Category Archives: News

አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞች ተለቀቁ

ከመስከረም 3 ቀን 2004 ዓ ም ጀምሮ በእስር ላይ የነበሩት የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም አራጌ ፥ የፓርቲያቸው አመራር አባላት የነበሩት አቶ ናትናኤል መኮንን፥ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ አንዱዓለም አያሌው የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ ም ከእስር ተለቅዋል።
Andualem Arage
አቶ አንዱዓለም አራጌ

በተመሳሳም የቀድሞ የጋምቤላ ፕሬዘዳንት የነበሩት አቶ ኦኬሎ አኳይ፥ የመብት ተሟጋቿ ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ፥ የኦፌኮ/መድረክ አመራር የነበሩት አቶ ኦልባና ሌሊሳ፥ የቀድሞ መኢአድ ፕሬዘዳንት አቶ ማሙሸት አማረ፥ የመኢዴፓ አመራር የነበሩት አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)፥ የኢብአፓ ፕሬዘዳንት የነበሩት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር፥ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበረው ወጣት ብርሃኑ ተክለያሬድ፥የመብት ተሟጋቿ ጫልቱ ታከለ እና ደርቤ ኢተና፤ የሙስሊሙ መፍትህ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና የመብት ተሟጋቾች አህመዲን ጀበልና አህመድ ሙስጠፋ እና አርቲስት ሴና ሰለሞን ከእስር ተለቅዋል።

በተለይ አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ተይዘው ከታሰሩ ጀምሮ በተለያየ ክስ መዝገብ ዕድሜ ልክ እስር ተፈርዶባቸው እንደነበር ይታወቃል።

ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በተመሳሳይ ቀን ከ746 ያላንሱ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለመግንግሥት መገናኛ ብዙኃን ማሳወቁ ይታወሳል። ይሁን እንጂ አሁንም በርካታ የፖለቲካ እስረኞች በተለያዩ የሀገሪቱ ወህኒ ቤቶች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁሟሉ።

የነ አቶ አንዱዓለም አራጌን መፈታት ተከትሎ በርካታ ህዝብ በአዲስ አበባ ቃሊቲ ወህኒ ቤት እና በየመሮሪያ ቤታቸው በመገኘት ደስታውን ሲገልፅና እና ድጋፉን ሲያደርግ ተስተውሏል። እነ አንዱዓለምም ለመላው ህዝብ ምሥጋናችውን አቅርበዋል።

አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ የኦፌኮ/መድረክ አመራሮች ከእስር ተለቀቁ

በኦሮሚያ ክልል ከሰኞ የካቲት 5 እስከ 7 ቀን 2010 ዓ ም በመላው ኦሮሚያ ክልል የተጠራውን ከቤት ያለመውጣትና የንግድ እቀባ ተከትሎ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ /መድረክ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፥ እና ሌሎች የፓርቲው አመራሮች በተለይም የፓርቲው ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ደጀኔ ጣፋ፥ የወጣቶች ክንፍ ሥራ አሥፈፃሚ አባል አቶ አዲሱ ቡላላ እና የወጣቶች ክንፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ጉርሜሳ አያኖን ጨምሮ 7 የፖለቲካ እስረኞች ተለቀዋል። እነ አቶ በቀለ ገርባ የካቲት 6 ቀን 2010 ዓ ም ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር መለቀቃቸው ታውቋል።

Bekele_Adama Public speech.jpg
አቶ በቀለ ገርባ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ህዝባዊ አቀባበል ላይ ንግግር ሲያደርጉ

እነ አቶ በቀለ ገርባ ከእስር መፈታታቸውን ተከትሎ በርካታ ደጋፊዎቻቸው ከአዲስ አበኣ ጀምሮ ከፍተኛ ህዝባዊ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በተለይም በመኖሪያ ከተሞቻቸው ህዝባዊ አቀባበሉ እስከምሽት እንደነበር ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
Bekele Gerba_Adama
በአዳማ/ናዝሬት አቶ በቀለ ገርባ የተደረገ ህዝባዊ አቀባበል

