተቃውሞ አድማሱን እንዲያሰፋ እንዳስገደደው ይነገራል፡፡
በተለይ ባለፈው እሁድ መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሞ ማኀበረሰብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውና በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚታደሙበት የኢሬቻ በዓል በደብረዘይት/ቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ እየተከበረ ባለበት ወቅት ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ አገዛዙ ላይ ተቃውሞውን ማሰማቱን ተከትሎ በተወሰደው ርምጃ አጠቃላይ ከ678 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው በመላው ኢትዮጵያ የበለጠ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ በዚህም በኦሮሚያ ክልል የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ህዝባዊ አብዮት መሸጋገሩንም የኦሮሞ መብት አራማጆች ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ ህዝቡ የአገዛዙ ሰዎች፣ ደጋፊዎችና ተባባሪዎች ናቸው የተባሉ ንበረቶች እና አገዛዙ የሚጠቀምባቸው የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ላይ ርምጃ መውሰዳቸው ታውቋል፡፡ የኦሮሞ ህዝባዊ ተቃውሞ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ የመንግሥት ወታደራዊ የኃይል ርምጃም ተጠናክሮ በመቀጠል የበርካታ ሰላማዊ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ባለው ህዝባዊ ተጋድሎ የቀጠለ ሲሆን፤ የመንግሥት ወታደራዊ እርምጃ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል በተጨማሪ በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳም ተመሳሳይ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ እና የመንግሥት የኃይል ርምጃ የቀጠለ ሲሆን፤ በዚህም በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛው ደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን ባሉ ወረዳዎችና ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞና ግጭቶች ተቀስቅሰዋል፡፡ በዚህም የሰው ህይወት መጥፋትን ጨምሮ የበርካታ ሰላማዊ ዜጎች የንግድ ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ የተለያዩ የኃይማኖት ተቋማትም ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አጠቃላይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳ ባሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በመንግሥት ወታደራዊ የኃይል ርምጃ የተገደሉ ሰላማዊ ዜጎች ቁጥር ከ 1,420 በላይ መድረሳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ህዝባዊ ተቃውሞቹ በውጭ ኃይል የተቀነባበሩ ናቸው በማለት ለመሸፋፈን ቢሞክርም ከህዝቡ፣ ከመብት አራማጆችም ሆነ ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ተቀባይነት አላገኘም፡፡