አቶ በቀለ ገርባ ከእስር መፈታታቸውን ተከትሎ ረቡዕ የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ. ም. አዳማ/ናዝሬት በሚገኘው አበበ ቢቂላ ስታዲየም በርካታ ህዝብ አቀባበል ያደረገላቸው ሲሆን፤ እርሳቸውም ለህዝቡ ንግግር አድርገዋል። አሁንም በርካታ የፖለቲካ እስረኞች በውህኒ ቤት እንደሚገኙና ሁሉም መፈታት እንዳለባቸው ያስታወሱት አቶ በቀለ፤ ከእስር እንዲፈቱ በመንግሥት ላይ ጫና በመፍጠር ድጋፍ ላደረገው ለመላው ህዝብ ምሥጋናችውን አቅርብዋል።

ዶ/ር መረራ ጊዱናን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ተፈቱ

በአውሮፓ ቤልጅየም በተደረገላቸው ግብዣ መሰረት በኢትዮጵያ ጉዳይ ውይይት አድርገው ሲአመለሱ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ታስረው የነበሩት ዶ።ር መረራ ጉዲና ከእስር ተለቀዋል። ዶ/ር መረራ የኦፌኮ /መድረክ ሊቀመንበር ሲሆኑ፤ በአቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንዳለ ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጎ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ ም ከእስር ተለቀዋል።
Dr. Merera _Ambo .jpg
ዶ/ር መረራ ጉዲና ከእስር ሲለቀቁ በአምቦ የተደረገላቸው ህዝባዊ አቀባበል ላይ

ዶ/ር መረራ ከእስር ሲለቀቁ በርካታ ቤተሰቦቻቸው፥ የትግል አጋሮቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ደማቅ አቀባበል ያደርጉላቸው ሲሆን፤ በተለይም በቡራዩ መኖሪያ ቤታቸው፥ እና በትውልድ አካባቢያቸው አምቦ በርካታ ህዝብ በተገኘበት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

Dr. Merera _Ambo 1
ዶ/ር መረራ ጉዲና ከእስር ሲለቀቁ በአምቦ የተደረገላቸው ህዝባዊ አቀባበል ላይ

ከዶ/ር መረራ ፥ የወለጋ ዩኒቨርስቲ መምህር ሩፋኤል ዲሳሳን ጨምሮ በደቡብ ክልል ኮንሶ እና ጌዲዮ ዞን የታሰሩ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች መለቀቃችው ታውቋል።

ቀደም ሲል መንግሥት በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል እየተደረገ ያለውን ህዝባዊ አመፅና ጫና ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚፈታ ቃል መግባቱ ይታወሳል።

ጋዜጠኛ እስክንድር እና ውብሸት ታዬ ከእስር ተለቀቁ

ላለፉት 6 ዓመት ከ6 ወራት በእስር ላይ የነበሩት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ዛሬ የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ ም ከእስር ተለቀዋል።

Journalist Eskinder, Woubshet and Zelalem
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፥ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና ጦማሪ ዘለዓለም ወርቅአገኝሁ

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በመንግሥት በቀረበበት ክስ የ18 ዓመት እስርት ተፈርዶበት የነበረ ቢሆንም፤ ጋዜጠኛ እስክንድር የፔን አሜሪካ “Freedom to write Award” እና የዓለም አቀፍ የፕሬስ ተቋምን “World press freedom Hero” የሚሉ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘቱ ይታወሳል። ከእስር እንደተፈታም ህዝቡ ላደረገለት ድጋፍና አቀባብል አመስግኗል።

ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በቀረበበክ ክስ 14 ዓመት እስር ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን፤ እ. አ. አ. የ213 ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ንፃ ፕሬስ “African free press Award” አሽናፊ ሲሆን በእስር ቤት ሳለ ሁለት መፅሐፍትን ለንባብ ማብቃቱ ይታወቃል።

ባለፈው ደብርሃን ድረ ገፅ ጦማሪ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ ባለፈው ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. የተበየነበት እስር በአመክሮ በማጠናቀቅ ከእስር የተፈታ ሲሆን፤ ክሳቸው በአቃቤ ህግ ይግባኝ እየታየ የነበሩት የዞን 9 ጦማሪያን ክስም ዛሬ እንዲቋረጥ መደረጉ ታውቋል።

የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ: በወልድያ የበዓለ ጥምቀት ግጭትና ግድያ የጸጥታ ኃይሉን ወቀሱ፤“የእነርሱ መዘዝ ነው፤ወጣቱ አበላሸ የምንለው ነገር የለም”

“መከላከያዎቹ እንዳይመጡ ቀድመን አሳስበናል፤ከዞኑም ጋር ተናበን እየሠራን ነበር፤”
“በሰላም ሊጠናቀቅ ባለበት ሰዓት መጥተው ግጥም አሉ፤ ይኸው ወጣቱን አሳበዱት፤”
“ወጣቱን ሌላ የፖሊቲካ አካል ቀሰቀሰው አሉ፤ ወታደሮቹን ማን ነው የቀሰቀሳቸው?”
“የበቀል ነው የሚመስለው፤እንደው ከራሳቸው መካከልም የሚያጠፋ ያለ ይመስለኛል፤”
“ታቦቱን ያከበሩት ካህናት፣በጎናቸው ባሉት ካህናት ተገድፈው ነው እንጅ ወድቀዋል፤”
“ተዉ ብሎ ይህን ማስተካከል እና መሥመር ማስያዝ ያለበት መንፈሳዊ አባት ነው፤”
“ቤተ ክርስቲያኗን ወጣቱ ሰምቶልናል፤ታቦቱ ከገባ በኋላ ሁሉም እንሙት እያለ ነበረ፤”
†††

“ተረጋግቶ እያለ ድኻ የሚረዳ ልጅ ገድለው ዳግም በእነርሱ ስሕተት ግጭቱ ቀጠለ፤”
“ሕንፃ እግዚአብሔር እያፈረሳችሁ ፎቅ ትጠብቃላችሁ፤”ብሎ ሕዝቡ በጣም ተቆጨ፤
“ስንቱስ ንብረት ወደመ? የእነርሱ መዘዝ ነው፤ ወጣቱ አበላሸ የምንለው ነገር የለም፤”
“መከላከያ ይውጣ፤ ወጣቱ ከከተማው ፖሊስ ጋር ይጠብቀዋል፤” በሚል ተስማማን፤
ርእሰ መስተዳድሩም፣ “ሠራዊቱን አስወጣለሁ፤ አጣሪ እልካለሁ፤ አጥፊው ለሕግ ይቀርባል፤ ይፋም አደርጋለሁ፤” ብለዋል፤ ልቅሶ ቤትም ገብተው አብረው እያለቀሱ አጽናንተዋል፤
“ከኹለት ዙር ውይይት በኋላ፣ ወጣቱን በየአቅጣጫው የሚመሩ ካህናት መድበን ወደየቤቱ እንዲገባ አድርገናል፤ በሰላም እየዘመረም ወደየቤቱ ተመልሷል፤”
“እኛም በየሐዘን ቤቱ እየዞርን ስናጽናና ውለናል፤ ርእሰ መስተዳድሩ ከተመለሱ በኋላ ከላኳቸው ልኡካን ጋራ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተካትተን እየመከርን ነው፤”
†††

his-grace-abune-ermias-speaks-on-the-woldias-massacre-e1516905706194
ፎቶ፡ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፤ የሰሜን ወሎ እና ከሚሴ ዞን ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ

በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ፣ በጥምቀት እና በቃና ዘገሊላ በዓል አከባበር ወቅት የተቀሰቀሰው ግጭትና የተፈጸመው ግድያ፣ በጸጥታ ኃይሉ ስሕተት የደረሰ ነው፤ ያሉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ረዳት፣ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፣ ለጠፋው የዜጎች ሕይወት እና ለወደመው ንብረት ወቀሱት፡፡

የቃና ዘገሊላ በዓል፣ እንደ በዓለ ጥምቀት ኹሉ በሥርዐቱ እየተከበረ በሰላም ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰዓት የመጣው የጸጥታ ኃይል “ያልተጠራ” እንደነበር የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ ከመጣ ችግር እንደሚፈጠር ስለታመነ እንዳይመጣ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ቀድመው አሳስበው እንደነበር አውስተዋል፡፡

his-grace-abune-qerlos
ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፤ የሰሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ለበዓሉ አከባበር፣ ሀገረ ስብከቱ ከዞኑ ሓላፊዎች ጋራ እየተናበበ በመሥራቱ የተጠየቀ ተጨማሪ ኃይል እንዳልነበርና “እነርሱ አይምጡ፤ እኛው በእኛው ፕሮግራማችንን እንመራለን፤” በማለት ቀድሞ እንዳሳወቀ ብፁዕነታቸው ጠቁመዋል፡፡

ይኹንና በመምጣታቸው ወጣቱን ለተቃውሞ እንዳነሣሡ ተናግረዋል፤ “ወጣቱን አሳበዱት፤ የተሳደበም ይመስለኛል፤ ድንጋይም ሳይወረውር አይቀርም፤ በጥይት ለቀሙት፤” በማለት የርምጃውን ኢፍትሐዊነት አስረድተዋል፡፡ በማግሥቱም ቀጥሎ የነበረው ግጭትና የንብረት ውድመት መንሥኤ የጸጥታ ኃይሉ እንደኾነ የተናገሩት ብፁዕነታቸው፣ “የእነርሱ መዘዝ ነው፤ እኛ ወጣቱ አበላሸ የምንለው ምንም ነገር የለም፤” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡

በሞትና መቁሰል ስለደረሰው ጉዳትም፣ “ብዙ ሰው ነው የተጎዳብን፤ ያላወቅነውም ይኖራል፤” ብለዋል ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፡፡ ግጭቱ በተከሠተበት ወቅት ከመርሳ ከተማ ወደ ወልዲያ ተመልሰው በዚያው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለማስተማር በዝግጅት ላይ እንደነበሩ ገልጸው፣ የጸጥታ ኃይሎቹ ለብተና በተጠቀሙበት አስለቃሽ ጢስ ታቦቱን ያከበሩት ካህናት፣ “በጎናቸው ባሉ ካህናት ተገድፈው ነው እንጅ ወድቀዋል፤” ብለዋል ጥልቅ ቅሬታ በሚደመጥበት አነጋገር፡፡

የጸጥታ ኃይሉን ለምን ማሠማራት እንዳስፈለገ እንደማያውቁ ብፁዕነታቸው ጠቅሰው፣ ኾነ ተብሎ የታቀደ እንደሚመስላቸው ሳይገልጹ አላለፉም – “ለምን እንደመጡ አናውቅም፤ ኾን ብለው ለመምታት ይመስላል፤ ከራሳቸው መካከልም የሚያጠፋ ያለ ይመስለኛል፤” ብለዋል፡፡ አያይዘውም፣ “ወጣቱን ሌላ የፖሊቲካ አካል ቀሰቀሰው ይባል፤ እነርሱን ወታደሮቹን ማን ነው የቀሰቀሳቸው? ሰላም እንዳይኾን!” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ከክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጋራ በኹለት ዙሮች በተካሔደው ውይይት፣ ወጣቱ በአጠፌታ ተሠማርቶበት ከነበረው የንብረት ማቃጠልና ማውደም አረጋግተው ወደ አዳራሽ እንዲገባ በማድረግ ከሌሎች የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ጋራ የተሳካ ሥራ እንደሠሩ ብፁዕነታቸው ይገልጻሉ፡፡ ቀደም ሲል ከእግር ኳስ ጨዋታ ጋራ ተያይዞ ተከሥቶ በነበረው የከተማዋ ግጭት በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የማረጋጋት አባታዊ ሚና እንደነበራቸው በማውሳት፣ “ቤተ ክርስቲያኗን ወጣቱ ሰምቶልናል፤” ሲሉ አመስግነዋል፡፡

ባለፈው ሰኞ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር በተገኙበት በተደረገው ውይይት፣ የመንግሥት ጥፋት በግልጽና በዝርዝር መቅረቡን፤ ለከተማው ሰላምና ጸጥታ በሚረዱ አጠቃላይ መፍትሔዎች ላይም ስምምነት እንደተደረሰ አስታውቀዋል፡፡ ሠራዊቱን ከከተማው እንደሚያስወጡ ርእሰ መስተዳድሩ የገለጹ ሲኾን፣ ለሰላሙና ጸጥታው ወጣቱ ከፖሊስ ተባብሮ እንደሚሠራም አረጋግጧል፡፡ ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ “ስለተፈጸመው ነገር የሚያጣራ አካል እልካለሁ፤ አጥፊው ለሕግ ይቀርባል፤ ለእናንተም ይፋ አደርጋለሁ፤” ማለታቸው ታውቋል፡፡

ከውይይቱ በኋላ አቶ ገዱ፣ ሐዘንተኞችን በየቤታቸው ተገኝተው በማጽናናታቸው ያመሰገኑት ብፁዕነታቸው፣ በቤተ ክርስቲያንም በኩል ካህናትን መድቦ ወጣቱ በሰላም ወደየቤቱ እንዲገባ ከማድረግ ባሻገር፣ እስከ ትላንት ድረስ ሐዘንተኞችን ሲያጽናኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በአኹኑ ወቅትም በክልሉ መንግሥት ተሠይሞ ከተላከው ልኡካን ቡድን ጋራ፣ እርሳቸውን ጨምሮ የከተማው የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የተካተቱበት ምክክር እየተካሔደ እንዳለ አስታውቀዋል፡፡

እየተከሠተ ያለው የግፍና የጥፋት ድርጊት፣ ሕዝብን ከሕዝብ እያለያየ መኾኑ በእጅጉ እንደሚያሳዝናቸው ብፁዕነታቸው ተናግረዋል፡፡ “ተዉ ማለት ያለበት፣ ይህን ማስተካከልና መሥመር ማስያዝ ያለበት መንፈሳዊ አባት ነው፤” ሲሉ ቤተ ክርስቲያን ጥፋትን የመከላከል፣ አጥፊውን የማውገዝና የመገሠጽ፣ የተበደለው እንዲካስና እንዲጽናና የማድረግ በአጠቃላይ የአገርን ሰላምና የሕዝብን አንድነት የማስጠበቅ ከባድ መንፈሳዊና ታሪካዊ ሓላፊነት እንዳለባት አመልክተዋል፡፡

አባቶችና መንበረ ፓትርያርኩ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር በመዳፈርና ሥርዐቷን በመጣስ ጭምር ስለተፈጸመው የወልዲያው ግፍ፣ አቋማቸውን እንዲያሳውቁና ኖላዊነታቸውን እንዲያረጋግጡ በብዙኃን መገናኛዎችና በመግለጫዎች የሚሰነዘሩት ጥያቄዎችና ወቀሳዎች እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

መኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲዎች፣ ከትላንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ በዓልን ለማክበር በወጡ የወልዲያ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ የተመለከተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድርጊቱን አለማውገዟ ያስተዛዝበናል፤ ብለዋል፡፡

ለተነሣው ግጭትና ለተወሰደው የግድያ ርምጃ የቀረበው ምክንያት፣ “መንግሥትን የሚቃወም ዜማ አሰማችሁ፤” የሚል እንደኾነ በመግለጫቸው የጠቀሱት ፓርቲዎቹ፣ “ይህ ደግሞ መብት መጣስ ነው፤” ብለዋል፡፡

አክለውም፣ “የጸጥታ ኃይሎች ቅዱስ ታቦትን ባከበሩ ቀሳውስት ላይ አስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸው ሃይማኖቱን መዳፈር በመኾኑ መንግሥት ድርጊቱን በማውገዝ የእምነቱን ተከታዮች በዐደባባይ ይቅርታ ይጠይቅ፤ ለሟች ቤተ ሰዎች የደም ካሳ እንዲከፍል፤ ግድያው እንዲፈጸም ትእዛዝ የሰጡም ኾነ ጉዳዩን በቸልተኝነት የተመለከቱ የዞኑ ባለሥልጣናት በሕግ እንዲጠየቁ፤ ግድያውን የፈጸሙ የመንግሥት ታጣቂዎች ለሕግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፤” ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን በመወከል በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ርእሰ መንበርነት አመራር የሚሰጠው ቋሚ ሲኖዶስ፣ ከልደት ጀምሮ በነበሩት ዐበይት ክብረ በዓላት ሳቢያ የተመደቡት ተለዋጭ አባላቱ ብፁዓን አባቶች በየአህጉረ ስብከታቸው በመኾናቸው አለመሰብሰቡ ተጠቁሟል፡፡ ሰሞኑን እስከ ግንቦቱ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ድረስ በተለዋጭነት በተመደቡት አራት ብፁዓን አባቶች አባላቱ በሚቀጥለው ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው፣ ጉዳዩን ይመለከተው እንደኾነም ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

ምንጭ፦ ሐራ ዘተዋሕዶ